ሰበታ ከተማ 9 ተጨዋቾችን ሊያሰናብት ወሰነ

ሰበታ ከተማ 9 ተጨዋቾችን ሊያሰናብት ወሰነ

“ክለቦች ለዝውውር ሲመጡ ያልከፈሉት የተጨዋች ደመወዝ እንደሌለባቸው የሚገልፅ ደብዳቤና ሰነድ ማቅረባቸው የግድነው”
አቶ ባህሩ ጥላሁን/የኢ.እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ/


ሰበታ ከተማ ወደ 9 የሚጠጉ ተጨዋቾችን ለማሰናበት የወሰነው ውሣኔ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ሀትሪክ ባገኘችው መረጃ በኃይሉ አሰፋ /ቱሳ/፣ ሳሙኤል ታዬ፣ ደሳለኝ ደባሽ፣ ወንድይፍራው ጌታሁን፣ ታደለ ባይሳ፣ ፍርድ አወቅ ሲሳይን ጨምሮ 9 ተጨዋቾችን ከክለቡ እንዲሰናበቱ መወሰኑና የክለቡ አቋም ለተጨዋቾቹ እንደተነገራቸው ያስረዳል፡፡

በተለይ ለሀትሪክ መረጃውን የሰጠውና ውል ያለው ተጨዋች እንደሚለው “ማንኛውም አሠልጣኝ ያልፈለገውን ተጨዋች የማሰናበት መብት አለው፡፡ ውል እስካለው ድረስ ግን ሕጋዊ በሆነ መንገድ መሸኘት አለበት፡፡ የኛ የሰኔና የሀምሌ ወር ደመወዝ አልተከፈለንም የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ሊከፈት የቀሩን ቀናቶች ናቸው፡፡ በነዚህ ጊዜ ማድረግ ያለባቸውን አድርገው መልቀቂያ ካልሰጡን ለኛ ከባድ ነው፡፡ በቃል ጠርተው ከማናገር ውጪ ምንም አላደረጉም፡፡ ካሁኑ ካልተስተካከለ ችግር ውስጥ ነው የምንገባው” ሲል ሁኔታውን በተለይ ለሀትሪክ አስረድቷል፡፡ የበጀት የመልቀቅና ያለ መልቀቅ ጉዳይ በርካታ ክለቦች ከመንግሥት ስር የመሆን ውጤት ሲሆን ገና አልተለቀቀም ብለው ደመወዝ ካልከፈሉ ክለቦች መሀል ሰበታ ከነማ አንዱ ነው፡፡

የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወሰነው ውሣኔ መሠረት የዝውውር መስኮቱ የፊታችን አርብ መስከረም 15/2013 በይፋ ተከፍቶ ለ3 ወራት የሚቆይና ፊፋ የፈቀደ መሆኑ ታውቋል፡፡ ክለቦች ተጨዋቾችን አነጋግረው ለማፀደቅ መስከረም 15/2013 እየጠበቁ ሲሆን ሰበታ ከተማ ውል ያላቸውን ተጨዋቾች ጉዳይ በፍጥነት ካልጨረሰ ሊቸገሩና ቦታ ሊያጡ እንደሚችሉ የሚሰጉ በርካቶች ናቸው፤ የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አለማየሁ ሚንዳ በተለይ ለሀትሪክ እንደተናገሩት “የ3 ወር ደመወዛቸውን ለመክፈል እያመቻቸን ነው ከዚያ ውጭ ሌሎች ሊሟሉ የሚገባቸውን ጉዳዮች ጨርሰን አሟልተን ለማሰናበት እየሰራን ነው ውል ያላቸው ተጨዋቾችም ሆኑ ውል የጨረሱትን ሌላ ክለብ እንዲፈልጉ ከሁለት ወር በፊት ነግረናቸዋል የሚፈልጉት ክለብ ከተገኘ በእኛ በኩል የሚፈጠር ችግር አይኖርም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የክለቡ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩሉ “የነበረብንን ክፍተት ለመዝጋት ያየናቸውን ስህተቶች ለማረም የሚረዱ ስራዎችን እየሰራን ነው፡፡ ከነዚህም መሀል አዳዲስ ቡድኑን ሊየጠናክሩ የሚችሉ ተጨዋቾችን ለማስፈረም በ2013 እቅዴ ውስጥ የሌሉትን ተጨዋቾች ማነጋገርና በሠላም መለያየት የግድ በመሆኑ ይህንን ነው ያደረግነው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል የ2013 የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት የፊታችን አርብ ሲከፈት ማን ለማን ክለብ ፈረመ የሚለው ጉዳይ ትኩረት የሚሰብ ሆኗል፡፡ በርካታ ክለቦችም በተጨዋቾች ይገባኛል ጉዳይ ውዝግብ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ እየተሰጋ ነው፡፡ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ተገኝቶ ያልፀደቀ ውል ተቀባይነት እንደሌለው እየታወቀ ክለቦች ተጨዋቾችን ማዘዋወራቸው ተጨዋቾችም ለተለያዩ ክለቦች ፊርማቸውን ማኖራቸው የሰሞኑ አስገራሚ ገጠመኝ በመሆኑ የክለብ ተወካዮች መሀል ፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ሲገናኙ ከቃላት ጦርነት እስከ ግብግብ ድረስ ሊገጥሙ ይችሉ ይሆን የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ክለቦች ማስፈረምና መያዝ ካለባቸው የተጨዋቾች ቁጥር በላይ አስፈረሙ መባሉ ግርምትን ፈጥሯል፡፡ አንድ ክለብ 25 ተጨዋች የሚይዝ ሲሆን 27 ተጨዋቾችን የሚይዙና የሚያስፈርሙ ክለቦች አሉ መባሉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ 25 ተጨዋቾች በያዝና ባልያዙ ክለቦች ውጤት ላይም ራሱን የቻለ ተፅዕኖ ይኖረዋልም ተብሎ ተሰግቷል፡፡ ከ25ቱ ተጨዋቾች ውጪ ያሉት ገብተው የሚሰለፉ ሲሆን በህጋዊነት የፈረመው አንድ ተጨዋች ልምምድ ይሰራል ደመወዝ ይወስዳል ነገር ግን ግጥሚያ ላይ አይሰለፍም ይህን መሰሉ ተንኮል በክለቦቻችን ላይ ታይቷል መባሉ ፌዴሬሽኑ ላይ ጣት እንዲቀሰር አድርጓል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የተጠየቁት የፌዴሬሽኑ ዋና ፀኃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ግን “በፍፁም አይደረግም” ሲሉ ይናገራሉ፡፡ “እንደዚህ አይነት ትልቅ ወንጀል ይሰራ እንደነበርና ከባለሙያዎችም ጋርም የሚሞዳሞዱ እንዳሉ ሰምተናል፡፡ ነገር ግን ለዚህ አይነቱ የኳሱን የፉክክር መድረክ የሚገድል ተንኮል በራችን ዝግ ነው በቲሴራ ላይ የተመዘገበው ሌላ የሚጫወተው ሌላ ነው ሲባል ሰምቻለሁ አሁን ግን በፍፁም አይደረግም ፌዴሬሽኑ በቀጣይ የራሱን ምርመራ አድርጎ ከደረሰበት ክለቡን ወደ ታችኛው ሊግ የማውረድ ርምጃ እንደሚወስድ በድርጊቱ ላይ የተሳተፉ የፌዴሬሽኑ ሠራተኞች ላይም ከሥራ የማባረር ርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ዝተዋል፡፡

የፊታችን አርብ መስከረም 15/2013 ስለሚከፈተው የዝውውር መስኮት የተጠየቁት ዋና ፀሐፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን “ዝውውሩ ሲከፈት ሀድያ ሆሳዕና፣ ወላይታ ድቻ፣ ጅማ አባጅፋር አዳማ ከተማና ሰበታ ከተማ የተላለፈባቸው እገዳ እንደፀና ነው፡፡ አሁንም ለሁሉም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የሚሳተፉና ዝውውር ለማድረግ የሚመጡ ክለቦች በሙሉ ምንም አይነት እዳ እንደሌለባቸውና ከእዳም ነፃ መሆናቸውን የሚያሳይ የሰነድ ማስረጃ ካላቀረቡ ዝውውር መፈፀም አይችሉም፡፡ ከዚህ በፊት በተላከው ደብዳቤ ብቻ የሚፈፀም ውል የለም” ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport