“ዘንድሮ የሚከፈለውን ገንዘብና ተጨዋቾቹንሚዛንላይ ብታስቀምጣቸው ገንዘቡ ይመዝናል”

የዛሬው Oldies but Goodies እንግዳችን የቅ/
ጊዮርጊሱ ብርሃኑ ፈየራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ
እግር ኳስ ከማይዘነጋቸውና በባለውለተኛነት
ከሚያስታውሳቸው ብርቅዬ ተጨዋቾች
- ማሰታውቂያ -
አንዱ የሆነው ብርሃኑ ፈይሳ (ፈየራ) ወደ
ኋላ አስርት ዓመታትን በትዝታ ፈረስ ጋልቦ
የትናንት የጨዋታ ዘመኑን እና ገጠመኙን
ያስታውሰናል፡፡ ፈረንጆች From Hero to
Zero እንዲሉ ትናንት በጀግንነትና በባለውለተኛ
ተጨዋችነት የምናውቀው ብርሃኑ ፈየራ
ሰባት ጊዜ ወድቆ ሰባት ጊዜ ተነስቷል፡
፡ ሕይወት ጀርባዋን በሰጠችው ጊዜ በጨዋታ
ዘመኑ ባለው ታሪክና ዝና ሳይኮፈስ፤ ስራን
ሳይንቅ ዝቅ ብሎ በመስራት ለብዙዎች
በአርአያነት የሚጠቀስ ተጨዋችም ነው፡
፡ “የሚያሳፍረውና የሚያስንቀው ዝቅ ብሎ
መስራት ሳይሆን ልመና ነው፤ ልመና እንደ
እሳት ይፋጃል” የሚል የጠነከረ አቋም ያለው
የቀድሞው ባለውተኛ ብርሃኑ ፈየራ የኢትዮጵያ
ቡና ደጋፊዎች “ብርሃኑ ፈየራ የዘመኑ
ፋራ፤ ገበሬው” እያሉ ስለሚያዜሙበት፣
በጨዋታ ዘመኑ ጩቤ ከጎኑና ከትራሱ ስር
ስለአለመጥፋቱ፣ አየር መንገድ ውስጥ ዕቃ
በመጫንና በማውረድ ስራ ስለመሰማራቱ፣
ትዳር አልበረክትለት ስለማለቱ፣ አራቱ የፊት
ጥርሶቹ ስለመውለቃቸው እና ስለሌሎች
የጨዋታ ዘመኑ አስገራሚ ታሪኮች ለሀትሪክ
ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ
በላይ አጫውቶት ከዚህ በታች ባለው መልኩ
ተጠናክሮ ቀርቧል፡፡
በእግር ኳስ በጣም የተደሰተበት ቀን:-በእግር
ኳስ የተደሰትኩበት ቀን ብዬ ለይቼ የምጠራው
ቀን የለም፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት የነበርኩባቸው
ዓመታት በሙሉ በእግር ኳሱ ትልቅ ደስታን
ያገኘሁባቸው ዓመታት ነበሩ፡፡ ጊዮርጊስ የድል፣
የአሸናፊነት ቤት በመሆኑና በርካታ ዋንጫዎችን
በእግር ኳስ ያገኘሁበት ቤት በመሆኑ ሁሉንም ቀን
በደስታ ነው የማነሳቸው፡፡
-በእግር ኳስ በጣም ያዘነበት፤ ልቡ የተሰበረበት
ቀን:- በጣም ያዘንኩበትና ልቤ የተሰበረበት ቀን
ለመከላከያ ስጫወት ያለጥፋቴ ያለ ኃጥያቴ ከክለቡ
የታገድኩበት ቀን በእግር ኳስ ህይወቴ በዋነኝነት
ያዘንኩበት ቀን ነው፡፡
-እግር ኳስ ተጨዋች ባይሆን ኖሮስ:-ምንም
ጥያቄ የለውም ጥሩ ወታደር እሆን ነበር፤ወታደር
የመሆን ጉጉት ብቻ ሳይሆን ህልምም ነበረኝ፡፡
-ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ባላየውና
ባልሰማው ብሎ የሚመኘው:- ስለጨዋታ ህግ
ወይም አስተዳደር ውስጥ ገብቼ ይሄ ይቀየር
አልልም፤ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ውለታ
ውለው ታሪክ ሰርተው የወደቁ ተጨዋቾችን ባላይ
ደስ ይለኛል፤ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ትልቅ
ስምና ታሪክ የነበራቸው ተጨዋቾች ወድቀው
ከንፈር ሲመጠጥላቸው፤ አይሆኑ ሆነው ሳይ
በጣም ያመኛልና ይሄን በእግር ኳሱ ውስጥ ባላየው
ባልሰማው ደስ ይለኛል፡፡
–ብርሃኑ ራሱን በ3 ቃላቶች ሲገልፅ:-ላመነበት
ወደኋላ የማይል፣ አስመሳይና አጎብዳጅ ያልሆነ
ግን ላመነበትና ለወደደው ህይወቱን ከመስጠት
ወደኋላ የማይል ሰው ነው ብርሃኑ፡፡
–በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑ ዛሬም ድረስ
የሚቆጭበት:-በክለብም በብሄራዊ ቡድን ደረጃ
ተመርጬ ትልቅ ደረጃ ደርሻለሁ፤ በዚህ ብፅናናም
በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ አለመካፈሌና ለስሜ
መጠሪያ የሚሆን ዋንጫ አለማንሳቴ፤ ከአገሬ
ብሄራዊ ቡድን ጋር የአለም ዋንጫ ውድድር ላይ
ሳልታይ ጫማ መስቀሌ ይቆጨኛል፡፡
-በምድር ላይ ካጣሃቸው መኖር አልችልም
ስለሚላቸው:- ዋናውና ትልቁ ነገር ከጌታዬ ቤት
(ከቤተክርስትያን) ውጪ፣ እንዲሁም ለእኔ መኖር
የተፈጠሩ የሚመስሉኝን ወላጅ የለኝም ብዬ
እንዳላስብ የሚያስረሱኝን ጓደኞቼን አነ ተፈሪ፣
ቶማስ አበበ፣ ክብረት ወዳጆና እነ መስፍንን
ማጣት ብቻ ሳይሆን ባይደውሉልኝ ራሱ ያመኛል
መኖርም አልችልም፡፡
-ኃይማኖት ቀይሯል ስለመባሉ:- እውነት
ነው ዛሬ በጌታ ህይወቴ ተቀይሯል፤ የጌታ ልጅም
ሆኛለሁ፤ በተስፋ መኖርን የተሻለች ነገን መናፈቅን
ጀምሬያለሁ፡፡ ጥሩ ክርስቲያን (ጴንጤ) ሆኛለሁ፡
፡ በዚህ በኩል ህይወቴ እንዲለወጥ ከጌታ ተልኮ
ትልቁን ሚና የተጫወተልኝ ፓስተር ሚኪ ነው፤
ተስፋ ባጣሁበት፤ መሄጃ በጠፋኝ ጊዜ፤ ሰማይና
ምድር እንደ አከንባሎና ምጣድ ገጥመውብኝ
ጨለማ በወረረኝ ሰአት ብርሃን እንዳለ ተስፋ
እንዳለ ያየሁት በጌታ ነው፤ ከእነችግሬ ከእነኃጥያቴ
የሚቀበለኝ፤ የተሻለ ነገን የሚሰጠኝ እሱ ብቻ
በመሆኑ ጌታን ተቀብያለሁ፡፡
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ግብ:-ኡጋንዳ ላይ
ባለቀ ሰአት ያስቆጠርኳት ግብ የእኔ የምንጊዜውም
ምርጥ ግቤ ብቻ ሳትሆን ለመታገዴም ምክንያት
የሆነች ግብ ናት፤ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ
ከኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር ስንጫወት ህዝቡ
በውጤታችን ተናዶ እየወጣ ባለበት፤ ጨዋታው
ሊጠናቀቅ ሲል በባከነ ደቂቃ ያስቆጠርኳት ግብና
የወጣው ተመልካችም ከግብዋ በኋላ በድጋሚ
ወደሜዳ የተመለሱበትን ግብ ከግቦቼ ሁሉ
አስበልጣለሁ፡፡ ይህች ግብ የህይወት ዘመኔ ምርጥ
ግብ ብትሆንም በነጋታው በብሄራዊ ቡድን
ቀለል ያለ ልምምድ ስንሰራ ከፍቃዱ
በላይ ጋር ተጋጭተን በቴስታ መትቼው
የታገድኩበትና ከቱኒዚያ የቀረሁበት
አጋጣሚ የግብዋ ደስታ ከአንድ ቀን በላይ
እንዳይቆይ ያደረገው አጋጣሚ አይረሳኝም፤
ከብሄራዊ ቡድኑ በዚህ የተነሳ ብታገድም
ብሄራዊ ቡድኑ ቱኒዚያ ሄዶ 8ለ2
ተሸንፏል፡፡
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ጨዋታ:-
መልሱ አንድና አንድ ብቻ ነው፤ ከኢትዮጵያ
ቡና ጋር ያደረኳቸው ጨዋታዎች በሙሉ
የእኔ የጨዋታ ዘመኔ ምርጥ ጨዋታዎች
ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ጨዋታዎች ለዋንጫ
ከሚደረግ ጨዋታዎች በላይ ስለሆኑ የእኔ የጨዋታ
ዘመኔ ምርጥ ጨዋታዎች የምላቸው ከኢትዮጰያ
ቡና ጋር ያደረኳቸውን ጨዋታዎች ነው፡፡
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ አስልጣኝ፦ ዛሬም
ድረስ ምትክ የማይግኝለት፤ ለኢትዮጵያ እግር
ኳስ የደማው አስራት ሃይሌ ነው፤ አስራት አሁን
እንደምንሰማው ከተጫዋች ገንዘብ የማይቀበል
ክብሩን የሚጠብቅ ትልቅ አስልጣኝ ነው፤ሌሎቹም
ከእሱ መማር አለባቸው።
–የጨዋታ ዘመኑ ምርጥ ተጫዋች፦አልያስ
ጁሃር ነዋ!
