“የታሪክ፣ የውጤትና የደጋፊዎች ሃብታም የሆነውን ታላቁን ክለብ የማገልገል ዕድል በማግኘቴ ራሴን እንደ ልዩ ዕድለኛ ነው የምቆጥረው” አቶ ዳዊት ውብሸት

ቅዱስ ጊዮርጊስ ለእኔ ከክለብም በላይ ነው”

“የታሪክ፣ የውጤትና የደጋፊዎች ሃብታም የሆነውን ታላቁን ክለብ የማገልገል ዕድል በማግኘቴ ራሴን እንደ ልዩ ዕድለኛ ነው የምቆጥረው”

አቶ ዳዊት ውብሸት


ገና ታዳጊ ህፃን እያለ ወላጅ አባቱ አቶ ውብሸት ክቡር ትሪቡን ይዘውት እየገቡ መሬት ላይ ያለውን አቧራ አያራገፈ እግር ኳስ መከታተልና ቅዱስ ጊዮርጊስን መደገፍ የጀመረው፤ትናንት አቧራውን አራግፎ መሬት ላይ በመቀመጥ ሲደግፈው፣በድሉ ሲቦርቅ የነበረው ጨቅላው ሕፃን ዛሬ ከ85 አመት በላይ እድሜ ያለውን ከሀገሪቱ ኃያላን ክለቦች አንዱ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስን በቦርድ አባልነት የመምራት ወርቃማ እድልን አግኝቷል፤የዛሬው እንግዳችን ወጣቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ አባልና የማርኬቲንግ ኃላፊ የሆነው አቶ ዳዊት ውብሸት፡፡
ከ30 አመታት በላይ የዘለቀ ጥብቅ ትስስር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለው ዳዊት ከስፖርቱ ውጪ በውብ ጌጥ ቢዝነስ ግሩፕ ሥር ያሉትን Tradepath International፣Crystal Automotives፣Folwerport፣Gcc፣wooDco Ethiopia፣aramex እና Dealmode የተባሉ ወደ ሰባት የሚጠጉ ድርጅቶችን በበላይነት የሚመራ ወጣት የቢዝነስ ሰው ነው፡፡ የወቅቱ የቻምፒዮንስ ሊግ፣ የፕሪሚየር ሊግና የፊፋ የአለም የክለቦች ሻምፒዮና የሆነውን ሊቨርፑልን ከ33 አመት በላይ ከመደገፉ በዘለለ የክለቡ ቋሚ የተመዘገበ አባል የሆነውን ዳዊት በርካታ የክለቡን ጨዋታዎች የተከታተለ በሊቨርፑል የቤተሰብ ያህል የሚቆጠርም ሰው ነው፡፡
የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ፍፁም ቀና ለሰው ልጅ ትልቅ አክብሮት ያለው ዳዊት ውብሸት 4ኛ ፎቅ በሚገኘው ደረጃውን በጠበቀውና የስራ መንፈስን በሚፈጥረው ቢሮው ተገኝቶ በግል ህይወቱ፣ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስላለው በደም የተሳሰረ ግንኙነት፣ 33 አመት ሙሉ ድጋፉን ስለሰጠው ሊቨርፑል፣ክለቡ በቅርቡ ከቢ.ጂ.አይ ኢትዮጵያ ጋር ስላደረጉት ታሪካዊ ስምምነት እንዲሁም ከስታዲየምና ከአክሲዮን ጉዳዩ ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎችን ይዞ ፊት ለፊቱ በመቀመጥ አነጋግሮት ለአንባቢያን በሚመች መልኩ አቅርቦታል፤አብራችሁን ሁኑ፡፡

ሀትሪክ፡- በመጀመሪያ ያለህን ውድ ጊዜ ሰውተህ ደረጃውን በጠበቀው ቢሮህ በክብር አስተናግደህ ለቃለ- ምልልሱ ስለተባበርከኝ በራሴና በአንባቢዎቼ ስም በጣም አመሰግናለሁ…?

ዳዊት፡- …እኔም እንግዳ በማድረግ…ከአንባቢዎቻችሁ ጋር ስላገናኛችሁኝ…በጣም አመሰግናለሁ…

ሀትሪክ፡- …ያሳለፍነው ሳምንት የእኔ ነው…ከአምስት በላይ የሚሆኑ ሰኬቶችን ያገኘሁበት ነው…በማለት ስትደሰት እንደነበር ወዳጅችህ ሹክ ብለውኛል…ይሄን ያህል የሚያስቦርቅ ምን አዲሰ ነገር ተገኘ…?

ዳዊት፡- …(በጣም ሳቅ)… ኦው.. እውነት ነው…ያሳለፍነው ሣምንት በእጩነነት ለእኔ የመጣ ነው… ማይል ሰቶንስ የሆኑ በጣም ትልልቅ ስኬቶችን ያገኘሁበት ልዩ ሳምንት ነበር፤ከሁሉም በላይ በጣም ያስደስተኝና ባለፈው ሣምንት ያሰካነው ከቢ.ጂ.አይ ኢትዮጵያ ጋር ያደረግነው ታሪካዊ ስምምነት ነው፡፡ የማርኬቲንግ ኃላፊ እንደመሆኔ ይሄንን ለማሳካት ከባልደረቦቼ ጋር ወደ 8 ወር አካባቢ የፈጀ ድርድር አድርገን በመጨረሻ በክለባችንም በቢ.ጂ.አይ ኢትዮጵያ ታሪክም በጣም የገዘፈ ታሪካዊ ስምምነት አድርገናል የመጀመሪያው የደስታዬ ምክንያት ከዚህ ይጀምራል፤ሌላው ለክለቡ ዘመናዊ አውቶብስ አስመጥተን ነገር ግን በኮቪድ 19 ምክንያትና ከዚያም በፊት በነበሩ አንዳንድ ነገሮች አውቶብሳችንን መረከብ አልቻልንም፤ይሄም ዘመናዊ አውቶብስ እጃችን የገባው የዛኑ ቀን ነው፤ሌላው ከስፖርት ጋር ባይያዝም የሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተገንብቶ ለህዝብ አገለግሎት የዋለውም እንዲሁ በዚህ ሣምንት ነው፤ በሸገር ዳቦ ፋብሪካ እውን መሆን እኔም በትንሹም ቢሆን አስተዋፅኦ ስለነበረኝ ባሳለፍነው ሣምንት መጠናቀቁ በጣም አስደስቶኛል፤ሌላኛው ደግሞ እሱም የግል ጉዳዬ ነው ለአንባቢው ይጠቅማል ባልልም በግሌ ትልቁ ስኬት ያገኘሁበት፣የነገው ህይወቴን በእውቀት እንድመራ የመጨረሻ ማረጋገጫ ያገኘሁበትን ማስተርሴን ለመስራት ውጪ ሀገር ስማር ስለነበር ያንን የጨረስኩበትና ማስረጃዬን የያዝኩት በዚሁ ባሳለፍነው ሣምንት ነው፤በአጠቃላይ በርካታ ስኬቶች ተንጋግተው የመጡበት ሣምንት በመሆኑ ሣምንቱ የእኔ ነው እንድል አስገድዶኛል…(ሣቅ)…፡፡

ሀትሪክ፡- …ከላይ ከጠቀስካቸው ውጪ አንድ የረሳኸው ነገር የለም…?

ዳዊት፡- …(እንድ መገረም…እንደመሳቅ እያለ)…ምን እረሣሁ…?…የረሣሁት ነገር ያለ አይመስለኝም…

ሀትሪክ፡- …የሊቨርፑል ደጋፊ እንደሆንክ አውቃለሁ፤ሊቨርፑል ከ30 አመት በኋላ ታሪካዊ ድል መጎናፀፉን ያረጋገጠው በዚሁ ባሳለፍነው ሣምንት ውስጥ ነበርና በዚህም መደሰትህን ነው የሰማሁት…?

ዳዊት፡- …(በጣም ሳቅ)…ትክክል ነህ…መረሣት የሌለበትን ነው የረሣሁት…፤…የሊቨርፑልም ድል ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ካገኘኋቸው ስኬቶች ጋር የሚደመር ነው…፤…30 አመት ሙሉ ጠብቀን ያገኘነው ድል በመሆኑ ሣምንቱን በደስታ አድምቀው ካለፉት ነገሮች አንዱ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ወደ ሊቨርፑሉ ጉዳይ በኃላ ላይ እንመለስበታለን…ከዚያ በፊት ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ ለተጨዋቾች የሰርቪስ አገልግሎት ስላስመጣው አዲሱ አውቶብስ አውራኝ እስቲ…?

ዳዊት፡- …ለክለባችን ተጨዋቾች ያስመ ጣነው አውቶብስ በጣም ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ መኪና ነው፤አውቶብሱ የ2019 ዓ.ም መጨረሻ ስሪት ነው…ያ ማለት የ2020 እንደ ማለትም ነው፤አውቶብሱ ስካኒያ ነው…የስውዲን ምርት ነው…47 መቀመጫዎችም አሉት።
ብዙ ጊዜ በሥራ አጋጣሚ እየወጣን የውጪ ክለቦች ፋሲሊቲዎችን እናያለን…የሚጓዙበት አውቶብስ ፍፁም የተለየ ነው…ከዚህ በመነሣት መቼ ነው የእኛም ክለብ በዚህ ደረጃ የሚሆነው?ብለን ሁሌም እናስብ ነበር ምስጋና አውቶብሱን ለገዙልን ለአቶ አብነት ገ/መስቀልና ለአቶ ጀማል አህመድ ይሁንና በመጨረሻ ይሄ ምኞታችን ተሳክቶልናል፤የአውቶብሱ መገዛት እንደ መኪና መግዛት ብቻ የምናየው አይደለም፤ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ክለብ እንደ መሆኑ ክለቡን የሚመጥን አውቶብስ ባለቤት መሆን አለበት፤ከዚህም ሌለ የአውቶብሱ መምጣትና ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ መሆን የተጨዋቾቹን ስነ ልቦና ከፍ ያደርጋል፤ከዚህም በላይ የክለባችንን ብራንድ በደንብ ያስተዋውቅልናል፤ተጨዋቾቻችንም ደረጃውን በጠበቀ፣የዘመኑን ቴክኖሎጂ በታጠቀ አውቶብስ ከሌሎች በተለየ ተጠቃሚ መሆናቸው የበላይነትና ትልቅ ኩራት እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡

ሀትሪክ፡- …እስቲ አሁን ደግሞ ወደ ሊቨርፑል እንመለስ…ሊቨርፑል መደገፍ የጀመርከው መቼ ነው? እንድትደግፍስ ምክንያት የሆነህ…?

ዳዊት፡- …ካልተሳሳትኩ ሊቨርፑልን መደገፍ ከጀመርኩ ወደ 33 አመት አካባቢ የሆነኝ ይመስለኛል፤ በጣም ልጅ እያለሁ ነው መደገፍ የጀመርኩት፤በነገራችን ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስንም ሊቨርፑልንም እንድደግፍ ምክንያት የሆነኝ ወላጅ አባቴ ነው፤በነገራችን ላይ የሊቨርፑል ደጋፊ ብቻ ሳልሆን የክለቡ Registered Member (የተመዘገብኩ አባልም) ነኝ፤ የራሴ የሆነ የአባልነት ካርድም ያለኝ ነኝ፡፡
ታስታውስ እንደሆነ ሁሌም ቅዳሜ ቅዳሜ Big league Soccer በሚል በሞቢል ስፖንሰርነት የእንግሊዝ ክለቦች ውድድር ይታይ ነበር፤በዚያን ዘመን ከአባቴ ጋር እግር ኳስ እከታተል ነበር፤በወቅቱ አባቴ የሊቨርፑል ደጋፊ ስለነበር…እኔም በእሱ አማካይነትና…በቡድኑ አጨዋወት ተስቤ መደገፍ ጀመርኩ…፡፡

ሀትሪክ፡- …የረዥም ዘመን ታማኝ ደጋፊ እንደመሆንህ…ሊቨርፑልን በቴሌቪዥን መስኮት ከመመልት በዘለለ በአካል ተገኝተህ ጨዋታዎችን የተከታተልክበት አጋጣሚስ አለ…?

ዳዊት፡- …አዎን…በጣም ብዙ…በዚህ በኩል በጣም እድለኛ ነኝ…፤…ከት/ቤት ከወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ በ25 እና 26 አመቴ አካባቢ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ብዙ የሊቨርፑልን ውድድሮች በአንፊልድም በሌሎች ከተሞችም እንዲሁም ከእንግሊዝ ውጪ ጭምር በአካል ተገኝቼ በርካታ ጨዋታዎችን ታድሜያለሁ፤በተለይ ወደ ስራ አለም ከገባሁ በኋላ ብዙ እድሎችን አግኝቻለሁ፤ከስራዬ ጋር በተያያዘ የብሪትሽ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ወኪል ስለነበርኩ ለአመታት ይሄንን እድል እንዳገኝ በቀላሉ እየሄድኩ እንድከታተል እድል ሆኖኛል፡፡ በወቅቱ በነበረኝ የስራ ትስስር ምክንያት ወደ እንግሊዝ ሀገር በብዛት እመላለስ ስለነበር ከዚህ ውጪም በትላልቅ የእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎች ትሬይኒንጎችንና ኮርሶችን እወስድ ስለነበር የመመልከት እድሉን ፈጥሮልኛል፤አጋነንክ ካላልከኝ በአመት ውስጥ ከ10 ያላነሱ የሊቨርፑል ጨዋታዎችን…ከዚህ አነሰ ከተባለ አራትና አምስት ጨዋታዎችን በአካል ተገኝቼ እከታተል ነበር፡፡

ሀትሪክ፡-ከእዚህ ውስጥ በትልቅነት የምታነሳውና የተመለከትከው የሊቨርፑል ጨዋታውን ጥቀስልኝ ብልህ…?

ዳዊት፡- …ለምሣሌ በ2005 ቱርክ ኢስታንቡል ላይ የተካሄደውን ጨዋታ ሊቨርፑል ሲያሸንፍ እኔ በቦታው የተገኘሁ የአይን ምስክር ነበርኩ፤ከዚህ ሌላ ባለፉት ሁለት አመታት ሊቨርፑል ለቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ የቀረበበትና ባለፈው አመት የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ባነሳበት ጨዋታ አሁንም በቦታው ነበርኩ፤ከዚህ ውጪ ሊቨርፑል በፊፋ የአለም የክለቦች ሻምፒዮና ኳተር ላይ ሻምፕዮን ሲሆን አሁንም ነበርኩ፤ብቻ ሊቨርፑል ጣፋጭና የማይረሱ ድሎች ባገኘባቸው ቦታዎች እንዲሁም በፕሪሚየር ሊግ በአንፊልድና በሌሎች ከተሞች እየተዘዋወርኩ ብዙ ጨዋታዎችን አይቻለሁ፡፡ አሁንም ከ30 አመት በኋላ ሊቨርፑል ዋንጫ ሲያነሣ በቦታው ተገኝቶ የመታደም እቅዱ ነበረኝ…ያው ኮቪድ መጥቶ አበላሸው እንጂ…፡፡

ሀትሪክ፡-ሊቨርፑል ከ30 አመት በኋላ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በማንሣቱ…የደስታህ ስሜት ምን እንደሚመስል አጋራኝ እስቲ…?

ዳዊት፡- …እውነት ለመናገር ዋንጫ እንዳናመጣ እንቅፋት የሆነው የ30 አመት ግድግዳን አፍርሶ የክለቡ ታሪክ በስኬት በመቀየሩ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ድሉን ምንም እንኳን የወቅቱ ወረርሽኝ የሆነው ኮቪድ ለማቀዝቀዝ ቢሞክርም ከ30 አመት ትዕግስት በኋላ ይሄን ታላቅ ድል በማግኘታችን በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ይሄንን የምልህ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ እንጂ ሌሎችን ደጋግመን አሳክተናል፤ግን እኔ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳታቸው ትልቁ ነገር ቢሆንም በየጊዜው እያሳዩ በመጡት ከፍተኛ ለውጥ ከዋንጫው የበለጠ አስደስቶኛል፤የተጨዋቾቹ አቅም የተገነባው ቡድን አሰልጣኙ በሜዳ ላይ የሚያሳዩት ፕርፎርማንስ የሚያከራ ደስታን የሚሰጥ ነበር፤የቻምፒዮንስ ሊግ፣የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ፣የፊፋ የአለም የክለቦች ዋንጫን አሁን ደግሞ ከረዥም አመት በኋላ የሊጉን ዋንጫ ማንሣታቸው ክለቡ እንደተለወጠና ወደ ኃያልነቱ ለመመለሱ በቂ ማስረጃዎች ናቸው፤በዘህ ደረጃ የተቃኘን፣ውጤታማ የሆነውን ሊቨርፑልን ማየት ነበር የምፈልገው፤ሊቨርፑል ባለፉት አመታት ባሳያቸው እንቅስቃሴዎች በጣም ደስተኛ ነኝ…የ30 አመት የዋንጫ ረሃቡም በዚህ መልኩ በመታገሱም እንደዛው፡፡

ሀትሪክ፡- …እንደረዥም ጊዜ ደጋፊነትህና አባልነትህ በአካል እየተገኘህ ጨዋታዎችን እንደመከታተልህ በአካል ያገኘኸው ያዋራኸው የሊቨርፑል ተጨዋች አለ… ?

ዳዊት፡- …ብዙዎችን ወይም ሁሉንም በቅርብ ርቀት አይቻቸዋለሁ፣አግኝቻቸዋለሁ ማለት እችላለሁ፤ ከሁሉም በላይ የክለቡ ምልክትና የረዥም ጊዜ አምበል ከነበረው ስቴቬን ጄራርድ ጋር ከመገናኘት በዘለለ አብረን ፎቶ የመነሣት እድልም አግኝቻለሁ፤ከእሱ ሌላ ዴቪድ ጀምስ የሚባለውን በረኛና ፈረንስያዊውን የክለቡ አጥቂ ጅብሪል ሲሴን በዋናነነት በአካል አግኝቻለሁ…የአሁኖችን ግን በቅርብ ርቀት የመመልከት እድል ነው ያገኘሁት…በነገራችን ላይ የክለቡ ቋሚ አባል (Member) ስትሆን የተለያዩ ቤኔፊቶች ታገኛለህ…ቀጠሮ ይያዝልህና የምትፈልጋቸው ተጨዋቾች መጥተው Face to Face (ፊት ለፊት) የምትወያይባቸው እድሎች ይሰጡሃል፤ልጆቼን መውሰድ ስለምፈልግና ከትምህርታቸው ጋር አልቀናጅ፣ አልገጣጠም እያለኝ እድሎችን እያቃጠልኳቸው ነው ከአንዴም ሁለቴ የዚህ አይነቱ እድል ተፈጥሮብኝ ነበር፤በነገራችን ላይ አባቴ ብቻ ሣይሆን ልጆቼም የቅዱስ ጊዮርጊስና የሊቨርፑል ደጋፊዎች ናቸው፡፡ በሊቨርፑል አባልነቴ ሊቨርፑል ምን ይመስላል? የሚለው ለማወቅ ባገኘነው (Tour) ልጆቼም ከእኔ ጋር ሊቨርፑልን ጎብኝተዋል ከታሪካዊ ፎቶና የድላቸው ማሳያ ጋር ለታሪክ የሚቀር ማስታወሻም ይዘዋል ክለቡንም በደንብ ታሪኩን የሚያውቁበት አጋጣሚም ተፈጥሮላቸዋል፡፡

ሀትሪክ፡- …ብዙ ሰው ዳዊት ውብሸት የሚለውን ስም የሚያውቀው ወደ ቦርድ አባልነት ከመጣህ በኋላ ነው…?…ከዚያ በፊት ከክለቡ ጋር የነበረህን ትስስር ወደ ኋላ ተመልሰህ አስታውሰኝ እስቲ….?

ዳዊት፡- ከላይ እንዳልኩህ እኔ የሊቨር ፑልም የቅ/ጊዮርጊስም ደጋፊ የሆንኩት በአባቴ ምክንያት ነው፤ በልጅነቴ አባቴ ስታዲየም ይዞኝ ይገባ ነበር፤በአብዛኛው ይዞኝ የሚገባው ክቡር ትሪቡን ስለነበር ደረጃው ላይ የሚገኘውን አቧራ ኧፍ ኧፍ ብለን እየጠረግን ነበር ጨዋታ የምከታተለው…ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ፍቅር በውስጤ የገባው…እያደኩ ስመጣ ራሴን የመቻል አቅም ላይ ስደርስ ወደ ጥላ ፎቅ ሄድኩ…ብዙውን አመታትም ያሰለፍኩት በጥላ ፎቅ ነው፤ትሪቡን ከአባቴ ጋር እየተቀመጥኩ ማየቴ ነፃነቴን ነፈገኝ እኔ በጊዮርጊስ ድል መጨፈር፣መቦረቅ እፈልጋለሁ…አባቴ እያለ ግን ይሄን ለማድረግ አልተመቸኝም፤ራሴን ችዬ ጥላ ፎቅ ስገባ ግን ነፃነቴን አወጅኩ፡፡
ከጓደኞቼ፣ከደጋፊው ጋር መጨፈር…ጎል ሲገባ፣ስናሸንፍ መቦረቅ ሆነ ስራዬ፤ጥላ ፎቅ ሆኜ ጊዮርጊስን ስደግፍ ነው ከእነ አቶ ጀማል ከእነ አቶ ነዋይ ጋር የተዋወኩት፤በአጠቃላይ ከድፍን 30 አመት በላይ ጊዮርጊስን ደግፌያለሁ…፡፡

ሀትሪክ፡- …በቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ አባልነት ትንሹ ሰው አንተነህ…ትሪቡን መሬት ላይ ተቀምጦ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲደግፍ የነበረው ዳዊት ከ85 አመት በላይ ያለው ታላቁን ክለብ እንድታገለግል ስትጠራ በውስጥ ምን አይነት ስሜት ተፈጠረ…?
ዳዊት፡- ..እውነቴ ነው የምልህ በጣም ደንግጬያለሁ፤ይሄንን ታለቅ ክለብ ለማገልገል እታጫለሁ ብዬ አስቤ ስለማላውቅ የሆነውን ማመን አቅቶኝ ድንጋጤ ውስጥ ወድቄ ነበር፤በጭንቅላቴ ውስጥ አንዳችም የጥርጣሬ ስሜት እንኳን አልነበረኝም፤ምናልባት በወቅቱ በሚሊኒየም አዳራሽ ከነበራችሁ አይታችሁት ይሆናል…አቶ አብነት ሲናገር…አቶ ጀማል ተነስቶ ሲያቅፈኝ ነው እውነት መሆኑን ያወኩት፤ወደ መድረክም ተጠርቼ ስሄድ መንገዱ ሁሉ ጠፍቶኝ ነበር…የማደርገውን ሁሉ እስከማላውቅ ድረስ ነበር፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው አንደኛ በልጅነቴ ስደግፈው የነበረው…የበርካታ ታሪክና የማያልቅ የድል ታሪክና የክለቡ ጌጥ የሆኑ ምርጥ ደጋፊዎች ባለቤት የሆነውን ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዳገለግል…በሀገራችን በርካታ ታላላቅና ስመ-ጥር የሆኑ ኩባንያዎችን ከሚመሩ ትልቅ እውቅትና የስራ ልምድ ካላቸው የቦርድ አመራሮች ጋር አብሬ እንድሰራ እድል በማግኘቴ ከዚህም በላይ ብሆን አይፈረድብኝም፤በታሪክ አጋጣሚ የሀገሪቱን ኃያል ክለብ ማገልገል ለእኔ የህይወት ዘመኔ ትልቁ እድልም ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ለቦርድ አባልነት ከመታጨትህ በፊት ክለቡን በተለያየ መንገድም ስታግዝ ነበር..?

ዳዊት፡- …ቅዱስ ጊዮርጊስ 80ኛ አመት ክብረ በዓሉን በትልቁ ለማክበር ባሰበበት ወቅት አካባቢ በቃልም በደብዳቤም ጥሪ ተደርጎልኝ በማርኬቲንግና በዝግጅት የጊዜያዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሆኜ ሠርቻለሁ፤ የማውቀውም ይሄንን ስለነበር ኃላፊነቱን ወስጄ ያሉትን ዲፓርትመንቶች በማደራጀት ሥራዎች በቶሎ እንዲያልቁ የተሳኩ እንዲሆኑ የበኩ ሌን አድርጌያለሁ፡፡ በሚሊኒየም አዳራሽ የተካ ሄደው ፕሮግራም በተለይ በማርኬቲንጉ በኩል እንዲሁም የተሰጠኝን ኃላፊነት በመውጣቴ ያ ታይቶ ይመስለኛል ለቦርድ አመራርነት የታጨሁት፡፡

ሀትሪክ፡- …ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአንተ ምን ማለት ነው…?…ግለፅልኝ ብልህ እንዴት ትገልፅልኛለህ…?

ዳዊት፡- …ከዚህ በፊትም ተናግሬዋለሁ የውስጤን የሚገልፀውም እሱ ስለሆነ አሁንም እየደግመዋለሁ፤ ለእኔ ቅዱስ ጊዮርጉስ MoreThan a club (ከክለብም በላይ ነው)፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለእኔ አንድ ክለብም አይደለም…እንደዛ ነው ውስጤ የሚያምነው፤ቅዱስ ጊዮርጊስ የሀገር ምልክት፣ብዙ ታላላቅ ታሪኮችንና ስኬቶችን በውስጡ ሸሽጎ የያዘ ክለብ ነው፣ክለቡን ለመግለፅ ቃላቶች ራሣቸው አቅም ያንሳቸዋል፤ ይሄንን በዚህ ደረጃ ያለን ክለብ ያውም በቦርድ ደረጃ ማገልገል…ለዚህ ታላቅ ክለብ ደፋ ቀና ማለት እድለኝነት ነው፤እስከአሁን ከከለቡ ለመስራት ሞከርኩ እንጂ ሠራሁ የምለው የለም፤ብዙ የማገልገል ህልም ነው ያለኝ…አላማዬና ፍላጎቴ ቅ.ጊዮርጊስ አሁን ከሚገኝበት የበለጠ ራሱን ችሎ፣የራሱ ስታዲየም ባለቤት ሆኖ…ውጪ እንደምናያቸውና በቅርበት እንደምናውቃቸው ክለቦች ሆኖ ማየት ነው ምኞቶ፤ ይሄ እንዲሳካ አውን እንደሆን የምስስተው ነገር የለም፤ያለኝን ሁሉ መስጠት ነው ፍላጎቴ፤በጥቂት ጊዜያትም ይሄ ህልሜ እውን ይሆናል፣ይሳካል ብዬ ነው ከባልደረቦቼ ጋር የምሰራው፡፡

ሀትሪክ፡- …ከሳምንት በፊት ከቢ.ጂ.አይ ኢትዮጵያ ጋር የአምስት አመት የኮንትራት ስምምነት ማድረጋችሁን ይፋ አድርጋችሁ የገንዘቡን መጠን ግን ደብቃችኋል በሚል ትወቀሳላችሁ፤ገንዘቡን ለምን መደበቅ አስፈለገ ብልህ ምን ትመልስልኛለህ…?

ዳዊት፡- …ችግሩ ምን መሠለህ እናንተ ከታሪካዊው ስምምነት በላይ ገንዘቡ ማወቁ ላይ ያነጣጠራችሁት እንጂ እኛ አልደበቅንም…አሁንም ከገንዘቡ በፊት የሁላችንም ትኩረት ሊሆን የሚገባው ስምምነቱ ላይ ነው…በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርም ሆነ በቢ.ጂ.አይ ኢትዮጵያ ታሪክም እንደዚህ አይነት የድርድር ሂደትና ስምምነት ተደርጎ ያውቃል ብዬ አላስብም፤ያ ለእኛ ትልቁ ስኬት ነው፤በወቅቱ የገንዘቡን መጠን መጥቀስ የማያስፈልግበት ቴክኒካል ጉዳይ ስለነበር ነው እንጂ…መደበቅ አስፈልጎ አይደለም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ውል አለው…ውሉም ተፈፅሟል…ውሉም ላይ ገንዘቡም ሁሉም ነገር በግልፅ ተጠቅሶ ተቀምጧል…የሚከፈልበት መጠንም ተጠቅሷል…ግን በዛን ወቅት ያንን ነገር መግለፅ ያላስፈለገበት ምክንያት ቴክኒካል ጉዳዮች ስለነበሩ ነው፤የሁለታችንን ጉዳይ ከመጠበቅ አንፃር እንጂ ሌላ አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡-አሁንም ዙሪያ ጥምጥም ከመሄድ በዘለለ የገንዘቡን መጠን ለመናገር የደፈርክ አትመስልም፤ ለማንም አታውራ ብለህ በጆሮዬ ሹክ በለኝ እስቲ…?

ዳዊት፡- …በጣም ሳቅ…ይሄን ያህል የገንዘቡ ነገር ለምን ያጓጓሃል..አንተ ኪስ አይገባ (በጣም ሳቅ)…

ሀትሪክ፡- …እኔ ይሄን ያህል የጨቀጨኩህ በአይነቱ የተለየ ታሪካዊ ስምምነት ስለሆነ…የገንዘቡ መጠንም በጣም ትልቅና ሌሎችንም ያነሣሣል የክለቡንም የቢ.ጂ.አይን ታላቅነት ያሳያል…ከሚል ቅን አስተሳሰብ ነው እንጂ ግዙፉ…የ100 ሚሊዮን ብር ስምምነት እንዳደረጋችሁ ወፍ መታ ሹክ ብላኛለች…?

ዳዊት፡- …በጣም ሳቅ…ከየት ፈልፍለህ አገኘኸው…(አሁንም ሳቅ)…እንግዲህ ከዚህ በኋላ ምን እንደምትሆን አላውቅም…አዎን የ100 ሚሊዮን ብር ታላቅ ስምምነት ነው ያደረግነው በወቅቱ እኮ ያልተናገርነው እንዳልኩህ ያላለቁ ቴክኒካል ነገሮች ስላሉ ነው እንጂ ምንም የሚያስደብቅ ነገር የለም… ለአምስት አመት 100 ሚሊዮን ብር ነው የተስማማነው፤በየአመቱ 20 ሚሊዮን ብር ነው ስምምነታችን…ከዚህ በኋላ ምንም አያደባብቀንም…ብንደብቀውም…በተለያየ መንገድ…ልክ እንደ አንተ እየተወራ ስለሆነ…በጣም ካጓጓቸሁ ይሄው ነው እውነቱ…፡፡

ሀትሪክ፡-ብዙ ክለቦች የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ ለከፋ አደጋ እየተዳረጉ ነው፤የተጫዋቾቻቸውን የአራትና የአምስት ወር ደሞዝ መክፈል እያቃታቸው ጭቅጭ ቃቸውን በየጊዜው ሲያሰሙ ይደመጣል፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኮቪድ ተፈትኗል…?

ዳዊት፡- …እውነት ለመናገር ኮቪድ የአለም ክፍል የለም…እኛም ጋ ቻሌንጆች (ፈተናዎች) ይኖራሉ… ከዚያ አንፃር እኛም መፈተናችን የማይቀር ነው፤ምክንያቱም ወጪያቻችንን አንዳንድ ነገሮች ለመሸፈን የሚያግዙን የስታዲየም ገቢዎቻችን ቆመዋል በውድድር የምናመጣቸው ነገሮችም እንዲሁ ቆመውብናል…ይህ መሆኑ ክለባችንን ተፈ ታትናል…ነገሮችም አልጋ በአልጋ ናቸው ማለትም አንችልም፤ ግን የወደፊቱን ቀድመን መስራታችን ለከፋ ፈተና እንዳንዳረግ ጫና እንዳይበረታ አድርጎናል፤ለኮቪድ ብለን ሣይሆነ ሌላም ነገር ቢመጣ በሚል ቀድመን የመዘጋጀቱ ለእንደዚህ አይነቶቹ ፈተናዎች እጅ እንዳንሰጥ አድርጎናል፡፡ ምስጋና ለስፖንሰሮቻችን…ምስጋና ለአ መራሮቻችን ለአቶ አብነት ገ/መስቀል ይሁንና ነገሮች ከመምጣታቸው በፊት ቶሎ ለመውጣት እያቀድን ስለምንሄድ…አሁን ክለቡ ችግር ላይ አይደለም…ኮቪድ 19 አለምን ሁሉ እየፈተነ ቢሆንም ከዚህ አንፃር ልጆቻችንን በደሞዝ ምክንያት ተቸግረው… ተሰቃይተውም የሚያልፉበት ሁኔታ እስከአሁን አልተፈጠረም…እንኳን የተወዘፈ ተወውና የወር ደሞዛቸው በሰዓቱ ተከፍሎአቸዋል…ጥቅማጥቅማቸውም ጭምር ተሰጥቶአቸዋል፤ስለዚህ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚያክል ትልቅ ክለብ በደሞዝ መክፈልና አለመክፈል ስሙ እንዳይነሳ ነው ቀደመን ስራችንን የምንሰራው፡፡

ሀትሪክ፡- …ጌታነህ ከበደ በአንድ ወቅት ለጋዜጣችን በሰጠው አስተያየት “ቅዱስ ጊዮርጊስ ለተጫዋቾች ደሞዝ ከመክፈል ባለፈ በተደጋጋሚ ስልክ በመደወል የሚጠይቅበት ሁኔታ የክለቡን ታላቅነት ይበልጥ አሳይቶኛል” በማለት ተናግሮ ነበር…እውነት ይሄን ያህል ርቀት ሄዳችኋል?

ዳዊት፡- …እውነት ነው ኮቪድ ከመጣ…እግር ኳሱ ከቆመ በኋለ የክለቡ የቦርድ አመራር በሰጠው አቅጣጫ አቶ አብነት ገ/መስቀል፣ እኔና የቡድን መሪው አቶ ታፈሰ በቀለን ጨምሮ ተጨዋቾቻችን የትነው ያሉት? ምን እያደረጉ ነው? ምንስ ጎደላቸው? በማለት በጋራም በተናጠልም እናናግራቸዋለን…የጎደላቸውን እንጠይቃቸዋለን፡፡ የተለያዩ ማብራሪያዎችን እንሰጣቸዋለን…አይዟችሁ በማለት እናበረታታቸዋለን…ሁሌም ለጥያቄያቸው መልስ ለመስጠት ጥረት እናደርግ ነበር፡፡ ባለፈው እንዳያችሁት ከቢ.ጂ.አይ ኢትዮጵያ ጋር በነበረው ስምምነት አምስቱ ተጫዋቾች ታሪካዊ ስምምነቱን በአካል ተገኝተው እንዲያዩ አድርገናል፤ በአጠቃላይ ተጫዋቾቻችንን በየጊዜው በተናጠልም በጋራ ስንከታተላቸው ነበር…አሁንም እየተከታተልናቸውና ያሉበትን ሁኔታ እየጠየቅናቸው ነው ይሄ ወደፊትም ይቀጥላል።

ሀትሪክ፡- የስታዲየሙ ግንባታ ጉዳይ አሁንም የደጋፊው የየዕለት ጥያቄ ነው፤ ግንባታው የውሃ ሽታ ሆነ ብለው ቅሬታ ለሚያሰሙ የዳዊት መልስ ምንድነው?

ዳዊት፡- በነገራች ላይ የስታዲየሙ የመገንባት ጉጉት የእኛ ከደጋፊው ይበልጣል ብዬ ነው የማምነው፤ ስታዲየሙ ተገንብቶ ለዚህ ድጋፊ ቢበረከት ከደጋፊው በላይ የምንደሰተው እኛ ነን፡፡ ስታዲየሙ ያልተገነ ባበት ዋናውና ትልቁ ምክንያት የገንዘብ ችግር ብቻ ነው፤ባለፉት ሶስት አመታት በሀገሪቱ የነበሩት የኢኮኖሚዎች ችግሮች የሚታወቁ ናቸው…ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ታይቷል፤ ስፖንሰሮቻችን ራሣቸው እንደ ካምፓኒ የዚህ ችግር ሠለባ በመሆናቸው እንዲሁም የዋጋ ንረት ተደማምሮ ስታዲየማችን እውን እንዳይሆን እንቅፋት ፈጥሯል፡፡
በነገራችን ላይ የስታዲየሙ አለመገንባት ከደጋፊው በላይ ማለት እችላለሁ ለእኛም ትልቁ ራስ ምታታችን ነው፤መቼ ነው ይሄንን ነገር አሳክተን እፎይ የምንለው የሚለው ነገር ሁሌም ያስጨንቀናል፡፡ እንደ ቦርድ ይሄን ለማሳካት የማናደርገው ነገር የለም፤ግንባታው ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ የገንዘብ እጥረት እጃችንን አስሮ ይዞናል፡፡ ባለፈው የአምስት አመት መሪ እቅድ ስናወጣ ወደ አምስተኛው አመታችን ሽግግር ላይ ነው የስታዲየም ግንባታን ነገር ያስቀመጥነው፤አሁን ክለቡ ትልቅ ህልም ይዞ ተነስቷል የሼር ካምፓኒ ጉዳይ፣ ሼር ካምፓኒው ሲቋቋም የምናገኘውን ገንዘብ መልሰን ቢዝነስ ውስጥ አስገብተን አቅማችን ማፈርጠም ስንችል ወደዚህ ነገር እንገባለን ከሼር ካምፓኒውና ከስፖንሰሮችን በምናገኘው ቶሎ እንጨርሰዋለን ባንልም ቢያንስ ጅማሬው ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የስታዲየሙ ነገር ይሁን ልቀበልህ…አሁን ደግሞ በቅርቡ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የሆኑት ኢንጂነር ታከለ ዑማ ለስፖርት ማኅበራችሁ በሰጡት 10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የትሬይኒንግ ሴንተር እንኳን ለመገንባት እንቅስቃሴ አልጀመራችሁም በሚል ቅሬታ የሚያነሱ አሉ ትቀበለዋለህ?

ዳዊት፡- ያለው እውነታ ሳያዩ ለወቀሣ መጣደፍ ጥሩ ነው ብዬ አላስብም፤ምክንያቱም እኛ የትሬይኒንግ ሴንተሩን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለመስራት ከፍተኛ ዝግጅት ላይ ነን፡፡ ሁሉም ነገር የራሱ የሆነ ሂደት አለው፤በዚያ መሠረት እየሄድንበት ነው እንጂ ችላ አላልነውም፡፡ በእኛ በኩል መስራት ያለብንን እየሰራን ነው፤ለምሣሌ የተለያዩ ዲዛይኖች ቀርበው፤የዲዛይን መረጣ አድርገናል፤በግልፅ ተወያይተንባቸዋልም፤እንደ ቦርድ ትሬይኒንግ ሴንተሩ ምን ምን አይነት ፋሲሊቲዎች ሊሟላለት ይገባል የሚለውን በደብ አይተናል፤የውጪ ሀገር ክለቦችን ተሞክሮ በመውሰድ በአቅማችን ልክ ይሄን ቢያሟላ፤…ይሄ ቢኖረው በሚለው ነገር ላይ በመወያየት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለመስራት የተንቀሳቀስን ነው እንጂ ትተነው አልተቀመጥንም፡፡ አሁን በምንፈልገው ፍጥነት እንዳሄድ እያደረገን ያለው በቦታው አካባቢ ያሉ ችግሮች ናቸው፤ ይሄ ቦታ ከተሰጠን በኋላ የካርታ ይዞታ ላይ ስንሠራ ቆይተናል፡፡ የባለቤትነት ማረጋገጫም ተሰጥቶናል፤ ቦታው ላይ የተፈጠሩት ችግሮች ተፈትተው ከተሰጠን በቀጥታ ወደ ልማት ነው የምንገባው፡፡ ይሄ ቃል የተገባለትና በጀት የተያዘለት በመሆኑ ስፖንሰሮቻችንም አብረው ለመስራት እርግጠኛ ስለሆኑ ከእግዚአብሔር ጋር ቦታውን እንደተረከብን ደቂቃም ሳናጠፋ ስራው እንጅምራለን፡፡

ሀትሪክ፡-የአክሲዮን ማህበሩ ጉዳይስ ምን ደረሰ?

ዳዊት፡-የአክሲዮኑ ጉዳይ እንግዲህ በጣም በጥሩ መንገድ ላይ ነው፤ ከመነሻው እንግዲህ አክስዮኑ የተለያዩ ብዙ ነገሮችን ማለፍ ነበረበት፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ ክለባችን ዘመናዊ የሆነ የምዘገባና የአባሎቹን ቁጥር ማወቅ ነበረበት፤ የአባልነት ምዝገባም ማካሄድ ነበረብን ይሄንን ሰብስክራይብ ሥራን ለማሠራት ለክፍያ ለሁሉ ለሚባል ኩባንያ (ድርጅት) ይሄንን ስራዎች ዘመናዊ ለማድረግና ኤሌክትሮኒክስ ለማድረግ ያሉትን ደጋፊዎችንን በትክክል ለመመዝገብ ነበር የመጀመሪያ ስራችን ማድረግ የነበረብን፤ እሱ ሥራ ብዙ ጊዜ ወስዶብናል፤ ምክንያቱም በትክክል አባሎቻችንን ካላውቅን ወደ ሼር መግባት አይቻልም፤ አሁን ባለው ሁኔታ በእኛ በኩል ሁሉም ዶክመንቶቻችን ዝግጁ ናቸው፤ በሚያዚያ ወር አካባቢ እንቅስቃሴ እንጀምራለን ብለን በነበረበት ወቅት በከተማ ውስጥ ትንሽ ግርግር ስለነበርና ስብሰባም ስላልተፈቀደ ነገሮችን ማሳለፍ ግድ ሆነ፤ ከዚያ በኋላ ዳግም ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት ስናስብ የኮቪድ 19 በሽታ እየተስፋፋ መምጣቱ ነገሮችን አባባሳቸው፤ ከዚህ ውጪ ግን በእኛ በኩል ዝግጅታችንን ጨርሰናል ዶክመንቶቹም ለአንተ ለማሳየት ያህል (በእጃቸው እያሳየ) እንጂ የሚቀረን ወደ ተግባር መግባት ነው፤ አሁን በሁኔታው ባለው ነገሮች በትክክል ብሄድ በፈረንጆች ኦገስት 1 ከሶስት ሣምንት በኋላ አካባቢ ማለት ነው ተጀምሮ ለአንድ አ መት የሚቆይ ሼሩን ለመሸጥ እንቀሳቀሳለን፡፡

ሀትሪክ፡- የአክሲዮን ማህበሩ ሼር የታሰበውን ያህል ክለቡን በሁለት እግር ያቆማል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል…?
ዳዊት፡- የሌሎች ክለቦች ልምድና የስኬቶቻቸው ምክንያትም የሚነግረን ይሄንን መንገድ በመከተላቸው ስኬታማ እንደሆኑ ነው፤ በዚህ መንገድ ተጉዞ በሁለት እግር መቆም ካልተቻለ ነገሮች ከባድ እየሆኑ ነው የሚሄዱት፤ እንግዲህ ቀደም ሲል እንደነገርኩህ አክሲዮኑ ከተሰበሰበ በኋላ ያ የተሰበሰበው ገንዘብ ቢዝነስ ውስጥ ገብቶ በደንብ መስራት አለበት፤ የቢዚነስ ሃሣቡ መነደፍ አለበት፡፡ ግን አክሲዮን ማህበሩ ገንዘብ አምጥቶ ቢዝነስ ውስጥ ገብቶ እስኪሰራበት ድረስ ክለቡ እንዳይቸገር ከ5-15 አመት የኮንትራት ስምምነት እያደረግን ነው፡፡ ያ ክለቡን ያስቀጥላል፤ አክሲዮንም በሌላ መንገድ ስራው ይቀጥላል፡፡

ሀትሪክ፡-የነባሮቹን ኮንትራት በማደሱ በኩል ምን እየተሰራ ነው? አዳዲስ ተጨዋቹን በማምጣቱ በኩልስ?

