“ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ተገኝቶ ያልተካሄደ የውል ፊርማ በቢቢሲ በሲኤንኤን በአልጀዚራ ቢታይም ትርጉም የለውም”አቶ ገዛኸኝወልዴ /ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዋና ስራ አስኪያጅ/

“ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ተገኝቶ ያልተካሄደ የውል ፊርማ በቢቢሲ በሲኤንኤን በአልጀዚራ ቢታይም ትርጉም የለውም”

“የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሕግን ስርዓትን መርህን አሰራርን ፕሮፌሽናሊዝምን መሠረት አድርጎ የሚሄድ አይደለም”
አቶ ገዛኸኝወልዴ
/ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዋና ስራ አስኪያጅ/

የኢትዮጵያ ቡና ወሳኝ  ተጨዋቾች ወደ ሌሎች ክለቦች መጓዛቸው ደጋፊዎች አበሳጭቷል:: የክለቡ አመራሮች ዝምታ ምንድነው? ከዝውውር አንፃር ጽ/ቤቱ ምን እየሰራ ነው? በሚል ባልደረባችን ዮሴፍ ከፈለኝ ወደ ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ጋር ደወለና ጥያቄውን አቀረበ፡፡የኢትዮጵያ ቡና የዝውውር ገበያ ዝምታ ምክንያቱ ምንድነው? አቶ ገዛኸኝ ግን “ጽ/ቤት ዝውውር ላይ የለበትም ይህን ኃላፊነት የያዘው የስራ አመራር ቦርዱ በመሆኑ እኔን አይመለከተኝም፡፡ በስራው ላይም ተሳትፎ እያደረኩ አይደለም “ሲሉ ምላሽ ሰጡ……. አቶ ገዛኸኝ በዝውውር ጉዳይ ላይ ባይኖሩበትም በዝውውር ሕጎችና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ደፋር ምላሽ ሰጡን.. እንዲህ አስተናገድነው፡፡ 

ሀትሪክ፡- የኮሮና ቫይረስ መከላከል ላይ እንዴት ነዎት?
ገዛኸኝ፡- ከባድ ነገር ከፊት ለፊታችን ያለ ይመስለኛል፡፡ በተቻለ መጠን ለመጠንቀቅ እየታገልኩ ነው ማክስ አድርጌ እንቀሳቀሳለሁ በየሰዓቱ እጅ ለመታጠብ እሞክራለሁ ከፍ ሲልም በሳኒታይዘር እጄን አጠራለሁ ከዚህ ውጪ ያለውን ደግሞ ፈጣሪ ነው የሚጠብቀኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የህብረተሰቡ ጥንቃቄስ ጥሩ ነው ማለት ይቻላል?
ገዛኸኝ፡- ህብረተሰቡ ጋር መዘናጋቶች ያሉ ይመስለኛል፡፡ አንዱና ዋናው ችግር የአኗኗር ሁኔታችንና የገቢ ምንጫችን ለዚህ አይነት ነገር የሚያጋልጥ ይመስለኛል፡፡ በየቀኑ ገንዘብ አግኝቶ ህይወቱን መምራት አለበት የዕለት ኑሮውን ለማሸነፍ በልቶ ለማደር መንቀሳቀስም አለበት፡፡ ሳልበላ በራብ ከምሞት በልቼ በኮሮና ብሞት ይሻለኛል የሚል አቋም የያዘ ይመስለኛል፡፡ ይህም ቢሆን ጥንቃቄ እያደረገ ስራውን መስራት ይገባዋል፡፡ ጥንቃቄ ሊጎለን አይገባም፡፡ በርግጥ ቤት ውስጥ መቀመጥ የሚለው ላይሆን ይችላል ጥንቃቄን ማድረግ ግን የግድ ነው ኢኮኖሚው በራሱ ለችግሩ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብዬም አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡-በውጪ አገራት ደረጃ ያለው ስርጭትስ ስጋት አይኖርም?
ገዛኸኝ፡- ያለው ሁኔታ እጅግ የሚያስፈራ ነው…. የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትኮ በጋራ የሚሉት በኢትዮጵያ ደረጃ ያለው የኮቪድ 19 ስርጭት ጣራ ላይ አልደረሰም እስቲ አስበው ጫፍ ላይ ሲደርስ ምን ሊኮን ይችላል የሚለው በጣም የሚያሰጋ ነው፡፡ አሁን ባለን የጥንቃቄ አልባነት እየተጓዝን ከሄድን በአለም አቀፍ ደረጃ የምንሰማቸው መጥፎና አስደንጋጭ ዜናዎች የሀገራችን የዕለት ተዕለት ዜና ሊሆን ይችላልና ከባድ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ማለት እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከኮቪድ 19 ስርጭት አንፃር ስፖርቱ ተጎድቷል የሚል ነገር አለ… እንደ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ተጎድቷል፡፡ማለት የሚያስችል ሁኔታ አለ?
ገዛኸኝ፡- በተለያየ ጊዜ እንደ ክለብ የደረሰብንን ጉዳት ለመግለፅ ሞክረናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 16 የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ሁለቱ ክለቦች ብቻ ናቸው በቀጥታ በመንግሥት በጀት ወስደው የማይንቀሳቀሱት፡ በራሣቸው የገቢ አቅም ልክ ለመጓዝ እየጣሩ ያሉ ክለቦች ሁለቱ ናቸው ከነኚህ 2 ክለቦች መሀል አንዱ ኢትየጵያ ቡና ነው……ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ከሌለ የክለባችን የገቢ አቅም እንደሚያሽቆለቁል ይታወቃል አንዱ የገቢ ምንጫችን የስታዲየም ገቢ ነው…..በዚህ አመት ከሜዳ እስከ 12 ሚሊዮን ብር ለማግኘት አቅደን የመጀመሪያው ዙር 5.5 ሚሊዮን ብር አግኝተናል፡፡ በ2ኛ ዙር እስከ 7.5 ሚሊዮን ብር ለማግኘት አቅደን ሳይሳካ በመቅረቱ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተጎድተናል ማለት ይቻላል፡፡ ከብራንድ ስፖንስራችን ጋር ተያይዞ የአልኮል ሻጭና ተቋም ስለሆነ፣/ሀበሻ ቢራ ፋብሪካ/ በዔክሳይዝ ቀረጥና ማስታወቂያ በይፋ መናገር በመከልከሉ እንዲሁም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተነሣ ገቢው ዝቅተኛ በመሆኑ ፓርትነርሺፓችን ላይ የደረሰው ጫና ለእኛም ተርፏል፡፡ ገቢው በማነሱ ወደእኛም የሚመጣው ገቢ እያነሰ እንዲሄድ ሆኗል፡፡ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሲኖር ነው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚኖርው…. በአንድ ጊዜ ከ80-100 ሚሊዮን ብር የሚበጅት ተቋም ሊኖር ይችላል ነገር ግን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ የማይገኝ ከሆነ ግን በአንድ ወቅት መቆሙ የማይቀር ነው በአጠቃላይ ግን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ኢትዮጵያ ቡና ላይ የተወሰነ ጉዳት ደርሷል፡፡
ሀትሪክ፡-በ2013 ዓ.ም በሀገር ደረጃ እግር ኳስ ይቀጥላል ለማለት ያስደፍራል?
ገዛኸኝ፡- ከቫይረሱ ጋር ተያይዞ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው መታየት አለበት፡፡ የኮቪድ 19 ስርጭቱ ገና ጫፍ ላይ አልደረሰም እየተባለ በቀን ከ800-900 ሰው በቫይረሱ እየተያዘ ነው…. ጫፍ ላይ ቢደርስ ደግሞ ከዚህ ቁጥር በላይ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል…. እግር ኳስ ወይም ስፖርት እንቅስቃሴዎችና ንክኪዎች ያለባቸው እንደመሆናቸው ይሄ ደግሞ ሌላ ችግር ማስከተሉ እንደማይቀር ጤና ሚኒስቴርም ሆነ አጠቃላይ መንግሥት ይረዳሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር የ2013 እግር ኳስ እንዴት ይሆናል የሚለው አሳሳቢ ሆኗል ውድድሩ ይኖር ይሆን? የሚለው ጥያቄ ስጋት ውስጥ የሚከት ነገር ከፊታችን ያለ ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡-ኮቪድ 19 ለመከላከል ኢትዮጵያ ቡና ምን እየሰራ ነው?
ገዛኸኝ፡-እንደ ክለብ ቫይረሱ በሀገር ደረጃ ተከስቷል ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ የመከላከያ መንገዶችን ህብረተሰቡ እንዲያውቃቸው በተለይ ደጋፊዎቻችን በተለያዩ አካባቢዎች እጅ የማስታጠብ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ በመኪና የተለያየ ቅስቀሳዎችን አድርገናል፡፡ ከዚያም ባሻገር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ኢኮኖሚካል እንቅስቃሴዎች ጨምሮ አጠቃላይ ገደብ ሲጣል በየቀኑ ስራቸውን መስራት ያልቻሉ ወገኖችን የመርዳት ስራ ተሰርቷል፡፡ እንደ ክለብና ደጋፊ ማህበር 700 ሺ ብር የሚያወጣ ሀብት ተሰብስቧል፡፡ በቅርቡ ለሚመለከታቸው ወገኖች ይደርሳል ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- አዲሱ የክለባችሁ ሜዳ ተመርቆ ስራ ጀመረ? ወጪውስ ስንት ደርሷል?
ገዛኸኝ፡- የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በነበረ ጊዜ በዚያው ደጋፊው ሜዳውን እንዲያይ ተደርጓል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻውን ሜዳችን ላይ መደረጉ ሜዳችንን ውብ አድርጎታል አየሩንም ጥሩ ያደርገዋል በሚል ሜዳው ላይ ስራውን ሰርተናል… የመለማመጃ ሜዳችን የሚቀረው አንዳንድ ነገሮች ጨርሶ ለማስመረቅ ትንሽ ጊዜ የሚፈጅ ይመስለኛል፡፡ እኔ ከመጣሁ ጀምሮ እስካሁን የተሻለ ሥራ ለመስራት ተሞክሯል በገንዘብ ደረጃ ከ1-5 ሚሊዮን እስከ 2 ሚሊዮን ብር ድረስ ወጪ አድርገናል፡፡
ሀትሪክ፡-ክለቦች የዝውውር መስኮቱ ሳይከፈት ዝውውር እያደረጉ ነው.. ያስኬዳል?
ገዛኸኝ፡- እንደ አጠቃላይ የዝውውር አካሄድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር መመሪያ የሚለው ላይ በአንቀፅ 8 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ የአንድ ተጨዋች ተገቢነት ወይም ምዝገባ የሚረጋገጠው ውሉ ከተጠናቀቀና ከውል ነፃ ከሆነ በራሱ ወይም ሕጋዊ በሆነው ወኪሉ አማካይነት ፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት በመገኘት ፈላጊ ክለቡ ተገኝቶ በፊት ለፊት ተስማምተውና ተፈራርመውበት በፌዴሬሽኑ ማህተም አርፎበት ሲጠናቀቅ ብቻ ነው ይላል…. ነገር ግን ይሄ እየሆነ አይደለም የውድድር መስኮቱም አልተከፈተም፡፡
አሁን እየተደረጉ ያሉ ዝውውሮች በመመሪያው መሰረት ሕጋዊ ናቸው ተብለው የሚወሰዱ አይደለም፡፡ አንድ ተጨዋች እዚህ ክለብ ነኝ ማለት ይችል ይሆናል፡፡ ሕጋዊ ሆኖ ዝውውሩ ተጠናቆ እገሌ የተባለ ተጨዋች እዚህ ክለብ ገብቷል ማለት የሚቻለው መስኮቱ ተከፍቶ ሕጋዊ ውል ሲደረግ ብቻ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-አንድ ክለብ የፈለገውን ተጨዋች ያስፈርም አሁን ባለው አካሄድ ርግጠኛ ሆኖ ተዘዋውሯል ማለት ይቻላል?
ገዛኸኝ፡- አይቻልም…. ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ተገኝቶ ያልተካሄደ የውል ፊርማ በቢቢሲ በሲኤን ኤን ይሁን በአልጀዚራ ቢታይ ትርጉም የለውም፡፡ በዋናነነት መስኮቱ ተከፍቶ ኤጀንቱ፣ ተጨዋቾቹና ክለቡ ወይም አሁን ባለው 3ኛ ወገን አካሄድ ፌዴሬሽን ተገኝተው ካልተፈራረሙና ሕጋዊ ማህተም ካልተመታ ሕጋዊ መሆን አይቻልም ስምምነት ፈፅመናል ሊሉ ይችላሉ የተጨዋቾች ተገቢነት ነው ማለት ግን አይቻልም፡፡
ሀትሪክ፡- ሀምሌ ላይ ከፈረመ አንድ ተጨዋች ደመወዙን ማግኘቱ አይቀርም… ሌላ ክለብ ፌዴሬሽን ወስዶ ቢያስፈርመውና ሕጋዊ ቢያደርገው የተከፈለው ደመወዝ እንዴት ሊሆን ይችላል?
