“እኛ ኢትዮጵያ ቡናዊያን ግድቡ ይገደባል ብለን ተንብየናል ቡና ዋንጫ በልቷል አሁን ደግሞ አባይ ይገደባል” ዳዊት እስጢፋኖስ /ሰበታ ከተማ/

“የሀገራችን የስፖርት ሚዲያዎች ለሀገራችን እግር ኳስ ሩቅ ናቸው ቢቀርቡን ኖሮ ህመማችን ይሰማቸው ነበር”

“እኛ ኢትዮጵያ ቡናዊያን ግድቡ ይገደባል ብለን ተንብየናል ቡና ዋንጫ በልቷል አሁን ደግሞ አባይ ይገደባል”
ዳዊት እስጢፋኖስ /ሰበታ ከተማ/


በርካታ ክለቦች ለተጨዋቾቻቸው ደመወዝ ባለመክፈል ውዝግብ ውስጥ ከገቡ 3 አመት ሞልቷቸዋል፡፡ በነዚህ ዘመናት ደግሞ የተጨዋቾች ህይወት ተመሰቃቅሏል ይህም ቢሆን ታዲያ ሚዲያው የሚገባውን ያህል ትኩረት አልሰጠውም በዚህም ተከፍቻለው የሚለው የሰበታ ከተማው የመሀል ሜዳ ኮከብ ዳዊት እስጢፋኖስ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ስለ ኮሮና ቫይረስና የህዝቡ መዘናጋት፣ ስለ አባይ ግድብ፣ አባይ ግድብ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ስላለው ግንኙነት፣ የህፃናቱ መደፈር፣ ስለ ትዳሩና ቤቴ ቤቴ ስለማለቱ፣ ስለ 2 ቀናቱ ረብሻ፣ የተለየ ስለሆነው የፀጉር ቁርጡ፣ ከሰበታ ከተማ ጋር ስላለው ኮንትራት፣ ስለቀጣይ ክለቡ፣ ያለደመወዝ ስለመጫወታቸው፣ የተጫዋቾች ማህበር ስላለው ጥቅም፣ ሚዲያው ለደመወዝ ጥያቄያቸው ትኩረት ስላለመስጠቱና ሌሎች ጉዳዮች ሰፊ ምላሽ ሰጥቷል፡፡


ሀትሪክ፡- ቤት ቤት አለ…12 ሰዓት ሲል ቤት ይገኛል… የቤት እመቤት ወደ መሆኑ እየሄደ ነው አሉኝ እውነት ነው… ?

ዳዊት፡- (ሳቅ በሳቅ) አዎ እውነት ነው…. (ሣቅ)

ሀትሪክ፡- እንደውም ቤት የምትገባው 12 ሰዓት ነው ስትባል አይ 11፡45 ላይ ትላለህ አሉ.. ይሄስ?

ዳዊት፡- (ሣቅ) ቤት ቤት ማለቱ ከኮሮናውም አንፃር ግዴታ እየሆነ ነው የውዴታ ግዴታ በለው… የግድ እሰበሳባለሁ ትንሽ ወጣ ወጣ የምለው የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማህበር ስብሰባ ሲያጋጥመኝ ነው እንጂ ብዙውን ጊዜ ቤት ነኝ፡፡ ሩብ ጉዳይ ለ12 ላይ አላርም አለኝ ሮጬ ቤቴ እገባለሁ… ግን ግን ቤት ውስጥ መሆንን ለእማወራ የሰጠው ማነው… ቤቱ የአባወራምኮ ነው (ሣቅ)

ሀትሪክ፡- ሚስትህ በደንብ አየችህና ለካ ባሌ ቆንጆና ቀይ ነው አለች፤.. እውነት ነው…?

ዳዊት፡- (ሣቅ በሳቅ) ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የ4 ሰዓት ፀኃይ የትም ሀገር የለም፡፡ ያለው ነገርህን ነው ገፎ ቁጭ የሚያደርገው፡፡ ፀሐይዋ ከሌለች የተመጣጠነ ምግቦችን እያበሰልን ከባለቤቴ ጋር እየሰራን ራሳችንን እየጠገን ነው ያለነው… የሰው ልጅ ሆዱ ፊቱ ነው ይባላልና ቤት ውስጥ መዋልና ጥሩ ጥሩ ነገር መጠቀም ፊት ላይ ያወጣልና… የሷም ቀልድ እውን ሆኗል፡፡

ሀትሪክ፡- አሃ ቤት ውስጥ ባለ ክትትል እንጂ በሜካፕ አይደለም እያልክ ነዋ?

ዳዊት፡- (ሣቅ በሳቅ) ኧረ በፍፁም በሜካፕማ አይሆንም በፍፁም

ሀትሪክ፡- ባልና ሚስት በኮሮና ቫይረስ የተነሣ ቤት ውሰጥ ረዘም ላለ ጊዜ መቆየታቸው ሲጨምር የድብድቡ ቁጥሩ እየበዛ መጣ የሚሉ አሉ… ቤትህ ገጥሞሃል…?

