“የኢትዮጵያ ተጨዋች አንገት የሚደፋበትና የሚበደልበት ዘመን መብቃት አለበት” ሚካኤል ጆርጅ /አዳማ ከተማ/

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ አኩራፊ ስትሆን ታሳምፃለህ ይባላል ዝም ስትልም ሞራልና ፍላጎት የለውም ይሉሃል

“የኢትዮጵያ ተጨዋች አንገት የሚደፋበትና የሚበደልበት ዘመን መብቃት አለበት”
ሚካኤል ጆርጅ /አዳማ ከተማ/

2000 ዓ.ም በኛ የሚሊኒየም አቆጣጠር የተጨዋቹ እድሜ 17 ነበር… ያኔ የሙገር ወጣት ቡድን አባል ሆኖ እግር ኳስን በክለብ ደረጃ ጀመረ፡፡ በ2001 18 አመት ሲሞላው ለሙገር ዋናው ቡድን በመሰለፍ የእግር ኳስ ተጨዋችነት ትልቁን ጅማሮው ሀ ብሎ መጓዝ ጀመረ፡፡ ከሙገር የሶስት አመት ቆይታ በኋላ ለሲዳማ ቡና፣ ለደደቢት፣ ለዳሽን ቢራና አሁን ደግሞ ለአዳማ ከተማ በመሰለፍ ትልቅ አቅሙን እያሳየ ይገኛል፡፡ ተናጋሪ ወይም አንደበተ ርቱዕ የሚባል ነው፡፡ በግልፅ ወይም በድፍረት ይናገራል፡ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ምን ያላነሳው ጉዳይ አለ?… ስለ ሙገር መፍረስ፣ ስለ ጥምር ሙያው፣ ስለባህሪው፣ ደደቢትን ለቆም ወደ ሲዳማ ቡና ለምን እንደሄደ፣ ጉቦ ጠየቀኝ ስላለው አሰልጣኝ፣ በቦታው ምርጡ ስለሆነው ተጨዋች፣ በአዳማ ለምን እንደቀጠለ፣ ስለብሔራዊ ቡድኑ እየሠራ ስላለው በጎ ተግባርና መሰል ጉዳዮች ድፍረት የተሞላው ምላሽን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡-የደሴ /ወሎ/ ቆንጆ ሲባል ለሴቶቹ ነው… አሁን ግን ለወንዶቹ ለነሚኪ ሆነ አሉ ትቀበለዋለህ?
ሚካኤል፡- /ሳቅ በሳቅ/ መገለጫው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ውበት መገለጫ ነው፡፡ እውነት ነው አብዛኛው ሰው ወሎ የቆንጆ ሀገር ነው ይላል… ለማንኛውም ከተሰጠኝ እቀበላለሁ /ሳቅ በሳቅ/
ሀትሪክ፡-ያደከው በሙገር ቤት እንደመሆኑ መፍረሱ አልከፋህም?
ሚካኤል፡- ሁለት ሶስት ጊዜ የመፍረሱን ነገር አስቤ ቅር ብሎኛል ሙገር በወረደና በፈረሰ ሰአት አብሬ አልነበርኩም.. በሙገር የእናትና የአባትህ ቤት ያህል ነው የሚሰማህ…. የፉገራ ወይም የማስመሰል ነገር የለም ከቤቴ ወጥቼ በ17 አመቴ ተቀብለው አሰድገው 3 መት ዋናው ቡድን ውስጥ እንዳገለገል አድርጎኛል፡፡ ሙገር የእግር ኳስን የህይወትንና የገንዘብን ትርጉም ያሳወቀኝ ክለቤ ነው፡፡ 100 ብርም ሆነ 100 ሺህ ብር ያወኩበትም ክለብ ነው፡፡ ከእኔ በፊት ብዙ የድሃ ልጆች ሀብታም ሆነዋል ስነ ምግባር ያልነበራቸው በስነምግባር ታንፀዋል ከኛ ከነሳላዲን ሰይድ ከነ አቤጋ በፊትም ብዙዎች በሙገር ተጠቅመዋል ይሄ ምርጥ ክለብ መፍረሱ በጣም ያሳምማል በጣም….


ሀትሪክ፡-ከሙገር በፊትም በኋላም ሌሎች ክለቦች ፈርሰዋል.. ምንድነው ምክንያቱ ትላለህ?
ሚካኤል፡- ትልቁ ችግር የማኔጅመንት የሰዎች መቀያየር ችግር ይመስለኛል፡፡ በ11 አመት ውስጥ ያየሁት እግር ኳስን የሚጠላ አመራር ከመጣ ኳሱ ይሞታል የሚወድ ከሆነ ግን እድገቱ ይታያል ለኔ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚመራው በግለሰቦች እንጂ በተቋማዊ ደረጃ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቁ ችግር ክለቦቻችን የተመሠረቱት በግለሰቦች ፍቃድ እንጂ በተቋማዊ መስመር አለመሆኑ ነው፡፡ ሰዋዊ ሂደት ያለባቸው ክለቦች ናቸው ያሉት፡፡ ትልልቅ ፋይናንስ ያላቸው እነ ጊዮርጊስም ቢሆኑ ሰዋዊ እንጂ ተቋማዊ አደረጃጀት የላቸውም እነ ሙገርም የተቸገሩት በዚህ ነው በሙገር በ2001 ከማደጌ በፊት የነበሩ የክለቡ ፕሬዚዳንቶች በኳስ ፍቅር ያበዱ በኳሱ የተለከፉ ትልቅ በጀት ለቢ ቡድኑ የሚበጅቱ ከዋናው ቡድን በላይ ድጋፍ የሚደረግለት ቡድን ነው፡፡ እንደተቋም አለመመራት የኳሱ ችግር ሆኗል፡፡ ኳስ የሚወድ ከንቲባ ከመጣ ያለበት ቡድን ስኬታማ ይሆናል ኳስ ከጠላ ደግሞ በዚያው መጠን ይወርዳል፡፡ አዳማን ብታይ ኳስ የሚወድ ከንቲባ ሲመጣ የ3 እና 4 አመት ውጤት አሪፍ ይሆናል፡፡ ከንቲባው ኳስ ካልወደደ ደግሞ የክለቡ ውጤት ይታሞታል ሙገርኮ አንድ ፕሬዚዳንት መጣ… አፈረሰው ያነው ትልቁ ችግር… መታረም ካለበት አደረጃጀቱ ተቋማዊ መሆን አለበት፡፡
ሀትሪክ፡-የአንተ ዋጋ ከ50 ሺ ብር በላይ አይብለጥ የሚል ሕግ ወጥቷል… ምን ተሰማህ ?
ሚካኤል፡- እጅግ በጣም ያንሰኛል፡፡ እግር ኳስ መዝናኛ ነው አለም ላይ ገደብ የሌለው ክፍያ ነው የሚከፈለው… እንደ ሌሎቹ የአውሮፓ ክለቦች ክፍያ እንፎካከር አላልኩም የነርሱን ያህል አቋም ስለማናሳይ /ሳቅ/ ነገር ግን እግር ኳስ ተጨዋች ለማኝ የሚዋጣለት የሚሰበሰብለት መሆኑ ግን መቆም አለበት፡፡ በዚህ ረገድ በሀገራችን አብዮት የፈነጠቁት ኮ/ል አወል አብዱራሂም ይመስሉኛል፡፡ ከኮ/ል በኋላ ብዙ ነገር ተለውጧል ተጨዋቾች መሬትና ቤት ኖሯቸዋል፡፡ የሚመኙትን ትዳር መያዝ ችለዋል፡፡ ጥሩ ሰብሰበዋል አጊጠዋል ኳስ አቁመውም ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ ይሄ ደግሞ የዘለቀው ግን ለ4 ወይም ለ5 አመት ብቻ ነው ከዚያ በኋላ ባሉት ጥቂት አመታት የተጨዋቹ ህይወት መቀመቅ ነው የገባው፡፡ ከ2003 በኋላ ነው የፊርማ ክፍያ ጣራ የነካው እስከ 2007 የነበሩ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ አንድ ሰው በሙዚቃ በፊልም ህብረተሰቡን ሊያዝናና ይችላል እግር ኳስም የደስታና የእብደትም የሁሉም ነገር ምንጭ ነው እንዴት ይገደባል? የምስማማው ክፍያው በብቃት ይሁን ከተባለ ነው፡፡ ሁሉም 200 ሺህ ብር ሊከፈለው አይችልም፡፡ 29ኙ 50 ሺ ብር ተከፍሏቸው አንዱ 200 ሺ ብር ሊከፈለው ይችላል በብቃትህ ልትለካ ትችላለህ እንጂ ገደብ አይደረግለትም ልክም አይደለም፡፡ አሰልጣኙ ፕሬዚዳንቱ በአጠቃላይ ማኔጅመንቱ የሚገባህ ይህን ያህል ነው ይላሉ እንጂ ድንገት ተነስቶ ገደብ ማበጀት አይገባም፡፡ ይሄ ሕግ ሲወጣ ምን እንዳሰቡ አልገባኝም አሳፋሪ ርምጃ ሆኖብኛል፡፡

ሀትሪክ፡-የሞግዚቷ ልጆች ፊልም ላይ ተውነሃል ጥሩ ምላሽ አገኘህ?
ሚካኤል፡- ጊዜው 2005 ይመስለኛል፡፡ በትምህርት ወይም በትልቅ ፍላጎት ያገኘሁት አይደለም፡፡ 2005 ኢንተርኮንቲኔታል መጥተው ነው ያገኙኝ፡፡ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ተመርጬ ኢንተርኮንቲኔታል ሆቴል ነው ያረፍነው፡፡ ትልልቅ ተጨዋቾችን ካስት ሊያደርጉ መጥተው ነው እኔን ያገኙኝ በጣም ከባድ እንደሆነ የሙሉ ጊዜ ስራዬና እረፍት እንደማይኖረኝ ነገሩኝ ግን እግር ኳስ ተጨዋች መሆኔ እንቅልፌ አንድ የሰራ አይነት መሆኑን አስረድቼ ክረምት መጥቶ እስክሰራ ድረስ ወደ 6 ወር ታግሰውኛል፡፡ ክረምት ላይ ፊልሙ ተሰርቶ ለተመልካች ቀርቧል፡፡ እንደ መጀመሪያ ፊልም ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- የጋዜጣው ባለቤት ይስሀቅ በላይ ይባላል መኪናው ተበላሽቶ አንተ ጋር ማሰራት ፈልጓል መቼ ልቅጠረው?
ሚካኤል፡- /ሳቅ በሳቅ/ የጋራጅ ባለሙያም ነህ ወይ እያልከኝ ነው /ሳቅ/ አዎ በጣም ጎበዝ ባለሙያ ሆኜ ያደኩበት የቤተሰብ ስራ ነው፡፡ ደሴ ውስጥ ጆርጂዮ ጋራጅ የሚባል ታዋቂ ጋራዥ አለ… እንደ ተሻለ ጋራዥ ደሴም ጆርጂዮ ጋራዥ ተብሎ የሚጠራ አካባቢ አለ፡፡ አባቴ ደሴ ውስጥ ብዙ ሜካኒኮችና ባለ ጋራዦች ያፈራ ነው፡፡ በ1953 ከባርኔሮ ጋር ሒልተንን ሰርቷል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በብረት ስራው በብየዳ ሰርቷል፡፡ ተንዳሆ እርሻ ልማትን ለ10 አመት ያህል ቴክኒካል ዳይሬክተር ሆኖ ሰርቷል፡፡ ወንድሜ ትልቅ ሜካኒክ እና ባለጋራዥም ነው በመሀል ያላቸው እህቴ ብቻ ናት ብረት ያልነካችው፡፡
ሀትሪክ፡-ተጨዋች ባትሆን ልትሰማራ የምትችልበት ስራ የጋራዥ ባለሙያ ወይስ ተዋናይ?
ሚካኤል፡- ያለ ጥርጥር የትልቅ ጋራዥ ባለቤትና ባለሙያ እሆን ነበር፡፡ ርክክቡ የተደናቀፈው በኔ ኳስ መውደድ ምክንያት ነው ወንድሜ ወደ ጣሊያን ተጉዞ ኑሮውን ሲመሰርት ከእህቴ ውጪ ያለሁት እኔ በመሆኔ ተረካቢ የመሆን እድል ነበረኝ፡፡ ነገር ግን በኳስ ፍቅር መለከፌና ርክክቡን ባለመቀበሌ ጋራዡ ወደ ሌላ ሰው እንዲተላለፍ አድርጓል፡፡ ይህ ባይሆን 100 ፐርሰንት በጋራዥ ባለሙያነት እሰማራ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡-በእግር ኳስ ህይወትህ ትልቅ ባለውለታ ነው የምትለው አሰልጣኝ አለ?
ሚካኤል፡- አዎ ትልቁ ባለውለታዬ አቶ አዳነ ናቸው በመቀሌ ከ17 አመት በታች ቡድን ውድድር ላይ የአማራ ክልልን ወክዬ ስጫወት አይተው አምነውብኝ ወደ ኳሱ መስመር ያስገቡኝ ሰው ናቸው አሰልጣኝ ግርማ……………ደግሞ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገውልኛል ብዬ አምናለሁ፡፡ በኔ በትልቁ የሚመሰገኑ ባለሙያዎች ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡-ተግባቢነትና ተጨዋችነት ባህሪህ ከየት መጣ?
ሚካኤል፡- ከቤተሰብ ይመስለኛል፡፡ እኔ የመጨረሻ ልጅ ነኝ እህቴ ስታገባ እኔ የ5ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ፡፡ ወንድሜም ሲያገባ የ7ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ፡፡ በጊዜ ነው ወደ ትዳር የገቡት የኛ ጋራዥ ትልቅ ነው የምንኖረው እኔ አባቴና እናቴ ብቻ ነበርን የሰፈር ልጅ እኛ ቤት ውሎ ቢያድር ቁጣም ግርፊያም አይደርስበትም ያደኩት እንዲህ ነው ብቻዬን መብላትና መጠጣት አልችልም፡፡ ሰፈሬ ውስጥ ብዙ ወንድሞች አሉኝ የቅርብ ጓደኞቼ 2 ወይም 3 ብቻ አይደሉም ብዙ ናቸው፡፡ ከደሴ ወጥቼ አዲስ አበባ ስገባ የተረከበኝ ሙገር ነው ይሄ ቡድን ደግሞ ቤተሰባዊነት የገነነበት ክለብ በመሆኑ አሁን ድረስ ያለው ባህሪዬ የቀጠለው በዚህ መልክ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-እድሜው የጨመረ ይመስለናል፡፡ ትልልቅ ሰው ሳይቀር አስታራቂ ሽማግሌ ነው አሉኝ እውነት ነው?


ሚካኤል፡- /ሳቅ/ 2008 ላይ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ሲኒየሮች ወደፊት ሁኑ ሲል እድሜዬን የሚያውቁት እነ ታፈሰ ተስፋዬ ይስቁ ነበር ብዙ ሰው የምገኝበት ቦታና የማወራቸውን ሰዎች ሲያዩ ይገረማሉ፡፡ የኖርኩት ህይወቴ ነው አስቤው ትልቅ ሰው ለመሆን ብዬም አይደለም የመጣሁበት አመጣጥ ነው እናቴም ከእድሜህ ትንሽ ፈጣን ብለሃል ትለኛለች…. ህይወት ራሷ ያደረገችው ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ለደደቢት ፈርመህ በ1 ወር ውስጥ ተለያያችሁ ለምን ይሆን?
ሚካኤል፡- በሙገር ለ3 አመት ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡ 2002 የ1 አመት ኮንትራት እየቀረኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈለገኝ፡፡ አሰልጣኙ ሚቾ ነበር እርሱ ሲለቅ የተኩት የጣሊያኑ አሰልጣኝ መረጃ ነበራቸውና ፈልገውኝ ሊወስዱኝ ለሙገር 60 ሺ ብር ይከፈል ሲባል አሰልጣኝ ግርማ ቡድኔን የገነባሁት በእርሱና በወንድሜነህ ላይ ስለሆነ አለቀውም አሉኝና የግድ ውሌን ጨረስኩ…. ከዚያ በኋላ በርካታ ክለቦች ፈልገውኝ አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ አሳመነኝና ለደደቢት ፈረምኩ፡፡
ሀትሪክ፡-ታዲያ ምን ተፈጠረ?
ሚካኤል፡- ለ2004 ውድድር ለደደቢት በ160 ሺ ብር ፈረምኩ፤ልጅ ነው የተሰጠው ብር ግን ብዙ ነው አሉና 160 ሺ ብር ላይ 10 ሺ ብር ጨምረን ውልህን ለ3 አመታት አድርገው ሲሉኝ አልተቀበልኩም፡፡ በተለይ ከአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ጋር ተከራክሬ ባለመስማማቴ ለቀብድ የተሰጠኝን 10 ሺ ብር መልሼ በቀጥታ ለሲዳማ ቡና ለ2 አመት ለመጫወት 250 ሺ ብር ፈረምኩ፡፡ ከደደቢት በአሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ ወደ ሚሰለጥነው ሲዳማ ቡና ተጓዝኩ፤በኳስ ተጨዋችነቴም ዘመን ሲበዛ ደስተኛ የነበርኩበት ክለብ ሲዳማ ቡና ነው 2004 እና 2005 ለብሔራዊ ቡድን የተጠራሁበት በግብ አግቢነት ከጌታነህ ከበደና ዳዊት ፍቃዱ /አቡቲ/ ጋር አንገት ለአንገት የተናነኩበትም አመት ነው… በደረሰብኝ የትከሻ ጉዳት 7 ጨወታ አልተጫወትኩም፡፡ ጌታነህ በ21 ግብ ዳዊት በ20 እኔ በ13 ግብ ከ1-3 ያለው ደረጃ ይዘን አጠናቀናል፡፡ ደስተኛ የሆንኩበት ጊዜዬ ያኔ ነበር… ጊዮርጊስና ቡናን ጨምሮ በርካታ ክለቦች ላይ ግብ ማስቆጠር ችያለሁ፡፡ ከ13ቱ ግቦች በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠርኩት አንድ ግብ ብቻ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- በተጨዋችነት ዘመንህ ጉቦ የጠየቀህ ደላላ ወይም አሰልጣኝ አለ?
ሚካኤል፡- በ2004 ሲዳማ ቡናን ያሰለጠነ አሰልጣኝ ነው 2004 ላይ ለነበረው ይሄው አሰልጣኝ በ250 ሺ ብር ፈርሜ ለ9 ጨዋታ ያህል ሜዳውን አላየሁትም…ምክንያቱንም አላወኩትም፤አንድ ተጨዋች ግን የፈረምነው ሰባታችንም ገንዘብ ሰጥተናል አንተም ለአሰልጣኙ ስጠውና ተጫወት አለኝ…እኔም እንቢ አልሰጥም አልኩ፤የክለቡ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ሳሳሞ ልጄ ብሎ ነው የሚጠራኝ ለአሠልጣኙ “ይሄን ልጅ አስገባው እንጂ” ሲለው ነው የገባሁት፡፡ የመጀመሪያ ጨዋታ ከሙገር ጋር አድርጌ ግብ አገባሁ…በቀጣዩ የአዳማ ጨዋታ ላይም አገባሁ…ሀዋሳ ላይም በተከታታይ ለሶስተኛ ጊዜ ግብ አገባሁ…በዛው አመት ውድድሩ ከመጠናቀቁ 4 ጨዋታ በፊት አሰልጣኙ መልቀቂያ አቅርቦ ተሰናበተና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ተተካ፤ይህ ጊዜ ገና በ21 አመቴ ኳስን የጠላሁበትና ወደ ጋራዥ ስራ ልመለስ ሁሉ ያሰብኩበት ትልቅ ጠባሳ የጣለብኝ በመሆኑ መቼም አልረሳሁም፡፡
ሀትሪክ፡- በተጨዋችነት ዘመን በቦታህ ምርጡ አጥቂ ማነው?
ሚካኤል፡- ከሀገር ውስጥ የምወደውና የማደንቀው ሲጫወትም የሚያደስተኝ ሳላሀዲን ሰይድ ነው፡፡ ከውጪ የሊቨርፑሉ ሮቤርቶ ፊርሚኖ ነው፡፡ በ9 ቁጥር ቦታ ለኔ ምርጡ እርሱ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የሊቨርፑል ደጋፊ ነህ?


ሚካኤል፡- አይደለሁም የማን.ዩናይትድ ደጋፊ ነኝ
ሀትሪክ፡- በዩናይትድ ውስጥ ምርጥ አጥቂ የለም ?
ሚካኤል፡- ከማን.ዩናይትድ በአሁኑ ሰዓት የሚያረካኝ አጥቂ የለም በተለይ በ9 ቁጥር ቦታ ላይ አላየሁም፡፡
ሀትሪክ፡- በአዳማ ውልህን ያራዘምከው ሌላ ክለብ ጠፋ ወይስ?
ሚካኤል፡- ሌሎች ክለቦችም ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከህይወቴ ተምሬ ውል ማደስ ችያለሁ፡፡ በተጨዋችነት ዘመኔ በ10 አመት ውስጥ 5 ክለብ አይቻለሁ አንድ አመት የቆየሁበት 4 አመትም ያሳለፍኩበት ክለብ አለ፡፡ በህይወቴ ትልቁ ስህተቴ ሲዳማ ቡናን ለቅቄ ለደደቢት መፈረሜ ነው፡፡ ትልቁን የፊርማ ብር 650 ሺ ብር ወስጄ ፈረምኩ፡፡ ይህን ብር ሲዳማ ቡና አቅርቧል፡፡ ነገር ግን ፕሮፌሽናል የመሆን የመታየት እድል ደደቢት ጋር አለ ብዬ የሊጉ ሻምፒዮን በመሆናቸው በአፍሪካ መድረክ የመካፈል እድላቸውን አይቼ ለደደቢት መፈረሜ ትልቁ ስህተቴ ነበር፡፡ ነገር ግን በሲዳማ ቡና መቆየት ነበረብኝ፡፡ ብዙ ታሪክ የሰራሁት ቡድኑ በኔ እስኪገነባ ድረስ ተፈላጊነቴ የጨመረበትን ሲዳማ ቡናን መተዌ ልክ አልነበረምና ከዚህ ተምሬ ለአዳማ ውሌን አራዝሚያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-ብዙ ተጨዋቾችኮ ለቀዋል…የክፍያው ጥያቄ ተመለሰ ወይስ?
ሚካኤል፡- በአዳማ የተበላሹ ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ ክፍያም ላይ ሆነ አመራር ላይ ችግር ነበር ከዚህ በፊት የነበረው ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ ይባላል፡፡ እንደ ላቲን ሀገር እንደ ብራዚል ፕሬዚዳንቶች በእግር ኳስ ያበደ ኳስን ከልቡ የሚያፈቅር የሚወድ በጣም የተሳካለት መሪ ነበር፡፡ ክለባችን 2ኛ ወጥቶ 180 ሺ ብር የሸለመ ቡድን ነበር አዳማ… 3ኛ ወጥተን 80 ሺ ብር የተሸለምንበት ጊዜ ነበር፡፡ እሁድ ተጫውተን ሰኞ ጠዋት የክለቡ የቡድን መሪ ኢንሴቲቫችንን በቦርሳ ይዞ ይመጣ ነበር እስከ 2009 ግማሽ ድረስ… ከዚያ በኋላ የአቶ አለማየው መነሣት የከንቲባዎች መቀያየር ችግር ፈጠረ፡፡ በ5 አመት ውስጥ በአዳማ 6 ወይም 7 ከንቲባዎች ተቀያይረዋል፡፡ የነርሱ መቀያየር ትልቅ ችግር ፈጥሯል፡፡
ሀትሪክ፡-አሁን ክፍያው ተፈፀመ ወይ እያለኩህ ነው?
ሚካኤል፡- /ሳቅ/ የ6 ወር ደመወዝ ነበረባቸው፡፡ የሁለት የሁለት ወር አድርገው ከፍለው አሁን ያለባቸውና ያልተከፈለን የአንድ ወር ብቻ ነው፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንታችን አቶ ገመቹ ኳስ በጣም የሚወድ ሰው ነው ረጅም ሰዓት ቁጭ ብለን አውርተን ተስማምተናል፡፡ አቶ አለማየሁ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሆኖ ተሹሞ ወደ ደብረዘይት መጥቷል፡፡ ከርሱ ጋርም በመነጋገር ክለቡን ለቅቆ ባለመሄድ ውሌን ልፈርም ላድስ ችያለሁ፡፡ እንደ ተጨዋች ብቻ ሣይሆን ከሱሌይማን መሀመድ ጋር ክለቡን እንደምመራ እንደምጠቅም ተነጋግረን ውላችንን አድሰናል፡፡
ሀትሪክ፡-የወጡት ወደ 9 የሚጠጉ ተጨዋቾች ያለ ውላቸው የተቀጡኮ አሉ፡፡ 150 ሺ ብር ፈርመው 34 ሺ ብቻ የሚከፈላቸው ነበሩ.. ይሄ አያሰጋም?
ሚካኤል፡- በአዳማ ከተማ የገንዘብ ጥያቄ አሁንም አልተመለሰም ቀድመው የፈረሙት ውል ያላቸው ከ50 ሺህ ብር በላይ አይቻልም የሚለው ሕግ ከመውጣቱ በፊት 100 ሺ ብር በላይ የሚካፈላቸው የነበሩ ተጨዋቾች አሁን ሲከፈላቸው የነበረው 34ሺ ብር ብቻ ነው ይሄ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን በ34 ሺ ብር ለፈረምን ለእኛ ያላባቸው የ1 ወር ደመወዝ ብቻ ነው ይህም ይስተካከላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- የአዲስ ቡድን ግንባታው ከባድ አይሆንባችሁም?
ሚካኤል፡- ስለ እውነት ለመነጋገር ከባድ ነው፡፡ እነዳዋ፣ በረከት፣ ቡልቻ፣ ከነአን፣ ምኞት ፣ እነ ጃኮ ፔንዜን ማጣት ከባድ ነው እንደ ቤተሰብ ነው ላለፉት 4 አመታት አብረን የኖርነው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የገነባው ቡድን ነው… ይሄን አዲስ ቡድን አፍርሶ የመገንባት ሥራ ነው የሚጠብቀን፡፡ ከእኛ ከሲኒየሮቹ ጋር እንዲሁም ከቢ ቡድን የመጡ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች ጋር ቡድኑን ተፎካካሪ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ አዳማ ትልቅ ቡድን ነው በተፈጠረው ነገር የመጣውን ሂደት አልፈን ተፎካካሪ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ አዲሶቹ አመራሮችና ከንቲባዎች ይህን ክለብ ማገዝ ይኖርባቸዋል እላለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-ስለ ደጋፊውና ክለቡ የምትለው ነገር አለ?
ሚካኤል፡- ክለቡ የከተማው ምልክት ነው ለናዝሬት ልጅ ህይወቱ ነው ክለቡ.. ለደጋፊው ክብር ሊሰጥ ይገባል ኢትዮጵያ ውስጥ ጥሩ ደጋፊ ካላቸው ክለቦች መሀል አንዱ አዳማ ነው ልምምድ ስንሰራኮ 200 እና 300 ሰው ነው የሚመለከተን…. ሰው የሚውለው ጊዜውን የሚያጠፋው በዚህ ቡድን ላይ ነውና ማገዝ አለባቸው ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡-ስለ ብሔራዊ ቡድን እናውራ…. ትጠራለህ ትቀነሳለህ…. እንዴት አለፍከው ስሜቱን?
ሚካኤል፡- የሚገርመው ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠራሁት በ2005 በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጊዜ ነው ምርጥ ብቃት ላይ የነበርኩበት ጊዜ ነበር፡፡ አሰልጣኙ ጠርቶኝ ቅር እንዳልሰኝ ጠንካራ ፉክክር እንደሚጠብቀኝ ነገረኝ፡፡ ሳላሀዲን ሰይድ፣ አዳነ ግርማ፣ መድሃኔ ታደሰ፣ ጌታነህ ከበደና ዑመድ ኡኩሪ ተጠርተዋል አሰልጣኙ ጥሩ ስለሆንክ እንጂ አንተን መጥራት ከባድ ነውና እንዳይሰማህ ይለኝ ነበር፡፡ በችሎታዬ ባለኝ አቋም አሰልጣኙ ደስተኛ ቢሆንም ከሌሎቹ አጥቂዎች እኔን አስቀድሞ ማሰለፍ ይከብደው እንደነበር ይገባኛል፡፡ ውሣኔውንም እቀበለዋለው ሶስት ወር ዝግጅት ሰርተን ውጪ ሲሄዱ ጠብቁ እንባል ነበር በተለይ ብዙ ጊዜ ነፍሱን ይማረውና ከሞገስ ታደሰ ጋር ነበር ሆቴል የምጠብቀው፡፡ ከዚያ በኋላ አሰልጣኝ ዮሀንስ ሣህሌም ሆነ አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌም ጠርተውኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ተጠርተህ መመለስ ተጠርተህ መቀነስ አላስኮረፈህም?
ሚካኤል፡-በአገራችን እግር ኳስ ተጨዋች ሆነህ አኩራፊ አለመሆን ከባድ ነገር ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ አኩራፊ ስትሆን ታሳምፃለህ ይባላል ዝም ስትልም ሞራልና ፍላጎት የለውም ይሉሃል የቱ ጋር እንሁን፡፡ በዚህ በኩል በጣም ከባድ ስሜት ይፈጥራል፡፡ በቡድኑ ውስጥ ተካትቼ ባልጫወትም አሰልጣኞቹ በእኔ ላይ እንደሚያምኑ ሲጠሩኝ ስለገለፁልኝ ብዙም አልተጎዳውም፡፡
ሀትሪክ፡- የበጎ ስራ ላም ጊዜ ወስደህ እየሰራህ ነው የሚል ነገር ሰማሁ..እውነት ነው?
ሚካኤል፡- የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ በኋላ ያለፉት 3 ወራት የቆየሁት ተወልጄ ባደኩባት ደሴ ከተማ ውስጥ ነው እዚያም ባምቡዋ ተብሎ በሚጠራው ሰፈሬ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን የበጎ አድራጎት ስራ እየሰራን ነው የመምህር አካለ ወልድ ት/ቤት ውስጥ ቦታ ተሰጥቶን ከ200-250 ሰው ባለፉት 60 ቀናት የምሳ ምገባ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ከአካባቢው በጎ አድራጊዎች ጋር ሆነን ማየት የተሳናቸው፣ አዛውንቶች፣ ህፃናቶች፣ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው፣ በህክምና እጦት የሚሰቃዩትን የቤት ጥገናና የቀለብ ድጋፍ አድርገናል፡፡ በዚህ በጎ ተግባር ላይ በመሳተፌ ደስተኛ ነኝ፡፡


ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችና ባለሙያዎች ማህበር አባል ነህ?
ሚካኤል፡- አዎ የማህበሩ አባል ነኝ፡፡ የዛሬ አራት አመት አካባቢ ማኅበሩን ለመመስረት ጥረት ቢደረግም በብዙ ምክንያቶች እንዳይመሰረት ተደርጓል፡፡ አሁን ግን እነ ዳዊት፣ እነ ፍፁም፣ እነ ኤፍሬም ያሉበት ይሄ ማኅበር ከገጠመው ፈተና አልፎ ሰብረው በመውጣት ሕጋዊ አካል ሆነዋል፡፡ ይሄ በጣም አስደስቶኛል፡፡ ብዙ የኢትዮጵያ ተጨዋቾች በዚህ ማኅበር ላይ ነው ተስፋ ያላቸው፡፡ ማኅበሩ የሚገባውን ያህል ጥግ ላይ ደርሷል ብዬ አላስብም፡፡ ብዙ እንዳይመሰረት የተፈለገበት ምክንያት በመሸነፉ ግን ደስተኛ ነኝ፡፡ ከአሰልጣኞች፣ ከፌዴሬሽን አመራሮች ከሚዲያ ሰዎችና ከብዙ አቅጣጫ ትግል የነበረበትና ፍልሚያ ሰብሮ ወጥቷል፡፡ በቀጣይ አሁን ካለበት በላይ መጓዝ ይጠበቅበታል፡፡ የኢትዮጵያ ተጨዋች አንገት የሚደፋበትና የሚበደልበት ዘመን መብቃት አለበት፤ አሁንም በኮሮና ቫይረስ ችግር ላይ በጎ ተግባር ላይ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው የተጨዋቾች ለቅሶና ሐዘን መቆም አለበት፤ ተጨዋቾቹም ከማኅበሩ ጋር አንድ አካል ሆነው መቆም አለባቸው፡፡
ሀትሪክ፡-የመጨረሻ የምስጋና ቃል አለህ?
ሚካኤል፡- አዎ አምላኬ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ ስለሁሉም እርዳታው ክብር መስጠት እፈልጋለሁ ከዚያም አባቴን ማመስገን እፈልጋለው ኮትኩቶና በተገቢው መንገድ አሳድጎ ታማኝ ለእውነት የቆመ ለሰው ልጅ ክብር ኖሮት በተገቢው ህይወት እንድገኝ ያደረገኝ አባቴን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ እናቴንና ቤተሰቦቼን ባለቤቴንና ልጆቼን፣ ጓደኞቼን፣ አሰልጣኞቼን ለደሴ ልጆች በአጠቃላይ በኔ ህይወት ላይ ድጋፋቸው ላልተለየኝ በሙሉ አመሰግናለሁ፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport