የካፍ ሻምፕየንስ ሊግ እና የካፍ ኮንፌዴሬሽን ፍፃሜ ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ስታድየሞች ታውቀዋል

 

በቀደሙት አመታት የካፍ የክለቦች ውድድር የፍፃሜ ጨዋታዎች በደርሶ መልስ ለፍፃሜ በቀረቡት ክለቦች ሜዳ የሚካሄድ ሲሆን የደርሶ መልሱ አሸናፊም የዋንጫው ባለቤት ይሆናል። ሆኖም ግን ይህ የደርሶ መልስ የፍፃሜ ጨዋታ በበርካታ አህጉራዊ ውድድሮች እየቀረ እየመጣ መሆኑ ይታወቃል። በቅርብ እንደምናስታውሰውም የደቡብ አሜሪካ ክለቦች የሚያደርጉት የኮፓ ሌቤርታዶሬስ ዋንጫ በደርሶ መልስ የሚያደርገውን የፍፃሜ ጨዋታ አስቀርቶ በ ፔሩ ኤል ሞነመንታል ስታድዮም ፍላሚንጎን እና ሪቨር ፕሌትን ያገናኘ ፍፃሜ ጨዋታ ማካሄዱ ይታወሳል።

የአፍሪካ እግርኳስን የሚያተዳድረው ካፍም በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊጉን እና የ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫውን ፍፃሜ ጨዋታ ያለደርሶ መልስ በአንድ ጨዋታ ብቻ በገለልተኛ ሜዳ የሚያካሂድ ይሆናል። በዚህም መሰረት የዘንድሮውን የቻምፕዮንስ ሊግ ፍፃሜ ጨዋታን እንዲያስተናግድ የተመረጠው በካሜሮን ድዋላ የሚገኘው ጃፓማ ስታድዮም መሆኑን ዛሬ ካፍ አሳውቋል። የቻምፕዮንስ ሊጉ የፍፃሜ ጨዋታ የሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንላ እና የግብፁ አል አህሊ አሸናፊ ከሞሮኮው ራጃ ካዛብላንካ እና ከግብፁ ዛማሌክ አሸናፊ መካከል እ.ኤ.አ ግንቦት 29 2020 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።

የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታን የሚያስተናግደው ደግሞ በሞሮኮ ራባት የሚገኘው ልዑል ሞሊ አብደላ ስታድዮም ሲሆን የፍፃሜው ጨዋታም የግብፁ ፓራሚድስ እና የጊኒው ሆሮያ አሸናፊ ከሞሮኮው አርኤስቢ ቤርካኔ ከሌላኛው የሞሮኮ ክለብ ሀሳኒያ አጋዲር አሸናፊ ጋር እ.ኤ.አ ግንቦት 24 2020 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል ።


 

የካፍ ቻምፕዮንስ ሊግ ፍፃሜ የሚካሄድበት የካሜሮኑ ጃፓማ ስታዲየም
የካፍ ቻምፕዮንስ ሊግ ፍፃሜ የሚካሄድበት የካሜሮኑ ጃፓማ ስታዲየም

የካፍ ኮንፌዴሬሽን ፍፃሜ የሚካሄድበት የሞሮኮው ልኡል ሞሊ አብደላ ስታዲየም
የካፍ ኮንፌዴሬሽን ፍፃሜ የሚካሄድበት የሞሮኮው ልኡል ሞሊ አብደላ ስታዲየም