THE BIG INTERVIEW WITH METO ALEKA FEKADE MAMO
በዮሴፍ ከፈለኝ
2012 በኮሎኔል አወል አብዱራሂም የሚመራው የሊግ ኮሚቴ ከስሞ ክለቦች የራሳቸውን ውድድር ሊመሩ ተዘጋጅተዋል…..የሊግ ካምፓኒ ምስረታው ሲከሽፍ ፌዴሬሽኑ ውድድሩን ለክለቦቹ ሰጥቶ ድጋፍ ማድረግን መርጧል……ሰባት አባላት ያሉት ግብረ ሃይል ከተቋቋመ በኋላ በስሩ የውድድርና ስነ ስርአት ኮሚቴ አዋቅሮ ውድድሩን ሊያካሂድ እየታገለ ይገኛል…….ውድድሩን እንዲመራ የተመረጠው የ2012 የኢትዮጲያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አዘጋጅ አቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደግሞ የኢትዮጲያ ቡና የስፖርት ክለብ የቦርድ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ናቸው…… ወሎ ሰፈር በሚገኘው ቢሯቸው ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ቆይታ የነበራቸው መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ስለ ሃላፊነቱ፣ስለ ዳኛ ኮሚቴና ምደባ፣የአቶ ዮሴፍ ስንብት ላይ የቡና እጅ ይኖርበት ይሆን፣ስለ ሜዳዎች ጥራት፣ የጸጥታ ዋስትና አለመገኘቱ፣በዝግ ይካሄድ ወይ ስለሚባለው፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በአቋም ተለያይተው ይሆን፣ ኢትዮጲያ ቡና የሚያስታውሳቸው ስራ ሰርተው ይሆን፣በሃገሪቱ እግርኳስ ዙሪያቅር ያላቸው ነገር ይኖር ይሆን፣በኢትዮጲያ ቡና ተተኪያቸው እየተዘጋጀ ይሆን በሚሉና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ምላሽ ሰጥተዋልና ተከታተሉት
ሀትሪክ፡- የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አዘጋጅ አቢይ ኮሚቴ የሚለው ስም እንደ ድግስ ረዘም ያለ አልመሰሎትም?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡-(ሳቅ በሳቅ) ከስሙ ምን አለህ….. (ሳቅ በሳቅ) ስሙ የፈለገ ይሁን ምን ያረግልሃል? ከስራው ተነስተህ እናውራ…… (ሳቅ በሳቅ)
ሀትሪክ፡- የሰብሳቢነት ኃላፊነትዎ ሹመት ወይስ ጫና?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ሹመት አይደለም፡፡ ሹመት ከነክብሩ ሲሆን ነው….. ከክብሩ ጋር ለቦታው የሚመጥን ቢሮ፣ መኪና፣ ደመወዝና አበል ሲኖረው ነው ሹመት የሚባለው…. ይሄን ስራ ስሩ ተብሎ ነው የተሰጠን….. ጫና አለው የተሰጠንን ኃላፊነት ለመወጣት ግን እየሞከርን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ምርጫው በርስዎ ላይ ያለውን እምነትስ አያሳይም?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ያሳያል… ክለቦች የራሳችንን ውድድር እንመራ አቅም አለን ውስጣችን ሰው አለ ገንዘቡም ከኛ ነው የሚወጣው ሊጉን በአግባቡ መምራት እንችላለን ብለው ተሰባስበው የሰጡት ውሳኔ ነው፡፡ ጥሩ አድርገን ለመምራት እንሞክራለን፡፡
ሀትሪክ፡- ከ35 አመት በላይ ኢትዮጵያ ቡናን መሩ በቃቸው እየተባለ…. ይባስ ብሎ በሀገር ደረጃ የሊግ ውድድር መሪ ሆኑ…. ሹመት ይከተለኛል ብለው ያስባሉ?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- የዚህ ሀገራዊ ኃላፊነት አመጣጥን ላውራህ… የሊግ ካምፓኒ የመመስረት አጀንዳ የያዘ ውይይት ተዘጋጀና የ16 ክለቦች ተወካዮች ተሰባሰቡ፡፡ ሲጀመር የሊግ ካምፓኒ ምስረታ አይቻልም በሚል ተወሰነ፡፡ 2ኛው ደግሞ ውድድሩን ለፌዴሬሽኑ አንተወውም የሚል አቋም በመያዙ ከራሳችን ክለቦች ተወካይ መርጠን ውድድሩን እንምራ ተባለ… ውሳኔው ላይ ጥድፍያና ፍጥነት አለበት፡፡ እንደ ቡና የተገኘነው ሼር ካምፓኒ ምስረታው ከሕግ አንፃር አግባብና ተቀባይነት የለውም የሚል አቋም ይዘን ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑም ውሳኔውን ተቀበለና ከክልልና ከተማ አስተዳደሩ አንድ አንድ ተወካይ ይመረጥ ተባለና የአዲስ አበባ ተወካይ ሆነን በሊጉ የምንካፈል እኛና ጊዮርጊሶች ተመካክረን ተመረጥኩ.. እኔ ወይም አቶ አብነት ነበር የምንሆነው አቶ አብነትም ስላልነበረ እኔ ተወከልኩ… ሰባታችን በጋራ ተወያየንና ሰብሳቢው ፈቃደ ይሁን ተብሎ ተመረጥኩ ሁኔታው ይሄ ነው፡፡ ተከተለኝ ለሚለው እኔጃ…ነው….?

ሀትሪክ፡-አዲስ አበባ እንደመኖርዎ የስራ ጫና የለብዎትም?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ይከብዳል.. ሊጉን የምናደራጀው ከምንም ተነስተን በመሆኑ ብዙ ሥራዎች ይጠበቁብናል መመሪያ ማውጣት የሰው ኃይል ማደራጀት (አንዱ በነፃ አገልግሎት የሚሳተፍ ሁለተኛው ተቀጥረው ቢሮ ውስጥ የሚሰሩ) በተጨማሪ ቢሮ ያስፈልጋል የመጀመሪያው አመት ትንሽ ከበድ የሚል ይመስለኛል፡፡ የተመረጥነው ሰባት ሰዎች እንደ ካውንስል ነን በስራችን ዋና ስራ አስኪያጅ፣ ውደድርና ስነ ሥርዓት፣ ማርኬቲንግ የተለያዩ ኮሚቴዎች ይዋቀራሉ፡፡ የዕለት ተዕለት ስራዎች በስራ አስኪያጁ ሲመራ እኛ በወር አንዴ እየተገናኘን ፖሊሲ ማውጣት ሕግና ደንብ ማዘጋጀት የመሳሰሉትን እንሰራለን፡፡
ሀትሪክ፡- በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የሚመራው ቡድኑ ላይ ሪጎሬ ሲሰጥ ተጨዋቾቹን ከሜዳ ውጡ ያለ አመራር ተካቷል፡፡ በዚህ አይነት የባህሪ አለመናበብ ስጋት የለባችሁም?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- እግር ኳስ ከማንኛውም ድርጅት በለው ኩባንያ ጥንቅቅ አድርጎ ሕግና ደንብ መመሪያ ያለው ተቋም ነው፡፡ ለምንም ነገር ቀዳዳ አይተውም፡፡ በፍጥነት የሚወሰኑ ጉዳዮችም አሉበት ውድድር ላይ ትልቁ አካል ዳኝነት ነው ዳኝነት ለመቅስበት የሚወሰን ውሳኔ ያለበት እንደመሆኑ ውሳኔው በስህተት ነው፣ ትክክለኛ ነው፣ በሙስና ነው? የሚለው ጉዳይ ይነሣል፡፡ የዳኝነትን ቀዳዳ ለመዝጋት ዳኛው ድጋፍ እንዲያገኝ ቫር /VAR/ መጥቷል ይሄ ደግሞ ክፍተቱን ለመዘጋት የተኬደበትን ርቀት ያሳያል፡፡ ይህን ያነሳሁት ቡድኖች እንዴት እንደሚጫወቱ ከቡድን መሪው፣ ከአሰልጣኙ…. ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቀውን ሁሉ ያስቀመጠ ደንብ አለው ማንም ይሁን ቡድኑን ና ውጣ ብሎ ውሳኔ ተቃውሞ ከተንቀሳቀሰ ዝም ተብሎ አይታይም ይቀጣል፡፡ እዚህኮ የሚገርም ነገር ነው ያለው፡፡ እዚያ ሄጄ አልጫወትም ሲል ለምን አትጫወትም ሲባል የሚጠሉኝ አሉ ይላል፤… ይህን መሰል ጉዳይ ፌዴሬሽኑ መቀበል አልነበረበትም ክለቦች ገና ሲጀመር የፊፋንና ካፍ ህግና ደንብ እቀበላለው ብለው ነው የሚፈርሙት፡፡ የፊፋን ህግና ደንብ በአግባቡ አለመተርጎም ራሱ አንድ ሙስና ነው ለምንድነው ሕጉ በአግባቡ የማይተረጎመው? ሜዳ ውስጥ ዳኛ ሲደበደብ ደብዳቢው ቡድን መሪ አንድና ሁለት አመት ብቻ ነው እገዳው የሚበቃው? አሁን ጠንክረን መታገል ያለብን ለእገሌ እገሌ ብለን አይደለም፡፡ የኳሱን ሕግ በተግባር መተርጎም ፍትሃዊነትን ያስገኛል፡፡ ወላይታ ዲቻ ይርጋለም ላይ ከሲዳማ ቡና ጋር አልጫወትም ካለ ፎርፌ ነው… ሲዳማም በተመሳሳይ…. አዲስ አበባ አምጥቶ ማጫወቱ ለምን አስፈለገ? ይሄ ህገ ወጥ አሰራር ነው አሁን ግን ይህ አይከሰትም፡፡ በሜዳህ ደጋፊዎችህ ረብሻ ካስነሱና ጉዳት ካደረሱ ፎርፌ ነው ቅጣቱ፡፡ የፊፋና የካፍ ሕግና ደንብ በአግባቡ መተርጎም አለመቻላችን ነው ችግሩ፡፡ በርግጥ ልዩ ልዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የገዢው መደብ ነው…ያስፈራል እያሉ ሕግ አለመተርጎም አይቻልም ለዚህ ነው ኳሱ የማይሻሻለው… እኛ ግን የፊፋን ሕግና ደንብን ለመተርጎም እንደፍራለን፤ አይ ይህ አይተረጎምም ካሉን ጥሎ መሄድ ነው…. ስህተት ሊኖር ይችላል ግን ፈርተን ዝም አንልም ዋናው ጉዳይ ትክክለኛ ሰውን በትክክለኛ ቦታ ማስቀመጥ ነው በዚያ ሰው ስራ ላይ ጣልቃ አለመግባት እንዳይገቡበትም መከላከል ይጠበቃል፡፡ ከተሳሳተ ወይም ካልቻለ ተጠያቂ ይሆናል ይባረራል ይሄ ነው በኛ ሀገር የጠፋው…. እኛ ግን ለመስራት ተዘጋጅተናል፡፡
ሀትሪክ፡-የዳኝነት ኮሚቴ ምርጫን በተመለከተ ኃላፊነቱ የናንተ ነው? ወይስ?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡-የዳኝነት ኃላፊነትን ለሊጎች አይሰጥም ብሎ ፊፋ ደንግጓል፡፡ የፊፋን ሕግ እናከብራለን፡፡ ዳኝነት ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ፍትሃዊ ውድድር እንዴት ይካሄዳል የሚለውን ከዳኛ ኮሚቴ ጋር ቁጭ ብለን እንወያያለን ይሄ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ዳኛ እኛ እንመድብ፣ ለኔ ሪፖርት ያድርጉ፣ እከሌና እከሌ ሲጫወቱ አደራህን እያልን ጣልቃ አንገባም፡፡ ነገር ግን ባለፉት አመታት እንዳነበረው ደላላ ጣልቃ የሚገባበት ሊሆን አይገባም፡፡ ይሄ አይደበቅም አንዳንድ ሰዎች ይህን ስል ሊቀየሙ ይችላሉ… ነገር ግን የእውነት የሆነ ነገር ነው፡፡ ይህን መጥፎ ድርጊት ማስወገድ አለብን ለዳኞች ሙሉ ነፃነት ሰጥተን የሚችሉትን መርጠን መመደብ ይጠበቃል ባለፉት አመታት ብዙ ያጫወቱ፣ ትንሽ ያጫወቱ ምንም ያላጫወቱ አሉ ይሄ ለምን ሆነ? በችሎታ ከሆነ እሰየው፡፡ ጥሩ ዳኝነት አሳይቷል ከተባለ መልካም….የስፖርት ቤተሰቡ የሊጉ ደረጃ ተሻሽሏል ብሎ እንዲያምን ማድረግ አለብን፡፡ የውድድርና ስነሥርዓት በሚገባ መምራቱ፣ ሜዳው በጊዜ መከፈቱ ህዝቡ በጊዜ መግባቱ ብቻ በቂ አይደለም ዋናው ቁልፍ ዳኝነቱ ነው ይህን ዳኝነት ፍትሃዊ ለማድረግ መወያየት አለብን፡፡
ሀትሪክ፡-የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በአቶ ኢብራሂም አህመድ ተተክተዋል.. በሹም ሽሩ ላይ የኢትዮጵያ ቡና እጅ ይኖርበት ይሆን?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- በፍፁም የለበትም… አቶ ኢብራሂም ማን እንደሆኑ አላውቅም ኢትዮጲያ ቡና ሙሉ በሙሉ የለበትም ግን አሁንም ድረስ ቦታው መያዝ ያለበት የዳኝነት ሙያው ባለው ሰው ነው ፊፋም የሚለው ይህንን ነው በዚህ ጉዳይ ላይም ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጋር የምንጋገርበት ጉዳይ ነው፡፡ የዳኞች ኮሚቴ በደንብ መጠናከር አለበት ዳኞች ኮሚቴን የሚመራው ባለሙያ ማነው የሚለው ለኛ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-እንደ ባለሙያ አቶ ልዑል ሰገድ በጋሻውን ለመመለስ እየተሞከረ ነው… ሰምታችኋል?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- እኔ አላውቅም… አልሰማሁም /ሳቅ/
ሀትሪክ፡-የሜዳዎችን ጥራት በተመለከተ ያለው ነገር ምንድነው?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ወደ 9 የሚጠጉ ሜዳዎች በኮሚቴ ደረጃ ታይተዋል ከዚያ ውስጥ 4 ሜዳዎች ማጫወት አይችሉም ተብሎ ታግደዋል ወደ 3 የሚጠጉ ሜዳዎች ደግሞ ማስተካከያ እንዲደረግባቸው ታዟል፡፡ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት አንድ ዙር የመገምገሙ ነገር ይቀጥላል፡፡
ሀትሪክ፡-ዋናው መመዘኛ የሜዳ ጥራት? ወይስ የደህነንት ጉዳይ ነው?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ሁለቱም መሰረታዊ ጉዳዮች,ናቸው በመጀመሪያ የተጨዋቾች ደህንነት መጠበቅ አለበት፡፡ ዝም ብለን የተቆፈረ ጉድጓድ ባለበት ሜዳ ላይ ገብተው እንዲሰባበሩ ማድረግ የለብንም ሜዳዎች የማስተካከል ሥራ ሊሰራ ይገባል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ተመልካቹ እንዳይጋጭ የጨዋታው ውጤት ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ዳኛው ላይ ጫና እንዳያደርግ ሜዳው ከደጋፊው ተለይቷል ወይ የሚለውን አይተናል፡፡
ሀትሪክ፡- ደጋፊዎች የመስመር ዳኛው አርማ ሊያወጣ ሲል ከኋላው አንቀው ይዘው እንደነበር ሰምተዋል?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡-/ሳቅ በሳቅ/ ይሄኮ ህዝቡ ብልህ ሆኗል ማለት ነው… በየቀኑ ዲ ኤስ.ቲቪ ስለሚያይ ይመስለኛል ተመልካቹ ባይጫወትም እንዴት ቡድኑን ከመከላከል ምን ማድረግ እንዳለበት አውቋል /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- የክልልና የከተማ አስተዳደር አመራሮች የፀጥታ ዋስትና አልሰጡምና.. የ2012 የፕሪሚየር ሊግ ውድድር አይካሄድ ይሆን የሚለው ስጋት አልገባዎትም?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- እንደርሱ ብዬ መደምደም አልፈልግም፡፡ ጥቅምት 15/2012 የነበረው ቀነ ገደብ ቢያልፍም ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ መታየት አለበት፡፡ በየቦታው ያሉ አመራሮች ቢዚ የሆኑበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የፀጥታ ጉዳዩ እጅግ ሲበዛ አሳሳቢ ነው፡፡ አንተም እንደ ጋዜጠኛ ጋዜጣዬን ለማነው የምሸጠው ብለህ ማሰብህ አይቀርም ለፀጥታው ማስከበር ቅድሚያ ሰጥተው ይሆን ብለን አስበናል፡፡ አሁንም እስከ ጥቅምት 30/2012 ድረስ ምላሽ ስጡን አለበለዚያ ከውድድር እንደወጣችሁ ቁጠሩት ብለን ልንልክ ነው፡፡ ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤት በቅርቡ ሲሰበሰብ መመሪያ ይሰጣል ብለን እንጠብቃለን… እነኚህ ሁኔታዎችን ደምረን ቀንሰን ውድድሩ ይካሄድ ይሆናል ብለን እናስባለን፡፡
ሀትሪክ፡-በዝግ ይካሄድ የሚለው መፍትሔ አይሆንም?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡-በዝግ የሚባል ነገር ልክ አይደለም፡፡ ፊፋ የደነገገው ሕግ አለ፡፡ በዝግ ለመጫወት የሚያስገድዱ ክስተቶች መኖር አለባቸው፡፡ ግብፅን ተመልከት የጸጥታ ሃይል በብሔራዊ ደረጃ የእግር ኳሱ ውድድር ይቀጥል ክለቦቹ ሀገር የሚወክሉ ናቸው ለፊፋና ካፍ ሕጎች አላፊነት አለብን ውድድሩን ለመጨረስ በዝግ ይካሄድ ብሎ ፊፋም አውቆት የተደረገ ሊሆን ይችላል… የኢትዮጵያ ሁኔታ ሲታይ እንደ ግብፅ የተከሰተ ነገር የለም…. በእርግጥም እንዳይከሰት መጠንቀቅ ግን ይኖርብናል፡፡
ሀትሪክ፡-የእንግዳው ቡድን ደጋፊ ሳይገባ የባለሜዳው ቡድን ደጋፊ ብቻ አስገብቶ ማጫወትስ መፍትሔ አይሆንም?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ለምን ይሆናል? አማራጭ ነው ማለትም አይቻልም ያልሆነ ተፅዕኖስ ለምን ይኖራል? የቡናና መቐለ ጨዋታ ጊዜ ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ አስተያየት ሲሰጥ ነበር፡፡ የኛ ደጋፊዎች የምንሰጣችሁ ቦታ ትንሽ ነው 1000 አውቶቡስ ይዛችሁ
አትምጡ ያለው ቦታ የ50 አውቶቡስ ብቻ ነው ማለት ፊፋም የሰጠው መብት ነው አበቃ፡፡ ይህን መብት አልፎ ፖሊስ አይቻልም ማለት አይችልም… አንዱ ያከራከረን ይሄ ነው፡፡ ሁለተኛው ይሄ ህገ መንግሥት የጣሰ አነጋገር ነው አሉ፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መንቀሳቀስ መብቱ ነው ወደሚል ተተርጉሞ በጊዜው ለማስረዳት ሞክረናል ጥፋቱ ደግሞ የፌዴሬሽኑ ነው፡፡ የፊፋን ሕግ ስለሚያውቅ የቡና መብት ነው ማለት ነበረበት ግን ዝም አለ፡፡ ይሄ አሁን መስተካከል አለበት ከፌዴሬሽኑ ጋር ቁጭ ብለን የምንወስነው እንግዳው ቡድን ስንት ፐርሰንት ይዞ ይምጣ በሚለው ዙሪያ ነው… መመሪያ መቀመጥ አለበት በፊፋ ደረጃ ሕጉ አለ ፐርሰንቱ ላይ ርግጠኛ ባልሆንም…
ሀትሪክ፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ይዘውት የነበረውን አቋም ትተው ወደዚህ እጥፍ ያሉት ስለተመረጡ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ.. በርግጥስ ታጥፈዋል?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ወደየት ነው የታጠፍነው /ሳቅ በሳቅ/
ሀትሪክ፡-ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር በተዟዙሮ ውድድር ላይ አልከፈልም ካላችሁ በኋላ አመራርነቱን ሲይዙ የአቋም ለውጥ አድርገው እጥፍ አሉ ለሚሉ መልስዎት ምንድነው?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- 2012 የምርጫ አመት ነው፤ 2011 ያየናቸው ችግሮች በ2012 ሊባባሱ ይችላሉ እንዳይባባስ የሚያደርጉ ሁኔታዎች እስከዛሬ ድረስ አላየንም፡፡ ረብሻ የሚፈልጉ ፖለቲከኞች እግር ኳስን ሰበብ አድርገው በህዝብ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ መጣር አለብን ብለን እንጂ ሌላ ፍላጎት የለንም፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ማሸነፍ አቅቷቸው ነው የሚሉትን ግን ተወው ምንም ትርጉም የለውም… በርግጥስ እስከዛሬ ውድድሩ ሲካሄድ ዋንጫ ያሸነፉት ክለቦች ውድድሩ በትክክል ተካሄዶ ነው የሚለውም ያከራክራል፡፡ መንግሥት ሁሉም በየክልሉ ይጫወት የሚለውን የኛን አቋም ሰማና ጠርቶ ውሳኔውን አከብራለው ሌሎቹ ክለቦች ደግሞ የፀጥታ ችግር የለም ለዚህ ነው የተዟዙሮ ውድድር ይሁን የምንለው ብለው የፀጥታ ዋስትና ሰጥተውናል ስለዚህ በዚህ መልክ መቀጠል አለበት፡፡ ለኛም የፀጥታ ዋስትና እንዲሰጡ ደብዳቤ ፃፉላቸው አለን… ይኸው አሁን ዋስትና ለመስጠት ፍቃደኛ ያልሆነ ክልል ከውድድሩ ይወጣል ብለን ወስንን እየጠበቅን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ እጥፍ አላልንም…..
ሀትሪክ፡-ምናልባት ግን የፀጥታ ዋስትና ቢመጣስ ተመልካቹን በደንብ መቆጣጠር ይቻላል ብለው ያምናሉ?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ዋስትና መፃፍ ለድርድር አይቀርብም ብለናል… የፀጥታ ኃይሉ ስታዲየሙንና ከተማውን በአግባቡ መጠበቅ ይችላል ከፀጥታ ኃይል አቅም በላይ የሆነ ችግር አለ ብለን አናምንም፡፡
ሀትሪክ፡- እርስዎ ሊጉን እየመሩ ቡና የሊጉን ዋንጫ ሲወስድ… ?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ፈቃደ አደላ ሊባል ነው…? /ሳቅ በሳቅ/
ሀትሪክ፡-አይ አይ… እርስዎ ሊጉን እየመሩ ኢትዮጵያ ቡና ዋንጫ ቢያነሳ ብለው አስበው ይሆን?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- አይ አላስብኩም…. በአጋጣሚ የኢትዮጵያ ቡና ቡድን ጥሩ ቡድን ነው የፈረሙትን ተጨዋቾችም አሰልጣኙን ስናይ የጊዜ ጉዳይ እንጂ እጅግ ጠንካራ ቡድን እንደሚሰራ እምነቱ አለኝ፡፡ ግን በገባነው ቃል አሰልጣኙ ላይ አላስፈላጊ ጫና አናደርግም 2012 ዋንጫ ብናገኝ ደስ ይለናል ባናገኝም ግን አንከፋም 2013 ግን በርግጠኝነት ዋንጫ እናገኛገለን ብለን ነው የምንጓዘውና ጉዞውን ወደፊት እያየነው እንሄዳለን፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና የሚያስታውሰኝን ስራ ሰርቻለሁ ብለው ያምናሉ?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- አላምንም… እንዲህ አድርጌያለው ብዬም አልናገርም ተረካቢው ትውልድ ነው ይሄን መናገር ያለበት፣ ተነስቼ ቅርስ ትቼልሃለው አደራህን የምለው ነገር የለም፡፡ የሰራሁትን አይተው ሌሎች ይበሉ እንጂ ይህን አደረኩ ብዬ አልናገርም፡፡
ሀትሪክ፡- ቅር የተሰኙበት በሀገራችን እግር ኳስ ላይ ቢያዩት የሚወዱት ነገር አለ?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ኳሳችን እድገት የለውም ነገር ግን በደመወዝ ከጋና ናይጄሪያና ዛምቢያ እንበልጣለን ተተኪ ታዳጊዎችም የሉንም በደመወዝ ምናልባት ደቡብ አፍሪካ ብትፎካከርን ነው ሊጉ ጠንካራ በመሆኑ ክፍያውም የተሻለ መሆኑ ይጠበቃል፡፡ የኛን ክፍያ ከፍ ያደረገው ምንድነው የሚለው መታየት አለበት፡፡ ኢንዱስትሪው ተበድሮ ነው የሚካፍለው የማዘጋጃ ቤቱ ኃላፊ ብር የለም ካለ አበቃ….. ክለቦች ቁጭ ብለን መነጋገር አለብን፡፡ 110 ሚሊዮን ህዝብ አለ፡፡ ይሄ በቂ አቅም እንዳለን ያሳያል… ለቀጣዩ ዘመን መንግሥትም ኃለፊነት አለበት፡፡ 110 ሚሊዮን ህዝብ ይዘን ተጨዋቾችን ለምን ከአፍሪካ እንቀጥራለን? ይሄ አይቆጨንም? ልንቆጭ ልናስተካክለው ይገባል… እኔ ራሴ ለዚህ ጥፋት አንዱ ተጠያቂ ነኝ፡፡ ክለቦች መፍትሄ መፈለግ አለብን ያኔ ነው ኳሳችንን ከሆስፒታል የምናስወጣው….. ሜዳ ያላቸው ክለቦች 5 አመት ያቅዱ ሜዳቸውን ለአሰልጣኞች ክፍት ያደርጉና ሁሉን ድጋፍ ይስጡት…ከዚያም በየአመቱ ምን ያህል ተጨዋች አሰልጥነህ አወጣህ? የሚለው የውጤት መለኪያ አድርገን መጠየቅ ይቻላል….መልሱ ልክ ካልሆነ ያኔ ሜዳውን መከልከል ይቻላል… መጀመሪያ ግን በራችን ይከፈት ተጨዋቾቹ ለጨዋታ ከደረሱ ደግሞ በሀገሬ ያሉ ክለቦችን ጠርቼ ለምን ከውጪ ትገዛለህ? ይኸው ወጣቶቹን ተረከብ ብዬ መነጋገር እችላለው ይሄ የኔ ኃላፊነት ይሆናል፡፡ ይሄን ጊዜ ነው ለብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተተኪ ተጨዋቾችን አፍርተን ኃላፊነታችን ተወጣን ማለት የምንችለው….ይሄ ባለመሆኑ ግን ቅር ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- እርስዎን የሚተካ መሪ በክለብዎ ደረጃ እየተዘጋጀ ይሆን?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ይህን ማሰብ ያለባቸው የክለቡ ባለቤቶች ናቸው… ባለቤቶቹ ቡና ላኪዎች፣ አቅራቢዎችና ደጋፊዎቹ ባለቤት እንደመሆናቸው ተተኪው ላይ መዘጋጀት አለባቸው….. በመተዳደሪያ ደንብ ውስጥ የክለቡ ፕሬዚዳንት የሚሆነው ከቡና ላኪዎች የሚወከለው ሰው ነው ይላልና የቡና ላኪዎች ውስጥ ደግሞ ትላልቅ ኢንዱስትሪ የሚመሩ ብዙ ሰዎች አሉና ተተኪ ፕሬዚዳንት ይጠፋል ብዬ አላምንም…. አቅምና ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ እንደኔ ግን መሆን ያለበት ረጅም ጊዜ መቆየት ሳይሆን በአፍላ ጉልበት ሰርተው ቶሎ ቶሎ ቢተካኩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በመተካካት አምናለው እያሉ ነው?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡-አዎ በደንብ እንጂ ትልቁ መፍትሔም ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡-የአዲስ አበባ ዋንጫ ተራዝሟል የመጨረሻ የዋንጫ ጨዋታው ደግሞ ወደ ህዳር 13 ሊጠጋ ነው ይሄ ማለት ደግሞ የፍፃሜ ጨዋታ አይካሄድም ወይም የሊጉ መጀመሪያ ቀን ሊራዘም ነው…. የርስዎ ምላሽ ምን ይሆን?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ማነው የሚያራዝመው? ገና መች ተወያየን… አንድ ሁለቴ ደውለውልኛል ከቅዳሜ ወደ ሐሙስ አዛውሩ ከተባለ ለምን ተዛወረ የሚለው መመለስ አለበት፡፡ በቂ ምክንያት ከተገኘ እኛም እንቀበላለን፡፡ ዝግጅት ስላልነበረ ቅዳሜ አታደርጉም ሀሙስ አድርጉ ሲባሉ ዝም ብለው ከተቀበሉ የኛ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ስንጫወት የደህንነት ስጋት ስላለ ጨዋታው በዝግ ይሁን አሉ፡፡ እንዴ ትላንትና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ስታዲየም ገብተው ፀልየው ወጥተዋል ምንም አልተፈጠረም…ለኛ ሲሆን ነው ወይ ስጋቱ? ያለው ችግር ከታወቀስ ለምን ርምጃ አልወሰዳችሁም? አልናቸው በርግጥ አንዳንዴ ከደህንነት አንፃር ሁሉንም ነገር ማወቅ መብታችን አይሆንም ለማንኛውም በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ማክሰኞ ተሰብስበን እንመክራለን /ቃለ ምልልሱ የተሰራው ባለፈው አርብ ነው/
ሀትሪክ፡-ድሮና ዘንድሮን ስናይ በፊት ምርጥ ኳስም አለ የደጋፊ ረብሻም ይከሰት ነበር … አሁን ግን ኳሱ የለም ረብሻው ጨምሯል፤.. እርስዎ የቱን ጊዜ ተመኙ?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ብዙ ጊዜ እድሜያቸው የገፋ ሰዎች የልጅነት ዘመናቸውን ነው እንደገና የሚመኙት… እንደርሱ ነው ካልተባለ በስተቀር በልጅነት ዘመኔ ያየሁት ኳስና የአሁኑ አይገናኝም… ኳስ ጨዋታው፣ የተጨዋቾቹ አቅም፣ ፍላጎትና ተሰጥኦ በፍፁም አይመጣጠንም፡፡ ድሮ እነ መንግሥቱ ወርቁን አስታውሳለው ከጨዋታ በኋላ ታኬታቸውን ቋጥረው ትከሻቸው ላይ አድርገው ነው ለሻወር ፍልውሃ የሚሄዱት….. የሚሰጣቸው ምናልባት 30 ሳንቲም ቢሆን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ጨረስኩ የመጨረሻ የሚሉት መልዕክት?
