መነሻ ገጽ ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣ ከጅማ ኩሎበር እስከ ሳንፍራንሲስኮ አሜሪካ ደያስ አዱኛ
ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣብቸኛዋ ባለቀለም የስፖርት ጋዜጣ

ከጅማ ኩሎበር እስከ ሳንፍራንሲስኮ አሜሪካ ደያስ አዱኛ

አጋራ
አጋራ

ዲያስ አዱኛ ግብ ጠባቂው ነው፤ ግብ
እንዳይቆጠርበት ከመጠበቅ አልፎ ግብ
አስቆጥሮስ ያውቃል፦ለሰሜ መጠሪያ የምትሆን
አንዲት ግብ አለችኝ፤ ሩዋንዳ ላይ የተካሄደው
የሴካፋ ሻምፒዮና ላይ በአሰልጣኝ ሰውነት
ቢሻው የሚመራው ቡድን አባል ሆኜ የሶማሌ
ብሄራዊ ቡድን ላይ የጨዋታ ዘመኔ ብቸኛ
የሆነች አንዲት ግብ በፔናሊቲ አስቆጥሬያለሁ፡፡
-በአንድ ወቅት የዚህ አምድ እንግዳ
የነበረው ሰለሞን (ልምጭ) “ከሌሎች ግብ
ጠባቂዎች ይልቅ ደያስ ላይ ጎል ማስቆጠር
ይቀለኛል” ብሏል፤ አንተስ በጨዋታ ዘመንህ
ግብ እያስቆጠረ ሲያስቸግርህ የነበረ ተጨዋች
ማነው፦(በጣም እየሳቀ) አሁን ምንም መካድ
አያሰፈልግም፤ ሰለሞን (ልምጭ) ከሩቅ እንደ
ሮኬት የሚተኩሳቸውን ኳሶች ያዝኳቸው ስል
መረብ ላይ ተወትፈው ነው የማገኛቸው፤
ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባላውቅም ሰለሞን
(ልምጭ) መግባት የሌለባቸውን ኳሶች ሁሉ
ነበር የሚያስቆጥርብኝ፤ አንዴ መብራት
ኃይል እያለሁ ከጊዮርጊስ ጋር ስንጫወት 2ለ1
እየመራናቸው ይመታል ብዬ ባላሰብኩት ሰአት
ከርቀት መትቶ ባለቀ ሰአት አግብቶብኝ አቻ
የተለያየንበትን ጎል አልረሳውም፤ ምክንያቱን
መግለፅ ቢቸግረኝም ሰለምን (ልምጭ) በጣም
ይፈታተነኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
-ከአዕምሮህ የማትጠፋ ከመናደድ ይልቅ
በድንቅ ችሎታው ተጠቅሞ ግብ ያስቆጠረብህ
ተጨዋችስ፦ነፍሱን ይማረውና የኢትዮጵያ
ቡናው አሰግድ ተስፋዬ፤ መብራት እያለሁ
አሰግድ ተስፋዬ ለማግባት የሚከብድ ኳስ
የግቡን ብረት አስታኮ ያስቆጠረብኝን ኳስ
ሁሌም ያስገርመኛል፡፡ እውነቱን ልንገርህ
ግቡ በመቆጠሩ ከመናደድ ይልቅ አሰግድን
እንድታደንቀው የሚያደርገው ነው፡፡
የጨዋታ ዘመኔ ምርጡ ቀኔ ነው
የምትለው፦የምስራቅ አፍሪካ (የሴካፋን)
ዋንጫ ያነሳንበትን ቀን፤ በአገር ደረጃ ትልቅ
ዋንጫም ስለሆነ፣ ባለሃብቶች ዳጎስ ያለሽልማት
መንግስት ደግሞ እውቅናና ሽልማት የሰጠበትን
ያን ቀን ሁሌም የጨዋታ ዘመኔ ምርጡ ቀን
ብዬ ነው የማነሳው፡፡
በጨዋታ ዘመንህ ልብህ የተሰበረበትና
በጣም ያዘንክበት ቀንስ፦መብራት ኃይል
እያለሁ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አዳማ ላይ
ስንጫወት ሰለሞን (ልምጭ) ከርቀት መትቶ
ግብ ያስቆጠረብኝና ደጋፊው የግቧን መቆጠር
ተከትሎ ያለ ሃጥያቴ ያለ ስሜ ስም በመስጠት
ክፉኛ የተቃወሙበት ቀን በጣም ያዘንኩበትና
ልቤ የተሰበረበት ቀን ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ
በእግር ኳስ ህይወቴ የማልረሳውና በጣም
ያዘንኩበት ቀን ደግሞ ቅድስ ጊዮርጊስ ከወንጂ
ጋር ወንጂ ላይ ስንጫወት ያየሁት ዘግናኛ ነገር
ዛሬም ድረስ በመጥፎ አጋጣሚነት የማነሳው
ነው፡፡ በእግር ኳስ ምክንያት የሰው ህይወት
የጠፋበት፣ ደም የፈሰሰበት፣ ብዙም ደስ
የማይሉ አሳዛኝ ክስተቶች የታየበት አጋጣሚ
ስለነበር ጊዜው ረጅም ቢሆንም ዛሬም ድረስ
በመጥፎነቱ የማነሳው ነው፡፡
-የትውልድ ቦታና የእግር ኳስ
አጀማመሩ፦ተወልጄ ያደግኩት ጅማ ውስጥ
ኩሎበር አካባቢ ነው፤ ከልጅነቴ ጀምሮ ግብ
ጠባቂ መሆን እየተመኘሁ ነው ያደግኩት፡፡
ለዚህ ምኞቴ ደግሞ ትልቁ ምክንያት የሆነው
ሰፈራችን ውሰጥ ጥላሁን ዘለቀ የሚባል ግብ
ጠባቂ ነበር በጣም ጎበዝና ምርጥ በረኛ ነበር፤
