ተመልካች አልባው ግን ትልቁ የሸገር ደርቢ

ተመልካች አልባው ግን ትልቁ የሸገር ደርቢ
አዲስ አበባ (ማክሰኞ 4፡ዐዐ)
ቡርቱካናማ ወይስ ቡናማ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ቅ/ጊዮርጊስን እና ኢትዮጵያ ቡናን የሚያገናኘው የሀገሪቱ ትልቁ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ሁሌም ቢሆን በብዙዎች ዘንድ ተጠባቂነቱ እንዳለ ሲሆን ሁለቱ ቡድኖች የስም ለውጥን ባመጣው እና ዲ.ኤስ.ቲቪም የአገሪቱን የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በቀጥታ ማስተላለፍ በጀመረበት የአሁን ሰዓት ላይ ወሳኙን ጨዋታ ሊያደርጉ ለማክሰኞ ቀጠሮን ይዘዋል፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ቤትኪንግ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች በታሪክ ተጫውተው በማያውቁበት የጠዋት ክፍለ ጊዜ ማክሰኞ በ4 ሰዓት ላይ ሲደረግ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ያለ ዘርፈ ብዙ ደጋፊዎቻቸው ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ለእዚህ ጨዋታም ወደ ሜዳ የሚመጡት ቅ/ጊዮርጊስ ከቀናቶች በፊት ሰበታ ከተማን በሰፊ የግብ ልዮነት በማሸነፍ እና ኢትዮጵያ ቡናም ትናንት ባደረገው ጨዋታ ሰበታ ከተማን 3-2 በሆነ ውጤት ባሸነፉበት ሁኔታዎች ላይ ነው፡፡
የቅ/ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና የሸገር ደርቢ ጨዋታ በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ ከ1991 ጀምሮ ለበርካታ ዓመታቶች የተካሄደ ሲሆን አብዛኛዎቹን ግጥሚያዎች ቅ/ጊዮርጊስ በማሸነፍ የበላይነቱን ወስዷል፡፡

በአዲሱ የውድድር ስያሜ ይህን የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድርን ማን በአሸናፊነት ይወጣል? ቡድኖቻቸው አሁን ላይ በምን አቋም ላይ ይገኛሉ? በሸገር ደርቢው ጨዋታ ከተጋጣሚያቸው የቱ ተጨዋች ስጋት ይሆንባችኋል? በሚሉና ሌሎችንም ተመሳሳይነት መልክ ያላቸውን ጥያቄዎች ከሁለቱ ቡድን ተጨዋቾች ውስጥ ከቅ/ጊዮርጊስ የግራ እና የቀኝ መስመሩን የኮሪደር ስፍራ ተጨዋች ሄኖክ አዱኛን ከኢትዮጵያ ቡና ወገን ደግሞ ግብ ጠባቂውን ተክለማሪያም ሻንቆን /ጎሜዝ/ የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አናግሯቸው ሁለቱም ተጨዋቾች ለጥያቄው ምላሻቸውን ሰጥተዋል፤ ቃለ-ምልልሱም በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡

ሀትሪክ፡- የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የሸገር ደርቢ ጨዋታን በምን መልኩ ለማድረግ ተዘጋጅታችኋል? ጨዋታውስ ምን መልክ ይኖረዋል?

ሄኖክ፡- የኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚኖረን የሸገር ደርቢ ጨዋታ ሁሌም በጉጉት የሚጠበቅ ቢሆንም እኛ ግን ይህን ጨዋታ ለማድረግ እየተዘጋጀን የሚገኘው እንደ ማንኛውም ፍልሚያ እና ለሁሉም ቡድኖችም እኩል ግምትንና ትኩረትን እንደምንሰጠው ነው፡፡ የዘንድሮውን የሸገር ደርቢ ጨዋታ በተመለከተ ይህ ወሳኛ እና ተጠባቂ ጨዋታ የሚደረገው የኮቪድ ወረርሽኝ እንደ ዓለም ሁሉ ወደ አገራችን መግባቱን ተከትሎ የሁለታችንም ደጋፊዎች በብዛት በማይታደሙበት እና ቁጥራቸው ከ1ዐ የማይበልጡ ደጋፊዎች ብቻ ጨዋታውን በሚመለከቱበት ሁኔታ ስለሆነም ከድባብ አንፃር በስታዲየም ውስጥ የሚኖረው ገፅታ ደብዘዝ ይላል፤ ይህ ሊሆን ቢችልም እኛ ግን በሜዳ ላይ ጥሩ እንቅሰቃሴን በማድረግ ግጥሚያውን ሞቅ አድርገን ለመውጣት ከፍተኛ ጥረታችንን እናደርጋለን፡፡

