የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በአዲስ አበባ ስታድየም አካባቢ ለሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ ድጋፍን አደረጉ-ምሳም አበሉ

በአዲስ አበባ ስታድየም የሚታደሙ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች እንደዚሁም ደግሞ የእነሱም የቅርብ ጓደኞች ኮሮና ቫይረስን በጋራ ለመከላከል ይቻል ዘንድ በትናንትናው ዕለት ለበርካታ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቫይረሱን ሊከላከሉ የሚችሉበትን የማክስ እና የሳሙና ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር የምሳ ማብላት ፕሮግራምንም አድርገዋል።


የአዲስ አበባ ስታድየም ላይ በነበረው የትናንቱ ልዩ ፕሮግራም ላይ እስከ 350 ለሚደርሱ የጎዳና ተዳዳሪዎች በነበረው የምሳ ማብላት ፕሮግራም ላይ ኮሮና ቫይረስን እንዴት መከላከል እንደሚቻል የግንዛቤ ማስበጫ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን ይህ ፕሮግራም የተዘጋጀበት ዋና ዓላማም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለጎዳና ተዳዳሪዎች እንደሌላው ማህበረሰብ በአሁን ሰዓት ማን አለላቸው በሚል ከእነሱ ጎን ለመቆም እንደሆነና በዕለቱም ከሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች የተሰባሰበው የገንዘብ እርዳታም ገቢው ለእነዚህ የጎዳና ተዳዳሪዎች ሆኖ የመጪውን የፋሲካ በዓል በሌላ ልዩ ፕሮግራም እንዲያሳልፉበት እንደሚደረግ ተገልጿል።


የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ባዘጋጁት ፕሮግራም ላይ ሁሌም በእንደዚህ አይነት ዝግጅት ላይ በመታደም የሚታወቀው ድምፃዊ ያሬድ ነጉ በክብር እንግድነት የተገኘ ሲሆን ከእሱ ውጪም በቦክስ ስፖርት ተወዳዳሪነታቸው ከዚህ ቀደም ይታወቁ ከነበሩት ውስጥ ታዋቂው ቦክሰኛ ፀጋስላሴ አረጋዊ ኮሮኮንች እና እንደዚሁም ደግሞ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሀላፊዎች መገኘታቸው ታውቋል።


በመጨረሻም ይህ ፕሮግራም ሲጠናቀቅ ለእነዚህ ጎዳና ተዳዳሪዎች ማን አላቸው በሚል የገንዘብ እርዳታና ድጋፍ ላደረጉት የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች እና በፕሮግራሙ ላይ ለታደሙት ሌሎች አካላትም ከአዘጋጆቹ ከፍተኛ ምስጋና ቀርቦላቸዋል።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website