ገዛኸኝ፡-ፌዴሬሽኑ የቀረበለትን ክስ ሊመለከተው የሚችለው ተጨዋቹ ወይም ክለቡ ሕጋዊ በሆነ መንገድ መፈራረም ከቻሉ ብቻ ነው፡፡ፌዴሬሽኑ እገሌ የሚባለው ተጨዋችና እገሌ የተሰኘው ክለብ እኔ ፊት መጥታችሁ የፈረማችሁት ውል ካለና ይህን ከጣሰ እቀጣዋለው እኔ ፊት መጥቶ ያልፈረመው ውል ሕጋዊ ባለመሆኑ ልቀጣው አልችልም ማለቱ አይቀርም፡፡ ክለቦችም የሚከፍሉበት ሕጋዊ  የክፍያ ስርዓት ትክክል አይደለም ማለት ነው፡፡ የመንግሥት ክለቦች አሰራርን በደንብ አውቃለው ሰርቼ ስለማውቅ አካሄዱን እረዳለሁ፡፡ ተጨዋቹ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ሄዶ እስኪፈርም ድረስ ከ5 ክለቦች ጋር ሊስማማ ይችላል ግን አያስቀጣውም የመንግሥት ክለቦች አንድ ተጨዋች ፈርሞ ደመወዝ ሲጠይቅ የፋይናንስ ኃላፊዎች የሚጠይቁት ከፌዴሬሽን ጋር ሄደው የተፈራረሙትን ውል አምጣ ነው የሚሉት፡፡ ከዚያ ውጪ ከሆነ ግን የክለቡ የፋይናንስ ስርዓት አካሄድ መመርመር ይኖርበታል፡፡ ከዚያ ውጪ የሚደረጉ ክፍያዎች ተቀባይነት ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ከመንግሥት ምንም አይነት ድጎማ የማይደረግላቸውና ፋይናንሳቸውን በራሣቸው የሚያንቀሳቀሱ ክለቦች በፌዴሬሽን ውልም ባይሆን በራሣቸው ከፍለው ውላቸውን ግን ፌዴሬሽኑ መስኮቱን በከፈተበት ቀን ላይ አድርገው ሊያካሄዱ ይችላሉ፤ ያለው እውነት ይሄ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በኮቪድ 19 ተጎድተንም ቢሆነ የተጨዋቾች ዋጋ እየጨመረ መሄዱ ጤነኝነት ነው?
ገዛኸኝ፡- ኮቪድ 19 በአለማችን እግር ኳስ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ የሚታይ ነው፡፡ የአውሮፓ ሀብታም ክለቦች ሳይቀር የተንገዳገዱበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በተጨዋቾች ዝውውር ላይም እየተሳተፉ እንዳልሆነ እየታየ ነው የሚገኘው ከዚህ የተነሣ የተጨዋቾች ዋጋ የወረደበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ይሄ የአለም ነባራዊ ሁኔታ ነው…. ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ኮቪድ 19 ኖሮም የፋይናንስ አቅማችንም ተጎድቶ የተጨዋቾች ዋጋ ግን በየጊዜው ይጨመራል ምክንያቱ ደግሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሕግን ስርዓትን መርህን አሰራርን ፕሮፌሽናሊዝምን መሠረት አድርጎ የሚሄድ አይደለም፡፡ የፕሮፌሽናሊዝምን አካሄድ ቢተገብር በተጎዳ ኢኮኖሚ ላይ ተጨማሪ ወጪ አይበዛም ነበር፡፡ በአውሮፓ ተጨማሪ ክፍያ የሚከፈለው ክለቦች ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያገኙ ርግጠኛ ከሆኑ ነው ተጨማሪ ገቢ ከሌለ ተጨማሪ ወጪ አያወጡም እኛ ሀገር ግን ተጨማሪ ገቢ ተገኘም አልተገኘም በየጊዜው የተጨዋቾች ዋጋ እያደገ ይሄዳል ለእግር ኳሱም ሆነ ለፕሮፌሽናሊዝም አካሄድ ትልቅ ጉዳት የሚያመጣ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ጨረስኩ.. የመጨረሻ የአባይ ውሃ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት መደረጉ ምን ስሜት ፈጠረብህ?
ገዛኸኝ፡- በአባቶቻችን አኩሪ ታሪክ በተለይ በአድዋ ድል የምንኮራ በነፃነት የኖርን በቅኝ ያልተገዛን ብለን የምንኮራ ህዝቦች መሆናችን ይታወቃል፡፡ ከሚገባ በላይ በአድዋ ድል የምንኮራ ድሉ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ የሚከበርም የሚወደድ በዚህ እጅግ የምንከራ መሆናችን ይታወቃል፡፡ የአባይ ውሃ ሙሌት ጅማሮ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ደግሞ ለኔ ዳግማዊ የአድዋ ድል አድርጌ ነው የምወስደውና ኩራትና ክብር እንዲሰማኝ አድርጓል፡፡
ሀትሪክ፡-በጣም አመሰግናለሁ፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport