በመሸሻ ወልዴ
በድሬዳዋ ከተማ ተወልዶ ያደገው ሙኸዲን ሙሳ በዘንድሮው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎአቸው ደረጃ ውስጥ እንደሚገቡና እሱም ለክለቡ ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ ግቦችን ለማስቆጠር እቅድን እንደያዘ ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሹን ሰጥቷል።
በእግር ኳሱ አሁን ለሚጫወትበት ድሬዳዋ ከተማ እና ከዛ በፊት ደግሞ ለሆሳህና ሀድያ ተጫውቶ ያሳለፈው ሙኸዲን ከሀትሪክ ድረ ገፅ ጋር ያደረገው አጠቃላይ ቆይታም ይሄንን ይመስላል።
ወላይታ ድቻን ስላሸነፉበት ጨዋታ
“ከወላይታ ድቻ ጋር የነበረን ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ እኛ የተሻልንም ነበርን። ከእረፍት በኋላ ግን እነሱ ጫና ፈጥረውብን ለመጫወት ቢችሉም በመጨረሻ ግን የሶስት ነጥብ ባለቤትና ባለድሉ እኛ ሆነን ልንደሰት ችለናል”።
ውጤቱ ለእናንተ ይገባችኋል?
“አዎን፤ ምክንያቱም ከእነሱ በተሻለ እኛ ጥሩ ተጫውተናልና”።
ወላይታ ድቻን በተመለከተ
“ጠንካራ እና ጥሩ ቡድን ነው። በተለይ ከፋሲል ከነማ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ በሚገባ አይተነዋል። መሻሻል የሚችል ቡድን ነው”።
ወላይታን ባሸነፉበት ጨዋታ ስለነበራቸው ጠንካራ ጎን
“ከሁሉም በላይ የተከላካይ ክፍላችን ነበር ጠንካራ ጎናችን”።
የድሬዳዋ ከተማ የሊግ ጉዞው የት ድረስ እንደሆነና እስካሁን ስላስመዘገቡት ውጤት
“ባለፉት አራት ጨዋታዎች 4 ነጥብን ይዘን ነበር። እንዳለን ጥሩ ጎን ይሄ ነጥብ ብቻ ለእኛ በቂያችን አልነበረም። አሁን ግን በአምስተኛው ጨዋታችን ላይ የነበረንን ግጥሚያ ስላሸነፍን ነጥባችንን ወደ 7 አስፍተነዋል። ከእዚህ በኋላም በሚኖሩን ጨዋታዎች ነጥብ ላለመጣል በመጫወት ይሄን አሸናፊነታችንን አስቀጥለን ዘንድሮ የደረጃ ተወዳዳሪ እስከመሆን ደረጃም ነው ከወዲሁ እቅድን የያዝነው”።
የድሬዳዋ ከተማ ቡድንን ከአምናው አንፃር ሲመለከተው እና ስለያዙት የተጨዋቾች ስብስብ
“በየጨዋታው ጥሩ ለመሆን ያለን ፍላጎት እና ከፍተኛ ተነሳሽነታችን ከአምናው ለየት ያደርገናል። ስብስባችንም ምርጥ የሚባል ነው”።
ስለ ክፍተት ጎናቸው
“ቡድናችን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቢደርስም እነዛን ብዙ ሲጠቀምባቸው አይታይም። ይህ ደካማ ጎናችን ሊሻሻል ይገባዋል”።
የእግር ኳስን መጫወት ሲጀምር ተምሳሌት ስላደረገው ተጨዋች እና ከውጪ ስለሚያደንቀው ተጨዋች
“የዮርዳኖስ አባይ አድናቂ ሆኜ ነው ያደግኩት እሱ ነው የእኔ አርአያዬ ከእዛ ውጪ ከባህር ማዶ ተጨዋቾች ደግሞ እኔ የማደንቀው ከማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊነቴ ጀምሮ ክርስቲያኖ ሮናልዶን ነው “።
የእግር ኳስን በመጫወቱ በቤተሰቡ አካባቢ ስለነበረው አመለካከት
“በእዚህ በኩል እነሱ ጥሩ አመለካከት
አላቸው። ኳሱን እንድጫወት በጣም ያበረታቱኝም ነበር። ባደረጉልኝ ድጋፍም ነው እዚህ ደረጃ ላይ ልገኝ የቻልኩት”።
በእግር ኳሱ ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሻለው ትላለህ? ዘንድሮ ስንት ግብ ታስቆጥራለህ?
“አዎን። ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሻለው። ከእዚህ በላይ በመጓዝም ለሀገሬ መጫወትም እፈልጋለሁ። ከጎል ማግባቱ ጋር በተያያዘ አምና በኮቪድ የሊጉ ውድድር እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ 5 ግብ አግብቼ ነበር። ዘንድሮ ደግሞ ጎል ማግባቱ ላይ ያሉብኝን አንድ አንድ ችግሮቼን በማስተካከል ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ ግቦችን ለማስቆጠር እቅድን ይዣለሁ”
በዲ ኤስ ቲቪ የሊጉ ጨዋታዎች መተላለፍ ስለመጀመሩ
“በእዚህ በኩል ጥሩ ነገርን እየተመለከትን ነው። ጨዋታዎቹ በመተላለፋቸው ወደ ውጪ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ወጥቶ ለመጫወት ይረዳናል። ከዛ በተጨማሪ የተጨዋቾቻችን የመጫወት ፍላጎትም ጨምሯል”።
በመጨረሻ….
“በእግር ኳስ ተጨዋችነት እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ ያገዙኝን ቤተሰቦቼንና የሰፈሬን ጓደኞች ማመስገን እፈልጋለው”።
አስተያየት ይስጡ