የአሌክስ ባርና ሬስቶራንት ባለቤት ለ16 የቀድሞ ባለውለተኞችና የስፖርት ቤተሰሰቦች ከፍተኛ ድጋፍ አደረገ

ከብስራተ ገብርኤል ወረድ ብሎ ከሚገኘው አደባባይ ፊት ለፊት የሚገኘው የአሌክስ ባርና ሬስቶራንት ባለቤት አቶ አለማየሁ ሰሊቶ ለ16 የቀድሞ የእግር ኳሱ ባለውለተኞችና የስፖርት ቤተሰቦች የሁለት ወር አስቤዛና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።


ጠ/ሚ አብይ አህመድ የማዕድ ማጋራት መልዕክትን ተከትሎ እንዲሁም ወቅቱ አለምና ሀገራችን በኮሮና ቫይረስ የከፋ መከራ ውሰጥ የወደቁበት ክፉ ሠዓት በመሆኑ ይሄንን መጥፎ ወቅት በመተሳሰብና በመረዳዳት ማለፍ አስፈላጊ ነው ከሚል በጎ ሀሳብ በመነሳት የአሌክስ ባርና ሬስቶራንት ባለቤት አቶ አለማየሁ ሰሊቶ ድጋፍ ያደረጉት ለ16 የቀድሞ የመቻል፣የመብራት ሀይል፣የቡና ገበያ፣የትግል ፍሬና የኢትዮጵያ ብ/ቡድን ተጫዋቾች፣አሰልጣኞችና የስፖርት ቤተሰቦች ሲሆን ከ60ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጓል።
በዕለቱ በአሌክስ ባርና ሬስቶራንት በተዘጋጀው ስነስርአት ባለውለተኞቻችን ናችሁ እናመስግናችሃለን በዚህ የፈተና ወቅትም ከጎናችሁ ነን በማለት ድጋፍ የተደረገላቸው 16ቱ ባባለውለታዎች አሠልጣኝ መርሻ ሚደቅሳ(ዋልያ፣መቻልና ኢት.ቡና)፣አሠልጣኝ በሀብቱ (መቻል)፣ቡታ አስመሮም(መቻል)፣አብዲ ከድር(ትግል ፍሬ)፣አረፋይኔ ምትኩ(መቻል)፣በቀለ አልሁ(ኒያላ፣መብራት ሀይል፣ባንኮችና ብ/ቡድን)፣ተሾመ ተፈራ/ተሼ ብረቱ/(ቡና ገበያ)፣ተስፋዬ/ጅማ/(ቡና ገበያ)፣መቶ አለቃ አይንሸት መንገሻ(መቻል)፣ተስፋዬ ተመስገን (ቅ.ጊዮርጊስ)፣ማስተር ቴክኒሺያን እሸቱ አስማማው(መብራት ሀይል አሠልጣኝ)፣ሣሚ አስፋው(የመቻሉ አስፋው ባዩ ልጅ)፣የሺጥላ ማሞ(መብራት ሀይል)፣ተስፋዬ አበበ(ቦክሠኛ)ከ3ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ ከአ.አ ስታዲየም ጠፍተው የማያውቁ አቶ ደበበ እንግዳወርቅና በመቻል የረዥም ጊዜ ደጋፊነትዋ የምትታወቀው ወ/ሮ መንበረ(ጦሩ)ናቸዉ።


በዕለቱ ከነበረው ፕሮግራም መረዳት እንደተቻለው ለ16ቱም ባለውለተኞች ለእያንዳንዳቸው 10 ፓስታ፣5ኪሎ ማኮሮኒ፣5 ሊትር ዘይት፣5ኪሎ የካኦ ጄጄ ዱቄት፣5ኪሎ ሩዝ፣10 የገላ ንፅህና መጠበቂያ ሣሙና፣10 የልብስ ሳሙና፣10 ሶፍት የተሰጣቸው ሲሆን ስጦታውን ይዘው ሲጓዙ መንገላታት እንዳይደርስባቸው በማሰብ ለትራንስፖርትና የጎደላቸውን ማሟያ እንዲሆን በማሰብ ለእያንዳንዳቸው ብር 1500 ከአቶ አለማየሁ ሰሊቶ ተበርክቶላቸዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸውን ባለውለተኞች በመወከል አስተያየት የተሰጠ ሲሆን ከ50አመት በላይ በእግር ኳስ ተከታታይነት የሚታወቁት አቶ ደበበ እንግዳወርቅ ከእናንተ ጀግኖች ጋር አብሬ ድጋፍ በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ ይገባኛል የካታንጋ ጣሪያ ሲያቃጥለኝ ስደግፋችሁ ኖሬያለሁ አቶ አለማየሁን ማመስገን እፈልጋለሁ እግዚአብሄር ይጠብቅህ አመሰግናለሁ ሁሌ ረጂና ደጋፊ ያድርግህ ብለዋል።

አሰልጣኝ በሃብቱ ገ/ማርያም በበኩሉ
ሰው ተቸግሮ ሳይሆን ዋናው መታወሱ ነው..አቶ አለማየሁ አስታውሶ ለሰጠን ድጋፍ አመሠግናለሁ እግዚአብሄር ይስጥህ ደስ ብለኛል..ጋዜጠኛ ይስሃቅና ሸዋረጋ ደስታንም አመሠግናለሁ ብሏል።

አሰልጣኝ መርሻ ሚደቅሳ በበኩሉ
የአቶ አለማየሁ ድጋፍ ኢትዮጲያዊነትን ያሳያል አግኝ ለክፉ አትገኝ በልጆችህ የማታ እንጀራ ብላ እንዳስታወስከን አምላክ ያስታውስህ ያለ ሲሆን ብቸኛዋ እንስት የነበረችው

መንበረ(ጦሩ)
ለኔ አስታዋሼ ጓደኛዬ ይስሀቅ ነው ማንም ሲቸገር ዝም የማይል ልብ አለው እግዚአብሄር ይጠብቅህ አቶ አለማየሁም ከፍ ያድርግህ ቤተሰቦችህ ተባርከው ይቅሩ አመሠግናለሁ በማለት የተሰማቸውን የደስታ ስሜት በእንባ ታጅበው ተተናግረዋል።
በፕሮግራሙ መዝጊያ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ከብዙ ማግባባትና ግፊት በሃላ እሺታውን ገልፆ አስተያየት የሰጠው የአሌክስ ባርና ሬስቶራንት ባለቤት አቶ አለማየሁ ሰሊቶ”ይሄንን አጭር ፕሮግራም ያዘጋጀነው ለእርዳታ ከሚል ስሜት ሳይሆን በአንድ ወቅት በድንቅ ችሎታቸው ያስደሰቱንን እንደ ሀገር ያስጨፈሩንን ብሎም ለሀገር ውለታ የዋሉልንን ባለውለተኞች በዚህ ክፉ ጊዜ አይዟችሁ ከጎናችሁ ነን አለንላችሁ ለውለታችሁም እናመሰግናለን ለማለት ነው”ካለ በሃላ”ሠው ለሠው የሚያስፈልገው በዚህ ፈተናና ችግር በበዛበት ወቅት ነው፤የተደረገው ድጋፍም ከውለታችሁ አንፃር በጣም ኢምንት እንደሆነ አውቃለሁ፤ሀገራችን ይበልጥ ሠላም ሆና ይሄ ክፉ ወረርሽኝም ጠፍቶ ይበልጥ የምንጠያየቅበት የምንደጋገፍበት ባለውለታዎችን የምናስታውስበት ጊዜ ይኖረናል፤በተረፈ በፕሮግራማችን ላይ ስለተገኛችሁ ከልብ እያመሰገንኩ ሃሳቤን ተተቀብለው ከጎኔ የቆሙትን ስማችን አይገለፅ ያሉ ደጋግ ጓደኞቼን ከልብ አመሰግናለሁ”በማለት አስተያየት ሰጥቶ ፕሮግራሙ ተጠናቋል።

 

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.