“የ2ዐዐ3ቱ የቡና ድል መቼም የማልደግመው ሁሌም የማነሳው ትልቁ ታሪኬ ነው”ሙሉአለም ጥላሁን

ጥርስ የማያስከድነው የሙሉአለም ጥላሁን አዝናኝ ቆይታ በቀጥታ ከጀርመን

“የ2ዐዐ3ቱ የቡና ድል መቼም የማልደግመው ሁሌም የማነሳው ትልቁ ታሪኬ ነው”

ብዙዎች ከተጫዋችነቱ ባልተናነሰ በቀልደኝነቱ ያውቁታል፤በኢት.ቡና እግር ኳስ ክለብ ውስጥም የራሳቸውን ደማቅ አሻራቸውን ካሳረፉ የ2003ቱ ባለታሪክ ተጫዋቾች አንዱ ነው፤ኢትዮጵያ
መድን፣ኢት.ቡና፣መከላከያ፣ወልዋሎና ወልዲያ የተጨዋቹ ጥበብና የግብ አሻራ ያረፈባቸው ክለቦች ናቸው፡፡ አሁን ኑሮውን በአውሮፓዊቷ ሀገር ጀርመን ካደረገ ጥቂት የማይባሉ አመታትን አስቆጥሯል፡፡
በቅርቡ ይህችን አለም የተቀላቀለውን ማህታን ሙሉአለም ጥላሁንን ጨምሮ ሁለት ልጆችን ከባለቤቱ ፀጋ አስራት ጣሴ ያገኘውና ፍፁም ደስተኛ ህወትን እየመራ እንደሆነ የሚናገረው የዛሬው
እንግዳችን የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡናው ስኬታማ ተጨዋች ሙሉአለም ጥላሁን ነው፤የሀትሪክ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ባልደረቦች ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴና ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ በስልክ ሞገድ አገር
አቋርጠው፣ባህር አሳብረው ወንዝና ድንብር ሳይገድባቸው በሳቅ ጀምረው በሳቅ የጨረሳቸውን ቃለ-ምልልስ ፍራንክፈርት እምብርት ላይ ከሚገኘው ሙለአለም ጥላሁን ጋር አድርገዋል፡፡
የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ኮሮና ቫይረስ ያመጣውን ድብርትና ጭንቀት በሚያባርርና ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ቃለ-ምልልሱን አቀናብሮት ከዚህ በታች አቅርቦልታል፤ወደ ቃለ-ምልልሱ ከመግባትዎ በፊት በደንብ ለመሳቅና ዘና ለማለት ይዘጋጁ፤መልካም ቆይታ፡፡

ሀትሪክ፡- …ሙሌ አንተ ጀርመን ብትሆንም ሀትሪክ የቦታ ርቀት ሳይገድባት ድንበር አቋርጣ ከአንባቢዎቿ ግር ልታገናኝህ መስመር ላይ ናት…?
ሙሉአለም፡- …ዋው!…በጣም ደስ ይላል…በጣምም ነው የማመሰግነው፤ አስታውሳችሁ ስለ ደወላችሁልኝና ከስፖ ርት ቤተሰቡ ጋር እንድገናኝ መድረኩን ስለፈጠራችሁልኝ…በዕውነት ከልቤ አመሰግናለሁ…፡፡
ሀትሪክ፡- …ሙሌ ከእግር ኳስ ችሎ ታው ባልተናነሰ በጣም ቀልደኛ…ጥርስ አይስከድኔ ተጫዋች ነው፤ የሁለት ሙያ (የተጨዋችነትና የኮሚዲ ሙያ) ባለቤትም ነው ይሉሃል…እውነት…ነው?
ሙሉአለም፡- …(በጣም ሳቅ)…እንደዛ ይላሉ…ግን…ከእኔ የባሱ ብዙ ቀልደኞች…ኮሚዲዎች አሉ…(ሣቅ)
ሀትሪክ፡- …አሁን የኮሮና ወረርሽኘ ሰውን ያስጨነቀበት ወቅቱ ስለሆነ ያለውን ድብርት ለማባረር አንባቢዎቻችንም የጠፋው ሣቃቸው እንዲመለስ…ዘና…ፈታ…የሚያደርግ ቆይታ ነው የምናደርገው ተዘጋጅተሃል…ሙሌ…?
ሙሉአለም፡- …ችግር የለም…ማዘናናት፣ማሳቅ…ከቻልኩኝ በጣም ደስተኛ ነኝ…ቀጥል…(ሣቅ)…
ሀትሪክ፡- …ከአንተ ጋር የሚኖረኝን ቆይታ የምጀምረው ከአንድ አስቂኝ ገጠመኝ ነው፤አንድ ጊዜ ግብፅ ለጨዋታ ሄዳችሁ ወደ ገበያ
(Shopping) ለመውጣት አስበህ…የቋንቋ ችግር ስላለና ሆቴሉ እንዳይጠፋብህ በማሰብ…ከሆቴላችሁ እስከ ገበያው ቦታ…ለምልክት በቾክ አስምረህ ሄደህ…በድንገት የዘነበው ዝናብ በቾክ ያሰመርከውን ምልክት
አጥፍቶብህ…ወደ ሆቴል ለመመለስ መከራህ አይተህ ነበር…በዚህም የተጨዋች መሳቂያ ሆነህ ነበር የሚል ነገር ሠማሁ…እውነት ነው…?
ሙሉአለም፡- …(በጣም ሳቅ)…የሚገርም ነው…እንደዚህ እያለ የሚያስ ወራብኝ ቢኒያም (ግስላ) ነው… (አሁንም ሳቅ)…እውነት ለመናገር እኔ እዚህ ደረጃ ላይ አልደረ ስኩም፤ እንደውም አንድ ነገር ልንገርህ
አብዛኛው ተጨዋች ገበያ የሚወጣው የእኔን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ተማምነው ነው።ይሄ አሁን የምትለው ነገር የደረሰው በእኔ ላይ ሣይሆን አንድ ስሙን በማልገልፅልህ ተጨዋች ላይ ነው፤ያ ተጨዋች የቋንቋ ችግር
ስላለበት፣የሆቴሉንም ስም ማንበብና መያዝ ስላልቻለ ማን ሞኝ አለ…?…ማን መሳቂያ ይሆናል…?…ብሎ ከሆቴሉ ጀምሮ ገበያ(Shopping) እስከወጣበት ድረስ…በቾክ እያሠመረ ቢሄድም…ሣይታሰብ
የመጣው ዝናብ…በቾክ ያሰመረውን አጥፍቶበት…በጣም ተሰቃይቶ…ሰዎች እንደምንም በምልክት ሆቴል አምጥተውት የተሳቀበት ጊዜ አለ…(በጣም ሳቅ)…እንጂ…እኔ ሙሌማ…!…በእንግሊዘኛ ቋንቋ የምታማ
አይደለሁም፤መናገሩን ተወው…ክለብ ውስጥ በእንግሊዘኛ ጥቅስ በመጥቀስ ሁሉ የምታወቅ ተጨዋች ነኝ…(በጣም ሳቅ)…

ሀትሪክ፡- …አንድ ጊዜ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና እያለህ ኮሞሮስ ለጨዋታ ሄደህ ከአንድ የሀገሪቱ ዜጋ ጋር ስትተዋወቅ ስምህን የገለፅክበት መንገድ ብዙዎችን አዝናንቷል…ታስታውሰዋለህ…?
ሙሉአለም፡- …ኡ…አቤት ወሬ…አቤት ቢኒያም(ግስላ)…(በጣም ሣቅ)…እሱ ነው ይሄን ሁሉ የሚያወራው…እንዳልኩህ ኮሮሞስ ለጨዋታ ሄደን ገበያ(Shopping)እንወጣለን…ሁሉም ተጨዋች በእኔ የቋንቋ ችሎታ
ስለሚተማመንና እኔ እንዳስተረጉምላቸው ስለሚፈልጉ ሁሉም ከበውኝ ነው የሚሄዱት… በኋላ ላይ ይሄን ኮሞሮሣዊ እናገኘውና እንተዋወቃለን…ስምህ ማነው…?…ስለው ነገረኝ…ቀጥሎ የአንተስ…?…ብሎ
ጠየቀኝ…(በጣም ሳቅ)…ሙሉአለም ስለው…ሊገባው አልቻለም…አስሬ…“What”…እያለ ይጠይቀኛል…መጨረሻ ላይ በእንግሊዝኛ ተርጉሜው ነግሬው…ለምን አልፋታውም…አልኩና ስሜ ሙሉአለም ነው ለማለት MY
Name is Full world ብዬው አረፍኩት… (በጣም ሳቅ)…Full ሙሉ…ለማለት ነው…world…ደግሞ…አለም…ለማለት ነው…Full world ሲገጣጠም ሙሉ አለም ይሆናል…ስለው…እሱ ሊገባው ነው ጭራሽ ግራ ተጋብቶ
ቁጭ…(በጣም ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …እዛው ኮሞሮስ ላይ እንዲህ በተመሳሳይ የእንግሊዝኛ ችሎታህን ያሳየህበት ሀገርህንም ያስተዋወቅክበት መንገድ ነበር አሉ…እሱንስ ታስታውሰዋለህ…?
ሙሉአለም፡- …(ያላባራ ሳቅ)……አቤት ወሬ…ይሄንንም ነግረውሃል…(ሳቅ)…ምን ሆነ መሠለህ…እዛው ኮሮሞስ አንድ በትውልድ ሞሮኮያዊ ሆና እዛው የምትኖር ልጅን…እናገኝና እንተዋወቃለን…ከተዋወቅን በኋላ
…ቅድምም ነግሬህ የለ…ተጨዋቾቹ በእኔ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ስለሚተማመኑ…(በጣም ሳቅ)…”ስለ ኢትዮጵያ በደንብ ንግራት…አስተዋውቃት ይሉኛል…(ሳቅ)እኔ የአንተ ወንድም…ደግሞ ለእንግሊዘኛ እልና…
ሀትሪክ፡- …ግን…ግን…እዚህ ጋር ላቋርጥህና…ይሄን ያህል እንግሊዘኛን አቀላጥፈህ ትናገራለህ ማለት ነው…?…ሁሉም አንተ ላይ እዳውን የጣለበት ነገር በጣም ገርሞኝ ነው…?
ሙሉአለም፡- …(በጣም እየሳቀ)…እንዴ…መጠርጠሩስ…በእንግሊዘኛ አልታማም (አሁንም ሣቅ)…እዚህ ደረጃ ለመድረስ…እንግሊዝኛን አቀላጥፌ ለመናገር ስንት እንደደከምኩ…ስንት መፅሐፍትን እንዳገላበጥኩ
እኔና እግዚአብሔር ብቻ ነን የምናውቀው…(አሁንም በጣም ሳቅ)…ኮሞሮስ ወደ አገኘሃት ሴት ልመልስህና…ጓደኞቼ እንደተማመኑብኝ ማሳለፈር የለብኝም አልኩኝና…ልጅቷን እንደ ምንም ብዬ በእንግሊዝኛ…“Do You
Remember Ethiopian Plane crash”…ስላት…ልጅቷ ምን ማለቱ ነው…?…ብላ በመገረም ፊቷን ጨምደድ አድርጋ “No…!…Idon’t Remember…” ስትለኝ ከዚህ በላይ ብዙ መግፋት
አልፈለኩም…ከዚያ አንቺማ እንዴት ታስታውሺዋለሽ አልኩና…ወዲያውኑ የወጋ ቢረሣ የተወጋ አይረሣም ብያት እረፍ…(በጣም ሣቅ)…

ሀትሪክ፡- …እንዴ በአማርኛ…?
ሙሉአለም፡- …ምንላድርግ…ታዲያ…(ሣቅ)…ፕሌናችን የተከሰከሰው እዛ…እንዴት አላስታውስም… ትለኛለች…?…(በጣም እየሳቀ)…በመልሷተ በሳጨሁ…የወጋ ቢረሣ የተወጋ አይረሣም…የሚለውን በእንግሊዘኛ
ለማለት ፈልጌ ከየት ላምጣው…(አሁንም በጣም ሣቅ)…በኋላ ላይ ሳጣራ ዲክሽነሪ ላይ ተረትም እንደ ስም የእንግሊዝኛ ትርጉም የለውም ለካ…(ያላባራ ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …ሙሌ በዋናነነት የተገናኘነው አንባቢዎቻችንን ከኮሮና ድብርት ለማላቀቅ…ዘና ፈታ ለማድረግ ነው…ስለዚህ አሁንም ከሚያዝናና ገጠመኝ አንወጣም…ሙሌ የቡና ተጨዋቾችን BBN፣ BBC፣ BBF በሚል
ደልደልሃቸዋል አሉ…እነዚህ ምህፃረ ቃሎች ትርጉማቸው ምንድን ነው…?
ሙሉአለም፡- …(በጣም እየሳቀ) ትክክል ነው BBN፣BBC እና BBF በማለት በሶስት ከፍያቸዋለሁ፤ BBN ማለት Beauty By Natuer ወይም የተፈጥሮ ቁንጅና ለማለት ነው…(ሣቅ)…BBC ደግሞ
Beauty By cosmetics ወይም በኮስሞቲክስ ቆንጆ ለመሆን የሚሞክሩ፣መስታወት ላይ የሚያፈጡ፣ ፀጉር ቤት ውለው የሚያድሩ ተጨዋቾች ያሉበት ነው፤ሌላው ደግሞ BBF…ነው…Beauty By Force
በጉልበት ቆንጆ እንሁን የሚሉ የተደለደሉበት ነው…(በጣም ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …እስቲ ከመጨረሻው BBF…ወይም…Beauty By Force…በግድ ቆንጆ እንሁን ያሉትስ እነማን የቡና ተጨዋቾች የተደለደሉበት ነው…?…(ሳቅ)…
ሙሉአለም፡- …(በጣም ሳቅ)…እዚህ ውስጥ እነ ታፈሰ ተስፋዬ ናቸው ያሉበት…(ያላባራ ሳቅ) በግድ ቆንጆ እንሁን ብለው የሚደክሙ…(ሣቅ)…፤…ታፈሰ ተስፋዬ፣ብላክ፣ቀስቴን የመሳሰሉ ናቸው…እነዚህ ደግሞ
በግድ ቆንጆ እንሁን ውስጥ ነው ያሉት…(በጣም ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …BBC…ወይም…Beauty By cosmotics ውስጥ እነማን ናቸው የተደለደሉት…?
ሙሉአለም፡- …(በጣም እየሳቀ)…BBC…ወይም…Beauty By cosmotics ውስጥ ያሉት…ገና ብቅ ያሉ ኳስ ተጨዋቾች ናቸው…ሀገር ልትጠፋ ነው ከሚለው ይልቅ የፀጉር ስታይላቸው፣የሚቀቡት ቅባት፣
የፐርሙ አይነት የሚያስጨንቃቸው ፍሪዝ፣ ፌዴ መቆረጥ እንቅልፍ የሚያሳጣቸው፣ከመስታወት ጋር በየሰዓቱ የሚፋጠጡ፣ለቅባት፣ለሽቶ፣ለዶዶራንት የሚጨነቁ የዘመኑ ተጨዋቾች የተካተቱበት ነው… (ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …አንተስ ራስህን የት ውስጥ ከተትከው…?…
ሙሉአለም፡- …(በጣም እየሳቀ)…ታሾፋለህ እንዴ…?…እኔማ BBN…Beauty by Natuer ውስጥ ነዋ …በተፈጥሮ ቆንጆ የሆኑት ውስጥ ነኛ…(በጣም ሳቅ)…ምን ይወጣልኛል….እዚህ ውስጥ እነ መስዑድን
የመሳሰሉ በተፈጥሮ ቆንጆ የሆኑ ተጨዋቾች የምንገኝበት ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …ዳዊት እስጢፋኖስን ረሳኸው መሰለኝ…እሱንስ የት ከተትከው…?
ሙሉአለም፡- …ምን እረሣዋለሁ…(በጣም ሳቅ)…እሱ እነ ታፈሰ ተስፋዬ ያሉበት ምድብ BBF…ወይም…Beauty By Force …በጉልበት ቆንጆ ውስጥ ነው…(በጣም እየሳቀ)…ዳዊት ስለቀላ ነው እንጂ ከእነ
ታፈሰ በምን ይለያል?…(ያለባራ ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …ግን ሙሌ ከዚህ ከቋንቋ ጋር በተያያዘ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ…እንግሊዝኛ ማወቅ ብቻውን መግባቢያ እንጂ እውቀት ነው ባልልም ብዙውን ጊዜ እናንተ ተጨዋች እንግሊዝኛ እንደ ቁምጣ ሲያጥራችሁ…ለመናገር
መከራችሁን ስታዩ ይታያል…የዚህን ምክንያት ምንድነው ማለት እንችላለን…?
ሙሉአለም፡- …እኔ እንኳን…ከዚህ አውጣኝ…(በጣም እየሳቀ)…
ሀትሪክ፡- …ማለት ጀርመን ከመጣህ በኋላ ማለትህ ነው…?…እኔ ግን የጠየኩህ እዚህ የነበርክበትን ጊዜ ነው…?
ሙሉአለም፡- …ሀገር ቤት እያለሁ እሻል ነበር… ጀርመን ከመጣሁ በኋላ እንደውም በጣም ጠፈቶብኛል…(በጣም ሣቅ)…እንግሊዝኛ እንደ ቁምጣ ያጥራችሃል ላልከው…ጥረት ነዋ…!…ጥረት አያደርጉም፤ተጨዋች
ሆኜ ላፕቶፕ የነበረኘ ብቸኛ ሰው እኮ እኔ ነበርኩ…(ከት ብሎ እየሳቀ)…አሁን ጣቴን ፎቶ አንስቼ ብልክልህ ከላፕቶፕ ጋር የነበረኝን የጠበቀ ግንኙነት በደንብ ያሳይሃል…(ሣቅ)…እኔ ነገን አስብ ነበር…ፕሮፌሽናል የምሆን
መስሎኝ…ቋንቋ ላይ ትኩረት አደርግ ነበር….የቋንቋ ትምህርትም ተምሬያለሁ…እንዳልኩህ ብዙ መጽሐፍትንም አገላብጬያለሁ…(በጣም ሣቅ)…

ሀትሪክ፡- …ኧረ ሙሌ…በቃህ…የምር አደረከው እንዴ…?…ነገሩን አከረርከው እኮ…በቋንቋ ከሚታሙት እኮ አንዱ አንተ ነህ…?
ሙሉአለም፡- …(ከት ብሎ እየሳቀ)…ስም አጥፊዎች በላቸው…ስንቱን ተጨዋች ከቋንቋ ችግር እስር ቤት ነፃ ያወጣሁት እኔ ነኝ…(በጣም እየሳቀ)…
ሀትሪክ፡- …ቡና እያለህ አንተንስ የሚተርብህ…የሚፎግርህ ማን ነበር..?
ሙሉአለም፡- …ማን ከማን ብዬ ልጥራልህ…ሁለም ይፎግሩኛል…ሁሉም የሚረባረበው እኔ ላይ ነው…(ሣቅ)…፡፡
ሀትሪክ፡- …ሙሌ ይሄን ያህል ዘና ካረከን ይበቃል…አሁን ኮስተር ወደአለ ጥያቄ እናምራ…ለመድን ከተጫወትክ በኋላ…ቡና የገባኸው ብቻ ሣይሆን ሙሉአለም የሚለው ስምም የታወቀው ኢትዮጵያ ቡና ከገባህ በኋላ ነው፤
ከዚህ በተጨማሪም ቡና በገባህበት አመት በክለቡ ደማቅ ታሪክ ካፃፉ ተጨዋቾች መካከልም አንዱ ሆነህበታልና 2003ትን እንዴት ነው የምታስታውሰው…?
ሙሉአለም፡-የቡና ታሪክ በእግር ኳስ ዘመኔ ካገኘሃቸው ሁሉ የላቀው የምኮራበት…ወደፊትም ለልጆቼ የምነግራቸው ትልቁ ታሪኬ ነው፤የምር ቡናን እየደገፍኩ ነው ያደኩት፤ቡናን እየደገፈ ላደገ ህልሙ ተሳክቶለት
ክለቡን ተቀላቅሎ ደማቅ ታሪክ የሚያፅፋበት የታሪክ አጋጣሚ ማግኘት ማለት ደግሞ የበለጠ እንድትደሰት ያደርጋል፡፡ቡና የ2003ቱን ድል ሲቀዳጅ የታሪኩ አካል ስለበርኩ የራሴ የሆነን አሻራ እንዳሳረፍኩ ይሰማኛል፤በዚህም
በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ለቡድኑ ስኬታማነት ጥሩ ተንቀሳቅሻለሁ…ወደ 13 አካባቢ የሚሆኑ ግቦችንም አስቆጥሬያለሁ…ፔናሊቲ በተደጋጋሚ ምክንያት ሆኜ አስገኝቼያሁ፤ ተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ በጉዳት ምክያት ባልሰለፍም
ቡደኑ ያንን ተሪክ በደማቅ እንዲያፅፍ ትንሽም ብትሆን አስተዋፅኦ አለኝ፤በአጠቃላይ ግን እስከአሁን በጣም የምኮራበትን ራሴንም በደብ ያስተዋወቁበት ቤቴ ነው፤እንደውም የቡና ደጋፊ “ቡና ታሪኬ ነው” እያሉ
የሚዘምሩት ሁሉ ለእኔ ነው የሚመስለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …በወቅቱ የነበረውን ስብስብ ግልፅልኝ ብልህ እንዴት ነው የምትገልፀው…?
ሙሉአለም፡- …በጣም የሚገርም ስብስብ ነበር…መግባባት የምንችል…በጣም ጥሩ እድሜ ላይ የምንገኝ ተጨዋቾች የተሰባሰብንበት ቡደን ነበር፤ከስብስቡ ምርጥነት በተጨማሪ የእድሉ ደረጃ (በዴክሶ) አሪፍ
አምበል መሆን ስብስቡን የበለጠ ምርጥና ታሪክ ሠሪ እንዲሆን አድርጎታል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለይ የመጨረሻ ጨዋታ አካባቢ ይሰጠን የነበረው ትዕዛዝ እንደ አምበል ሣይሆን እንደ አሰልጣኝ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ የእድሉን
ሚና ብዙ ጊዜ አነሣዋለሁ…በጣም ይመራን ነበር፡፡ በከፍተኛ የራስ መተማመን ወደ መዝናናቱ የማምራት ነገር ነበረብን…እድሉ ግን እየደወለ ካምፕ እያስገባ…ራሳችጣን ጠብቀን ስኬታማ እንድንሆን በጣም አግዞን ነበር፡፡
በተለይ ከእኔ ጋር በጣም ጥሩ ግንኙነት ነበረን…እኔ ጋር ደውሎ ካምፕ ይዞኝ ይገባል…ከአንድ አድናቂዬ በግል ሽልማት ሁሉ እንዳገኝ አድርጎኛል፡፡ የነበረው ነገር በጣም ጥሩ ነበር…እንደ ስብስብ ምርጥ ብቻ ነበረን
ሣይሆን…ጥሩ እግር ኳስ ተጫውተን…ጥሩ ስኬትም አስመዝግበናል፡፡


ሀትሪክ፡-በ2003 ቡና የሊጉ ሻምፒዮን ከሆነ በኋላ የነበረው ድባብና በተለይ የደጋፊው ሁኔታ ፍፁም ልዩ ነበር፤ደስታና ፈንጠዝያውን ለተመለከተ ሀገሪቱ ለአለም ዋንጫ ያለፈች ይመስል ነበር…ይሄንንስ ታስታውሳለህ?
ሙሉአለም፡- …ኡ…በጣም ልዩ ነበር…የተሻለ ነገር ወደፊት ሊመጣ እንደሚችል እገምታለሁ…በእኔ የግል እምነት ግን የነበረው ሁኔታ ዳግም የሚመለስ ሁሉ አይመስለኝም፤መቼም የማይዘነጋ ታሪክ ነው ያየነው፡፡ የቡና
ደጋፊ እንኳን ትልቁን ድል አግኝቶ በማንኛውም ጨዋታ በጣም የተለየ ነው… የሚገርምህ ነገር በደጋፊ ታጅቤ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ እየተዘመረ መጫወትን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ቡና ስገባ ነው፤የዚህ አይነት ታሪክ ለሌለው
ለእንደ አኔ አይነቱ ተጨዋች አመት ሙሉ በዚህ ደጋፊ መሃል ተጫውቶ ማሳለፍ መታደል ብቻ ሣይሆን መቼም የምትረሣው አይደለም፤የደጋፊው አደጋገፍ ዛሬም ድረስ የማስታውሰው…ከውስጤ የማይጠፋ ነው…በተለይ
ከደደቢት ጋር ስንጫወት የነበረውን …የደጋፊውን ሁኔታ ሳስታውስ ልክ ዛሬ የሆነ ያህል ነው የሚሰማኝ…ደጋፊው መደገፍ ብቻ ሣይሆን እውቀትም ያለው ደጋፊ እንደሆነ ያየሁበት ነው…
ሀትሪክ፡-…እንዴት…ማለት…?
ሙሉአለም፡- …ደደቢቶች በጌታነህ ከበደ ጎል አግብተውብን…ደጋፊው ከመደንገጥና ከመረበሽ ይልቅ በጣም ይዘምር ነበር፤ይሄ ድጋፋቸው ለእኔ ድጋፍ ብቻ አይደለም…ቢገባብንም መልሰን እንደምናገባ… በድጋፋቸው
የነገሩን እነዚህ ደጋፊዎቻችን ናቸው፤እኛ አይደለንም ደጋፊዎቻችንን እናሸንፍላችኃለን ያልናቸው፤እነሱ ናቸው በድጋፋቸው አግብተን እንደምናሸንፋቸው የገለፁልን፡፡ደደቢቶች አግብተውብን አደጋገፋቸውና አጨፋፈራቸው ሲታይ
የገባብን ሣይሆን ያገባን ነበር የሚመስለው፤የደጋፊው አደጋገፍ ፍፁም ልዩ ነበር፤በተለይ ለእኔ በጣም የተለዩ ናቸው፡፡በየቦታው ድንኳን እየጣሉ…እየሸለሙኝ አሣልፌያለሁ፤ከደጋፊው በጣም ብዙ ገንዘብ ተሸልሜያለሁ…እኔ
የምናፍቀው እንደዚህ አይነቱን ቡና ነው፤አንዳንዴ እንደውም ይሄ ደጋፊ ደጋግሞ ዋንጫ ቢወስድ ያንስበታል እላለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ሙሉአለም ብዙ ሲጠበቅ በአጭር ጊዜ ታይቶ በአጭር ጊዜ ነው የጠፋው የሚሉ አሉ፤ ሙሌ የጨዋታ ማቆሚያ ጊዜህ ደርሶ ነው ከእግር ኳስ የራከው…?
ሙሉአለም፡- …በፍፁም!…ሣይደርስ ነው የራኩት…እንደውም በጣም አሪፍ የምጫወትበት ጊዜ ላይ ነው ራቅ ያልኩት፤አሁን በደንብ የበሰልኩበት፣የምሰራውን በደንብ የማውቅበት፣የማገናዝብበት፣በእውቀት
የምንቀሳቀስበት ጊዜ ላይ ነው ሸሸት ያልኩት፤ቤተሰብ የመምራት ኃላፊነትን መሸከም የቻልኩበት በአጠቃላይ ኳስን በደንብ…በእውቀት የምጫወትበት ጊዜ እንጂ የማቆምበት አይደለም፡፡
ሀትሪክ፡- …ታዲያ ለምን ከኳስ ለመራቅ ወሰንክ…?
ሙሉአለም፡-..በቃ በኳሱ ላይ በማየው ነገር እየተሰላቸሁ መጣሁ፤ከመድን ጀምሮ ኢት.ቡና፣መከላከያና ሌሎች ክለቦች ውስጥ ጥሩ የጨዋታ ጊዜዎችን አሳልፌያለሁ፡፡ ግን የሆነ ሰዓት ላይ ይመስለኛል የእግር ኳሱ
ስሜት እየተቀየረ መጣ፤ የክልል ክለቦች እየበዙ መምጣታቸውን ባልቃወምም እነሱ እየበዙ ሲመጡ በፊት የነበረው ስሜት እየጠፋ የመጣ ይመስለኛል…ነገሮች እየተቀየሩ በመምጣታቸው እግር ኳስን እንደፈለከው
እንድትጫወትበት የምትችልበት ሁኔታ አልተፈጠረም፤በተለይ ወደ ክልል ለጨዋታ ስትሄድ አሸንፈህ እንደምትመጣ ሣይሆን ተሸንፈህ እንድትመጣ ውስጥህ እያሰበ ነው ለጨዋታ የምትሄደው…የሚሆነውን ታውቀዋለህ፤
አንዳንዴ እንደውም ምን እንደምል ታውቃለህ?


ሀትሪክ፡- …ምን ትላለህ…?
ሙሉአለም፡- …ይሄ ሁሉ ወጪ ለምን ይወጣል…?…ብዬ እንዳስብ ሁሉ ያደርገኛል፤ ስልጠናዎች ተለዩ፣የአሰልጣኞች ፍርሃት እየበዛ መጣ፣ጨዋታዎች በ1ለ0 እንዲገደቡ በፍርሃት ተገደዱ፣መከላከል ላይ ያተከሩ
ጨዋታዎችም በጣም ብዙ፣ረዥም ኳስ በዛ፣በቃ ምን ልበልህ እግር ኳስ ጨዋታ አልመስል ሁሉ አለ…በወቅቱ ጨዋታ ሊናፍቅህ ሲገባ…ከጨዋታ ይልቅ ትሬይኒንግ መስራት ይናፍቀን ጀመር፤ ምርጥ ትሬይኒንግ ሠርተን የሜዳ
ላይ ጨዋታችን ከሠራነው ጋር አይገናኝም፤በቃ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ተደምረው የመሰላቸት ስሜት ውስጥ አስገባኝ…በቃ ተሰላቸሁ…መጨረሻ ላይ ሸሸሁ፡፡
ሀትሪክ፡-…በዚህ በተፈጠረብህ የመሰላቸት ስሜት…ከዚህ በኃላ በቃ ጫማ ሰቅለሃል ብሎ መናገር ይቻላል…?
ሙሉአለም፡- …እውነት ለመናገር ገና የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አልደረስኩም…፤…የነበረው እግር ኳስ መልኩን በመቀየሩ ነው ወደ ትዳር የገባሁት…ሀገር ጥዬም የሄድኩት…መሰላቸት እንጂ የማቆም ሃሣቡ
አልነበረኝም፤ውሳኔዬን መልሼ እያየሁት ነው…በቀጣይ የሚሆነውን እናያለን፡፡
ሀትሪክ፡- ለትልቅ ቡድን እንደመጫወትህ…ከቡና ጋር ትልቅ ታሪክ እንዳለው…እንዲሁም የብቃትህን ያህል…ለብ/ቡድን ስትጠራና በቋሚነት ስትጫወት አልታየህም…ሀገርህን ያለማገልገልህ ችግር የአንተ ወይስ
የአሰልጣኞች…?
ሙሉአለም፡- …እውነት ለመናገር ከአንድም ሶስቴ ለብ/ቡድን ተጠርቼ ተመልሼያለሁ…፤…በጉዳት ምክንያት የታሰበውን ያህል አላገልገል እንጂ መከላከያ እያለሁ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከአራት ጊዜ በላይ
ጠርቶኛል…ዮሐንስ ሳህሌ አጨዋወቴን በጣም ይወደዋል፤ሀገርን ማገልገል የምችልበት አቅም እንዳለኝም ይናገር ነበር፡፡ ግን ነገሩ እንዳልከው ነው እመረጣለሁ ደግሞ ወዲያው እመለሳለሁ፤ የዚህን ምክንያት በሀለት ክፍዬ
ማስቀመጥ ነው የምመርጠው…እኔ በምጫወትበት ቦታ አሰልጣኞች የሚፈልጓቸው ምርጥ ምርጥ ተጨዋቾች ነበሩ፤እነ ጌታነህ ከበደ፣አዳነ ግርማ ወደ አጥቂነት የተመለሰበት ጊዜ ነበር፣እነ ሳላህዲን ሰይድ፣ዑመድ ኡኩሪን
የመሳሰሉ ምርጥ ምርጥ ተጨዋች ነበሩ፤ የእነሱ መኖር የሸፈነኝ ይመስለኛል፤ሌላው አሰልጣኞች ለአጨዋወቴ የሚመች ተጨዋች የሚሉት ነገር እድሉን እንዳጣ ያደረገኝ ይመስለኛል፤አሁን ላይ ቢሆን ምናልባት ነገሮች
ተለውጠው ልናይ የምንችልበት ዕድል ሊኖር ይችል ነበር…የሚል ግምት አለኝ…
ሀትሪክ፡- …ማለት…?
ሙሉአለም፡- …ለምሣሌ የአሁኑ የብ/ቡድን አሰልጣኝ በፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ጎል አግቢ የሆነውን ሙጂብ ቃሲምን አልመረጠውም፤ለአጨዋወቴ ይመቻል…አይመችም…?…የሚለውን እንጂ ጎል ማግባቱን
አላየውም…አሰልጣኙ…፤…በዛ ወቅት እንደዚህ አይነት ውሳኔ የሚወስኑ አሰልጣኞች አልነበሩም፤ሁሉም ሲመርጡ መስፈርታቸው ጎል አግቢ ነው፤የፈለገ ቢመጣ ግብ አግቢ የሆነን ተጨዋች አይዘሉም፡፡ እንደውም እከሌ
ይሄን አግብቷል፣እከሌ በዚህ ያንሣል ላይ ነው የሚያተኩሩት፤ ይሄ ይመስለኛል ብዙ እንዳልመረጥ ያደረገኝ፤ከዚህ ሌላ እንግዲህ አሰልጣኞቹ ያዩብኝ ደካማ ነገር ይኖራል፡፡
ሀትሪክ፡- …ከማን ጋር ስትጫወት ጨዋታ ይቀልሃል…?…ወይም ይመችሃል?
ሙሉአለም፡- …እከሌ ብዬ ለይቼ የምጠራው ተጨዋች የለም…ከሚድፊልዶች ጋር በዚያ ተግባብቼ ነው የምጫወተው፤መድን እያለሁ ከእነ ታደለ መንገሻ፣ሚካኤል (ጣሊያን) ጋር በጣም ተግባብቼ በመጫወት ነው
ያሳለፍኩት፤ወደ ቡና ስመጣም እንዲሁ ከመስዑድና ከዳዊት እስጢፋኖስ ጋርም በጣም ተግባብቼ ነው ያሳለፍኩት እንጂ…አንድ ሰው ነጥዬ…ለጎል የሚሆን ኳስ ይሰጠኝ ነበር ብዬ የምጠራው የለም…፡፡
ሀትሪክ፡- …አንተ ተግባብቼ እጫወት ነበር ትላለህ እንጂ ጥቂቶች ቢሆኑም ሙሌ አንድ ሁለት ተቀባብሎ ከመሄድ ይልቅ ለብቻው ኳስ ይዞ በጉልብቱ ጥሶ መሄድንና ጎል ማግባትን ነው የሚመርጠው ብለው የሚያሙህ
አሉ…ሀሜቱን ትቀበላለለህ…?
ሙሉአለም፡- …በፍፁም አልቀበልም…!…እንደዚህ የሚሉ ሰዎች ስታዲየም ገብተው የማያውቁ ሰዎች ናቸው፤ምክንያቱም ገብተው ቢያውቁ ኖሮ እንደዚህ አይነት ስህተት አይሳሳቱም ነበር፤ ምናልባት
ከተከላካዮች ጋር ስታገል አይተውኝ ያቺን መዘው ከሆነ አላውቅም፤ እኔ እንደውም አንድ ነገር ልንገርህ ከሚስቴና ከልጆቼ ቀጥሎ የምወደው ነገር ቢኖር ደብል ፓላስ ነው፤ ደብል ፓስን ከመውደዴ የተነሣ እግዚአብሔርን ካልፈራሁ አንድ ሁለት
እየተቀባበልኩ በደብል ፓስ ጅማ ድረስ ሁሉ ልሄድ እችላለሁ …(በጣም ሳቅ)…


ሀትሪክ፡- …ብዙ ጊዜ ፔናሊቲ ቦክስ ውስጥ ጥፋት እየተሰራብህ አትወድቅም…በዚህ የተነሣም መድንና ኢትዮጵያ ቡና ማግኘት የሚገባቸውን ፔናሊቲ አሳጥተሃቸው የሚሉህ አሉ…?
ሙሉአለም፡- …(በጣም ሳቅ)… አንድ የማልክደው ነገር ብልጠት ላይ ብልጥ አልነበርኩም፤የምር ፋውል ሲሰራብኝም ሣይሰራብኝም ዳኛ ለማታለል ብዬ መውደቅን አላስብም፤የሆነ የትምክህት ባህሪ ነገር ነበረብኝ…(ሣቅ)…በዚህማ እንዴት ተገፍቼ እወድቃለሁ
አይነት…ግን ደግሞ ፔናሊቲ ውስጥ በትክክል ወድቄ ፔናሊቲ ያስገኘሁበት ጊዜም ብዙ አለ፤ያላስገኘሁበት ጊዜም እንደዛው፡፡ የሚገርምህ ነገር ከድሮ ጀምሮ የተከላካይ ዱላ እያረፈብኝ…ግን የዳኛ ከለላ የሌለኝ ብቸኛ ተጨዋች እኔ ነኝ፤እግሬን ስታየው ዘጠኝ ቦታ ተፈነካክቷል፤የጨዋታ
ዘመኔን ፎቶ ለባለቤቴ ሣሣያት ተጠበብሶ፣ተቦዳድሶ አይታ በጣም ደንግጣለች፡፡
ሀትሪክ፡- …ለአንተ ምርጡ አሰልጣኝ ማነው?
ሙሉአለም፡- …ገ/መድህን ኃይሌ ነው፤መድን እያለሁ ስዩም አባተ (ነፍሱን ይማረው) ወደ ዋናው ቡድን ቢያሳድገኝም ገ/መድህን ኃይሌ አቅሜን አይቶ የመሰለፍ እድል አየሰጠ የሆነ ቦታ ደርሼ ለማየት ይታገል ነበር፤የእውነት ደግሞ በስልጠና ዘመኔ
በስብዕናው፣በሙያው ስኬታማ የሆነ አሰልጣኝ ያየሁት እሱን ነው፤ተጨዋች አቅሙን አውጦቶ እንዲጫወት የሚያደርግ ትልቅ አቅም አለው፡፡ ጥሩ አሰልጣኝ መሆኑን የሚገነባቸውን ቡድኖችን…በመከላከያ በተደጋጋሚ በጥሎ ማለፍ ስኬታማ ሆኗል በጅማ፣ በመቐለ 70
እንደርታ የሠራቸው ስራዎች ስለ እሱ ያወራሉ፡፡
ሀትሪክ፡- መሉአለም ወደ ቢዝነሱ ጎራ እያለ ነው…?
ሙሉአለም፡- …አዎን እየተንቀሳቀስኩ ነው፤የጀርመን ምርቶች ብቻ የሚሸጡበት የስፖርት ትጥቅ መሸጫ ቤት ቦሌ መድሃኒአለም ጋር አለኝ፡፡ ብዙ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከእኔ ተጠቃሚ ሆነዋል ሌሎች ተጨማሪ የቢዝነስ ስራዎችንም የመስራት ሃሣቡ አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …ጀርመን ካሉ የቀደሞ ተጨዋቾች ጋር የምትገናኙበት አጋጣሚስ አለ…?
ሙሉአለም፡- …አዎን…አለ…!…በጣም ጥሩ ግንኙነትም አለን፤ ከትልቁ ብጀምርልህ ከግርማ አብርሃ የቀድሞ የህንፃ፣የመቻል፣የኢት.ብ/ቡድን ተጨዋች እንዲሁም የኤርትራ ብ/ቡድንን ያሰለጠነ፣ዳንኤል (ቦርጬ)፣ዳንኤል አስገዶም (መድን የነበሩ)፣ዘውዱ
መድንና ቡና የነበረ፣ደቡብ ፖሊስና አዳማ የተጫወተው አማኑኤል፣ሙሉጌታ ከሚባሉ ተጨዋቾች ጋር እንገናኛለን፤እርስ በእርስ ካልተከባበርን ካልተቀራረብን አይሆንም በሚል እየተገናኘን እንጫወታለን፡፡
ሀትሪክ፡- እንደዚህ በቋንቋ ችግር የምታማው የቀድሞ የክለባችሁ ተጨዋች ቢኒያም (ግስላ) አሁን አሜሪካ ነው ያለውና ያ የቋንቋ ችግር ታሪክ ሆኖ የቀረ…፤…እንግሊዝኛንም አቀላጥፎ የሚናገር አይመስልህም… ?
ሙሉአለም፡- …(በጣም እየሳቀ)…ምንድነው የምታወራው…አሁንም አኔ ነኝ …ጀርመን ሆኜ አሜሪካ ድረስ የማስተረጉምለት…(በጣም ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …ይሄን ያህል…?
ሙሉአለም፡- …ቢኒያም እኮ የተለየ ሰው ነው…ቤተሰቦቹ እንዳይቆጡት “እርሳስ ገንፍሎብኝ ነው” ያለ ሰው እኮ ነው ቢኒ…(በጣም ሳቅ)…ቢኒያም(ግስላ)…እኔ ባልኖርለትና ከጀርመን ባላስተረጉምለት ኖሮ
በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንደተሰቃየ ነበር የሚኖረው…(አሁንም ሳቅ)…የቢኒ ነገር አያልቅም…አሜሪካ ገብቶም ይሄ የቋንቋ ችግር ስቃዩን አብልቶታል…አሜሪካንም ሆነ ውጪ ሀገር…ልጆች አባታቸውን ማንኛውንም ነገር
ይጠይቃሉ…እንደ እኔ ተምረህ ተዘጋጅተህ ካልጠበቅ…Dad…ይሄ ምንድነው?…ምን ማለት ነው? እያሉ ስቃይህን ነው የሚያበሉህ…እንደ እኔ ካልቻልክ መፋጠጥ ነው…(በጣም ሳቅ)… ቢኒያም እንደ እድል ሆኖ ይሄ
ችግር አሜሪካ ድረስ ተከትሎት ሄዶ ፈተናውን አይቷል…(በጣም ሳቅ)… ልጁ “በእንግሊዝኛ…Dad…ይሄ ምንድነው?” ሲለው ቢኒ ምን ይመልስ…ፍጥጥ፤ልጁ የአባቱን ችግር አይቶ ቢተወው ምን አለበት…ይበልጥ እልህ
የያዘው ይመስል ደግሞ ደጋሞ Dad ይሄ ምንድ ነው?” እያለ ይወጥረዋል…ይሄንን የታዘበችውና የቢኒን ችግር የምታውቀው ባለቤቱ ከእኔ ጋር አብራ ስለተማረች የእንግሊዝኛ ብቃቴን ታውቀዋለች…(በጣም ሣቅ)…መሃል
ትገባና ልጇን “ቤቢዬ ለምንድነው አባትህን በጥያቄ የምታስጨነቀው?…ተወው በቃ” ስትለው ቢኒ ተገላገልኩ እፎይ ከማለት ይልቅ ምን ቢላት ጥሩ ነው?…ለጥያቄው መልስ እንደሚመልስ ሰው “ተይው እንጂ ልጅ
እኮ ነው የሚፈልገውን ነገር ይጠይቀኝ”…ብሎ የመለሰ ደፋር ሰው ነው…(በጣም ሳቅ)…እኔ ግን የቢኒን ችግር ስለማውቅ አላሳፍረውም ከጀርመን አሜሪካ ድረስ አስተረጉምለታለሁ…(ያላባራ ሳቅ)…
ሀትሪክ፡-ምግብ ላይ በጣም ደፋር ነው አይምርም ይሉሃል…?

ሙሉአለም፡- …መቼ ነው…?…አሁን ከሆነ ስህተት ነው…ምክንያቱም እድሜ ለባለቤቴ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረኩ ነው፤ሰውነቴን ብታየው በጣም ቀንሻለሁ፤ እንደውም አሁን ነው መጫወት ያለብህ ልትለኝ
ትችላለህ፤በፊት ግን አልዋሸህም ምግብ ላይ ቀልድ አላውቅም ያገኘሁትን ነው ጠርጌ የምበላው፤ ሂሊኮፕተር ላይ ሳይቀር ድግስ ተደግሷል ብባል በምን እንደ ምንደርስበት ባላውቅም ለምግብ ብዬ መሄዴ ግን
አይቀርም፤አሁን ግን ላይፍ ስታይሌን…አመጋገቤን…እድሜ ለባለቤቴ ቀይሬያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ህይወት በጀርመን ምን ይመ ስላል?
ሙሉአለም፡- …ህይወት በጀርመን በጣም አሪፊ ነው፤ ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር በጣም ደስተኛ ህይወትን እያጣጣምኩ ነው፡፡


ሀትሪክ፡- …በቅርቡ ሁለተኛ ልጅ ማግኘትህን ሠምቻለሁ፤ከዚያ በፊት ግን እስቲ ባለቤትህን አስተዋውቀኝ…?
ሙሉአለም፡- …ባለቤቴ ፀጋ አስራት ጣሴ ትባላለች፤ ግንኙነታችን በጓደኛዋ አማካይነት ተጀምሮ ዛሬ ጀርመን ውስጥ በአንድ ጣሪያ ስር ጣፋጭ ፍቅር እየኮሞኮምን እንድንኖር አድርጎናል፤ያው እኔ ከላይ እንዳልኩህ
BBN ወይም Beauty By Natuer የተፈጥሮ ውበት ነው ያለኝ ከዚህ አንፃር መልከ መልካም ባል ነው ያገኘቸው (በጣም ሳቅ) ከባለቤቴ ጋር ከመጋባታችን በፊት መጀመሪያ ፎቶዬን ነበር ያየችው በአካል ስንገናኛ
በፎቶ ሸውዶኛል አለች (በጣም ያላባራ ሣቅ)…ከባለቤቴ ጋር የዛሬ 6 አመት አካባቢ ተዋውቀን…ሽማግሌ ልኬ፣በሠርግ ተጋብተን እየኖርን ነው፤በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡ ከባለቤቴ ሁለት ወንድ ልጆችን አግኝቻለሁ፤የመጀመሪያ
ልጅ 4 አመት አካባቢ ሞልቶቷል፤ሁለተኛው በቅርቡ ነው የተወለደው…ማህታን ሙሉአለም ጥላሁን ይባላል፤ማህታን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሲሆን የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው፡፡
ሀትሪክ፡-አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ቡና እያለ ዳዊት እስጢፋኖስን አንድ የምትናገረው ነገር ነበር አሉ፤ ዳፉን ተመልከተው የሚል…ለምንድነው እንደዛ የምትለው?
ሙሉአለም፡-…(በጣም ሣቅ)…ምንድነው መሠለህ ዳዊት እስጢፋኖስ ሁሌም በተመሳሳይ ደቂቃ ነው ተቀይሮ የሚወጣው፤ዳዊት ጥሩ ይሁን አይሁን ያቺ ደቂቃ ስትደርስ ተቀይሮ ይወጣ ነበር፤አንዴ የጦፈ ጨዋታ
ውስጥ ሆነን ዳዊትም ጥሩ ስለነበር ያቺን ሰዓት ረስቷት በስሜት ይጫወታል መጨረሻ ላይ ሰዓቷ ስትደርስ አጠገቡ ሄድኩና “ዳዋ…ዳፉን (ሰዓቱን) ተመልከተው አልኩት፤እንዳልኩትም ሰዓቱ ደርሶ ተቀይሮ ወጣ፤ከዳዊት
ጋር…በተያያዘ አንዴ ምን ሆነ መሠለህ…
ሀትሪክ፡- …ምን ተፈጠረ…?
ሙሉአለም፡- …አሁንም አሰልጣኝ ፀጋዬ ነው…በአንድ ጨዋታ ላይ ጥሩ እየተጫወትኩ…እንዴትና ስንት ማግባት አለብኝ እያልኩ ራሴን እያነሰሳሁ ጥሩ ስሜት ላይ እያለሁ…ምክንያቱን በማላውቀው ሁኔታ ሙሉአለም
አሁን ታርፋለህ አለኝ…በጣም ተናደደኩ ጫማዬን አውላልቄ መሬቱን በጫማ ነረትኩት…ብቻ ምን አለፋህ በጣም ተበሳጨሁ…የዚያን ጊዜ ዳዊት ወደ እኔ መጥቶ “ሙሌ አይዞህ ጥሩ ነው የተጫወትከው…ዋናው ጥሩ
መጫወትህ ነው ተረጋጋ ደግሞ እንደዚህ አይደረግም…ጫማህን አውልቀህ መሬት መደብደብህ ልክ አይደለም” ብሎ መክሮኝኝ ወደ ሜዳ ገባ፡፡ እኔም በጣም ስለተበሳጨሁ ወደ ሻወር ቤት ሣልገባ እዛው ተቀምጬ
ቀረሁ፤ለካ ያቺ ዳዊት የሚቀየርባት ሰዓት ደርሳ ነበር…ዳዊት ተቀይሮ ሲወጣ መሬቱ፣ብረቱ አልቀረው ያገኘውን ሁሉ እየጠለዘ መጣ መጀመሪያ መክሮኝ አልነበር…እኔም በተራዬ እንዴ ዳዊት እንደዚህ አይደረግም እኔን
ስትመክረኝ አልነበረም…?…ስለው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው“ባክህ ምክር አንዳንዴ ለራስ አይሠራም” …(በጣም ሳቅ)…ብሎኝ መካሪና ተመካሪ አብረን ሻወር የወሰድንበት ጊዜ አይረሣም፡፡


ሀትሪክ፡- አንዴ ከቲፒ ማዜምቤ ጋር ስትጫወቱ ማልያ ወርውረሃል በሚል ከደጋፊው ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶብሀ ነበር…ለምን ያንን አደረክ?
ሙሉዓለም፡- …እውነት ለመናገር አልወረወርኩም፤ሲደርስብኝ በነበረው ተቃውሞ በጣም ተበሳጭቼ ማልያውን አውልቄ ያዝኩ እንጂ አልወረወርኩም፤ብዙ ደጋፊዎች ግን የወረወርኩ ነው የመሰላቸው፡፡ከ2005
መጀመሪያ ጀምሮ የማላውቀው ተቃውሞ ይደርስብኝ ነበር ፤በአሰልጣኝ ፀጋዬ ጊዜ ብዙ ጨዋታ አልተሰለፍኩም…ቤንች ነበርኩ፤ፀጋዬ ለስልጠና ወደ ሀንጋሪ ከመሄዱ በፊት ምስጋና ለይስሀቅ ሽፈራው (ፊዚዮቴራፔስት)
ይሁንና እሱ አስታርቆን ሊሄድ ሲል አንድ ጨዋታ ተሰለፍኩ፤ፀጋዬ ሀንጋሪ ሲሄድ ካሊድና ፊቱሼ ቡድን ይዘው ነበርና የመሰለፍ ዕድል ሰጡኝ፤የሚገርምህ በ11 ጨዋታ ስምንት ጎል አስቆጥሬያለሁ፡፡ ጥሩ እየተጫወትኩ ግብ
እያስቆጠርኩ በሚገርም ሁኔታ አንዳንድ ሚዲያ ላይ ትችት ቢሆን ጥሩ ግን ስድብ ሁሉ ይወርድብኝ ነበር፤ በ2006 ጥላ ፎቅ አካባቢ የተወሰኑ ደጋፊዎች በማላውቀው ሁኔታ በጣም ይቃወሙኝ ነበር፤ በተቃውሞው በጣም
ተበሳጭቼ ማልያውን አውልቄ ስወጣ ወረወረው ተባልኩኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ከተወሰኑ ደጋፊዎች ጋር አለመግባባት ተፈጠረ፤በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደማልችል ተረዳሁ፤በመጨረሻም ያለ ፍላጎቴ ከክለቡ ጋር በስምምነት
ተለያየሁ፡፡
ሀትሪክ፡- አንዳንድ አሰልጣኞች ገንዘብ ይቀበላሉ ይባላል፤ አንተስ ክለብ ለመግባት ገንዘብ ተጠይቀህ ታውቃለህ?
ሙሉ አለም፡- በፍፁም…ተጠይቄ አላውቅም፤ብጠይቅም ደግሞ አልሰጥም፤ ክለብ ለመግባት ገንዘብ ልሰጥ ቀርቶ ክለብ ሳንድዊች እንኳን ከፍዬ አልበላም፤ ክለብ የሚል ቅጥያ ስም
ስላለው…(በጣምሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …ፕሮፌሽናል የመሆን ህልምስ ነበረህ…?
ሙሉአለም፡- …እመኝ ነበር…አልቀጠ ለም እንጂ…አንድ ጊዜ…ዕድሉ መጥቶ ነበር፤በተለይ የኬንያው ሊዮፓርድስ እንዲሁም የሱዳን ክለብ ጠይቀውኝ ነበር፤ያው በተለያየ ምክንያት ሳይሳኩ ቀረ እንጂ ከዚህም የራቀ
የፕሮፌሽናል ምኞት ነበረኝ፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.