የመድን ስፖርት ክለብ ሁለት እግሩን ላጣው የቀድሞው አርቢትር ኮሮና እስኪጠፋ የሚቆይ ከፍተኛ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገባ

የመድን ስፖርት ክለብ ሁለት እግሩን ላጣው የቀድሞው አርቢትር ኮሮና እስኪጠፋ የሚቆይ ከፍተኛ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገባ

በሸዋረጋ ደስታ የሚመራው ማኅበር አርቢትሩ እንዲረዳ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል

 

በይስሐቅ በላይ

አሁን የሆነውን ሁሉ አምኖ ለመቀበል ይቸግራል፤ የሚያዩት ነገርም ልብን ይነካል፤ የቀድሞው አርቢትር አለም ንፅበህ ሜትር በሜትር በሆነች ክፍል ውስጥ ኩርምት ብሎ ተኝቶ ለተመለከተው ውስጡ በሀዘን ይንሰ ፈሰፋል፤
ከዛሬ ሶስት አመት በፊት በገጠመው የስኳር ህመም ሁለቱም እግሮቹ ተቆርጠው አልጋው ውስጥ ኩርምት ብሎ ተኝቶ ለተመለከተው ውስጡ በሀዘን ይደማል፡፡
ትናንት ጥቁር የዳኝነት ልብሱን ለብሶ ፊሽካውን በእጅ ይዞ በሀገር ውስጥም በኢንተርናሽናል የውድድር መድረክም ኢትዮጵያ የሚለውን ታላቅ ስም አንግቦ ሜዳውን ከዳር እስከዳር ሲያካልልበት የነበሩት የማይደክሙት ሁለቱም እግሮቹ ዛሬ ተቆርጠው አልጋ ላይ ወድቆ የተመለከቱት ሁሉ ያዩትን ማመን አቅቷቸው አዝነዋል፤እንባቸውን አፍስሰው የሀዘን ማቅ ለብሰው ከጠባቡ መኖሪያ ቤቱ ወጥተዋል፡፡


በዚህ ክፉና ለሰው ልጅ ሰው በሚያስፈልግበት ወቅት በሰማው ነገር ብቻ አዝኖ ከመቀመጥና ከንፈር ከመምጠጥ ይልቅ ወደ መኖሪያ ቤቱ ማምራትን የመረጠው የቀድሞ የተጨዋቾችና የደጋፊዎች የመረዳጃ ማህበር ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ የሆነው አቶ ሸዋረጋ ደስታና ባለፈው ቅዳሜ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ምክትል ስራ አስፈፃሚና የስፖርት ክለቡ ቦርድ አቶ መንግሥቱ መሀሩና የክለቡ ፕሬዚዳንት አቶ ተምትም ቶላ በቀድሞው ኢንተርናሽናል አርቢትር አለም ንፅበህ መኖሪያ ቤት ተገኝተው የገጠማቸው ነገር ከዚህ የተለየ አልነበረም፤ባዩት ነገር ልባቸው ተነክቷል፤ሳያስቡትም እንባዎቻቸው በሁለቱም ጉንጮቻቸው ያለገደብ ፈሷል፡፡
በገጠመው የስኳር ህመም በመጀመሪያ አንደኛውን በመቀጠል ሁለተኛውን እግሩ ተቆርጦ ካለፉት ሶስት አመታት ጀምሮ አልጋ ላይ የወደቀው የቀድሞው ኢንተርናሽናል አርቢትር አለም ንፅበህ በዚህ የከፋ ደረጃ ላይ መገኘቱ የሰሙትን ሁሉ ከልብ አሳዝኗል፤ለከፍተኛ ድንጋጤም ዳርጓል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በዳኝነት፣በሀገር ውስጥም ታላላቅ ጨዋታዎችን ከመምራት ባለፈ በኢንተርናሽናል የውድድር መድረኮች ጨዋታዎችን በመምራት የሀገርን ስም በማስጠራት ያገለገለ፣በኮሚሽነርነትም ታላላቅ ውድድሮች በኃላፊነት በመምራት የሚታወቀው እንዲሁም አሁን እግር ኳሱን በዳኝነት የተቆጣጠሩትን የእነ በአምላክ ተሰማን ትውልድ እነ ትግል ግዛውን የመሳሰሉ ዳኞችን አስተምሮ ለሀገር በማብቃት በሙያው ትልቅ ውለታን የዋለው ኢንተርናሽናል አርቢትር አለም ንፅበህ ሁለቱም እግሮቹ መቆረጣቸው ብቻ ሳይሆን መታመሙ እንኳን ሳይሰማ በዚህ በከፋ ሁኔታ ውስጥ ወድቆ መገኘቱ ብዙዎችን ለድንጋጤ የዳረገ አጋጣሚ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
“አለም ንፅበህ በከፋ ሁኔታ ላይ ወድቆ ተኝቷል፤ለምን አትረዱትም” የሚል የመነሻ ጥቆማ ሀገራችንን በኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ በመወከል ቀዳሚ ከሆኑት ዳኞች መካከል አንዱ ከሆነው አመለሸጋው አርቢትር ኃይለመላክ ተሰማ የደረሰው የቀድሞ የተጨዋቾችና የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ሸዋረጋ ደስታ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ድጋፍ ለማድረግና ለመጠየቅ በአቶ አለም ንፅበህ መኖሪያ ቤት የገጠመው ነገር ግን ለማመን የሚከብድ ነበር፡፡
አቶ አለም ሁለቱም እግሮቹ ተቆርጠው አልጋ ላይ ኩርምት ብሎ ወድቆ በማየቱ እንባውን መቆጣጠር አቅቶት አንብቷል፤በዕለቱ ለአቶ አለም ይሄን ክፉ ጊዜ እንዲያሳልፉ ይዞለት የሄደው የአንድ ወር አስቤዛንና የገንዘብ ድጋፍ ካደረገ በኋላ ግን ይሄ የአገር ባለውለተኛ በዚህች ሜትር በሜትር በሆነች ክፍል ውስጥ ወድቆ ተረስቶ መቅረት የለበትም ቀናና መልካም ሰዎችን እንዲሁም ለማህበረሰቡ የሚቆረቆሩና የሚደግፉ ድርጅቶችን በማስተባበር ድጋፍ ማድረግ አለብኝ በማለት ለራሱ ራሱ ቃል ገብቶ በሀዘን የፈሰሱትን እንባዎቹን መቆጣጠር አቅቶት ከቤቱ ይወጣል፡፡
ከአቶ አለም ንፅበህ መኖሪያ ቤት በሀዘን ተኮማትሮ የወጣው የቀድሞ የተጨዋቾችና የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዚዳንት የሆነው አቶ ሸዋረጋ ደስታ ከዚያች ቀንና ሰዓት ጀምሮ የተለያየ ጥረት በማድረግ ላይ እያለ ለአቶ አለም ንፅበህ ያደረገውን የሰሙት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ምክትል ስራ አስፈፃሚና የስፖርት ክለቡ ቦርድ አቶ መንግስቱ መሀሩ “ይሄንን የሀገር ባለውለተኛ እኔም በግሌ ላግዘው እፈልጋለሁ፤ እንደዚህ ሆኖ ዝም የምልበት አንጀት የለኝም” በማለት ሸዋረጋ ደስታን ይጠይቁታል፡፡
አቶ ሸዋረጋ ደስታም ከዚህ ውይይታቸው በኋላ ድጋፉንና እርዳታውን ድርጅታዊ መልክ ለማስያዝ በማሰብ ሁሌም ማህበራዊ ኃላፊነቱን በብቃት በመወጣት ተለይቶ የሚታወቀውንና አሁን በቅርቡ ለተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ድጋፍ የሚሆን 10 ሚሊዮን ብር በመስጠት ቀዳሚ የሆነውን የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ስር ያለውን ስፖርት ክለብን ለምን በደብዳቤ አልጠይቅም በማለት ደብዳቤ ያስገባል፡፡
ደብዳቤው የደረሳቸው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ምክትል ስራ አስፈፃሚና የስፖርት ክለቡ ቦርድ ኃላፊ የሆኑት አቶ መንግስቱ መሀሩና የክለቡ የኮሚቴ አባላት “የሆነውን ሁሉ በአካል ተገኝተን ማየትና ማረጋገጥ አለብን” በማለት በአቶ አለም ንፅበህ መኖሪያ ቤት ባለፈው ቅዳሜ ቢጓዙም ባዩት ነገር ሁሉ እጅግ አዝነውና እንባቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ከመመለሳቸው ውጪ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ወዲያውኑ አቶ አለም ንፅበህ የሀገር ባለውለተኛ በመሆኑ፣በአለም አቀፉ የውድድር መድረክ የሀገርን ስም ያስጠራ፣በርካታ ዳኞችን አስተምረው ያፈሩ ባለሙያ በመሆናቸው ከገጠማቸው የከፋ የአካል ማጣትና የኑሮ ውጣ ውረድ በተጨማሪ የኮሮና ቫይረስ በሀገራችንም በመላው አለም ያለውን ህዝብ ለከፋ አደጋ እየዳረገ በመሆኑ የስፖርት ክለቡ እንደ አንድ የስፖርቱ ባለድርሻ ድጋፍ ልናደርግላቸው፤ልናግዛቸው ይገባል የሚል ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ፡፡
በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ስፖርት ክለብ ከተመሠረተበት አላማ በተጨማሪ ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት በማሰብ ከትናንት ማክሰኞ ጀምሮ ለቀድሞው አርቢትር አለም ንፅበህ የኮሮና ቫይረስ ከሀገር እስከሚጠፋ ድረስ የቤት ኪራይ ወጪያቸውን ለመሸፈንና ምንም አይነት ገቢ የሌላቸው በመሆኑ ጤንነታቸውን ለመንከባከብና ቤተሰባቸውን ለመመገብ(ለአስቤዛ)የሚውል የብር 5ዐዐዐ ወርሃዊ ድጋፍ ለማድረግ ወስኗል፡፡


ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ሁሌም የሚታወስና የማይዘነጋ ተግባርን ለዘመናት በመፈፀሙ ተለይቶ የሚታወቀው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የገንዘብ ድጋፉንም አስቤዛውንም በየወሩ በራሣቸው የመኪና አገልግሎት ለማቅረብ መወሰናቸው መድኖችን ይበልጥ አስመስግኗቸዋል፡፡
በቀድሞ የተጨዋቾችና የደጋፊዎች መረዳጃ ማህበር ስም በደብዳቤ መድኖችን ከመጠየቅ አልፎ ቀድሞ በአቶ አለም ንፅበህ ቤት በአካል ተገኝቶ ድጋፍ ያደረገው አቶ ሸዋረጋ ደስታ መድኖች በተለይ አቶ መንግስቱ መሀሩ ባደረጉት ነገር በጣም መደሰቱን ገልጿል፡፡
“አቶ መንግስቱ መሀሩ ለስፖርቱ ቅርብ የሆኑ፣ለስፖርቱ እድገት የለፉና የደከሙ ሰው በመሆናቸው የባለውለተኞች ችግር ይገባቸዋል፤ትልቅ ዋጋም ይሰጣሉ” ያለው አቶ ሸዋረጋ ደስታ “መድኖች በአጭር ጊዜ እዚህ ውሳኔ ላይ ደርሰው ከባለውለተኛው ጎን በመቆማቸው በራሴም በማበራችን ስምም ከልብ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፤መረጃውን የሰጠኝ “እባካችሁ ድረሱለት” ያለኝን የቀድሞው ኢንተርናሽናል አርቢትር ኃይለመላክ ተሰማንም ማመስገን እፈልጋለሁ፤በቀጣይም ሌሎች ግለሰቦች፣ድርጅቶችም የመድንን መንገድ በመከተል በዚህ ክፉ ወቅት ከባለውለተኛው ጎን እንዲቆሙ ጥሪዬን እያቀረብኩ፤ የቤቴን ያህል የማየውን ንግድ ባንክንና ሌሎች ባለሀብቶችን በማስተባበር ድጋፍ ማድረጌን እቀጥላለሁ፤ የሰው ልጅ ሰው ባጣበት ጊዜ ሰው ሆኖ ለመቅረብ ከመሞከር በላይ ምንም የሚያስደስት ነገር የለም” ብሏል ሁሌም ለተቸገሩና ለተጎዱ ባለውለተኞች እጁን ቀድሞ በመዘርጋት ተለይቶ የሚታወቀው ሸዋረጋ ደስታ።
በቅርቡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ ሸዋረጋ ደስታ ለቀድሞ 10 የስፖርቱ ባለውለተኞች የ2 ወር አስቤዛና የገንዘብ ድጋፍ ከጓደኞቹ ጋር ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.