መቶ አለቃ ፈቃደ፡- እግር ኳስ አላማ አለው ዝም ተብሎ ሜዳ ሄዶ መጫወት ብቻ አይደለም፡፡ ኳሱ ትልቅ ገንዘብ የሚገኝበት ሆኗል እንደ ድሮ በነፃ የምትጫወትበት አይደለም ተጨዋቾቹ ሙያቸውን በአግባቡ ያክብሩ ይስሩ፡፡ ጥቅም ማግኘታቸው ጥሩ ቢሆንም ከነርሱም የሚጠበቀው ብቃትን ይተገብሩ… ይሄ ከሌለና የራስ ሙያ ራስህ ካላከበርከው ማንም ሊያከብርልህ አይችልም ይሄ ባለመሆኑ በጣም አዝናለው፡፡ የኛ ሀገር ተጨዋቾች ከአሰልጣኙ ውጪ በተጨማሪ ለልምምዳቸው ጊዜ ቢሰጡ ጥሩ ነው ሮናልዶን ተመልከቱ አሰልጣኙ 1 ሰዓት ቢያሰለጥነው ነው እርሱ ግን 5 ሰዓት ይጨምርበታል… ይሄ ነው ሙያ ማክበር፡፡ ወደ አሠልጣኝ ስንሄድ የኛ ሀገር ስልጠና ልኩን አላውቅም ነገር ግን ልምድ ያላቸው አሰልጣኞች ሌሎች አሰልጣኞችን ለማሰልጠን የሚያደርጉት ጥረት ምንድነው… እኔ ይኑር አይኑር አላውቅም፤ አሰልጣኞቹ ችሎታቸውን ለማሳደግ የማታ ይማሩ አይማሩ መረጃው የለኝም… ምናልባት የሚማሩ ይኖሩ ይሆናል፡፡ ከዚያ አልፈው ከትልልቅ የአውሮፓ ት/ቤቶች ጋር ያላቸው ግንኙነት ምንድነው? ከደመወዝ ጨምሩልኝ ጥያቄ ወጥተው ክለቦቻቸውን ሄደን እንማር ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? አይመስለኝም… ተመልካቹ ጋር ስንሄድ ያልሰራውን ማጨድ ይፈልጋል፡፡ ቡድኑ ሲዘጋጅ ምን ይመስላል? ራሴን ጭምር ነው የምወቅሰው… አሁን ኢትዮጲያ ቡና ውስጥ ከጠቅላላው በጀት ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ ለደመወዝ ነው የምናወጣው ሌላው የምግብ የትራንስፖርት ሲባል ያልቃል ይህን ያህል ሚሊዮን ብሮችን ክለቡ አውጥቶ በንብረት ደረጃ ምንም የለውም፡፡ ስለዚህ ይህን እንዴት ነው የምንለውጠው ተብሎ መጠየቅ አለበት አለበለዚያ ከመንግሥት ካዝና ወይም ከህዝቡ እየወሰድን በደመወዝ እንጨርሰዋለን፡፡ የእውነቴን ነው ክለቦች ቁጭ ብለን መነጋገርና አካሄዱን መለወጥ አለብን… ወደ አካዳሚ ፊታችንን ማዞር የግድ ነው፡፡ ቡና ዘንድሮ ሁሉንም በሚያስችል መንገድ ነው ተጨዋቾችን የለወጠው… ይሄን በየአመቱ ማድረግ ይቻላል? አይቻልም ስለዚህ ካለፈው ስህተት እየተማርን የእስከዛሬው መንገድ አክሳሪ ስለነበር ለነገው ቁጭ ብለን አዲስ አቅጣጫ መቀየር ያለብን ይመስለኛል፡፡ ይህን አመራር መስጠት ያለበት ደግሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነው…. በየአመቱ አወዳድሮ መሸለም ብቻ በቂ አይደለም… ወደ ልማት እንግባ…… ክለቦች ምን ላይ ይሳተፉ? በማለት አቅጣጫ የማስቀመጥ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡
አስተያየት ይስጡ