“ኒጀርን ለማሸነፍ ለግጥሚያው ከፍተኛ ትኩረትን ሰጥተናል፤ ልምምዳችንን በብቃት እየሰራን ነው”ሱራፌል ዳኛቸው

“ኒጀርን ለማሸነፍ ለግጥሚያው ከፍተኛ ትኩረትን ሰጥተናል፤ ልምምዳችንን በብቃት እየሰራን ነው”


“እኛ የብሔራዊ ቡድናችን ተጨዋቾች ፕሮፌሽናል እንጂ እንደ መደበኛ የጤና ቡድን ተጨዋቾች ስላልሆንን በአሁን ሰዓት በአካል ብቃቱ በኩል ብቁ ነን”
ሱራፌል ዳኛቸው


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምዕራባዊቷ ሀገር ካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ወሳኞቹን የማጣሪያ ጨዋታዎቹን ባለፈው ዓመት ላይ ማድረግ የጀመረ ሲሆን ከኮቪድ ወረርሽኝ መግባት በኋላም ቀጣዮቹን ግጥሚያዎች ላለፉት በርካታ ወራቶች በእረፍት ላይ ከቆየ በኋላ በቅርቡ ልምምዱን በመጀመሩ ቀሪ ጨዋታዎቹን ከጥቅምት 30 ጀምሮ የሚያደርግ ይሆናል፡፡


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን /ዋልያዎቹ/ በእዚህ የማጣሪያ ጨዋታው በተደለደለበት ምድብ እስካሁን በማዳጋስካር በመሸነፍ እና ኮትዲቭዋርን በማሸነፍ ከኒጀር አቻው ጋር ያለበትን ሶስተኛ ጨዋታውን እየተጠባበቀ ሲገኝ በተደለደለበት ምድብም በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች በሚያስመዘግበው ውጤት ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድሉን ይወስናል፤ ዋልያዎቹ ከዛሬ 8 ዓመት በፊት ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፉበትን ታሪክ ዳግም ለማስፃፍ በአዲሱ አሰልጣኛቸው ውበቱ አባተ በመመራት ዝግጅታቸውን የጀመሩ ሲሆን ለእዚህ ቡድን የተመረጡ የተወሰኑ ተጨዋቾችም ከኮቪድ ጋር በተያያዘ በተደረገላቸው ምርመራ ቫይረሱ በውስጣቸው ሊገኝ በመቻሉ ከቡድኑ ስኳድ ለብቻቸው እንዲገለሉ ከተደረጉ በኋላ የአሁን ሰዓት ላይ እያገገሙ በመምጣታቸው እነሱም ለብቻ ልምምድ እየሰሩ መሆኑም እየተገለፀ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥቅምት 30 ከሜዳው ውጪ ከኒጀር አቻው እና በቀናቶች ልዩነት ደግሞ በሜዳው ስለሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ ቡድኑ እያደረገ ስለሚገኘው ዝግጅት፣ በጨዋታዎቹ ስለሚያስመዘግበው ውጤት፣ በካምፑ ውስጥ ስላለው የቡድኑ መንፈስ፣ ስለ ቡድኑ ተጨዋቾች ወቅታዊ አቋም እና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድኑን በኃላፊነት እየመራ ስላለበት ሁኔታ የቡድኑን ወሳኝ ተጨዋች ሱራፌል ዳኛቸውን ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አናግሮታል፤ ተጨዋቹም ምላሾቹን በሚከተለው መልኩ ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ሰጥቷል፤ መልካም ንባብ፡፡


ሀትሪክ፡- በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በቅርቡ ኒጀርን በቀናት ልዩነት ሁለት ጊዜ ትገጥማላችሁ፤ ለጨዋታው እያደረጋችሁት ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?


ሱራፌል፡- የእስካሁኑ ዝግጅታችን በጣም አሪፍ እና ጥሩ ነው፤ ካለፈው ሳምንት የመጀመሪያ ቀናት አንስቶም ነው በቀን ሁለት ጊዜ ቅድሚያ ከሜዳችን ውጪ ለምናደርገው ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በመቀጠል ደግሞ በሜዳችን ላይም ላለብን ጨዋታ በማሰብ በአካልም ሆነ በአህምሮ ደረጃ እየተለማመድን የሚገኘው፡፡


ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ለወራቶች ከእግር ኳሱ ርቃችሁ ከመምጣታችሁ አኳያ በቀጥታ ወደ ዝግጅቱ ስትገቡ ልምምዱን ለመስራት አልተቸገራችሁም ነበር?


ሱራፌል፡- አዎን፤ ለበርካታ ወራቶች አርፈን ከመምጣታችን እና ከሜዳም ከመራቃችን አኳያ ሲታይ ብዙም አልተቸገርንም፤ ወደ ልምምዱ ስንገባም አንድ አንድ ተጨዋቾች ብቻ በሚፈለገው መልኩ አይደለም የእኛ ሀገር ተጨዋቾች የውጪ ሀገር ተጨዋቾችም እንደሚያጋጥማቸው ሁሉ በተወሰነ መልኩ ፊት ያልነበሩ ቢሆንም በጊዜ ሂደት ግን እነዛም ተጨዋቾች ከቡድኑ አባላት ጋር በአካል ብቃቱ ረገድ ተስተካክለው በመምጣት የአሁን ሰዓት ላይ ሁላችንም የቡድኑ ተጨዋቾች በጋራ በከፍተኛ ሞራል ላይ ሆነን ለወሳኙ ጨዋታ የሚያዘጋጀንን ልምምድ በመስራት ላይ ነው የምንገኘው፡፡


ሀትሪክ፡- በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ከበርካታ ወራቶች በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾችን ልምምድ ላይ ስትመለከታቸው በተለየ መልኩ ያስተዋልከው ነገር አለ?


ሱራፌል፡- አዎን፤ ከሁሉ በላይ በቡድኑ ውስጥ ነባር የሆኑትም ሆነ በአዲስ መልክ የተመረጡት የዋልያዎቹ ተጨዋቾች ለእዚያን ያህል ወራቶች ከኳሱ ርቀው መጥተው ልምምዱን በብቃት ሲወጡ ማየቴ ነው እኔን ያስገረመኝ፤ ይህን ስመለከትም በዋናነት ያስዋልኩት ነገር እኔን ጨምሮ በቡድኑ ውስት የምንገኘው ተጨዋቾች እንደ አንድ ስፖርተኛ ምን ያህል በእረፍቱ ወቅት ልምምዳችንን እየሰራን እና ራሳችንንም እየጠበቅንም እንደነበርን ነው ለማወቅ የቻልኩትና በአጠቃላይ ሲታይ አሁን ላይ መቶ ፐርሰንት በሚባል ደረጃ ነው ልምምዳችን እየሰራን ያለነው፡፡


ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ወደ ዝግጅት በመጡበት እና ወደ ልምምድ ውስጥም በገቡበት ሰዓት የሰውነታቸው መጠን በጣም ጨምሮ እንደነበርና አንዳንዶቹም ዳሌ አውጥተውም ነበር ተብሎም ሲነገር ነበር፤ ይህን ስትሰማ ምን አልክ?


ሱራፌል፡- ይህን በተመለከተ ብዙ ነገሮችን ሰምቻለው፤ ግን እንደሚወራው አይደለም፤ ስለ አንድ ጉዳይ አንድ ሰው ሊያወራ የሚገባው በቦታው ተገኝቶ ሲመለከትና ሲያይ ነው፤ የብሔራዊ ቡድናችንን ተጨዋቾች በተመለከተ ሁሉም ተጨዋች ከእረፍት ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ ነው ወደ ዝግጅት የመጡት፤ በእዛን ወቅት አይደለንም እኛ የውጪ ሀገር ተጨዋቾች እንኳን ከእረፍት ሲመለሱ በአንዴ በፊት ውድድር ላይ በነበሩበት የፊትነስ ደረጃ ላይ የማይሆኑበት ሁኔታም አለና በምትሰራው ስራ ነው ብቁ አቋምህ ላይ የምትመጣውና እኛ ጋር ነገሮች በጣም ተጋነው ነው የቀረቡት፤ ስለዚህም የቡድናችንን ተጨዋቾች በአካል ብቃቱ በኩል ስላላቸው ፊትነስ ዝም ተብሎ ተጋኖ ሰውነታቸው ጨምሯል ከሚባል በቅርቡ ሁሉም ተመልክቶ ፍርድ ቢሰጥ ጥሩ ነው፤ እኛ ተጨዋቾች እኮ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች እንጂ እንደ መደበኛ የጤና ቡድን ተጨዋቾች አይደለንም፤ እግር ኳሱ ስራችንና በሰራነው መጠንም የሚያበላን ስራም ስለሆነ ለዛም ስንል ራሳችንን ጠብቀን በመምጣትም ነው የዋልያዎቹን የዝግጅት ወቅት ለመቀላቀል የቻልነውና በብሔራዊ ቡድኑ ዙሪያ ለተነሳው አስተያየት ይሄን ብቻ ነው ለማለት የምፈልገው፡፡


ሀትሪክ፡- የዋልያዎቹ የተወሰኑ ተጨዋቾች ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በተደረገላቸው ምርመራ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው እና ለብቻቸውም ልምምድ እየሰሩ እንደሆነ ተገልጿል፤ የተጨዋቾቹ በቫይረሱ መያዝ በቡድኑ ውስጥ ስጋትን ፈጥሯል?


ሱራፌል፡- በፍፁም፤ የብሔራዊ ቡድናችን ጥቂት ተጨዋቾች በእዚህ ወረርሽኝ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ ቫይረሱ ወደ ሌሎቹ የቡድኑ አባላቶች እንዳይዛመት በአሁን ሰዓት ከእኛ ተገልለው እና ልምምዳቸውንም ለብቻቸው በመስራት ላይ ነው ያሉት፤ እነዚህ ተጨዋቾችም አሁን ላይ ከእዚህ በሽታ ማገገም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ስላሉ እና ወረርሽኙንም እንደ ኖርማል እና በቫይረሱ የተያዙ ቢሆኑ እንኳን ከእዚህ ወረርሽኝ በኋላ ራስህን እየጠበቅክ በምትሄድበት ሁኔታ ላይ ከተገኘ ኳስን ጤናማ ሆነህ መጫወት ያስችልሃልና ይሄን ስመለከት ቡድኑን የሚያሰጋው ነገር ብዙም የለም፤ ከዛም ውጪ በቫይረሱ የተያዙት የዋልያዎቹ ተጨዋቾችም ከፈጣሪ እርዳታ ጋር በቅርብ ጊዜ ውስጥ ቡድናችንን ተቀላቅለውም ልምምዳቸውን አብረውን ይሰራሉ ብዬም አስባለው፡፡


ሀትሪክ፡- ዋልያዎቹ አሁን ላይ በመስራት ላይ ያላችሁት ልምምድ ምን ምንን ያካትታል?


ሱራፌል፡- በቀን ሁለት ጊዜ ለአራት ሰዓት የምንሰራው ልምምድ መጀመሪያ ላይ ወደ ኳሱ ከመግባታችን በፊት ለወሳኙ ጨዋታ 90 ደቂቃ ሊያጫውተንና ሊያስጨርሰን በሚችል መልኩ የአካል ብቃታችን ሙሉ ለሙሉ ፊት መሆን ስላለበት የፊዚካል፣ የፊትነስ /የትንፋሽ/ ልምምዶች ላይ አተኩረን ነበር ስንሰራ የነበረው፤ ከዛ በኋላ ደግሞ ኳስን መሰረት ባደረገ መልኩም የምንሰራቸው ልምምዶች አሉና በዛ ደረጃ ነው እየተለማመድን ያለነው፡፡


ሀትሪክ፡- ለአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታው በካፍ አካዳሚ በመቀመጥ ልምምድን እየሰራችሁ ይገኛል፤ በካምፑ ውስጥ ስላለው የቡድን መንፈስ እና ስለአዋዋላችሁ ምን የምትለው ነገር ይኖርሃል?
ሱራፌል፡- ዝግጅታችንን መስራት ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ በአሁን ሰዓት ያለው የካምፕ መንፈሳችን በጣም ጥሩ ነው፤ ለአንድ ቡድንም የቡድን መንፈስ /ቲም ስፕሪት/ ወሳኝ በመሆኑም በሜዳ ላይም ከሜዳ ውጪም ሁላችንም ተከባብረን ነው የምንገኘው፤ ከዛ በተጨማሪም በቅርቡ ስላለብን ወሳኙ የኒጀር ጨዋታም እያሰብን ነው ግጥሚያውን በጉጉት እየጠበቅንም የምንገኘው፤ ሌላው በካምፕ ውስጥ ስላለን አዋዋል ደግሞ ሁላችንም ተጨዋቾች ዲስፕሊን ሆነን ነው ለሁሉም ነገር እየተዘጋጀን የምንገኘው፣ በቂ እንቅልፍን እንተኛለን፤ ጥሩ ምግብንም እንመገባለን፤ ልምምድ ላይም ሆነ የምግብ ሰዓት ላይም የሚያረፍድ ተጨዋች ማንም የለም፤ ልምምዳችንንም በሜዳ ላይም ከሜዳ ውጪም በተግባር እና በቲዎሪ ደረጃም ከአሰልጣኛችን ውበቱ የሚሰጠንን በቂ ትምህርት በመውሰድ ራሳችንን እየለወጥን ያለንበት ሁኔታ ላይ ስለምንገኝ ይሄን ሁሉ ስትመለከት ዋልያዎቹ ምን ያህል ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ዝግጁ መሆናቸውን ነው የምትረዳው፡፡


ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን /ዋልያዎቹን/ የማሰልጠን ኃላፊነት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ከቦታው ተነስቶ ነው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በመረከብ እያሰለጠናችሁ የሚገኘው፤ በሚሰጣችሁ ልምምድ ዙሪያ ልዩነት አለ?


ሱራፌል፡- ብዙም ልዩነት አላየሁም፤ ሁለቱም አሰልጣኞች ኳስን መሰረት ባደረገ መልኩም ነው ይህም ማለት ኳስን ይዘን በመጫወት የተጋጣሚን ቡድን እንዴት ማሸነፍ እንደምንችል ነው ስልጠናን እየሰጡን የነበሩት፤ ከእነሱ ከልዩነቱ ይልቅ ብዙ የሚያመሳስላቸውንም ነገር ነው ለመመልከት የቻልኩት፤ ያ መሆን መቻሉ ደግሞ ለእኛ በጥሩነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡


ሀትሪክ፡- የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ወደ ኃላፊነቱ ሲመጣ በስኳዱ ቀደም ሲሉ ከነበሩት ተጨዋቾች ውጪ ሌሎች ተጨዋቾችንም በቡድኑ አካቷል፤ ከመረጣቸው ውስጥም ወጣቶች ይበዛሉ፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ? ውበቱስ ይህን ቡድን የት ድረስ ያስጉዘዋል?


ሱራፌል፡- የብሔራዊ ቡድናችን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የዋልያዎቹን ኃላፊነት ሲረከብ ይሄን ቡድን ጥሩ ያስጉዘዋል የሚል እምነት አለኝ፤ አሰልጣኙን በሙያው ቆይታ እንደማውቀው እግር ኳስን በጥሩ መልኩ የሚጫወት ቡድን እንደሚሰራ የታወቀ ነው፤ ከዛ ውጪም እያንዳንዱ ተጨዋች ያለውን አቅም አውጥቶ እንዲጫወትም የሚፈቅድና በወጣት ተጨዋቾች ላይም ያለው እምነት ከፍተኛ ስለሆነ እነዚህን ስራዎቹን እንዳደንቅለት ነው የሚያደርገኝ፤ አሰልጣኝ ውበቱ ዋልያዎቹን ከተረከበበት ጊዜ አንስቶም ቡድኑን በአካል ብቃቱ በኩል በጣም ፊት ለማድረግ አስፈላጊውን ስራ እየሰራ ይገኛል፤ በስራው እየተሳካለትም ይገኛል፤ ወደ ብሔራዊ ቡድን ስብስቡ ደግሞ ወጣት ተጨዋቾችንም በአብዛኛው ጠርቶም ማምጣቱ ሊያስደንቀውም ይገባልና እንደ እኔ ምልከታ ብዙ ወጣት ተጨዋቾች በእሱ ስር ቢሰለጥኑ እንደሁም እነሱም ሀገሪቷም በጣም ተጠቃሚ የምትሆንበት እድሏም ሰፊ እንደሚሆንም አውቃለሁኝ፡፡


ሀትሪክ፡- የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚዎች የወዳጅነት ጨዋታን እያደረጉ ባለበት ሰዓት እኛ ግን ያለ አቋም መለኪያ ጨዋታ ላይ ነው የምንገኘው ይሄ ከኒጀር ጋር ለሚኖርብን የቅርብ ጊዜ ጨዋታ ስጋት አይሆንብንም ?


ሱራፌል፡- የአቋም መለኪያ ጨዋታን ማድረግ ለአንድ ቡድን በጣም ወሳኝ ነው፤ የእኛ ይህን ጨዋታ አለማድረግ በተወሰነ መልኩ ሊጎዳን የሚችል ቢሆንም ግጥሚያውን ላለማድረግ እንድንችል ግን ከሁሉም በላይ የጎዳን የኮቪድ ወረርሽኝ ወደ አገራችን መግባት መቻሉና የሊግ ውድድራችን ደግሞ ተቋርጦ ተጨዋቾቻችን በየቤታቸው የሚገኙ በመሆኑ ነውና ጊዜው ባመጣው ክፉ ወርርሽኝ ምክንያት ያ ሳይሳካ ቀርቷል፤ ሌሎች ሀገሮች ግን ሊጋቸው እየተካሄደ እና ተጨዋቾቻቸውም በሚጫወቱበት የሊግ ውድድር እንቅስቃሴ ላይ በመሆናቸው ሀገሮቻቸው የአቋም መለኪያ ጨዋታን ለማድረግ ሳይቸገሩ ቀርቷል፤ አሁን ላይ ደግሞ ለእኛ ከኒጀር ጋር የምናደርገው ጨዋታ ከመቃረቡ እና ዝግጅትን የጀመርነውም ሰሞኑን ከመሆኑ አኳያም ጊዜው አጭር ስለሆነ ያለ ወዳጅነት ጨዋታ ለግጥሚያው ብንገባም ለኒጀሩ ጨዋታ የሚያግዘንን ልምምድ በመስራት ግጥሚያውን በብቃት ለመወጣት ጠንክረን እንሰራለን፡፡


ሀትሪክ፡- ከኒጀር ጋር የምታደርጉት ይሄ ጨዋታ በጣም አጓጉቷችኋል?

ሱራፌል፡- በሚገባ፤ ለዛም ነው ልምምዳችንን ጠንክረን እየሰራን ያለነው፤ አሁን ላይ በከፍተኛ ሞራል ላይም ነው የምንገኘው፤ በተለይ ደግሞ ቡድናችን ኮቪድ ወደ አገራችን ከመግባቱ በፊት በማጣሪያው ጨዋታ የአፍሪካውን ትልቅ የእግር ኳስ ሀገር ኮትዲቭዋርን ያሸነፈበት ጨዋታም ለቡድኑ ትልቅ ስንቅ እና ሞራልም ስለሆነው ጨዋታው ላይ ለሚኖረን ስነ-ልቦናም የሚያግዘን ነውና ያን አሸናፊነት አስቀጥለን መጓዝም ነው የምንፈልገው፡፡


ሀትሪክ፡- የዋልያዎቹን የተጨዋቾች ስብስብ እንዴትና በምን መልኩ ተመለከትከው?
ሱራፌል፡- ከሚገባው በላይ ጥሩ ስብስብ አለን፤ ወጣት ተጨዋቾች የበዙበትም ነው፤ ሲኒየር ተጨዋቾችም አሉን፤ ከዛ በተጨማሪ ደግሞ ሀገራችን ከ31 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫው ስታልፍ የቡድኑ አባላት ከሆኑት መካከል ጌታነህ ከበደ እና ጀማል ጣሰውም በስኳዱ የተካተቱ ተጨዋቾች ስለሆኑ የእነዚህ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች መኖር ጭምር እኛን ሊያነሳሳን የሚችል ነገር ስለሚኖር ከ8 ዓመት በፊት ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፍንበትን ታሪክ በድጋሚ እንድናሳካው ያደርገናል፡፡


ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቋሚነት ለመሰለፍ ስለሚኖረው ፉክክርስ ምን ትላለህ?


ሱራፌል፡- ከተመረጡት ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች አኳያ የቡድኑ ቋሚ ተሰላፊ ለመሆን በሁሉም ተጨዋቾች ዘንድ ከባድ ፉክክር ነው የሚደረገው፤ ሀገርህን እና ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ወገንህን ወክለህ የምትጫወት ስለሆነም ያን የመሰለፍ እድል ለማግኘትም ከአንተ ብዙ ነገርም ይጠበቃል፡፡


ሀትሪክ፡- በመጨረሻ?

ሱራፌል፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ እንዲችል በጋራ ሁሉም አካል ከጎኑ ሊሆን ይገባል፤ ይሄ ቡድን ብቃት ያላቸውን ተጨዋቾች እና ጥሩ አሰልጣኝን ይዟል፤ ቡድኑ ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይም ወክሎ የሚጫወት በመሆኑም ተጨዋቾች ትልቁን አደራ እና ከፍተኛ ሀላፊነትም ተሸክመው ያሉበት ሁኔታ ላይ ስላሉ ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ሁላችንም በከፍተኛ ዝግጅት ላይ ነው የምንገኘው፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website