እሱን እያየሁና እያደነቅኩ ማደጌ በበረኝነቱ
እንድገፋበት ምክንያት ሆኖኛል፡፡
-ወላጅ አባቱ ጥሩ መካኒክ እንጂ እግር ኳስ
ተጨዋች እንዲሆን ስለአለመፈለጋቸው፦አምላክ
ነፍሱን በነገት ያኑርልኝና ወላጅ አባቴ አቶ
አዱኛ ጉርሙ በጅማ የታወቀ ሜካኒክ ነበር፡
፡ የራሱ ትልቅ ጋራዥም ነበረው፤ ከስር ከስሩ
እያልኩ የእሱን ሙያ እንድወርስ እንጂ ኳስ
ተጨዋች እንድሆን አይፈልግም ነበር፡፡ እሱ
ጥሩ ተጨዋች ሳይሆን ጥሩ መካኒክ ሆኜ
እንዳድግለት ነበር ምኞቱ፡፡ የእኔ ልብ ግን
የአባቴን ትዕዛዝ ጥሶ ወደ እግር ኳሱ ሸፈተ፡፡
-የእግር ኳስ የመጀመሪይ ክለቡ፦መጀመሪያ
ማሊያውን ለብሼ የተጫወትኩት ክለብ ጅማ
ውስጥ ውሃ ልማት ለሚባል ክለብ ነው፤
ነፍሱን ይማረውና አሁን በህይወት የሌለው
አሰልጣኝ መታሰቢያ በዚህ ቡድን ውሰጥ
አካተተኝ ፤በጣም የሚገርምህ አሰልጣኙ ወደ
ቡድኑ ሲያመጣኝ አንተን የምይዝህ ለዚህ
ቡድን በቻ አይደለም ትልቅ ደረጃ የምትደርስ
ግብ ጠባቂ ስለምትሆን ነው ይለኝ ነበር፡፡
በወቅቱ የተነበየው ትንቢት አገርን እስከመወከል
አድርሶኛል፤ ከጅማ ውሃ ልማት ወደ ጅማ
ምርጥ ከዚያ ወደ ዝዋይ በመሸጋገር ለዝዋዩ
ኢትኮ እያልኩ ወደ መብራት ኃይል መጣሁ፡፡
-የፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያው ክለቡ
ሰለሆነው መብራት ሃይል፦ወደ መብራት ኃይል
የመጣሁት ትልቅ ግብ ጠባቂ ትሆናለህ ብሎ
በተነበየልኝ አሁን በህይወት በሌለው አሰልጣኝ
መታሰቢያ አበበ አማካይነት ነው፤ አሰልጣኝ
መታሰቢያ የደብረዘይት ሰው ነው፡፡ በወቅቱ
የመብራት ኃይል አሰልጣኝ የነበሩት ማስተር
ቴክኒሺያን ሐጎስ ደስታም የደብረዘይት ሰው
ነበሩ፡፡ አሰልጣኙ ለእሳቸው ነገራቸው እስቲ
ይምጣና ልየው አሉት፡፡ መብራት ለሙከራ
ሄድኩኝ፤ ጋሽ ሐጎስም “ተስፋ ያለህ ልጅ
ነህ ታድጋለህ” ብለው በቡድኑ ውሰጥ
አካተቱኝ፡፡ ነገር ግን መብራት ኃይል በመያዜ
ብደሰትም በቡድኑ ውሰጥ በለጠ ወዳጆንና
ፀጋ ዘአብ አስገዶምን የመሳሰሉ የክለቡ ብቻ
ሳይሆን የአገሪቱ ምርጥ በረኞች ስለነበሩ
እነሱን አስቀምጦ መሰለፍ ከባድ ስለሆነብኝ
ለምን ክለቡን ለቅቄ አልወጣም የሚል ሃሳብ
መጣብኝ፤ በዚህ ምክንያት መብራት በገባሁበት
አመት ተመልሼ ወጣሁ፡፡
ከመብራት ወደ ሙገር ስለገባበት
ሁኔታ፦እንዳልኩህ መብራት ውስጥ በለጠንና
ፀጋ ዘአብን የመሰሉ የአገሪቱ ምርጥ ግብ
ጠባቂዎች አሉ፤ እነዚህን በረኞች አስቀምጦ
መሰለፍ እንኳን በእውን በህልምም የማይታሰብ
ነው። በክለቡ ውስጥ ዝም ብዬ ተይዤ
መብላትና ደሞዝ ማግኘት እችል ነበር፡፡ ከዚህ
ይልቅ በውስጤ ትልቅ የመሰለፍና የመጫወት
ጉጉቱ ስለነበረኝ ለመልቀቅ ተነሳሳሁ፤በዚህ
ሁኔታ ውስጥ እያለሁ አንድ ቀን የሙገር
አሰልጣኝ የሆነው ተስፋዬ ገብሩ ሜክሲኮ
ወደሚገኘው ካምፓችን ይመጣል፡፡ ሳየው ለምን
አላናግረውም? አልኩና ደፍሬ ወደ ተስፋዬ
ጋር ሄድኩኝ፡፡ ኮች አንተ ጋር መጥቼ በአንተ
ሰልጥኜ መጫወት እፈልጋለሁኝ ውሰደኝ
አልኩት፤ ተስፋዬም የነበረውን ነገር ያውቅ
ነበርና አላመነታም በዚህ ሁኔታ ወደ ሙገር
ሄድኩኝ፡፡
-በድጋሚ ከሙገር ወደ መብራት ኃይልና
የሙገር ቆይታውን በተመለከተ፦አጋጣሚው
በጣም ይገርማል፤የሚገርምህ ሙገር ሶስት
አመት ያህል ተጫውቻለሁ፤ እነዚህ ሶስት
አመታት ይበልጥ እንድበስል እንደታይም
አድርገውኛል፤ ደያስ ማነው…? ምን አይነት
ግብ ጠባቂ… ነው…? የሚለውን በድንብ
አሳይቼበታለሁ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ የመብራቶች
ቀልብ ወደ እኔ ላይ እንዲያርፍና ወደ ክለቡ
በድጋሚ እንድመለስ እንዲጠይቁኝ አድርጓቸው
ተመለስኩ፡፡ የሙገር ቆይታዬ እንደ እድል
ሆኖም ተስፋዬ ገብሩንና ኢንስትራክተር ካሳሁን
ተካን በመሰሉ ታላላቅ አሰልጣኞች የመሰልጠን
