የጨዋታ ዘገባ | ስሑል ሽረ እና ሀድያ ሆሳእና ነጥብ ተጋርተዋል

 

ትግራይ ስታድየም ላይ ሀድያ ሆሳእናን ያስተናገዱት ስሑል ሽረዎች በሜዳቸው ነጥብ ጥለዋል።አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ባሳለፍነው ሳምንት ከድሬዳዋ ነጥብ ይዞ ከተመለሰው ስብስብ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ቀይ ካርድ የተመለከከተውን ወንድወሰን አሸናፊን በምንተስኖት አሎ፣አዳም ማሳላቺን በክብሮም ብርሀነ ሲቀይሩ የሀድያ ሆሳእና አሰልጣኝ ሆነው ከተሾሙ በኃላ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ያደረጉት አሰልጣኝ ፀጋይ ኪዳነማርያም በበኩላቸው በወላይታ ድቻ ከተሸነፈው ቡድን አንድ ቅያሬ አድርገዋል፤የቡድኑ አምበል ደስታ ዲቻሞ ወጥቶ በረከት ወልደዮሐንስ ገብቷል።

ስሑል ሽረዎች የቀድሞው ተጨዋቾቻቸው ቢስማርክ አፒያ እና ቢስማርክ አፖንግን እንዲሁም የቀድሞ ወጌሻቸው ቢንያም ተፈራን የማስታወሻ ስጦታ በመስጠት የተጀመረው የመጀመርያው አጋማሽ ብዙ ሙከራዎችን ያላስተናገደ ነበር።

በ4-3-3 የተጨዋቾች አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት ስሑል ሽረዎች ከመሀል ሜዳ ወደ መስመር በሚወጡ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር ያደረጉዋቸው እንቅስቃሴዎች እንደ ሌላው ጊዜ ውጤታማ ሊሆኑላቸው አልቻሉም።የነዚህ እንቅስቃሴዎች ማሳያ ሚሆኑት በጨዋታው የመጀመርያ 25 ደቂቃዎች የተደርጉ ሙከራዎች ናቸው።ከመሀል ሜዳ ሀብታሙ ሸዋለም ያሾለከው ሰንጣቂ ኳስ ከግራ መስመር ተነስቶ ወደ ሳጥኑ የገባውን አብዱልለጢፍ መሐመድ ቢያገኘውም ጋናዊው የመስመር አጥቂ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

እንግዶቹ ሀድያዎች 4-5-1 ቅርፅን በመያዝ አብዛኛው የመጀመርያ አጋማሽን ወደ ኃላ አፈግፍገው በራሳቸው ሜዳ አሳልፈዋል።በዚህም ምክንያት ለተደጋጋሚ የስሑል ሽረ የመስመር ጥቃቶች ቢዳረጉም እንደቡድን የነበራቸው የመከላከል ጥምረት ጥሩ ስለነበር ጥቃቶቹን ለመመከት አልተቸገሩም።

በፈጣን ሽግግር ከመሀል ሜዳ የተጀመረው የስሑላውያን ማጥቃት እንቅስቃሴ ቀኝ መስመር ላይ ለነበረው ዓወት ገብረሚካኤል ደርሶ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዓወት ያሻማው ኳስ አቬር ኦቮኖ በጥሩ ሁኔታ አውጥቶበታል።በተመሳሳይ አሁንም ከመሀል ሜዳ ከነፃነት ገብረመድህን የተነሳው ኳስ ቀኝ መስመር ላይ ለነበረው ያሳር ሙገርዋ ጋር ደርሶ ኡጋንዳዊው አማካኝ አጠገቡ ልነበረው ክፍሎም ገብረህይወት አቀብሎት በግራ እግሩ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ ጨዋታው ላይ ጥሩ የነበረው አቬር መልሶበታል።

የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ሰዐት ሀድያ ሆሳእናዎች በመልሶ ማጥቃት ከመሀል ሜዳ ወደ ቀኝ መስመር የተላከውን ኳስ ሱራፋኤል ዳንኤል ጋር ደርሶ ወደ ውስጥ ያሻማው አደገኛ ኳስ ምንተስኖት አሎ ደርሶ በጥሩ ሁኔታ መልሶታል።በተጨማሪ ከዚህ ሙከራ ትንሽ ደቂቃዎች በኃላ አሁንም ከመሀል በረጅሙ አፈወርቅ ሀይሉ የላከው ኳስ ሳጥኑ ውስጥ በግራ በኩል ለነበረው ቢስማርክ አፒያ ጋር ደርሶ የመታው ኳስ ምንተስኖት አሎ በቀላሉ ይዞታል።

በዚህም መሠረት የመጀመርያው አጋማሽ ምንም ግብ ሳይስተናገድበት ተጠናቋል።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ በተመሳሳይ ብዙ ሙከራዎችን ያላሳየው ሁለተኛው አጋማሽ በግቦች ያልታጀበ ነበር።ሀድያ ሆሳእናዎች በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ 10 ደቂቃዎች ላይ ተጭነው በመጫወት ከቆሙ ኳሶች እድሎችን መፍጠር ችለዋል።በ48ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት አፎርቅ ሀይሉ ሲያሻማው በረከት ወልደዮውሀንስ በግራ እግሩ መቶት ቢየስቆጥረውም የዕለቱ የመስመር ዳኛ ከጨዋታ ውጪ በማለት ሽረውታል።በተጨማሪ ይሁን እንደሻው ያሻማው የቆመ ኳስ እዮብ በቀታ በግምባሩ ሲገጨው ለትንሽ ከግቡ ጎን ወጥቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃዎች ላይ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለማስመለስ ሀይለአብ ሀይለስላሰን ወደ ሜዳ ያስገቡት ስሑል ሽረዎች የጨዋታው የኳስ ቁጥጥር ብልጫን መመለስ ቢችሉም የጠሩ የግብ እድሎችን መፍጠር አልቻሉም።ስሑላውያን በሁለተኛው አጋማሽ አብዱልለጢፍ መሐመድ ከቀኝ መስመር አሻምቶት ክፍሎም ከሀድያ ተከላካዮች መሀል ሾልኮ በመውጣት በግምባሩ የጨረፈው እና ኤቨር ኦቮኖ በቀላሉ የያዘው እንዲሁም ከግራ መስመር ሀይለኣብ አሻምቶት ሳጥኑ ውስጥ በቀኝ በኩል የነበረው መድሀንየ ብርሀነ መትቶት ከግቡ ጎን የወጣው ኳስ በስሑላውያን በኩል ሚጠቀሱ ሙከራዎች ናቸው።በዚህም መሠረት የስሑላውያን የመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ምንም ግብ ሳያስተናግድ በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።

ውጤቱን ተከትሎ ስሑል ሽረዎች አራተኛ ደረጃቸውን ለወላይታ ድቻ ሲያስረክቡ ሀድያ ሆሳእናዎች ነጥባቸውን ወደ 10 ከፍ አድርገዋል።

Hatricksport website writer

Twitter

ዳዊት ብርሀነ

Hatricksport website writer