ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ያልገባ የውክልና ውል ተቀባይነት የለውም ተባለ

ማንኛውም የተጨዋቾች ወኪል በስሩ ያሉት ተጨዋቾች ውል ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ገብቶ ካልፀደቀ በስተቀር ተቀባይነት የለውም ሲል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

ከፌዴሬሽኑ በተገኘ መረጃ ፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ሳይመጡና ውሉ በህጋዊነት ሳይፀድቅ ተጨዋቾቹ የኛ ናቸው የሚለው ውዝግብ በተደጋጋሚ ማጋጠሙን ገልጾ ተጨዋቹ ከክለቡ ጋር ሲፈራረም የሚፀድቀው ፌዴሬሽን ጽ/ቤት በመምጣት እንደሆነ ሁሉ የሶስተኛው ወገን ውልም የሚፀድቀው ፌዴሬሽኑ ባለበት እንጂ አየር በአየር አይሰራም ብሏል፡፡ ከውል ጋርም ተያይዞ ውሉ የሚፀድቀው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ፌዴሬሽን ጽ/ቤት በመምጣት ብቻ መሆኑን ተገንዝበው የሚመጠበቅባቸውን እንዲፈፅሙ ጠይቋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ተጨዋቾች የውክልና ክፍያ ላለመፈፀም የሚሄዱበት መንገድ ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ሀትሪክ ባገኘችው መረጃ መሰረት የሶሶተኛ ወገን ፍቃድ የሌላቸው ወኪሎች ጋር በመደራደር ክለብ ካገኙ በኋላ ሕጋዊ ፍቃድ ስለሌላቸው አንከፍልም የሚሉ ተጨዋቾች መኖራቸው እየተነገረ ነው፡፡ ብልጣብልጥነት ያለባቸው ተጨዋቾች ወኪሉ ከፌዴሬሽኑ ጋር ፍቃድ እንደሌለው የሚያውቁትን ወኪል አነጋግረው ክለብ ሲያገኙ ስልካቸውን ማጥፋትና ቃል የገቡትን ክፍያ አለመፈፀም እየተለመደ መጥቷል፡፡

ተጨዋቾችና ክለቦች ፍቃድ ከሌላቸው ወኪሎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቆም ወይም ከተጠቀሙ የሚገባውን ክፍያ ለወኪሎቹ መስጠት የግድ ይሆናል ይሄ የሞራል ጉዳይ ነው ሲሉም የእግር ኳስ የሕግ ሰዎች ይናገራሉ፡፡
የሶስተኛ ወገን ውል በሕግ አስገዳጅነት የሌለው በመሆኑ ተጨዋቾችና ክለቦች ፍቃድ ከሌላቸው ወኪሎች ጋር የመስራት እድል እንደፈጠረላቸው ሀትሪክ ያኘችው መረጃ ያስረዳል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport