“በእግር ኳሱ ለመለወጥ እና የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ስል ወደ መቐለ አምርቻለሁ” ምንተስኖት ከበደ /አፍሪካ/ /መቐለ 70 እንደርታ/

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኑ ለሆነው መቐለ 70 እንደርታ በቅርቡ ፊርማውን ያኖረው ምንተስኖት ከበደ /አፍሪካ/ በመጪው ዓመት የውድድር ተሳትፎአቸው ከአዲሱ ክለቡ ጋር ለራሱ የመጀመሪያውን ለክለቡ ደግሞ ሁለተኛውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ከክለብ አጋር ጓደኞቹ ጋር ለማንሳት ማቀዱን ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው ስማቸው ከፍ ብሎ ለሚጠሩት የአዳማ ከተማ እና የመከላከያ ክለቦች በተከላካይ መስመሩ ላይ በመጫወት ጥሩ የሚባል ጊዜን ያሳለፈውን ይህን ተጨዋች ሀትሪክ ከመከላከያ ወደ መቐለ 70 እንደርታ ስላደረገው ዝውውርና ስላሳለፈው የኳስ ህይወቱ አጠር ባለ መልኩ አነጋግረነዋል፤ ተከታተሉት፡፡

ወደ መቐለ 7ዐ እንደርታ ስላደረገው ዝውውር
“የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ያለኝን የውል ጊዜዬን ካጠናቀቅኩኝ በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የዓምና ሻምፒዮና መቐለ 70 እንደርታ ላመራ የቻልኩት ክለቡ የሊጉ ጠንካራ እና ውጤታማ ቡድን ስለሆነ እንደዚህም ደግሞ በተጨዋችነት ዘመኔ ሌሎች ስኬቶች ተጎናፅፌ ያላሳካሁትን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ድል ከዚህ ቡድን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ለማግኘት እና የክለቡ አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌም ካለው የማሰልጠን ምርጥ ብቃት አንፃር አሁን ላይ ያለኝን ችሎታ እና አቅም ባለው የማሰልጠን ልምድ አቅሜን በጣም ያስደግልኛል ብዬ ስላሰብኩ ቡድኑን ለመቀላቀል ችያለሁ”፡፡
በመከላከያ ክለብ ውስጥ ስላሳለፈው የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው
“የመከላከያ ክለብ ውስጥ የነበረኝ ያለፉት አራት አመታት የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ጥሩ የሚባል ነው፤ በፕሪሚየር ሊጉ ላይ እያለን ጠንካራ የነበረውን ቡድናችንን ውጤታማ ለማድረግ የሚቻለኝን ጥረት አድርጌያለው፤ ወደ ከፍተኛው ሊግ ከወረድን በኋላ ግን ዘንድሮ ቡድኑን መልሶ ወደነበረበት ቦታ ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረትን ብናደርግም ኮቪድ 19 ወደ አገራችን በመግባቱ እና አጠቃላይ ውድድሩም በመሠረዙ ወረርሽኙ ደግሞ በዓለም ጭምር የመጣም በመሆኑ ይህ ሳይሳካ ቀርቷል፤ ያም ቢሆን ግን እንደ ግልም ቢሆን ጥሩ ጊዜን ነበር ያሳለፍኩት”፡፡
ወደ ታችኛው ሊግ ወርዶ የእግር ኳስን ስለ መጫወት
“በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ቡድንን አሳድጌ ለመጫወት ቻልኩ እንጂ ከጓደኞቼ ጋር አንድ ክለብን አውርጄ ኳስን የተጫወትኩበት ጊዜ አንድም አልነበረም፡፡ የእዚህ ዓመት ላይ ግን ይህ እውን ሆነ፤ መከላከያ በታችኛው ሊግ ወርዶ መጫወት ያልነበረበት ክለብ ነበር፤ ያ መሆን መቻሉም ያማል፤ በተለይ ደግሞ በታችኛው ሊግ ስትጫወት ከሜዳዎች ምቹ አለመሆንና ከሌላም ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በጣም ከባድ ነገርንም ልንመለከትበት ችለናልና ይህን ፈፅሞ የምትመኘውም”፡፡
ከመከላከያ ተጨዋችነቱ በፊት አዳማ ከተማ እያለ ስለነበረው ተሳትፎ
“አዳማ ከተማ በነበርኩበት ሰዓት ይህን ክለብ ሳገለግል የነበርኩት ከከፍተኛ ሊጉ ጀምሮ ነው፤ በቆይታዬም ቡድኑን በሚገባ ለማገልገልም ችያለው፤ በታችኛው /የከፍተኛ ሊ/ግ ተሳትፏአችንም በሰፊ ነጥብ ተከታዮቻችንን በመብለጥ የፕሪሚየር ሊጉን ከጓደኞቼ ጋር እንዲቀላቀል አድርጌዋለው፤ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደግን በኋለም ከአንድም ሁለት ጊዜ ጠንካራ ቡድንን ይዘን ቀርበንና ሊጉንም በ3ኛ ደረጃ በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት የሆንበት ጊዜ አለና እነዚህ በክለቡ ቆይታዬ ትልቅ የሚባሉ ውጤቶች ናቸው፡፡
የመከላከያ ወደ ከፍተኛው ሊግ መውረድ
“ወደ ታችኛው ሊግ ለመውረዳችን ዋንኛ ምክንያቶቹ ጣታችንን ሌላ ቦታ መቀሰር ትክክለኛ ነገር ስላልሆነ እግር ኳሳዊ የሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡ ጥቂት ችግሮች የሚባሉት ደግሞ ከስዑል ሽረ ጋር ስንጫወት የደረሰብን በደል እና ሌላው ደግሞ ስዑል ሽረ ከወልዋሎ አዲግራት ጋር ሲጫወት ያለ አግባብ ጨዋታውን እንዲያሸንፍ የተደረገበት መንገድ ነው”፡፡
ከመቐለ 70 እንደርታ ውጪ ሊያመራ ስለነበረባቸው ክለቦች
“መቐለ 70 እንደርታ ገፍቶ ስለመጣና ቀድሞ ስለጠየቀኝ እኔም ደግሞ መጫወትን እዛ ስለፈለግኩ እንጂ በኤጀንቶች እና በደላሎች አማካኘነት ወደ ወልቂጤ ከተማ፣ አዳማ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ የምገባበት እድል ነበረኝ፤ ግን ቀዳሚ ምርጫዬ መቀለ ሆነና ለቡድኑ ፈረምኩ”፡፡
ስለ ትዳር ህይወትህ
“የእግር ኳስን ስትጫወት የትዳር ህይወት በጣም አስፈላጊ ነው፤ እኔም ከባለቤቴ ሳራ አክሊሉ ጋር በመሰረትኩት ትዳር መልካም የህይወት እና የትዳር ጊዜን ከቤተሰቦቼ ጋር እያሳለፍኩ ነው፤ ሁለት ልጆችን ማለትም ማራማዊት እና አሜንን ከባለቤቴ ላገኝም ችያለውና ይሄ በጣሙን ያስደሰተኝ ነው”፡፡
በኮቪድ ወቅቱን በምን መልኩ እያሳለፈ እንደሆነ
“ኮቪድ ከባድ ወረርሽኝ ሆኗል፤ ይህን ስላወቅኩም አሁን ላይ ከአዲስ አበባ በተሻለ አዳማ ከተማ ያለው ነገር የሚሻል በመሆኑ እና የባለቤቴም ቤተሰቦች እዛ ስላሉ ቤተሰቦቼን እዛ በመውሰድ ጊዜውን እያሳለፈኩ ነው፤ ለኮቪድ አስፈላጊውን ጥንቃቄም እያደረግኩኝ ነው”፡፡
በመጨረሻ
“የእግር ኳስ ዘመኔ በክለብ ተጨዋችነት ብቻ እንዲያበቃ አልፈልግም፤ ለብሔራዊ ቡድን መጫወትን እፈልጋለሁ፤ ያን ጠንክሬ በመስራትም እልሜን አሳካለው”፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website