የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር በዳኞች ላይ የሚፈጸመው ጉዳት እየተባባሰ መጥቷል በሚል ቅሬታ ሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ለሶስት ሳምንታት የትኛውንም ውድድር እንደማያጫዉቱ ባወጡት ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ አስታውቀው ነበር።
ይሁን እንጂ ማህበሩ ዛሬ በጁፒተር ሆቴል ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ባደረገው ውይይት “በማህበሩ አቋም መግለጫ የተነሱት ጥያቄዎች ከሞላ ጎደል ምላሽ በማግኘታቸው” ዳኞች ነገ ስራቸውን ለመጀመር መወሰናቸውን ገልጿል።
“ሁሉም የዳኞች ጥያቄ ባይመለሱም በውይይቱ ላይ በማህበሩ የቀረቡ ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ ሳይሆን በጊዜ ሂደት በፌደሬሽኑ የሚመለሱ መሆናቸው ከመግባባት ላይ መደረሱን” ማህበሩ አስታውቋል።
ዳኞች ውድድር እንደማያካሄዱ በመግለጻቸው ምክንያት የ23 ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አልተካሄደም።
የዳኞች ማህበር ሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ወደ ውድድር ለመመለስ 10 ቅድመ ሁኔታዎች እንዲተገበሩ አስቀምጦ ነበር። እነዚህም ከዚህ በታች የተጠቀሱት ናቸው።
በ2010 ዓ.ም የውድድር ዘመን የተጎዱ ዳኞች ተገቢው ካሳ እንዲሰጣቸው፣ ውድድሩን ከመጀመራችን በፊት በውድድር ደንቡ መሰረት የመድህን ዋስትና (ኢንሹራንስ) እንዲገባልን፣ ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ በሃገር ውስጥም ሆነ ውጭ ሃገር ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ፤
ከክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመግባባት የዳኞች ጥበቃ እንዲደረግ፣ በወንዶች እና በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ለመዳኘት በሚደረግ ጉዞ አውሮፕላን የሚደርስበት ቦታ ሁሉ የአውሮፕላን ትራንስፓርት እንዲመቻች፣ የአልቢትር እያሱ ፈንቴን ጉዳይ ጨምሮ ፖሊስ ያወቃቸው የስርዓት አልበኝነትና የመብት ጥሰቶች ተገቢውን የህግ ፍርድ እንዲያገኙ እንዲደረግ፤
ፌዴሬሽኑ ለዳኞች እና ለታዛቢዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያመቻች፣ ማህበሩ ያለአግባብ ለጠቅላላ ጉባኤ ያወጣው ወጪ በፌዴሬሽኑ በህጋዊ ደረሰኝ አማካኝነት እንዲመለስ፣ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎቹ አሰራር በግልፅ እንዲጠየቅ እና ተገቢው የህግ ከለላ በሌለባቸው ስታዲየሞች ውድድር እንዳይካሄድ የሚሉ ናቸው።
” ስሜታችንን ለተጋሩ የስፖርት ቤተሠብ፣ ክለቦች ሚዲያው፣ የማህበራችን አባላትን አመሰግናለሁ። ውድድሩ ከነገ ጀምሮ መካሄድ እንደሚጀምር አረጋግጣለሁ”
አቶ ትግል ግዛው
” ክስተቱ ሁሉም እግር ኳሳዊ ጉዞ በስርአትና በመመርያ መሰረት መካሄድ እንዳለበት አሳይቶናል። እኛም ያቆምነው ሰው እንዳይሞት አስበን ነው።ጸጥታውን በጋራ እንጂ በፖሊስ ብቻ አይጠበቅም። አሁን ግን ማህበሩ ጋር ስምምነት በማድረጋችን ከነገ ጀምሮ ውድድሮች የሚቀጥሉ ይሆናል”
ፕሬዝዳንቱ ጁነይዲ ባሻ

በስብሰባው ላይ ከየክልላቸው ተወከለው ከመጡ ዳኞችና ከፌዴሬሽኑ አካላት የተለያዩ አሳቦች ቀርበዋል ፣ከቀረቡት ሀሳቦች መካከል :-
👉”እናንተ አንድ ብትሆኑ እኛም አንድ እንሆን ነበር።
ከመቶ 25ቱ አልተመለሰም።የፌዴሬሽኑ ሳይሆን የኛ ጉባኤ ነውና እንደፈለኩ እናገራለው።በሰውነታችሁ አከብራለው ሃሳባችሁን ግን አናከብርም።

እድሜ ለአማራ ቲቪ ዳኛውን ሲያሯሩጡ አይተናል እናንተ ባታሳዩኝ። ከከፍተኛ ሊግ ማንን እንደሚያልፍ ተሰርቶ አልቋል። እንደ አዲስ አበባ ተወካይነቴ አልቀበልም”
አርቢትር አሰፋ ደቦጭ
👉”ኮማንድ ፖስቱ የተቋቋመው ለሁላችን ደህንነት ነው
ፌዴሬሽን ደግሞ በአቶ ጁነዲን የሚመራ ዳኛ የሚመድብ ኮማንድ ፖስት አቋቁሟል ይሄ ደግሞ ተገቢ አይደለም ። ቦታ እስኪያገኝ ድረስ ታግሎ ቦታውን ሲይዝ ባለሙያ የሚገድል ሰው አለ ተው
ሊባል ይገባል። ”
የማህበሩ ም/ል ፕሬዝዳንት ሚካኤል አርአያ
👉”የቀይ ካርድ ውሳኔን የሚያሽሩት አቶ አበበ ገላጋይ ናቸው”
ዳኞች ውሳኔ ለመወሰን የተቀመጡላቸው መስፈርቶች አሉ። ለምሳሌ ተጫዋች በጨዋታ ላይ ሲያጠፋ የሚሰጠው የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ ወይም ቀይ ካርድ ዳኛው ሲሰጥ የተቀመጡ መስፈርቶች አሉን።

በዚሁ ቢጫ ካርድ ወይም ቀይ ካርድ እንሰጣለን። ሆኖም ይህ አሰራር እየተሻረ ነው። እንዲያውም አንዳንድ ተጨዋቾች ቀይ ካርድ ስንሰጣቸው ችግር የለውም አንተ ቀይ ካርድ ብትሰጠኝ ነገ የሚያነሳልኝ አካል አለ” እያሉ ያፌዙብናል ይሄ ፌዝ ነው። ”
ኢ/ር አርቢትር ዳዊት አሳምነው
👉 ” አንቺ ከቦክስ ተረፍሽ እንዴ እየተባልኩ ነው ያጫወትኩት ይሄ መታረም አለበት ይሄ የተኩስ ማቆም ስምምነት ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ነው”
አርቢትር ማርቆስ
👉”ፌዴሬሽኑ 1+1=2 ነው እያለ አይደለም 1+1=2 ሊሆን ይችላል እያለን ነው። ይሄ ልክ አይደለም እኛ የምንፈልገው ድርድር አይደለም ጥያቄውን መልሱልን”
ኢ/ር ረዳት ዳኛ ክንዴ ሙሴ
👉 ” ይሄ መንግስታችን ነው ስፖርቱ የልማቱ አንዱ አካል ነው ያለው።መንግስትና ማህበራችን አድማ አይፈልጉም ሴትና ወንድ እኩል ነው እየተባለ መለያየት ተገቢ አይደለም”
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ትግል ግዛው
የኢትዮጵያ ዳኞችና ፌዴሬሽኑ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተክትሎ ኘሪሚየር ሊጉ በተስተካካይ ጨዋታዎች በቀጣይ ሳምንት ሲቀጥል ከዚህ በታች በተገለፀው መሠረት መርሐ ግብሮቹ እሚከናወኑ ይሆናል።

አስተያየት ይስጡ