የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

• ፌዴሬሽኑ የብር 2,000,000.00 (ሁለት ሚሊዮን ብር) ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉም በበኩሏ የብር 400,000.00 (አራት መቶ ሺህ ብር) ድጋፍ አድርጋለች፤

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወሰነው መሰረት ዛሬ መጋቢት 17/2012 ዓ. ም. በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽ/ቤትና በኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር በመገኘት ለህዳሴ ግድቡ ግንባታና ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ የሚውል የብር 2,000,000.00 (ሁለት ሚሊዮን ብር) ድጋፍ አድርጓል፡፡

በድጋፍ አሰጣጡ ወቅት በማስተባበሪያ ም/ቤቱ የተገኙት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀ/ም/ፕሬዝዳንት ክብርት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉና የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ሲሆኑ ፕሬዝዳንቷ ክብርት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ባስተላለፈችው መልእክት ፌዴሬሽናችን 9ኛ አመቱን ሊደፍን ጥቂት ቀናት ብቻ የቀሩትን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከመጀመሪያው ጀምሮ አትሌቶችንና የአትሌቲክሱን ቤተሰቦች በማስተባበር በቦንድ ግዢ፣ በስጦታ፣ ታላላቅ ሩጫዎችን በማስተባበር ከቲ-ሸርት ሽያጭና ከመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ገቢ በማስገባት ከመንግስት ጎን መሆኑን ሲያረጋግጥ እንደቆየ አመልክታለች፡፡

አሁንም ፌዴሬሽኑ ግንባር ቀደም በመሆን ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ መፋጠን ያግዝ ዘንድ፣ እንዲሁም ሌሎች አካላት በቡድንም ሆነ በግል የድርሻቸውን ይወጡ ዘንድ ይሄንን አርአያነት ያለው ተግባር ሲፈጽም በርካቶች ከጎናችን ይሰለፋሉ የሚል እምነት አለኝ፤ ካለች በኋላ ግድባችን አድዋችን በመሆኑ ድጋፋችን ቀጣይ ነው፤ ስትል አስረድታለች፡፡

ከዚህ ጋር በማያያዝ አቶ ቢልልኝ መቆያ የኢአፌ ጽ/ቤት ኃላፊ ባሰሙት ንግግር ፌዴሬሽኑ ከአሁን በፊት በብር 500,000.00 (አምስት መቶ ሺህ ብር) ቦንድ በመግዛት ቀዳሚ አጋርነቱን ያረጋገጠ ሲሆን ዛሬም ያው የቦንድ ግዢ በብር 500,000.00 (አምስት መቶ ሺህ ብር) እንዲቀጥል በስራ አስፈፃሚው መወሰኑንና ከዚህ ቀደም ፌዴሬሽኑ ከቲ-ሸርት ሺያጭ ብር 3,000,000.00 (ሶስት ሚሊዮን ብር) ለማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ገቢ ማድረጉን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከግንባታው ጋር በተያያዘ ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በግሏ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የብር 200,000.00 (ሁለት መቶ ሺህ ብር) ድጋፍ አድረጋለች፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ም/ቤት ጽ/ቤት ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሮማን ገ/ሥላሴ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምሳሌያዊ ተግባር በጣም አበረታች መሆኑን አስረድተው ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የም/ቤቱ አባል ከመሆኗም በላይ የክብር አምባሳደር መሆኗን ጠቁመው በእሷ የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከስፖርት ፌዴሬሽኖች፣ ተቋማትና ማህበራት ግንባር ቀደም በመሆን ለፈጸመው አኩሪ ተግባር ምስጋናዬ ከፍ ያለነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም አትሌቶች፣ የአትሌቲክሱ ቤተሰቦች፣ የሁሉም የስፖርት ተቋማት ይሄንን ፋና ወጊ ተግባር በመከተል የሃገር ወዳድነታቸውን በተግባር እንዲያስመሰክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተያያዘ ሌላ መረጃ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአለም አቀፍ ደረጃ ወረርሺኝ ተብሎ የተፈረጀውና የወቅቱ ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ በመከላከል ተግባር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወሰነው መሰረት የብር 1,000,000.00 (አንድ ሚሊዮን ብር) ድጋፍ ለኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር በዛሬው እለት አስረክቧል፡፡

ተቀ/ም/ፕሬዝዳንቷ ክብርት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በኢፌዲሪ ጤና ሚኒስትር ዋና መ/ቤት በመገኘት ድጋፉን ለክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር አስረክባለች፡፡ ኮማንደር ደራርቱ ከርክክቡ በኋላ ባስተላለፈችው መልእክት ማንኛውም ኢትዮጵያን እወዳለሁ የሚል ዜጋ በዚህ የጭንቅ ወቅት ከመንግስትና ከህዝባችን ጎን በመቆም ይሄንን አስከፊ ወረርሺኝ በሚችለው ሁሉ አግዞ ሊከላከል ይገባዋል ስትል ገልፃለች፤ አያይዛም መዘናጋት እንኳንስ ለእኛ ታዳጊ አገር ቀርቶ ለበለጸጉትም አስከፊ ውጤት ማስከተሉን በሚዲያዎች የምነሰማው የእለት ተእለት መርዶ ነው፤ ብላለች፡፡

አክላም ኮማንድር አትሌት ደራርቱ ቱሉ እኔ በግሌ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመከላከል የብር 200,000.00 (ሁለት መቶ ሺህ ብር) ለኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር ድጋፍ ማድረጌን ልገልጽ አወዳለሁ ካለች በኋላ ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ በዚህ ወቅት በጋራ እንዲረባረብና ወረርሺኙን እንድንመክት ያስፈልጋል፤ በማለት ጥሪዋን አስተላልፋለች፡፡

ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር በበኩላቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ወሳኝ ሰዓት ከጎናችን በመሆን ላሳየው አብሮነት እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፣ ፌዴሬሽኑ በማንኛውም ሁኔታ ከመንግስት ጎን በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝ ግልፅ ነው፤ ያሉት ዶ/ር ሊያ … ክብርት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በግሏ ብር 200,000.00 (ሁለት መቶ ሺህ ብር) ያበረከተችው ድጋፍ አስደናቂ ከመሆኑም በላይ ፈር ቀዳጅና የሚመሰገን ተግባር እንደሆነ አመልክተው ድጋፉ ሁሉንም ዜጋ አሳታፊ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

Via- #የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን

Hatricksport website Editor

Twitter

kidus Yoftahe

Hatricksport website Editor