“ከሁሉም ጨዋታ ቀላሉ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የምናደርገው ነው” ዳዋ ሁቴሳ/ አዳማ ከተማ/

     ከሁሉም ጨዋታ ቀላሉ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የምናደርገው ነው

… የአዳማ ማሊያ እኛ እየተጫወትንበት ያለው የአዳማ ማሊያ ሳይቀየር ዘንድሮ 5ኛ አመቱን ነው የያዘው

 

ከዮሴፍ ከፈለኝ

ጉጂ ክልል ጉጂልጣ ከተማ ቀርሳ ወረዳ በቡና ምርቷ ትታወቃለች፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ ስሟን የሚያስጠራ ምልክት አግኝታለች ዳዋ ሁቴሳን… የአዳማ ከተማው ኮከብ “ጊዜው ለክለቤ ጥሩ አይደለም ነገር ግን ከ1-3 ያለውን ደረጃ ይዘን ለማጠናቀቅ እንፋለማለን ታሪካችን ሊበላሽ አይገባምም” ሲል ይናገራል፡፡ ዳዋ ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ስለ አስተዳደጉ፣ ልምምድ ስለማቆማቸው፣ ክለቡ ስላለበት የፋይናንስ ችግር፣ኢትዮጲያ ቡናን ስላሸነፉበት መንገድ፣ ቅ/ጊዮርጊስ ለመግባት ስላለው ተስፋ፣ ስለብሔራዊ ቡድን፣ ስለሚያደንቀውና ተምሣሌቴ ናቸው ስለሚላቸው እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ሰፋ ያለ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

   ሀትሪክ፡- አዳማ ልምምድ በድጋሚ አቆማችሁ ምንድነው ምክንያቱ?

ዳዋ፡- ምንም ከፍያ አልተሰጠንም ወደ 16 ተጨዋቾች እንጠጋለን፡፡ ያለፈው አመት የግንቦትና የሰኔ ወር ደመወዝ መች ተከፈለን..? እንከፍላችኋለን ግቡ ችግር የለም ብለውን ዝግጅት የጀመርነው ሳይከፈለን ነበር አሁን ድረስ ዝም ብለዋል የጊዜ ገደብ እየሰጡን ደጋግመው ሳይከፍሉ ስንጫወት ዝምታቸው በዛና ዛሬን ጀምሮ አቁመናል /ቃለ ምልልሱ የተሰራው ሐሙስ እለት ነው/ ባለፈው ባህርዳር ስንሄድ ስትመለሱ ረቡዕ ወይም ሐሙስ እናስገባላቸዋለን ብለው ዝም ብለውናል፡፡ ውል ያለን ወደ 19 እንጠጋለን አዲሶቹ 4 ቢሆኑ ነው ብዙው የክለቡ ተጨዋች ውል ያለው ነው የ12 ጨዋታ ኢንሴንቲቭ እንኳን  አልተከፈለንም እንዲሁ በችግር ውስጥ ነን፡፡

ሀትሪክ፡-ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን እንዲያውቅ ደብዳቤ አልፃፋችሁም?

ዳዋ፡- ደብዳቤማ ለፌዴሬሽኑም አስገብተናል ምንም ምላሽ አልተሰጠንም ለቡድኑ ደብዳቤ ላኩና ክፈሉ ቢባሉም ቢጠሩም አመራሮቹ አልተገኙም ፌዴሬሽኑም ዝም አለ የት እንደምንሄድ ሳይቀር ግራ ገብቶናል፡፡ 

ሀትሪክ፡-ከባህርዳር መልስ ምን አሏችሁ?

ዳዋ፡- ማን መጥቶ አናገረን ዝምታን መርጠዋል መፍትሔ ብለን ያሰብነው ልምድ ማቆም ነበረና አቁመናል፡፡ 

ሀትሪክ፡-የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ አቋም ምን ይመስላል?

ዳዋ፡- አሰልጣኙማ እንዲከፈለን ነው የሚፈልገው…. ሲከፈለንኮ ነው ለቡድኑ ውጤት የምንታገለው  ተጨዋቹ ሜዳ ውስጥ ገብቶ እንዲታገልለትኮ ደመወዝ ሊከፈለን ይገባል፡፡ ፋይናንስ የለንም ችግር አለብን ብለው ነው የሚያወሩት…ይሄ ደግሞ ቡድኑን እየጎዳ ነው መጥቶ ያናገረን የለም በጣም ተከፍተናል፡፡ /ቃለ ምልልሱን ከሰራን በኋላ ክለቡ የአንድ ወር ደመወዝ ለቆላቸው በነጋታው አርብ ዕለት ልምምድ ሰርተዋል/

ሀትሪክ፡-አንተ ከቀርጫ ወረዳ እንዴት ተገኘህ.. መነሻህ ምንድነው?

ዳዋ፡- ኳሱ በወረዳዋ ብዙም አላደገም እንጂ እንደ ጉጂ ዞን ምርጥ ከተማ ናት፡፡ በሰዓቱ ተማሪ ነበርኩ በት/ቤታችን ወረዳውን እየወከልን ነገሬ ቦረና ላይ እንጫወት ነበር፡፡ ነገሌ ደግሞ ኦሮሚያ ሊግ ይጫወት ነበርና ለት/ቤት ስጫወት አይተው ነገሌ ቦረናዎች ለኛ ተጫወት ብለው ከነርሱ ጋር ጀመርኩ ትንሽ ወራት ነው የተጫወትኩት… ድሬዳዋ ላይ የክልል ሻምፒዮና ስንሄድ ክልሉን ወክዬ ስጫወት አዩኝና ድሬዳዋ ለሚገኘው ናሽናል ሲሚንት ፈረምኩ… የኳስ ተጨዋችነቴ ጉዞ እንዲህ ሲል ጀምሮ አዳማና ጊዮርጊስን አካቶ አሁን ያለሁበት ደረጃ ደርሷል… ይህን ይመስላል፡፡ 

ሀትሪክ፡- ስለ ት/ቤት አወራኸኝ.. ተማሪ ሳለህ በጣም የሚከብድህ ትምህርት ምንድነው?

ዳዋ፡- ምንም ከባድ ትምህርት አልገጠ መኝም፡፡ ጎበዝ ተብለው ከሚጠሩ ተማሪዎች ተርታ ውስጥ ነበርኩ እስከ 10ኛ ባለው ክፍል አንደኛ ወይም ሁለተኛ ነበር ስወጣ የነበርኩት….. ሁሉንም ትምህርት እወዳለሁ የሚከብደኝም ትምህርት አልነበረም….. በጣም ከባድ የሚባሉትን ሂሣብ ፊዚክስ ኬሚስትሪ… በደንብ እሰራቸው ነበር.. ከባድ ትምህርት አልገጠመኝም እያልኩህ ነው፡፡ 

ሀትሪክ፡- ኳስ ተጨዋች ባትሆን ምን እሆን ነበር ብለህ ትገምታለህ?

ዳዋ፡- ኳስ ተጨዋች ባልሆን ምናልባት በትምህርቴ ቀጥዬ ጥሩ ደረጃ ላይ እገኝ ነበር.. በትምህርት ጎበዝ ስለነበርኩ  አባቴ በደንብ ያበረታታኝ ነበር ኳስ እንድጫወት አይፈልግም ትምህርቴን እንድቀጥል ብቻ ነው የሚያግዘኝ፡፡ 

ሀትሪክ፡- ኳስ ተጨዋች መሆንህን ሲያውቁ አባትህ ምን አሉ?

ዳዋ፡- ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን ተመረጬ በቲቪ ቃለ ምልልስ ሲደረግልኝ ነው ያዩት….. አባቴ በጣም ተደሰተ እንዳልጫወት ኳሱን እንዳልቀድደ አሁን  ግን ደስ አለው ዳዋ ሁቴሳ ሲባል ልጄ ስሜን አስጠራህ ብሎ አመሰገነኝ ከዚያ በኋላ ግቢ ውስጥ ማንም ይጫወት ፍቃድ ተገኘ፡፡ ልጆቹን መርዳት ጀመርኩ አባቴ ኳስ የሚጫወቱ ሲጠፉ ተጫወቱ እንጂ እያለ  ኳስ መግዢያ ገንዘብ መስጠት ሁሉ ጀመረ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በኳስ ዙሪያ ነፃነት ታወጀ እልሃለሁ፡፡ 

ሀትሪክ፡-አዳማ 4ኛ አመትህን ይዘሃልና… ስለከተማዋ የምትለው ነገር አለ?

ዳዋ፡- ዋው ምርጥ የምወዳትና የተመቸኝ ከተማ ናት… ለኑሮም ለደህንነትም የምትመች ከተማ ከመሆኗም በተጨማሪ ለአዲስ አበባና ለቅርብ ከተሞች ቅርብና አዋሳኝ በመሆኗ ተወዳጅ አድርጓታል፡፡ ነዋሪውም የተሻለ መሆን የሚፈልግ ነው ካለው ነዋሪ ጋር ተዋደህ ተግባብተህ ተስማምተህ መኖር ተችላለህ፡፡ አዳማን አትጠግባትም የምትወድድም ከተማ ናት፡፡ 

ሀትሪክ፡- ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ስትጫወቱ ከማሸነፍ ውጪ በሰፊ ግብ እንረታለን ብላችሁ ገምታችኋል?

ዳዋ፡- የኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ ደጋጋሜ አይቼዋለው አዳማ መጥቶ የሚጫወት ቡድን አየሩ እንደ ሚከብደው ይታወቃልና ቡናን ደግሞ ተጭነን ከተጫወትን እንደምናሸንፈው ርግጠኛ ነበርን፡፡ ከሁሉም ጨዋታ ቀላሉ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የምናደርገው ነው….. ከጨዋታው በፊት እያወራንበት የነበረ ጉዳይ ነው የእነሱ አጨዋወት ከበረኛ የሚጀመር መሆኑ ይታወቃል እንደኔ እምነት እንዲህ ተጫውቶ ማሸነፍ ትንሽ ይከብደናል ተጭነን ከተጫወትን ብዙ ማግባት እንደምንችል ተነጋግረን ገብተን ተሳክቶልናል…..ቀላል ጨዋታ ብለን የገባነው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደረግነውን ግጥሚያ ነው፡፡ 

ሀትሪክ፡- የአዳማ ከተማ የሊግ ጉዞ ስኬታማ ነው ማለት ይቻላል?

ዳዋ፡- አይደለም በዘንድሮ የውድድር አመት ደስ የሚል ነገር የለውም መገኘት የነበረብን ደረጃና አሁን ያለንበት አይገናኝም በዚህ ቅር ብሎኛል በዚያ ላይ የገንዘብ ችግር አለብን….. አመራር ላይ ያሉት ሰዎች ጥሩ ነገር ለቡድኑ የላቸውም እንደ ክለባችን ስብስብ ያለንበት ደረጃ አይገባንም ነበር፡፡  

ሀትሪክ፡- ከደመወዝ ጋር በተያያዘ ሲኒየሮቹን የማሰናበት እቅድ መያዙን ሰማን… ተነግሯችኋል?

ዳዋ፡- ወሬው ሰምተናል ግን መጥቶ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረን ኃላፊ የለም አሉባልታ እየሰማን ነው ብዙ ገንዘብ የሚከፈላቸውን እንለቃለን መባሉን ብንሰማም ለኛ የነገረን ሰው የለም፡፡ 

ሀትሪክ፡- በደመወዝ ጥያቄ ቡድኑ ሃሣቡ ተከፍሏል ልምምድ አልሰሩም እየተባለ ኢትዮጵያ ቡናን መርታችሁ ኳሱ ቀላል መሆኑን አያሳይም?

