የጨዋታ ዘገባ| ጅማ አባ ጅፋር ከወራጅ ቀጠና ስጋት የራቀበትን ድል ድሬደዋ ላይ አሳክቷል

 

በ14ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ላይ ጅማ አባጅፋርን ከድሬደዋ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በባለሜዳው ጅማ አባጅፋር 2-1 አሽናፊነት ተጠናቋል።

ዋና አሰልጣኙ ሳይዝ ወደ ሜዳ የገባው ጅማ ከ80 ደቂቃዎች በላይ በጎዶሎ የተጫዋቾች ለመጫወት ቢገደድም አሸንፎ መውጣት ችሏል። ጅማዎች ከአስራ ሶስተኛ ሳምንት በሀዋሳ ከተማ ከተሸነፈው ስብስባችው ወስጥ ሰዒድ ሀብታሙ፣ አብርሀም ታምራት እና ብሩክ ገብረዓብ አስወጥተው በምትካቸው መሐመድ ሙንታሪ፣ ኤርሚያስ ኃይሉ እና ተመስገን ደረሰ ቀይረው ሲያስገቡ ዋና አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በወላጅ አባታቸው ህልፈት ምክንያት ጨዋታውን መምራት ሳይችሉ ቀርተዋል። በአንፃሩ ድሬደዋ ከተማ በሜዳው ከስሑል ሽረ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ አማረ በቀለን በያሬድ ዘውድነህ፣ ዋለልኝ ገብሬን በያሬድ ታደሰ ምትካቸው አስገብተዋል።

የመጀመርያው አጋማሽ በፈጣን እና ሳቢ በነበረው የጨዋታ እቅስቃሴ በመጀመያዎቹ ሰባት ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተደጋጋሚ ወደ ግብ በመድረስ የግብ እድሎች ተፈጥረዋል። ጨዋታው ከተጀመረ ገና በ4ኛው ደቂቃም በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በቀኝ መስመር ኤርሚያስ ሀይሉ ኳስን ይዞ ገብቶ ወደ መሐል ለቡዙዓየሁ እንዳሻው ያሻግረውን ኳስ ለማዳን ሲረባረቡ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ በተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ኤርሚያስ ኃይሉ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ጅማዎች በጊዜ ባገኙት ጎል አጀማመራቸውን ቢያሳምሩም የተከላካዮቹ መዘናጋት በ6ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ ተገጫጭቶ ለሪችሞንድ አዶንጎ የደረሰው ኳስ ሪችሞንድ አምልጦ ሲወጣ የጅማው ተከላካይ አሌክስ አመዙ ጥፋት በመስራቱ የዕለቱ አርቢትር በላይ ታደሰ በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥተውታል። ጥፋቱን ተከትሎ በተሰጠው ቅጣት ምት በ10ኛው ደቂቃ በረከት ሳሙኤል ግሩም ጎል ከመረብ በማሳረፍ ድሬዳዎችን አቻ ማድረግ ችሎዋል።

ከግብ መቆጠር ቦሀላ መረጋጋት ያልታየባቸው ጅማዎች በ15ኛው ደቂቃ ላይ ሙኅዲን ሙሳ በተከላካዮች መሐል ሾልኮ ከግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ ጋር ተገናኝቶ ያልተጠቀመው አጋጣሚ ድሬዎች በጨዋታው ወደ መሪነት ሊሸጋገሩ የሚችሉበት አጋጣሚ ነበር። ከዛች ሙከራ በኃላ ግን ጅማዎች ንጋቱ ገ/ሥላሴን ከመሐል አፈግፍጎ የተከላካይ ክፍሉ እንዲረዳ ከተደረገ በኃላ በአንፃራዊነት መረጋጋት ተስኖት የነበረውን የኋላ ክፍል ለማረጋጋት ችለዋል።
ጅማዎች በ23ኛ ደቂቃ ላይ ኤርሚያስ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ውስጥ ጫፍ ተጠግቶ ያሻገረውን ኳስ ተመስገን ደረሰ አስቆጥሮ በድጋሚ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኃላ እጅጉን የተሻሉት ጅማዎች በተመስገን ደረሰ እና በቡዙዓየሁ እንዳሻው አማካኝነት ለግብ የቀረቡ መከራዎች አደርገዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም ብዙ ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ታይቶበት ሊጠናቀቅ ችሏል ::

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ብዙ ሙከራዎችን ያላሳየው ሁለተኛው አጋማሽ ጅማዎች ኤርሚያስ ሀይሉ አስወጥተው ከድር ኸይረዲንን በማስገባት በመከላከል ላይ የነበራቸውን ክፍተት ዘግተው አልፎ አልፈው በመልሶ ማጥቃት በተመስገን ደረሰ እና ብዙዓየሁ እንደሻው አማካኝነት ያለቀላቸው የግብ እድሎችን አምክነዋል። ጅማዎች በ72ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ላይ ተመስገን ደረሰ ለቡዙዓየሁ እንዳሻው ያሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ የግብ አግዳሚ የመለሰበት ሙከራ ተጠቃሽ ነበር ። በጨዋታ ለግብ የቀረበ ሙከራ ያደረጉት ድሬዎች በአማካዩ ለኤልያስ ማሞ አማካይነት ግሩም መከራ ቢያረግም መሐመድ ሙንታሪ ያዳነበት እንዲሁሞ በ88ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ለዳኛቸው የተሻገረለትን ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ።

ጨዋታው በጅማ አባጅፋር የበላይነት ሲጠናቀቅ ውጤቱ በዚህ በመጠናቀቁን ተከትሎ የጻውሎስ ጌታችው ቡድን ነጥባቸውን ወደ 18 ከፍ በማድረግ ደረጃቸውን ወደ አስራ እንደኛ ከፍ ሲያደርጉ ድሬዎች በበኩላቸው በዛው ነጥባቸው በአስራ አምስትኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

Hatricksport website writer

ዳዊት ታደሰ

Hatricksport website writer