መነሻ ገጽ ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣ “አሳዳጊዬን በሞት ተነጥቄ ከቀብር በቀጥታ ነው ለጨዋታው የመጣሁት” “ሽንፈቱ ሀዘኔን ድርብ አድርጎታል” አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ
ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣ

“አሳዳጊዬን በሞት ተነጥቄ ከቀብር በቀጥታ ነው ለጨዋታው የመጣሁት” “ሽንፈቱ ሀዘኔን ድርብ አድርጎታል” አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ

አጋራ
አጋራ

 

​ተደራራቢ ሀዘኖችን አስተናግዷል፤ 
በአንድ በኩለ የወላጅ እናቱ ያህል ያሳደጉትን 
አክስቱን በሞት ተነጥቋል፤ በሌላ በኩል 
ደግሞ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ሌላ አዲስ ታሪክ 
ለማፃፍ የነበረው ህልሙ ተጨናግፏል፡፡ እነዚህ 
ሁኔታዎች የወጣቱን አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን 
ልብ በሀዘን አድምተውታል፡፡ ነገሮች ሁሉ 
አክስቱን አፈር አልብሶ ለሌላ ወሳኝ ተልዕኮ 
ከቀብር መልስ ወደ ቤቱ ሳይሆን በቀጥታ ወደ 
አዲስ አበባ ለመጣው ፋሲል ተካልኝ በጣም 
ፈታኞች ነበሩ፡፡ “አክስቴን አፈር አልብሼ 
በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ ስቴዲየም ነው 
የመጣሁት፤ ምክንያቱም እንደ ቤተሰቤ አንድ 
አካል የማየው ቅ/ጊዮርጊስ የሰጠኝን አደራና 
ከባድ ሀላፊነት ለመወጣት ሀዘኔን ዋጥ አድርጌ 
ከመምጣት ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረኝም” 
በማለት በሀዘን በተሰበረ ስሜት የሚናገረው 
ፋሲል ተካልኝ በዕለቱ ቡድኑ ተሸንፎ ህልሙ 
በመጨናገፉ የተሰማውን ስሜት ሲገልፅ 
“ደጋፊያችን አንገቱን ደፍቶ በመሄዱ ከልቤ 
አዝኛለሁ፤ ምክንያቱም ለእነሱ የሚገባቸው 
ይሄ አይደለምና” ካለ በኋላ ሽንፈቱ በውስጡ 
ስለፈጠረው የህመም ስሜት ሲናገር “ከሁሉም 
በላይ በክለቡ ሽንፈት የሚሰማን የህመም 
ስሜት የሚጠዘጥዘንና የሚያመን እኛን ነው፡፡ 
ምክንያቱም እኛ የክለቡ አሰልጣኞች ብቻ ሳንሆን 
ደጋፊዎችም ማሊያውን ለብሰን ለስኬታማነት 
የደማንለት ክለብ በመሆኑ ከማንም በላይ 
ያመናል ብል አላጋነንኩም” በማለትም 
ይናገራል፡፡ የሀትሪክ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር 
ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ
በተደራራቢ ሀዘን 
ውስጡ የተጎዳው አሰልጣኝን ፋሲል ተካልኝን 
ከብዙ ማግባባት በኋላ በክለቡ ወቅታዊ ጉዳዮች 
ዙሪያ አነጋግሮታል፡፡

ፋሲል በዚህ ከባድ ችግር 
ወቅት ጋዜጣችንንና አንባቢዎቻችንን አክብሮ 
ለጥያቄዎቻችን ምላሽ ለመስጠት ስለተባበረን 
በአንባቢዎቻችን ስም እያመሰገንን በገጠመው 
መሪሪ ሀዘንም የተሰማንን ሀዘን እየገለፅን ከእነ 
ቤተሰቡ መፅናናትን እንመኝለታለን፡፡ 
ሀትሪክ፡- ፋሲል በጣም ይቅርታ ወደ ዋናው 
ጉዳያችን ከመግባታችን በፊት የግል ጉዳይህ የሆነ 
ነገር ልጠይቅህ?
ፋሲል፡- (እንደ መደንገጥ እያለ) ምንድነው 
እሱ ጠይቀኝ?
ሀትሪክ፡- ፋሲል ለቅዳሜው የማሜሎዲ 
ሰንዳውንስ ጨዋታ የመጣው በሞት የተነጠቀውን 
አክስቱን ቀብሮ ከቀብር ቦታ ወደ ሜዳ የመጣው 
በቀጥታ ነው የሚል ነገር ሰምቼ በጣም አዝኛለሁ፤ 
የሰማሁት ነገር እውነት ነው…?
ፋሲል፡- …(አንገቱን አቀርቅሮ በተሰባበረ 
የሃዘን ስሜት)… ማነው የነገረህ?… አዎን 
የእናቴን ያህል ያሳደገችኝና ለዚህ ያደረሰችኝን 
እንደ እናቴ የማያትን አክስቴን ቀብሬ ነው 
በቀጥታ ወደ ሜዳ የመጣሁት፡፡
ሀትሪክ፡- የእናት ያህል የምትቆጥራቸው 
አክስትን ቀብሮ ወደ ሜዳ መምጣትና ቡድኑ 
የሚያደርገውን ወሳኝ ጨዋታ መምራት ፈታኝና 
ከባድ አይሆንም?
ፋሲል፡- እጅግ በጣም ፈታኝ ነው፤ 
በአንድ በኩል ለአንተ እዚህ መድረስ የጎላ 
ድርሻ ያለውን ሰው በሞት ተነጥቀህ፣ 
ቀብረህ፣ በከባድ ሃዘን ውስጥ ሆነህ፤ በሌላ 
በኩል የክለቡ ደጋፊ ብቻ ሳይሆን እንደ ሃገር 
የሚጠበቅ ትልቅ ጨዋታን እንድትመራ 
ሃላፊነት መሸከም ሁለት ራሳቸውን የቻሉ 
ከባድ ፈተናዎች ቢሆኑም ሁለቱንም እንደ 
አመጣጣቸው መቀበልና ማስተናገድ አማራጭ 
የሚቀርብለት አይሆንም፡፡ ሃዘኑን መርሳት 
በጣም ከባድ እንደሆነ ብረዳም ይሄ ታላቅ 
ክለብና ደጋፊ የሰጠኝን አደራ መወጣት 
ስላለብኝ አክስቴን ቀብሬ ሃዘኔን ዋጥ አድርጌ 
አደራዬን ለመወጣት ከቀብር ቦታ በቀጥታ 
ወደ ሜዳ መጥቻለሁ፡፡ የገጠመኝ ሃዘን በቀላሉ 
የሚረሳ ባይሆንም ለጊዜውም ቢሆን ሃዘኔን 
ወደ ጎን በማድረግ ትኩረቴን ሁሉ ለጨዋታው 
ሰጥቼ ደጋፊውና ክለቡ የሰጠኝን ሃላፊነት 
በስኬት ባይደመደምም ለመወጣት የምችለውን 
አድርጌያለሁ፡፡ ምንም እንኳን ሃዘኑ የበረታ 
ቢሆንብኝም በዚህ ወሳኝና ቁርጥ ቀን አክስቴን 
በሞት ተነጥቄያለሁ ብዬ የቤተሰቤ ያህል 
ከማየው ክለቤ መሸሽን አልመረጥኩም፡፡ ሃዘኔን 
ረስቼ አብሬው መሆንን ነው የመረጥኩት፡፡
ሀትሪክ፡- የወላጅ እናት ያህል የምታያቸውን 
ያሳደጉህን አክስትህን በሞት ተነጥቀህ ቅዱስ 
ጊዮርጊስም አዲስ ታሪክ የሚያስፅፍበትን አጋጣሚ 
በሽንፈት በመደምደሙ ድርብ ሃዘን እንድታስተናግድ 
አድርጎሃል ብዬ አስባለሁ፤ ከዚህ በኋላ ሰኔ 24ትን 
ሁሌም በክፉነት ስታስታውሳት ነው የምትኖረው 
ማለት ነው?
ፋሲል፡- ቀኖችን በመውቀስና ለነገሮች 
ተጠያቂ በማድረግ የማምን ሰው አይደለሁም፤ 
እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ መልካምና መጥፎ 
ትዝታዎችን ይዘው እንደሚመጡ ስለማውቅ 
ቀኖችን አልወቅስም፤ አልወነጅልምም፡፡ 
ይሄ የህይወት አንዱ አካል ከመሆኑ አንፃር 
በተቻለኝ መጠን አምላክ ጥንካሬውን ሰጥቶኝ 
መጥፎውን እየጣልኩ ጥሩ ጥሩ ትዝታዎች 
ብቻ ከእኔ ጋር አብረው እንዲኖሩ ማድረግን 
ነው የማስቀድመው፡፡ በአጭሩ መጥፎ የሚባሉ 
አጋጣሚዎችን በመርሳት ነው የማምነው፤ 
ድርብ ሃዘን ያስተናገድኩት ሰኔ 24 መሆኑ 
ቀኑን ጠቅሰህ ያስታወስከኝም አንተው ነው፤ 
እንዳልከው ሃዘኑ ከባድ ቢሆንም ከመቀበልና 
ከመፅናናት ውጪ ቀኖችን ተጠያቂ አላደርግም፡
፡ 
ሀትሪክ፡- ለመንፈስ ጥንካሬህ አድናቆናቴን፤ 
ለደረሰብህ ሃዘን ደግሞ መፅናናትን በመመኘት 
ወደ ዋናው ጉዳያችን እንግባ እስቲ፤ በእግር ኳስ 
ህይወትህ እስከ ዛሬ ከገጠሙህ መራራ ሽንፈቶች 
ወይም ለታላቅ ታሪክ ተጠግተህ ካጣሃቸው ውጤቶች 
በመጥፎነቱ የምታነሳው የቅዳሜውን የማሜሎዲ 
ሰንዳውንስ ጨዋታ ነው ብል ከስህተት ትቆጥርብኝ 
ይሆን?

ፋሲል፡- አዎን ተሳስተሃል፤ የቅዳሜው 
የሰንዳውንስ ጨዋታ በተለይ በአሰልጣኝነት 
ህይወቴ በመጥፎነቱ የማነሳው ሁለተኛው 
ክፉ አጋጣሚዬ ነው ማለት ይቀለኛል፡፡ ከዚህ 
በፊትም ልክ እንደ አሁኑ በክለባችን ታሪክ 
ወደ አዲስ የውጤት ምዕራፍ የምንሸጋገርበትን 
አጋጣሚ ከዛማሌክ ጋር አቻ በመውጣት 
ያጣንበት ወቅት በቁጭት ነው የማስታውሰው 
፡፡ ይህ ጨዋታ በክለባችን ብቻ ሳይሆን 
በአገራችንም አዲስ ታሪክ የምንሰራበት ወርቃማ 
አጋጣሚ ነበር ማለት እችላለሁ፤ የፎርማት 
ለውጥ ሳይኖር ስምንት ውስጥ ለመግባት 
ደቂቃዎች ብቻ የቀሩበት ወቅት ነበር፡፡ ያን 
አጋጣሚ ሁሌም በቁጭት የማነሳው ነው፡፡ 
የአሁኑም ከዛማሌክ የማይተናነስ ቢሆንም ግን 
ሁለተኛው መጥፎ የእግር ኳስ አጋጣሚዬ ነው 
ለማለት እችላለሁ፡፡ 
ሀትሪክ፡- ከጨዋታው በፊት በውስጥህ የነበረው 
ስሜት ምንድነው? በሜዳችንና በደጋፊያችን ፊት 
እንደመጫወታችን ሰንዳውንስን አሸንፈን ታሪክ 
እንደምናፅፍ የእርግጠኛነት ስሜት በውስጥህ ነበር?
ፋሲል፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ቀደሞ 
እርግጠኛ መሆን የማይታሰብ ነው፤ ውስጤ 
ግን ከጨዋታው በፊት አንድ ነገር ደጋግሞ 
ይነግረኝ ነበር፡ ይሄንን ጨዋታ ካሸነፍን ብቻ 
ከህልማችን ጋር እንደምንገናኝ፤ የአዲስ ታሪክ 
ባለቤት ለመሆን ይበልጥ በእግር ኳሱ ከፍ 
ብለን ለመታየት ያገኘነውን እድል መጠቀምና 
ማሸነፍ ብቻ እንዳለብን ውስጤ ያወራኝ ነበር፡
፡ ይንን ለማሳካት የሚያስችሉ ስራዎችን 
ለመስራት ሞክረናል ግን አልሆነም፡፡
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ እግር 
ኳስ ለማፃፍ ተቃርቦ የነበረው ሌላው አዲስ ታሪክ 
በሜዳው በመሸነፉ ተስተጓጉሏል፤ ለዚህ ውጤት 
መጥፋት ተጠያቂው ማነው? አሰልጣኞቹ ፋሲል 
ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታ ወይስ ተጨዋቾቹ?
ፋሲል፡- ይሄንን መመለስ ይከብደኛል፤ 
ሽንፈቱ አይመለከተኝም የሚል ግትር ያለ 
ምላሽ የለኝም፤ ልልህ የምችለው ግን አንድ 
ነገር ብቻ ነው፡፡ ለውጤቱ መጥፋት እኔም 
ዘሪሁንም እንደ አሰልጣኝ የድርሻችንን 
እንወስዳለን የሚል መልስ ብቻ ነው ልሰጥህ 
የምፈልገው፤ ከዚህ ውጪ በሽንፈቱ ማግስት 
ማንንም መወንጀልም ሆነ ማንም ላይ ጣቴን 
መቀሰር አልፈልግም፡፡ 
ሀትሪክ፡- አንተ እንደዚህ ብትልም ደጋፊው 
ከጨዋታው በኋላ በተለይ አንተና ዘሪሁንን 
ተቃውሟል፤ የደጋፊው ተቃውሞ ለውጤት መበላሸቱ 
ዋነኛ ተጠያቂዎች እናንተ ናችሁ የሚል መልዕክት 
ያለው አይመስልህም?
ፋሲል፡- /ሳቀ/እግር ኳስ ውስጥ በተለይ 
በአሰልጣኝነት ለኖረ ሰው ይሄን አይነቱ 
ተቃውሞ አዲስና የመጀመሪያ አይደለም፤ ከዚህ 
በፊትም በተደጋጋሚ ለመናገር እንደሞከርኩት 
በእግር ኳስ እንደ ባህል ወይም ያልተፃፈ 
የሚመስል ህግ አለ፤ ስታሸንፍ ሙገሳዎች 
ከአሰልጣኝ ይልቅ ወደ ተጨዋቾች ይጎርፋሉ፤ 
ስትሸነፍ ደግሞ አሰልጣኝ ተወቃሽ ወይም 
ተጠያቂ የሚሆንበት ባህል ነው ያለው፤ ይህን 
አይነቱ አጋጣሚ በስልጠና ህይወታችን ውስጥ 
አብሮን የኖረና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ 

ሀትሪክ፡- …እሺ…የደጋፊውን የጠነከረ 
ተቃውሞ እንዴት ነው የምታስተናግደው…?
ፋሲል፡- …ነገርኩህ እኮ… ደጋፊ ሁሌም 
ልክ ነው፤ ስታሸንፍ ያመሰግንሃል አቅፎም 
ይስምሀል፤ ስትሸነፍ ደግሞ ይቃወምሃል 
ተጠያቂም ያደርግሃል፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር 
አብዛኛው የክለባችን ደጋፊ ይሄን የሚያደርገው 
ለክለቡ የተሻለ ውጤትን ከመመኘት፤ 
ሽንፈትንም አጥብቆ ከመጥላት የሚመጣ 
ነው፡፡ ከእግር ኳስ የወጣ አጀንዳ እስከሌለው 
ድረስ ለምን ተቃወመ በሚል ደጋፊው ሊወቀስ 
አይገባም፤ ምክንያቱም በእግር ኳስ ድጋፍና 
ተቃውሞ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች 
ናቸውና፡፡ እንደዚህ አይነት ነገሮች በዚህ ሙያ 
ውስጥ እስካለህ ድረስ ተፈራርቀው ይመጣሉ፤ 
ዛሬ ሙገሳ፤ ነገ ደግሞ የጠነከረ ተቃውሞ፤ 
ከዚያ ደግሞ ሙገሳ… ይሄን አምነህ መቀበል 
ነው፡፡ 
ሀትሪክ፡- በቅዳሜው የሰንዳውንስ ጨዋታ 
በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ፕሪንስ የሳተው 
ንፁህ ኳስ፤ በ44ኛው ደቂቃ ደግሞ ሳላህዲን ሰይድ 
የሳተው የፍፁም ቅጣት ምት የጨዋታውን ውጤት 
የቀየረ፤ ወደ ታሪክ የሚደረገውን ጉዞም የገታው 
አይመስልህም?
ፋሲል፡- አሁን ባለፈና በተዘጋ ነገር ላይ 
እንደዚህ ቢሆን…ወይም… ባይሆን እያልኩ 
ወደ ኋላ ተመልሼ መተሳሰብን አልመርጥም፡
፡ እውነት ነው በሁለቱ ተጨዋቾች በዋናነት 
ያገኘናቸውን ዕድሎች በአግባቡ ብንጠቀምበት 
ኖሮ ጨዋታው ሲጠናቀቅ እሁን ያገኘነውን 
ውጤት ልናገኝ የማንችልበት ሁኔታ ሊኖር 
ይችል ነበር ብሎ መገመትም ይቻላል፡
፡ አጋጣሚዎችን በአግባቡ ብንጠቀም ኖሮ 
በሁለተኛው 45 ደቂቃ የተሻለ የአሸናፈነት ስነ-
ልቦናን ይዘን ልንገባ እንደምንችል መመስከር 
እችላለሁ፡፡ ግን እንደ ቡድን አሰልጣኝነቴ 
በዕለቱ ውጤት ያጣነው ሁለቱ ተጨዋቾች 
ያገኟቸውን ዕድሎች ስላልተጠቀሙበት ነው 
የሚል ድምዳሜ የለኝም፡፡ እነዚያን የግብ 
ዕድሎችንም ካመከንን በኋላ ከ45 ደቂቃዎች 
በላይ ንፁህ የጨዋታ ጊዜያቶች በእጃችን ላይ 
ነበሩ፡፡ 
ሀትሪክ፡- የጥያቄዬ ዋና አላማ አጋጣሚው 
ጎድቶናል አልጎዳንም የሚለው ነው?
ፋሲል፡- ይሄ የሚያከራክር አይደለም፤ 
ኳሶቹ ወደ ግብነት ቢቀየሩ ኖሮ ጨዋታውን 
የመቀየር፤ የውጤት የሀይል ሚዛኑ ወደ 
እኛ እንዲያዘነብል ማድረጋቸው የማይካድ 
ነው፤አጋጣሚዎቹ ይህን ያህል ትልቅ አቅም 
ነበራቸው፡፡ የተሸነፍነው ግን በሁለቱ ኳሶች 
መሳት ብቻ ነው ብዬ ግን ድምዳሜ ላይ 
አልደርስም፡፡ 
ሀትሪክ፡- ሳላህዲን የክለቡ የመጀመሪያው 
የፍፁም ቅጣት ምት መቺ ነው ወይስ የውድድሩ 
ኮከብ ግብ አግቢነት መሪነቱን እንዲያጠናክር ነው 
ፔናሊቲ እንዲመታ የተደረገው?


ፋሲል፡- ምንም ጥያቄ የለውም በዕለቱ 
የመጀመሪያው የፍፁም ቅጣት መቺያችን 
የመጀመሪያው ምርጫችን ሳላህዲን ሰይድ 
ስለሆነ ነው የመታው፤ ቢያገባው ኖሮ ይሄን 
ጥያቄ ታነሳው ነበር? አታነሳውም…
ሀትሪክ፡- ይሄን ጥያቄ ያነሳሁልህ ስለሳተው 
ሳይሆን ከራሴ ግምትና በሃይሉ አሰፋ (ቱሳ) 
ለመምታት ፍላጎት አሳይቶ ስለነበር ከአንተ መልስ 
ጋር ስለተጋጨብኝ ነው?
ፋሲል፡- ምንም የሚጋጭ ነገር የለውም፤ 
ሳላህዲን የመጀመሪያው መቺያችንና 
ምርጫችን ነው፡፡ ለዚህም በቂ ምክንያቶችም 
አሉን አንደኛው ሳላህዲን ጎል አግቢያችን ነው፤ 
ሁለተኛው ሳላህዲን ያለው አቅም፣ ያለው 
ልምድ ይሄን ሃላፊነት በቅድሚያ ለመውሰድ 
ከበቂ በላይ ነው፡፡ በእነዚሁ መሰረታዊ 
ምክንያቶች ወደ ሜዳ ስንመጣ እሱን 
የመጀመሪያው መቺ አድርገን ነው የመጣነው፡፡ 

 
ሀትሪክ፡- በቅዳሜው ጨዋታ የአቀያየር 
ታክቲካል ስህተት ፈፅማችኋል በሚል የሚወቅሷችሁ 
በርካቶች ናቸው፤ በተለይ በሃይሉ አሰፋ (ቱሳ) 
መቀየሩ፣ያልታሰበው ፍሬዘር እንዲወጣ መደረጉና 
መሃል ላይ ያለው ክፍተት እየሰፋ በሄደበት ወቅት 
እንኳን ምንያህል ተሾመን ለመቀየር አለማሰባችሁ 
ታክቲካል ስህተት እንደፈፀማችሁ በመቁጠር ቅሬታ 
ለሚያቀርቡባችሁ ምን መልስ አለህ?
ፋሲል፡- ቡድኑን በቅርበት የምናውቀው፣ 
ለጨዋታዎች በቂ ዝጅት ያደረግነው እኛ ነን፤ 
በተለይ አንድ ቡድን ሲሸነፍ ሲያሸንፍ የማይነሱ 
በርካታ ነገሮች ይነሳሉ፡፡ እኛም በመሸነፋችን 
ሽንፈቱን ተከትሎ ብዙ አስተያቶች ሊሰነዘሩ 
ይችላሉ፡፡ በተለይ እከሌ ወጥቶ እከሌ መግባት 
ነበረበት እከሌን ለምን አልየቀራችሁትም? 
እከሌን ለምን አስገባችሁት? የሚሉ፤ ሁሉም 
ከራሱ ዕይታ በመነሳት ያመነበትን የተሰማውን 
አስተያየት መሰንዘርይችላል፤ ለምን ሰነዘረ ብሎ 
መውቀስ ግን አይቻልም፡፡ ሁሌም አሰልጣኝንና 
ደጋፊዎችን የማያስማማ ነገር ቢኖር 
የተጨዋች አቀያየር ነው፤ ይሄንን እናውቃለን፡
፡ በአቀያየርም ሆነ በአሰላለፉ የሁሉንም 
ተመልካች ስሜት ማርካት ደግሞ ሌላው ከባዱ 
ነገር ነው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ የተቀመጥነው 
የገባውን ተመልካች ፍላጎት ለማሟላት 
ብቻ አይደለም፤ በእያንዳንዱ የተጨዋች 
ቅያሪ ወይም አሰላለፍ ላይ አስተያየት 
ልሰጥህ አልችልም፤ ልልህ የምችለው ግን 
ቅዱስ ጊዮርጊስን ለአሸናፊነት ያበቃል ብለን 
ያመንበትን ልንሰራ ነው የተቀመጥነው፡፡ 
ተጨዋች ስናስገባም ሆነ ስናስወጣ የራሳችን 
የሆነ በቂ ምክንያቶች አሉን፡፡
ሀትሪክ፡- በስማቸው ብቻ የምትፈሯቸው፤ 
ሌሎች የተሻሉ ሆነው በስማቸው ብቻ የምታሰልፏቸው 
ተጨዋቾች አሉ በሚልም ትታማላችሁ፤ ሃሜቱን 
ትቀበለዋለህ?
ፋሲል፡- (እንደ መሳቅ እያለ) ባለፉት 
ጨዋታዎች የተጠቀምናቸውን አሰላለፎችም 
የቀየርናቸውን ወይም ያስገባናቸውም 
ተጨዋቾች መለስ ብሎ ማስታወስና ማየት 
በራሱ ለዚህ ጥያቄ በቂ መልስ ይሰጣል የሚል 
ዕምነት ነው ያለኝ፤ ወይም ያንን መለስ ብሎ 
አይቶ መፍረድ መልካም ነው፡፡ ለእኛ ትልቁ 
ምስል ክለባችንና የክለቡ ውጤት ብቻ ነው፤ 
በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ማንም የፈለገ ስምና 
ታሪክ ይኑረው ከክለቡ በላይ አይደለም፡
፡ ይሄን እኛም ተጨዋቾችም ደጋፊውም 
በደንብ እናውቀዋለን፡፡ ከክለቡ ውጤት ይልቅ 
ለተጨዋች ክብር ሰጥተን ወይም ፈርተን 
የምናደርገው አንዳችም ነገር የለም፤ ወደፊት 
አይኖርም፡፡ 
ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአሰልጣኝ ፋሲል 
ተካልኝና ዘሪሁን ሸንገታ አቅም በላይ ነው፤ ትከሻቸው 
የዚህን ታላቅ ክለብ ጫና ወይም ሃላፊነት መሸከም 
አይችልም ብለው በድፍረት ጥያቄ የሚያነሱ አሉ፤ 
መልስህ ምንድነው?
ፋሲል፡- ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ 
አመለካከት ወይም አተያይ አለው፤ የሁሉም 
ሰው አመለካከትም ለምን እንደ እኔ አልሆነም 
የሚል ቅሬታም የለኝም፡፡ ከፈለገ “ፋሲል 
አይችልም” ደስ ካለው ደግሞ “ፋሲል ይችላል” 
የማለት መብቱ የተጠበቀ ነው፤ ይሄ በራሱ 
ዕይታና ሚዛን የሚወሰን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ፍርጥ አድርገህ ንገረኝ እስቲ፤ 
በፋሲል ዕይታስ?
ፋሲል፡- በእኔ እይታ ፋሲል ይሄንን ጫና 
አይደለም ሌላም ቢመጣ የሚቋቋም ደንዳና 
ትከሻ አለው ብዬ ነው የማምነው፡፡ በዚህ 
ዙሪያ በግሌ ተጠራጥሬ አላውቅም፡፡ አሁን 
ስንሸነፍ ለምን እንደዚህ አይነት አስተያየት 
ሊሰነዘር እንደቻለም ለእኔ ግልፅ አይደለም፤ 
ቅዱስ ጊዮርጊስን በዚህን መሰሉ ሃላፊነት 
ስንመራ የሰንዳውንስ ጨዋታ የመጀመሪያችን 
አይደለም፡፡ ጊዮርገስ ቤት ሃላፊነት ተሰጥቶን 
መስራት የጀመርነው ዛሬ አይደለም፤ እናንተም 
ጋዜጠኞች ጊዮርጊስ ዘንድሮ ዋንጫ አያነሳም 
ባላችሁበት፤ ደጋፊውም በተስፋ መቁረጥ 
ውስጥ በወደቀበት ሰዓት እኮ ሃላፊነታችንን 
በብቃት ተወጥተን ክለቡን ከለመደው ክብርና 
ድል ጋር አገናኝተነዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ጊዮርጊስ 
ታላቅ ክለብ ቢሆንም ክለቡን የመሸከም 
አቅሙም ደንደን ያለ ትከሻውም አለን ብዬ 
ነው የማምነው፡፡
ሀትሪክ፡- ተቃውሞው ሲበዛና እየጠነከረ ሲመጣ 
ወደ ምሬት አትገባም? ከዚሁ ሁሉ ለምን ከሃላፊነቴ 
አልነሳም የሚል ሃሳብስ ብልጭ ብሎብህ አያውቅም?
ፋሲል፡- አንዳንዴ ምክንያታዊ ያልሆኑ 
ተቃውሞዎች፤ ለሁሉም ነገር አንተን ተጠያቂ 
የማድረግ ሁኔታ ሲመጣ ሰው ነኝና ስሜቴ 
ሊጎዳ እንደሚችል መሸሸግ አልፈልግም፡፡ ግን 
በጣም የሚገርምህ ነገር አንዳንድ ጊዜ ሰዎች 
እኔን ስለሚያስቡበት ነገር ብዙም ተጨንቄ 
አላውቅም፤ እኔ ሁሌም የምጨነቀው ገና 
ለገና ተቃውም ይደርስብኛል ብዬ ሳይሆን 
ስለምሰራው ስራ ብቻ ነው፡፡ በእያንዳንዱ 
እርምጃዬ ላይ ፍፁም ስላልሆንኩ ስህተቶችን 
ልሰራ እችላለሁ፤ እነዛን ስህተቶች ለማስተካከል 
ነው የምጨነቀው፡፡ ሰዎች በዚህ መልኩ 
ቢረዱኝ ነው ደስ የሚለኝም፡፡ 
ሀትሪክ፡- አንተ በምታስበው መልኩ የሚረዳህ 
ባታገኝስ?
ፋሲል፡- ምን ማድረግ እችላለሁ፤ ሁሉም 
ሰው እኩል ይረዳኛል ብዬ ጠብቄ ስለማላውቅ 
ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ የሚረዱኝ በጣም 
ብዙዎች እንዳሉ ሁሉ ያልተረዱኝ ደግሞ በጣም 
ጥቂቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ 
እኔና ዘሪሁን የምንሰራው ተመካክረን፤ ለክለቡ 
በሚጠቅም መልኩ አይተን ነው የምንወስነው፤ 
ከዚህ ውጪ ሰዎች በግላቸው ተነስተው 
ተጨባጩን ነገር ሳያዩ ፋሲል እንደዚህ ነው 
ወይም እንደዚያ ነው ቢሉ ለምን አሉ አልልም፤ 
ምክንያቱም መብታቸው ነውና፤ ዋናው ነገር 
እኔ በራሴ ላይ ያለኝን ዕምነት አለማጣቴ ነው፤ 
ይሄ ነው ወሳኙም ነገር፡፡
ሀትሪክ፡- ዋናው አሰልጣኝ ሆላንዳዊው ማርቲን 
ኖይ በዚህ ወሳኝ ወቅት አለመኖራቸው ቡድኑን 
ጎድቶታል የሚሉ አሉና እውነት የእሳቸው አለመኖር 
ጊዮርጊስን ጎድቶታል ማለት ይቻላል?
ፋሲል፡- ማርቲን ትልቅ አሰልጣኝ ነው፤ 
የከፍተኛ ልምድና እውቀት ባለቤትም ነው፡
፡ ከዚህ በመነሳት አብሮን ቢኖር ብዙ ሊረዳን 
እንደሚችል መካድ አያስፈልግም፤ ቢኖር በጣም 
ይጠቅመናል፡፡ ማርቲን ባይኖርም በቅዳሜው 
ጨዋታ ይዘን የገባነው ቡድን ከእሱ ጋር አብረን 
ያዘጋጀናቸውን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላው 
አዲስ ተዓምር እንዳልፈጠርን አውቃለሁ፡፡ 
አሰላለፋችንም አቀያየራችንም እሱ በነበረበት 
ጊዜ ስናደርግ ከነበረው ያን ያህል የተጋነነ 
ልዩነት ፈጥረናል ብዬ አላስብም፡፡ በአጭሩ እሱ 
ለዓመታት ሲሄድበት ከነበረው መንገድ ሙሉ 
በሙሉ ወጥተን የሰራነው ነገር እንደሌለ በዚህ 
መልኩ ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎች ራሳቸው 
ይጠፋቸዋል ብዬ አላስብም፡፡ አንተም ሆንክ 
ይሄንን ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎች ምናልባት 
በመጀመሪያዎቹ 45 ደቂቃዎች እነዛን ጎሎች 
አስቆጥረን ብናሸንፍ ኖሮ በእርግጠኝነት አሁን 
የምትጠይቀኝን ጥያቄ አትጠይቀኝም ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- በዘንድሮው የቶታል ካፍ ቻምፒዮንስ 
ሊግ ጠንካራውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ተመልክተናል 
ማለት ይቻላል?
ፋሲል፡- ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠቴ 
በፊት አንተ ራስህን አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ…
ሀትሪክ፡- …ጠይቀኝ… ይቻላል…?
ፋሲል፡- …የዘንድሮውን ውድድር… 
የምድብ ድልድል ስትሰማ… ቅዱስ ጊዮርጊስ 
በዚህ ደረጃ ይፎካከራል፤ ለሌላ አዲስ ታሪክ 
ይሮጣል ብለህ አስበህ ነበር? ይሄን አሁን 
የጠየቅኩህ ድልድሉ በወጣበት ጊዜ የጠየቅከኝ 
ጥያቄ እንደነበር ስለማስታውስ ነው፡፡ 
ጊዮርጊስን አሁን በሚገኝበት ደረጃ አስበኸው 
ነበር? መልስልኝ እስቲ…?
ሀትሪክ፡- …በእርግጥ በምድብ ድልድሉ 
ውስጥ የወቅቱ ሻምፒዮን ሰንዳውንስ ጠንካራዎቹ 
ኤስፔራንሶች እና ቪታዎች ስለነበሩ ምድቡ ያስፈራ 
ነበር፤ የሞት ምድብም የሚል ስያሜ የተሰጠውም 
ከዚህ በመነሳት በመሆኑ ዕውነት ለመናገር እኔም 
ሆንኩ ሌሎች ጊዮርጊስ በጣም እንደሚቸገር ነበር 
ግምታች…
ፋሲል፡- …አመሰግናለሁ፤ይሄን ነው …
ከአንተ..መስማት.የፈለኩት… ዛሬ ግን ቀደም 
ሲል የነበረው የአንተ አይነቱ ስሜት በጊዮርጊስ 
ጥንካሬና ውጤታማነት ተቀይሯል፡፡ ምድብ 
ድልድሉ ፈታኝ ነው፤ ጊዮርጊስ ዕድለኛ 
አይደለም፤ ጠንካራ ቡድኖች ናቸው የደረሱት፤ 
በጣም ይቸገራል በሚል ከጨዋታው በፊት 
ሲነገርለት የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን 
በሚያሳፍር መልኩ ሳይሆን በሚያኮራ ሁኔታ 
ምድብ ውስጥ እየተፎካከረ ለተጋጣሚዎቹ 
አስጨናቂ ሆኖ ነው የታየው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ 
ባሳየው ጥንካሬው መጀመሪያ ምድብ ውስጥ 
መግባታችን ብቻ እንደ ትልቅ ታሪክ ሲነሳ ከቆየ 
በኋላ በቡድኑ ተፎካካሪነት የብዙዎች ፍላጎትና 
ግምት አድጎ 8 ውስጥ እስከ መግባት መመኘት 
ጀመርን፤ ፍላጎታችንም አደገ፡፡ የወቅቱ የሀገሪቱ 
ሻምፒዮን፣ በአፍሪካ የገዘፈ ስም ካላቸው 
ሶስቱም ክለቦች ጋር ተደልድሎ ደረጃ መዳቢ 
አልሆነም፡፡ ከዚህ ይልቅ የውድድሩ አስገራሚ 
ቡድን እንደሆንን ነው የውጪ ሚዲያዎች 
ሳይቀሩ ሲዘግቡ የነበረው፡፡ እዚህ ይደርሳሉ 
ተብለን ባልተጠበቅንበት ሰዓት ፍላጎታችን 
ሩብ ፍፃሜ መግባት አለብን ወደሚል 
ተመነደገ፡፡ ስለ ሌላ አዲስ ታሪክ መታሰብ 
ነው የተጀመረው፡፡ ይሄ ሁሉ አዲስ ምኞት 
የመጣው ክለቡ ካሳየው ጥንካሬ ነው፤ ምንም 
እንኳን ፍላጎታችን አድጎ ሩብ ፍፃሜ በመግባት 
አዲስ ታሪክ የማፃፍ ዕድላችን ባይሳካም ቅዱስ 
ጊዮርጊስ በውድድሩ ጥንካሬውን አሳይቷል፤ 
ለመጪዎቹ አመታትም የውደድሩን 
ባህሪ ስንላመድ ለብዙዎች ፈተና ልንሆን 
እንደምንችል ያሳየንበት ስኬታማ ጉዞ ነበር 
ነው የምለው፡፡
ሀትሪክ፡- ሩብ ፍፃሜ ደረጃ ላይ ደርሳችሁ 
መቆማችሁስ ተስፋ ያስቆርጥሃል?
ፋሲል፡- ህይወት አሁንም ይቀጥላል፤ 
በዚህን መሰሉ ውድድር ስንሳተፍ ገና የመጀ 
መሪያችን ነው፡፡ ይሄ ዓመት እስከ መጨረሻው 
ድረስ ባይወስደንም እንኳን ከውድድሩ ባህሪ 
በመነሳት የተሻለ ለመጓዝ ምን መስራት 
እንዳለብን ተምረንበታል፡፡ ሁላችንም ብዙ 
ርቀት፣ ወደፊት ለመጓዝ የምንችለውን 
አድርገናል፤ በቀጣይም በዚህ ውድድር ላይ 
ስለምንካፈል የተሻለ ቡድን ይዘን በመምጣት 
ከፍ እያለ የመጣውን ህልማችንን እናሳካዋለን፡፡ 
ዛሬ ብንሸነፍም እንደ አዲስ ማለማችን ለተሻለ 
ነገር መዘጋጀታችን ይቀጥላል፤ የሚቆም ነገር 
የለም፡፡ 
ሀትሪክ፡- የደቡብ አፍሪካ ተጨዋቾችን፣ 
አሰልጣኞችን እና የቡድኑ አባላትን በአጠቃላይ 
ያስገረመ የድጋፍ አሰጣጥ ሲሰጥ ለነበረው ግን 
በውጤት ስላልተካሰው ደጋፊ ምን ትላለህ?


ፋሲል፡- ቅዳሜ ዕለት በስቴዲየም የነበረው 
ደጋፊ የሚገባው ሽንፈት አልነበረም፤ ከሶስት 
ነጥብ በላይ የሚሰጥ ነገር ቢኖር ከዚያ በላይም 
ይገባው ነበር፡፡ ከመነሻውም የእኛ ህልማችን 
አመቱን ሙሉ ልዩ ሆኖ አሁን ለምንገኝበት 
ደረጃ ላደረሰን ደጋፊ አዲስ ታሪክ ማጎናፀፍ 
ነበር፤ ግን አልሆነም፡፡ በዋናነት ማሸነፍን 
ስንፈልግና ስንመኝ የነበረው ለእነዚህ 
ለምናከብራቸው ደጋፊዎቻችን ነበር፡፡ ይሄ 
ሳይሆን ቀርቶ እንደለመዱት በድል ሳይሆን 
በሽንፈት ወደ ቤታቸው በመመላሳቸው ከልቤ 
አዝኛለሁ፤ በጣምም ተሰምቶኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ለአንባቢዎቻችንም ሆነ 
ለጋዜጣችን ክብር ሰጥተህ ከሃዘን ላይ ተነስተህ 
ለጥያቄዎቻችን ምላሽ ስለ ሰጠኸኝ እግዚአብሄር 
ያክብርልኝ፤ እግዘአብሄር ያፅናህ ብለን አመስግነን 
ከመለያየታችን በፊት ቀረ የምትለው ነገር ካለ?
ፋሲል፡- በእግር ኳስ ጨዋታ ማንም 
ፐርፌክት (ፍፁም) አይደለም፤ በዓለም ላይ አሉ 
የተባሉ አሰልጣኞች ላይ እንኳን ፍፁማዊነት 
የለም፡፡ በእርግጥ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚያክል 
ትልቅ ቡድን እየመራህ ውጤት ሲጠፋ 
ሰዎች አይቀየሙኝም ቅሬታ አያቀርቡብኝም 
ብሎ ማሰብ አይቻልም፤ ግን ደጋፊዎች 
ተቃውሟቸውን በስድብ ሳይሆን ስሜትን 
በማይጎዳ መልኩ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ሌላው 
ቢቀር ቢያንስ እስከ ዛሬ ለክለቡ ውጤታማነት 
ለሰራናቸው ስራዎች ተገቢውን ክብር ቢሰጡ 
ደስ ይለኛል፡፡ ለዚህ ክለብ ውጤታማነት እኔም 
ዘሪሁንም ያለንን ሁሉ ያለስስት ሰጥተናል፤ 
ወደፊትም እንሰጣለን፡፡ የምወደውን ሰው 
በሞት ተነጥቄ አፈር አልብሼ ሮጬ የመጣሁት 
ጊዮርጊስ የቤተሰቤ አካል በመሆኑ እንደሆነ 
ሰዎች ሊረዱልኝ ይገባል፡፡ አንዳንዶች ለመቀበል 
ቢቸግራቸውም በእያንዳንዱ የቅዱስ ጊዮርጊስ 
እርምጃ፣ መልካም ገፅታ ላይ ይነስም ይበዛ 
የእኔና የዘሪሁን አሻራ አለ፡፡ ሁሉንም የቅዱስ 
ጊዮርጊስ ጨዋውን ደጋፊ ባይወክሉም አንዳንድ 
ደጋፊዎች ቅሬታቸውን በስድብ መልኩ 
ባይገልፁ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ለተሰጠኝ 
ዕድል አመሰግናለሁ ቻዎ…! 
ሀትሪክ፡- …ፋሲል… ቆይ… ቆይ… አንድ 
የቀረ የመጨረሻ ጥያቄ አለኝ…
ፋሲል፡- …አይበቃም… ምን… ቀረህ… 
ደግሞ…?
ሀትሪክ፡- …ከዚህ በኋላ… ቅዱስ ጊዮርጊስ… 
ፔናሊቲ ቢያገኝ… እንደ አሰልጣኝ… ሳላህዲን 
ሰይድን …ታስመታዋለህ…?
ፋሲል፡- …(በጣም ሳቀ)… ዛሬ ላይ ሆኜ… 
የምወሰነው ነገር አይደለም፤ ግን አስረግጬ 
የምነግርህ ነገር ሳላህዲን ሰይድ… ወሳኝ 
ግብ አግቢ ተጨዋቻችንና የክለባችን እጅግ 
አስፈላጊው ተጨዋቻችን መሆኑን ብቻ ነው…፡
፡ …ጨረስኩ በል ቻው…
ሀትሪክ፡- ፋሲል…በል…ቻው…አመሰግናለሁ…

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣዜና እረፍትዜናዎች

የጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አጭር የህይወት ታሪክ

ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ከእናቱ ከወ/ሮ ጌጤ ገ/ስላሴ እና ከአባቱ ሀምሳ አለቃ ወልዴ...

ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣ

ሀትሪክ አሁንም ቀጠሮ ማክበር ስልጣኔ ነው በሚለው አቋሟ ጸንታለች

ቅዳሜ ጠዋት በቀጠሮ  ቀናችን  እርስዎ ጋዜጣዋን በእጅዎ ያስገቡ እንጂ አዳዲስና ያልተሰሙ መረጃዎችን...

ሀትሪክ ስፖርትጋዜጣዜናዎች

ሀትሪክ አሁንም ቀጠሮ ማክበር ስልጣኔ ነው በሚለው አቋሟ ጸንታለች

ቅዳሜ ጠዋት በቀጠሮ  ቀናችን  እርስዎ ጋዜጣዋን በእጅዎ ያስገቡ እንጂ አዳዲስና ያልተሰሙ መረጃዎችን...