ዳዊት፡- /ሳቅ/ ተያያዞማ ብዙ ነገሮች መጡ… መች ግጭት ብቻ ነው የሴትና ወንድ ህፃናት መደፈርንም አስከተለ እንጂ ሪፖርቱ ልክ ነው ሲጀመር ቻይና ውስጥ ነው ድብድቡ በዝቷል የተባለው… በየቀኑ ወደ ፍቺ የሚሄዱ ወደ ሺዎች እየደረሱ ነው ተባለና እቀልድ ነበር፡፡ ቤት ውስጥም ወደዚያ ነው የምንሄደው እያልኩ እቀልድ ነበርና ቤት ውስጥ ሲኮን ውሃ ቀጠነ ማለት እንደሚበዛማ ይጠበቃል (ሣቅ)

 

ሀትሪክ፡- የህፃናቱን መደፈር እንዴት ሰማኸው?

ዳዊት፡-በጣም ተሰምቶኛል አዝኛለሁ፡፡ የኔን ፀባይ አይቼ ለህፃናቱ አዘንኩ ወደ ቤቴ የምመለሰው በናፍቆት ስለሆነ ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ለብዙ አመታት እግር ኳስ ተጨዋች ቤት ውስጥ ይህን ያህል ጊዜ ተቀምጦ አያውቅም ይሄ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ያም ሆኖ በጣም ተከፍቻለሁ በጣም ያስደነግጣል ሰው መሆናችንን የዘነጋው ይመስላል በዘር መቧጨቁ እንዳለ ሆኖ ይሄ ችግር ሲፈጠር የሰው ልኬት ምንድነው? ያስብላል፡፡ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠርን ሆነን አባት ልጁን የእንጀራ ልጁን ወንድ ልጁን መድፈሩን ስንሰማ ፈጣሪስ እንዴት ይታረቀን? እንዴትስ ዝም ይበለን? የመጣብን ነገርም ልክ ነው ያስብላልኮ….በጣም ያስፈራል… ልጄ 3 አመቱ ነው ከ15 አመት በኋላ የሚገጠመው ምን ይሆን ብዬ ሳስብ ያስደነግጣል፡ አስበው ኳስ ተጨዋች ነኝ ባለቤቴ ሆስተስ ናት በስራ ገጠመኝ ባንኖር ምን ይሆን ብዬ ሰጋሁኮ በፊት ወጥቶ መግባት ነገር የሚያስፈራው አሁን ደግሞ ቤት ውስጥ ሆነ ከቤትህ የት ትሸሻለህ…? በገዛ አባትህ በእንጀራ አባትህ መደፈር ያስደነግጣል እግዚአብሔር ምህረቱን ያምጣልን ድሮ መደፈር የሚያሰጋው ከቤት ውጪ ነበር አሁንማ ቤት ውስጥ ሆነኮ ከቤትህ የት ትሸሻለህ፡፡ መሸሸጊያው ላይ ከመጣ አስጊ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ባልነትህና አባትነት ባንተ ላይ ያመጣው የባህሪ ለውጥ አለ?

ዳዊት፡- በጣም ይለውጣል… በባልነቴ ብዙ ሳልቆይ ነው ወደ አባትነት የተቀየርኩት…. ባል ስሆንም በግል ትውውቅና የፍቅር ጊዜ እንደነበረው ነው ፍቅሩና ስሜቱ… ልጆች ሲመጡ ደግሞ አባትነቱ መጣ… አሁን ታጋሹና ብዙ ኃላፊነት ያለበት ዳዊት ሆኛለው፡፡ አልፎ ተርፎም ትውልድ መቅረፅ ስላለብኝ አስተማሪ ሆኜም እየኖርኩ ነው፡፡ ከትዳር ውጭ አግሬሲቭነቱ አለ ቁጡነቱ አለ አሁን ግን አባት ነኝ የሚለው ማዕረጉ ብዙ ነገር ይለውጣልና በዚያ ላይም ሆኖ መገኘት ይጠይቃልና መርከቡ ውስጥ ሆኖ እየነዳ ማሳየት እንዳለበት ካፒቴን ቤቴን በኃላፊነት እየመራሁ ነው ኃላፊነቱ ደግሞ የግድ የባህሪ ለውጥ ያመጣል፡፡

ሀትሪክ፡-ቆይ ቆይ ውዝግቡ በቤቴ የለም እያልክ ነው?

ዳዊት፡- /ሳቅ/ አለ እንጂ… በማልፈው መንገድ እያለፍኩ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በኳሱም በትዳሩም አብዶኛ ነኝ እያልክ ነው?

ዳዊት፡- /ሳቅ በሳቅ/ መች ይቀራል.. ባለቤቴም ታልፈኛለች እዚህኮ ያለው መተላለፍ ነው በአቻ ነው የሚያልቀው/ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ሆሊፊልድና ታይሰን ለሊት ላይ ተቧቅሰው ጠዋት ላይ አንዱ ውጤት ሲጠይቅ ጓደኛው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… አቻ ወጡ ብሎ እርፍ…?

ዳዊት፡-/ሳቅ በሳቅ/ በቦክስ አቻ… ? /ሳቅ/ በኛ ቤት ግን መተላለፍ ስላለ ውጤቱ አቻ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ዳዊት ቤት ቤት ከማለቱ የተነሣ… መዝናናት ቀንሷል የሚል ጥቆማ ደረሰኝ.. እውነት ነው?

ዳዊት፡- /ሳቅ/ ይሄኮ ከበሽታው በፊትም ያመጣሁት ባህሪ ነው ቤት ቤት ማለቴን ጓደኞቼ ለምወደውት የነበረ ባህሪዬ ነበር.. በጣም እዝናና ስለነበር ቤት ቤት ማለቴን የግድ ለምደውታል ዋናው ደስታ ያለው ቤቴ ውስጥ ነውና ሮጬ ወደ ቤቴ ማለቴ እውነት ነው በፊት የነበሩት መዝናናቶችና የማይሆን ቦታ ላይ መታየቶች አሁን በእጥፍ ቀንሷል፡፡

ሀትሪክ፡- ምስጋናው ለባለቤትህና ልጅህ ይሁና?

ዳዊት፡-ምስጋናማ ለፈጣሪ ይሁንልኝ

ሀትሪክ፡-ተው እርሱን አላልኩም ፈጣሪን ለተነፍስከውም ታመሰግነዋለህ….. ስትዝናናምኮ ፈጣሪ ነበር?

ዳዊት፡- ልክ ነህ… የመጀመሪያው ፈጣሪማ እንዳለ ይታወቃል ያው እነርሱ ሁለተኛ ስለሆኑ ነው…. ትዳሬ ትልቅ ጥቅም ሰጥቶኛል በሚለው ይያዝልኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ኮቪድ 19ኝን እንዴት አየኸው? ህብረተሰቡስ እየተጠነቀቀ ነው ማለት ይቻላል? 7 ሰው ዛሬ ሞተ ተባለ /ቃለ ምልልሱ የተሰራው ማክሰኞ ዕለት ነው)

ዳዊት፡- እጅግ በጣም ነው የሚያስፈራው.. አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የወጣ ጊዜ ሁሉም ይጠነቀቅ ነበር ብዙ ነገሮች በዝግ ነበር ሲሰሩ የነበሩት… ከትንሽ ጊዜ በኋላ ደግሞ መደበኛ ስራዎች ተጀምሯል… መጠጥ ቤቶቹ መገበያያ ስፍራዎቹም ወደ መደበኛ ተግባራቸው ሲመለሱ ህዝቡም ተመልሷል… የሚገርመው መጀመሪያ አካባቢ ወደ ውጭ አልወጣሁም ነበርና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ወደ ውጪ ስወጣ ህዝቡም ውጪ ነው ያለው ሁሉም ነገር እንደበፊቱ ነበር የቀጠለውና እንዴ የተዘጋው መቼ ነበር ብዬ ጠየኩ የተዘጋው ሰዓት ላይ አልነበርኩም መሰለኝ /ሳቅ በሳቅ/ ከወጣው በኋላ ባየሁት ፈርቻለሁ በ7 ሰው መሞት አዝኛለሁ ለሟቾቹ ቤተሰቦች ወዳጆች ጓደኞች መፅናናትን እመኛለሁ፡፡ ነገር ግን እንደተከተልነው የህይወት መንገድ በቀን 7 ሰው መሞቱ ትንሽ ነው ማለት ይቻላል በትንፋሽ ይተላለፋል በንክኪ ይተላለፋል እግር ላይ ቫይረሱ ይቆያል እየተባለ ሰው ግን በነፃነት እንደፈለገ ከኖረ በበሽታው መያዛችን አይቀርም ሰይፉም መቁረጡን ይቀጥላል… በጣም ያስፈራል የሌሎች ሀገራት መንግስታት የከፈቱትን አንዳንዶች እየዘጉ ነው የኛም መንግሥት ተመሳሳይ አስገዳጅ ሕግ ያወጣል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-የረብሻው ጊዜ በ2 ቀናት ከ100 በላይ ሰው ሲሞት ከኮሮና በላይ ረብሻው ገደለ ይሄ በሽታ ምን አጠፋ የሚሉ ሰዎች አሉ… ገዳያችን አልበዛም?

ዳዊት፡-በጣም በዛ እንጂ… የመደፈሩ አስፀያፊ ድርጊት ራሱኮ ግድያ ነው አንዳንዱን በቁም እንገድላለን በአባቱ የተደፈረ ሕፃን እንዴት ብሎ ነው ቀሪ ዘመኑን የሚኖረው? ይሄ ከግድያ የሚተናነስ አይደለም በረብሻውም ብዙ ወጣት አጣን… ይሄ ቫይረስ ዳግም አለ ገዳያችን በዛ ብቻ ሳይሆን ከምንችለው በላይ ነው የሆነው እግዚአብሔር ምህረቱን ያምጣልን ነው ማለት የምችለው፡፡

ሀትሪክ፡-አባይና ዳዊት ይተዋወቃሉ?

ዳዊት፡- አባይና እኔማ የቅርብ ሰዎች ነን ቀድሞ ነው የምንተዋወቀው ብዬ አምናለሁ… 2003 ከቡና ጋር ዋንጫ ስናነሳ “አባይ ይገደባል ቡና ዋንጫ ይበላል” የሚል ዜማ ነበረን ከዚህ ጋር በተያያዘ የቅርብ ትውውቅ አለን ማለት ይቻላል እኛ ኢትዮጵያ ቡናዊያን ግድቡ ይገደባል ብለን ተንብየናል ቡና ዋንጫ በልቷል አሁን ደግሞ አባይ ይገደባል ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ትስስሩ አለን የአባይ ቤተሰብ ነኝ የምለውም ለዚያ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ግድቡ እንዲገደብ አደረኩ የምትለው አስተዋፅኦ አለ?

ዳዊት፡- በቻልኩት መጠን ለግድቡ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ…ከዚህ በፊትም የምችለው ሁሉ ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ እንደዜጋም እንደ ስፖርት ሰውም በተለያዩ መድረኮችና ሀገር በወከልንበት ሰዓት ቦንዶችን በመግዛት በ8100 ቴክስት አየላኩኝ የምንችለው አድርገን ቆይተናል ወደ ፍፃሜው እየመጣ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ አገር የሚጠቅም የትውልድ መሻሻልን የሚያመጣ በመሆኑ በትኩረት ነው ዜናዎችን የምከታተለው፡፡

ሀትሪክ፡-የግብፅ ድንፋታን እንዴት አየኸው…? የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ግብፅን የምንገጥመው በብሔራዊ ቡድናችን ሳይሆን በጠንካራው መከላከያ ሰራዊት ነው ማለታቸውንም እንዴት አገኘኸው?

ዳዊት፡- /ሳቅ/ ለአንድ እግር ኳስ ተጨዋች ደስ የሚል አባባል አይደለም… ኳስ ተጨዋች ሁሌ ለማሸነፍ ነው የሚገባው ቢሸነፍም ታርጌቱ ማሸነፍ ብቻ ነውና ቀልዱ ትንሽ ያማል… ሁለትና ሶስት ሚዲያዎች ላይ ነው አባባሉን የሰማሁት… የአገራችን ምሁራኖችም ሲያነሱት ሰምቻለሁ፡፡ ሲደገም ግን ተበሳጨሁ?

ሀትሪክ፡- እኔ ስላልኩህ አብደሃላ…

ዳዊት፡-አንተማ ለ4ኛ ጊዜ ነው የተናገርከው/ሳቅ/ ወደ ግብፅ ጩኸት ስንመለስ ጦርነት ቢነሣ ብሔራዊ ቡድናችን እንደማይሄድ ርግጥ ነው መከላከያ ሰራዊታችን ግን በጥንካሬው ርግጠኛ ነኝ ሲጀመር ልዩነቱ በዲፕሎማሲ ቢፈታ ደስ ይለኛል፡፡ በርግጥ አለመስማማታቸው ሰምቻለሁ… ያ ማለት ውይይቱ ይቆማል ማለት አይደለም ያለንበት ዘመን 21 ክፍለ ዘመን እንደመሆኑ ወደ ጦርነት ይገባሉ ብዬ አልሰጋም ገላጋይም አስታራቂም ገብቶበት ሠላም ይፈጠራል ብዬ አስባለው ያ ባይሆን ግን መከላከያ ቡድን ውስጥ እንደመጫወቴ ለመከላከያ ሠራዊት ቅርብ በመሆኔ ለምንም የማይበገሩ ናቸው በነርሱ ርግጠኛ ነኝ ስጋት የለብኝም ግን ቅድሚያ ለዲፕሎማሲ ቢሰጥ ደስ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የፀጥጉር ቁርጥህ ለየት ያለ ሆኗል… ልጅ ነኝ ለማለት ያህል ነው?

ዳዊት፡- /ሳቅ/ የተቆረጥኩበት ምክንያት አለኝ ልጅነት ወሳኝና የሚፈልግ ጊዜ ቢሆንም ቢፈለግም አይመለስም የተቆረጥኩት በአዲስ መንፈስ ለመምጣት ቢሆንም ዋናው ምክንያት ግን በኮቪድ 19 የተነሣ ነው ቶሎ ቶሎ ፀጉር ቤት መሄድ አስቸጋሪ ስለሆነ ፀጉሬን አሰናብቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-በፀጉር አቆራረጥህ… የመጣ አስተያየት የለም?

ዳዊት፡- ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድን መመረጥ ትፈልጋህ እንዴ ተብያለሁ.. /ሳቅ/ አዲስ መስሪያ ቤት መቀጠር ትፈልጋለህ እንዴ ብለውኛል… ትንሽ ቀልድ ቢጤ ወርወር ተደርጎብኛል፡፡

ሀትሪክ፡-ከሰበታ ከተማ ጋር የ1 አመት ኮንትራት አለህ ያኔ ኮንትራቱ ሲያበቃ… 3 ወይም 4 አመት ትጫወታለህ… እድሜው ይፈቅዳል..?

ዳዊት፡- ጨዋታውን መቀጠል አለመቀ ጠሌን ውስጤ ነው የሚነግረኝ… አሁን ግን ሁለቱም እየተጋጩብኝ ነው እግር ኳሱ በጥሩ ደረጃ እየሄደ ነው ወይ የሚለው ለኔ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖብኛል ምናልባት በዚያ ምክንያት ይሆናል እንጂ የማልጫወተው የአቅም ችግር የለብኝም፡፡ ኳሱ ላይ ለውጥ ማምጣት የምችልበት ሁኔታ ከሌለ የመሰልቸት ነገር ይመጣልና ቀጣዩ ጊዜ አስግቶኛል በእቅድ ደረጃ የተያዘ ነገር ባይኖርም እንደምጫወት ግን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ዳዊት በጭንቅላቱ ነው የሚጫወተው እንጂ በፊትነሱ አይደለም የሚሉ አሉ.. እንዴት ያየኸው?

ዳዊት፡- ለኔ እድሜ እየጨመረ ሲሄድ አረጀ ነው የሚባለው… በርግጥም እድሜዬ እጨመረ ሲሄድ የማስብ አቅሜ እየጨመረ ይሄዳል… በአለም ላይ በተቃራኒው የሚሆነው ብዙ የማይጫወቱት ናቸው ብዙ የሚያስቡት… ብዙ ባሰብክ ቁጥር ብዙ ኢነርጂ ነው የምታወጣውና ታስባለህ ሲባል ሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪ ያስባልና ቶሎ ይደክማል.. ሜዳ ላይ ሩጫና ጉልበት ሲያመዝን እኔ በአዕምሮ ስለምጫወት ሰውነቴ ቶሎ አይደክምም… ብዙ አስቦ ትንሽ ነገር የሚያርገው ብዙ ኢንርጂ ያወጣልና… እንዴት እንደቆየሁ አላውቅም ራሴን እጠብቃለሁ ብል ሰዎች ትንሽ ሊስቁ ይችላሉ በተለይ ከመጠጡ አንፃር አንድ ስም ይወጣብህና ስሙ ተከትሎህ ይሄዳል… /ሳቅ/ ነገር ግን ራሴን ሳልጠብቅ ወደ 16 አመት ሙሉ መጫወት ባልቻልኩ ነበር እግዚአብሔር ይመስገንን ለዚህ ደርሻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-የሰበታ ከተማ ኮንትራት ሲያልቅ በቡና ማሊያ ዳግም የምናይህ ይመስልሃል?

ዳዊት፡- /ሳቅ/ ባለፈው የዝውውር መስኮት ላይ ከአሰልጣኙ ጋር ተነጋጋረን ነበር በኋላ ግን ወደ ሰበታ ከተማ አቅንቻለሁ… ከዚያ ውጭ በወሬ ደረጃ ነው የሰማሁት በቀጥታ ከቡድኑ ወይም ከአሰልጣኞቹ የመጣ ነገር የለም… ወደፊት ግን የሚሆነውን የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-ዘመን የማይሽረው የአድናቆት ስንኝ ከቡና ደጋፊዎች ተበርክቶልሃል…. “የምን ሜሲ ሜሲ የምን ቶሬስ ቶሬስ እኛም ሀገር አለ ዳዊት እስጢፋኖስ” የሚለው ዜማ ሁሌም ይታወሳል.. ተመሳሳይ ዜማ ያለው አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ብቻ ይመስለኛል…. አንተ ዜማውን በጣም ስለምትወደው ስልክ መጥሪያ አድርገኸዋል አሉኝ… እውነት ነው?

ዳዊት፡- /ሳቅ በሳቅ/ ይሄ ነገር ሌላ ክለብ እንዳልገባ የታሰበ ይመስላል /ሳቅ/ ስልኬ ላይ የለም ስታዲየም ውስጥ በህብረት ሲባል እንጂ በሞባይል ጥሪ ስሰማው ክብደቱ ያንሰብኛል /ሳቅ/

ሀትሪክ፡-የደመወዝ ጉዳይ ሲነሣ ሁኔታው ከበደ ያለ ይመስላል.. ያለ ደመወዝ ኑሮ አይከብድም?

ዳዊት፡- በጣም ይከብዳል… በቤተሰብ ዙሪያ እያወራን ነውና ዳዊት የትላንቱ አይደለም… ቤተሰብ ይመራል በኪራይ ቤት ይኖራል የሚበላ የሚጠጣ… ሲባል ብዙ ውጪ አለ… የምትፈልጋቸውን ነገሮች የምታደርገው ሠርተህ ባገኘኸው ገንዘብ ልክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተጨዋቾችን ከሌላው አለም የሚለዩን ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እኛን የሚደግፍም ነገር የለም ከሜዳ፣ ከስልጠና አንስቶ ለኛ የሚያደላ ነገር የለም፡፡ አብዛኛው ተጨዋች ከዝቅተኛ ማህበረሰብ እንደመምጣቱ ቤተሰብን የማስተዳደር ኃላፊነት ሲረከብ ትዳር ሲመሰረት የመምራት ኃላፊነቱ ከበድ ይላል፡፡ ይሄ ማለት የሚገኙ ገንዘቦችን ለብቻው አይደለም የሚጠቅመው ማለት ነው፡፡ ይሄ መታሰብ አለበት፡፡ አንዳንድ ትልቅ ሰው የምንለው ተጨዋቾች ለምን በራሽን ካርድ አይሰለፉም ሲልም አድምጠናል ይሄ አግባብ አይደለም እኛ የምንኖረው ከህዝብ ጋር ነው የህዝብ ልጆች ነን ማህበረሰባችንን የምንጠቅመው እኛው ነን ክፍያው ለሀገሪቱ እንጂ ትልቅ የሚባለው ከሌላው ሀገር ጋር አይገናኝም ብር ሲገኝ ስራ ሲገባም ተመልሶ እዛው ነው ኢንቨስት የሚደረገውና ተጨዋቹች መደገፍ አለባቸው፡፡ እናቱና አባቱን የሚረዳ እህት ወንድሞቹን የሚያስተምር ትዳሩን የሚመራ ተጨዋች ይበዛልና አሁን ባለው ሁኔታ ከባድ ሆኖብናል… ደመወዝተኛ ከመሆናችን ውጪ የተለየ ገቢ የለንም፡፡ ይሄ መታወቅ አለብን፡፡

ሀትሪክ፡-የተጨዋቾች የጨዋታ ዘመን አጭር ነው ከዚህ አንፃር የቀጣይ ዘመናት ስራ የምትሰሩት አሁን ነውና ይሄስ አይከብድም?
ዳዊት፡- አንድ ጊዜ ከአንድ የሂሣብ ሠራተኛ የሆነ ባለሙያ ጓደኛዬና የኛ ማህበር በጋራ አንድ ጥናት ተደርጎ ነበር አንድ ተጨዋች ለ15 እና 20 አመት ቢጫወት ተባለና ሂሣብ ተሰራ… ይህን ደግሞ ለዘመናት ማለትም እስከ 70 አመት ቢቆይ ተብሎ ሂሣቡ ሲካፈል በወር የ200 ብር ደመወዝተኛ ሆኖ ተገኘ፡፡ በእግር ኳስ የጨዋታ ዘመን የሚገኘው ብር ለጡረታ ዘመን የሚበቃ መሆን አለበት ማለት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ እያለ ደመወዝ አለ መክፈል ከባድ ነው ትልቅ ጉዳት ያስከትላል ተጨዋቾቹና ቤተሰቡ አይብሉ አይጠጡ ማለት ከባድና ኃላፊነት የጎደው ውሳኔ ይመስላል አርቆ ማሰብ ቢቻል ደስ ይለኛል፡፡ እንደሌላው ህብረተሰብ ሰራተኞና የወር ደመወዝተኛ ነን… በርካታ ክለቦች በ5 ወር ውስጥ የትኛውንም ሠራተኛ ማህበር ደመወዝ ማቋረጥ አይቻልም የሚለውን የመንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየጣሱ ናቸው መንግስትም ደግሞ ምንም አይነት ምላሽ እየሰጠ አይደለም… ከባድ ችግር ውስጥ ነን ያለነው፡፡ ተጨዋቾችንኮ ደመወዝ ሳይከፈል በመቅረቱ ችግር ውስጥ ናቸው፡፡ ንብረት መሸጥ፣ ወደ ሌላ ስራ ተዛውሮ ለመስራት ተገደዋል፡፡ አንድ ተጨዋች ደሞዝ ሳይከፈለው ቀርቶ በራይድ የትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ተቀጥሮ ስራ እንዲሰራ ከተገደደ ለአገራችን የእግር ኳስ ሰዎች የሞት ያህል ነው በጣም አሳዛኝ ነገር ላይ ነው ያለነው፡፡

ሀትሪክ፡- ፌዴሬሽኑ ምን ማድረግ አለበት ትላለህ?

ዳዊት፡- በእርግጥ ፌዴሬሽኑ ሀምሌ 5/2012 ድረስ ለተጨዋቾቻቸው ደመወዝ የልከፈሉ ክለቦች ዝውውር ማድረግ አይችሉም ከጽ/ቤቱም ማንኛውንም አይነት ግልጋሎትን አያገኙም ብሏል፡፡ ቀነ ገደቡም አልፎ በርካታ ክለቦች ደመወዝ አልከፈሉም፡፡ ፌዴሬሽኑ ክለቦች ላይ የጣለው ዕገዳ ለተጨዋቾች ምግብና መጠጥ አይሆንም ውድድር መካሄድ ሲጀመር ያኔ ከፍለው መወዳደር ይችላሉኮ ተጨዋቹ ከነቤተሰቡ ከሞት በኋላ ማለት ነው ከተጎዱ በኋላ ምን መፍትሔ ቦታ አይኖረውምና ፌዴሬሽኑ እንደገና ውሳኔውን በመመርመር ደመወዝ ሊያስከፍል ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ ያለ ደመወዝ ህይወት ከባድ ነው ያለችውም እያለቀ ስለሆነ ፌዴሬሽኑ ከዚህ አንፃር ጠንካራ ርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የሚዲያ ትኩረት አናሳ ነው የሚል ቅሬታ ስታሰማ ሰምቻለሁ መነሻህ ምንድነው?

ዳዊት፡- ከእግር ኳስ ጋር በተያያዘ ኑሯቸውን የሚመሩ አካላት አሉ፡፡ በርካታ ባለድርሻ አካላት ለምሣሌ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ የክለብና የፌዴሬሽን አመራሮች ጋዜጠኞች ኳሱ ስላለ አብረን የምንኖረው ህይወት ነው… ጋዜጠኛውም ስፖርት ከሌለ ስራ ይቀይራል ወይ እንደሌላው ስራ አጥ ይሆናል ይሄ ነው እውነቱ… ታዲያ ይህን እግር ኳስ እንዴት ነው መጠበቅ ያለብን? አለምን ማንቀጥቀጥ እየቻሉ ዝም ማለታቸው ቅር ያሰኛል በተለይ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ረዘም ያለ ትኩረት የሰጡት ስለውጪው ብቻ ነው ለአንድ ኢትዮጵያዊ ተጨዋች ቤተሰብ ስለ ሮናልዶ ስለሜሲ ቢወራ ለኛ መጠጥና ምግብ አይሆንም፡፡ በአሁኑ ሰዓት እንደ ዜጋ፣ እንደ መብት ተሟጋች እንደ ባለሙያ እንደ ቀና ሰው መጮህ ያለባቸው የሚዲያ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ፍትህ እስክናገኝ ድረስ መጮህ መናገር አለባቸው ብዬ አስባለው፡፡ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የሰጡትን ደካማ አቋም ነው የማየው ተመልከት.. እንደ ዝውውር አይነቱ ዜና ነው የሚሰማውና ትኩረት ያገኘው…ስለ ሌሎች ሊጎች መጀመርና ተዛማች ዜናዎች ነው የሚወራው የኛ የደመወዝ ችግር እየተነገርኮ አይደለም የኛ ሀገር ቀጣይ የኳስ ታሪክ ያሰጋኛል፡፡ በመክፈልና ባለመክፈል ንትርክ ውስጥ ስንተኛ አመታችን መሆኑ ቢታይ ስጋት መፍጠሩ አይቀርም ያለፉትን 3 አመታት ማንኛውም ተጨዋች ጥሪት ሰብስቧል ብዬ አላምንም፡፡ ከ6 ወር ደመወዝህ 3 ወር ተክፍሎህ የ3 ወር ላይከፈልህ ይችላልና የ6 ወሩን ኑሮ በ3 ወር ነው የምታብቃቃው ችግሩ ይሄን ያህል የከፋ ይመስለኛል… እንደኔ የሀገራችን የስፖርት ሚዲያዎች ለሀገራችን እግር ኳስ ሩቅ ናቸው ቢቀርቡን ኖሮ ህመማችን ይሰማቸው ነበር ብዬ አስባለው፡፡ የክለቦችን መጥፎ አሰራር ተመልክተው ለመፍትሔ ይጮሁ ነበር ብዬም አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- ምንም አልተናገሩም አላወሩም ማለት ግን አይከብድም?

ዳዊት፡- ምናልባት አንድ ሚዲያ በወር አንዴ ሊናገር ይችላል ይሄ ግን በቂ አይደለም፡፡ የመኖር የመብላት የመጠጣት ቤተሰብ የመምራት የህልውና ጉዳይ ነውኮ ጊዜ አይሰጥም ጮኸውልን መብታችንን ሊያስከብሩ ይገባል፡፡ እንደሌላው የህብረተሰብ ክፍል ከመንግስት ድጎማ እየጠበቅን አይደለም የሰራንበትን ደመወዝ ነው የጠየቅነው፡፡ ላገላገልነው በትክክለኛው መንገድ ይከፈለን ነው ያልነው… በዚህ ጉዳይ መንግሥትም ሊያግዘን ይገባል፡፡ ሚዲያዎች እጃችን ላይ ባሉ ውሎች አግዘውን ችግራችን እንዲፈታ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በዚህ ጉዳይ በሚዲያው ቅር ተሰኝቻለሁ፡፡ እነርሱ ብዙ ነገር ማድረግ ስለሚችሉና ከእነሱ ብዙ ጠብቄ ባለማግኘቴ እዝኛለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-ሚዲያ ብለህ ትኩረት ያደረከው ሬዲዮ ላይ ብቻ መሆኑ ተገቢ ነው?

ዳዊት፡- በተለይ ብዙ ጊዜውን የያዘው ሬዲዮ ስለሆነ ነው እንጂ ሁሉንም ይመለከታል፡፡ ሬዲዮ ከብዛቱ በቀየኑና በየሰዓቱ ብዙውን ጊዜ የተቆጣጠሩት እነርሱ ስለሆነ እንጂ ችግሩ በሬዲዮ፣ ቴሌቭዥንና የህትመት ሚዲያዎች ላይም አለኮ…ሁሉም ስፖርት ላይ ተመርኩዞ ህይወቱን እየመራ ያለው አካል ይመለከተዋል የዳዊትም ሆነ የሌላው ተጨዋች ጉዳይ ይመለከታቸዋል ከሰብዓዊነት አንፃርም ሊያዩት ይገባል ያኔ ነው የሚሰማቸው የሰራህበትን ስራ ክፍያው ግን የለም መባልን እንዴት እንደሚጎዳ ሊረዱና ሊጮሁልን ይገባል ያደላቸው አገሮች ኮቪድ 19 ከመጣ ጀምሮ ከደመወዛቸው ውጪ ድጎማ እያደረጉላቸው ነው፡፡ ተቀራርበው ተነጋግረው ከተጨዋቾቻቸው ጋር ተስማምተው ደመወዝ የከፈሉም አሉ… በተቃራኒ መወያየት ያልተቻለባቸው ክለቦችም አሉ… በጊዜው ኃላፊነታቸውን ለተወጡና የተጨዋቾቻቸውን ደመወዝ ለከፈሉ ክለቦች ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለው፡፡ በአጠቃላይ ሚዲያው ከዝምታ ወጥቶ እንደሚያግዘን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ባለሙያዎች ማህበር ከተመሰረ ተበት አጠር ያለ ጊዜ አንፃር ጥንክሬው የጎላ ነው ማለት ይቻላል?

ዳዊት፡- አዎ ጥንካሬው ይበልጣል… በውስጡ ያሉት ሰዎች ከልባቸው ተቆርቁረው የመጡ ሰዎች በመሆናቸው ያገባኛል ኖሬበታለሁ ብለው ስለሚያስቡ ማህበሩ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ በሙሉ ኃይላቸው እየሰሩ በመሆኑ ጥንካሬው ከምስረታ ጊዜው በላይ ሄዷል፡፡ እንደ ማህበር የሰራነው ስራ ከጊዜው አጭርነት አንፃር በልጧል ባይ ነኝ፡፡ በውስጡ ያሉ ጠንካራ ሰዎች የማህበሩን ጥንካሬ አጉልተውታል፡፡

ሀትሪክ፡- የማህበሩ አመራሮች በዝውውር ጣልቃ ይገባሉ ኮሚሽን ይቀበላሉ የሚለውን የኢንተር ሚዲየሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ትችት እንዴት አገኛችሁት?

ዳዊት፡- ሀትሪክ ላይ የወጣውን ዜና አይተነዋል በዚህና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ማህበራችን ምላሽ የሚሰጥበት በመሆኑ አሁን ምንም መናገር አልፈልግም ነገር ግን ማህበራችን በርካታ መልካም ስራዎችን እየሰራ ነው በዋናነነት የተጨዋቾችን መብት ማስከበር ላይ እየሰራ ይገኛል ለተጨዋቾቹ መናገር የምፈልገው መብታችሁን የሚያስከብር ማህበር ስላለ ከማህበሩ ጋር መቀራረብና ጥሩ ግንኙነት መፍጠር ዞሮ ዞሮ ጥቅሙ ለራስ ነውና ማህበሩን ብትቀላቀሉ ደስ ይለናል ማህበሩ ወዳንተ ይቀርባል እናንተም ለመቅረብ መዘጋጀት አለባችሁ እላለው፡፡ በዚህ አጋጣሚ እስከዚህ ሰዓት ድረስ ላደረስን እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን የምለምነው ቀረው ዘመናችን ከኮቪድ 19 የነፃ በሰላምና ፍቅር ከዘረኝነት ወጥተን የምንኖርበት ጊዜ እንዲሆንልን እፀልያለሁ አምላኬንም እማፀናለሁ… እግዚአብሔር የሚወደውን ስናደርግ ብቻ ነው ጥሩ ሁኔታዎችን የሚፈጠሩት በሽታዎች የሚወገዱትና ከክፉ ስራ ተመልሰን ከፈጣሪ ጋር የምንታረቅበት ጊዜ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-የመጨረሻ ጥያቄ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ ሙላለም ጥላሁን ከጀርመን ከሀትሪክ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ አንብበሃል… ?

ዳዊት፡- አዎ በደንብ አንብቤያለሁ /ሳቅ/

ሀትሪክ፡-ታዲያ ሙላለም እንዳለው ደዊት BBF Beauty By force በግድ ቆንጆ የሆነ የሚለውን ተቀበልከው…?
ዳዊት፡- /ሳቅ በሳቅ/ BBF ነው Beauty by Force… /ሳቅ/ አነበብኩት… ግን እንደዚያ ያለኝ ሰው እራሱ ቢቢሲ ነው፡፡ Beauty by cosmotics ያለ ኮስሞቲክስ ውጪውን ማየት የማይችል ሰው ነውኮ ይህን ያለኝ /ሳቅ/ ለማንኛውም በዚህ ደረጃ አስቤ ተጨንቄ አላውቅም ፈልጌ ባላመጣሁት ነገር ፈፅሞ አልጨነቅም /ሳቅ/

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport