“የጣና ሞገድ ደጋፊዎች የራሳቸው ቀለም ያላቸዉ ምርጥ ደጋፊዎች ናቸው ፤ {Yellow Wall} የሚል መጠሪያ ካላቸው የዶርቱሞንድ ደጋፊዎች ጋር ይመሳሰሉብኛል” አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ (ባህር ዳር ከነማ) ክፍል-1

 

🔑“ኮረና ቫይረስን ለመግታት ከጥንቃቄው በላይ እንደየእምነታችን መፀለይ ብቻ ነው መፍትሄው”

🔑“የእርካታ ጥግ ላይ ደርሻለሁ ባልልም በአንደኛው ዙር ውጤት አልተከፋሁም”

🔑“የጣና ሞገድ ደጋፊዎች የራሳቸው ቀለም ያላቸዉ ምርጥ ደጋፊዎች ናቸው ፤ {Yellow Wall} የሚል መጠሪያ ካላቸው የዶርቱሞንድ ደጋፊዎች ጋር ይመሳሰሉብኛል”
አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ (ባህር ዳር ከነማ)


ከ22,156 በላይ ህዝብን በሞት መነጠቁ ከ490,253 በላይ የሚሆነው ህዝብ ደግሞ በአሁን ሰዓት አለምን ሁሉ ባስጨነቀው ኮሮና ቫይረስ መጠቃቱ የባህር ዳር ከነማውን አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ደስታውን ነጥቆታል፡፡ በተለይ ቫይረሱ በሀገራችን 12 ሰዎች ብቻ መያዛቸው መጠነኛ እፎይታን ቢሰጠውም እንደ ጣሊያን ያሉ ሀገራት በአንድ ሌሊት በርካታ ዜጎች በሞት መነጠቃቸው የስጋቱንም መጠን ከፍ አድርጎበት ክፉኛ አስጨንቆታል፡፡ “ጥንቃቄና ለመከላከል ርብርቦሽ ማድረጉ የሚደገፍ ቢሆንም ከዚህ ወረርሽኝ የሚታደገን አንድ ነገር ብቻ ነው…እሱም ሁሉም እንደየእምነቱ ወደ ፈጣሪው መፀለይና ምህረትን መለመን ብቻ “ ሲል ይናገራል፡፡
በጉልበተኛው ኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሊጉ በመቋረጡ ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆኖ ቤቱ እንዲቀመጥ የተፈረደበት የባህር ዳር ከነማው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በአንደኛው ዙር ስላስመዘገበው ውጤት፣ቡድኑ በሜዳው ጠንከራ ሆኖ ከሜዳው ውጪ ጥርስ አልባ ስለመሆኑ፣ የአንደኛው ዙር ምርጡ ተጨዋችና ቡድን ማን እንደሆነ እንዲሁም “የተለየ ቀለም ያላቸው ምርጥ ደጋፊዎች ናቸው “ስላላቸው የጣና ሞገድ ደጋፊዎች ዙርያ የኮረና ቫይረስ በመላው አለም እያደረሰ ባለው ጉዳት ምክንያት በተሰበረ የሀዘን ድባብ ውስጥ ሆኖ ከሀትሪክ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ጋር ከዚህ በታች ያለውን ቁም ነገር ያለው ቆይታ አድርጓል፡፡


ሀትሪክ፡- …ፋሲል እንዴት…ነህ ኮረና ቫይረስ እንዴት እያረገህ ነው…?

ፋሲል፡- …ኮረና ቫይረስ እኔን በተናጠል ወይም እኛ ሀገር ብቻ ሣይሆን መላው አለምን በጣም እያስጨነቀ፣ እያሯሯጠን ነው፤ትምህርት ቤቶችን፣ የእግር ኳስ ሜዳዎችን፣የመዝናኛ ቦታዎችን ሁሉ ከእንቅስቃሴ ውጪ በማድረግ ፀጥ እረጭ አድርጓቸዋል፡፡ ብዙ ሰዎች ሞተዋል በብዙ ሺዎች ደግሞ እንደዚሁ በቫይረሱ የተጠቁበት ሁኔታ ያለበት በመሆኑ አለም አስቸጋሪ ወቅት ላይ እንድትገኝ አድርጓል፡፡ በጣም የሚገርመው ቫይረሱ ሀብታም፣ደሃ…ባለስልጣን ወይም ተራ ሰው ብሎ ሳይለያይና ሳይከፋፍል ሁሉንም እያስጨነቀ ነው፡፡ በተሻለ የቴክናሎጂና የገንዘብ አቅም ላይ ነን፣የአለም ገዢዎች ነን…የሚሉትን ሀገሮች ሣይቀር ያልማረ…በጣም የፈተነን ወረርሽኝ ነው፡፡ በሀገራችንም የተጋባው ይኸው የአለም ጭንቀትና የስጋት ስሜት ነው፤እንግዲህ ከመንግሥትና ከህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን መመሪያዎችና በሽታውን ለመከላከል የሚረዱትን ነገሮች ተግባራዊ በማድረግ ለመከላከል መታገል ነው፡፡

ሀትሪክ፡-ብዙዎች በሽታውን ለመከላከል ይረዳሉ ያላቸውን መገልገያዎች ለመግዛት ወደ ፋርማሲ ሲሮጡና ፋርማሲዎችንና ከነማዎችን በሰልፉ ሲያጨናንቁ ታይቷል፤ ፋሲልስ ከስጋት በመነጨ ወደ እነዚህ ቦታዎች ሮጧል…?

ፋሲል፡-… (ሣቅ)…ወደ ከነማ መድሃኒት ቤቶች በመሮጥ ሰልፍ እስከማጨናነቅ ደረጃ እንኳን አልደረስኩም፤ቀድሜ በምችለውና በአገኘሁት አጋጣሚ ለመጠንቀቅ፣ለመዘጋጀት ሞክሬያለሁ፡፡ ወደ ከተማ ስትወጣ የምታየው ሰልፉና ሩጫው ግን በጣም ያስጨንቅሀል፡፡ በተለይ የሰልፉ መጨናነቅ በሽታው እንዲስፋፋ ምክንያት እንዳይሆንና የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስ ስርጭቱም እንዳይባዛ እያልኩ በጣም እንድሰጋም አድርጎኛል።

ሀትሪክ፡- …የሠላምታ ስታይልህንስ ቀይረሃል፤ ጓንትና የፊት ማስክስ አድርገሃል…?

ፋሲል፡-… (ሳቅ)…የእኛ ባህል በጣም አስቸጋሪ ነው…አዲስ ነገር ቶሎ ሲመጣ ቶሎ ለመልመድ ስንቸገር ይታያል፤በጣም ተቀራርበን፣ተዋደን ከመኖራችን የተነሣ አትተቃቀፉ፣አትጨባበጡ እየተባለ ረስተነው እንጨባበጣለን፣እንተቃቀፋለን፤ይሄ የሚደገፍ አይደለም…መርሳትም የለብንም፤አሁን አሁን ግን መንግሥትም ሚዲያውም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ በመሆኑ ሰው እየተረዳ፣እየገባው መጥቷል፡፡ እኔ ከሚሰጠው መግለጫ በመነሣት የራሴን ጥንቃቄ ከመውሰድ በዘለለ ጓንትና የፊት ማስክም እስከ አሁን አልገዛሁም፣አላደረኩምም፡፡ በቀጣይ እንግዲህ ግድ ከሆነ አብረን እናየዋለን፡፡


ሀትሪክ፡- …ጉልበተኛው የኮረና ቫይረስ በአለም ላይ ጉልበቱን እንዳሳየ ሁሉ በስፖ ርቱም ላይ ጡንቻውን አሣይቷል፤ በዚህ የተነሣም ውድድሮች ይዘጋሉ…እግር ኳስም ይመሰቃቀላል ብለህ አስበህ ነበር…?…በተፈጠረው ነገርስ አልተገረምክም…?

ፋሲል፡- የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስተላለፈው መልዕክት ለእኔ ከእግር ኳስ ወይም ከስፖርት ውድድሮች መዘጋት በላይ ነው፤ነገሮች እኛ የማንቆጣጠራቸው ከእኛ አቅም በላይ ሆነው የሚያስጨንቁን፣ የሚፈታተኑን፣ የሚያሰቃዩንና በሞት ጭምር የሚነጥቁን ነገሮች ለካ አሉ ብዬ እንዳስብ ወደላይ ቀና ብዬ እንዳይ አድርጎኛል፡፡

ሀትሪክ፡- …በዓለም ላይ ይሄ ሁሉ ፈተናና መዓት እንዲወርድ የሆነበትን ምክንያት ምን ልንለው እንችላለን…?

ፋሲል፡- …ይሄ ቫይረስ ትንሽ ትልቅ፣ ሀብታም ደሃ፣ በስልጣኔ ጣሪያ የነካ ያልነካ፣ የአለም ኃይል ሀገር ወይም ደካማ ሀገር ብሎ ሣይነጣጥል ሁሉንም እኩል የፈተነ በሽታ መሆኑን ሣይ ጉዳዩን ከኃይማኖታዊ ጉዳይ ጋር ማያያዙን ነው የመረጥኩት፤ምናልባት አምላክ ሊያስተምረን ፈልጎ የተፈጠረ አጋጣሚ ይሆን እንዴ? ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም ጥቁር ነጭ፣ ሀብታም ደሃ፣ የዚህ ብሔር የዛ ብሔር፣የዚህ ሀገር የዛ ሀገር እያልን እየተገዳደልን እየተጫረስን ስለሆነ እንዲሁም እግዚብሔርን ከመፍራት ወጥተን የፈጠረንን አምላክ ቃል እየጣስን በመሄዳችን ሊያስተምረን ፈልጎ ይሆን? ብዬ እስከማስብ ሁሉ ደርሻለሁ፡፡ ክፋታችንና ተንኮላችን፣ጥላቻችን መጠኑን እያለፈ በመምጣቱ እንድንማርበት ፈልጎ ይሆን? እንድል ነው ያደረገኝ…፡፡

ሀትሪክ፡- …በቀጣይ ከዚህ ችግር ለመውጣት ወይም ለመገላገል ምን መደረግ አለበት ይላል ፋሲል…?

ፋሲል፡- …ይሄ አለምን ሁሉ ያስጨነቀው ነገር… ከእኔ አቅም…ከእኔ አእምሮ…በላይ የሆነ ነገር ቢሆንም…እንደ እኔ የግል አስተ ያየት ሁሉም ሌላውን ነገር ትቶ በየራሱ እምነት አምላክ ምህረትን እንዲስጠን በእስካአሁኑ በቃችሁ እንዲለን አብዝቶ መፀለዩ ነው ዋናውና ትልቁ መፍትሔ ብዬ የማስበው፡፡ ይሄንን በሽታ ገንዘብ ያላቸው…በስልጣኔ አደግን ያሉ…የአለም ገዢዎች ነን…የሚሳነን ነገር የለም ብለው የሚያስቡ ሀገሮች ሣይቀሩ ማቆምና በአጭሩ መግታት እንኳን አልቻሉም፤ይሄ ከሰው ልጅ አዕምሮ በላይ መሆኑንም ስለሚያሳይ ለእኔ ሁሉን ነገር ማድረግ ወደሚችለው አምላካችን እንደ እየዕምነታችን መፀለይ ብቻ ነው መፍትሔው ፡፡

ሀትሪክ፡- …በዚህ ጉልበተኛ በሆነው ቫይረስ አማካይነት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ ሴሪ አ፣ ላ ሊጋና ሌሎች ታላላቅ ኢንተርናሽናል ውድድሮች እንደተቋረጡ ሁሉ የእኛም ፕሪሚየር ሊግ እንዲቋረጥ ተደርጓል፤ይሄንን ጠብቀህ ነበር…?

ፋሲል፡- …ሁለት የተዘበራረቀ ስሜት ነው በውስጤ የነበረው…እንደ አሰልጣኝ ሙያው እግር ኳስ ብቻ እንደሆነ ሰው ከስፖርት ተለይቶ ማሳለፍ ከባድ ስለሆነ ባይቋረጥወይምአይቋረጥም ብለህ እስከማሰብ ትደርሰለህ፣ በሌላ በኩል ግን ምትክ አልባውን የሰውን ህይወት የሚነጥቅ ቫይረስ በመሆኑ መቋረጡ አማራጭ የሚቀርብለት አይደለም ትክክል ነው ብለህም ታስባለህ፡፡ በሽታው በቀላሉ የሚዛመት በመሆኑ በተለይ ብዙ ሰዎች በአንድነት በተሰበሰቡበት ቦታ በፍጥነት የመተላለፉ መንገድ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር በሽታውን መቆጣጠር እስከሚቻል ጊዜ ድረስ መቆም አለበት ተብሎ መወሰኑ ከዜጋው ከሚጨነቅ መንግሥት የሚጠበቅ ነውና ውሳኔው ተገቢ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ እኛ ጤና ስንሆን ነው ስፖርት የሚኖረው…የስፖርት ቤተሰቡም በእግር ኳሱ የሚደሰተው ጤና ሲሆን ነውና ለጤና፣ለሰው ልጅ ህይወት ቅድሚያ ተሰጥቶ መዘጋቱ ተገቢ ነው፡፡ የበሽታውን ስርጭት ለመግታትና የሰውን ህይወት ለማዳን ሲባል እኮ ነው በአለም ላይ ውድደሮች የተዘጉት፤እኛም ከአለም ውጪ ስላልሆንን መዘጋቱ ተገቢም፣የሚጠበቅም ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ከበሽታው አስጊነትና አስፈ ሪነት አንፃር ፕሪሚየር ሊጉ ተዘግቶ የሚቀር አይመልህም…?…ከዚህ በኋላ ውድድሩ ተመልሶ የሚጀመር ይመስልሃል…?

ፋሲል፡- …እኔ በባህሪዬ ጨለምተኛ ስላልሆንኩ ጨለማ የሆነ ነገርን ማሰብ አልፈልግም፤ እግዚአብሔር ፀሎታችንን ሰምቶ በቃችሁ ብሎን በሽታው ጠፍቶ በፍጥነት ወደ ውድድር እንመለሳለን የሚል ምኞትና ተስፋ ነው በውስጤ ያለው፤ከዚህ በመነሣት በዚሁ ተዘግቶ ይቀራል የሚል ጨለማ አስተሳሰብ የለኝም፡፡እግዚአብሔር በልጆቹ ላይ ስለማይጨክን ምህረቱን አውርዶልን እኛ ብቻ ሣንሆን የአለም ህዝብም ከጭንቀቱ ተገላግሎ ወደ እለት ተዕለት እንቅስቃሴው ይመለሳል የሚልበ ተስፋ የተሞላ እምነት ነው በውስጤ ያለው፡፡

ሀትሪክ፡- …ለእንደ አንተ አይነቱ ረዥሙን ህይወቱን በስፖርት ላሳለፈ ሰው ያለ ውድድርና ያለ ልምምድ ማሳለፍስ ከባድ አይሆንም… ?

ፋሲል፡- …በጣም ከባድ ነው…ግን ምን ማድረግ ትችላለህ? የሆነው ከመቀበል ውጪ፤እኔ በባህሪዬ ውድድር በሌለኝ ሰዓት ለቀናት አይደለም ለሰዓታትም ቢሆን ያለ ስፖርት ማሳለፉ አልችልም…ወጥቼ ኳስ እጫወታለሁ…ስፖርትም እሠራለሁ፡፡ያለ ውድድርና ያለ ልምምድ ማሳለፍ ህይወትህ የቆመ ያህል እንዲሰማህ ያደርጋል፤ካለ ውድድርና ልምምድ ማሳለፍ በጣም ፈታኝ አስጨናቂም ነው የሆነብኝ…፡፡

ሀትሪክ፡- …አሁን በሽታው ካለው አሳሳቢነትና ፕሪሚየር ሊጉም በመቆሙ ስለቡድንህ፣ስለስራህ ማሰብ አቁመሃል…?

ፋሲል፡- …እንዴት አቆማለሁ?…በተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ባልሆንም ለሥራው የሚያግዙኝን በተለይ ከወረቀትና ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ስራዎችን በቤቴ እየሰራሁ ነው፤ በእርግጥ አሁን መንግሥት ከሰጠው መግለጫ በመነሣት ለጊዜው እረፍት በምክር አጅበን ለተጨዋቾች ሰጥተናል፤በአካባቢያቸው፣በቤታው ራሣቸውን እየጠበቁ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ መክረን ነው ለዕረፍት የላክናቸው፡፡ ስፖርቱን እርግፍ አድርጎ መቀመጥ ጉዳት ስላለው ጥንቃቄ የተሞላበት የግል ልምምድ እንዲሰሩ ነው ሞክረን የላክናቸው፡፡ በቀጣይ ሣምንት እንግዲህ ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር የሚሰጠውን መመሪያ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ልምምድ የመጀመር ሃሣቡ አለን፡፡ ልምምዶች ውድድሮች ይቀጥላሉ? ይቆማሉ?የሚለው ለመወሰን መንግሥት የሚሰጠውን አቅጣጫ ጆሮ ሰጥተን የምናዳምጥ ነው የሚሆነው፡፡

ሀትሪክ፡- …እስቲ አሁን በኮሮና ዙሪያ ከያዝነው ጥያቄ እንውጣ…ፋሲል የአንድ ክለብ ሙሉ አሰልጣኝ ሆኖ መስራት ከጀመረ ወራቶች ተቆጥረዋል፤ባህር ዳር ከነማ በፋሲል ሙሉ የአሰልጣኝነት ስራ የመጀመሪያው የበኩር ክለቡ ነውና…ይሄ ሁኔታ በውስጥህ ምን አይነት ስሜት ፈጠረ?

ፋሲል፡- …በእርግጥ በፊትም ቅ/ጊዮርጊስ እያለህ ዋና አሰልጣኝ ሆኜ የሰራሁባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ…ምናልባት ከአሁኑ ጋር ልዩነቱ አሁን ሙሉ ዋና አሰልጣኝ…ጊዮርጊስ እያለሁ ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ ተብዬ መጠራቴ…ካልሆነ በስተቀር፤አሁን በባህር ዳር በሙሉ ዋና አሰልጣኝነት ቡድኑን ይዤ መምራቴ በሙያዬ ይበልጥ ከፍ እያልኩ እያደኩ መምጣቴን ያሳያል፤ይሄ መሆኑ በራሱ ከፍተኛ የሆነ በራስ የመተማመን ስሜት በውስጤ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ በዚህ ደረጃ ራሴን የመፈተንና ራሴን በዚህ ቦታ የማግኘት ህልም ነበረኝ፤አሁን ያንን ህልሜን በባህር ዳር መኖር በመጀመሬ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ከለመድኩት ባህል በተለየ ሌላ ባህል፣ሌላ ታሪክ፣ሌላ ውጤትና ደጋፊ ባለበት ክለብ ውስጥ ራሴን ማየትና መፈተን እፈልግ ነበርና አሁን ራሴን በዚህ ደረጃ በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ…፡፡

ሀትሪክ፡- …በውጤትህም፣ እንደመጀ መሪያ የሙሉ አሰልጣኝነት ዘመንህም … ከባህር ዳር ጋር የተሻለ ተጉዘሃል ብሎ መናገር ይቻላል…፤…ካስመዘገብከው ውጤትና ካገኘኸው የመጀመሪያ ስኬት በመነሣት ለምን ዘገየሁ?ምነው ቀደም ብዬ ብወሰን ኖሮ…ብለህ ራስህን የወቀስክበት አጋጣሚ የለም…?

ፋሲል፡- …በዚህ ደረጃ ቁጭትም…ሆነ…ወቀሣ ውስጥ አልባባሁም…፤…መሆን በሚገባኝ፣ በፈለኩበት ጊዜ ነው ወደዚህ ኃላፊነት የመጣሁት፡፡ እኔ ረዥሙን የስልጣና ህይወቴን ቅ/ጊዮርጊስ ውስጥ በምክትል አሰልጣኝነት ያሳለፍኩበት ጊዜ ነው የነበረው፤ያ በምክትልነት የሳለፍኩት ጊዜ ደግሞ ለእኔ…ልክ ትልቅ ት/ቤት (ዩኒቨርሲቲ) ውስጥ እየተማርኩ ያሳለፍኩ ያህል ነው የሚሰማኝ፡፡ በጣም ትላልቅ የሚባሉ…የሀገርም ውስጥም ሆነ ኢንተርናሽናል ውድድሮች ላይ አንድ አሰልጣኝ ለመገኘት የሚመኘበት ቦታ ላይ ቡድኑን እየመራሁ ሁሉ ደርሻለሁ፤በጣም ትላልቅ የቻምፒዮንስ ሊግና የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድሮች ላይም ተሳትፊያለሁ…ቡድኑን ይዤም ቀርቤያሁ፡፡ እነሱን እድሎች ያገኘሁት በረዳትነት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በዋና አሰልጣኝነት በመሆኑ የትልቅ ት/ቤት (ዩኒቨርሲቲ) ያህል ተምሬበታለሁ፤ዕውቀትም ትልቅ ልምድንም አግኝቼበታለሁ፤ዋና አሰልጣኝ የሚለው ማዕረግ ቢቀርብኝም ዕውቀትም ልምድም እንዳገኝበት የረዳኝ ወርቃማ አጋጣሚ በመሆኑ ባለፉት ጊዜያት እንዳልከፋም ያደርገኛል፡፡ለዛሬው የሙሉ አሰልጣኝነቴም ሆነ ለቀጣይ አሰልጣኝነቴ ትልቅ ግብአት የሚሆነኝ ትምህርት አግኝቼበታለሁና በፍፁም አልቆጭበትም፤አሁን በአሰልጣኝነት በሁለት እግሬ እንድቆም የእርካብ ያህል የሆኑኝ እነዛ በረዳትነት ያሳለፍኳቸው ጊዜያቶች ናቸው፡፡

ሀትሪክ፡- …ስለዚህ በረዳት አሰልጣኝነት ያሳለፍኳቸው በርካታ አመታት ያልባከኑ በመሆናቸው አልቆጭም እያልከኝነው…?

ፋሲል፡- …ትክክል…!…እንዴት እቆጫ ለሁ …? …እኔ እንደውም ከመቆጨት ይልቅ ራሴን በጣም እድለኛ የሆንኩ ያህል እንዳስብ ነው የሚያደርገኝ…፤…ለዛሬው ማንነቴ ጥርጊያ መንገዱን የከፈቱልኝ እኮ በምክትል አሰልጣኝነት ያሳለፍኳቸው እነዛ መልካም የሚባሉ አመታት ናቸው፡፡ እነዛ ትምህርቶች ናቸው ለዛሬ አሰልጣኝነቴ ስንቅ ሆነው እያገለገሉኝ ያሉትና ለፀፀት የሚዳርገኝ አንዳች ነገር የለም፤ደግሞም ብዙዎቹን ነገሮች ያደረኩት አምኜበትና ፈልጌ ነው…ወደፊት መድረስ ለምፈልገው ግቤ ጉልበት ይሁኑኛል ብዬ አምኜና ፈልጌ ያደረኩት ነገር በመሆኑ ፀፀት ሣይሆን ደስታ ነው የሚሰማኝ፡፡

ሀትሪክ፡- …ፋሲል በሙሉ የአሰልጣኝነት ህይወቱ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅ/ጊዮርጊስን በተቃራኒ ሆኖ ነጥብ ለመንጠቅ ተፋልሟል፤ይሄ የሙያው ባህሪ ቢሆንም ፋሲልን ለዚህ ያበቃውን…ብዙ ታሪክና ድሎችን ያስመዘገበበትን ክለብ ሲገጥም ስሜቱ ምን ነበር? ከሌሎች ጨዋታዎችስ ተለይቶብህ ነበር…?

ፋሲል፡- …እውነቱን ለመናገር ያደክበ ትን፣ ብዙ ወርቃማ ታሪኮችን ያፃፍክበትን ክለብ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቃራኒ ሆኖ ሆኖ መግጠም የተለየ ስሜት እንዲሰማህ ያደርጋል፤ በአሰልጣኝነት ህይወቴ ጊዮርጊስን ነጥብ ለመንጠቅ በተቃራኒ ገጥሜ ስለማላውቅ እንደመጀመሪያ የሆነ የማላውቀው ስሜት ተሰምቶኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የሆነ የመጨናነቅ ስሜት ይፈጥርብሃል፡፡በሌላ በኩል ግን አንድ ደስ የሚል ስሜት በውስጥህ ሲመላለስም ይሰማሃል፤በምወዳቸው፣በጣም በማከብራቸው፣ስሳሣት አርመው፣ስጎበዝ አበረታተው ለዚህ ያደረሱኝ ደጋፊዎች ፊት ቡድን ይዤ ለዚህ ደረጃ በቅቼ በማየታቸው ትልቅ ደስታ እንዲሰማኝ አድርጓል፡፡ ግን ሁልጊዜ እንደምልህ አሰልጣኝነት የምወደው ሙያዬ /ፕሮፌሽኔ/ ነው፤የምወደውን ነገርና ሙያዬን /ፕሮፌሽኔን/ ለይቼ የማይ ሰው ነኝ፡፡ በተቻለኝ መጠን ለሙያዬ በጣም ታማኝ መሆንን…ለዛ መገዛትን ነው የማስቀድመው፡፡

ሀትሪክ፡- …የጣና ሞገድ ደጋፊዎች ይለያሉ…?

ክፍል ሁለት ይቀጥላል…….

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.