ዳዊት፡- በነገራችን ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ጉዳይ መስራት የሚጀምረው ቀድሞ ነው፤ ባለቀ ሰዓት የመሮጥ ነገር የለም፤ ያሉት ተጨዋቾች ኮንትራታቸው ከሚያልቀው ጋር እየተነጋገርን ነው መቀጠል ያለባቸውን እናስቀጣላለን፤…ከውጪ የሚመጡትንም በሀገር ውስጥ ያሉትን ተጨዋቾች በተመለከተ እንደ አለብን ክፍተት እያየን ከሰኔ 30 በኋላ የምናደርገውን እንደ ቦርድ የሚወስን ይሆናል፤…ሊጉ መቼ እንደሚጀምር ካረጋገጥን በኋላ ነው ተጨዋቾችንም አሰልጣኞችንም ከውጪ መቼና እንዴት እናምጣ ወደሚለው የምንሄደው፡፡

 

ሀትሪክ፡- …ሊጉ ሊቋረጥ አንድ ጨዋታ ሲቀረው የኮቺንግ ስታፉን በሙሉ አባራችሃል…ይሄንን ውሳኔያችሁን የተቀበሉ እንዳሉ ሁሉ የተቃወሙም አልጠፉም…ውሳኔው ትክክል ነው ትላለህ?

ዳዊት፡- …የቅዱስ ጊዮርጊስ ባህል የሚያሳየን ምንድነው…ቤቱ የሻምፒዮኖች ቤት መሆኑን ነው… ያለፉት ሁለት አመታት ግን ከዋንጫ ውጪ ሆነን ነው ያሳለፍነው፤ ምንም እንኳን በጅማ የተነጠቅነው ዋንጫ በግሌ ባያሳምነኝም፤በዚህ ሁኔታ ሁለት አመት አሣልፈን ሶስተኛ አመት መድገም የለብንም፤ ከክለቡ ባህል ውጪ ያለ ሻምፒዮናነት ክብር…የሀገር ውክልና በአፍሪካ የውድድር መድረክ የመካፈል እድልን የሚያሰጡ አዝማሚያዎችን እያየን ዝምታን መምረጥ ሣይሆን ማስተካከል ነው ያለብን፤ሜዳ ላይ እንዳያችሁት ቅዱስ ጊዮርጊስ መስሎ ያለመታየት ነገር ነው የነበረው፡፡
ልብ ካላችሁ አይታችሁት ከሆነ ወደ ሶስት ጨዋታ የሚሆን በአዲስ አበባ ስታዲየም ተጫውተን በሶስቱም ነው ነጥብ የጣልነው፤ያንን ሶስት ጨዋታ አሸንፈን ቢሆን ኖሮ በእኛ ፕላን መድረስ የነበረብንን…የመሪነት ርቀታችንን አስጠብቀን ወደፊት እንጓዝ ነበር፡፡ አሁን ግን ሶስተኛ ሆነን ያጠናቀቅነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች በሙሉ በምን መጡ? ብለህ ብታየው ከፍተኛ የፕሮፎርማንስ ችግር፣የአሰልጣኞች ፈረስትሬሽን ነበሩ፤ያንን መለወጥ ማስተካከል ስለሚያስፈልግ ይሄንንም በወቅቱ ካላደረግን…ቀሪዎቹ ዘጠኝ ጨዋታዎችን በነበረው መልኩ የምንቀጥል ከሆነ ሌላ የከፋ ችግር ውስጥ ይከተናል ብለን ስለሰጋን ደረጀን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት አምጥተን ቡድኑ በቅንጅትና ግንኝነቱን በማጠናከር በዲሲፒሊን የታነፀ ሆኖ የሚቀጥሉትን ዘጠኝ ጨዋታዎች ጥሩ በመንቀሳቀስ ተወዳዳሪ ሆኖ ዋንጫ ለማግኘት የሚያስችልንን አቅም ለመገንባት ነው ውሳኔው የተወሰነው፤በዚህ መሠረት ለመጓዝ እየተንቀሳቀስን ባለበት በዚህ ሰዓት ይሄ በሽታ መጥቶ ውድድሮች ለመቋረጥ ተገደዱ፡፡

ሀትሪክ፡- ከአሰልጣኞቹ ስንብት በኋላ የቀድሞ የክለቡ አሰልጣኝ የነበሩትን ማርቲን ኖይን የማስመጣት እንቅስቃሴ ተደርጎ እንደነበርና ስምምነት እንዳደረጋችሁ ተነግሮ ነበር? በእርግጥ አሰልጣኝ ይመጣሉ?

ዳዊት፡- ውድድሩ መቼ እንደሚጀመር ባልተረጋገጠበት ሁኔታ እንደዚህ አይነት ድምዳሜ ላይ መድረስ ከባድ ነው፤ኳሱ መቼ እንደሚጀመር የምናውቀው ነገር የለም፤አሰልጣኞች ሌሎች የውጪ ተጨዋቾችን ብናመጣም መጥተው ምንም የሚያደርጉት ነገር የለም፤አሁን ያለው ብቸኛ አማራጭ ያሉንን አሰልጣኞችና ተጨዋቾችን ይዞ መቀጠል ነው የሚል ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ዳዊት ለሰጠኸኝ ሰፊ ቃለ-ምልልስና ለጊዜህ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ዳዊት፡- …እኔም በጣም አመሰግናለሁ…በመጨረሻ ግን አንድ ነገር ብል ደስ ይለኛል…ሁላችንም ከኮሮና ቫይረስ ራሳችንን እንጠብቅ…!!…የመጨረሻው መልዕክቴ ነው፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.