የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና እና የአንዚ ማካቻካላ ተጫዋች የነበረው ጋቶች ፓኖም ለኢትዮጵያ ቡና ጋር ዳግመኛ የማገልገሉ ነገር ተጨናግፏል።
የኢትዮጵያ ቡና የፌስቡክ ገፅ እንዳስነበበው “ድርድሩ ሊሳካ ያልቻለው ጋቶች ለክለቡ ባቀረበው የተጋነነ የክፍያ ጥያቄ አማካኝነት ነው።ጋቶች በየወሩ የተጣራ 250.000ብር የጡረታ ወይም የስራ ግብርን ሲጨምር 37800 ብር በድምሩ ለስድስት ወራት 1.5 ሚሊዮን ብር ጠይቋል።” በማለት ጠቅሶ ” የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብም ካለው አቅም አንጻር ለጋቶች ፓኖም በወር ታክስን ጨምሮ ለአንድ አመት 130,000 ብር እንዲሁም ለሁለት አመት በወር 150,000 ብር ለመክፈል እና ጋቶች የውጭ እድል ባገኘ ጊዜ ክለቡ በዝውውር ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም በመተውና እና ከተጨዋቹ የሚያገኛቸው ግልጋሎቶች ለጋቶች ክብር ሲባል ለመተው ሀሳብ ቢያቀርብም ተጨዋቹ በሀሳቡ ባለመስማማትና ከሌሎች ክለቦች የተሻለ ክፍያ እንዳገኘ በመግለጡና ለቡና ለመጫወት ባለመፍቀዱ ድርድሩ እንዲቋረጥ ተስማምተዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የተገደደው ክለቡ ካለው የመክፈል አቅም ብቻም ሳይሆን ለአንድ ተጨዋች የተጋነነ ክፍያ ለመፈጸም የማይፈቅደው ብዙም የብቃትና የችሎታ ልዩነቶች በሌለበት ሊግ ውስጥ የቡድኑን ሌሎች ተጨዋቾች የመጫወት ፍላጎት ላይ ተጽእኖ ላለማድረስ፣ በቡድን ብቃት ላይ የተለየ ተፅዕኖና በቀጣይ የተጨዋቾች ዝውውር ላይ የተለየ ጫና ላለመፍጠር ካለው አላማ አንጻርም ጭምር ነው።” በማለት አክሏል።
ጋቶች በኢትዮጵያ ቡና ከወጣትነቱ ጀምሮ የተጫወተ ሲሆን ወደ ሩሲያው ክለብ አንዚ ማካቻካላ እስከተዛወረበት እለት ድረስ ለቀድሞ ቡድኑ ከፍተኛ አገልግሎት ሲሰጥ ነበር። በአንዚ በቋሚነት በቂ የመሰለፍ እድል ያላገኘው ጋቶች ከክለቡ ጋር ያለውን ውል በስምምነት አፍርሶ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ዘመን ጀምሮ መጫወት የጀመረ ሲሆን አሁንም እያገለገለ ይገኛል። ከሩሲያ ከተመለሰ በኋላም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ልምምድ እየሰራ እንደሆነ ይታወቃል።
የጋቶች ቀጣይ ማረፊያ የት ይሆናል ለሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ እየተነሳ ሲሆን ከሀገር ውስጥ ወላይታ ድቻ እና መቐለ ከተማ ግንባር ቀደም ፈላጊዎቹ ሆነው ቀርበዋል። ከሀገር ውጪ ደግሞ ስማቸው ያለተጠቀሰ ክለቦች የልጁ ፈላጊ ሆነው ብቅ ብለዋል። የጋቶች ቀጣይ ማረፊያ በቅርቡ የሚታወቅ ይሆናል።
ተጨዋቾች ከሚጫወቱበት ቡድን ጋር ላለመቀጠል ሲፈልጉ የሚያቀርቡት ክፍያ የተጋነነ መሆን አዲስ ነገር አይደለም ፡፡ የክለብ አመራሮች ፣ እግር ኳሱን በበላይነት የሚመራው የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፤ የክለቡ ባለቤት የሆኑት የመንግስትና የልማት ድርጅቶችና የሚዲያ አካላት በተጨዋቾችና አሰልጣኞች አመላመል እና ዝውውር ጉዳይ ላይ የሚጠየቀውን ክፍያ በተመለከተ ቀርበው ካልተነጋገሩ ከአቅም አኳያ በርካታ ክለቦች የመፍረስ ዕጣ እንደሚያጋጥማቸው ጥርጥር የለውም ፡፡ በተግባርም የታየ ጉዳይ ነው ፡፡ በአለምና በአፍሪካ የእግር ኳስ ደረጃችን ምን ላይ ነው ያለው ? በሀገራችን እየተካሄዱ ያሉት ውድድሮች ተመልካችን የሚያዝናኑና ለወደፊት ለሚገነባው ብሄራዊ ብድን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚመጥን ነው ? ድርጅቶች ከገቢ አኳያ ተጠቃሚ ናቸው ወይ ? የሚለው መታሰብ ያለበት ጉዳይ ይመስለኛል ፡፡