ተክለማርያም፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና የሸገር ደርቢ ጨዋታ በሀገሪቱ የኳስ ታሪክ ውስጥ ሁሌም ቢሆን ተጠባቂው እና ትልቁ የደርቢ ጨዋታ ሲሆን የዘንድሮውም የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ያለ ደጋፊዎቻችን ሊካሄድ የማክሰኞ ቀንን ስለቆረጠ ለእዛ ጨዋታ በሚገባ እየተዘጋጀን ይገኛል፤ ይህን ጨዋታ የምናደርገው ሰበታ ከተማን ረትተን ወደ አሸናፊነቱ መንፈስ በተመለስንበት ሁኔታ ስለሆነም ለእኛ በጥሩ መንፈስ ወደ ሜዳ እንድንገባ ያደርገናልና ጨዋታውን በጉጉት ነው እየተጠባበቅኩትም የሚገኘው፡፡

ሀትሪክ፡- በሸገር ደርቢ ከእዚህ ቀደም ለምን ያህል ጊዜ ተሰልፈህ ተጫወትክ? በመጫወትህስ ስሜቱን እንዴት አገኘኸው?

ሄኖክ፡- ወደ ክለቡ ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ነው በእዚህ ተጠባቂው የደርቢው ጨዋታ ላይ ተሰልፌ ለመጫወት የቻልኩት፤ ይህን ጨዋታ ሳደርግም ግጥሚያው በሁለቱ ክለቦች ምርጥ ደጋፊዎች ታጅቦ የተከናወን በመሆኑ በውስጤ የተሰማኝ የደስታ ስሜት በጣም ከፍተኛም ነበርና በእንደዚህ ያለ ጨዋታ ላይ መሳተፍ መቻልን ወደፊትም ቢሆን ሁሌም የምትናፍቀውም ነው፡፡

ተክለማሪያም፡- ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር በሚደረገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ አምና ቡናን እንደመቀላቀሌ እስካሁን የተጫወትኩት ጨዋታ ለሁለት ጊዜያት ያህል ነው፤ በእዚህ ሁሌም ተፎካካሪ በሆኑ ቡድኖች ፊት ይህን ተጠባቂ ጨዋታን ለማድረግ በመቻሌም የማላውቀው አይነት የደስታ ስሜት ሊሰማኝም ችሏል፤ ይሄን የደርቢ ጨዋታ ስመለከትም አንዱ አንዱን አሸንፎ ለመውጣት የሚያደርገው ትግልን በተነፃፃሪነት መልኩም አንዱ በአንዱ መሸነፍን ፈፅሞ የማይፈልግበትን ሁኔታ እና ሌላ ምንም አይነት መጥፎ የሚባል ነገርን ስላልተመለከትኩ ለደርቢው ጨዋታ ጥልቅ ፍቅር እንዲኖረኝና ግጥሚያውን ጓጉቼም እንድጠብቀው ነው እያደረገኝ ያለው፡፡

ሀትሪክ፡- የቤትኪንግ የፕሪሚየር ሊጉ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ያለ ደጋፊዎቻችሁ ነው በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የምትከናውኑት፤ ይህን ተጠባቂ ጨዋታ በእዚህ መልኩ መደረጉን አስመልክታችሁ ምን ትላላችሁ?

ሄኖክ፡- የሁለታችን ክለቦች የደርቢው ጨዋታ ያለደጋፊዎቻችን የሚካሄድ መሆኑ ከላይ እንደገለፅኩት በስታዲየም ውስጥ ከእዚህ ቀደም ከሚታየው ደማቅ ድባብ አኳያ ሁኔታዎችን ደብዘዝ ሊያደርገው ቢችልም ለእኛ ግን የደጋፊዎቹ አለመኖር ብቻ የሚያመጣብን ምንም አይነት ተፅዕኖ አይኖርም፡፡ ጨዋታውንም ያለ ደጋፊዎቻችን ለግጥሚያው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እና ጥንቃቄም አድርገንበት ልናከናውነው ተዘጋጅተንበታል፡፡

ተክለማሪያም፡- በእርግጥ የሁለታችንን የደርቢ ጨዋታ ደጋፊዎቻችን በሜዳ ላይ ተገኝተው በህብረ ዝማሬያቸው ቢያበረታቱንና እንደዚሁም ደግሞ ለየቡድኖቻቸውም ተጨዋቾች ከፍተኛ ወኔን በመስጠት የማሸነፍ ስሜት ውስጥ ቢያስገቧቸው በስታድየም ውስጥ ደስ ከሚለው የአጨፋፈር ድባብ አኳያ መልካም ነበር የሚሆነው፤ ይህ እንዳይሆን ግን ለዓለምም ሆነ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት የሆነው የኮቪድ ወረርሽኝ በርካታ ደጋፊዎችን ወደ ሜዳ እንዳይመጡ ህጉ ስላስደነገገ ይሄ ሳይሆን ቀርቷል፤ እኛ ግን ያለ ደጋፊ መጫወትን አስቀድመን ስላወቅን እና ደጋፊዎቻችን ደግሞ ግጥሚያዎችን በቤታቸው እና በመዝናኛ ማዕከላቶች በቀጥታ ስርጭት የሚመለከቱበት አጋጣሚዎች ስለተፈጠረላቸው እነሱ ከጎናችን እና ከጀርባችን እንዳሉ እና ሞራልም እንደሚሰጡን አድርገንም ነው ግጥሚያውን ለማድረግ የተዘጋጀነው፡፡

ሀትሪክ፡- ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሸገር ደርቢ ጨዋታን ማክሰኞ ማን በአሸናፊነት ይወጣል?

ሄኖክ፡- ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ያለምንም ጥርጥር አሸናፊው እኛ ቅ/ጊዮርጊሶች እንሆናለን፡፡

ተክለማሪያም፡- እርግጠኛ ነኝ፤ አሸናፊነቱ ወደ እኛ ክለብ ነው የሚያመራው፡፡

ሀትሪክ፡- በማክሰኞው የሸገር ደርቢው ጨዋታ ከእናንተ ተጋጣሚ የቱ ተጨዋች ስጋት ሆኖባችሁ ያስፈራችኋል?

ሄኖክ፡- እኔ ሁሉንም የቡድኑ ተጨዋች በእኩል ሁኔታ ነው የማየው፤ እንደ አንድ ተጨዋችም አከብራችዋለው፤ ከእዛ ውጪ በእዚህ ተጠባቂ የደርቢ ጨዋታ ላይ ከእነሱ ወገን የሚያስፈራኝም ሆነ ተፅዕኖን ይፈጥርብል ብዬ የምሰጋው ተጨዋች አንድም አይኖርም፡፡

ተክለማሪያም፡- ኢትዮጵያ ቡና ከሌሎች ክለቦች አንፃር እንደ ቡድን የራሱ የሆነ የአጨዋወት ባህሪህ ስላለው እና እንደ ቡድንም በመጫወት የሚንቀሳቀስም በመሆኑ በማክሰኞው ጨዋታ ላይ ከቅ/ጊዮርጊስ ወገን የትኛውም ተጨዋች እኛን አያስቸግረንም፤ ለእዛ ጥሩ ዝግጅትንም አድርገናል፡፡

ሀትሪክ፡- በቤትኪንጉ የሸገር ደርቢ ከተጋጣሚያችሁ ለየቱ ተጨዋች ከፍተኛ አድናቆት አለህ?

ሄኖክ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ተጨዋቾች ውስጥ ከብዙዎቹ ጋር በብሔራዊ ቡድን ደረጃ አብረን የነበርንበት እና እዛም ተግባብተን የተጫወትንበት አጋጣሚዎች ስላሉ ከእነሱ ወገን የማደንቀው ተጨዋች ሁሉንም እንጂ አንዱን ተጨዋች ነጥዬ አይደለም፤ ሁሉም ተጨዋቾች ለእኔ ጥሩ ናቸው፡፡

ተክለማሪያም፡- ከቅ/ጊዮርጊስ ተጨዋቾች አድናቆት የምሰጠው ለሁሉም ተጨዋቾች ነው፤ እኔ አንደ አንድ እግር ኳስ ተጨዋች አይደለም ለእነሱ እኛን ለሚፎካከሩን የሌላ ክለብ ተጨዋቾች ክብርም አድናቆትም ነው ያለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊጉ ያላችሁ ወቅታዊ አቋምና እያስመዘገባችሁት ያለው ውጤት ምን ይመስላል?

ሄኖክ፡- የቡድናችን ወቅታዊ አቋም ጥሩ እና የሚያበረታታ ነው፤ የሊጉን ውድድር ስንጀምር በሽንፈት ነበር የጀመርነው፤ ከዛም ስለ ሽንፈታችን በሚገባ ተነጋገርን፤ ክፍተቶቻችንን እና ድክመቶቻችንንም አወቅን፤ በስተመጨረሻም ከሸንፈታችን በከፍተኛ ሁኔታ አንሰራርተን በመምጣት እና ለእያንዳንዱም ግጥሚያዎች ጥንቃቄ የተሞላበትን ትኩረት በመስጠታችን አሁን ላይ ወደ አሸናፊነቱ መንፈስ መጥተን የሊጉ አስፈሪ ቡድን መሆናችንን እያሳየን ይገኛል፡፡ ለእዚህ ውጤት መሳካትም በተሟላ ሁኔታ ጥሩ የቡድን ስብስብ ያለን መሆኑ ረድቶናል፤ ከዛ ውጪም በከፍተኛ ሁኔታ ሁሉም የቡድኑ ተጨዋች በአሰልጣኙ የሚሰጠውን የጨዋታ ታክቲክ እና ልምምድን በአግባቡ ስለሚከታተሉ እና በተግባርም ደስ ብሏቸውም ስለሚሰሩ ያም ነው ወደ ሻምፒዮንነት ማማው ሊወስደን የሚችለው፡፡

ተክለማሪያም፡- ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ የራሱ የሆነ አጨዋወት ያለው ክለብ ነው፤ ያንንም በሜዳ ላይ በመከተል ከጨዋታ ወደ ጨዋታም ራሱን እያሻሻለ እና በጥሩ ሁኔታም በመዋሀድ ላይ ያለ ስለሆነ በአቋም ደረጃም ሆነ እያስመዘገበ ባለው ውጤት ጥሩ ቡድን እንዳለው አሳይቷል፤ ወደፊት ደግሞ ከእዚህ በበለጠ እየተሻሻለ ስለሚሄድ ምርጡ ቡና እንደሚገነባ እና እንደሚፈጠር እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በሸገር ደርቢው የሚፋለማችሁ ቡድን ስለያዘው የጨዋታ ታክቲክ ምን የምትሉት ነገር አለ፤ ከእዛ ተነስታችሁ በምን መልኩስ ግጥሚያችሁን ልታደርጉ ነው?

ሄኖክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ከእዚህ ቀደም የያዘው አጨዋወት በአብዛኛው ኳስ ይዞ መጫወትን ነበር፤ ወደ ጎል ብዙ አይሄዱምም ነበር፤ የጎንዮሽ ኳስንም ያበዙ ነበር፤ አሁን ላይ ደግሞ አጨዋወታቸውን ብዙም ባለቀቀ መልኩ ወደፊት ለመጫወት የሚችሉበትን እንቅስቃሴም ስለተመለከትኩባቸው በሸገር ደርቢው ጨዋታ ላይ ቡድናችን በምን መልኩ መጫወት እንደሚኖርበት ከአሰልጣኛችን የሚሰጠንን ታክቲክ በመተግበር ግጥሚያውን በድል ለመወጣት ተዘጋጅተናል፡፡

ተክለማሪያም፡- ቅ/ጊዮርጊስ ጠንካራ እና ጥሩ ቡድን ነው፤ በአጨዋወት ደረጃም ኳስን ተቆጣጥሮ ከሚጫወተው ከእኛ ክለብ አንፃር በጣምም የሚለይ ጨዋታንም ነው በሜዳ ላይ የሚያሳየው፤ ይሄን ስለምናውቅ ከእነሱ ጋር በሚኖረን ጨዋታ በታክቲኩ ረገድ እነሱ ለእኛ ጨዋታ ምን አይነት አጨዋወትን ይዘው እንደሚመጡ ስለምንረዳና ለዛም ከወዲሁ እያሰብንበት ስለሆነ፤ ከዛም ውጪ ከእነሱ አጨዋወት ይልቅ የራሳችን አጨዋወት ላይ በማተኮርና በሜዳ ላይም እነሱን በምን መልኩ በማቆም እንደምናሸንፍ የሚረዳንን እና የሚያዋጣንንም እንቅስቃሴ ለመከተል ዝግጁ ነንና የጨዋታውን ቀን እየተጠባበቅን ነው የምንገኘው፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ….?

ሄኖክ፡- በሸገር ደርቢ ጨዋታ ከእዚህ ቀደም ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ ብዙ ሽኩቻዎችን ሜዳ ላይም ከሜዳ ውጪም እንመለከት ነበር፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይሄ ሁኔታ እየቀረ መጥቷል፤ ሰላማዊ እግር ኳስን እያየንም ነው፤ በማክሰኞው የቤትኪንግ የደርቢ ጨዋታም ይሄ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ምንም እንኳን ያለ ደጋፊዎቻችን ቢካሄድም እኛ ተጨዋቾችም ሰላማዊ ነገሩን በማስቀጠል ግጥሚያውን ፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ ለማድረግ ተዘጋጅተናል፡፡

ተክለማሪያም፡- የሸገር ደርቢ ከእዚህ በፊት ደጋፊ ለደጋፊ እንደዚሁም ደግሞ የሁለቱ ቡድን ተጨዋቾች በሜዳ ላይ በመጣላት ብዙ ሽኩቻን ይፈጥሩ ነበር፤ በዓለም ላይም ትላልቅ እና ብዙ የደርቢ ጨዋታዎችን ስንመለከት እስከመጣላትና እስከመገዳደል ሲደርሱም ያየንበት ሁኔታም ነበር፤ ይሄ ተገቢ ያለሆነ ነገር ነው፤ በደርቢው ጨዋታ በእኛ ሀገር ላይ የነበረው ሽኩቻ እና የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት አሁን አሁን ቀርቷል፤ በማክሰኞው ጨዋታም ላይ የእዚህ ደርቢ ተፋላሚ የሆኑት የሁለታችን ቡድን ደጋፊዎች ግጥሚያውን ስታድየም ሳይገቡ በዲ.ኤስ.ቲቪ የሚከታተሉበት ሁኔታ ስላለና እዛ ሲገናኙ ደግሞ በጋራ ኳሱን ስለሚመለከቱ እና ማሸነፍና መሸነፍ ደግሞ ያለም በመሆኑ ይህን በማወቅ ጨዋታውን በሰላም እንዲያዩ መልህክቴን እያስተላለፍኩ እኛም ተጨዋቾች ይህን ግጥሚያ መላው ዓለም በዲ.ኤስ.ቲቪ የሚመለከትበትም ሁኔታ ስላለ ኳሱ የሚፈልገውን ነገር ብቻ በሜዳ ላይ በማሳየት ግጥሚያው በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ምኞቴ ነው፡፡

Hatricksport website editor

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Hatricksport website editor