እድልንም አስገኝቶልኛል፤ በውጤት ደረጃም
ሙገር በአንድ ወቅት በጣም ቶፕ የሆነ ጠንካራ
ቡድን ነበር፡፡ የአገሪቱን ኃየላን ክለቦች በልጦ
የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን በመውሰድም
ውጤታማ እስከመሆን ደረጃ ደርሶ ነበር፡፡
-ብዙ ታላላቅ ተጨዋቾችን ያፈሪው
ማልያውን ለብሶ የተጫወተለት ሙገር
ፈርሶ ታሪክ ሆኖ ሰለመቅረቱ፦የሙገርን
መፍረስ የሰማሁት አሜሪካን አገር ሆኜ ነው፤
እውነት ነው የምልህ ሙገር ማሊያውን
ለብሼ የተጫወተኩበት ክለብ በመሆኑ ፈረሰ
የሚለውን ዜና ስሰማ ቤተሰቤን በሞት
የተነጠቅኩ ያህል በጣም ነው የደነገጥኩት፤
በጣምም ነው ያዘንኩት፡፡ ምክንያቱም ሙገር
ለውጤት ወይም ለዋንጫ ብቻ ሳይሆን ለአገር
በርካታ ተጨዋቾችን የማፍራት ለየት ያለ
ሃሳብ ወይም ራዕይ ይዞ የሚንቀሳቀስ ክለብ
ነበር፡፡ እነ ሳላህዲን ሰይድን እነ አንዱ አለም
(አቤጋን) የመሳሰሉ ለአገር ትልቅ ስራን የሰሩ
ተጨዋቾችን ያፈራ ክለብ ሩቅ አስቦ በአጭሩ
ሲቀር ከምር ያሳዝናል፤ በየክለቡ በታዳጊና
በዋና ብሄራዊ ቡድን የሙገር ማልያን ለብሶ
ያለፈ ተጨዋች ፈልገህ አታጣም፤ በዚህ
ደረጃ ለአገር ትልቅ ጠቀሜታን የሚሰጥ ክለብ
እንደዋዛ ፈርሶ ማየት ለማመን የሚከብድ ነው፡
፡ ማሊያውን ለብሶ እንደተጫወተ ብቻ ሳይሆን
እንደ አገር ከልብ አሳዝኖኛል፡፡
-በጨዋታ ዘመኑ እነማን በተከለካይነት
ከፊቱ ሲሰለፉ ጨዋታ ይቀለዋል እነማንስ
ይረዱታል፦በተለይ መብራት ኃይል
በነበርኩበት ጊዜ እነ አፈወርቅ ኪሮስ፣ ዮናስ
ገ/ሚካኤል፣ዳንኤል የሻው ከፊቴ ሲሰለፉ
ጨዋታው በጣም ቀሎኝ እጫወታለሁ፤
በጣምም እንናበባለን። ጊዮርጊስና ብሄራዊ
ቡድን እያለሁ ደግሞ በተለይ ደጉ ደበበ
ነገሮችን በጣም ያቀልልኝ ነበር፡፡
-አብሬው ባለመጫወቴ የምትለው ተጨዋች
ወይም በዚህ ስብስብ ውሰጥ ባለመካተቴ
ብለህ የምትቆጭበት፦ሩዋንዳ ላይ ዋንጫ
ይዞ የመጣው በሄራዊ ቡድን ውስጥ ተይዤ
መጨረሻ ላይ ተቀንሼያለሁ፤ ያ ቡድን ግን ወደ
ሩዋንዳ ሄዶ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር
ውጪ ዋንጫ አመጣ፤ ዋንጫ በማግኘታቸዉ
ከህዝቡ የተደረገላቸውን አቀባበል ሳይ በጣም
ተቆጨሁ፡፡ ምነው ባልቀነስና በዚህ ስብስብ
ውስጥና የዚህ ትልቅ ታሪክ አካል በሆንኩ ብዬ
በጣም ተቆጨሁ፤ ግን የሚያስደሰተው በ1997
ዓ.ም ፀፀቴን የሚያስረሳ የሴካፋን ዋንጫ
በማግኘቴ ተክሻለሁ፡፡
-የተለየ አድናቆት የሚሰጠው የአገር
ውስጥ ምርጥ አሰልጣኝ፦እንደ አጋጣሚ ሆኖ
ብዙውን ጊዜ የሰለጠንኩት በውጭ አገር
አሰልጣኞች ነው፤ መብራት ኃይል እያለሁ
ለጋሽ ሐጎስ ደሰታ፤ ከዚህ ውጪ ግን በእኔ
የእግር ኳስ ህይወት የገዘፈ ታሪክ አላቸው
ብዬ በተለይ የምጠራቸው አሰልጣኝ ሰውነት
ቢሻውና አስራት ሃይሌ ናቸው፤ ለእነሱ የተለየ
ክብር አለኝ፡፡
-ከአገር ውሰጥ በጣም የምታደንቀው
ምርጥ ተጨዋች፦ለእኔ ወደር የሌለው
የምንጊዜም ምርጡ ተጨዋች ሙሉአለም ረጋሳ
ነው፤ ሙሌ ጎበዝ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ድረስ
ያልተተካ ተጨዋች ነው፡፡
በጨዋታ ዘመኑ የተከፈለው ከፍተኛው
ደሞዝ፦መብራት ሃይል እያለሁ 1800 ብር
ለመጀመሪያ ጊዜ የቆጠርኩት ትልቁ ደመወዜ
ነው፡፡
-የፊርማ ገንዘብስ አግኝቶ ያውቃል፦30ሺህ
ብር ለፊርማ ተብሎ ተከፍሎኛል፤ ከመብራት
ኃይል ወደ ቅድሰ ጊዮርጊስ ስዘዋወር የተሰጠኝ
ትልቁ የፊርማ ገንዘብ ነው፤ ከዚህ ውጪ
በጨዋታ ዘመኔ ያገኘሁት ትልቁ ገንዘብ ሼህ
አላሙዲን የሴካፋን ዋንጫ በማንሳታችን
ለእያንዳንዳችን የሰጡት 50ሺህ ብርና
መንግስትም በውጤቱ አኩርታችሁናል ብሎ
ኮንዶሚኒየም ቅድሚያ ሰጥቶን የገዛነው ትልቁ
የእግር ኳስ ስጦታዬ ነው፤ ዛሬ ከአሜሪካን
ስመጣ አረፍ የምልባት ገርጂ ኮንዶሚኒየም
ቤቴ መንግስት በሽልማት የሰጠኝ ናት፡፡
-እግር ኳስ ተጨዋች መሆንህ የገንዘብ
ወይስ የሰው ሀብታም አድርጎሃል፦ሁለቱንም
አልነፈገኝም፤ እግር ኳስ ተጨዋች ሆኜ
በማሳለፌ የገንዘብም የሰውም ሀብታም
አድርጎኛል፡፡ አሁን ለምገኝበት እውቅናና
የታሪክ ባለቤት ያደረገኝ ያመንኩት እግር
ኳስ ነው፤ በጨዋታ ዘመኔ ገንዘብ ላይ
ጎበዝና ጠንቃቃ መሆኔ፣ ራሴን የምጠብቅ፣
በዲሲፕሊን የምመራ ተጨዋች በመሆኔ
ሁለቱንም እንዳላጣ አድርጎኛል በዚህም እግር
ኳስን አመሰግነዋለሁ እንጂ አልወቅሰውም፡፡
-ጎመንና ፈላሻው እየተባለ ስለሚጠራበት
ቅፅል ስሙ፦(በጣም እየሳቀ) ብዙውን ጊዜ
ቅፅል ስም የሚያወጣልኝ ደጉ ደበበ ነው፡፡ ደጉ
ምክንያቱን ዛሬም ድረስ ባላውቅም “ፈላሻው”
እያለ ይጠራኝ ነበር፡፡ በስሙ ከመጠራት
ውጪ ትርጉሙን ዛሬም ድረስ አልነገረኝም፤
ትርጉሙን እሱ ነው የሚያውቀው፡፡ “ጎመን”
የሚለውን ደግሞ ሰውነት ቢሸው ነው
ያወጣው፤ ሰውነት ጎል ሲገባብህ “ጎመን” ይላል
ተጨዋቾቹም ያንን ይዘው “ጎመን” አሉኝ በቃ
ይሄው ነው፡፡
ከአገር ውጪ ድጋፉን የሚሰጠው፦ለቀያይ
ሰይጣኖቹ ማንቸስተር ዩናይትድ፤
-ከባህር ማዶ አድናቆት የሚሰጠው
አሰልጣኝ፦አሁን በእንግሊዝ ማን.ሲቲ፣ ቀደም
ሲል በስፔኑ ባርሴሎና የነገሰው ፔፕ ጋርድዮላ

-ከውጪ ድጋፉን ያለስስት የሚሰጠውና
የሚወደው ብሄራዊ ቡድን፦በውጤት ባይክሰኝም
የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን፤
-ባገኘውና ለአንድ ደቂቃም ቢሆን
ባወራው ብሎ የሚመኘው ተጨዋች? ምንስ
ይጠይቀዋል፦
የአርሰናሉ ፓትሪክ ቪዬራን፣በጨዋታ
ዘመኑ እንደሱ አይነት ለውጤት እልህ ያለውና
ትልቅ አቅም ያለው ተጨዋች ባለማየቴ የእሱ
አድናቂ ነኝ፤ እኔ የምኖረው ሳንፍራንሲስኮ
ውስጥ ነው እሱም እዛ ኒውዮርክ ሲቲን
ያሰለጥናልና አንድ ቀን ባገኘው ለሰኮንዶች ብቻ
ባወራውና ምስጢሩን ብሰማ በጣም ደስ ይለኝ
ነበር፡፡
-ደያስ ተጨዋች ባይሆን ኖሮስ፦የተዋጣለት
ምርጥ መካኒክ ነዋ…! እድሜ ለአባቴ ትልቅ
ሙያን አውርሶኝ ነው ያለፈው፤ በልጅነቴ ከእሱ
የተማርኩት ትምህርት አትላንቲክንም አቋርጬ
እንጀራ እበላበታለሁ፤ የመኪናን ብልት ፈትቶ
የሚገጣጥም ምርጥ መካኒክ ነበር የምሆነው፤
ግን አሁንም ከጨዋታ ዘመኔ በኋላም ሆኛለሁ
በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡
-የቅዱስ ጊዮርጊስ ሹፌር መጠነኛ
ህመም ገጥሞት ተጨዋችም ሹፌርም ሆኖ
ስላገለገለበት አጋጣሚ፦
ይሄ ነገር የት መሰለህ የሆነው? ቅድስ
ጊዮርጊስ እያለሁ ለጨዋታ ወደ አርባምንጭ
ሄደን ስንመለስ በጣም የምናከብረውና
የምንወድደው ሹፌራችን በየነ መጠነኛ የምግብ
መመረዝ ህመም ያጋጥመውና መኪናውን
መንዳት ይቅተዋል፡፡ አጋጣሚው ሁሉም
ያልጠበቀው ስለነበር ምን ልንሆን ነው? ብለው
ብዙዎች ይደነግጣሉ፤ በዚህን ጊዜ ብድግ ብዬ
የሹፌሩ መቀመጫ ላይ ስቀመጥ ብዙዎች
ደነገጡ፤ መኪናውን እስከማስነሳው ማንም
አላመነም ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ አንቀባርሬ
አዲስ አበባ አደረስኳቸው፡፡ እኔ ከአባቴ ጋር
ጋራዥ ስላደግኩ ከልጅነቴ ጀምሮ ከባድ መኪና
አሸከረክር ስለነበር ብዙም አልተቸገርኩም፡፡
የሚገርምህ ከእኔ ውጪም አንተነህ ፈለቀም
መኪናውን ሊያሽከረክር ነበር፡፡ አያያዜን ሲያይ
ነው የተወው እንጂ እሱም አቅሙ ነበረው፡፡
-ከእግር ኳስ ጋር የተለያየው የጨዋታ
ዘመኑ ተጠናቆ ነው፦አይደለም…! ብዙ
ቀሪ የጨዋታ ዘመኖች እያሉኝ ነው ኳስን
ያቆምኩት፤ አሜሪካን አገር በአመታዊ ውድድር
ላይ ስጫወት የሚያዩኝ አሁንም ለምን ለክለብ
አትጫወትም? እያሉ ይጠይቁኛል፤ ይሄ በራሱ
ያለ ጊዜዬ ማቆሜን የሚጠቁመኝ ነው፤ አሁን
ውሰጤም አቅሜም መጫወት ትችላለህ ነው
የሚሉት፤ ነገር ግን የእንጀራ ጉዳይ ሩጫ ሆኖ
ከኳሱ ጋር ብዙ አልዘለቅኩም፡፡
-ሶሰት ዋንጫ በአንድ አመት ስላገኘበት
መብራት ሃይል ቆይታውና ስለስብስቡ፦ከሙገር
የሶሰት አመት ቆይታ በኋላ ወደ መብራት
ስመለስ ሁለት ቦታ በመፈረማችን እኔና ደበበ
የሚባል ተጨዋች ትንሽ ተቸግረን ነበር፤
ለሙገርም ለመብራትም በመፈረሜ በዚህ
የተነሳ ውዝግቦች ተፈጥረዋል፡፡ ነገር ግን
በወቅቱ የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ የነበረው አቶ
ይስሐቅ ታፈረ በጣም መጨነቃችንን አይቶ
“አንዴ ተሳስታችኋል፤ ግን መርጠህ ተጫወት”
አለኝ እኔም በተሰጠኝ የምርጫ እድል መሰረት
መብራት ኃይልን መርጬ ከሶሰት አመት በኋላ
ወደ ክለቡ ተመለስኩ፡፡ ያ ወቅት ግን ለመብራት
የሽግግር ወቅት የሚባል ነበር ምክንያቱም
የቡድኑ ነባርና ወሳኝ ተጨዋቾች የነበሩት
እነ ኤልያስ ጁሃር፣ በለጠ ወዳጆን የመሳሰሉት
ተጨዋቾች ተቀንሰው ቡድኑን በወጣቶች
የመገንባት እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ከዚህ መነሻነት
አጀማመራችንና ውጤታችን ጥሩ አልነበረም፡
፡ በኋላ ላይ እየተሻሻልን ሄደን ሁለተኛ ሆነን
አጠናቀናል፡፡ 1994 ዓ.ም ግን ለመብራትም
ለእኔም ልዩ አመት ነበር፤ ሶስት ዋንጫዎችን
በአንድ የውደድር ዘመን አግኝተን ታሪክ
ያፃፍንበት ነው፡፡ ያ ውጤታማ ጊዜ በእግር
ኳስ ዘመኔ በስኬት የማነሳው ነው፡፡ የፕሪምየር
ሊጉን፣ የፀባይና የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን
በመሰብሰብ ታሪክ አፅፈናል፤ ቡድኑ ለዚህ
ስኬት የበቃው ምርጥ ስብስብ ስለነበረው ነው
ዮርዳኖስና ስምኦን አባይ፣ አንዋር ሺራጅ
(ትንሹ)፣ ዮናስ ገ/ሚካኤል፣ ዳንኤል የሻውን
የመሳሰሉ እግር ኳሱ ሊረሷቸው የማይችሉ
ተጨዋቾች እንዲሁም ጋሽ ሐጎስ ደስታን
የመሰሉ ምርጥ አሰልጣኝን ያሰባሰበ ቡድን
ነበር፡፡
-ከመብራት ኃይል ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ
አገባቡ፦የመጨረሻ ጨዋታዬን በ1975 ዓ.ም
ለመብራት ኃይል ተጫውቼ እንደጨረስኩ ነው
ጊዮርጊሶች ያነጋገሩኝ፤ በወቅቱ የክለቡ የቡድን
መሪ የነበረው ኤፍሬም ግዛቸው ነበር “ለምን
ወደ ጊዮርጊስ አትመጣም” ብሎ ያነጋገረኝ፤
ጊዮርጊስ ትልቅ ታሪክና ውጤት ያለው ቡድን
በመሆኑ ጥያቄው ሲቀርብልኝ ሁለቴ ማሰብ
አልፈለኩም ወዲያውኑ ተስማምቼ ነው
የገባሁት፡፡
-ቅዱስ ጊዮርጒስ የገባሁ መብራት ሃይል
እያለ ጎል ለቆ ነው በሚል ስለመወቀሱና
ስለመታማቱ፦በእግር ኳስ ህይወቴ በጣም
ካዘንኩባቸው ነገሮች አንዱ እንደዚህ አይነት
መሰረተ ቢስ ወሬ በመወራቱ ነው፤ ሰዎች
አጋጣሚውን ለእንደዚህ አይነት ስም ማጥፊያ
በመጠቀማቸው ከልቤ እንዳዝን አድርጎኛል፡፡
ጊዮርጊሶች እኔን ወደ ክለባቸው የሚወስዱኝ
በችሎታዬ እንጂ ጎል ሰለለቀቅኩላቸው
አይደለም እንደዚህ አይነት ድርድርም ሲደረግ
አይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡ ነገሩ ምን
መሰለህ መብራት ኃይል እያለሁ ከጊዮርጊስ
ጋር ስንጫወት ከርቀት በመምታትና በቅጣት
ምት የተለየ ችሎታ ያለው ሰለሞን (ልምጭ)
ጎሉን ለቅቄ መውጣቴን አይቶ ከርቀት የመታት
ኳስ ትገባለች፡፡ ይሄ ጨዋታ ደግም በጣም
የሚጠበቅ ነው፤ እኛም በጨዋታው ብናሸንፍም
ብንሸነፍም በውጤታችን ላይ የሚያመጣው
ለውጥ የለም፡፡ ከእኛ ይልቅ ይሄ ጨዋታ
ለኢትዮጵያ ቡና በካፍ የክለቦች ሻምፒዮና
ለመሳተፍ ወሳኝነት ነበረው፡፡ የእኛ ማሸነፍ
ቡናዎች እድሉን እንዲያገኙ ይረዳቸው ነበር፡
፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ሰለሞን (ልምጭ)
ከርቀት መትቶ ግብ አሰቆጠረብኝ፤ በዚያው
ተሸንፈን። በጨዋታው ወቅትም ጨዋታው
ካለቀ በኋላ ደጋፊዎች ሆን ብዬ እንደለቀቅኩ
አድርገው በጣም ተቃወሙኝ፤ በአመቱ ደግሞ
ጊዮርጊስ ስገባ ያንን ጎል ለቅቄ እንደገበሁ ተደርጎ ተወራ፡፡እኔ እኮ ከዚያ በፊትም በ1994
እና በ1995 ዓ.ም ለመግባት ጫፍ ደርሼ ነበር፤
ነገሮች ግን ለምን በዚህ መልኩ እንደተተረጎመ
አልገባኝም፤ እኔ እንደዚህ አይነት ስብዕና ያለኝ
ተጨዋች ባለመሆኔ ደጋፊው ያለ ኃጥያቴ
ባሳየው ተቃውሞ በጣም ማዘን ብቻ አይደለም
በጣም ነው የተበሳጨሁት፤ ይሄን አጋጣሚ
ሁሌም በመጥፎነቱ ነው የማነሳው፡፡ ጊዮርጊስ
ለመግባት ችሎታ እንጂ ጎል መልቀቅ አስፈላጊ
አለመሆኑን ካለመረዳት የመጣ ተቃውሞ
ይመስለኛል፡፡ አሁን ነገሩ አልፏል ይሄው እኔም
አለሁ፡፡
-ደያስ 6 አመት በብርቱካናማው ማሊያና
የቡድን ስብስቡን በተመለከተ፦ቅዱስ ጊዮርጊስ
በጣም ትልቅ ታሪክና ውጤት ያለው ክለብ ነው፤
ክለቡን ከተቀላቀልኩ በኋላም ያረጋገጥኩት
ይሄንኑ ነው፡፡ ከካምፑ ጥበቃ እስከሰራተኞች፣
ደጋፊው፣ የቦርድ አመራሮች፣ተጨዋቾች፣አሰልጣኞች ድረስ ከሻምፒዮንነት ውጪ የቀደመ
አጀንዳ የላቸውም፤ በቃ ይሄ የክለቡ መገለጫ
ባህሪይ ነው፤ እኔ ወደ ጊዮርጊስ የገባሁት 1995
ዓ.ም መጨረሻ ለ1996 ዓ.ም የውድድር ዘመን
ነው፤ ወደ ክለቡ ስገባ የተቀበለኝ አሰልጣኝ
ሚስተር ሃንስ ነበር፡፡ አሰልጣኙ ውጤታማ
አልነበረም፤ የክለቡ ግብ ጠባቂ ደግሞ ታዲዮስ
ስለነበር በገባሁበት አመት የተሰፍኩበት ጨዋታ
በጣም ትንሽ ነበር፡፡ በ1997 ዓ.ም ለዝግጅት
ከቡድኑ ጋር ሄደን ተዘጋጅተን መጣን በመሃል
ግን አሰልጣኝ ሃንስ ተባሮ ዳኛቸው ቡድኑን
በጊዜያዊነት ተረከበ፡፡ ጥሩ ባንሆንም የተሻልን
ሆነን የአመቱን ውድድር አጠናቀቅን፡፡ በቀጣይ
አሰልጣኝ ሚቾ መጣ፡፡ ሚቾ ሲመጣ እድሉን
ሰጠኝ 1997 ዓ.ም በቂሚነት የመጫወት
እድልን አገኘሁ፤ የፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮናም
ሆንን፤ ለብሄራዊ ቡድንም የመመረጥ እድሉን
አገኘሁ፡፡ ጊዮርጊስ በነበረኝ ቆይታና ወደ ክለቡ
ለመምጣት የወሰንኩት ውሳኔ ትክክል መሆኑን
ያረጋገጥኩት ሻምፒዮን በመሆኔና ለብሄራዊ
ቡድን የመመረጥ እድልን በማግኘቴ ነው፡፡
ስብስቡ ራሱን የቻለ ብሄራዊ ቡድን ብትለው
ነው የሚሻለው፤ አገሪቱ ውስጥ ያሉ ምርጥ
ምርጥ ተጨዋቾችን የያዘ ክለብ በመሆኑ
ለመሰለፍ ያለው ፉክክርም ቀላል አይደለም፡፡
ይሄ ደግሞ ጠንክረህ እንድትሰራ ይደርግሃል፤
የፕሮፌሽናል አስተሳሰብ በውስጥህ እንዲፈጠር
ያደርጋል፡፡ ከአሜሪካ ከመጣሁ በኋላም ቡድኑ
ልምምድ ሲያደርግ አይቻለሁ፤ አሁንም ክለቡ
የፕሮፌሽናልነት መሰረቱን እንዳልቀቀ ነው
ያረጋገጥኩት፤ ይበልጥ ተጠናክሮ መሄዱን
ነው የታዘብኩት። በአጭሩ በጊዮርጊስ ጥሩ
የሚባል የስኬት ጊዜ ነው የነበረኝ፡፡
-ወደ አሜሪካ ስለመጓዙ፦በድንገትና
በአጋጣሚ ነው ወደ አሜሪካ
የተጓዝኩት፤ስለአሜሪካ ትልቅነትና ስልጣኔ
እሠማለሁ እንጂ ወደዚያ ስለመሄድ አሰቤ
አላውቅም ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው
እወዳለሁ የቅዱስ ጊዮርጊስና የብሄራዊ ቡድን
ግብ ጠባቂ የነበረው ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ ነው
ዛሬ ኑሮዬን በአሜሪካ የሚያደርገውን የግብዣ
ወረቀት ያመጣልኝ፤ በመጣልኝ የግብዣ እድል
መሰረት ሄድኩኝ፤ የተሻለ ህይወት ለመኖር
ስል በመጨረሻ እዛ ለመስራትም ወሰንኩ
ማለት ነው፡፡
-ህይወት በአሜሪካ የነበረውን የህይወት
ውጣ ውረድ፦እውነት ለመናገር አሜሪካ
ከውጪ እንደምታምረው ሁሉም ነገሯ ቀላል
አይደለም፤ ዛሬ የደረስኩበት ደረጃ ለመድረስ
ብዙ ፈተናዎችንና ውጣ ውረዶችን ማሳለፍ
ግድ ነበር፡፡ በፈተናዎች ውስጥ ሳታልፍ አልጋ
በአልጋ የሚሆን ነገር የለም፤ ለፈተናዎች
የማትሸነፍ በጣም ጠንካራ ሰውም መሆን
አለብህ፡፡ አይመጥነኝም ብለህ የምትንቀው
ስራ መኖር የለበትም፤ ብዙዎች በዚህ ነገር
ሲቸገሩ ይሰማል እኔ ግን ከልጅነቴ ጀምሮ
ዝቅ ብዬ ማደጌ ነገሮችን አቅልሎልኛል፤ በዚህ
መንገድ ማደጌ በጣም ጠቅሞኛል፡፡ የቤተሰብ
ታክሲ እነዳ፣ጋራዥ ውስጥ በሞተር ዘይት
የተጨማለቀ ቱታ ለብሼ ግሪስ በግሪስ ሆኜ
እሰራ ስለነበር ያ አጋጣማ ስለ ስራ ክቡርነት
እንዳውቅ በጣም ረድቶኛል፤ ነገሮችንም
በአሜሪካ አቅልሎልኛል፡፡ ከፊትህ የተጋረጡ
ፈተናዎችን በዚህ መልኩ ማለፍ ከቻልክና
ጠንክረህ ከሰራህ ህይወት በአሜሪካ ጣፋጭ
ነው፡፡ ለሚሰራ በዲሲፕሊን ለሚኖር ሰው
አሜሪካ ምቹ ናት አሜሪካ ራስዋ የምትወደው
ጠንክሮ የሚሰራ ነው፤ ከሰራህ ትኖራለህ፡፡
-አሜሪካን የሚኖር ሰው ምን ትሰራለህ
ተብሎ ባይጠየቅም ስለምትሰራው ስራ፦ምንም
የምደብቀው ነገር የለም ጋራዥ ውስጥ
እሰራለሁ፤ ሜካኒክም ነኝ፡፡ አባቴ ያወረሰኝ
ሙያ በጣም ጠቅሞኛል አትላንቲክን
አቋርጬም እንጀራ እየበላሁበት ነው፤ በጋራዥ
ውስጥ በሜካኒክነት ሙያ እሰራለሁ የአበሾችና
የጥቁሮች መኪኖችን በሙያዬ እሰራለሁ፡፡ ከዚህ
ውጪ ዘመናዊ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጥ
ኡቨርም እሰራለሁ፤ ከዚህ በተጨማሪም መኪና
እየገዛሁ እሸጣለሁ፤ የተሻለ ህይወት እንዲኖረኝ
በተለያየ መንገድ ጠንክሬ እየሠራለሁ ነው፡፡
-በአሜሪካ ፕሮፌሽናል ተጨዋች ለመሆን
ስላደረገው ጥረት፦ፕሮፌሽናል ተጨዋች
የመሆን ትልቅ ህልም ነበረኝ ይህንን ለማሳካት
ደግም የአርጀንቲናው የአለም የወጣቶች
ሻምፒዮና ነበር፤የአለመብሰል ነገር ስለነበር
አልተጠቀምንበትም እንጂ እድለኞች ነበሩ፡
፡ ካለመብሰል ሌላ ግንዛቤውም እውቀቱ በዚህ
ዙሪያ አለመኖሩ ፌዴሬሽኑም በዚህ በኩል
ያመቻቸልን የከፈተልን መንገድ አለመኖሩ እኔን
አይደለም ብዙዎች ፕሮፌሽናል መሆን ሲችሉ
በዚህ ክፍተት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ወደ አሜሪካ
ከሄድኩ በኋላም የፕሮፌሽናልነት ህልሜን
ለማሳካት ጥረት ማድረጌን አላቋረጥኩም፤
በዚህ በኩል ኢንጂኒዬር በኃይሉና አቶ
ያረጋል የሚባሉ የቀድሞው የቅድስ ጊዮርጊስ
ተጨዋችና የስፖርት ሰዎች የተለያዩ ጥረቶችን
አድርገውልኛል፤ ሳንሆዜ ለሚባል ክለብ
ለመጫወትም ጥሩ ተስፋ ነበረኝ፡፡ በሰአቱ
ወረቀት ካለመኖሩ ጋር ተዳምሮ አልተሳካም፡
፡ በዚህ መሃል ጋሽ ያረጋልን በጣም ነው
የማመሰግነው ተስፋ አልቆረጠም፤ LA BLUE
TOOTH የሚባል ክለብ ጋር ለሙከራ ላከኝ፡፡
ከLA GALAXY ጋር ሁሉ የወዳጅነት ጨዋታ
አድርጌያለሁ፡፡ እነሱ ቤት ተከራይተውልኝ
እዛው እንድቆይ ነበር የፈለጉት በአሜሪካ ወደ
ኳስ ሙሉ በሙሉ ስትገባ የሚረዳህ ሰው የግድ
ያስፈልጋል፡፡ እኔን ይሄንን ሁሉ የማደርገው
የወሰዱኝ ሰዎች የቤት ኪራይ እየከፈሉልኝ
ነው፤ ሁሌም ደግሞ ሰውን እያስቸገርክ መኖር
ከባድ ስለሆነ ሰውን ማስቸገር ከበደኝና መጨረሻ
ላይ ስራ መሰራት አለብኝ የሚል ውሳኔ ወስኜ
ወደ ኦክላንድ ሳንፍራንስሲስኮ ተመለስኩኝ፡፡
በስራም በመጠመዴ የፕሮፌሽናልነት ህልሜ
መንገድ ላይ ቆመ፡፡
-ስፖርተኛ ሰለሆነችው ባለቤቱና የትዳር
ህይወቱ፦ባለቤቴ ፀገነት ተሰማ በቅፅል ስሟ
ማርታ ትባላለች፤በጣም ብዙና ረጅም የፍቅር
ታሪክ ነው ያለን፡፡ ጅማ ላይ የተጠነሰሰው
ለጋው ፍቅራችን ፍሬ አፍርቶ አሜሪካን
ድረስ ተከትሎን መጥቶ ሄቨን ዲያስ አዱኛ
የምትባል የዘጠኝ አመት ልጅ አፍርተን
ሳንፍራንሲስኮ ውስጥ በደስታና በፍቅር
እየኖርን ነው፤እንዳልከው ባለቤቴ እንደ
እኔው የስፖርት ሰው ናት፤ የጠረጴዛ ቴኒስ
ተጨዋች ፡ ለባንኮችና ለሙገር እንዲሁም
አገርን በመወከል አልጀርስ ድረስ ሄዳ
ተጫውታለች፤ሁለታችንም በተለያዩ የስፖርት
ዘርፍም ቢሆን አገርን እስከመወከል የበቃን
የስፖርት ቤተሰቦች ነን፡፡ በጣም የሚገርምህ
ከእሷ ጋር 18 አመታትን በፍቅርና በትዳር
አሳልፈናል፤ አሁን በአሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ
በተለያየ የሰራ ሙያ ላይ ተሰማርተን ከልጃችን
ጋር በአንድ ላይ እየኖርን ነው ፤ፍቅራችን
የራሱ የሆነ ብዙ ታሪክ ያለው ነው፡፡ አሁን
በእስራኤል አገር የሚኖረው መልካሙ ነው
የመገናኘታችን ምክንያት የሆነው፡፡
-በእግር ኳስ ህይወቱ ትልቅ ታሪክ
ስለፃፈበት የአርጀንቲናው የአለም ወጣቶች
ዋንጫ፦የአርጀንቲናው የአለም ወጣቶች ዋንጫ
በእግር ኳስ ታሪካችን ከፍ ያለውን ቦታ
ይወስዳል፤ ፍፁም የማይነዘጋ ሁሌም እንደ
አዲስ የሚታወስ ምርጥ የሆነውን ትዝታውን
ጥሎልን ያለፈ ውድድር ነው፡፡ አርጀንቲና
በእግር ኳሱ ብቻ ሳይሆን በህዝቧ፣ ሴቶቹ
ለእኛ ተጨዋቾች ባላቸው ፍቅር የተለየ
ትዝታ ነው ያለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ባለፈው
አንተ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ለጌታሁን መንግስቱ
ያዳረግክለትን ቃለ-ምልልስ ትሪቡን ስፖርት
የሬድዮ ፕሮግራም ላይ እነ ኤፍሬም የማነና
ፍቅር ይልቃል ያቀረቡትን ትረካ ሰምቼ በጣም
ነው ያዘንኩት፤ ጌታሁን በዚህ ደረጃ ላይ
መገኘቱ ያሳዝናል፡፡ አርጀንቲና ላይ አብረን
ስለነበረን በሰማሁት ነገር በጣም አዝኛለሁ፡፡
ከዚያ ውጪ ጌታሁን የ14 አመት አርጀንቲናዊ
ልጅ አለኝ ብሎ ለአንተ መግለፁ አስገርሞኛል፣
አስቆኛልም፤ እኔ ይሄንን እንደሰማሁ ለባለቤቴ
ጌታሁን የ14 አመት ልጅ አርጀንቲና ላይ አለኝ
ብሏል፤ ቀጥሎ ደግሞ የእኔን ልጅ ጠብቂ ብዬ
ቀልጄባታለሁ፤አስቄያታለሁም። አርጀንቲና
በሁላችንም ልብ ውስጥ ልዩ ትዝታ አላት፡፡
-ስለአሰልጣኝ ጋርዚያቶ፦ሁሌም በየዘመኑ
እንደ አበባ የሚፈነዱ ብቅ የሚሉ ተጨዋቾች
አሉ፤ አሰልጣኝ ጋርዚያቶም በአንድ ወቅት
ፈንድተው የወጡ ተጨዋቾችን ተጠቅሞ ትልቅ
ስምና ታሪክ አፅፏል፤ ስሙ ጊዜው አልፎም
እንዲነሳ አድርጎታል፡፡ ጌቱ ተሾመ፣ዮርዳኖስ
አባይ፣ አሸናፊ ግርማ፣ዮናስ ገ/ሚካኤል፣
ዘውዱ በቀለ፣በቀል እልሁ እኔን ጨምሮ ያኛው
ትውልድ ካለፈ በኋላ እንደ አዲስ ብቅ ያልን
የእግር ኳስ ትውልድ ነበር፡፡ ጋርዚያቶ ይሄንን
ትውልድ ሳያባክን መጠቀሙ ረድቶታል፤
ከዚህ ውጪ ያለውን ችሎታ ከአለምና
ከተጨዋቾቻችን ጋር በማጣመር አዲስ
የስልጠና አብዮት በመፍጠር ንቅናቄ የፈጠረ
ምርጥ አሰልጣኝ ነው ለእኔ፡፡
-ደያስ አዱኛ ራሱን በሶስት የተመረጡ
ቃላቶች ምረጥ ቢባል እንዴት ይመርጣል፦
ራሴን በራሴ በሶስት ቃላት መግለፅ
ይከብደኛል፤ አንድ ስለ ራሴ የማውቀው ግን
ቅን ሰው መሆኔን ብቻ ነው፤ ከዚህ ውጪ
ደግ ነኝ፣አዛኝ ነኝ ብዬ ለራሴ ከምመሰክር ሰው
ቢመሰክር ይሻለኛል፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣዜና እረፍትዜናዎች

የጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አጭር የህይወት ታሪክ

ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ከእናቱ ከወ/ሮ ጌጤ ገ/ስላሴ እና ከአባቱ ሀምሳ አለቃ ወልዴ...

ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣ

ሀትሪክ አሁንም ቀጠሮ ማክበር ስልጣኔ ነው በሚለው አቋሟ ጸንታለች

ቅዳሜ ጠዋት በቀጠሮ  ቀናችን  እርስዎ ጋዜጣዋን በእጅዎ ያስገቡ እንጂ አዳዲስና ያልተሰሙ መረጃዎችን...

ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣዜናዎች

ሀትሪክ አሁንም ቀጠሮ ማክበር ስልጣኔ ነው በሚለው አቋሟ ጸንታለች

ቅዳሜ ጠዋት በቀጠሮ  ቀናችን  እርስዎ ጋዜጣዋን በእጅዎ ያስገቡ እንጂ አዳዲስና ያልተሰሙ መረጃዎችን...