“የቅዱስ ጊዮርጊስን ህዝባዊነት ካረጋገጥን በኃላ አስተማማኝ የፋይናንስ አቅም በመፍጠራችን ኩራት ይሰማኛል” አቶ አብነት ገ/መስቀል (የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የቦርድ ፕሬዚዳንት)

“የቅዱስ ጊዮርጊስን ህዝባዊነት ካረጋገጥን በኃላ አስተማማኝ የፋይናንስ አቅም በመፍጠራችን ኩራት ይሰማኛል”
አቶ አብነት ገ/መስቀል (የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የቦርድ ፕሬዚዳንት)

“ቅዱስ ጊዮርጊስ ያሳደገኝ ክለቤ ነው፤ ለውለታው ልሰራለት እንጂ ልሸለም አይገባም”
አቶ ጀማል አህመድ


✍️በዮሴፍ ከፈለኝ 

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የበርካቶች እጅ ባጠረበት ከባድ ወቅት ለአምስት አመት የሚቆይ የመቶ ሚሊዮን ብር የስፖንሰር ሺፕ ድጋፍ ያገኙት ፈረሰኞቹ እጅግ ዘመናዊ የሆነ ሰርቪስ ከውጭ አስመጥተዋል፡፡

ከሲዊድን የተመረተውና ከዱባይ ቀጥታ አዲስ አበባ የደረሰው የስካኒያ ምርት የሆነው ይህው ዘመናዊ መኪና 47 ሰው የመያዝ አቅም ያለው መሆኑ ታውቋል፡፡ የክለቡ የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ገ/መስቀልና የክለቡ የልብ ደጋፊና የቅርብ ደራሽ መሆኑ የሚነገርለት አቶ ጀማል አህመድ በጋራ የዘመናዊ አውቶብስ የገዙ ሲሆን ባለፈው ማክሰኞ በሸራተን አዲስ ግቢ ውስጥ በተካሄደ ስነ ሥርዓት ላይ የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን በቀለ ቁልፉን ከአቶ አብነትና ከአቶ ጀማል እጅ ተረክበዋል፡፡

ከርክክብ ስን ሥርዓቱ በኋላ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ድጋፍ ላደረጉና አጋርነታቸው ላሳዩ ተቋማት የምስጋናና የእውቅና አሰጣጥ መርሀ ግብር ተካሄዷል፡፡ የክለቡ የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ አብነት እንደተናገሩት “የቅዱስ ጊዮርጊስ ህዝባዊነትን ዳግም ካረጋገጥን በኋላ ክለቡ ላይ የልማት ስራ ሰርተን አስተማማኝ የፋይናንስ አቅም በመፍጠራችን ኩራት ይሰማናል፡፡ ይህ የሚሳካው አጋሮቻችንን ከጎናችን ማሰለፍ በመቻላችን ነው፡፡ እነዚህን ውድ አጋሮቻችንን በክለቡ የስራ አመራር ቦርድ በብዙኃን ደጋፊዎቻችንና በራሴ ስም አመሰግናለሁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡


አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው “በሽልማቱ ደስ ብሎኛል ቅዱስ ጊዮርጊስ ያሳደገኝ ክለቤ ነው፤ ለውለታው ልሰራለት እንጂ ልሸለም አይገባኝም፤ ብዙ ትልልቅ ሰዎችን ያስተዋወቀኝና እንደ ቤተሰብ እንድንሆን ያደረገ ክለብ ነው” ሲል ደስታው ገልጿል፡፡ አቶ ዳዊት ውብሸት በተለይ ለሀትሪክ እንደገለፀው “የመጀመሪያው በሆነው ይህ መሠል ፕሮግራማችን ላይ አዘጋጅ ሆኜ ለአጋሮቻችን ባደረግነው ምስጋናና እውቅና ደስተኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ ነገር ሰርቻለሁ ብዬ አላምንም፤ ብዙ የመሰራው ነገር ከፊቴ ይጠብቀኛል፡፡ ክለቡ ደረጃውን የጠበቀና የአፍሪካ መጠሪያ የሆነ ክለብ እንዲሆን ለማድረግ በሙሉ ኃይሌ እንድሰራ ጉልበት ይሆነኛል” በማለት ሽልማቱ የፈጠረበትን ስሜት ተናግሯል፡፡ በሸራተን አዲስ በተካሄደ በዚህ ስነ ሥርዓት ላይ ለክለቡ ትልቅ ውለታ ለዋሉት አቶ አብነት ገ/መስቀልና ለአቶ ጀማል አህመድ ልዩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡


ቢጂአይ ኢትዮጵያም ክለቡና ተቋሙ ለፈጠሩት ግንኙነት ከፍተኛ ሚና የተወጡ ገንዘብ ከራሳቸው ኪስ ለክለቡ እያወጡ እኛንም አምጡ የሚሉን የቅርብ ሰዎች ናቸው በሚል ለቦርድ ፕሬዚዳንቱ አቶ አብነት ገ/መስቀል ለአቶ ጀማል አህመድና ለክለቡ የስራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ዳዊት ውብሸት የካባ ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡ አቶ አብነት ሽልማቱ ለበለጠ ኃላፊነት ያነሳሳል በሽልማቱ ተደስቻለው ለቀጣዩ ስኬታማ ስራ ከእግዚአብሔር ጋረ ተዘጋጅተል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ወክለው “በጉዞ አድዋ” ላይ የክለቡን አርማ ከፍ ያደረጉት ሰቲና ሲራጅ እና ዳናዊት አለማየሁ ደጋፊውን ወክለው በመገኘት በክለቡ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳ የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፕሬዚዳንትና የመጀመሪያውን የክለቡን ሰርቪስ ያበረከቱት አቶ ህሩይ ተ/ማርያም ናቸው፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport