የጨዋታ ዘገባ | ሳቢ ባልሆነው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ተጋርቷል

 

በ17ኛው ሳምንት የኢትዮጲያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን አስተናግዶ 1-1 በሆነ ውጤት ነጥብ ተጋርተው ወተዋል።

በጊዜያዊ አሰልጣኝ ብርሀኑ ወርቁ የሚመሩት ሀዋሳ ከተማዎች ባለፈው ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ 3-1 ከተረቱበት ስብስብ ሀብቴ ከድርን በላውረንስ ላርቴ፣ ተስፋዬ መላኩ እና ሄኖክ አየለን በቢሊንጌ ኢኖህ እና በብርሀኑ በቀለ ቀይረው የገቡት ሀይቆቹ ከመጀመሪያዎቹ አጨዋወት እንቅስቃሴ ያልተሻለ የአጨዋወት እንቅስቃሴ ተስተውሎባቸዋል።

በዚህ የዝውውር መስኮት አራት ያህል ተጫዋችን ወደ ቡድኑ የቀላቀለው እና በሜዳቸው በመቐለ 70 እንደርታ 1-0 የተረቱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከባለፈው ጨዋታ ፀጋሰው ድማሙ፣ በረከት ወ/ዮሐንስ፣ ሱራፌል ዳንኤል እና ቢስማርክ ኦፖንግ ወጥተው ቢኒያም ሲራጅ፣ መድሀኔ ብርሀኔ፣ ተስፋዬ አለባቸው እና ሳሊፍ ፎፋና አስገብተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

በኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ የተመራው የሀዋሳ ከተማ እና የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በአሰልቺ ነበር። ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት የመረጡት ሁለቱ ቡድኖች ወደ ጎል በመድረስ በኩል ሀዋሳዎች የተሻሉ ነበሩ። 13ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ከተማው መስፍን ታፈሰ ከመሀል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ በጥንቃቄ አረጋግቶ በግራ መስመር በኩል በቀጥታ ወደ ጎል ሲመታው የግቡን ቋሚ አስታኮ መረብና ኳስ በማገናኘት ሀዋሳዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ ነበር። ከጎሏ መቆጠር በኋላ በተወሰነ መልኩ የተነቃቁ የሚመስሉት ሀዋሳዎች 23ኛው ደቂቃ ላይ ያኦ ኦሊቨር ብቻውን ከመሀል ሜዳ ኳስ እየገፋ ሳጥን ወደ ውስጥ ቢገባም ሳይጠቀምበት የአቨር ኦቮኖ ሲሳይ ሆናለች። በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በይሁን እንዳሻው እና በአፈወርቅ ሀይሉ ወደ ጎል ከሚላኩ ኳሶች ውጪ ሀዲያዎች የተረጋጋ አጨዋወት አልታየባቸውም።

በዛሬው ጨዋታ የቀዘቀዘ እንቅስቃሴ ሲታይበት የነበረው ብሩክ ታፈሰ በአንድ ሁለት ቅብብል ያኦ ኦሊቨር ከመስፍን ታፈሰ አድርጎ አመቻችቶ የሰጠው ኳስ የሀዋሳዎችን ማሸነፍ እድል ታለመልም የነበረች ነበረች።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ሀዲያዎች የማእዘን ምት አግኝተው ይሁን እንደሻው ወደ ጎል አሻምቶ ሳጥን ውስጥ በነበረው ንክኪ አፈወርቅ ሀይሉ አግኝቶ ጎል በማስቆጠር ሀዲያዎችን አቻ ማድረግ ችሎ እረፍት ወጥተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ከመጀመሪያው የተሻለ እንቅስቃሴ ቢጠበቅም በሁለቱም በኩል ወጣ ገባ ያለ የጨዋታ እንቅስቃሴ ታይቷል። እንደ መጀመሪያው ሁሉ በቅብብል ወደ ጎል በመድረስ ባለሜዳዎቹ የተሻሉ ናቸው። ባንፃሩ ሀዲያዎች መከላከል ላይ ያመዘነ አጨዋወት ይዘው ሲመለሱ አልፎ አልፎ ወደጎል በመድረስ እና ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አምክነዋል።

ብርሀኑ በቀለን በአቤነዘር ዩሀንስ ያልተሳካ ቅያሪ ያደረጉት ሀዋሳዎች ኳስ ወደ ኋላ እየተመለሱ መሀል ሜዳውን አሳስቶ ለሀዲያዎች ወደ ፊት ገፍተው ውጤቱን ለመቀየር የሚያስችል አጋጣሚዎች ቢኖሩም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 10 ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት ሁለቱም ቡድኖች ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል ቢደርሱም ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱንም ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ በ23 ነጥብ በ8የግብ እዳ በ7ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሀዲያ ሆሳዕና 14ነጥብ በ13 የግብ እዳ የሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛል።