የኢትዮጵያ ኘሪሚዮር ሊግ ለመጨረሻ ጊዜ በ22ኛው ሳምንት አዲስአበባ ላይ መከላከያ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በተገናኙበትና ፍፃሜውን ሳያገኝ በሁከት በተጠናቀቀው ጨዋታ መነሻነት ውድድሩ ተቋርጦ የሰነበተ ቢሆንም ዛሬ በአዲስአበባና ክልል ላይ በሚካሄዱ ተስተካካይ ጨዋታዎች ይጀምራል፡፡
የኢትዮጵያ ኘሪሚዮር ሊግ ከሁለት ሳምንታት መቋረጥ ቆይታ በሇላ በተስተካካይ ቀሪ ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምር አዲስ አበባ ላይ ኢትዮ ኢሊክትሪክ በሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲያስተናግድ አዳማ ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲዮም አዳማ ከተማ በሜዳው ወላይታ ድቻን ይገጥማል፡፡በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም አዲግራት ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩ/ቲ ከ መቀለ ከተማ ያገናኘውና ሳይጠናቀቅ ተቋርጦ ቀሪ 45ደቂቃው በይደር ተይዞ የነበረውና በገለልተኛ ሜዳ ዛሬ ሽረ ላይ እንደሚካሄድ መርሃ ግብር በፌዴሬሽኑ የተያዘለት ጨዋታ ከፀጥታና ሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች በተገናኘ ጨዋታው ላይካሄድ እንደሚችል የተነገረ ቢሆንም ሁለቱም ቡድኖች ወልዋሎና መቀለ ከተማ ወደ ሽረ መግባታቸው ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲዬም ከቀኑ 10:00 የሚጀምረው የኢትዮ ኢለክትሪክና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ውጤቱ ለሁለቱም ቡድኖች ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅጉን ያስፈልጋቸዋል፡፡ኢትዮ ኢሊክትሪክ አሁን ካለበት የወራጂ ቀጠናው አፋፍ ላይ ረግቶ ለመቆየትም ቢሆን ውጤቱ አስፈላጊ ነው፡፡በተለይም በወራጂ ቀጠናው የሚገኙት አርባምንጭከተማና ድሬድዋ ከተማ እንዲሁም 13ኛ ደረጃ ላይ ያለው ወልዋሎን ጨምሮ ተስተካካይ ቀሪ ጨዋታ ያላቸው መሆኑ ኢሊክትሪክ እራሱን ከወራጂ ቀጠናው አፋፍ ላይ ለማቆየት ከዚህ ጨዋታ ውጤት ማስመዝገብ የሚጠበቅበት ሲሆን ፈረሰኞቹ በበኩላቸው ከሊጉ መሪ ጅማ አባጅፋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ከማጥበብም ባሻገር በቀጣይ በሌላ ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታ የሊጉን መሪነት ከጅማ አባቡና ለመረከብ ዛሬ የግድ ጨዋታውን ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ኢሊክትሪክ በ21ነጥቦች ካለበት 12ኛ ደረጃ ጨዋታውን ቢያሸንፍም እንኳ ደረጃውን የሚያሻሽልበትና ከፍ የሚልበት ዕድል ባይኖርም ወራጂ ቀጠና ከሚገኙት ክለቦች ያለውን የነጥብ ልዩነት ለጊዜውም ቢሆን የሚያሰፋበት ዕድል ለማመቻቸት የሚጫዎት ሲሆን ፈረሰኞቹ ነጥባቸውን ከ33 ወደ 36 በማድረስ ከመሪው ያለውን የነጥብ ልዩነት ከወዲሁ ወደ 3 ለማጥበብ ትኩረት ሰጥተው ይጫዎታሉ፡፡
አሁንም በዋንጫ ፍክክሩ ውስጥ የሚገኘው አዳማ ከተማ በሜዳው ከወላይታ ድቻ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ሌላኛው ተጠባቂ ጨዋታ ነው፡፡አዳማ ከተማ የመጨረሻ ጨዋታውን ጎንደር ላይ ከፋሲል ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ሲመለስ ወላይታ ድቻ ከሜዳው ውጭ ወደ መቀለ አምርቶ በባለሜዳው መቀለ ከተማ ሽንፈት አስተናግዶ ለዚህ ጨዋታ ሲቀርብ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካኘ አዲስ ታሪክ ሲያፅፍ ቁልፍ ተጨዋች የነበረው ግብ ጠባቂው ወንደሰን ገረመው በክለቡና በተጫዎቹ በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ዛሬ እንደማይሰለፍ ይጠበቃል፡፡
አዳማ ከተማ ይህን ጨዋታ አሸንፎ ነጥቡን ከ33 ወደ 36 አድርሶ በሰንጠረዡ የፈረሰኞቹን ውጤት ጠብቆ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ የሚልበትን አጋጣሚ ለማግኘት በሜዳው ድቻን የሚፋለም ሲሆን ወላይታ ድቻ ከዚህ በሇላ ወደ ዋንጫ ፍክክሩ ይመለሳል ባይባልም መሪዎቹን ተጠግቶ ለማጠናቀቅ ዛሬ ባለሜዳውን አዳማ እንደሚፈትን ይጠበቃል፡፡ወላይታ ድቻ በ27 ነጥቦች በሰንጠረዡ 9ኛ ደረጃ ተቀምጧል፡፡
አስተያየት ይስጡ