ዳዋ፡- በጣም ቀላል መሆኑን አይቼበ ታለሁ… ስናከብደው እንጂ ኳሱ አይከብድም.. እግር ኳስ በጭንቅላት የምታደረገው ጨዋታ ነው ማድረግና እችላለው ብሎ አምዕሮህ ካመነ ኳስ ቀላል ነው ሰራህም አልሰራህም ማለቴ ነው…. የኛ ሀገር ኳስ በጣም የወረደ መሆኑን በዚህ ነው የምትረዳው፡፡ ተገቢ ልምምድ ሳትሰራም ማሸነፍ የምትችልበት ሀገር ነው.. ስራህ ሳይሆን በስራ ሳታሰበውም ማሸነፍ እንደምንችል አይተንበታል ይሄ ደግሞ እንዳልከው ኳሱ ገና መሆኑ ያሳያል፡፡ 

ሀትሪክ፡- የአዳማ ከተማ አመራሮች ቡድኑን በደንብ እየተንከባከቡ ነው ማለት ይችላል?

ዳዋ፡- አይመስለኝም እንደዚህ ብዬም አልዋሸም በአዳማ ደረጃ ስታስብ ብዙ ችግሮች አሉብን እኛ እየተጫወትንበት ያለው የአዳማ ማሊያ ዘንድሮ 5ኛ አመቱን ነው የያዘው … እንዴትስ እንደ ክለብ 5 አመት ሙሉ በአንድ ማሊያ ይጫወታል.. ምንድነው ይሄ..? ከዚያም ውጪ ካምፕ ያለው የምግብ አመጋገባችን አዳማን የሚመጥን አይደለም ከዚህ በፊት የነበረው ስምና አሁን ላይ ያለው ነገር አይገናኝም፡፡ 

ሀትሪክ፡- ምክንያቱም ወይም ችግሩ ታውቋል?

ዳዋ፡- አልታወቀም ከዚህ በፊት የነበሩ የከተማዋ ከንቲባዎች ኳስ የሚወዱ ይመስሉኛል አሁን ቦታው ላይ ያለው ሰው ስለ ኳሱ ግዴለሽ ይመስለኛል የሚገባኝና የማስበው እንዲህ ነው…. አለበለዚያ ኳስ ትልቅ አቅምና ቦታ እንዳለው አልተረዳ ይሆናል አዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ከተባለ አዳማን በደንብ የምታስተዋውቅበት ክለብ ነው  የአሁኑ አዳማ ከንቲባ በደንብ የተረዳው አልመሰለኝም፡፡

ሀትሪክ፡- በማህበራዊ ኑሮ ኳስ ተጨዋች ጥሩ አይደለም ይባላል… አንዴ መስኡድ መሃመድ ለተጨዋች ነጥብ ቢሰጥ 2/10 የምናገኘው ብሏል.. አንተስ?

ዳዋ፡- በማህበራዊ ኑሮ አሪፍ ነኝ ብዬ ነው የማስበው፤ ከማንም ሰው ጋር ሠላም መፍጠር በሠላም መኖር የምችል ተግባቢ ሰው ነኝ ሰውን ማስከፋት አልሻም.. ከዚያ ውጪ ሀዘንና ደስታ ላይ በተቻለኝ መጠን እገኛለሁ፡፡ ጥሩ ግንኙነት አለኝ ብዬ አስባለው፡፡ 

ሀትሪክ፡-አብረህ ከተጫወት ኳቸው ላንተ ምርጡ ማነው? አብሬው ብጫወት የምትለውስ?

ዳዋ፡- አብረውኝ ከተጫወትኳ ቸው መሀል ከነ አዳነ ግርማና ሳላህዲን ሰይድ ጋር መጫወቴ አስደስቶኛል… ሃገራችን ላይ አሉ ከተባሉት ጋር በመሆኑ ሁሌ ስደሰት እኖራለሁ….. አብሬው ብጫወት ደግም ደስ የሚለኝ ከዳዊት እስጢፋኖስ ጋር ነው ጎበዝ ተጨዋች ነው ስታዲየም ገብቼ ሲጫወት አይቼ ተደስቻለው ለአጥቂ የሚመች ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ውጤታማ በመሆኑ ከርሱ ጋር ብጫወት ደስ ይለኛል ልጫወት ብችልም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ 

ሀትሪክ፡- እስከ 13ኛው ሳምንት ድረስ ካየሃቸው ክለቦች ምርጡ ላንተ ማነው?

ዳዋ፡- የተለመዱ ክለቦች ናቸው.. እነ መቐለ 70 እንደርታ ፋሲል ከነማ ልክ እንደአምናው ጥሩ ላይ ናቸው…. ያም ቢሆን ከማውቀው በተለየ መልኩ ጥሩ ብቃት ላይ ነው የምለው ክለብ የለም፡፡ 

ሀትሪክ፡- የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስንኮ ዘለልከው?

ዳዋ፡- አዲስ አበባ ላይ የመጨረሻው 15ኛው ሳምንት ጨዋታ የምናደርገው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እንደመሆኑ ከባድ ጨዋታ ይመስለኛል፤ ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድን ነው እኛም አሁን ያለንበት አቋም ጥሩ ባይሆንም ጠንካራ መሆናችንን እናውቃለን፡፡ 3 አመት ሙሉ ጥሩ ተፎካካሪ ነበር ጊዮርጊሶችን ባለፉት 3 አመታት ከብደናቸው በሊጉ አሸንፈውን የሚያውቁ አይመስለኝም አንዴ የረቱን በሲቲ ካፑ ብቻ ነው የአዳማ ማሊያ ባደረኩባቸው አራት አመታ ሙሉ ጊዮርጊስ አሸንፎን አያውቅም ጥሩ ታሪክ ሰርተናል በመጨረሻ ሳምንት ጨዋታችን ለጊዮርጊስ ግጥሚያው ይከብደዋል ብዬ አስባለው፡፡ 

ሀትሪክ፡- በሊጉ የ2012 የውድድር አመት ከሜዳ ውጪ ማሸነፍ ከባድ ሆኗል… ይሄ ለየት አያደርገውም?

ዳዋ፡- አዎ! በጣመ ስንገረምም ነበር ሁሉም ክለብ በሜዳው ኃይለኛ ሆኖ ተዘጋጅቶ የሚጠብቅበት አመት ሆኗል ለዚህ ነው ከባድ 

የሆነው፡፡ ከሜዳ ውጪ 3 ወይም 4 ጨዋታ ማሸነፍ የቻለ በሜዳው ስለማይሸነፍ የዋንጫ እድል አለው ላለመውረድ የሚጫወተውም በሜዳው ላይ ከባድ ሆኗል፡፡ ሀድያ ሆሳዕና ከታች ሆኖ ከሜዳውም ውጪ ይሁን በሜዳው ጠንካራ ተፋላሚ እየሆነ መምጣቱ የሊጉን ውድድር አክብዶታል፡፡ ከሜዳ ውጪና ሜዳ ላይ የሚለው የአስተሳሰብ ውጤት ነው ህሊናህ በሜዳዬ መሸነፍ የለብኝም ስለሚል እንጂ በኛ ሀገር እግር ኳስ በሜዳ ላይ ይሁን ከሜዳ ውጪ የሚባል ነገር የለም፡፡ አቋምና አስተሳሰብህ ከተቀየረ ከሜዳ ውጪም ማሸነፍኮ ይቻላል፡፡ 

ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን እንዴት ትገልፃቸዋለህ?

ዳዋ፡- ቃላት ያጥረኛል ለመግለፅ……በኔ የተጫዋችነት እድገት ላይ ትልቅ ድርሻ የአሰልጣኝ አሸናፊ ነው፡፡ ከአሰልጣኙ በፊት ትልቅ ድጋፍ ያደረገልኝ የብሔራዊ ቡድናችን ዋና አሰልጣኝ የነበረው ማርያኖ ባሬቶ ነበር፡፡ ከርሱ በኋላ የኔ የተጫዋችነት ብቃት ላይ ተፅዕኖ ያሳረፈው አሰልጣኝ አሸናፊ ነው ትልቅ ለውጥ እንዳመጣ አድርጎኛል በፊት የሌለኝ በርሱ ስር ስሰለጥን ያገኘሁት ብዙ ነገር አለ….. ግዴለሽ ነበርኩ ይሄ ባህሪ የተቀየረው በአሸናፊ ነው ጊዮርጊስ እያለው ግብ ብስትም ሆነ ኳስ ባበላሸ አልገረምም ነበር አሁን ግን ተለውጫለሁ በራስ መተማመን ትኩረት ሰጥቼ ለመጫወቴ የአሰልጣኝ አሸናፊ ድጋፍ የተለየ ነበር በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኝ አሸናፊን ላመሰግን እወዳለው፡፡ 

ሀትሪክ፡- ዳዋ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የመጫወት አቅም አለኝ ብሎ ያምናል? ፍላጎቱስ አለው?

ዳዋ፡- ሲጀመር ከጊዮርጊስ የለቀኩት በቦታዬ የነበሩት ተጨዋቾች በብቃት የሚጫወቱበት ወቅት በመሆኑና ለፕሪሚየር ሊጉ አዲስ መሆኔ ነው እንዳልታይና እንድለቅ ያደረገኝ፡፡ ዛሬ ላይ የተሻለ ልምድ አለኝ ብዬ አስባለው፡፡ ለመጫወት የሚያስችል ልምዱም አለኝ፡፡ ያኔ ስለቅ ዋና አላማዬ የነበረው  ወጥቼ ብቃቴን በማሳየት ተመልሶ ለጊዮርጊስ መጫወት ስለሆነ በርግጠኝነት ቅዱስ ጊዮርጊስን እመለሳለሁ ብዬ አስባለው፡፡ 

ሀትሪክ፡- ከሃገር ውስጥ ያንተ ተምሣሌት ማነው?

ዳዋ፡- ከሃገር ውስጥ እንደ ተምሣሌት የማየው አዳነ ግርማን ነው ከውጪ ደግሞ ክርስቲያኖ ሮናልዶ…… 

ሀትሪክ፡- ዳዋ ከከነአን ማርክነህ ጋር ያለው ጥምረት ምርጥ ነው ሊባል ይችላል?

ዳዋ፡- አዎ ከሜዳ ውስጥም ይሁን ከሜዳ ውጪ ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ በማህበራዊ ጉዳይ ጓደኛዬም ነው ሜዳ ላይም ያለን ጥምረት ጥሩ የሚባል ነው፡፡ የምለውን ሰምቶ የሚለኝን አዳምጬው ተቀባብለን ነው የምኖረው፡፡ በኔ በኩል ቲሙን ጠቅመን እርስ በርስም እየተጠቃቀምን እንገኛለን ብዬ አስባለው፡፡ 

ሀትሪክ፡- ቡና ላይ ያስቆጠርከው ግብ የ2012 የሊግ ውድድር 200ኛ ግብ ተብሎ ተመዘገበ.. ምን ተሰማህ?

ዳዋ፡- በጣም ነው የተደሰትኩት ጓደኛዬ ነው ቴሌግራም ላይ የላከልኝ ሳየው አላመንኩም በጣም ነው ደስ ያለኝ ይሄ ምርጥ ታሪክ ነው አድርጌዋለው ብዬ የምናገረው እውነት በመሆኑ ደስ ብሎኛል…. ዳዋ ሄነሪ መረብ ወጣሪ መባሌ ከልብ ያስደስተኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት አልጓጓህም….? ለምንስ ከቡድኑ ራቅክ?

ዳዋ፡- በርግጥም  በጉዳት ምክንያት ለትንሽ ጊዜ ከዋሊያዎቹ ስብስብ ርቄያለው አሁን ላይ እግዚአብሔር ይመስገን ጥሩ አቅም አለኝ ብዬ አስባለው ለሀገሬ ብሔራዊ ቡድን ትልቅ ነገር መስራት እፈልጋለው ለሀገሬም ለመጫወት ጓጉቻለሁ፡፡ 

ሀትሪክ፡- ከስፖርታዊ ጨዋነት አንፃር አንዳንድ ፀቦች ብቅ እያሉ ነውና … ምን ትመክራለህ?

ዳዋ፡- እግር ኳስ ከፖለቲካና ከዘረኝነት መጠበቅ አለበት ብዬ አስባለው፡፡ ብዙ ነገርን መለወጥ የሚችል ስፖርት ነው ትዝ ካለህ እነ ድሮግባ ሀገር ላይ ችግር ሲነሳ አንጫወትም በማለት ሁኔታውን የቀየሩበት ሂደት የሚረሳ አይደለም፡፡ ሀገርን ከችግር ሲያወጣ እንጂ የረብሻ ምክንያት መሆን የለበትም ሁሉም ወደ ሜዳ ሲመጣ እግር ኳስን ብቻ አስቦ ቢመጣና ከአላስፈላጊ ስሜታዊነት ራሱን ቢጠብቅ ደስ ይለኛል፡፡ 

ሀትሪክ፡- ከኳስ ውጪ መዝናኛህ  ምንድነው?

ዳዋ፡- በጣም የምወደውና የምዝናናው በፑልና በፕሌይ ስቴሽን ብቻ ነው…..

ሀትሪክ፡- የሀገራችንን የፖለቲካ ሂደት ትከታተላለህ?

ዳዋ፡- አዎ! አንዳንዴ ፈልጌ ሌላ ጊዜ ሳልፈልግ የምሰማው ነገር አለ፡፡ ከሰዎች ይመጣል በሚዲያም ሲነገር እሰማለሁ፡፡ 

ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ምን ትመኛለህ?

ዳዋ፡- ፍቅርና ሠላም በዝቶ እንደሌሎች ታላላቅ ሀገሮች አድጋ ለማለት በእድገቷ ላይ ብቻ ብናተኩር ሀገር ከማውደም ብንከለክል ደስ ይለኛል በተቻለ መጠን ለሀገር ሠላም ወደ ፈጣሪ መፀለይ ቢበዛ ደስ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ከውጪ የማን ደጋፊ ነህ?

ዳዋ፡- የማን.ዩናይትድና የሪያል ማድሪድ ቀንደኛ ደጋፊ ነኝ ከጣሊያን የጁቬንቱስ ሆኛለው…. በተለይ የሮናልዶ መግባት የአሮጊቷ ደጋፊ አድርጎኛል፡፡ 

ሀትሪክ፡- እስቲ ስለ ትዳርህ አስተ ዋውቀን?

ዳዋ፡- ባለ ትዳርና የ1 ልጅ አባት ነኝ፡፡ ባለቤቴ ወ/ሮ ውባለም አበራ ትባላለች፡፡ አሪፍ ሚስት ናት፡፡ የሀገሬ ልጅ ስትሆን ሙሉ ድጋፍ ታደርግልኛለች 6 አመት በጓደኝነት ቆይተን ነው ወደ ትዳር አለም የገባነው…… የምወደውን ቤተሰብ በመምራቴ ደስ ብሎ ኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የውጪ የሙከራ እድል አልገጠመህም?

ዳዋ፡- አልሞከርኩም እድሎች ግን መጥተውልኝ ሳልቀበል ቀርቻለው  ኤጀንቶች ቢመጡም ብዙም ስላለመንኩበት ሳልሄድ ትቼዋለው 

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ቃል?

ዳዋ፡- ማመስገንን የምፈል ገው ለዚህ ደረጃ ላበቃኝ ቸሩ መድሃኒያለም ነው….. ቤተሰቦቼ እናት አባቴን ጓደኞቼን አብሮ አደጎቼን፣ ቀርጫ ሲያሰለጥኑኝ የነበሩትን አሰልጣኝ ተሾመ፣ብዙ ነገር ያደረገልኝ ወንድሜ ይመር፣ ተመስገንን፣ ዘሪሁን የሚሰኙ ቤተሰቦቼን አመሰግናለሁ…… ብዙ ነገር በኔ ህይወት ላይ ያደረጉት ሁሉ ማመስገን እፈልጋለው፡፡ 

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport