“ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አሁንም በቂ የሆነን ጥንቃቄ እያደረግን ነው ብዬ አላስብም”አህመድ ረሺድ /ሺሪላ/ (ኢትዮጵያ ቡና)

ኮቪድ 19 እንደ ሌላው ዓለም ሁሉ ወደ አገራችን ከገባ ወራትን አስቆጥሮ ያለፈ ሲሆን በእዚህም ወረርሽኝ ምክንያት እግር ኳሱ በእኛም ሀገር ሊቋረጥ መቻሉ ይታወሳል፤ ይሄ ሊግ ከተቋረጠ በኋላም ቫይረሱን ለመከላከል እንዲቻል የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራቶች በአገራችን የስፖርቱ አካባቢ እና በሌሎች ስፍራዎች ላይም እየተከናወነ ይገኛል፤ በእዚህም የገንዘብ እና የቁሳቁስ ማሰባሰብ ፕሮግራሞች ላይ የተለያዩ እግር ኳስ ተጨዋቾች እንደ ግልም እንደ ቡድንም በመሆን ማህበራዊ ጉዳይ ላይ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ ሲገኙ ከእነዚህም ተጨዋቾች መካከል አንዱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የኢትዮጵያ ቡናው የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች አህመድ ረሺድ /ሺሪላ/ ይገኝበታል፤ ይሄን ተጨዋች ስለ ኮሮና ቫይረስ፣ ኮሮናን እንዴት መከላከል እንደሚቻል፣ ስለ ማሀረበራዊ ተሳትፎው፣ ይሄን ጊዜ በምን እንደሚያሳልፍና ወጣ ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቀነው ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቶናል፡፡

ሀትሪክ፡- ኮሮና ቫይረስ /ኮቪድ 19/ አሁንም ድረስ ለዓለም ከፍተኛ ስጋት ሆኗል፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎችም አሳጥቶናል፤ ስለወረርሽኙ ወደ አገራችን መግባቱን ካወቅክበት ጊዜ ጀምሮ ያለህ ስሜት ምን ይመስላል?
አህመድ፡- እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቫይረሱ ሀገራችን ውስጥ ገባ ከተባለበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ነገር ስሰማ በግሌ ከባድ የሆነ ስጋት ውስጥ ነው የወደቅኩት፤ ምክንያቱም እንደምታውቀው የአገራችን የጤና ሴክተር ትንሽ ደከም ያለ ስለሆነና በእዚሁም የህክምናው ዘርፍ ደግሞ ትልልቅ የሚባሉት የአውሮፓ ሀያላን ሀገራት ማለትም እነ ስፔን፣ ጣሊያንና የመሳሰሉት ሀገራት በቀዳሚነት ስፍራው ላይ ሆነው ምንም ነገሮችን ሊፈጥሩ ስላልቻሉ ከዛ ተነስቼ ነው እኛ ከምንሰጠው ዝቅተኛ እና አነስተኛ ህክምና አኳያ እነሱ ያልቻሉትን እኛ እንዴት እንችለዋለን የሚል ስሜት በውስጤ ስለተፈጠረብኝ የወረርሽኙን መግባት ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሰማው ከፍተኛ የድንጋጤ ስሜት ነው በውስጤ ሊፈጠርብኝ የቻለው፡፡
ሀትሪክ፡- ኮቪድ 19 ወደ አገራችን መግባቱን በቅድሚያ እንዴት አወቅህ? በእዚህ ወረርሽኝ ዙሪያስ ህብረተሰቡ ሊጠነቀቅ እንዲችል ምን የምታስተላልፈው መልህክት አለህ?
አህመድ፡- የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አገራችን መግባቱን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ከጅማ አባጅፋር ጋር በተጫወትንበት ዕለት እና ተጫውተንም እየተመለስን በነበርንበት ሰዓት ነው፤ ወዲያውንም ስለ በሽታውም ስንሰማ በጣም ነው የደነገጥነው፤ ስለዚህም ይሄን በሽታ በተመለከተ አሁን ላይ ላስተላልፍ የምፈልገው ነገር ቢኖር መደንገጡ ብቻ ምንም አይነት መፍትሔ ስለማይሆን በመንግስት እና በህክምና ባለሙያዎች ደረጃ የሚሰጡትን መመሪያዎች አስፈላጊ በሆነ ሁኔታ በተግባር ላይ በማዋል እንደዚሁም ደግሞ ራሳችንንም በመጠበቅ ነው ጥንቃቄ ልናደርግ የሚገባን፤ ይህን ካደረግን በሽታው ምንም እንኳን አስከፊ ቢሆንም የመዳን እድል አለውና ያን በትክክል ከሰማከው፤ ከተገበርከው፤ ሰምተህም ከፈጣሪም ልመናውን ካገኘህ በሳይኮሎጂ እና በምንም ነገር ጠንካራ የምትሆንበት ነገር አለና በእዚህ ነው ልንጓዝ የሚገባን፡፡

ሀትሪክ፡- ህዝባችን ግን ኮሮና ቫይረስን እየተጠነቀቀ ነው ማለት ይቻላል?
አህመድ፡- ኡ!ኡ! በፍፁም፤ በእዚህ በኩል እንኳን መንግስት በጣም አሳስቦ አሳስቦ ሊሰራበት የሚገባው ነገር ይሄ ነው፤ በተለያየ አጋጣሚ ለእዚህ ቫይረስ መከላከያ ይሆን ዘንድ በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ በመሰማራት የተለያየ ቦታዎች ሄጃለው፤ እዛ የምታየው ነገር ኢትዮጵያ በተቃራኒው ቻይናን ነው የምትመስለው፤ እኛ በሽታውን ተቆጣጥረንም ሌሎች ሀገራትንም የምንረዳም ነው የሚመስለው፤ ከዛ ውጪ ሁሉም ግድየለሽም ነው፤ ተራራቅ ስትለው ተቀራርቦ ታየዋለህ ከዛ ውጪም ሌሎች ሌሎች ነገሮችንም ሲያደርግ ታየዋለህ፤ እና ሰዉ መመሪያን ካለማክበር ጋር በተያያዘ ከመንግስት ጋርም እልህ የተጋባም ነው የሚመስለው፤ ስለዚህም ከመንግስት ጋር እልህ ተጋባህ አልተጋባህ አንተን ነው እንጂ የሚጎዳህ እነሱን አይደለም፤ ስለዚህም እንደ ሀገር ጠቃሚ የሆኑና ጥሩ ነገርን እያደረጉልን ያሉ ሰዎችን እናሳጣቸዋለን፤ ለእነሱ እኛ ካልተጠነቀቅንላቸው ልፋታቸው ከንቱ ነው፤ ያ ስለሆነም መንግስት አሁንም አሁንም በዚህ ጉዳይ ላይ ሊያስብበት ይገባልና እንደ አንድ ግለሰብ በጣም የታዘብኩት ነገር ይሄን ነው፤ በአጋጣሚ አንድ ቦታ ላይ እርዳታ ለማድረግ ሄደን የገጠመኝንም ልናገር አታሟርትብኝም የሚልህ አለ፤ እናውቃለን ከሚሉ ሰዎች ሁሉ ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችንም ትሰማለክ፤ የማይጠበቅ አስተሳሰቦችም ይታሰባልና ይሄን ነገር ህዝባችን ሊጠነቀቀው ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ እየተሳተፍክ ይገኛልና በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
አህመድ፡- እንደ እኛ በኢኮኖሚዋ ደካማ እንደሆነች ሀገር በእዚህ ማህበራዊ ጉዳይ ላይ በመሳተፌ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ህዝቡም ያለውን ነገር እየሰጠም ነው፤ ይሄ ይበልም ያሰኛል፤ በእስልምና እምነትም ስጥ ይሰጥሃል የሚልም ነገር አለና እኔም እንደ ግልም እንደ ቡድንም ባለኝ አቅም እርዳታን አድርጌያለው፡፡
ሀትሪክ፡- እኛ ለእኛ የሚል ተቋምም በቅርቡ ተቋቁሞ በእዛ ፕሮግራም ላይ በመጋበዝ ጉብኝትን አድርገሃል፤ አንድ አንድ ነገርም ለማድረግ ቃል ገብታችኋል፤ ተቋሙን እንዴት አገኘኸው?

አህመድ፡- የእኛ ለእኛ ተቋም እስካሁን ኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ እየተደረጉ ካሉ ፕሮግራሞች ሁሉ ለየት ያለ ነገርን ሲሰራ ተመልክቼያለው፤ ይሄ ተቋም የጎዳና ተዳዳሪዎችን ጨምሮ አዘውንቶችንም ጭምር ለመደገፍ የተነሳ ነው፤ በቁሳቁስም ሆነ በገንዘብ ድጋፍ ስለሚፈልግ ከጎኑ ልንቆምለት ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- በኮሮና ቫይረስ ኳስን ካቆምክ በኋላ ምን እየሰራ ነው? ከኳስ መራቅስ ስሜቱ ምን ይመስላል..
አህመድ፡- ከኳስ መራቅ በጣም ከባድ ነው፤ ብዙ ነገሮችም ይናፍቁሃል፤ በተለይ የቡድን ጓደኞችና ደጋፊዎች፤ ስለዚህም ይህ ውድድር ፈጣሪ ሁሉንም ነገር ሰላም አድርጎልን ብንጀምረው ደስ ይለኛል፤ ከኳሹ ከራቅኩ በኋላም በግሌ ልምምድን እየሰራወ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ለአንተ ከባዱ እና የሚያስቸግርህ አጥቂ ማን ነው?
አህመድ፡- ብዙዎቹ አጥቂዎች ጥሩ ቢሆኑም ከሁሉም በተሻለ ሳላህዲን ሰይድ ነው ያንን ያህል ባይከብደኝም አንድአንዴ ግን የሚያስቸግረኝ ወቅት አለና እሱን ነው በቀዳሚነት ስሙን መጥራት የምፈልገው፡፡
ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ አብረኸው ባለመጫወቱስ የሚቆጭህ?
አህመድ፡- ከአጠገቡ ሆኜ ባለመጫወቴ አሁንም ድረስ የሚቆጨኝ ተጨዋች ራሱ ሳላህዲን ሰይድ ነው፤ ከእሱ ጋር በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የብሄራዊ ቡድን የተጨዋቾች ስብስብ ውስጥ ቡድኑን በያዘው ሰዓት ብቻ ልምምድን ማድረግ ነው የቻልኩትና ከእዚህ የተለየ አጥቂ ጋር አብሬው ከአጠገቡ ብጫወት በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ አብረኸው ስትጫወት የተለየ ስሜት የሚሰጥህ ተጨዋችስ አለ?
አህመድ፡- አዎን፤ በተለይ ከመስዑድ መሐመድ ጋር፤ እንደዚሁም ደግሞ ከአቡበከር ናስር፣ ከዳዊት እስጢፋኖስ፣ ከኤፍሬም ወንድወሰን እና ከኤልያስ ማሞ ጋር ስጫወት በጣም ደስ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- መፅሐፍቶችን የማንበብ ልምዱ አለህ?
አህመድ፡- አዎን፤ ግን የማነባቸው መፅሐፍቶች እንደ እምነቴ ሀይማኖት ነክ የሆኑትን ነው፤ በተለይ የሐዋሪያቶችን የህይወት ታሪክ በህክምናው ሙያና በሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ አሉና የእነሱን ሳነብ በጣም ደስ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ከአውሮፓ ሀገራት እግር ኳስ ጨዋታዎች ውስጥ የየትኛው ሀገር የሊግ ውድድር ይበልጥብሃል?
አህመድ፡- የሁሉንም ሀገራት ሊጎችን የምከታተል ቢሆንም ለስፔን ላሊጋ ቅድሚያውን እሰጣለው፤ የባርሴሎናም ደጋፊ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ከእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የምደግፈው ቡድን አለ?
አህመድ፡- አዎን፤ የአርሰናል ደጋፊ ነኝ፤ የእነሱ ብሆንም አሁን ባለው እግር ኳስ ጨዋታ ደግሞ የማንቸስተር ሲቲም ጨዋታም ይስበኛልና እነሱንም እየወደድኳቸው ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ሊቨርፑል የፕሪምየር ሊጉን ውድድር በሰፊ ነጥብ ተከታዩን ማንቸስተር ሲቲን እየመራ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ውድድሩ ተቋርጧል፤ ይሄ የሊግ ውድድር ከዚህ በኋላ ባይካሄድ ዋንጫው ሊሰጠው ይገባል ወይንስ አይገባም?
አህመድ፡- እንደ እኔ የእግር ኳስ አመለካከት አንድ ክለብ ረጅም የውድድር ጉዞን አድርጎ እና ብዙ ውጣ ውረዶችንም አይቶ ተከታዮቹን በበርካታ ነጥቦች ከበለጠና የሊጉ ውድድር የማይቀጥል ከሆነ ዋንጫው ሊሰጠው ይገባል፤ ስለዚህም እኔ የሊቨርፑል ደጋፊ ባልሆንም፤ የክሎፕ አድናቂ ባልሆንም፤ ለቡድኑ ጥላቻ ባይኖረኝም የረጅም ዓመታት የዋንጫ ጥሙ በአንድ እና በሁለት ጨዋታዎች ሊያጣ አይገባውምና ዋንጫው ቢሰጠው በጣም ደስተኛ ነው የምሆነው፡፡
ሀትሪክ፡- በዓለም እግር ኳስ የየትኛው ተጨዋች አድናቂ ነህ?
አህመድ፡- የሊዮኔል ሜሲ፤ እሱ ለእኔም ሆነ ለዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያን ሁሉ የተለየ ተጨዋች ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ……?
አህመድ፡- እባካችሁ ወገኖቼ፤ ወገኖቼ ይሄ የኮቪድ 19 ቫይረስ ሀይማኖትን ዘርን ምንም የሚለየው ነገር የለምና እንጠንቀቅ ነው የምለው፤ ለቤተሰባችን ለአገራችን አስፈላጊው ሰውም ነንና ሁላችንም በየእምነታችን እየፀለይን የጤና ጥበቃና መንግስትንም መመሪያዎችን አዘወትረን እየተጠቀምን እንቆይ በመጨረሻም ዓላ ሀገራችንን ይባርካት፡፡

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook

hatricksport team

Hatricksport team