-በጨዋታ ዘመኑ በጣም ያስቸገረው ተጨዋች:-
ውይ አልያስ ጁሃር ነዋ…!! ከእሱ ውጪ ሌላ ሰው
መጥራት ይቸግረኛል፤ ኤልያስ እኮ ጉድ ናት፤
በእርግጥ በወቅቱ እነ አሰግድ ተስፋዬን የመሳሰሉ
ምርጥ ተጨዋቾች ነበሩ ግን እንደ ኤልያስ አይነት
አስቸጋሪ የማይጨበጥ ተጫዋች አላጋጠመኝም፡፡
አሰግድ ጎበዝና ምርጥ አጥቂ ነው ኳስን ከተቆጣጠረ
እንዴት ማለፍ እንዳለበት ያዉቃል ያልፍሃል፤ ግን
በጣም ፍጥነት ስለሌለው ትደርስበታለህ፤ ኤልያስ
ጁሀር ግን እንዴ ካለፈህ አለቀልህ በቃ! ንፋስ ነው፤
ቴክኒኩም ፍጥነቱም ስላለው ጉድ ነው የሚሰራህ፡፡
ኤልያስን ምነው ሜዳ ውስጥ ባላገኘሁት የምትለው
አይነት ልዩ ተጨዋች ነው፡፡
-አብሮት ተጣምሮ ሲጫወት በጣም የሚመቸው:-
ፋሲል ተካልኝ፤ በወቀቱ በክንፍ በኩል እየተከላከለም
እያጠቃም ስለሚጫወት በጣም ይመቸኝ ነበር፤
ፋሲል ገና ኳስ ሳልይዝ ነው የሚረዳኝ፤ በጭንቅላት
የሚጫወት ተጨዋችም ነበር፤ ሜዳ ላይም በጣምም
እንናበባለን፤ ስለዚህ ምርጫዬ ፋሲል ተካልኝ ነበር፡፡
-አብሮት ባለመጫወቱ ዛሬም ድረስ
የሚቆጨው:- መቆጨት ሳይሆን ከኢትዮጵያ ቡናው
ካሳዬ አራጌ ጋር አብሬው ብጫወት በጣም ደስ
ይለኝ ነበር፤ በጣም አደንቀውም እወደውም ነበር፡
፡ አንድም ቀን አብሬው የመጫወት ዕድል ሳላገኝ
ነው ኳስ ያቆምኩት፤ በጣም የሚገርምህ አሰልጣኝ
እያለም በካሳዬ ቡድን ውስጥ ብሆን የት ጋ ነበር
የምሰለፈው? እንዴትስ ነበር የምጫወተው? እያልኩ
ራሴን እጠይቅ ነበር፤ ግን ሁለቱም አልሆነም፡፡
–በእግር ኳስ ተማሮ ኳስ ለማቆም የወሰነበት
አጋጣሚ:-መከላከያዎች በወሰኑብኝ ፍትሃዊ ያልሆነ
ውሳኔ ለማቆም ማሰብ አይደለም እስከ ዘላለሙ ድረስ
ከእግር ኳስ አለም እንድገለል አድርጎኛል፤ታምሜ
ጦር ሃይሉች ፊዚዮቴራፒ እየተከታተልኩ ሳለ
ፊዚዮቴራፒ አይከታተልም የት እንደሚውልም
አናውቅም ብለው እኔን ውሸታም አድርገው
እገዳ በጣሉብኝ ጊዜ ከዚህ በኋላ የምን ኳስ ነው
ከእንግዲህ በቃኝ ብዬ ወስኜ እኔና እግር ኳስ በዚህ
የተነሳ ተቆራርጠናል፤ ከውሳኔያቸው በኋላ ይቅርታ
ጠይቅና ተመለስ ቢሉኝም እርም ኳስ በቃኝ ብዬ
አቁሜያለሁ፡፡
–አሰልጣኝ አስራት አባቴ ነው ሲል ቆይቶ “አባቴ
አስራት አይደለም ፈይሳ ነው” ስላለበት አጋጣሚ:-
(በጣም አየሳቀ) አንዳንዴ ስትበሳጭ የማትናገረው
ነገር የለም፤እኔም በወቅቱ መከላከያዎች ያን ውሳኔ
ሲወስኑብኝ ከፈረሙት ሰዎች አንዱ አስራት ስለነበር
አስራት እንዴት ይፈርማል? እንዴትስ አያምነኝም?
ብዬ በጣም ከመናደዴ የተነሳ “አስራት አባቴ
አይደለም፤ አባቴ ፈይሳ ነው” ብዬ ተናግሬያለሁ፡
፡ ያ እውነተኛው ስሜቴ፤ ከልቤ የወጣ አይደለም
በንዴትና በብስጭት የተናገርኩት ነው እንጂ አስራት
እንኳን ያኔ ዛሬም ድረስ አባቴ ነው፡፡ አስራት
ከአባትም በላይ ለዛሬ ማንነቴ ያበቃኝ ትልቅ
ባለውለተኛዬ ነው፡፡
-ብርሃኑ በጨዋታ ዘመኑ ሀብታም ነበር
ግን ምን ያደርጋል ሁለት ላዳ ታክሲዎች
ቢኖሩትም ቁርጥም አድርጎ በልቷቸዋል
ስለመባሉ:-እውነት ነው ሁለት ላዳዎች ነበሩኝ፤
በወቅቱ የሁለት ላዳ ባለቤት መሆን ሀብታም
የሚል ስም ሊያሰጥህ ይችላል፤ ግን እኔ
በወቅቱ ሁለቱ ላዳ ብቻ አልነበረም የነበረኝ፤
ኮንዶሚኒየም ቤት ሁሉ ነበረኝ፡፡
–ይሄ ሁሉ ሀብት የት በኖ ጠፋ ስለመባሉ:-
ከሁለቱ ላዳዎች አንደኛውን መብራት ሃይል
አካባቢ ለነበረው ኮንዶሚኒየም ቤት መጨረሻ
አድርጌዋለሁ፤ አንደኛውን ደግም ወቅቱ
የፈጠረብኝን ችግር ነው ያሸጠኝ። ታዋቂ
ብትሆንም አለመብሰል ይጎዳሃል፤ በወቅቱ
የነበረኝ ትዳር በመፍረሱ ላዳውንም ቤቱንም
ሸጪ ንብረት ተካፍያለሁ፡፡
–በተለምዶ ቴሌ ባር ወይም ናዝሬት
ፔንሲዮን አካባቢ በፍቅር ወጥመድ
ሰለመውደቅ:- እንደእ ድል ሆኖ ጥሩ ጥሩ የሴት
ጓደኞች ያጋጥሙኛል፤ ግን እስከመጨረሻው
አልዘልቅም፡፡ አብዛኛዎቹ ጥለውኝ ወደውጭ
ይሄዳሉ፤ እንደውም በዚህ የተነሳ አንተ
ለአገር ውስጥ ነህ ለውጪ አትሆንም ይሉኝም
ነበር፡፡ ወደ ውጪ የሚወጡትም ቃል ኪዳን
ተሳስረንም ቢሄዱ ከወጡ በኋላም ዞር ብለው
አያዩኝም፤ ግን እኔ ዛሬም ድረስ መልካም ነገር
እንዲገጠማቸው ነው የምመኘው፡፡ ናዝሬት
ፔንሲዮን አካባቢ ትርሃስ የምትባል ጓደኛ
ነበረችኝ፤ የራስዋ ባር ነበራት፤ እዚህ ቤት
ያልመጣ የጊዮርጊስ፣ የቡና፣ የባንክና የመከላከያ
ተጨዋች የለም፤ እንተዋወቃለን፡፡ የፈየራ
ቤት ነው ስለሚባል ምድረ ተጨዋች ይመጣ
ነበር፤ እዚህ ቤት ያልተሰራ ታሪክ የለም፡፡ እኔ
ከክፍለ አገር እንደመጣሁ የማውቀው ይህችን
ጓደኛዬ ብቻ ነው፤ ከዚህ በፊት የማውቀው
ነገር ስላልነበረ በፍቅር እብድ ብዬ ነበር፤
ግን የእሷም ከእሷም በኋላ የነበረውም ትዳር
ፈርሷል፡፡
-ትዳር አልበረክትለትም ስለማለቱ:-
ዕውነት ነው በተለያየ ምክንያት አልበረክትልህ
ብሎኛል፤ በዚህ ጉዳዩ እኔ ማንንም ተጠያቂ
አላደርግም፤ ለተፈጠረው ነገር ሁሉ ተጠያቂው
እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ምክንያቱም እኔ ሃይለኛና በጣም
አስቸጋሪ ሰው ነበርኩ፤ ከአንድም ሶስት ትዳሬን
ብቻ አይደለም ንብርቴንም ያጣሁት በራሴ
ችግር ምክንያት ነው፡፡ አለማገናዘቤ፣ሃይለኛነቴ
ትንሽ ትዕግስት ውሰጥ አለ መኖሩ ብዙ ነገር
አሳጥቶኛል፡፡ ደግነቱ ከሶሰተኛዋ ጓደኛዬ
በአባትዋ ጣልያናዊ ከሆነችው ጓደኛዬ ዛሬ
የእኔ እኩያ የሆነ የ14 ዓመት ወንድ ልጅ
መፅናኛ አግኝቻለሁ፡፡ ሴቶቹም የራሳቸዉን
ህይወት መስርተው ወልደው ጥሩ ጥሩ ኑሮ
እየኖሩ ነው፤ አሁንም የበለጠ የተሳካ ህይወት
እንዲኖሩ ነው የምመኝላቸው፡፡
–ከዚህ በኋላ በትዳር ጉዳይ ተስፋ
ቆርጧል፦በፍፁም አልቆረጥኩም፤ የብቸኝነት
ህይወት የሚገፋ ባለመሆኑ ዳግም ወደ ትዳር
አለም የመመለስ እንቅስቃሴ ጀምሬያለሁ፡
፡ ያለፈው የፈረሰው የትዳር ህይወቴ ብዙ
አስተምሮኛል፤ ለችግሩ ምክንያት እኔው
ራሴ በመሆኔ ራሴን ወቅሼ የተሻለ ህይወት
እንዲኖረኝ እየተንቀሳቀስኩ ነው፤ የጌታ
ልጅ በመሆኔም ከግራ ጎን አጥንት ወስዶ
ጥሩ የትዳር አጋር ይሰጠኛል ብዬ ተስፋ
አደርጋለሁ፡፡
-በጨዋታ ዘመኑ ከትራሱ ስር ጩቤ
ስለአለመጥፋቱ፦በጊዜው ከክፍለ ሃገር ነው
የመጣሁት፤ ስለ አዲስ አበባም ጥሩ ጥሩ ነገር
አልሰማም ነበር፤ ከዚህ በመነሳት ወደ አዲስ
አበባ ስመጣ ጩቤ ጎኔ ላይ ሻጥ አድርጌ ነው
የመጣሁት፡፡ የሚገርምህ ብዙ ሰው ዛሬም ደረስ
አንድ ጩቤ እነደነበረኝ ነው የሚያውቀው፤ እኔ
ወደ ጊዮርጊስ ስመጣ ከአንድም ሁለቴ ጩቤ
ነው ይዤ የመጣሁት፤ በወቅቱ ወገቤ ላይ
ጩቤ ሻጥ ካላደረግኩ ያመኛል፤ ካለ ጩቤ
መንቀሳቀስ አልችልም ልምድም ሆኖብኛል፡፡
ወንድ ልጅ ወይ ጎኑ ላይ ወይ ትራሱ ላይ
ጩቤ ሻጥ ካላደረገ ምኑን ወንድ ሆነ እየተባለ
እየሰማሁ ነው ያደግኩት፤በዚህ ምክንያት
ለጊዮርጊስ ለመጫወት ወደ አዲስ አበባ ስመጣ
ከአንድም ሁለት ጩቤ ነው ይዤ የመጣሁት፤
እንደመጣሁ ትራሴ ስር ሻጥ አደረኩት፤
በዚያን ጊዜ አልጋዬን የሚያነጥፉ ሴቶች
ሲያዩት ያልተለመደ ነገር ስለሆነ ነው መሰል
በጣም ደነገጡ፤ ከዚያ ከትራሴ አስወገድኩት፡
፡ አንዳንዴ ናዝሬት ፔንሲዮን ስሄድ ለክፉም
ለደጉም ብዬ ጎኔ ላይ ሻጥ አደርገው ነበር፡፡ ስገባ
ስፈተሽ ጩቤ ስለታየና ብዙ ጊዜ ስለምጋጭ
የቤቱ ባለቤት ጣቢያ ወሰደው ሁለተኛ ቤቴ
እንዳይደርስ ብለው አስፈርመውኛል፡፡
–ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዋች ጋር ሜዳ
ውስጥ ስለሚፈጠረው ግጭት፦ የኢትዮጵያ
ቡና ደጋፊዎችን በጣም ነው የምወዳቸው፤
ከእነሱ ጋር ስጫወት ከእነሱ ጋር ካልተጣላሁ
የተጫወትኩ አይመስለኝም፤ የስድብ ሱስ
ያለበት ሰው ታውቃለህ? ቡናዎች ካልሰደቡኝ
ዛሬ ምን ነካቸው? እንዴት ዝም አሉኝ? ብዩ
እበሳጫለሁ፤ እነሱ ለቡድናቸው ውጤታማነት
ሲሉ የማይከፍፈሉት መስዋዕትነት
እንደሌለ ስለማውቅ ሲሰድቡኝ እንደስድብ
አልወስደውም፤ እነርሱ በመሳደባቸው
ልክ ናቸው እኔም መሰደቤ ጠቅሞኛል፡
፡ ደግሞም ዛሬ ሜዳ ውስጥ ከምትሰማው
አንፃር ስድብ አይባልም፤ አሁን የምትሰማው
ይዘገንናል፤ አጥንት የሚሰብሩ ስድቦችን ነው
የምትሰማው፤ በእኛ ጊዜ ግን ይሄ የለም፡፡
“ብርሃኑ ፈየራ የዘመኑ ፋራ
ሰለመባሉ”፦መጀመሪያ ላይ ብርሃኑ ገበሬው፤
ገበሬው ነበር የሚሉኝ፤ “ብርሃኑ ፈየራ
የዘመኑ ፋራ” የሚለው የመጣው በኃላ
ነው፤እነሱ ቡድናቸውን ለማበረታታት
የሚፈልጉትን ሶሰት ነጥብ ለማግኘት እንጂ
እውነት ገበሬ ሆኜ ወይም የዘመኑ ፋራ ሆኜ
እንዳልሆነ ስለማውቅ እንደስድብ ሳይሆን
ጥሩ እንድጫወት እንደሚያንቀሳቅሰኝ ነዳጅ
ነበር የምቆጥረው፡፡ አንተ ይሄን ትላለህ
እንጂ አንድ ጊዜ ያውም ከሐዋሳ ዱቄት ጋር
ወሳኝ ጨዋታ እየተጫወትን ጭንቅላቴ
ተጎድቶ በቃሬዛ ሲወጣ ድፍን ስቴድየሙ
“ይቀበር፤ ይቀበር” ብለውኛል እኮ፡፡ በወቅቱ
በጣም ተጎድቼ ስለነበር እነ ዶክተር አያሌው
መጥተው አይተውኝ ደሜ በጣም ስለፈሰሰና
ጭንቅላቴ በመተርተሩ በፋሻ አስረው
ወደ ሆስፒታል በፍጥነት መሄድ እንጂ
መጫወት የለበትም ብለው በመወሰናቸው
በቃሬዛ ስወጣ የቡና ደጋፊ እንዳለ “ይቀበር፤
ይቀበር” ሲሉኝ እኔ ደግሞ አልቀበርም አለሁ
ብዬ ከቃሬዛው ላይ ድንገት ተነስቼ በእግሬ
ስወጣ ድፍን ስቴድየሙ የሚሰድቡኝ የቡና
ደጋፊዎች ጭምር በሳቅ ነው የሞቱት፡፡
የቡና ደጋፊዎች እንደዛ ብለው ይሳደቡ እንጂ
ሁሉም ነገር የሚያልቀው ሜዳ ውስጥ ነው፤
ሜዳ ውስጥ ያበሽቁኛል፤ይሰድቡኛል ከሜዳ
ውጪ ግን ሰላም ነን፤ የሚገርምህ ጊዮርጊስ
እየተጫወትኩ የተከራየሁት የቡና ደጋፊዎች
ቤት የምኖረው ደጋፊው በብዛት የሚኖርበት
ሳሪስ ነበር፡፡ እኔ ለቡና ደጋፊዎች የተለየ
ፍቅር አለኝ፤ ዛሬም ድረስ ያስታወሱኛል ጥሩ
ግንኙንትም ነው ያለን፡፡
–ስለመፈንከቱና የፊት ጥርሶቹ
ሰለመውለቃቸው፦ ለጊዮርጊስ ብዙ ዋጋ
ከፍያለሁ፤ ክለቡ ከእኛ ህይወት በላይ
እንደሆነ አድርገን ስለምንገባ የምንሳሳው ነገር
የለም፡፡ በእኛ ጊዜ ገንዘብ የለም መስዋዕትነት
ግን ነበር፤ከፊት ለፊት ያለው ጥርሴ (በእጁ
እያሳየ) አራቱም ረግፈው በአርቴፊሻል ጥርስ
ተተክተዋል፡፡ እንኳን ዋናው ጥርሴ በወርቅ
የተተካው አርቴፊሻል ጥርሴ ሁሉ ወልቋል፤
ለምትወደው ከለብ የምትሳሳው ነገር የለም፡፡
ክለቤ ከአንዴም ሁለቴ አስተክሎኛል፤መጨረሻ
ላይ ግን ሴራሚክ ጥርስ ያስተከለልኝ ዶክተር
አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ነው፤ ጉልበቴን አናቴን
ብታየው ጠባሳ የሌለበት ያልተሰነጠቀ
ቦታ የለም፡፡ አሁን በዚህ ደረጃ መስዋዕት
የሚከፍል አለ ብትል አልቀበልህም፡፡
–የካኑን ፎቶ ራስ ሆቴል ውስጥ
ስለመለጠፍ፦ ንዋንኮ ካኑ በወቅቱ የነገሰ
ተጨዋች ነበር፤ የፀጉር ስታይሉ፣ ሹርባው፣
ቁመቱ፣ ቅጥነቱና አካሄዱ ከአንተ ጋር
ይመሳሰላል ብለው ብዙዎች “ካኑ” እያሉ ነበር
የሚጠሩኝ፤ እኔም በጣም እወደው ስለነበር
ለብ/ቡድን ተመርጬ ራስ ሆቴል ባረፍንበት
ጊዜ ፎቶውን ከጋዜጣ ላይ ቀድጄ መኝታ
ቤት ውጥ ለጥፌው ነበር፡፡ ራስ ሆቴል ብቻ
ሳይሆን ጊዮርጊስ ካምፕ ውስጥ ሳይቀርም
ፎቶውን ሳገኘው እየለጠፍኩ መኝታ ቤቴ
በካኑ ፎቶ ተጥለቅልቆ ነበር፡፡
–ለጊዮርጊስ እንደ ፈረመ ፍርፍር ወይም
ወጥ ይሰራልኝ ስለማለቱ፦ወደ ጊዮርጊስ ስመጣ
ምግቡን መላመድ አቅቶኝ ነበር፤ በተለይ
ከፖስታ ዘር ጋር መግባባት አልቻልንም፤እኔ
ማሳደጊያ ውስጥ ነው ያደኩት፤ እንጀራ በወጥ
ወይም በበርበሬ መብላት ነው የለመድኩት፤
እዚሀ ደግሞ ፓስታና የፈረንጅ ምግቦች
አሩስቶ ምናምን ነው የተለመደው፤ሌሎቹ
ጥርግ አድርገው ይበላሉ እኔ ግን ልለምደው
አልቻልኩም፡፡ መጨረሻ ላይ ሲመረኝ በቃ
እኔ ይሄ ፖስታ የምትሉትን ነገር መብላት
አልቻልኩም ፍርፍር ወይም ወጥ ስሩልኝ
አልኳቸው፤ አንዴ አንዴ ይሄ ፖስታ
የሚባለውን ነገር ለመሸሽ እንጀራ እየገዛሁ
ሁሉ አፈርፍሩልኝ እል ነበር፡፡
–አየር መንገድ ውስጥ ተቀጥሮ ዝቅ
ብሎ ስለመስራቱ፦ አየር መንገድ ውስጥ እቃ
በማውረድና በመጫን ስራ ላይ ተሰማርቼ
ስሰራ ብዙዋች ደንግጠዋል ብቻ ሳይሆን
ለማመንም ተቸግረዋል፡፡ ለጊዮርጊስም
ለብሄራዊ ቡድንም የተጫወተ ታዋቂ ተጫዋች
ሆኖ እንዴት ዝቅ ብሎ ይሰራል? ብለው
ብዙዎች ተገርመዋል፡፡ የውጪውን ተወውና
ራሳቸው የአየር መንገድ ሠራተኞች ወሬውን
ሰምተው አናምንም በማለት ስራቸውን ጥለው
እየመጡ ያዩኝ ነበር፤ እነሱ ለእኔ ያፍሩ ነበር፡
፡ “እንዴት ይሄን የመሰለ ታዋቂ ተጫዋች
ካርቶን ይሸከማል? ብለውም ያዝኑልኝ ነበር፤
እኔ ግን ስራ አይናቅም ዝቅ ብሎ መስራትም
አያሳፍርም የሚል የጠነከረ እምነት ነው
የነበረኝ፡፡ የሚያሳፍረውና የሚያሸማቅቀው
ልመና ብቻ ነው፤ እንደ ልመና ሰውን ዝቅ
የሚያደርግ የሚያሳፍር ነገር የለም፤ ስትለምን
የሰው ፊት እንደ እሳት ነው የሚለበልብህ፤
የሚፈጅህ፤ እኔ አየር መንገድ ውስጥ ከሁለት
አመት በላይ ሰርቻለሁ፤ በወር 900 ብርም
ሰው ሳልለምን ፊት ሳይገርፈኝ በላቤ አገኝ
ነበር፡፡ ከዚህች ገንዘብ ላይ 400 ብር የቤት
ኪራይ ከፍዬ በቀረችው አብቃቅቼ እኖር ነበር፡፡
አየር መንገድ ውስጥ ያሉ ሰራተኞች ታሪኬን
በማወቃቸውና ውለታዬን በማሰታወስ በስራ
እንኳን የማልጎዳበትን እንድሰራ ይመርጡልኝ
ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ እንደውም አለቃ
አድርገውኝ ነበር፤ ከሴኩሪቲ ጋር እንድሰራም
መድበውኛል፡፡ ስራን አለመናቄ አስከበረኝ፤
ለሰዎች ምሳሌ አደረገኝ እንጂ አላሳፈረኝም።
መሰረት እችላለሁ ከልመና ይሻለኛል ብዬ
ራሴን አሳምኜ ነው የገባሁት፡፡
–ስለ መጀመሪያ ደሞዙ፦እኔ ወደ ጊዮርጊስ
ስመጣ 600 ብር ነበር ደምወዜ፤ በወቅቱ ከእኔ
በፊት የነበሩት ትላልቅ ተጨዋቾች 800 ብር
ያገኙ ስለነበር ከዚያ አንፃር ደሞዜ በጣም ብዙ
ነበር፤ ይልቅ ያ ህዝብ ሁሉ ያጨበጨበለት
ሙሌ ሙሌ እየተባለ የሚዘመርለት እኔ ወደ
ጊዮርጊስ ከመምጣቴ በፊት እቤቱ ድረስ ሄጄ
የምጨፍርለት ተጫዋች ከምገምተው በታች
ሆኖ ሳገኘው በጣም ተገርሜያለሁ፡፡በወቅቱ
የሚያገኙት በጣም ትንሽ ነበር፤ የእኔ ክፍያ
ከአዲስነቴ አንፃር የተሻለ ነበር፡፡
–ደሞዙ አሁን ከሚከፈለው በወር 166
ሺህ ብር ጋር ሲያነፃፅረው ዛሬ ተጨዋች
ብሆን ይል ይሆን?፦እንደዚህ ብዬ የምመኘው
ነገር የለም፤ እነዛን ከመሳሰሉ የእግር ኳስ
ፈርጦች ጋር ተጫውቼ በማለፌ በጣም ነው
የምኮራው፡፡ የድሮውን ደሞዝ ብቻ ሳይሆን
እግር ኳሱን ብታወዳድረው ዛሬ ገንዘብ እንጂ
ኳስ የለም፤ እውነት እናውራ ካልክ አሁን
ገንዘብ እንጂ ኳሱ የለም፤ እንኳን ጥሩ
ጨዋታ ጥሩ የአካል ብቃት ያለው ተጨዋች
ማየትም ብርቅ ነው፡፡ ገንዘቡንና ተጨዋቹን
አንድ ሚዛን ላይ አውጥተህ ብትመዝናቸው
ገንዘቡ የሚመዝን ይመስለኛል እግር ኳሱና
ብሩ አልተመጣጠኑም፤ የተጫዋቾች ክፍያ
በጣም ማደጉ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤
ተጫዋች መውደቅ የለበትም በእኛ ይብቃ
እያልን ብሩ በዛ ብለን የምንጮህ ከሆነ እርስ
በእርሱ ይጋጫል፡፡ ከዚህ በላይም ማደግ
አለበት፤ አህን የምታየው ግን ደጋፊውና
ገንዘቡ አድጓል ኳሱ ግን የለም፡፡ ሜዳ ውስጥ
የሚታየው የሚያሳፍር ነው፤ የገንዘቡን
ያህልም ባይሆን ኳሱ ማደግ አለበት፡፡ የብሩ
ማደግ ብቻውን ትርጉም የለውም፤ እኛ ምንም
በሌለበት ለኳስ መስዋዕትነት ከፍለናል፤ የዛሬ
ተጫዋቾች ለዚህ ተመልካች መስዋዕትነት
መክፈል አለባቸው፡፡ ክለቦች፣ ፌዴሬሽኖች፣
የሚዲያ ሰዎችና ተመልካቾች ብሩና ኳሱ
እንዲቀራረቡ መወያየት አለባቸው፡፡
–አሁን በምን ስራ ላይ ይገኛል፦ ከሰልጠና
አልራኩም፤ አራት ዓመት እድሜ ያስቆጠረ
የወሎ ተወላጆችን ያሰባሰበ ላኮሞልዛ የሚባል
የእግር ኳስ ቡድንና ማህበር አለን፤ ይሄንን
ቡድን በሳምንት ሁለት ቀን አሰለጥናለሁ፤
የዞኑኑ እግር ኳስ ለማሳደግ በየአመቱ ወደ
የክልሎች እየወጣን እንጫወታለን፤ አገር
የሚረከቡ ተጨዋቾች እንዲሆኑ ለፕሮጀክት
የተለያዩ የኳስ ትጥቀች፣ድጋፎችንም
እናደርጋለን፡፡ ባለፈው ሐዋሳ ወጥተን
ተጫውተን አሸንፈናል፡፡ በበአል ሰሞንም
ወደ ወልድያ ተጉዘን ወልድያ ኢንተርናሽናል
ስቴድየም ውስጥ ተጫውተን ደሴ ነጋዴዎችን
አካለወልድ የሚባል ቡድን ጋር ተጫውተናል፡
፡ ለፕሮጀክቶችም እገዛ አድርገናል፡፡ ኳሱን
ለማሳደግ ለፕሮጀክቶች የተለያዩ የቁሳቁስ
እገዛዎችን የሚያደርግ ማህበር ነው፡፡ ስራን
በተመለከተ በአሁን ሰአት ኢቦንጊዳ የቀላል፣
የከባድና የማሽነሪ ጎማዎችና ባትሪ መሸጫ
ድርጅት ውስጥ ነው ተቀጥሬ የምሰራው፡
፡ ከወደኩበት ከተረሳሁበት ቦታ አንስተው
በዚሁ ድርጅት ውስጥ የስራ እድል አንዳገኝ
ያደረጉኝን የኢቦንጊዳ ባለቤት ስራ አስኪያጅ
አቶ ተፈሪ አርጋውን ቶማስ አበባውን
በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ለብርሃኑ
መፅዋዕት መስጠት ሳይሆን ሶስት ድርጅቶች
አሉ እዚያ መጥቶ ጎማና ባትሪ በመግዛት
በተዘዋወሪ እኔን መጥቀም ይቻላል፡፡
ከአምላኬ ቀጥሎ ተስፋ ባጣሁበት ሰአት ተስፋ
የሆነኝን ባለውለተኛዩን ተፈሪ አረጋውንና
ቶማስ አበባውን መስፍን ነጋን ሁሌም ፊቱን
የሚያዞርብኝን ክብረት ወዳጆንና የተለያዩ
ትጥቆችን ስፖንሰር በማድረግ የሚተባበረንን
የኬርአውድ ኢንተርናሽናል ሆቴል ሐዋሳ
ባለቤት የሆነው አቶ ሙራድን ለመልካም
ስራቸውና ከጎኔ በመሆናቸው በዚህ አገጣሚ
ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡


