“በኔ እምነት ከክለቡ በላይ መመስገንም ሆነ መከበር ያለባቸው አቡበከርና ሚኪያስ ናቸው” አቶ ገዛኸኝ ወልዴ የኢትዮጵያ ቡና ዋና ስራ አስኪያጁ

 

ኢትዮጵያ ቡና የወጣቶቹን አቡበከር ናስርና ሚኪያስ መኮንን ውል ለ5 አመት ማራዘሙ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
ከ25 ተጨዋቾች 24ቱን ለ1 አመት ብቻ ያስፈረሙ ክለቦች በታዩበት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና የሁለቱ ወጣቶችን ኮንትራት እስከ 2017 ድረስ ማራዘሙ ለአሰልጣኙ ካሳዬ አራጌ ትልቅ ደስታ የፈጠረ ሆኗል፡፡ ሁለቱ ወገኖች ያደረጉት ስምምነት ፌዴሬሽን በመገኘት ማፅናት የሚጠበቅባቸው ቢሆንም ወጣቶቹ ያለማንም አስገዳጅነት የመፈረማቸው እውነት የጎላ ሆኗል፡፡ አቡበከርና ሚኪያስ ቀሪ የ3 እና የ2 አመት ውል የነበራቸው ሲሆን ተጨማሪ አመታትን በከለቡ ለመቆየት መፈረማቸው በክለቡ ላይ ያላቸውን እምነት ያሳያል ተብሏል፡፡
አህመድ ረሺድ/ሽሪላው/፣ፈቱዲን ጀማል፡ አማኑኤል ዮሀንስና በረከት አማረ ላጣው ኢትዮጵያ ቡና የወሳኝ ተጨዋቾቹን ውል ለማራዘም መስማማቱ እፎይታ ያስገኘ ሆኗል፡፡ ግብ ጠባቂው አቤል ማሞና የግራ ተመላላሹ ዘዛርያስ ቱጂም ቡድኑን ያጠናከሩታል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

በውል ማራዘሙ ዙሪያ ከሀትሪክ ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ በበኩላቸው “በኛ ክለብ የተደረገው ውል ማደስ አስደስቶኛል፡፡ ቀሪ አንድ አመት እያላቸው ውላቸው ረዘም ላለ ጊዜ እንዲራዘም መስማማታቸው በክለቡ ላይ ያላቸውን እምነት ያሳያል በኔ እምነት ከክለቡ በላይ መመስገንም ሆነ መከበር ያለባቸው አቡበከርና ሚኪያስ ናቸው፡፡ ክብርና ምስጋና ሊሰጣቸው ይገባል የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለመለወጥ በሚደረገው ስራ ውስጥ ገብተዋል ማለት ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ዋና ስራ አስኪያጁ ጨምረውም ለኢትዮጵያ ክለቦች ባስተላለፉት መልዕክት “ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በስተቀር የተረጋጋ ቡድን ተገንብቶ ያውቃል ወይ? እርሱም ቢሆን ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ስላለው በየሁለት አመት ልጆቹን የማቆየት እድል ስላለው ነው ሌሎቹ ጋር ግን ይህ የለም፡፡ የተረጋጋ ቡድን ካልተገነባ በሀገሪቱ እግር ኳስ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ከባድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ ሆኖ እንዳይወጣ የሚያደርገው ጠንካራ የሊግ ውድድር ጠንካራ የእግር ኳስ ስርዓት ስለሌለን ነው ይህን አሰራር ለማስተካከልና ፕሮፌሽናል አሰራር ለማስፈረን ሁሉም መጣር አለበት፡፡ ክለብ ከክለብ ዝውውር ተደርጎ አያውቅም ረጅም ኮንትራት በመስጠት ክለቦች ከታች ወጣቶችን ማሳደግ ሲጀምሩ ከላይ ያሉ የሊጉ ክለቦች ለክለቦቹ ከፍለው ተጨዋች ማዘዋወር ይጀምራሉ ያኔ ታች ያሉ ክለቦች ከመንግሥት የፋይናንስ ድጎማ ተላቀው ራሣቸውን ማጠናከር ይጀምራሉ ያ ደግሞ ወጣቶች ላይ የሚያተኩር አካዳሚዎችን እንዲከፍቱ ወጣቶች ላይም እንዲታመን ያደርጋልና ሁሉም ክለቦች ይህን መሰል አሰራር በመከተል ለሀገሪቱ እግር ኳስ የሚችሉትን ያደርጉ ዘንድ ጥሪ አስተላልፋለሁ” ሲሉ ለሀትሪክ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport