“ኢትዮጵያዊያኖች በፕሮፌሽናል ደረጃ ወደ ውጪ ወጥቶ መጫወትን ይፈራሉ፤ያን ችግር ሊያስወግዱት ይገባል” ዑመድ ኡኩሪ

“በግብፅ ሊግ ለመጫወት በራስ የመተማመን ብቃትና ልበ

ሙሉ መሆን ያስፈልጋል”

“ኢትዮጵያዊያኖች በፕሮፌሽናል ደረጃ ወደ ውጪ ወጥቶ
መጫወትን ይፈራሉ፤ያን ችግር ሊያስወግዱት ይገባል”

ዑመድ ኡኩሪ

በግብጽ ሊግ ለተለያዩ ክለቦች በመጫወት ያሳለፈው ዑመድ ኡኩሪ በአሁን ሰዓት በጉዳት ላይ ሲገኝ ከአንድ ወር በኋላም ወደ ክለቡ ልምምድ እንደሚመለስ ይናገራል፤ ዑመድ በሀገር ውስጥ በነበረበት ሰዓት
ለመከላከያ፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት የቻለ ሲሆን 2006 ላይ ከክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከማንሳት ባሻገር የኮከብ ተጨዋችነት እና የኮከብ
ግብ አግቢነትንም ሽልማቶች በጣምራ ሊያገኝም ችሏል፤ ከተጨዋቹ ጋር ጋዜጠኛመሸሻ ወልዴ ዘ ቢግ ኢንተርቪው በሚለው አምድ ላይ በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ቆይታ አድርጓልና ተከታተሉት፡፡

ሀትሪክ፡- የግብፅ ሊግ ሲጀመር የኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራህ ነበር፤ በኋላ ላይ ጉዳት አጋጠመህና ከሜዳ ራቅህ፤ በአሁን ሰዓት በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለህ?
ዑመድ፡- ልክ ነህ፤ ሊጉ ሲጀመር በሰባት ጨዋታዎች አራት ግቦችን አስቆጥሬ የኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራው ነበር፤ ወዲያው ግን በእግሬ ላይ የደረሰብኝ ጉዳት ከጃንዋሪ ወር አንስቶ ከሜዳ እንድርቅ አድርጎኛልና
ለክለቤ ግልጋሎቴን እየሰጠሁት አይደለም፤ ከእዚህ በመነሳት በአሁን ሰዓት እኔ የምገኝበት ሁኔታ በህክምና ዶክተሬ አማካኝነት ወደ ጨዋታ በፍጥነት ለመመለስ እንድችል በቂ የሆነ የጥንካሬ እና ሌሎች የአካል ብቃት
ልምምዶችን በእሱ አማካኝነት በመስራት ነው፤ ፈጣሪ ይመስገን አሁን ላይ በጤንነቴ በኩል ከፍተኛ መሻሻልን እያሳየው ነው፤ ከአንድ ወር በኋላም ወደ መደበኛው የክለቤ ልምምድ እመለሳለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከሜዳ ከእግር ኳሱ የራቅ ከው በጉዳት ከዛም ባሻገር ባትጎዳ እንኳን ኮቪድ 19ም ወደ ግብፅ የገባበት ሁኔታ ስላለ ከኳሱ መራቅህ አይቀርም ነበር፤ ያን ስሜት በምን መልኩ ነው የምትገልፀው?
ዑመድ፡- ያለ ኳስ ከሜዳ መራቅ በጣም ከባድ እና ፈታኝ ነገር ነው፤ አይደለም ለእኛ ስራችን ለሆነው የእግር ኳስ ተጨዋቾች ይቅርና ለሌላውም ኳስን ለሚወድ ህዝብና ማህበረሰብ ሁኔታዎቹ አስቸጋሪዎች
ናቸው፡፡


ሀትሪክ፡- ከኳስ ለእዚህን ያህል ጊዜ የራቅክበትን ወቅትስ ታስታውሳለህ?
ዑመድ፡- በፍፁም፤ ለወራቶች ያህል የራቅኩት አሁን ነው፤ በጉዳትም አሁን ላይ ደግሞ ጉዳት ላይ ባለሁበት ሰዓትም በኮቪድ 19 የተነሳ ሌሎችም ተጨዋቾች ከኳሱ የራቁበት ሁኔታም ስላለ ያ ለሁላችንም ነገሮችን
ከባድ አድርጎብናል፤ ከእዚህ ቀደም አይደለም ለወራቶች ለአንድ ወር እንኳን ከኳስ አልራቅኩም፤ የራቅኩትም ለአንድ እና ለሁለት ሳምንት ብቻ ነው፤ የአሁኑ ለየት ይላል፡፡
ሀትሪክ፡- በግብፅ የኮቪድ 19 ሁኔታ ምን ይመስላል… የአንተስ ጥንቃቄ?
ዑመድ፡- በግብፅ ስላለው የኮቪድ 19 ሁኔታ በቤት ውስጥ ስለምውል ብዙ ነገሮችን ለማለት ባልችልም ከማዳምጣቸው ነገሮች በመነሳት ግን ህዝቡ ጥንቃቄው ላይ ጉድለት ያለበት ይመስለኛል፤ ህብረተሰቡ
በየመንገዱ ላይ አብሮና ተሰባስቦ ነው የሚጓዘው፤ ወረርሽኙ ወደ ሀገሪቷ የገባም አይመስልም፡ ጥንቃቄ በጣም ይጎላል፤ ለእዚያም ነው በቫይረሱ የተያዙ የሰዎች ቁጥርንም በሀገሪቷ ከጊዜ ወደጊዜም እየጨመረ
እንዲመጣ ያደረገው፡፡ ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ እኔ ስለማደርገው ጥንቃቄ ደግሞ ጊዜዬን በቤቴ ውስጥ በማሳለፍ ላይ ነው ያለሁት፤ በጉዳት ላይ ስለሆንኩም ዶክተሬ ወደ እኔ ይመጣና በእሱ አማካኝነትም
የሚያስፈልጉኝን የስፖርት እንቅስቃሴዎችንም እየሰራው ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በእዚህን ጊዜና ሰዓት ምን ናፍቆሃል?
ዑመድ፡- ኳስ ነዋ! ሌላ ምን ሊናፍቀኝ ይችላል፤ ምክንያቱም የምሰራው እና ሌት ከእሌትም የማዘወትረው እሱን ስለሆነ ወደ ኳሱ መመለስ በጣም ናፍቆኛል፡፡
ሀትሪክ፡ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ወደ ግብፅ በመሄድ መጫወት ከጀመርክ ስንት አመታትን አስቆጠርክ?
ዑመድ፡- አሁን ላይ ስድስት አመታት ሆኖኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ለእዚህን ያህል ጊዜ ስትቆይ ስንት ግቦችን አስቆጠርክ?
ዑመድ፡- እስከ 25 ግቦች ይደርሳሉ፤ እነዚህንም ግቦች ያስቆጠርኩት ለሁለት እና ለሶስት ዓመታት ያህል ለተጫወትኩባቸው ክለቦች ሙሉ ሲዝኑን ሳልጨርስም ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በግብፅ ሊግ ቆይታህ የአንተ የምንጊዜውም ምርጡ ተጨዋች ማን ነው?

ዑመድ፡- በጣም ምርጡ እና የማደንቀው ተጨዋች የፒራሚዱን የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች አብደላን ነው፤ ይሄ የብሔራዊ ቡድኑና በፊት ላይ ደግሞ ለአልአህሊ ክለብ ይጫወት የነበረውን ተጨዋች ላደንቀው
የቻልኩትም ከዓመት ዓመት የማይዋዥቅ እና ምርጡን አቋሙን ስላሳየም ጭምር ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በግብፅ ሊግ ቆይታህ ምርጡ የጨዋታ ጊዜዬ ብለህ የምታስበውስ የቱን ነው?
ዑመድ፡- በጣም ምርጡ ጊዜዬ ለ…. ክለብ በምጫወትበት ሰዓት ለግብፅ ሊግ የኮከብ ግብ አግቢነት የተፎካከርኩበትን እና የኮከብ ግብ አግቢነቱንም በ3ኛ ደረጃ ላይ ሆኜ ያጠናቀቅኩበትን ወቅት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የኮከብ ግብ አግቢነቱን በስንት ግብ ልዩነት ነበር ያጣከው?
ዑመድ፡- በአራት ግቦች፤ እኔ 11 ግቦችን ሳስቆጥር የኮከብ ግብ አግቢው ተሸላሚው ደግሞ 15 ግቦችን ነበር ያስቆጠረው፡፡
ሀትሪክ፡- የኮከብ ግብ አግቢነቱን በምን ያጣኸው ይመስልሃል? በማጣትህስ ተከፍተሃል?
ዑመድ፡- በግብፅ ሊግ የኮከብ ግብ አግቢነቱን ክብር ላጣ ችያለው ብዬ የማስበው ያኔ እኔ ግቦችን የማስቆጥረው በጨዋታ ላይ የሚገኙ ግቦችን ብቻ ስለማስቆጥር እና ከእኔ ፊት ያሉት ሁለቱ ተጨዋቾች ደግሞ
ኮከብ ግብ አግቢውን ጨምሮ ክለባቸው የሚያገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትንም ጭምሮ መትተው ስለሚያገቡ ነው፤ በዛ የበለጡኝም ይመስለኛል፤ የኮከብ ግብ አግቢነቱን ክብር በወቅቱ ሳጣም እኔን ፈፅሞ
አልከፋኝም፤ ምክንያቱም የግብፅ ሊግ በጣም ጠንካራ ፉክክር የሚደረግበት እና እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ሀገራት መጥተህ ደግሞ በእዚህ ደረጃ ላይ ለመፎካከር ስትችል አንተ ያለህ ብቃት ምን ያህል ጥሩና ከዚህ የበለጠም
መስራት ከቻልክ ከፍተኛ ደረጃም ላይ መድረስ እንደሚቻልም ያሳየኝ ጊዜ ስለነበር ያን ዓመት ከምርጥ የጨዋታ ዘመኖቼ መካከል በቀዳሚነት ደጋግሜ የማነሳው ነው፡፡
ሀትሪክ፡- እንደ መላው ዓለም ሁሉ የግብፅ ሊግም በኮቪድ 19 ምክንያት ተቋርጧል፤… አሁን ላይ ከውድድሩ መጀመር ጋር በተያያዘ ምን አዲስ ነገር አለ?
ዑመድ፡- እስካሁን በቂ የሆነ መረጃው የለኝም፤ ግን እርግጠኛ ባልሆንም አዝማሚያው ውድድሩ እንደሚጀመር ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በግብፅ ሀገር የእስካሁን ቆይታህ ምግቦችን አብስለህ መብላት ትችላለህ? ወይንስ ደግሞ አስቤዛህን እየገዛ ነው የምትመገበው?
ዑመድ፡- የእውነት ለመናገር ምግብ አብስሎ መብላቱ ላይ የለሁበትም፤ ስለዚህም ወደ ሱፐር ማርኬት በመሄድ ነው የሚያስፈልጉኝን ምግቦች የምገዛው እና አሁን ላይ ደግሞ እንደዚህ ያለ ክፉ ወረርሽኝ ሲመጣ
ዲሊቨሪ ስላለ ስልክ በመደወል የምፈልጋቸው ምግቦች እቤቴ ድረስ የሚመጡልኝ፡፡
ሀትሪክ፡- በግብፅ ቆይታህ አሁን ላይ ለብቻህ ነው የምትኖረው?
ዑመድ፡- ለጊዜው አዎን፡፡
ሀትሪክ፡- የብቸኝነት ስሜት እየተሰማህ ነዋ!?
ዑመድ፡- የብቸኝነቱን ስሜት በሚመለከት ምን ታደርገዋለህ፤ ምንም ነገርን ማድረግ ስለማትችል ከፈጣሪ እርዳታ ጋር የሚመጣውን ነገር ትጠብቃለህ፡፡
ሀትሪክ፡- እንደ እግር ኳስ ተጨዋችነትህ በግብፅ ሀገር የኑሮ ቆይታህ ምን የተለየ ነገር ገጥሞሃል ?
ዑመድ፡- እዛ ያለው ነገር ከኢትዮጵያ በጣም ይለያል፤ ኳስ ተጨዋች ስትሆን እነሱ ጋር ኳሱ ስራህ እና ስራህም ብቻ ነው፤ ስለፕሮፌሽኑም በደንብ እንድታውቅም ያደርጉሃል፤ ያን በጣም ስለተረዳሁት ስራዬን
እንዳከብረውና አጥብቄው እንድይዘውም አድርጎኛል፡፡ ከዛ ውጪ በኳሱ ህይወትህንም በምን እና እንዴትም ባለ ሁኔታ መምራት እንዳለብህም የምታውቅበትም የተለየም ነገር አለና ያ ለየት ይላል፡፡


ሀትሪክ፡- በግብፅ ቆይታህ በጣም የወደድከው ነገር?
ዑመድ፡- ለእግር ኳስ ያላቸው ፍቅር፤ በተለይም ደግሞ ለሀገራቸው የሊግ ውድድር ቅድሚያን የሚሰጡበት እና ስለ ሊጋቸውም ጥንካሬ እንደ አውሮፓ ስታንዳርድ ሁሌም ሌት ተቀን ሚዲያዎቻቸውም ሆነ የስፖርት
ቤተሰቡ የሚያወሩበት ሁኔታ አለና ያን በጣም ወድጄላቸዋለው፡፡ እዛ ሁሌም ስለ ግብፅ እያንዳንዱ ተጨዋች እና ክለቦች ነው በተደጋጋሚ ጊዜ የሚወራው በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ እከሌ የተባለው ተጨዋች ምን አደረገ?
ምንስ ሰራ ብለው ቁጭ ብለውም ነው ቀኑን ሙሉ ስለኳሱ የሚያወሩት፤ ከዛ ውጪም በእያንዳንዱ ቻናልም የሀገሪቱ የሊግ ውድድር ጨዋታዎች በቀጥታ የሚተላልፍበትም ሁኔታ ስላለ እዛ በየካፌው እና ሆቴሎችም
በመሰብሰብ ግጥሚያውን የሚመለከቱበት ሁኔታም አለ፤ በሜዳ ላይ በምታሳያቸው ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴዎችም ለችሎታህ ክብር እና አድናቆትንም ሰጥተው አብረውህ ፎቶግራፍ የሚነሱበት ሁኔታም ስላለ ኳስን
ምንያህል እንደ ሚወዱትና መቼም ቢሆን ከአህምሮአቸውም እንደማያስወጡትም ትረዳለህና ያ እነሱን እንድትወዳቸውም ያደርጉሃል፡፡
ሀትሪክ፡- ወደ ግብፅ ሊግ አንድ ተጨዋች መጥቶ ለመጫወት ምን ምን ነገሮችን ማሟላት ያስፈልገዋል?
ዑመድ፡- በመጀመሪያ ዓላማ ሊኖርህ ይገባል፤ በእዚህ ውስጥም ኳሱ ስራህ መሆኑን አምነህ ተቀብለህ ልታከብረው እና በጣምም ዲሲፕሊን ልትሆንም ይገባል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በራስ የመተማመን ችሎታህም
የተለየና ልበ ሙሉም መሆን ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ለማሟላት ከቻልክ እና የሚገጥምህንም ቻሌንጅ የምትቋቋም ከሆነ በምትፈልገው ደረጃ ላይ እዚህ መጥተህ መጫወት ትችላለህ፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ተጨዋቾች በእዚህ ደረጃ ላይ ሆነው በመምጣት ታዲያ ለምን በብዛት መጥተው አይጫወቱም?
ዑመድ፡- የኢትዮጵያ ተጨዋቾችን ወደ ውጪ ሀገር ወጥተው ያለ መጫወት ችግርን እኔ ወደ ግብፅ ሀገር ባመራሁበት ወቅት በሚገባ አይቼው የሚጎድለንን ነገር አውቄዋለው፤ “ኢትዮጵያኖች ወደ ውጪ ሀገር
ወጥቶ መጫወትን እንፈራለን፤ ለመጫወት ይህን የፍራቻ ባህሪይን ማስወገድ እና ሊያጋጥሙን የሚችሉ ችግሮችንም ስለመቋቋምም ማሰብ አለብን፡፡
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ በነበርክበት ሰዓት ከክለብህ ቅ/ጊዮርጊስ ጋር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ለማንሣት ችለሃል፤ ያኔ የነበረህን የደስታ ስሜት ታስታውሰዋለህ?
ዑመድ፡- በጣም! ያ ዋንጫ ለእኔ የመጀመሪያዬም የሊጉ ዋንጫ ነበር፤ ገና ከመከላከያም መጥቼ በገባሁበት ዓመት ላይ ድሉን የተቀዳጀሁበት ወቅት ስለነበር ያ የደስታ ስሜት መቼም ቢሆን ከአህምሮዬ ውስጥም
የሚጠፋ አልነበረምና በጊዜው ተሰምቶኝ የማያውቅ አይነት የደስታ ስሜትም ነው በውስጤ ሊፈጠርብኝ የቻለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር በጊዜው የሊጉን ዋንጫ ከማንሳት ባሻገር በኮከብ ተጨዋችነትም በኮከብ ግብ አግቢነትም በመመረጥ የጣምራ ሽልማትንም አግኝተሃል፤ ያ የደስታ ስሜት አሁንም አብሮህ ነው ያለው?
ዑመድ፡- በጣም እንጂ ስሜቱን እንዴት ብዬም እንደምገልፅልህ አላውቅም ለእኔ ልዩ ጊዜም ነበር፤ ከክለቤ ጋር ሻምፒዮና ከመሆን አንስቶ ወቅቱ የድርብ ድል ባለቤትና በኮከብነቱም ተሸላሚ የሆንኩበትም ስለነበር
ልዩ ስሜትን በውስጤ ፈጥሮብኛል፤ የደስታ ስሜቱ አሁንም ከውስጤመ አልጠፋም፡፡


ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ ምርጡ ጊዜዬ የምትለው የቱን ነው?
ዑመድ፡- በመከላከያ በቅ/ጊዮርጊስ እና ወደ ግብፅ ሊግም መጥቼ በተጫወትኩባቸው እያንዳንዱ ጊዜያቶች በራሴ ላይ የተመለከትኳቸው ጥሩ ጥሩ ነገሮች ስላሉና በችሎታዬም ላይ የማይዋዥቅ አቋሜን
ስላሳየሁባቸው እንደዚሁም ደግሞ በኳሱም ስለተደሰትኩባቸው ሁሉም ለእኔ ምርጥ የጨዋታ ጊዜያቶቼ ናቸው፤ ስለዚህ አንዱን ከአንዱ ማስበለጥን ፈፅሞ አልፈልግም፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ዘመንህ ምርጡ ጨዋታዬ የምትለውስ?
ዑመድ፡- የቱን ጠርቼልህ የቱን እንደምተወው ባለውቀውም በመከላከያ ክለብ ውስጥ በነበርኩበት ሰአት አዲስ ማልያ መጥቶልንና ቡናዎች ደግሞ ያኔ እነ ኢብራሂም ሁሴንን ቢኒያም ሀይሌ /ዋሴን/ ዕድሉ ደረጄንና
ግሩም ስዩምን የመሳሰሉትን ተጨዋቾች በያዘበት እና ጥሩም እግር ኳስን በሚጫወትበት ከዛ ውጪም በአጨዋወታቸውም ተፅዕኖን በሚፈጥሩበት ሰዓት ከእነሱ ጋር እኔና መድሀኔ ባስቆጠርናቸው ግቦች 2ለ2
የተለያየንበትን እና የእግር ኳስ ተመልካቹንም ህዝብ ቁጭ ብድግ ያደረግንበት ጨዋታ ለእኔ መቼም ቢሆን የሚረሳኝ አይደለምና ያን ግጥሚያ በምርጥነቱ በቀዳሚነት ደረጃ ላይ ነው የማስቀምጠው፡፡ ከእሱ ቀጥዬ ሌላ
ምርጥ ጨዋታዬ የምለው አሁንም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ስንጫወት ሀትሪክ የሰራሁበትን ጨዋታ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ከአጠገብህ ጋር ሆኖ ሲጫወት በጣም የተመቸህ እና የተስማማ ተጨዋች…?
ዑመድ፡- መድሀኔ ታደሰ ነዋ! ከእሱ ጋር በመከላከያ ክለብ ውስጥ አብረን የፊት አጥቂ ስፍራውን እየመራን ተጫውተናል፤ ምርጥ እና የአማረም ጥምረት ነበረን”
ሀትሪክ፡- ይሄ ምርጥ የሆነውን ጥምረትህን አጠር ባለ ቃላት ስትገልፀው …?
ዑመድ፡- ዋ! መድሀኔ ልዩ ተጨዋች ነው፤ ያኔ በመከላከያ ክለብ ውስጥ አብረን በተጫወትንበት ሰዓት በእንቅስቃሴው በኩል በጣም ከመግባባታችን ባሻገር አንዳችን ለአንዳችን ኳስንም ያለ ስስት የምንሰጣጥበት
ጊዜና ወደተቃራኒ ሜዳ የግብ ክልልም ጋር በፍጥነት ሁለታችንም የምንደርስበትና እሱ ደግሞ በሚፈጥረው ክፍተትም ጎሎ ችን የማስቆጥርበት ጊዜም ስለነበር የእኔና የመድሀኔ ጥምረት ለየት ያለ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- ለአንተ ምርጦቹ አማካዮች?
ዑመድ፡- ፋሲካ አስፋው እና ዳዊት እስጢፋኖስ፤ ከሁለቱ ጋር በመከላከያ ክለብ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ ለመጫወት ችያለውና እነሱ ናቸው በአህምሮዬ የሚመጡት፤ ሁለቱ ኳስን ሲያገኙህ በፈለግክበት ሰዓት
አቋቋምህን አይተው አመቻችተው ይሰጡሃል፤ ልዩ ክህሎት ያላቸው ተጨዋቾችም ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመንህ መቼም የማትረሳው እና የሚቆጭህ ጨዋታ?
ዑመድ፡- ከግብጹ ዛማሌክ ጋር ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስጫወት ያደረግኩትን ነው፤ በጊዜው ቡድናችን ምርጥ አቋም ላይ ነበር፤ እነሱን 2-1 መርተንም ወደ ምድብ ድልድሉ ልንገባ ከጫፍ በደረስንበት ሰዓት የአቻነት ግብ
አስቆጥረውብን የወደቅንበት ጨዋታ መቼም አይረሳኝም፤ ያን ዕለት ምሽትን ያለ እንቅልፍም ነበር ያሳለፍኩት ለአንድ ሳምንት ያህልም በሀዘን ስብሰለሰልም ነበር፤ አሁንም ድረስ ያ ጨዋታ በሀዘኔታነቱ ከአህምሮዬም
ፈጽሞ አይወጣም፡፡

ሀትሪክ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ አብሮህ ባለመጫወቱ የሚቆጭህ ተጨዋች አለ?
ዑመድ፡- እኔንጃ! አለ ብዬ ግን አላስብም፤ ምክንያቱም ብዙዎቹን በተጫወትኩባቸው ክለቦች እና በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ስላገኘዋቸው አሁን ላይ የሉም፡፡
ሀትሪክ፡- ከጋምቤላ ክልል ወጥተህ፤ የእግር ኳስንም እዛው ጀምረህ ዛሬ ላይ በባህር ማዶ ክለቦች ውስጥ ወደ ግብፅ በማምራት እስከ ፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ ላይ ደርሰሃል፤ ከዛ ክልል ወጥተህ ለሌሎች ተጨዋቾች
ተምሳሌትህ ስለመሆንህ ምን ትላለህ ?
ዑመድ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ማንኛውም ተጨዋች ልጅ ሳለህ ኳሱን ለስሜት እንጂ ስራዬ ነው ብሎ የሚያስበው ነገር ባለመኖሩ እንደዚሁም ቤተሰቦችም ከኳሱ ይልቅ በትምህርትህ ላይ እንድታተኩር
ስለሚፈልጉ የአሁን ሰዓት ላይ እኔ ከዛ ኳስን ለስሜት ብዬ መጫወት ጀምሬ በእዚህ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ ላይ ለመድረስ በመቻሌ በጣም ነው የሚገርመኝ፤ በእግር ኳሱ እኔ ከወጣሁበት የጋምቤላ ክልልም
ለሌሎች ተጨዋቾች መውጣት የጥርጊያውንም በር እና መንገድን ስለከፈትኩም በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- በዓለም እግር ኳስ የአንተ የምንጊዜውም ምርጥ እና ጀግናው ተጨዋች ማን ነው?
ዑመድ፡- ዲዲየር ድሮግባ በዋናነት ሆኖ ሲቀጥል ደግሞ ክርስቲያኖ ሮናልዶም ሌላው ምርጡ ተጨዋች ነው፤ሁለቱ በጣም ነው የሚመቹኝ አጨዋወታቸውም ይስበኛል፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን ከእዚህ በኋላ ለምን ያህል አመት እጫወታለው ብለህ ታስባለህ?
ዑመድ፡- ዋናው ነገር ጤንነት ይኑረኝ እንጂ እግዚብሔር አምላኬ እስከፈቀደልኝና አቅሙም እስካለኝ ጊዜ ድረስ ኳስን እጫወታለው፡፡
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታህ ጠንካራ ሹቶችን ወደ ግብ ትመታ ነበር፤ ከዛ በመነሳት ወደ ግብፅ ካመራህ በኋላ ያ ሹት እና የምንሰማውም የሹት ድምፅ አሁን ላይ መስማት ናፈቀን፤
መስማት ካቆምንም ቆየን የሚሉ አሉ፤ በእዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ…?
ዑመድ፡- በጣም ከሳቀ በኋላ እኔንጃ ይሄንን ያህል ነው በሰው አህምሮ ውስጥ የተቀመጥኩት ማለት ነው፤ በእዚህ መልኩ እንደምታሰብ የእውነት አላውቅም ነበር፤ ስለዚህ በሁኔታው ዙሪያ ምን ብዬ እንደምገልጽ
አላውቅም፡፡ ያም ሆኖ ግን ኳስን ወደ ግብ አክርሮ መምታት ሁልጊዜም ጥሩ ነው ለአንድ የእግር ኳስ ተጨዋች አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች ውስጥም አንዱ ይሄ ነው፡፡ ምክንያቱም ወደ ጎል ኳሷን ካልመታካት ጎሏ አትገባም፤
አንድአንዴ የራስህ የሆነ ኳሊቲ እንዳለህ ሁሉ እንደዚህ ያለ ወደ ግብ የመምታት ብቃቶችም ሊኖርህ ይገባልና እነዚህ ደግሞ በተደጋጋሚ ጊዜ ልምምዶች ዳብረው የሚመጡም ናቸውና በእዛ ላይ ጠንክረህ ልትሰራባቸው
ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ግን….
ሀትሪክ፡- ላቋርጥህና… ምን ያለበለዚያ?
ዑመድ፡- ወደ ባህር ማዶ ሄደህ የፕሮፌሽናል ተጨዋች በምትሆንበት ሰዓት ኳስን አሲስት የሚያደርግልህ ተጨዋቾችን ልታጣ ትችላለህ፡፡ ይሄን ችግር የምታውቀው ያኔ ነው፤ ስለዚህም እያንዳንዱ ተጨዋች ወደ ውጪ
ወጥቶ ይሄን ቢያየው ጥሩ ነው ብዬ አስባለው፡፡ ያኔም ጥረ ግረህ ብላ የሚባል ነገር አለና የኳስ አሲስት የማይደረግልህ ሁኔታ ሲያጋጥምህ እንዴት አድርጌ ነው ለቡድኔ ጎል የማገባው በሚል ወደ ግብ አክርሮ ኳሶችን
የመምታት ጥቅሙን ያኔ ትረዳዋለህና ይሄን ልናዳብረው የሚገባን ነገር ነው፡፡
ሀትሪክ፡- “ዑመድ ኡኩሪ፤ መረብ ወጣሪ” ይሄ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደጋጋሚ ጊዜ የሚሰማህ የአድናቆት ድምፅ ነበር፤ ከዛም ውጪ ከግብፅ ወደ አዲስ አበባ በምትመጣበት እና ወደ ስታዲየምም ጨዋታ ለማየት
በምትገባበት ሰዓት ይስተጋባ ነበር፤ የቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ይሄን አንስተው ሲዘምሩልህ እና ሲያስታውሱ በውስጥህ ምን አይነት ስሜት ነው የሚሰማህ? አሁንስ በእዛ ሁኔታ መጠራቱ አይናፍቅህም?

ዑመድ፡- ዋው! በጣም ይናፍቃል እንጂ፤ እንዴትስ አይናፍቀኝ፤ ህብረ ዝማሬው ሁሌም በአህምሮዬ ውስጥም ነው ያለው፤ እሱን ስሰማም ምን ያህል በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ እንዳለውም ስለምረዳ
ያን በ2005 እና በ2006 የነበርኩበትን ቡድንም እንዳስታውስ ያደርገኛል፤ በተለይ የ2006ቱ ቡድን የሚገርምም ነበርና እነዚህ ደጋፊዎቻችን ሁሌም ስሜን እያነሱ ሲያሞግሱኝ ስሰማ ለእነሱ ያለኝ አድናቆት ይጨምራል፤
በእዚሁ አጋጣሚም ላመሰግናቸውም እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- የመከላከያ ተጨዋች በነበርክ እና ገናም ከጋምቤላ በመጣህበት ሰዓት አንተን ቃለ ምልልስ ለመስራት ሲፈለግ ዑመድ እኮ አማርኛ አይችልም በሚል ኢንተርቪው እንዳትሰራ የተደረገበት ጊዜ ነበር… ይህን
ታስታውሳለህ…?
ዑመድ፡- /ትንሽ ሳቅ ካለ በኋላ/ ይህን ከአንተ ነው ገና ዛሬ የሰማሁት፤ ሲጀመር ያኔ አብዛኞቹ ጓደኞቼ የጋምቤላ ክልል ተወላጆች ቢሆኑም እኔ ግን አማርኛን ጭምር እየተናገርኩም ነበር ያደግኩት፤ በወቅቱ
ኢንተርቪው ብዙ ላለማድረጌ ዓይናፋርነቱ ስላለ እና ስለምፈራ እንጂ አማርኛ ሳልችል ቀርቼ አይደለም፡፡ በእዛም የተነሣ ነው የክለባችን አብዛኛዎቹ ሰዎች ኢንተርቪው እንዳልሰጥ ከመፈለግ አኳያ ያን ሊሉ የሚችሉት፡፡
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጨዋችነት ቆይታህ እነማን ነበሩ ጥርስህን ሳያስከድኑ አንተን ያዘናኑ የነበሩት…. የሚያበሽቁህስ?
ዑመድ፡- ብዙ ናቸው፤ ከአብዛኛዎቹም ጋር በተለይ በቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ አብረን ተጫውተናል፤ በተለይ ደግሞ ጀማል ጣሰው የብሔራዊ ቡድን ላይ በነበርንበት ሰዓት በጣም ቀልደኛ እና ሁሉ ነገርህንም
የሚከታተል ስለሆነ እሱ አስቂኙ ተጨዋች ነበር፤ ሌላው አዳነ ግርማም የዋዛ አይደለም፤ ያኔ ማንን ጠርቼ ማንን እንደምተው አላውቅም፤ በኃይሉ አሰፋ /ቱሳ/ ያሬድ ዝናቡ፣ አሉላ ግርማ፣ ሳላሀዲን ሰይድን የመሳሰሉት
ሁሉ የሚያዝናኑኝ እና እኔን ለማብሸቅምም የሚሞክሩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ እነሱ ሁሉም እኔን የሚያበሽቁበት ነገር አያጡም፡፡
ሀትሪክ፡- በአማርኛ ንግግርህ አይደለም አይደል?
ዑመድ፡- በእዛ እንኳን አልታማም፤ ቅድምም ገልጬልህ ነበር፤ በብሔራዊ ቡድንና በክለብ ስንገናኝ እየተፎጋገርንም ነበር ጊዜውን የምናሳልፈው፤ አቦ ያኔ እንዴት ደስ የሚል ጊዜ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- እንደ ስፖርተኛነትህ የምትመርጠው የተለየ አመጋገብ አለ?
ዑመድ፡- በፍፁም ማንም ሰው የራሱ የሆነ አመጋገብ እና የሚወደው ምግብ ሊኖር ይችላል፤ እኔ ግን ምግብን አልመርጥም፤ ያገኘሁትንና የሚስማማኝን ሁሉ ነው የምበላው፡፡
ሀትሪክ፡- በባህር ማዶ እና በሀገር ውስጥ አሰልጣኞች ሰር መሰልጠን ስላለው ልዩነት ምን የምትለው ነገር አለ?
ዑመድ፡- አብዛኛውን የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔን በውጪዎቹ አሰልጣኞች ስለሰለጠንኩ ልዩነታቸውን መግለፅ ትንሽ ከበድ ይላል፤ በጊዜው በብሔራዊ ቡድን እና በክለብ ደረጃ እያለው በኤፊ ኦኔራ፣ በቶም
ሴይንትፌት፣ በባሬቶ፣ በማይክል ክሩነር እና በማርቲን ኖይ በምሰለጥንበት ሰዓት ምን አልባት ከእኛዎቹ አሰልጣኞች ጋር ልዩነት ሊሆን ይችላል ብዬ የማስበው እነሱ ታክቲክ ላይ ስለሚያተኩሩ እና ዲሲፒሊን እንድትሆንም
ስለሚያደርጉህ ነው፡፡


ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ሳለህ የአንተ ምርጡ እና በቀዳሚነት ስፍራ ላይ የምታስቀምጠው አሰልጣኝ ማንን ነው?
ዑመድ፡- በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ ዛሬ ላይ ለደረሰኩበት የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ እኔን ከማሰልጠን አልፎ በትንቢትም ደረጃ የተናገረው ነገር ስላለ ለእኔ የምንጊዜም ቁጥር አንዱ እና የማደንቀው ምርጡ
አሰልጣኝ አስራት ሀይሌ ነው፤ አስራት ማለት ለእኔ አባቴም ጭምር ማለት ነው፤ ከእሱ ባሻገር ደግሞ ፈጣሪ ነፍሱን ይማረው አሰልጣኝ ስዩም አባተም ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የመረጠኝ ሁኔታም አለና
እሱን ጭምር ነው የማደንቀው፡፡
ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ስለ አንተ ምን አይነት ትንቢቱን ቢያስቀምጥ ነው ስሙን ከፍ አድርገህ ልትጠራው የቻልከው?
ዑመድ፡- በጊዜው እኔ የመከላከያ ተጨዋች ነበርኩ፤ እሱ ደግሞ አሰልጣኛችን፤ ያኔ ታዲያ ቡድናችን ወደ ሐረር ሄዶ በሐረር ቢራ ክለብ ሽንፈትን ባስተናገደበት ሰዓት ከጨዋታ በኋላ እና እዚህም መጥተን በቡድናችን
ዙሪያ በምንነጋገርበት ሰዓት የክለቡ በእድሜ በጣም ትንሹ ተጨዋች እኔ ትልልቆቹ ደግሞ እነ ፋሲል ተካልኝ እነ ሳሙኤል ደምሴ /ኩኩሻ/ ነበሩና አስራት ምን አላቸው መሰለህ፤ ከእዚህ ቡድን ተጨዋቾች መካከል
በዕድሜ ትንሹ ተጨዋች ዑመድ ነው፤ ገናም ልጅ ነው፤ ከአንድ እና ከሁለት አመት በኋላ ይሄን ልጅ የት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ታዩታላችሁ ነበር ያለው፤ አሰራት በጊዜው ግማሽ ሲዝን ላይ ቢለቅም እኔም አለሳፈርኩትም
ስራዬን በርትቼ እና ጠንክሬ ሠርቼ ከአንድ አመት በግማሽ ወር በኋላ በቡድኑ ውስጥ ጥሩ ተጨዋች እና ጎልቼም ወጥቼ ክለቤን ከመጥቀም ባሻገር እስከ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋችነት ደረጃ ከዛም አልፎ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ
ክለብ ውስጥም ገብቼ የኮከብ ተጨዋችነትንም የኮከብ ግብ አግቢነትም ሽልማቶች እንዳገኝና ወደ ግብፅም በመሄድ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ እንድጫወት የቻልኩበትም ሁኔታ ስላለ የእሱ ለእዚህ ደረጃ እንድደርስ
አስቀድሞ የሰጠው ትንበያ መቼም ቢሆን አይረሳኝምና በጣሙን ላመሰግነው እፈልጋለው፤ ሌላውንም አሰልጣኝ ስዩምንም ጨምሮ፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ….?
ዑመድ፡- በእግር ኳስ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ ቤተሰቦቼ ከአስተዳደግ አንስቶ ብዙ ነገሮችን አድርገውልኛል፤ ሌላው ብዙ ያሰለጠኑኝም አሰልጣኞች ይጠቀሳሉ እነሱንና ሁሌም ከእኔ ጎን በመሆን ሲደግፉኝ የነበሩትን
ደጋፊዎቼንና በተለይ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስን እና የመከላከያ ደጋፊዎችን ማመስገን እፈልጋለው፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website