የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ አጋማሽ የሚደረጉ ሲሆን ሰባት ጨዋታዎች ነገ (ረቡዕ) ሲደረጉ ቀሪ አንድ ጨዋታ ደግሞ ሀሙስ የሚደረግ ይሆናል። በነገው እለት ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ድሬዳዋ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ የሚያደርጉትን ጨዋታ ለእናንተ እንዲስማማ አድርገን እንደሚከተለው ዳሰነዋል። መልካም ንባብ።
ጨዋታ: ድሬዳዋ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ
የጨዋታ ቀን: ረቡዕ ጥር 20/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ፌደራል አርቢትር ወልዴ ንዳው
የጨዋታ ቦታ: ድሬዳዋ ስታዲየም
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ላይ የደረሰ ሲሆን በዚህ ሳምንትም በ10ኛው ሳምንት ወደ ወልቂጤ ስታዲየም ተጉዘው በወልቂጤ ከተማ የተሸነፉት ድሬዳዋ ከተማዎች በሜዳቸው ሰበታ ከተማን ያስተናግዳሉ።
የዘንድሮው የአሰልጣኝ ስምዖን አባይ ድሬዳዋ በሊጉ በርካታ ግቦች የሚቆጠሩበት ደካማ የተከላካይ ክፍል ያለው ሲሆን ይህ ድክመቱም በሊጉ ወራጅ ቀጠና ውስጥ እንዲዳክር አስገድዶታል። ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ እስካሁን በሊጉ በተደረጉ 10 ጨዋታዎች 19ግቦችን በማስተናገድ በሊጉ ብዙ ግብ የተቆጠረበት መሆን ችሏል። በ10ኛው ሳምንት ወደ ወልቂጤ የተጓዙት ድሬዎች ሳዲቅ ሴቾ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ በወልቂጤ ከተማ ተሸንፈው ተመልሰዋል።
እንደ ሌሎቹ የሊጉ ቡድኖች ሁሉ ከሜዳቸው ውጪ ድል ማድረግ የከበዳቸው ሰበታ ከተማዎች የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ሶስት ነጥብ ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን አጨዋወቱን ከተጋጣሚያቸው ባህርይ አንፃር የሚቃኝ በመሆኑ በነገው ጨዋታ ኳስን በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ተቆጣጥሮ የጎል እድሎችን ለመፍጠር እንደሚጥር ይጠበቃል። ቡድኑ ጎሎችን ከተለያየ አቅጣጫ ለማግኘት የሚጥር መሆኑ እንደ ጠንካራ ጎን ይነሳል። በሜዳ ተገቢነት ምክንያት የሜዳ ጨዋታቸውን በአዲስ አበባ ስታዲየም እያደረጉ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች በ10ኛው ሳምንት ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሊጉ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነውን ሀዋሳ ከተማን ገጥመው በፍጹም ገ/ማርያም እና አዲሱ ተስፋዬ ሁለት ግቦች ሀዋሳ ከተማን 2-1 ማሸነፍ ችለዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ከደረሰበት ሽንፈት አገግሞ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ሰበታ ከተማ ደግሞ አሸናፊነቱን ለማስቀጠል እና ከሜዳው ውጪ የመጀመሪያ 3ነጥቡን ለማግኘት የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ በእግር ኳስ አፍቃሪው ዘንድ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል ረመዳን ናስር አሁንም ከጉዳቱ ያላገገመ በሰበታ ከተማ በኩል ደግሞ ዳዊት እስጢፋኖስ፣ በኃይሉ አሰፋ እና አስቻለው ግርማ በነገው ጨዋታ ግልጋሎት የማይሰጡ ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