ወልቂጤ ከተማ ለአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የ6 ወር ደመወዝ ልክፈል አለ

ፌዴሬሽኑ አልተቀበለውም
-ፌዴሬሽኑ ለድጎማ የወሰነው 28 ሚሊዮን ብር እስካሁን አልተከፈለም
– ለሉሲ አሰልጣኝ 30 ሺህ ብር ለዋሊያ አሰልጣኝ 125 ሺህ ብር…?
– ለ3 ብሔራዊ ቡድን፣ ለ10 አሠልጣኞች በወር 500 ሺህ ብር በዝቷል?


የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዋሊያዎቹን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን ውል አላድስም ማለቱን ተከትሎ የወልቂጤ እግር ኳስ ክለብ የአሠልጣኙን የ6 ወር ደመወዝ ልክፈል ማለቱን ፌዴሬሽኑ ውድቅ አደረገው፡፡
የሀትሪክ ምንጮች እንደገለፁትና የፌዴሬሽኑ የጽ/ቤት ኃለፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እንዳመኑት የክለቡ ፕሬዚዳንት የሆነው አቶ አበባው ሰለሞን ደውሎ የ6 ወር ደመወዙን ለመቻል መጠየቁን አምነው ጥያቄውን ለብሔራዊ ቡድን ካለው መልካም ሃሳብ ተነስተው እንደሆነ ገምተናል ሲሉ ተናገረዋል፡፡ ዋና ፀሐፊው ለሀትሪክ ሲናገሩ “ተቋሙ ለዚህ አያንስም አሰራሮች ተስተካክለው ተቋማዊ መሆን አለባቸው አሁንም ውላቸው ላልታደሰ አሰልጣኞች ገንዘብ የመክፈል አቅም አለን ነገር ግን ውድድር በሌለበት እግር ኳሱ በተቋረጠበትና መች እንደሚጀመር ባልታወቀበት ውሉን አለማደሳችን ተገቢ ነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

“በኛ በኩል የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው ላቀረበው ጥያቄ አመሰግነን ቅድሚያ ግን በክለባቸው ላሉ ተጨዋቾች ተገቢውን ክፍያ በጊዜ እንዲከፍሉ ነግረን ተለያይተናል” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ 2.8 ሚሊዮን ብር ለክልልና ከተማ አስተዳደር ፌደሬሽኖች ድጎማ አበርክተናል የገንዘብ ችግር የለም ቢሉም ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ገንዘቡ አለመለቀቁ የሀትሪክ ምንጮች አስረድተዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ በተደጋጋሚ ጊዜ የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን አመራሮች ቢሮን ያንኳኳበት ምስጢር የገንዘብ እጥረት መሆኑን ለፌዴሬሽኑ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ለአሰልጣኞቹ የምንከፍለው ገንዘብ አላጥንም የሚሉት የፌዴሬሽኑ የቢሮ ኃላፊዎች በተቃራኒ ደግሞ ለአስሩ አሰልጣኞች የሚከፈለው ገንዘብ ብዙ ነው ማለታቸው በአካውንታቸው ያለው ገንዘብ መመናመኑን ላለማመን የተደረገ ምክንያት ነው በማለት ፌዴሬሽኑን የሚተቹ ሰዎች ተበራክተዋል፡፡ አሁን ድረስ ፌዴሬሽኑ .8 ሚሊዮን ብር በአካውንቱ ውስጥ ለወጪ ተዘጋጅቷል ወይ የሚለውን በርካቶች ይጠራጠራሉ፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለዋሊያዎቹና ለሉሲዎች አሰልጣኞች ይከፍል የነበረው ደመወዝ ልዩነት መስፋቱ የጾታ ልዩነት እያደረገ ነው እንዴ የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ ታውቋል፡፡ ሀትሪክ በደረሳት መረጃ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የተጣራ 125 ሺህ ብር የሉሲዎቹ አለቃ ብርሃኑ ግዛው የተጣራ 30 ሺህ ብር የሚከፈላቸው መሆኑ ቅሬታ አስነስቷል፡፡ በሁለቱ አሰልጣኞች የ4 እጥፍ ክፍያ ልዩነት ያለ ሲሆን በ2005 ሉሲዎቹና ዋሊያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፉ ሼህ መሀመድ አላሙዲን የጾታ ልዩነት ሳያደርጉ ለሁለቱም አምስት አምስት ሚሊዮን ብር በሽልማት መልክ ማበርከታቸው ሲታይ የሁለቱ አሰልጣኞች የደመወዝ ልዩነት መስፋቱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በተለይ የሁለቱ አሰልጣኞች ደመወዝ እኩል ይሁን ማለት ባይቻልም ሊቀራረብ እንደሚገባና ይህን ያህል ልዩነት መስፋቱ ተገቢ አይደለም የሚሉ የስፖርት ቤተሰቦች በርካታ ናቸው፡፡ ሀምሌ 30/2012 ለሚጠናቀቀው የአሰልጣኝ አብርሃም ኮንትራት ውል እንደማይታደስ ሀምሌ 2 ይፋ ሲደረግ የሉሲዎቹ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ኮንትራት ሰኔ 18/2012 ተጠናቆ ውሉ እንማይታደስ የተነገረው ግን ከሁለት ሳምንት በኋላ ሀምሌ 2/2012 መሆኑ ልዩነቱ የሚያሳይ ተደርጎ ተወሰዷል፡፡ የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩም ልዩነቱ የሰፋ መሆኑን አምነው ምክንያቱ ደግሞ የአልጣኞች የቅጥር ሁኔታ የሚገልፅ ማኑዋል ባለመኖሩ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ አቶ ባህሩ ፌዴሬሽኑ ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት የቅጥር ሂደቱን የሚያስተካከል ማኑዋል እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ ባህሩ እንደሚሉት “በወር ለአልጣኞች የሚከፈለው ብር በዝቷል የሚል አቋም አለን በወር 500 ሺህ ብር ለሶስቱ ብሔራዊ ቡድኖች አሰልጣኞች ስንከፍል ቆይተናል ለዋሊያዎቹ 4 (ለዋና፣ ለምክትል፣ ለግብ ጠባቂ አሰልጣኞችና ለፊዚዮቴራፒስት) ለሉሲዎቹ 3 /ዋና፣ ምክትል ግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን /ዋና፣ ምክትልና ግብ ጠባቂ አሰልጣኞች/ እየከፈልን ቆየተናል አሁንም የአቅም ጉዳይ ሳይሆን ለብሔራዊ ቡድኑ የሚጨምር ነገር ስለሌለ ውሉን አላደስንም” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport