“የልጅነት ህልሜ ዕውን በመሆኑ ዕድለኛ ነኝ፤ የታሪክ፣ የስኬትና የድል ምልክት የሆነውን የቅዱስ ጊዮርጊስን ማልያ ለመልበስ መታደልን ይጠይቃል” ከነዓን ማርክነህ አዳማ/ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከነዓን ማርከነህ የሚለው ስም በእግር ኳሱ መንደር ከፍ ብሎ የሚጠራ ስም ከሆነ ውሎ አደሯል፤ ከአዳማ ከ17 አመት በታች ቡድን የሚመዘዘው የከነዓን ማርከነህ የእግር ኳስ ህይወት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በአዲስ አበባ ከተማና በአዳማ ዋናው ቡድን በኩል አድርጎ የሀገሪቱ ኃያል ክለብ ወደ ሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተመንድጓል፡፡
ወደ ፈረሰኞቹ ቤት ያደረገው ዝውውር ከተሳካ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተለይ ለሀትሪክ አስተያየቱን የሰጠው ከነዓን ማርከነህ “የልጅነት ህልሜ ወደ እውነት በመቀየሩ በጣም ተደስቻለሁ፤ ከሀገሪቱ ታላቅ ክለብ ጋር የእግር ኳስ ህይወቴን ደማቁን ታሪክ አፅፋለሁ” ሲልም ተናግሯል፡፡
“ወላጅ አባቴ ለእኔ ሮል ሞዴሌ አንበሳዬም ነው፤ እሱ አባትም እናትም ሆኖ ነው ለዚህ ያበቃኝ፤ የእሱን ውለታ በህይወትም እንኳን ብከፈለው የሚመጥነው አይደለም” በማለት ለሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዴተር ለሆነው ለጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ያጫወተው ከነዓን “ከፈጣሪ ቀጥሎ ትልቁን ምስጋና አብዝቼ የምሰጠው ሁሉ ነገሬ ለሆነው አባቴ ነው” ሲልም ተናግሯል፡፡
“ብዙ ፈተናዎችንና ውጣ ውረዶችን አይቼ ነው እዚህ የደረስኩት፤ ትዕግስትን፣ ፈተናን ተጋፍጦ ማሸነፍን ያስተማረኝ አባቴ ነው፤ የመጫወቻ ጫማ እንኳ የሌለኝ መናጢ ደሀ ነበርኩ፤ ዛሬ ግን የፈጠረኝ አምላክ ምስጋና ይድረሰውና ከትንሽነት አንስቶ ትልቅ አድርጎኛል፤ በአንድ ወቅት የመጫወቻ ጫማ አጥቼ የምገዛበት አቅም ስላልነበረኝ በቆዳ ጫማ ልጫወት ስል ኳስ ታፈነዳብናለህ በሚል ያለፍላጎቴ በረኛ እስከመግባት ሁሉ የደረስኩበትን ጊዜ አልረሣውም” የሚለው በፍቅር ህይወቱ ድብቁ ነገር ግን አመለሸጋውና ቁመተ መለሎው የናዝሬት የአብራኳ ክፋይ የሆነው ከነዓን ማርከህ ለሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስላደረገው ዝውውር በክለቡ ማሳካት ስላሰባቸው ነገሮችና ስለቀጣይ እቅዶቹ አንድም ነገር ሳይሸሽግ አጫውቶታል፡፡

ፈጣን ጥያቄዎች ለከነህን ማርከነህ

ለአንድ ቀን አግኝቼው ብጨብጠውና ባወራው የምትለው በጣም ታዋቂ ሰው…ከሀገራችን ይሁን ከውጪ…?
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ለሰከንድም ቢሆን የማግኘት እድል ባገኝ ከምንም ነገር በላይ በጣም እደሰታለሁ፤ርዋንዳ ለጨዋታ ሄደን ስንመለስ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ታገኙታላችሁ ተብለን ገና ሳናገኘው በጣም የተደሰትኩበት አጋጣሚ ነበር፤አሁንም እድል ቀንቶኝ የሀገሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ባገኝ ስሜቴን መግለፅ የምችል አይመለኝም፡፡ አጠገቤ ያለው ጥሩ ነገር ሲሰራ እያየሁ ያለሁትን መሪዬን በቅድሚያ ባገኘው ሠላም ብዬው ፍቅሬን ገልጬለት የማስታወሻ ፎቶ አብሬው ብነሣ በጣም ነበር የምደሰተው፤ እንደው በጠ/ሚኒስትሩ ደረጃም ባይሆን ፖል ፖግባን በጣም ስለማደንቀው እሱንም ባገኘው አልጠላም፡፡”
– የሙዚቃ ምርጫህና በጣም የምታደንቀው ድምፃዊ….?
“በአብዛኛው የአፍሪካ ሙዚቃ እሠማለሁ፤ከሀገር ቤት ደግሞ ያልደረስኩባቸው ያመለጡኝ ሙዚቃዎች ይመቹኛል፤የቴዲ አፍሮ በጣም አድናቂ ብሆንም የአስቴርንና የጂጂም ደስ ይሉኛል”
– ተመችቶህ ደጋግመህ ያየኸው ፊልም…?
“ብዙ ፊልም አይቻለሁ፤በጣም ያስለቀሰኝ፣ያስጨነቀኝና ብሎም ያስተማረኝ ፊልም ግሩም ኤርሚያስ የተወነበት “ላምባ” የተሰኘው ፊልም ነው፤“ላምባ”ውስጥህን የሚነካ መቼም የማትረሣው አይነት ፊልም ነው”
– ፊስ ቡክ ላይ ተጥደው ከሚውሉ ወይስ ፌስ ቡክን በሩቁ ከሚሉ…ከየትኛው ወገን ነህ…?
“ፊስ ቡክ እጠቀማለሁ፤ የሚያስፈልጉኝ…የሚጠቅሙኝ ላይ ነው ትኩረት የማደርገው …ከዚያ በዘለለ ፊስ ቡክ ላይ ተጥጄ የምወል ሱስኛ አይደለሁም”
– ለአንድ ቀን ስልጣን ቢሰጥህ ለእግር ኳስ ምን ትጨምራለህ…?…ወይስ ምን ትቀንሣለህ…?
“…የመጀመሪየ እርምጃዬ…የእጅ ውርወራን ማስወገድ ነው…ምክንያቱም በእግር ኳስ ጨወታ የእጅ ውርወራ ትርጉሙ አልገባህእያለስለሚያስቸግረኝነው፤ሜዳ ውስጥ በእጅ ስትነካ ቅጣት ምት፣ፔናሊቲና ቢጫ ካርድ እየተሰጠህ…ኳስ ሲወጣ በእጅ መወርወር አብሮ የሚሄድ ስለማይመስለኝ…የእጅ ውርወራ በእግር እንዲጀመር በስልጣኔ አደርግ ነበር”
– በተጫዋቾች ላይ…ባላየውና ባልሰማው…የምትለው…?
“…ከእግሩ ይልቅ በአፉ የሚጫወት ተጨዋች አልወድም…፤…መጫወቱን ትቶ በሌላ ተጨዋች ህይወት የሚገባ ሰው አይመቸኝም።ሁሉም የተሰጠው ጉልብት አቅም አለው…አቅሙ እስከሰጠው ይሰራል…ሣይችል ሲቀር ግን በአፉ መጫወት ሲጀምር በጣም ይደብረኛል…ወደ አሉባልታና በሰው ህይወት ሲገባ ማየትና መስማት አይመቸኝም”
– የምታሽከረክረው አውቶሞቢል…?
“…ለጊዜው የ2007 ሞዴል ስሪት የሆነች ቶዮታ ኮሮላ
– ድንገት ኪስህ ላይ ፍተሻ ቢደረግ ስንት ብር ይገኛል?
“ለክፉም ለደጉም ብዬ ሁለት ሺህ ብር አካባቢ ይዤ የመውጣት ልምዱ ስላለኝ ሁለት ሺህ ብር አካባቢ ሊገኝብኝ ይችላል”
– ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስወጣህ…?
“…እኔ ጥሩ ተመጋቢ ነኝ…፤…ውድም ቢሆን ጥሩ ምግብ ከሆነ ለማውጣት አልሳሳም…ምናልባት ምግብ ይሆናል የሚያስወጣኝ”
– ለውበትህ በመጨነቅ…ለኮስሞቲክስና…ለተለያዩ መዋቢያዎች ገንዘብህን ታፈሳለህ…?…መስታወት ላይ ሲያፈጡ ከሚውሉ ተርታ ነህ?
“…በፍፁም…አይደለሁም…እኔ እንደውም ግድ የለኝም…መስታወት ላይ ሳፈጥ መዋልን ተወውና መስታወት ራሱ የማየት ልምዱ የለኝም፤…ፀዳ እላለሁ…ራሴን አጠብቃለሁ…ልክ የሥራ ያህል ግን ለውበቴ በመጨነቅ እንቅልፍ አላጣም…ፀጉሬን በሎሽን ነካ ነካ ካደረኩ አበቃሁ…”
– ከነዓን አባካኝ ወይስ ቆጣቢ?
“…አባካኝም ቆጣቢም አይደለሁም…መሀል ላይ ነው ያለሁት…አስፈላጊ ሲሆን አወጣለሁ…መቆጠብ ካለብኝም እቆጥባለሁ…፡፡
– አዳማ እያለህ የማትረሣው የክለባችሁ የሙዚቃ አጨዋች DJ?
“2010 ላይ ወደ ላይ እንዳደኩ አካባቢ የታፈሰ ተስፋዬን አይነት የሚያዝናና ሰው እስከአሁን አላየሁም፤ ታፈሰ ተስፋዬ የቲማችን DJ ነበር…ይዘፍናል…ይደንሳል…ያዝናናል…”
– በእግር ኳስ ተጨዋችነህ ጥርስ የማያስከድን ኮሜዳ/አስቂኝ/ የምትለው?
”የጀማል ጣሰው አይነት አዝናኝ ሰው አለ…?…እኔ አይመስለኝም…ጀማል ጥርስ የማያስከድን…በጣም አስቂኝ ሰው ነው…ከእሱ ጋር ከተገናኘህ ሙሉ ቀን መሳቅ ነው…እሱ ለእኔ የተለየ አስቂኝ ሰው ነው”
– የምግብ ምርጫህ?
“…እኔ በጣም በላተኛ ነኝ…ምግብ ላይ ቀልድ አላውቅም…በተለይ ጥሬ ስጋ ነፍሴ ነው…አሁን ኮሮና ቫይረስ የሚባል በሽታ መጥቶ ተውኩት እንጂ…ጥሬ ስጋ በጣም ተጠቃሚ ነኝ፤ ከስጋ ጋር ልዩ ፍቅር አለኝ…ከዚያ ውጪ ክትፎ በጣም ይመቸኛል፡፡
– አብሮህ ሲጨወት የሚቀልህ?
“ብሩክ ቃልቦሬና ኤፍሬም ዘካሪያስ ከጎኔ ሆነው ሲጫወቱ በጣም ምቾት ይሰማኛል…ጨዋታም በጣም ይቀለኛል፤
– አላንቀሳቅስ ብሎ ያስቸገረህ ተጨዋች?
“…በዚህ ደረጃ የለም…ተቸግሬም አላውቅም…”
– አብሬያቸው በአንድ ማልያ ብጫወት ብለህ የምትመኛቸው ተጨዋቾች?
“ሳላሀዲን ሰይድና ሽመልስ በቀለ”

ሀትሪክ፡- …ስልክህ ላይ ደውሎ—በቅዱስ ጊዮርጊስ እንደምትፈለግ መጀመሪያ ያበሰረህ ማነው…?

ከነዓን፡- …ተስፋዬ የሚባል የክለቡ ደጋፊና…ክለቡ ውስጥ የሚሰራ ሰው አለ…እሱ ከክለቡ ኃላፊዎች ጋር በማገናኘት ወደ ክለቡ እንድመጣ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፤ እሱ ነው መጀመሪያ ወደ ክለቡ እንደምመጣ ደውሎ የነገረኝ…፡፡

ሀትሪክ፡- …ቅ/ጊዮርጊስ እንደሚያስፈር ምህ ስታረጋግጥ በውስጥህ የነበረው የደስታ ስሜት እንዴት ነበር… እስቲ እሱን ስሜት አጋራኝ…?

ከነዓን፡- …ዋው ስሜቱ በጣም ይለያል… ፤… በቃላት ለመግለፅ የሚከብ ድ የሆነ የተለየ የደስታ ስሜት ነው የተሰማኝ፤ ምክንያቱም ያስፈረመኝ ክለብ የሀገሪቱ ትልቁ ክለብ ነው፤ጊዮርጊስ ብለህ ብ/ቡድን ነው የምትለው…ብ//ቡድኑም ሀገርን የሚወክል በመሆኑ ነው እንጂ ከጊዮርጊስ በላይ የለም፤በዚህ ደረጃ ላለ ክለብ መፈረም የማያባራ ደስታ በውስጥህ እንዲፈጠር ያደርጋል፤የሀገሪቱን ትልቁን ክለብ መለያ ለብሼ የምጫወትበት እድል በማግኘቴ የተሰማኝን ደስታ ስሜት ምን እንደሚገልፀው አላውቅም፡፡

ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስ ና ከነዓን ያገናኛቸው አጋጣሚ ነው ወይስ ለክለቡ የመጫወት ህልሙ ነበረህ?

ከነዓን፡- …ፈረንጆች “Dream come True’ እንደሚሉት የልጅነት ህልሜ ነው እውን የሆነው፤ እኔና ቅዱስ ጊዮርጊስ ስንፈላለግ የነበረው ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ነው፤ከ17 አመት በታች ሻምፒዮና ውድር ላይ ለአዳማ ከነማ ሀ-17 ቡድን ስጫወት የተደለደልነው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነበር፤እንደ አጋጣሚ ከእነሱ ጋር ሁለቴ ተገናኝተን ሁለቴም አሸንፈናቸዋል…ዋንጫውንም ወስደናል፤እንግዲህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው እነሱም ሲፈልጉኝ…እኔም ስፈልጋቸውየነበበረው፤በ2010ም…በ2011ም እንዲሁ ፍላጎት በሁለታኝም በኩል ነበር፡፡ በያዝነው አመትም በሁለተኛው ዙር ወደ ክለቡ ልቀላቀል የምችልበት አጋጣሚም ተፈጥሮ ነበር፤ነገር ግን ከአዳማ ጋር ኮንትራት ስለነበረኝ ሳይሳካ ቀርቶ፣የምንገናኝበት ቀን አልደረስ ብሎ እንጂ አነሱም ሲፈልጉኝ እኔም ስፈልጋቸው ነው የቆየነው፡፡

ሀትሪክ፡- …የቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያን ለብሶ የመጫወት ህልሙ ነበረኝ ብለሃል…?…ለዚህ ያበቃህ ምክንያት ምንድነው…?

ከነዓን፡- …አንደኛውና ትልቁ ምክንያት ክለቡ የአሸናፊነት…የድል ምልክት መሆኑ ነው…በርካታ ድሎችን በማስመዝገብ የሀገሪቱ ክለቦች የበላይ የሆነ ክለብ መሆኑ…ከሀገር አልፎ በአፍሪካ የውድድር መድረክም በጥንካሬው መታወቁ በርካታ ተጨዋቾችን ለ/ቡድኑ ያበረከተ …ፕሮፌሽናልነትን የሚከተል የደጋፊዎች ሀብታም የሆነ ክለብ መሆኑ…እኔም ወደ ክለቡ እንድሳብ ምክንያት ሆኖኛል፤በ2008 አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስማር ክለቡ ኢተርናሽናል ጨዋታ ሲያደርግ አዲስ አበባ ሲታዲየም ገብቼ ሳላህዲን ሰይድ ባገባት ግብ ቡደኑ ያሸነፈ እለት ደግሞ እኔስ አንድ ቀን የዚህን ክለብ ማልያ ለብሼ እንደዚህ አይነት ታሪክ እሠራ ይሆን? የሚል ጉጉት በውስጤ ተፈጠረ…በቃ…ከዚያች ቀን በኋላ በፈረሰኞቹ ተማረረኩ፡፡

ሀትሪክ፡- …ስለ ክለቡ ያለህ እውቀት የት ድረሰ ነው…?

ከነዓን፡- …የቅዱስ ጊዮርጊስን ታሪክ የማያውቅ የራሱን ታሪክ የዘነጋ ሰው ነው ብዬ ነው የማምነው፤ ምክንያቱም የክለቡ ታሪክ የአደባባይ ምስጢር ስለሆነ፤የቅዱስ ጊዮርጊስን ታሪክ እንኳን ስፖርት ውስጥ ያለ…ማንም የሚጠፋው አይመስለኝም፤እኔ የናዝሬት ልጅ ነኝ…ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ ሲባል እየሰማሁ ያደኩ ሰው ነኝ፤ደግሞም ታሪክን በማየትም በመስማትም ታውቃለህ፤እኔም ልክ እንደ ሌላው ቅዱስ ጊዮርጊስ የታሪክ፣የስኬት፣የአሸናፊነትና የሀገር ምልክት የሆነ ክለብ መሆኑን ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ባለፈው በሸራተን አዲስ የፊርማ ስነ-ስርዓቱ ሲከናወን ከአቶ አብነት ገ/መስቀልና ከሌላው የቦርድ አባል አቶ ዳዊት ውብሸት ጋር ማልያውንን ይዛችሁ ፎቶ ተነስታችሃል…የነበረው ስነ-ስርዓት ምን ይመስላል? የቦርዱን ፕሬዚዳንት በአካል ስታገኛቸው ምን ታዝበክ…?…ምንስ አወራችሁ…?

ከነዓን፡- …በጣም የሚገርም አጋጣሚ ነበር…፤…ከሁሉም ነገር በላይ የሰጡን ክብርና ያሳዩን ፍቅር ለክለቡ እንቅልፍ እንድታጣ የሚያደርግ ነው፡፡ አቶ አብነትን ከዚህ በፊት በአካል አግኝቻቸው አላውቅም ነገር ግን ለተጫዋቾች ስላላቸው አስተሳሰብ…ተጫዋቾች ህይወታቸው እንዲለወጥ…እግር ኳሱ እንዲያድግ ስለሚያደርጉት ነገር እሰማ ነበር፤በፊርማ ስነ-ሥርዓቱ ላይ በተግባር ያየሁት ነገር ግን ከሰማሁት በላይ ነው፤አቶ አብነት በጣም ብዙ የስራ ኃላፊነት ያላቸው…በርካታ ድርጅቶችን በኃላፊነት የሚመሩ…ከበርካታ ታላላቅ ኃላፊዎች ጋር የሚገናኙ ሰው ቢሆኑም…ከእኛም ጋር እኛን መስለው የሚታዩ…በጣም ተጨዋች…በጣም ተግባቢ…ቀለል ያሉ ሰው እንደሆኑ አይቼ ተገርሜያለሁ፡፡ ከእሳቸው ሌላም አቶ ዳዊት ውብሸትም እንዲሁም ቀለል ያለ ተግባቢ ሰው ነው፤የሰጡን ክብር…ፍቅርና የተጨዋቾ አያያዝና…አቀራረባቸውን ሳይ ሌሎች ክለቦችም ከዚህ ቢማሩ…ተጨዋቾችን በክብር ቢይዙ የተሻለ ነገር ሊሠሩ እንደሚችሉ ሊረዱ ይችላሉ የሚል ሃሣብ በውጤ ተፈጥሮአል፡፡

ሀትሪክ፡- …በግልስ ምን አወራችሁ…“አይዞህ አንተ ብቻ በርታ…ለክለቡ ስኬታማነት አስተዋፅኦ አድርግ እንጂ…ለገና አንድ ፎቅ ጣል አደርግልሃለሁ በማለት በጆሮህ ሹክ አሉህ?

ከነዓን፡- …(በጣም ያላባራ ሳቅ)… እንደዚህ አይነት ነገር አላወራ ንም፤ ምክንያቱም በጊዮርጊስ ቤት የሚቀድመው ቁስ እንዳልሆነ አው ቃለሁ፤ ማልያውን መውደድ እንጂ ጥምን ማሳደግ በቤቱ ቦታ የለውም፤ከእሳቸው ጋርም የፊርማው ስነ-ሥርዓት እስኪጀመር የማውራት እድል ቢኖረንም እንድንበረታ ሞራል ነው የሰጡን፡፡

ሀትሪክ፡- የጊዮርጊስ ተጨዋች መሆንህ በፊርማ አረጋጋጠሃል…ለክለቡ ምን አዲስ ነገር ይዘህ ትመጣለህ…?

ከነዓን፡- የተለየ ተዓምር ይዤ እመጣለሁ አልልህም፤ በቡደኑ ውስጥ…በሀገሪቱ አሉ የተባሉ የላቀ ችሎታ ባለቤት የሆኑ ምርጥ ምርጥ ተጨዋቾች አሉ፤በብ/ቡድን፣በኢንተርናሽናል መድረክ የላቀ ልምድና ችሎታ ባለቤት የሆኑ፣ታሪክ ያስመዘገቡ፣ድል የለመዱ ተጨዋቹ ያሉበት ቤት ነው፤በዚህ ስብሰብ ላይ እንደ አንድ ተጨማሪ ጉልበት ሆኜ የክለቡን ታሪክና ውጤት ለማስቀጠል ነው ወደ ክለቡ የምመጣው፤አቅሜ እስከፈቀደ ድረስ ለክለቡ ያለኝን ሁሉ ያለስስት ለመስጠት…ለስኬታማነት መስዋዕነት ለመክፈል ነው ለክለቡ የፈረምኩት፤አሁን እየተዘጋጀሁ ያለሁት ለዛ ነው፤ወደ ቅድስ ጊዮርጊስ የመጣሁት ከክለቡ ጋር ብዙ አዳዲስ ታሪኮችን ለማሳካት ነው፤ደግሞም የእግር ኳስ ምርጡን ታሪኬን በቅ/ጊዮርጊስ ቤት የማፃፍ ትልቅ ሀቅም አለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- …ለጊዮርጊስ መፈረምህ ቀደም ሲል ከፊርማካቸውና ከተዘዋወ ርክባቸው ክለቦች የተለየ የሚያደርገው ነገር አለ?

ከነዓን፡- …በጣም አለ…እንዳልኩህ ጊዮርጊስ የሀገሪቱ ትልቅ ክለብ ነው…የታሪክ፣የውጤት፣የደጋፊ ሀብታም የሆነ ክለብ ነው፤ከሀገር አልፎ በአፍሪካ መድረክም የሚታወቅ ክለብ ነው፤ከዚህ አንፃር በጣም ይለያል፤ለክለቡ ፊርመህ ማልያውን ለመልበስ አንዳንዴ ከችሎታህ በተጨማሪ መታደልም ያስፈልጋል፤ ሁሉም ክለብ የራሱ ነገር ቢኖረውም ከእስከ አሁኑ የእግር ኳስ ህይወቴ የቅ/ጊዮርጊስ ለየት ይልብኛል፡፡

ሀትሪክ፡- …ለዝዝውውሩ ምን ያህል ብር ተከፈለህ? ብዬ ብጠይቅህ ምን ትለኛለህ?

ከነዓን፡- …(በጣም ሳቅ)…ይሄ ጥያቄ ለጊዜው ይለፈኝ ነዋ የምልህ…(አሁንም ሣቅ)…

ሀትሪክ፡- …የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ሙዝሙርን ከወዲሁ ማጥናት ጀም ረሃል…?

ከነዓን፡- …የሚገርምህ አሁን ለማለት ወይም ለመወደድ ስል አይደለም የምመልስልህ፤የክለቡን መዝሙር የማውቀው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (ግቢ) እያለሁ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ እኔ መዝሙሩን ስዘምር የነበረው ከድሮ ጀምሮ ስለነበር እንደ አዲስ ማጥናት አያስፈልገኝም፡፡

ሀትሪክ፡- ከዚህ በኋላ ደጋፊው ስምህን እየጠራ የሚዘምርበት አጋጣሚ ይፈጠራል፤እስቲ ስለ ክለቡ ደጋፊ ከወዲሁ ምን ትላለህ?

ከነዓን፡- …ደጋፊው በእኔ አንደበት የሚገለፅ አይደለም…በእውቀት የሚደ ግፍ… በጣም ስነ-ስርዓት ያለው…ኳስን ከልቡ የሚወድ ደጋፊ ነው፤ሁሌም ለአግር ኳሱ ድምቀት…ተጨዋቾችን ለማበረታታት አዳዲስ ነገር የሚፈጥር አእምሮ ያላቸው ምርጥ ደጋፊዎች ናቸው፡፡

ሀትሪክ፡- …በዚህ መልኩ ለገለፅካቸው ደጋፊዎች ምን አይነት መልዕክት ታስተላልፋለህ? ምንስ ቃል ትገባለህ?

ከነዓን፡- …ይሄ ክፉ ወረርሽኝ አልፎ ወደ ሜዳ ስንመለስ እናንተን በደንብ ለማስደሰት…ለመካስ ወደ ክለቡ የመጣሁበትን ምክንያት ለማሳየት ከወዲሁ መዘጋጀቴን ነው የምገልፀው፤ከቡድኑ ተጨዋቾች ጋር በጋራ በመሆን ሁሌም ደስታን እንደምንፈጥርላቸው ነው ቃል መግባት የምፈልገው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር አናሳፍራችሁም…እግዚአብሔር ለውድድር ያብቃን እንጂ እንደአለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት (የዘንድሮውን ጨምሮ) መከፋት፣ባዶ እጃችሁን ወደ ቤት መሄድ አይኖርም፤ወደ ለመዳችሁት አሸናፊነትና…ወደተለመደው ክብራችሁ እንመልሳች ኋለን፤ ለዚህ ደግም የምሰስተው ነገር አይኖረኝም… ማለት ነው የምፈልገው…፡፡

ሀትሪክ፡- …በልጅነህ ስትደግፈው ለነበረው ክለብ ፊርማህን ካኖርክ በኋላ የክለቡን ማልያ መቼ ነው ለብሼ የምጫወተው የሚል ጉጉት በውስጥህ አልተፈጠረም?

ከነዓን፡- …በጣም ትልቅ ጉጉት በውስጤ አለ፤ በቡርቱካናማ ለባሽ ደጋፊዎች ታጅቦ መጫወት ያለው ስሜትን ለማጣጣም…ክለቡን ለማገዝ በጣም በጣም ነው የጓጓሁት፡፡ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጫወት ካልጓጓህ ምን ሊያጓጓህ ነው?…አምላክ ብቻ ኮሮናን ያጥፋልን…ወደ ሜዳ ይመልሰን እንጂ…ጉጉቴ በቃላት አይገለፅም…ደግሞ አይቀርም ቀኑ ደርሶ ጉጉቴን እወጣለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- …ግን እኮ በቦታህ…በጣም ምርጥ…ምርጥ የሚባሉ ተጨዋቾች አሉ፤ ከዚህ አንፃርስ አትሰጋም?

ከነዓን፡- …ትክክል ነህ…በጣም ምርጥ…ምርጥ የሚባሉ ተጨዋቾች አሉ…ግን…ለክለቡ ስፈርም ይሄንን አውቄ…ራሴንም ለፈተና እንደማዘጋጅ አውቄ ነው፤ጊዮርጊስ የምር ጦች ስብስብ ወይም አሉ የተባሉ ተጨዋቾች ያሉበት ቤት እንደሆነ አውቃለሁ፤በእኔ የጨዋታ ሚናም የማይቀመሱ ምርጥ ልጆች እንዳሉም አይጠ ፋኝም፤ ግን የሚያወጣህ ስራህ ነው…የተሻልኩ ሆኜ ካልቀ ረብኩ ቦታ እንደማይኖረኝ አውቃ ለሁ፤ ስለዚህ ጠንክሬ ሰርቼ ብቁ ሆኜ ለመቅረብና ሌላውን ውሳኔ ለአሰልጣኙ መተው ነው የምፈልው፤ከእኔ የሚፈለገውንና የሚጠበቀውን ማድረጌ ብቻ ነው የሚያስጨንቀኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ የዘን ድሮውን ጨምሮ ለሶስት ዓመታት ከሊጉ ዋንጫና ከሀገር ውክልና ውጪ ሆኖ ነው ያሳለፈው፤ስለዚህ ነገር ምን የምትለው አለ?

ከነዓን፡- …በዚህ ጉዳይ ለመ ናገር ሙሉ ነኝ ብዬ አላስብም…ምክንያቱም ገና ፊርማዬ እንኳን አልደረቀም፤ግን በእኔ የግል አረዳድ…ይሄ ከክለቡ ባህልና ታሪክ ውጪ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በጊዮርጊስ ቤት ያልተለመደና አዲስ ታሪክ ነው፤ጊዮርጊስን የማይመጥን የማይገልፁ ዓመታትም ናቸው፡፡ ያለ ድል ባለፉት ዓመታት ላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የጊዮርጊስ ስም ከሻምፕዮንነትና ከሀገር ውክልና ውጪ መሆኑ በጣም የሚያስቆጭ ነው፤እኔም ከቡድን ጓደኞቼ ጋር በመሆን ክለቡን ወደሚታወቁበት አሸናፊነትና ወደ አፍሪካ የውድድር መድረክ እንዲመለስ የበኩሌን ጥረት አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- …ከነዓን ምን አይነት ሰው ነው…?

ከነዓን፡- …ከሰው ጋር ብዙም ለመግባባት የሚቸግረኝ አይነት ሰው ነኝ፤ከዚህ ውጪ ከጓደኞቼ ጋር በጣም እጫወታለሁ…እግባበለሁ፣መዝናናት፣መሳቅ መጫወት ደስ ይለኛል፡፡ ሜዳ ውስጥ ስገባ ግን ስራዬ ስለሆነ ከዚህ በተቃራኒ ሲሪዬስ ነኝ፤ በስርዓት የመስራት ግዴታ አለብኝ፤ ካልደረሱብኝ አልደርስም፤ እየተመ ታሁ እንኳን ዝም ብዬ ነው የምጫወተው፤ሜዳ ውስጥ መናገር ያስጠላኛል፤ሁሌም ትኩረቴ ስራዬ ላይ…ኳስ ላይ ነው የማደርገው፡፡

ሀትሪክ፡- በ2008 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስትማር እንደነበር አውቃለሁ፤ ትምህርቲ የት ደረሰ?

ከነዓን፡- አዎን አንድ ዓመት እንደተ ማርኩ ከኳሱ ጋር አብሮ ሊሄድልኝ ስላልቻለ ዊዝድሮው አድርጌያለሁ፤በዚያን ጊዜ የቤተሰቡ ትልቁ ልጅ አኔ ስለሆንኩ ከባድ ኃላፊነት ነበረብኝ፤ ቶሎ ለቤተሰቤ መድረስና መርዳት ስለነበረብኝ ትምህርቱን አቁሜ ወደ እግር ኳሱ አዘንብያለሁ፤ራሴን፣ቤተሰቤን መርዳት የምችልበት ነገር ያስፈልገኝ ስለነበር ለዚያ ደግሞ በወቅቱ እግር ኳስን መጫወት የምችልበት አቅሙ ስለነበረኝ ትምህርቱን ትቼ ወደ ኳሱ አዘንብያለሁ፡፡ኳሱንም ትምህርቱን አብሬ ለማስኬድ ሞከርኩ አልቻ ልኩም፤ በዩኒቨርስቲ ደረጃ ስትማር የተሻለ ውጤት ለማ ምጣት ሙሉ ጊዜ ሰጥተህ ማጥናት አለብህ፤ኳሱ ደግሞ ለዚህ አይመችም፡፡ ተዟዙረህ ስለሆነ የምት ጫወተው ከዚህ አንፃርም ትምህርቴን ማስኬድ አልቻልኩም፤ አንድ ዓመት ተምሬ ዊዝድሮው አድርጌያለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- …ምን ነበር የምታ ጠናው? በቀጣይስ የመቀጠል ሃሳቡ የለህም…?

ከነዓን፡- …ሳጠናው የነበረው ስፖርት ሳይንስ ነበር፣ ትምህርቱ በኳስ ውስጥ እያለ ሁም… ከኳሱ ስለይም በጣም የሚጠ ቅመኝ ነበር… ግን አልሆነም፤አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው በወቅቱ የወሰንኩት ውሳኔ ከነበረብኝ ችግር አንፃር ልክ ቢሆንም ማቋረጤ ግን ዛሬ ላይ ያንገበግበኛል፤ከዚህ መነሻነት በቀጣይ እንደእግዚብሐር ፈቃድ ትምህርቴን የመጨረስ እቅድ አለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ሌላው በ2010 ክረምት አካባቢ ወደ ሰርቪያ ሄደህ ነበር…ባይሳካልህም ምን ተማርክበት?

ከነዓን፡- …ትክክል ነህ ሄጄ ነበር… በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ተመልሼያለሁ፤ ብመለስም ግን ትልቅ ትምህርትና ልምድ አግኝቼ ነው የተመለስኩት፡፡ ብዙውን ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ታለንቱ አለን…ኳስ እንችላለን እንላለን…ግን ታለንት ብቻውን ብዙ ርቀት አይወስድም እኛ ታለንቱ አለን እንደምንል ሁሉ እነሱ ፊዚካሊ ፊት ናቸው፤በጣም ጠንካሮች ናቸው፤ሰራተኞችም ናቸው፡፡ በጣም ከምነግርህ በላይ ስራቸውን ያከብራሉ፤ይወዳሉ፡፡ ስራህን የምታከብር ከሆነ ስኬታማ ትሆናለህ፡፡ ሰርቪያ ላይ እንዳየሁት ሁሉም ተጨዋቾች በፕሮፌሽናል አእምሮ የተገነቡ ናቸው፤በኳስ ስኬል እኛ የተሻልን ነን…በአካል ብቃት ግን በደንብ ይበልጡናል፤ታክቲካሊ ዲስፒሊንድ ናቸው…ታክቲካሊ ዲስፒሊንድ የምትሆነው አካል ብቃታህ ጥሩ ሲሆን ነው…ኳስ ስለቻልክ ብቻ እጫወታለሁ ማለት አይቻልም…ይሄንን ሁሉ አይቼ ተምሬ ነው የመጣሁት፡፡

ሀትሪክ፡- …ይሄን አይተህ ከተመለስክ በኋላ ፕሮፌሽናል ተጨዋች የመሆን ህልምህ ላይ ተስፋ ቆረጥክ?

ከነዓን፡- …በፍፁም ተስፋ አልቆርጥም…ፕሮፌሸናል ተጨዋች ለመሆን ገና ብዙ እንደሚቀረኝና ብዙ መስራት እንዳለብኝ ተምሬ ስለመጣሁ በዚያ ለይ ጠንክሬ መስራትና ራሴን በደንብ ማዘጋጀት ከዚያ በኋላ ዕድሉን መሞከር ነው ያሰብኩት፡፡አሁንም የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ህልሜ ትልቅ ነው፤ የራሴንም የሀገሬንም ስም የማስጠራት ትልቅ ህልም ነው ያለኝ፡፡ ከፈጣሪ ጋር ቢሆንልኝና ቢሳካልኝ በጣም ነው የምደሰተው፤አሁን ደግሞ ጊዮርጊስ ገብቻለሁ፤ጊዮርጊስ በጣም ትልቅ ክለብና በአፍሪካ መድረክ በመሳተፉ በጣም የሚታወቅ ክለብ ነው፤በዚህ ቡድን ውስጥ መታቀፌ በራሱ ለሕልሜ አንደኛው አቋራጭ መንገድ ነው፡፡ በዚህ ቡድን ውስጥ በመታቀፌ በራሱ እኔ ሳልሄድ ዕድሉ ያለሁበት ድረስ ሊመጣ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል፤በአጠቃላይ ቅድሚያ የምሰጠው ለክለቤ ቢሆንም ፕሮፌሽናል የመሆን ሕልም ማለሜንም እቀጥላለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- …አዳማ አንተን ከታዳጊነት አንስቶ ለዚህ ያበቃህ ክለብ ነው፤አዳማን መለየት አልከበደህም?

ከነዓን፡- በጣም ትልቁና ሲረብሸኝም የነበረው ነገር ይሄ ነው፤አዳማ ባለውለታዬ ነው፤ለዚህ የበቃሁትም ምክንያት የሆኑኝም እነሱ ናቸው፡፡ አዳማዎችን በጣም ነው የምወዳቸው፤የማከብራቸውም፡፡ ከእነሱ ባልለይ በጣም ደስ ይለኝ ነበር፤ግን ሕይወት ነው፤እነሱም ይረዱኛል ብዬ አስባለሁ፤ሁሌም ለአዳማዎች መልካሙን ሁሉ ነው የምመኘው፤አሳድገው ለዚህ ስላደረሱኝ ከልቤ አመሰግናቸዋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ሳላመሰግናቸው ባልፍ ተገቢ አይሆንም ቅር ይለኛል በሚል የምታመ ሰግናቸው ካሉ?

ከነዓን፡- ለእኔ እዚህ መድረስ የብዙ ሰዎች ርብርቦሽ አለ፤ሁሉንም መጥቀስ ለእኔ ከባድ ነው፤ቦታህም ላይበቃኝ ይችላልየዘነጋኋቸው ካሉ ይቅር እንዲሉኝ እጠይቃለሁ፡፡ በዚሁ በኩል በመጀመሪያ ፈጣሪዬን… ከትንሽነት አንስቶ ትልቅ ያደረገኝ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ከእሱ ውጪ አባትም እናትም ሆኖ ያሳደገኝ ወላጅ አባቴን…በልጅነቴ ያሰለጠኝን ሄኖክ ዘለቀ፣ከዚያ ከፍ ስል በፕሮጀክት ወክማ የሚባል ፕሮጀክት ውስጥ ያሰለጠነኝ አትክልት እሱ በእኔ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው፤በ2006 ምትኩ ፈቃዱ 2007…አዳማ ሀ-17 ውስጥ እያለሁ የዛሬ መንገዴዴን የከፈተልኝ ኤፍሬም እሸቱ በጣም ምርጥ ቡድን ከመገንባት ባለፈ ሻምፕዮን እንድንሆን ያደረገ፤በጣም ከፍ እያልኩ እያደኩ እየበሰልኩ ስመጣና ወደ ዋናው ቡድን ካደኩ በኋላ የዋናው ቡደን ስታፍ አባላት አሸናፊ በቀለ፣አሁን በሰበታ የውበቱ ምክትል የሆነው ይታገሱ፣ ፊዚዮትራፒስቱ ጃክና ሌሎችም አሸብር ወደ አ.አ ዩኒቨርስቲ እንድሄድ ምክንያት የሆነኝ አሰልጣኝ ተገጌ ነጋሽ፣፣ በፀሎት ልዑልሰገድ፣ወደ አዲስ አበባ ከነማ ያመጣኝ ስዩም ከበደንና ሌሎችንም በእኔ የእግር ኳስ ህይወት አሻራቸውን ያሳረፉትን ሁሉ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.