በይስሀቅ በላይ(ከለንደን ኦሎምፒክ ስታዲየም)
የ10ሺ ሜትር የሪዮ ኦሎምፒክ አሸናፊና የርቀቱ የሪከርዱ ባለቤት፤የ2017 የ16ኛው የለንደን የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው አልማዝ አያና ዛሬ በተካሄደው የ5000ሜትር ፍፃሜ ለሀገርዋ ሶስተኛውን የብር ሜዳልያ አስገኘች።
አልማዝ አያና በሪዮ ኦሎምፒክ በተመሳሳይ ሁኔታ ቀድማት ወርቅ በነጠቀቻት ኬንያዊታ ኦንሳንዶ ኦብሪ ተቀድማ ነው።ኦብሪ 15 አትሌቶች የተሳተፉበትን የ5ሺ ሜትር ውድድር በአሸናፊነት ያጠናቀቀችው 13:34:86 በሆነ ሠዓት ሲሆን አልማዝ አያና በበኩሏ ውድድራን 14:40:35 በሆነ ሠዓት በመግባት አጠናቃለች።
ከውድድሩ በኃላ ሀትሪክን ጨምሮ ለተለያዩ ሚዲያዎች በጋራ የሰጠችው አልማዝ አያና ባገኘሁት ውጤት በጣም ተደስቻለሁ፤ባገኘሁት ውጤትም አልተከፋሁም በማለት የተናገረች ሲሆን ከዚህ የበለጠ ውጤት እንዳታመጣ ጉዳት እንቅፋት እንደሆነባትና ከእነ ጉዳትዋ መወዳደርዋን ገልፃለች።
ከአልማዝ አያና ጋር በዚህ ውድድር ላይ የተሳተፉት ሰንበሬ ተፈሪ 4ኛ፣ለተሰንበት ግደይ 11ኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።
አትሌት አልማዝ አያና ያስመዘገበችው የብር ሜዳሊያ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ቢሆንም አልማዝ ሪዮ ኦሎምፒክ ላይ በተመሳሳይ የአራራጥ ታክቲክ በተመሳሳይ አትሌት ወርቁን መነጠቅዋ ለ10ሺ ሜትር ብቻ የተፈጠረች አትሌት ናት እንዴ?የሚል ጥያቄን እንዲያነሱ እያስገደዳቸው ሲሆን ኬንያዎች የአልማዝ አያናን አራራጥ አጥንተው የሪዮውን ድል ሲደግሙ እኛ ባለንበት መጠበቃችን ወርቁን አሳጥቶናል በማለት በርካቶች ከወዲሁ ቅሬታቸውን በማቅረብ ላይ ናቸው።
ኢትዮጵያ በለንደን አለም ሻምፒዮና በ2 ወርቅና በሶስት የብር ሜዴሊያ ከቤጂንጉ የአለም ሻምፒዮና ባነሰ ውጤት ፍፃሜውን አግኝታል።

አስተያየት ይስጡ