“ኢት.ቡናን የለቀቅኩት ለገንዘብ ብዬ ሳይሆን ክብርን ፍለጋ ነው” አህመድ ረሽድ (ሼሪላ) ባህር ዳር ከተማ

“የተጨዋቾች ህይወት እንደ ጎማ ነው፤ ካገለገልን በኋላ እንጣላለን”

“ኢት.ቡናን የለቀቅኩት ለገንዘብ ብዬ ሳይሆን ክብርን ፍለጋ ነው”
አህመድ ረሽድ (ሼሪላ) ባህር ዳር ከተማ


ደስተኛ እንዳልሆነ ንግግሩ ሁሉ ያሳብቃል፤ በሆነው ሁሉ እንደተከፋም ደጋግሞ ይናገራል፤በእርግጥ ከባህርዳር ከነማ ጋር በፊርማ ቢተሳሰርም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የተለያየበት መንገድ ግን ደስታውን ነጥቆታል፡፡ “በቃ እውነቱን ልንገርህ በክለቡ ተገቢው ክብር አልተሰጠኝም፤በአንድ ወቅት ለክለቤ ውጤታማነት ስታገል ሜዳ ውስጥ ህይወቴ ለማለፍ ተቃርቦ ነበር፤በዚህ ደረጃ ዋጋ የከፈልኩለት ክለቤ ግን ላቀረብኩለት ትንሽ ጥያቄ ምላሽ ሊሰጠኝ ባለመቻሉ በጣም ተከፍቻለሁ” ይህ ቃል የኢትዮጵያ ቡናው አህመድ ረሺድ (ሽሪላ) ቃል ነው፤በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ሽሪላ በሚል ቅፅል ስሙ ተቆላምጦ የሚጠራው አህመድ ረሺድ ከክለቡ ጋር ሲያደርገው የነበረው ድርድር ባለመሳካቱ ወደ ጣና ሞገዶቹ ባህር ዳር ከነማ መዛወሩ እውን ሆኗል፤ “የተጨዋች ህይወት የጎማ ያህል ነው፤ ጎማ ካገለገለ በኋላ እንደሚጣለው የእኛም እጣ ፈንታ ካገለገልን በኋላ መጣል ነው” የሚለው ሽሪላ “በደጋፊው ትልቅ ክብርና መወደድ ቢኖረኝም በክለቡ ግን ተገቢው ክብር ስላልተሰጠኝ ያለ ፍላጎቴ ለመልቀቅ ተገድጃለሁ” በማለት ቁጭት በተሞላበት ስሜት ከኢትዮጵያ ቡና መለያየቱ ዕውን ከሆነ በሃላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተለይ ለሀትሪክ ተናገሯል፡፡
የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ በተዘበራረቀ ስሜት ውስጥ ያለውን በኃይማኖታዊ እውቀቱም በጥንካሬውም የሚታወቀውን አህመደ ረሺድ (ሽሪላን) በቃ አንተና ኢትዮጵያ ቡና ተለያያችሁ?ቡናን የለቀቅከው እውነት ለገንዘብ ነው? በማለት ጀምሮ ሌሎችን በማስከተል ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጓል፤ተከተሉን፡፡


ሀትሪክ:-አንድ ነገር በቅድሚያ ልጠይቅህ ነው? ሽሪላ ኢትዮጵያ ቡናን ለገንዘብ ሲል ነው የለቀቀው?

አህመድ፡- …እንዴ? መጀመሪያ ለቃለ-ምልልሱ ስለተባበርከን እናመሰግናለን…ኑሮ ህይወት ሠላም ነው? ኮሮናስ እንዴት እያረገህ ነው…ብሎ አግባብቶ ነው ወደ ከባድ ጥያቄ የሚገባው (ሣቅ) አንተ ግን ዘለህ ገንዘብ ላይ ገባህ?

ሀትሪክ፡- …እሺ ሽሪላ ኮርስ እየሰጠኸኝ ነው መሰለኝ…ስለተባበርከን አመሰግናለሁ…ህይወት እንዴት ነው…ኮሮናስ እንዴት እያረገህ ነው…?

አህመድ፡- …(በጣም ሳቅ)…ጋዜጠኛ ባልሆንም አካሄዱ እንደዛ ይመስለኛል፤.. ወደ ጥያቄህ ስመለስ ህይወት ያለ እግር ኳስ ብዙም ጣዕም የለውም ኮሮና ቫይረስ የምንወደውን ነገር ነው የነጠቀን፤ያም ቢሆን አልሀምዱልላሂ ለቤተሰብ የፍቅር ጊዜ እንዲኖረን አድርጓል፤መጥፎው አጋጣሚ ያላሰብነውን ጥሩ ነገር ሰጥቶናል፤ ቤተሰቦቼን ጓደኞቼን በተለይ ለባለቤቴ የተንበሸበሸ ጊዜ እንድሰጥ በማድረጉ ኳሱን ቢነጥቀንም በዚህ እየተፅናናሁ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- እስቲ አሁን ወደ ዋናው ጉዳዮችን እንግባ፤የምር ሽሪላና ኢት.ቡና ጨክነው ተለያዩ ማለት ነው?

አህመድ፡- …አዎን እውነት ነው ተለያይተናል…፤…ለረዥም ወራት ከክለቡ ጋር ስታገል የነበረውን ከኢት ቡና መልቀቅ ጋር ስሜ ተያይዞ እንዲነሣ ካለመፈለጌና የመልቀቄ ነገር ዕውን እንዳይሆን ነበር፤ግን አልተስካልኝም በመጨረሻ እኔና ቡና ያለ ፍላጎቴ ተለያይተናል፡፡

ሀትሪክ፡- …ባህር ዳር ከነማ ከመግባትህ በፊት በድርድሩ ተስማምታችሁ ለቡና እንደፈረምክ ተወርቶ ነበር እኮ…?

አህመድ፡- …ልክ ነህ ተወርቶ ነበር፤ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ይሁን ሌላ አላውቅም ፈርሟል ብሎ ነግሮናል በሚል ሚዲያ ላይ ተወርቶ ነበር፤በወቅቱ የተወራው ወሬ ግን ሆን ብሎ የተወራና በእኔ ቀጣይ ህይወት ላይ የራሱ የሆነን አደጋ የሚፈጥር ነበር፤ምክንያቱም ከቡና ጋር ካልተስማማሁ የግድ ወደ ሌላ ክለብ መዛወር አለብኝ፤ ከዚህ አንፃር ወሬው ክለብ ያሳጣሃል…ለፈላጊዎቼም በር ይዘጋል፤ከቡና ጋር የሚደረገውን ስምምነት ሲጠባበቁ የነበሩ ስማቸውን የማልጠቅስልህ ወደ አራት የሚጠጉ ክለቦች ሁኔታውን ለማጣራት እኔጋ ደወለው እስከመጠየቅ ሁሉ ደርሰው ነበር፡፡ ሳልፈርም ነበር ፈርሟልተብሎ የተወራው፡፡

ሀትሪክ፡- …ብዙዎች አህመድ (ሽሪላ) ያውም በዚህ ወቅት ቡናን ጨክኖ የሚለቅበት አንጀት የለውም ሲሉ ይደመጥ ነበር፤ ቡናን ጨክኖ እስከመልቀቅ ያደረሰህ ምንድነው?

አህመድ፡- …ከመጀመሪያው ስጀምርልህ ለኢት.ቡና እየተጫወትኩ ያለሁት ከሁለት አመት በፊት በነበረው ደሞዝ ነው፤ለክለቡ እየሰጠሁ ያለሁት ግልጋሎትና እየተከፈለኝ ያለው የሚመጣጠን አይደለም፤ሌሎች ተጨዋቾች የሚያገኙትን አውቃለሁ፤ወደ ሌላ ክለብ ብዛወር ምን እንደሚሰጡኘ በተለያየ ጊዜ ይገልፁልኛል፤ነገር ግን ክለቡን ስለምወደው…የቤተሰቤ አካል ያህል አድርጌ ስለማየው…በቤተሰቤም በጣም የሚደገፍ የሚወደድ ክለብ በመሆኑ ቡናን በገንዘብ መለካት አልፈለኩም፡፡ በዚህ የተነሣም አንድም ቀን በገንዘብ ዙርያ ከቡና ጋር ተደራድሬ ወይም ይሄን ያህል ሚሊዮን ብር ይሰጠኝ ብዬ ጠይቄ አላውቅም፤ነገሮች እያደጉ እየተለወጡ ተጨዋቾች ተጠቃሚ እየሆኑ ባለበት ጊዜ እኔ ግን ሁሉም ነገር ከቡና አይበልጥም ብዬ ዛሬም ከሁለት አመት በፊት በነበረው ደሞዜ ተጫወት ስባልኩት ይሄም አላስከፋኝም፤ሌላ ቦታ ብሄድ የማገኘውን አውቃለሁ፤ ግን ሁሉም ነገር ከቡና አይበልጥ ብዬ እሺ አልኩ፤ግን ቤተሰብ እንዳለው ሰው የገጠመኝን ችግር አስመልክቶ ትንሽ ጥያቄ አቅርቤ አዎንታዊ ምላሸ ሊሰጡኝና ሊያስተናገዱኝ ባለመቻላቸው በጣም ከፋኝ…ተበሳጨሁ…በመጨረሻም ለመለለያየት በቃን፡፡

ሀትሪክ፡-…ምን ጠይቀህ ነው…?…የሁለት አመት ገንዘብ በአንዴ ስጡኝ ያልከውን ነው ትንሽ ጥያቄ ያልከው?

አህመድ፡-…በእርግጥ እኔ ተጫወትኩ ስራዬን ሰራሁ ወደ ቤቴ እንጂ ፌስ ቡክ ላይ የመጠመድ ልምዱ የለኝም፤የፌስ ቡክ ተጠቃሚ የምባል ሰውም አይደለሁም፤ግን ፌስ ቡክ ላይ ሽሪላ የሁለት አመት ደሞዜን በአንዴ ካልከፈላችሁኝ እለቃለሁ ብሎ ጠየቀ በሚል ስናፈስ እንደነበር ሰምቼ አዝኛለሁ፤እኔም ሆንኩ ሌሎች የክለቡ ተጨዋቾች የሁለት አመት ደሞዛችንን በአንዴ ስጡን ብለን አልጠየቅንም፤ ወደ እኔ ስትመጣ የጠየኩት የቤተሰብ ከባድ ችግር ገጥሞኛልና ሌላ ነገር አትሰጡኝ ይቀርብኝ የስድስት ወር ደሞዜን ስጡኝና የገጠመኝን ችግር ልወጣ ስላቸው…ብር የለንም ችግር ላይ ነን ወደፊት ግን ካገኘን እናስተካክልልሃለን የሚል ምላሽ ሰጡን፤ከሣምንት በኋላ በሚዲያ ላይ ገንዘብ ማግኘታቸውን ሰማንና እንደገና ጥያቄ አቀርብኩላቸው፡፡

ሀትሪክ፡- …ምን አይነትገንዘብ… ምን አይነት ጥያቄ…?

አህመድ፡- …የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ክቡር ታከለ ኡማ ለኢት.ቡናና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ያለባቸውን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ ይረዳል በሚል ለእያንዳንዳቸው 15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን በሚዲያ ስሰማ ይሄ ያላሰቡት እቅዳቸው ውስጥ የሌለ ገንዘብ ስለሆነ አሁን ጥያቄያችን መልስ ሊያገኝ ይችላል ወደ ሌላ ውሳኔ ከመሄዴ በፊት ለምን አለናግራቸውም ብዬ የሚመለከታቸውን ሰው አናገርኩ…

ሀትሪክ፡-ምን መልስ አገኘህ?

አህመድ፡-በሚገርምህ ሁኔታ የተለሳለሰ መልስ አገኛለሁ ስል በድጋሚ የተሰጠኝ ምላሽ ችግርና እዳ እንዳለባቸውና ሊያስተናገዱኝ እንደማይችሉ ነው፤በእርግጥ ምን እዳ እንዳለባቸው የሚያውቁት እነሱ ናቸው…በምላሻቸው በድጋሚ ተስፋ ቆረጥኩ…ከምላሻቸው የተረዳሁት ነገሩ እንደማይሆን ስለሆነ የራሴን ውሳኔ መውሰድ አለብኝ የለብኝም የሚል ነገር ውስጥ ገበሁ፤እኔ ክለቡን ከመውደዴ የተነሣ የተጨዋቾች ደሞዝ በሁለት አመት ውስጥ ወዴት እንደተመነደገ እያወኩ ከሁለት አመት በፊት በነበረው ደሞዝ ተጨዋት ስባል እሺ አልኩ እንጂ አልተደራደርኩ…ይሄን ያህል ሚሊዮን ብር ይሰጠኝ አላልኩም…በገጠመኝ ችግር ምከንያት የስድስት ወር ደሞዜን ስጡኝ ነው ያልኩት…ይሄን ማድረግ ትልቅ ነገር ሆኖ ነው?…እኔ ቤተሰብ አለኝ…ገንዘብ የጠየኩት በገጠመኝ ችግር ምክንያት ነው፤መልስ ብጠብቅ መልስ የሚሰጠኝ አጣሁ…ቤተሰብ ስላለኝ ህይወት መቀጠል ስላለበት ከዚህ በላይ መለመንም መታገስም የለብኝም ብዬ ወደ ውሳኔ ሄድኩ፤ቡናን በዚህ መልኩ መለየት ምርጫዬም ፍላጎቴም አልነበረም፡፡

ሀትሪክ፡- ከንግግርህ ስረዳ ቡናን በመልቀቅህ ስሜትህ የተጎዳ ይመስላል፤ ከቡና በዚህ መልኩ ስትለያይ የነበረህ ስሜት…ለመወሰንስ አለተቸገርክም?

አህመድ፡- በጣም ይረብሻል፤ በጣም ያስጨንቃል፤ እውነት ለመናገር በተሰጠኝ ምላሽ ከልቤ አዝኛለሁ፣እኔ ሌላ ነገር አልጠየኩም…በሚሊየን ቤት ይከፈለኝ ብዬ አልተደራደርኩም…ችግር ገጥሞኛል…የ6 ወር ደሞዜን ስጡኝ ነው ያልኩት፤ቡድኑን እንደ ቡድን ሣይሆን እንደ ቤተሰቤ አንድ አካል አየው ስለነበር በተሰጠኝ ምላሽ በጣም ተከፍቻለሁ ፡፡
ምክንያቱም ቡና ብዙ ነገር ቢያደርግልኝም እኔም በግሌ ለቡና ብዙ ነገር…የሚገባውን ከፍያለው ብዬ አስባለሁ፤ለቡና ውጤትና ክብር መስዋዕት እስከመሆን ደርሻለሁ…ፈጣሪ ብሎ ተረፍኩኝ እንጂ የቡናን ማልያ ለብሼ እስከመሞት ሁሉ ደርሼ ነበር፡፡ በህይወት ደረጃ ለመክፈል ካልሳሳሁለት ቡና ጋር በዚህ ደረጃ እለያያለሁ ብዬ አላስብም፤የሆነውን ሁሉ ሳስበው እውነት ይሄ ለእኔ ይገባል?የሚል መጥፎ ስሜት በውስጤ በመፈጠሩ ነው የተሰማኝ፡፡

ሀትሪክ፡-ቤተሰቦችህ እናትህን ጨምሮ የቡና ደጋፊ እንደሆኑና የተለየ ስሜት እንዳላቸው አጫውተኸኛል…፤…ሃሳብህን ለማስቀየር አልሞከሩም…?

አህመድ፡- …ከቤተሰቦቼ በጠቅላላ በተለይ እናቴ በጣም ታግላኛለች፤ከቡና ውጪ መፈረም የለብህም ብላም ሞግታኛለች፤እህት ወንዶችቼ ባለቤቴም እንደዛው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሁሉም የስፖርት ቤተሰብ የሚያውቀው…ለቡና ትልቅ ስራ የሰራው ዛሬም ድረስ የክለቡ ተቆርቋሪ የሆነው አብዱራህማን መሀመድ (አቡሸት) ከቡና ጋር እንድቀጥል ብዙ ግፊት አድርጎብኛል፡፡ “ከሁለት አመት በፊት በነበረው ደሞዝህ ተጫወት እንኳን ብትባል እሺ በል ከምታገኘው ጥቅም ይልቅ ኢት.ቡናን አስበልጠህ ተጫወት ስለ ጥቅም እንዳታወራ ምክንያቱም ከጥቅሙም ከሁሉም ነገር ቡና ይበልጣል” ሁሉ ብሎኝ ነበር፡፡እኔም ሌላ ነገር አልጠየኩም ባለው ደሞዜ የቤተሰብ ችግር ስለገጠመኝ የስድስት ወር ስጡኝ ነው ያልኩት፤ቡናን በገንዘብ ለክቼው ሳይሆን የቤተሰብ ችግር ስለገጠመኝ ብቻ ነው፤እንዳልኩህ ቤተሰቦቼን፣ጓደኞቼን፣ወዳጆቼን ማሳመኑን ከባድ አድርጎብኛል፤ቀላል የማይባል ትግልም ገጥመውኛል ግንየህይወትጉዳይነው፤ቤተሰብ አለኝ፤ህይወትም የግድ መቀጠል ስላለበት ደስተኛ ባይሆኑም ተቀብለውኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ከኢትዮጵያ ቡና መለያየትህን ለባህር ዳር ከነማ በመፈረም አረጋግጠሃል? ከኢትዮጵያ ቡና ምን ታጣለህ (Miss) ታደርጋለህ ?

አህመድ፡- ገና ስለመልቀቅ ሳስብ ውስጤን የረበሸው የደጋፊው ነገር ነው፤ደጋፊውን በጣም ነው የማጣው (Miss) የማደርገው፡፡ እንኳን ሀገር ውስጥ የትም ብትሄድ እንዲህ በቀላሉ የምትረሣው ደጋፊ አይደለም፡፡ እኔ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ እዳ አለብኝ፤ከታች አሣድጎ፣አበረታቶ፣ሳጠፋ አርሞ፣ስጠነክር አበረታቶ ነው እዚህ ያደረሰኝ፤የዚህን ደጋፊ ውለታ ሳልከፍል ሳልክሰው መውጣቴ ይቆጨኛል፡፡ በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በጣም እንደተወደድኩ ከሚዘመርላቸው ተጨዋቾች አንዱ ሆኜ ነው ያሳለፉኩት፡፡ ይሄ ለእኔ ትልቅ ኩራትና ክብርም ነው፤ይሄን ክብርና ፍቅር የሰጠኝን ደጋፊ የምገልፅበት ቃላት የለኝም፤ስሜቴንም ልገልፅላቸው አልችልም…በጣም ነው የምወዳቸው ከማለት ውጪ፤ የትም ብሔድ ከውስጤ የማይጠፉ የቤተሰቤ አካል ናቸው፤ሁሌም ሳከብራቸው ነው የምኖረው፤እነሱን በጣም ነው የማጣቸው (Miss) የማደርጋቸው፡፡

📸 ©Natanim pictuers

ሀትሪክ፡-.. አሁን ወደ ባህር ዳር ሄደሃል በኢት.ቡና ቆይታዬ ሳላሳካው ወጣሁ ብለህ የምትቆጭበት ነገር አለ?

አህመድ፡- …አዎ በጣም አለ…በእኔ የተጨዋችነት ዘመን የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በድጋሚ አንስቶ ደጋፊው ሲደሰት ባይ በጣም እደሰት ነበር፤ ከቡና ጋር አንድ ትልቅ ታሪክ አፅፌ አለመውጣቴ ይቆጨኛል፤ቡና የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ቢያነሳ…በአፍሪካ የውድድር መድረክ ሲካፈል ሣላይ መውጣቴ ዛሬ ብቻ አይደም ወደፊትም የምቆጭምበት ነው፡፡

ሀትሪክ፡-ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የመለያየት እድል ሲገጥምህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፤ከዚህ በፊት ከቡና ወጥተህ ድሬደዋ አሁን ደግሞ ወደ ባህር ዳር ሄደሀል ግጥምጥሞሹን እንዴት አገኘኸው?

አህመድ፡- የጠየከኝ ጥያቄ ለእኔ በጣም ከባድ ጥያቄ ነው…

የተወሰነውን ለመመለስ… ግጥምጥሞሹን በመልካምነት የምታነሣው አይደለም…አሁንም ባለፈው ስለቅም ፍላጎት ኖሮኝ አይደለም…ቡናን ገፍቼ አላውቅም…ይልቁንም ከቡና እየተገፋሁ ነው የምወጣው፡፡

ሀትሪክ፡- አንተ ምከንያቱ ሌላ ነው ብትልም…አንዳንድ ደጋፊዎች ግን ለገንዘብ ብለህ ቡናን እንደለቀክ ነው የሚነገሩት ትቀበለዋለህ?

አህመድ፡- …በፍፁም አልቀበለውም…ባለፈው ድሬደዋ ስሄድ…አሁንም…ለገንዘብ ነው የሄደው ተብያለሁ፤ሰዎች ቁጭ ብለው ለምን እንደዚህ አይነት ፍርድ ገምድል ፍርድ እንደሚፈርዱ አይገባኝም፤እንደዚህ ብለው ከመፍረዳቸው በፊት ለምን እውነታውን ቀረብ ብለው ለማወቅ አይጥሩም፤እንዲህ ከማለታቸውና ከመፍረዳቸው በፊት መጀመሪያ የተጨዋቹን ችግር ቢረዱ አይሳሳቱም ነበር፤ ከዚህ ሌላ ከፍርዱ በፊት ቤታቸውን ክለባቸውን ቢፈትሹ መልካም ነው…ተጨዋች ላይ ከመጠቆምና ከመፍረድ በፊት ምንድነው ችግሩ?ተጨዋቹ ምን ፈልጎ ነው?ተገፍቶ ነው ወይስ ገፍቶ ነው? ብለው ቢጠይቁና ከዚያ በኋላ ፍርድ ቢሰጡ ደስ ይለኛል…ምክንያቱም ሁሉም ተጨዋች ሊለቅ ጥፋተኛ…ክለቡ ግን ትክክለኛ ተደርጎ ፍርድ ገምድል ፍርድ ሲሰጥ ስለማይ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-ስለዚህ ቡናን የለቀኩት ለገንዘብ ብዬ አይደለም እያልክ ነው?

አህመድ፡-… በትክክል…ቡናን መቼም በገንዘብ ለክቼው አላውቅም፤ቡናን የለቀኩበት ዋናው ምክንያት ገንዘብን ፍለጋ ሣይሆን ክብርን ፍለጋ ነው፤ክብር ማለት ደጋፊ ስያከብርህ ሲወድህ ደስ ይልሃል…ደጋፊውን በተመለከተ መጀመሪያም ነገሬሃለሁ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬው የለኝም…ለእኔ ትልቅ ቦታ አላቸው፤አንዳንዴ ትልቅ ነገር እየሠራህ “አመሰግናለሁ” መባል እንኳን ክብር ነው…መነሳሳትንም ይፈጥራል፤ ከአንተ ያነሰ ሥራ የሠሩ ሲመሰገኑ አንተ ወጪ የሌለው ምስጋና እንኳን ስትነፈግ ይሰማሀል፤ከዚህ አንፃር እኔ ገንዘብን ሣይሆን ይሄንን ክብር ፍለጋ ነው የወጣሁት፤ ገንዘብ ቢሆን ኖሮ ከቡና ጋርም ይሄን ያህል ስጡኝ ብዬ እደራደር ነበር፤ብዙ ቃል ተገብቶልኝ ያልተደረገልኝ ነገር አለ…ከሁለት አመት በፊት በነበረው ደሞዝህ ተጫውት ስባል እሺ ያልኩት የተጨዋቾች ደሞዝ የት እንደደረሰ ጠፍቶኝ ሣይሆን ክለቡን በገንዘብ መለካት ስላልፈለኩ ነው፤በየፌስ ቡኩ ግን የሁለት አመት ደሞዙን በአንዴ ስጡኝ ብሎ ጠይቆ ነው በሚል ሲናፈስ ነው የነበረው፤ይሄ 100 ፐርሰንት ውሸት ነው…ችግር ስለገጠመኝ የስድስት ወር ደሞዜን ስጡኝ ብቻ ነው ያልኩት፡፡

ሀትሪክ፡- …አንተን ጨምሮ በርካታ ተጨዋቾች ማለትም ፈቱዲንና አቡበከር ጭምር የ2 አመት ይሰጠን ብላችኋል የተባለውስ…?

አህመድ፡- …ይሄን ነገር እንኳን አነሳኸው እነዚህ ተጨዋቾች ላይ የሚወራው ደስ ስለማይልና ለከለቡ ስለማይጠቅም ከፈቀድክልኝ ብናገር ደስ ይለኛል፤እነዚህ ተጨዋቾች እንደተባለው በፍፁም አልጠየቁም…አብሬያቸው እስከተጫወትኩ…እስካሳለፍኩ ድረስ ጓደኞቼ የጠየኩት አጭር ቃል ነው “በጣም ችግር ላይ ነን…ከቻላችሁ የአመት ካልቻላችሁ ደግሞ የስድስት ወር ስጡን ነው ያሉት”ይሄን መጠየቅ ምንድነው ሀጢአቱ? እኔ 10 ሚሊዮን ብጠይቅ ክለቡ ደግሞ አይ አስር ብር ነው የምችለው ሊል ይችላል… ይሄ መብቱ…ነፃ ገበያ ነው፡፡ ተጨዋቾቹ ስንባል የእኛ ህይወት የመኪና ጎማ ያህል ነው፤ልክ እንደ ጎማ አገልግሎታችን ሲያልቅ የምንጣል ነን፤ይሄ ግልፅ ነገር ነው፡፡ የጨዋታ ዘመናችን ሲያልቅ ስንጎዳ የምንጠቀመው አሁን በጨዋታ ዘመናችን አቅማችን ባለበት ሰዓት መሰብሰብ ከቻልን ነው…አሁን በምናየው ሀቅ እኮ ተጨዋች ሲጎዳ የሚያሳክመው ማን እንደሆነ ይታወቃል፤አንድ ሌላ እውነት ልንገርህ…

ሀትሪክ፡-ምን… ?

አህመድ፡- አንዳንዶች ካልሆኑ በስተቀር ተጨዋቾች ስንባል በትምህር የገፋን አይደለንም፤ ሌላውን ተወው እኔን እንኳን ብትወስድ ለኳስ ብዬ ትምህርቴን 11ኛ ላይ ነው ያቆምኩት…ድግሪ ዲፕሎማ አብዛኞቻችን የለንም፡፡ በዚህ በኳስ በምናገኘው ደሞዝ ነው ቤተሰቦቻችንን፣ትዳራችንን የምንመራው የምናስተዳድረው፤በጨዋታ ዘመንህ ማግኘት ያለብህን ካላገኘህ ስትጎዳ ተጫዋቹ ብቻ ሣይሆን ቤተሰቦቹም ችግር ላይ ይወድቃሉ፤በዚህን ጊዜ ስንት እንደሚገኝበት ባይታወቅም የአንድ ቀን የስታዲየም ገቢ ሊለቀቅልህ ይችል ይሆናል…እሱም ጥሩ ቲፎዞ ካለህ ነው፤ ከዚህ ባስ ሲል ደግሞ ፌስታል ተይዞ ነው የሚለመንልህ…ከዚህ ውጪ የሚደረግልህ የለም፡፡ ታዲያ በጨዋታ ዘመንህ ለነገ ስንቅ የሚሆንህን በችሎታህ መጠን መጠየቅና መሰብሰብ ኃጢያቱ አይገባኝም…ተጫዋቹ ከጨዋታ ወይም ከጉዳት በኋላ የሚገጥመውን ችግር ሰዎች ሳይረዱ ይሄን ያህል አገኘ የተጨዋቾች ደሞዝ በዛ ሲሉ ታያለህ…ተጨዋች እኮ ያንን ደሞዝ የሚያገኘው ደክሞ ላቡን አፍስሶ ነው…እኔ ከሰው ይልቅ የማዝነው በሚዲያው ነው….?

ሀትሪክ፡- …ሚዲያው ደግሞ ምን አደረገህ…?

አህመድ፡-.. የሰውን ሙያ ለመናቅ አይደለም…አንዳንድ ሚዲያዎች ደሞዛቸው በዛ እያሉ ሲከላከሉ ታያለህ…እኛ እኮ ገንዘብ የምናገኘው ላባችንን አፍስሰን ደክመን ነው፡፡ በስፖንሰር ታጅበህ ቀኑን ሙሉ አውርተህ የምታገኘውና ላብህን አፍሰስህ ደክመህ የምታገኘው አንድ አይደለም፤ይሄንን የምልህ ውስጤን ስለሚይመኝ ነው፡፡ የሆነ የአየር ሰዓት ገዝተህ ሶስትና አራት ሚሊዮን ብር ሰብስበህ ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብለህ መተቸቱ ተገቢ ነው አልልም፤ተጨዋች በጨዋታ ዘመኑ በአቅሙ ማግኘት የሚገባውን ማግኘት አለበት፤ምክንያቱም እንዳልኩህ ተጨዋች ማለት የመኪና ጎማ ያህል ነው…አገልግሎ ሲያልቅ ይጣላል፤ኧረ እንደውም ጎማ ይሻላል፤ተመልሶ ለበርባሶም ይሁን ለሌላ ይውላል፤ስለዚህ የተጨዋች ደሞዝን ስንቆጥር ባንውል…ተጨዋች ገንዘቡን የሚያገኘው ላቡን አፍስሶ ደክሞ መሆኑን ብንረዳ ደስ ይለኛል ፡፡

ሀትሪክ፡- ከታች የሚያድጉ ተጨዋቾቹ ቡና ውስጥ አልበረክት ብለዋል የሚሉ አሉ ትቀበለዋለህ?

አህመድ፡- …እውነት ነው…የአያያዝ ችግር ነው ብዬ ነው የማስበው፤በእኛ ቤት ያደጉ ተጨዋቾች በደጋፊ እንጂ በቦርዱ አካባቢ ጥሩ ክብር እንደሌላቸው እኔ ራሴ ምስክር ነኝ፤ምንም ስለማይመጣብኝ በግልፅ ልንገርህ…ስም ባልጠቅስልህም ከታች የሚመጡ ተጨዋቾች ክብር አይሰጣቸውም፤ቲሙን ለሚወዱ…ማልያውን ከልባቸው ለሚወዱ ክብር ሲሰጣቸው አታይም፤ከታች ከመጡትና ክለቡን ከልባቸው የእውነት ከሚወዱት ይልቅ አጭበርብረው በአፋቸው ብቻ ቡናን እወዳለሁ ብለው ፎግረው ለሚሄዱ ነው ክብር ሲሰጡ የምታየው፤ይሄንን በመናገሬ ነገ ብዙ ትችት እንዳሚደርስብኝ አውቃለሁ…ግን እውነት ስለሆነ ምንም የሚያስፈራኝ ነገር የለም፤እኔ ግልፁን ልንገርህ እንደውም በእኔ ይብቃ ማለትን ነው የምፈልገው፡፡

ሀትሪክ፡- ብዙውን ጊዜ አቡበከር ናስር ከአፍህ አይጠፋም ለእሱም የተለየ አድናቆት እንደለህ እሰማለሁ፤የተለየ ምክንያት አለህ?

አህመድ፡- እንነጋገር ካልከኝ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁን ሰዓት እንደ አቡበከር አይነት አጥቂ የለም ብዬም የማምን አንደኛው ሰው እኔ ነኝ፤አቡኪን የዚህ ሀገር ሊግ አይመጥናትም፤አቡኪ ከሀገር ውጪ ወጥቶ መጫወት የሚያስችል እምቅ አቅም ያለው ተጨዋች ነው፡፡ እሱ ከሀገር ውጪ ወጥቶ ሲጫወት ማየት ሕልሜ ነው፤ራሱንም ሀገሩንም ማስጠራት የሚያስችል ችሎታ ስላለው።ከእሱ ውጪ ቡና ውስጥ ብዙ አቅም ያላቸው ታዳጊዎች አሉ…እነ ሚኪን መውሰድ ትችላለህ፤ተገቢው ክብር እየተሰጣቸው ነው ወይ? ካልከኝ ለእኔ መልሱ የሚያስቅ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-ባህርዳር ከነማና አንተ መስማማታችሁን በፊርማህ አረጋጋጠሃል? እንዴት ተገናኛችሁ?

አህመድ ፡- ከባህር ዳር በፊት ከቡና ጋር በኮንትራት ዙሪያ መስማማት አለመስማ ማታችንን የሚከታተሉ አንድ አራት ክለቦች ነበሩ፡፡ በዚህ መሀል ከቡና ጋር ያለኝ ኮንትራት መጠናቀቁን አብረን እንደማንቀጥል እንደተሰማ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ደወለልኝ…አወራን ደስተኛ መሆኔንና ፍቃደኝነቴን ገለፅኩለት…እሱም ከአመራሮች ጋር ተነጋገረ… ከእኔም ጋር አወሩ…በቃ በሃሣብ ወዲያው ተግባባን…ሁሉም በጣም ተደሰቱ…እንደዚህ አይነት ተጨዋች አላገኘንም እስኪሉ ድረስ በሃሣብ ተስማማን…በመጨረሻም ዝውውሩ እውን ሆነ…፡፡

ሀትሪክ፡- …ከአሰልጣኝ ፋሲል ጋር በብ/ቡድን አብራችሁ ሰርታችኋል፤ በድጋሚ መገናኘታችሁን እንዴት አገኘኸው፤ ፋሲል አንተ ለምትፈልገው ፋሲልም ለሚፈልገው አጨዋወት የተመቸሁ ነኝ ትላለህ…?

አህመድ፡- …ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠቴ በፊት ፋሲልን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ፤ እሱ ለማሳካት ለሚያስበው ነገር ትመጥናለህ ብሎ የቡድኑ አካል እንድሆን ምርጫው ስላደረገኝ ከልብ ላመሰግነው እፈልጋለሁ፤በመቀጠል አንዳንዴ የምታውቀው…አብረኸው የሠራኸው አሰልጣኝ ሲሆን ያለህን ክህሎት አውጥተህ ለመጠቀም ትልቅ ነፃነት ይሰጥሃል፤ከፋሲል ጋር በብ/ቡድን ደረጃ አብሬ በመስራቴና አቅሙንም ስላየሁት እንደሚመቸኝ እንደማልቸገር አምኜ ነው የመጣሁት፤ከፋሲል ጋር በመስራት አቅሜን በምፈልገው ደረጃ አውጥቼ በመጫወት የስኬት ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ብዬ አስባለሁ፤ባህር ዳሮችን እንደምታውቃቸው የአጭር ኳስ አቀንቃኞች በመሆናቸው አጨዋወታቸው የምፈልገው አይነት ነው፤አሰልጣኝ ፋሲል ከሜዳ ውጪም ጥሩ ስብዕና ያለው ለተጨዋቾች የሚያስብ ሰው ስለሆነ ይበልጥ ሊመቸኝ የሚችል ቦታ እንደሆነ ነው የማምነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ወደ ክለቡ የሄድከው ስለ ባህር ዳር ከነማ ምን ያህል አውቀህ ነው…?

አህመድ:- …ስለ ቡደኑ የተለየ ጥናትና ለማወቅ ጥረት ያደረኩት ልፈርም አካባቢ ነው፤ ከመፈረሜ በፊት ብዙ ቪዲዮዎችን ተመልክቻለሁ፤ይሄን ስልህ ግን ከዚያ በፊት እውቀቱ አልነበረኝም ማለቴ አይደለም፤ ስለ ቡድኑ በቂ መረጃው አለኝ…አብረንም በተቃራኒ ተጫውተን አይቻቸዋለሁ፤ በጣም አሪፋና ሣቢ እግር ኳስ ይጫወታሉ ብዬ በግሌ ከማስባቸው ቡድኖች አንዱ ባህር ዳር መሆኑንም አውቃለሁ፤ለዚያም ነው የመጀመሪያ ምርጫዬ ያደረኳቸው፡፡በተለይ ማራኪ በሆነው የአጭር ኳስ አጨዋወታቸው አንፃር ከሌሎች ጥያቄዎች በፊት እነሱን ማስቀደም መርጫለሁ፡፡ –
ሀትሪክ፡ …በእርግጥ ጊዜው ገና ቢሆንም…ወደ ባህር ዳር የመጣኸው…ምን አልመህ…?…ምን አሳካለሁ ብለህ ነው…?
አህመድ:- በኢት.ቡና በተለይ ከስኬት ጋር ብዙም እድለኛ አልነበርኩም…በቡና ቆይታዬ ፕሪሚየር ሊጉን ከደጋፊዎች ጋር ከፍ አድርጌ አንስቼ የመሳም ትልቅ ህልም ነበረኝ፤ያ ህልሜ ሣይሳካልኘ ነው ወደ ባህር ዳር የተዛወርኩት፡፡ በኢትዮጵያ ቡና ያላሳካሁትን ህልሜን በባህር ዳር እውን የማድረግ ህልም ይዤ ነው የመጣሁት፤ባህር ዳር ትልቅ ክለብ ነው፤በዋንጫ ፉክክር ውስጥም በቅርብ ርቀት የነበረ ቡድን ነው፤ከዚህ አንፃር ከክለቡ ጋር የፕሪሚየር ሊጉን አሊያም የጥሎ ማለፍ ዋንጫን በማንሣት በአፍሪካ የውድድር መድረክ የመሳተፍ ትልቅ ህልምን ይዤ ነው ወደ ክለቡ የመጣሁት፡
ከክለቡ ጋር የተስማማሁት ዝም ብሎ ለመፈረም ሳይሆን ክለቡን ስኬታማ የማድረግ ህልምም ሰንቄ ነው፤ከክለቡ አመራሮችም ጋር ስናወራ ብዙ ተስፋ እንደተጣለብኝ ነው፤እንደ ግለሰብም እንደሀገርም ለእግር ኳሱ እድገት የአቅሜን ጡብ ለእግር ኳሱ ማበርከትም ሌላኛው ይዤው የምሄደው ጉዳይ ነው፡፡ –

ሀትሪክ:- የባህር ዳር ደጋፊዎች (የጣና ሞገዶች) የተለየ በሆነው የድጋፍ አሰጣጣቸው ይታወቃሉ፤ለእነሱስ ከወዲሁ ምን ትላቸዋለህ?

አህመድ :- የባህር ዳር ደጋፊዎች በጣም የተለዩና ምርጥ ደጋፊዎች መሆናቸው በተቃራኒ በገጥምናቸው ጊዜ አይቻቸዋለሁ፤ በቅርቡ ደግሞ የድጋፉ አሰጣጣቸውን፣ስሜታቸውን፣ለክለቡ ውጤት ያላቸውን ትልቅ ሚና በቪዲዮ ደጋግሜ አይቼ ተገርሜያለሁ፤እውነት ለመናገር ቡድኑ የእንደዚህ አይነት ደጋፊ ባለቤት በመሆኑም ለውጤቱ ትልቅ ኃይል ይኖረዋል፤የባህር ዳር ህዝብ እግር ኳስ ወዳድ መሆኑንም ለብ/ቡድን ዝግጅት እዛ በነበርንበት ጊዜ በተግባር አይቻለሁ፤ወጥተው ድጋፍ ሲሰጡ የምታየው በስሜት ነው…በእነሱ ፊትም እንዳትሸነፍ አድርገው እንደሚደግፉም በተግባር አይቻለሁ፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ደጋፊዎችን መቀላቀልም ከፍተኛ ደስታን ፈጥሮልኛል፤በቀጣይም በውጤት የታጀበ ጥሩ የደስታ ጊዜ ከአላህ ጋር ይኖረናል ነው የምላቸው፡፡

📸©natanim pictures

ሀትሪክ፡-…የባህር ዳር ከነማን ማልያ ለብሰህ በተቃራኒ ኢት.ቡናን መግጠም ምን መልክ እንደሚኖረው ለስከንድም ቢሆን ያሰብክበት አጋጣሚ አለ?

አህመድ፡- የሚገርምህ አሁን ከአንተ ጋር ከመደወላችን በፊት (ማክሰኞ ማለቱ ነው) በዚህ ጉዳይ ከቤተሰቦቼ፣ ከጓደኞቼ ከአቡበከር ናስር (አቡኪ) ጋር እያወራን ነበር…(ሣቅ)…እንዴት ነው ቡናን በተቃራኒ መግጠም…? እየተባባልን ነበር፤ሁላችንም ለጥያቄው መልስ ለማግኘት ከብዶን ንበር፡፡ እውነት ለመናገር ቡናን በዚህ መልኩ መግጠም በጣም ከባድ ነው፤ግን ምን ማድረግ ይቻላል? ግዴታም ነው…ስራም ነው? ኢት.ቡና የታወኩበት…ትልቅ ደረጃ የደረስኩበት ክለብ በመሆኑ ክብር ቢኖረኝም ለለበስኩት ማልያ ታማኝ መሆን ግንን አለብኝ፤በእኛ ሃይማኖት እምነት ከመሃላ በላይ ነው፤በዚህ ደረጃ መግጠም ቢከብድም የግድ ስለሆነ እወጣዋለሁ፡፡ ብዙ ተጨዋቾች ስኬታማ ያደረጋቸውን ማልያ ይወዱታል፤በተቃራኒ ለመግጠም ሲጨነቁ ከአቅም በላይ ለመጫወት ሲሞክሩ ይታያል፤ግን አንድ እውነት አለ…ለከፈለህ…ማልያውን ለለበሰከው ክለብና ደጋፊ ታማኝ መሆን፤ይሄን መተግበር እግር ኳሳዊ ብቻ ሣይሆን ሃይማኖታዊም እንደሆነ ማስመር እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- …ወደ ባህር ዳር ላደረከው ዝውውር ስንት ተከፈለህ ብልህ መልስ አገኛለሁ…?

አህመድ ፡- …አንድ.. ሁለት ብዬ ቆጥሬ ብነግርህ አይጠቅምህም…ከዚህ ይልቅ እንደው በደፊናው ኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ ክፍያ የሚከፈላቸውን ያህል አሪፍ ክፍያ ነው የተፈፀመልኝ ብልህ ይቀለኛል፡፡

ሀትሪክ፡… የመጨረሻ የምትለው ካለ የሚል አሰልቺ ጥያቄ አንስቼ ከምንለያይ…አንተን ለዚህ ስላበቁህ ቤተሰቦችህ ምን ትላለህ የሚል ጥያቄ አቅርቤ በምስጋና ብንለያይስ?

አህመድ ፡- …በጣም ደስ ይለኛል…ነፍሱን ይማረውና አባቴ በህይወት የለም፤ ቤተሰቦቼ እናቴን ጨምሮ የኢት.ቡና ደጋፊ ናቸው፤በተለይ እናቴ ለቡና ያላት ፍቅር ፍፁም የተለየ ነው…አሁን እንኳን ከቡና ውጪ ለማንም እንዳልፈርም እናቴ ያደረገችው ትግል ቀላል የሚባል አይደለም፤በዚህ አጋጣሚ እናቴን እንግዳወርቅ አሊን በጣም እወድሻለሁ…ጤናሽ ይብዛልኝ…ኑሪልኝ…ላደረግሽልኝ ነገር ሁሉ ምስጋናዬን የበዛ ነው ማለት እፈልጋለሁ፡፡ አባቴ በህይወት እያለ ብዙ ቅርበት ስለነበረን የጓደኛ ያህል ስለምንቀራረብ በሞት ስንነጠቅ በጣም ተቸግሬ ነበር፤ በዚህ ችግር ወቅት የአባቴ ምትክ ሆኖ በተጨዋችነቴ እንድቀጥል በጣም የረዳኝን ታላቅ ወንድሜን ነቢል ረሻድን ከልብ አመሰግናለሁ…በጣም ነው የምወድህ…አንተ ስለሆንክ ነው ጠንክሬ ለዚህ የደረስኩትና ውለታህ አለብኝ…ሁሌም ስወድህ ሳከብርህ እኖራለሁ፤እህቴ አይዳ ረሺድም የአንቺ መልካም ስራና ውለታስ እንዴት ይረሣል?ስለምታስቢልኝ ለእኔ ስለምትጨነቂልኝ…ስለምታደርጊልኝ ነገር ሁሉ አመሰግናለሁ፤ከእነሱ በተጨማሪ የጀርባ አጥንት ያህል ሆነሽ ሁሌም ሙሉጌታ አንቺን አለማመስገን ውለታሽን የመካድ ያህል ነው፤ከእኔ ጋር ብዙ ውጣ ውረድ ያሳለፍሽ ነሽና አንቺንም አመሰግናለሁ፡፡ ቡናን በመልቀቄ እንደተከፋሽብኝ አውቃለሁ፤ግን የህይወት ጉዳይ ነውና ተረጅኝ እላለሁ፤በአጠቃላይ ሁሉንም መዘርዘር ባልችልም ቤተሰቦቼን ከጎኔ የሆናችሁትን ሁሉ በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡


የዕለቱ መልዕክት
አህመድ ረሽድ (ሼሪላ) ባህር ዳር ከተማ
ስለ አባይ ግድብ


የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት ተሞልቶ በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል፤አላህ ይሄን ስላሳየኝ አመሰግናለሁ፤ባለፈው እሁድ 10፡00 ሰዓት የመጀመሪያው ዙር ሙሌትን አስመልክቶ ህዝቡ ደስታውን ሲገልፅ አዲስ አበባን በክላክስ በጥሩንባ ሲበጠብጡ ከዋሉት ውስጥ እኔና ባለቤቴ እንገኛለን፤አባይ ለእኔ ከውሃም በላይ ነው ትርጉሙ፤አባይ ከእኔ አልፎ የልጅ ልጄ ንብረት ነው፡፡ አባይ የነገ ህልውናችን፣የማንነታችን አሻራ ነው፡፡አባይን የሚያክል ትልቅ ሀገራዊ ጉዳይ ይዘን ያላለቀ የቤት ሥራ እየለብን መረባረብ ሲገባን በዝር፣በሃይማኖትና በጎሣ ተከፋፍለን ሀገራዊ ግዴታችንንና ትልቁን ነገር እየረሣን ነው፡፡ ሀይማኖታዊ ነገር አደረከው ካልልከኝ በስተቀር በእስልምና ነብያችን እንዳሉት “ሁላችሁም የአደም ልጆች አንድ ናችሁ፤የምትለያዩት በስነ-ምግባራችሁ…በምትሠሩት መልካም ነገር እንጂ አንዳችሁም ከአንዳችሁም ዘር የተለያየችሁ አይደላችሁም፤አንዳችሁም ከአንዳችሁ በምንም ታክል አትበልጡም፤አላህን በመፍራትና በጥሩ ስነ ምግባር እንጂ ብለዋል፡፡ ነብያችን ዘረኝነትን ቃላት አጥተውለት “ጥምብ” ነው ያሉት… ዘረኘነት ከምንም በላይ የሚያስጠላ ነገር ነው…በዘር ከመከፋፈል አንድ ሆነን አባይን ለብርሃን እናብቃ በአባይ ከምንም በላይ በአንድነታችን እንተሳሰር፤ኦሮሞ፣ትግሬ፣አማራ እያልን ከመከፋፈል ወደ ፈጣሪ አልቅሰን አንድ እንሁን፤ለልጅ ልጆቻችን ትልቅ ቅርስ እንተውላቸው፤ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይባርክ ማለት ነው የምፈልገው፡፡


ስለ ኮሮና ቫይረስ
ረስተነው ችላ ብለነው ግድ የለሽ ሆነን እንጂ ኢትዮጵያዊያን አደጋ ውስጥ ነን፤ በፍጥነት ወደ መጀመሪያው ጥንቃቄ ካልተመለስን በራችን ላይ የቆመ ህይወት ነጠቂ አደጋ አለ፤ግዴለሽነታችን ሲበዛ የበሽታው ስርጭትም፣የሚያዘው ሰው ቁጥርም ሞቱም በዚያው መጠንበዝቷል፡፡ዛሬ ቤታችን ውስጥ ደርሶ ሀዘኑን ባንቀምሰውም የማናውቀው ሰው ቢሞትም ዞሮ ዞሮ የአደም ልጆች አንድ እስከሆኑ ድረስ የገዛ ወንድማችንን፣እህታችንን፣ቤተሰቦችንን እያጣን ነውና ያለነው ሁላችንም እንጠንቀቅ፤የአንድም ሰው ህይወት ቢሆን ማጣት የለብንም፤አቅም አለን ኃያልም ነን…ሁሉንም ማድረግ እንችላለን…የሚሳነን የለም…የሚሉትን ያስከፈለቸውን ዋጋ አይተናል…እኛ ደሃዎችን አቅም የሌለንን ምን ሊያደረግን እንደሚችል ማሰብ ከባድ አይደለም፤የሰው ህይወት እንደ ቅጠል እንዲረግፉ መፍቀድ የለብንም ምክንያቱም ይሄ የማርዮ ጌም ጨዋታ አይደለም፤ማርዮ ጌም ስትጫወት ሰባት ስምንት ነፍስ አለው፤አንዱ ቢሞት በሌላኛው ነፍስ ልትጫወት ትችላለህ፤የእኛ ግን ምትክ የሌለውና ውዱን ነብሳችንን የሚነጥቅ ስለሆነ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ እህቶቼ፣ወንድሞቼ፣እናቶች፣አባቶች ሁላችንም ይሄንን አስከፊ ጊዜ አብረን እንለፍ፣እንረዳዳ ለሌላቸው ደርሰን ይሄን መጥፎ ጊዜ እንሻገረው፤ወደ አምላካችን አብዝተን እንፀልይ ነው የምለው፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.