የጨዋታ ዘገባ | ተጠባቂው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 5ጨዋታዎች ዛሬ (ቅዳሜ) ሲደረጉ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ጎንደር አፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ላይ የተደረገው እና ኢንተርናሽናል አርቢትር ሊዲያ ታፈሰ በጥሩ ሁኔታ በመራችው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ሳይሸናነፉ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በደረጃው አናት ላይ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ቢሸናነፉ ኖሮ የሊጉ ደረጃ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚችል በመሆኑ በጉጉት ሲጠበቅ ነበር።

እጅግ ባማረ እና ደማቅ የደጋፊዎች ዝማሬ በታየበት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ተጋጣሚያቸውን ተጭነው ለመጫወት ፈረሰኞቹ ደግሞ ጥንቃቄን መሰረት አድርገው ሲጫወቱ ተስተውሏል። በጨዋታው ግብ በማስቆጠሩ ረገድ አፄዎቹ ቀዳሚ ነበሩ።

ጨዋታው በተጀመረ 10ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማው ኢዙ አዙካ ያስቆጠራት ግብ ፋሲል ከነማን መሪ ማድረግ ችላ ነበር። ከግቡ መቆጠር በኋላ ፋሲል ከነማዎች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት የቅዱስ ጊዮርጊስን የተከላካይ ክፍል ሲፈትኑ ተስተውሏል። ሆኖም ግን ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ እንግዳዎቹ ግብ ማስቆጠር ችለዋል።

37ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ የመታውን ኳስ የፋሲል ከነማው ግብ ጠባቂ ሚካኤል ሳማኬ ቢያወጣውም በቅርብ ርቀት ላይ ይገኝ የነበረው ጋዲሳ መብራቴ በቀላሉ አስቆጥሮት ቡድኑን አቻ ማደረግ ችሏል።

ከዚህች ግብ መቆጠር 2ደቂቃ በኋላ 39ኛው ደቂቃ ላይ የፈረሰኞቹ ሀይደር ሸረፋ ከጌታነህ ከበደ ተቀብሎ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሚካኤል ሳማኬ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 2ደቂቃዎች ሲቀረው 43ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት እራሱ ሱራፌል ዳኛቸው መቶት በግቡ አናት ላይ ወጥቶበታል። በዚህም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ አሜ መሐመድን አስወጥተው ሳላዲን ሰዒድን ያስገበት ፈረሰኞቹ ተጭነው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በሜዳው ምቹ አለመሆን ምክንያት ተደጋጋሚ ኳሶች ሲበላሹ ማስተዋል ተችሏል። ባለሜዳዎቹ ፋሲል ከነማዎች በሙጂብ ቃሲም እንዲሁም ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ በዋለው ሱራፌል ዳኛቸው አማካኝነት በርካታ ኳሶችን ቢሞክሩም ወደ ግብነት መቀየር አልቻሉም።

74ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ የአፄዎቹ ተከላካዮች በትክከል ማውጣት ተስኗቸው የቀድሞው የፋሲል ከነማ ተጫዋች አቤል ያለው ጋር የደረሰችውን ኳስ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ እንግዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ ነበር።

ጨዋታው በዚሁ ውጤት ሊጠናቀቅ ነው ተብሎ ሲጠበቅ 84ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሄኖክ አዱኛ ሱራፌል ዳኛቸው ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት የውድድሩ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሙጂብ ቃሲም ወደ ግብነት ቀይሮት ቡድኑን ከሽንፈት ታድጓል። ይህ ግብም ለሙጂብ ቃሲም በውድድር አመቱ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛት ወደ 14አድርሷል።

ውጤቱንም ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ27ነጥቦች አሁንም ሊጉን ሲመራ ፋሲል ከነማ በ1ነጥብ አንሶ በ26ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook

hatricksport team

Hatricksport team