“ብዙዎቹ ክለቦችና አሰልጣኞች ኢትዮጵያዊ ግብ ጠባቂ ላይ እምነት የላቸውም ይሄ መቀየር አለበት”ጀማል ጣሰው (ፋሲል ከነማ)

“ብዙዎቹ ክለቦችና አሰልጣኞች ኢትዮጵያዊ ግብ ጠባቂ ላይ እምነት የላቸውም ይሄ መቀየር አለበት”

“የአባይ ግድብ ከአደይ አበባ ስታዲየም ጋር እኩል ቢያልቅ ደስ ይለኛል”

“የኮሮና ቫይረስ ሳይኖር ተጠንቅቀን በደንብ ሲሰራጭ ግን እንዲህ ቸልተኛ ያደረገን ምንድነው?”
ጀማል ጣሰው (ፋሲል ከነማ)


ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለምዶ ሰፈረ ሠላም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ በግብ ጠባቂነት ድንገታዊ ገጠመኝ ሀገርን ለአፍሪካ ዋንጫ እስከማሳለፍ የደረሰ ታሪክ ሰርቷል፡፡ በመብራት ኃይል ወደ ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ ሳይጫወት ሀዋሳ ከተማን ከተቀላቀለበት የትልቁ ስኬት ጅማሮው በኋላ የደደቢት፣ የኢትዮጵያ ቡና፣ የመከላከያ፣ የጅማ አባቡናና የድሬደዋ ከተማን ማሊያ የለበሰ ሲሆን ዘንድሮ በፋሲል ከነማ ማሊያ 2ኛ አመቱን ይዟል፡፡ በ2005 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወርቃማ ዘመን ለደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ሲታለፍ ባለድርሻ ከነበሩ የቡድኑ አባላት መሀል ይጠቀሳል ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው… ኮሮናን የመከላከል ሂደቱ ምን ይመስላል? ኳሱ አልናፈቀህም? ከፋሲል ከነማ ጋር ያለህ ኮንትራት ይቀጥላል? ኮሜዲያኑ ግብ ጠባቂ ነህ? ኮከብ በረኛ ስትባል ደነገጥክ? አሰልጣኞች በሀገር ውስጥ በረኞች ላይ እምነቱ አላቸው? ከውጭ ሀገር ግብ ጠባቂ ይምጣ ወይስ ይቅር? ከኔ ሲሳይ ባንጫ ይሻላል ያልከው በየትኛው ልብህ ነው? የአምናው የሊግ ድል በማጣታችሁ ምን ተሰማህ? አሁንስ ለአፍሪካ ዋንጫ እናልፋለን? አባይ ይገደባል ወይስ? የሚሉና ሌሎች አነጋጋሪ ጥያቄዎች ካቀረበለት የሀትሪክ ባልደረባ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር የነበራቸው ቆይታ ይህን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- እግር ኳሱ አልናፈቀህም…?

ጀማል፡- ኳሱማ በጣም ናፍቆኛል፡፡ ከኳስ ጋር ያለን ቁርኝት ከባድ ነውና ናፍቆኛል… በእንዲህ አይነት ሁኔታ ይቆማል ብሎ ማንም አያስብምና ግር ያሰኛል በግሌ በጣም ናፍቆኛል፡፡

ሀትሪክ፡- በፋሲል ከነማ 2ኛ አመትህን ይዘሃል…. ኮንትራቱ ዘንድሮ ያልቃል ካለቀስ ይራዘማል… ወይስ?

ጀማል፡- እውነት ነው ኮንትራቱ ዘንድሮ ያልቃል፡፡ በመጣው የኮሮና ቫይረስ የተነሣ ምንም አላገለገልንም ክለቡ ግን ደመወዛችንን ሳያጎድል እየሰጠን ነው… በሀገር የመጣ ችግር ቢሆንም ሳናገለግል እየከፈለን ነውና ክለቡ የሚለንን ሰምተን ሳይጎዳ ሁሉ ነገር ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከተጨዋች የሚፈልጉትን ነገር የሚጠይቁት ለተጨዋቹ የሚያስፈልገውን አሟልተው በመሆኑ ያስደስታሉ በደመወዝ ይከፈለን ውዝግብ የፋሲል ከነማ ስም ሲነሣም አላየሁም በዚህ አጋጣሚ አመራሮቹን ላመሰግን እፈልጋለው፡፡ ህጉ በሚለው ፋሲል ከነማም እኛም ሳንጎዳ በሠላም እንወያይና የሚመጣውን እንቀበላለን ብዬ አምናለው፡፡

ሀትሪክ፡- ወደ 7 የሚጠጉ ክለቦችን ማሊያ አድርግሃል የክለብ ለውጡ ምክንያት ምን ይሆን… ገንዘብ… ቋሚ ተሰላፊ የመሆን ፍላጎት… ወይስ?

ጀማል፡- ቋሚ ሆኖ ከመሰለፍ ጋር የተያያዘው ምክንያት ብዙም አይደለም… አንዳንዱ ክለብ አብርሃቸው ሆነህ አብረህ ተቀምጠህ አጨዋወትህ ላይገባቸው ወይም መኖርህን ላያስታውሱ ይችላሉ….ለአሠልጣኙ አጨዋወት አልመች ብዬም ይሆናል የሚገርመኝ የምወጣው ሁልጊዜም በሠላም መሆኑ ነው፡፡ ከሌላ ክለብ ጋር ወደ ወጣሁባቸው ክለቦች ጋር ለጨዋታ ስሄድ የክለቡ ደጋፊዎች ይሁኑ አመራሮች የሞቀ አቀባበል ያደርጉልኛል ለምን ወጣሁ እስክል ድረስ የምገረመው ያኔ ነው፡፡ የእግር ኳስ ባህሪይ ከመሆኑ ውጪ የተለየ ምክንያት የለውም፡፡


ሀትሪክ፡- ተጨዋቾች ግብ ጠባቂው ጀማል ከሚሉ ይልቅ ኮሜዲያኑ ይሉሃል… ያን እንዴት አየኸው ኮሜዲያን የምትባለው ከአኗኗር ካክበት ስፍራ ወይስ ሌላ ምክንያት አለው?
ጀማል፡- ተወልጄ አድጌ ብዙ ጊዜ የኖርኩት ከኳስ ሜዳ ዝቅ ብሎ ባለው ሰፈረ ሠላም የሚባል አካባቢ ነው ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈው ግን ከኳስ ሜዳ ልጆች ጋር ነው በተለይ በፊት ከነ ፋዲጋ (ብርሃኑ ቦጋለ) ግስላው (ቢኒያም) ጋር እጫወት ነበርና እነርሱ ጋር ደግሞ የሚገርም ጨዋታ አለና ከዚያ የወረስኩ ይመስለኛል ለኔ ከሰው ጋር መግባባትና መቀለድ ቀላል ነው፡፡ የቀልዱ ምንጭ አዋዋሌ ሣይሆን አይቀርም፡፡ የተወለድኩት ግን ሰፈረ ሠላም ከፍተኛ 7 ት/ቤት አካባቢ ነው፡፡ ኳስ ሜዳ ነው ስል የሰፈሬ ልጆች እየተቀየሙኝ ነው ሰፈረ ሠላም ተወልጄ ማደጌን በግልፅ መናገር እፈልጋለሁ (ሳቅ) ያም ሆኖ ታዲያ ከኳስ ሜዳ ልጆች ጋር መገኘቴ አይቀርምና ቀልደኛ ያደረገኝ አዋዋሌ ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- በረኛ የሆንከው የልጅነት ተምሣሌት ነበረህ እንዴ?

ጀማል፡- ተምሣሌት የለኝም ተምሣሌት መሆን በኛ ሀገር በተለይ ይከብዳል… ብዙዎች ሲጫወት ባልደርስበትም አጨዋዋትህና ድፍረትህ እንደ አሊ ረዲ ነው ይሉኛል…. ባየው ደስ ይለኝ ነበር ደፋር ነው ምርጥ ብቃቱ ላይ እያለ ነው የተጎዳው በጉዳትና በህመም ከኳስ መለየቱ ያሳዝነኛል… በነገራችን ላይ በረኛ የሆንኩት ግን በአጋጣሚ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- እስቲ ይሄን አጋጣሚ አብራራው?

ጀማል፡- ተጨዋች መሆን ነበር ደስ የሚያሰኘኝ… ነገር ግን ታምራት ምክረ የሚባል ሰው ግብ ጠባቂ ያደረገኝ… አንድ ቀን … በገንዘብ አስይዘን ኳስ እንጫወት ነበር…. ታዲያ ይሄ የምልህ ታምራት የሚባለው ሰው በወቅቱ ተስፋ ለኢትዮጵያ የሚባል ፕሮጀክት ላይ ይጫወት ነበር… እዚያ ሰርቶ ይመጣና የሰፈር ልጆች ስንጫወት ይመለከት ነበር፡፡ አንዴ ትዝ ይለኛል ቀኑ ቅዳሜ ነው በሆነ ሰዓት ላይ በረኛ ስትገባ በቁጥር ነውና ቁጥር ደርሶኝ በረኛ ገባሁ ገንዘቡን በጣም እፈልገው ነበርና ወጥሬ ተጫወትኩ እኔ ጎል ላይም አይገባም እዚያም ጎል ላይ አልገባ አለ… እንዲያውም አንዱ ሁለቱም ጋር የገባኸው ግብ ጠባቂ አንተ ነህ እንዴ? ብሎ አስቆኛል /ሳቅ በሳቅ/ ያ ገጠመኝ አላህ ተጨመረበትና ሁሉን ነገር ከፈተልኝ /ሳቅ/ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የቀበሌ አሰልጣኝ ሲሆን በረኛ እኔን መረጠኝ.. እንዲህ ነው ታሪኩ የጀመረው…. የማልረሳው አንድ ገጠመኝ ደግሞ አለ፡፡ ለኪራይ ቤት የሚጫወት ዘላለም የሚባል በረኛ እኛ ጋር መጥቶ ሲጫወት አየሁት… ይወረወራል.. በኃይል ይወድቃል… እንዴ ይሄንንማ አልበልጥም አልኩና አሰልጣኙ ጋር ሄጄ ላቁም እንዴ? ይሄ ልጅኮ ኃይለኛ ነው ስለው ሰደበኝ እሱን አይተህ ትፈራለህ? አንተ ጋር አሪፍ ነገር አይቻለሁ በዚያ ላይ ደግሞ ክለብ ስላለው አይገባም አለኝ ድፍረቴን ባውቅም ሲወድቅ አይቼው ፈራሁ… ነገር ግን አቋምህን አፅና አትዋዥቅ አንዴ በረኛ ሆነሃል አትመለስም አለኝና አበረታታኝ ከዚያ በኋላ እንዳለው…. ግብ ጠባቂ ሆኜ ቀረሁ…. አሁን ግን በረኛ አይደለሁም… ቤት ነኝ /ሳቅ በሳቅ/

ሀትሪክ፡- በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ባሎች ቤት ሲሆኑ የባልና ሚስት ድብድብ ተበራከተ ተባለ ምን ትላለህ?

ጀማል፡- ይሄኮ መጀመሪያውኑ አይተዋ ወቁም ማለት ነው… አሁን የሚጣሉት ሳይተ ዋወቁ ተጋብተው ይመስለኛል በኔ በኩል አላገባሁም የፍቅር ጓደኛ ግን አለኝ…


ሀትሪክ፡- እጩ ሚስት ማለትህ ነው?

ጀማል፡- ባሎን ዶኦር አደረከው /ሳቅ በሳቅ/

ሀትሪክ፡- አንተ ኮከብ ስትባል እጩ አልነበረም አሉኝ እስቲ የአመቱ ኮከብነትህን ጊዜ አስታውሰኝ?

ጀማል፡- በወቅቱ ጥሩ አቋም ላይ ነበርኩ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ አዳነና አሉላም በምርጥ አቋም ላይ ነበሩ… ያኔ መድፈኛ የሚባል ጋዜጣ ነበርና የዘንድሮ ኮከብ ማን ይመስልሃል ሲለኝ ኮከቡ ያለው ሰማይ ላይ ነው ከወረደ እንኳ ኮከቡ እኔ ነኝ ብዬዋለው..በረኛ ተከላካይ አጥቂ ተብሎ ሲመረጥ ሳይሆን በአመቱ እንቅስቃሴዬ ምርጥ ስለነበርኩ የአመቱ ኮከብ ተብዬ ተሸልሜያለሁ፡፡ የመጨረሻ ጨዋታ ቀን ሙሉጌታ ምህረት ይደውልለኝና ከቤቴ ቀጥታ ስታዲየም አብሬው ገባሁ ጨዋታውን ላይ እንጂ ኮከቡ ማን እንደሆነ አይታወቅም… ጨዋታው ሊጠናቀቅ ወደ 20 ደቂቃ ሲቀረው ነው የስታዲየሙ አስተዋዋቂ የነበረው ምስግና መብራቱ ጋር መረጃው ደረሰ፡፡ ማነው ኮከቡ አይታወቅም… 450 ተጨዋች ኮከብ የነበረበት አገር ላይ ነበር የኖርነው… ሁሉም ኮከብ ነበር ተጨዋች ስለተባለ ነው እንጂ አሰልጣኞችም ኮከቦች ነበሩ /ሳቅ/ የአመቱ ኮከብ ተጨዋች ጀማል ጣሰው ተብሎ ሲጠራ እነርሱ ሜዳ ላይ ናቸው ያሉት እኔ ወደ ትሪቩኑ ሮጥኩ /ሳቅ/ ደንግጬኮ ነው… አልጠበኩትም ብዬ ስናገር በራሱ ሌላ ዜና ተሰራ… ምንም ሳይነገር እጩዎች ሳይኖሩ 450 ተጨዋች ኮከብ በሆኑበት ሀገር እንዴት ኮከብ ነኝ ልበል….? /ሳቅ/ አሁን ግን ተሻሽሎ እጩዎች መኖራቸው ያስደስታል፡፡

ሀትሪክ፡- ኮከብ ሰማይ ላይ ነው ያለው…. ኮከቡ ከወረደ ግን ኮከቡ እኔ ነኝ ብለህ ለጋዜጣው ከተናገርክ በኋላ ኮከብነቴን አልጠበኩም ማለት ይቻላል?

ጀማል፡- /ሳቅ/ እንኳን አመቱን በምርጥ ብቃት ጨርሼ አንድ ጨዋታ ላይ ጥሩ ከሆንኩ ኮከብነትን ማሰቤ አይቀርም ነገር ግን ኮከብ በረኛ እንጂ የአመቱ ኮከብ ተጨዋች የሚለውን ማዕረግ አልጠበኩም ይሄ እውነት ነው በወቅቱ የተዘጋጀው የኮከብነት ዋንጫ አንድ ነበር፡፡ ያንን በመውሰዴ ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ከዚያ በኋላ ግን እንኳን ኮከብ በረኛ ጥሩ የምንለው በረኛ ጠፋ… ይሄስ አያምም?

ጀማል፡- እዚህ ላይ በደንብ መናገር እፈልጋለው ኮከብ በተባልኩበት ጊዜ ምርጥ በረኞች ነበሩን እኔ ባልሆንም በወቅቱ ከነበሩት አሪፍ በረኞች አንዱ ኮከብነቱን ይወሰድ ነበር፡፡ ቋሚ ተሰላፊና ምርጥ በረኞች ለሀገር የሚጠቅሙ ነበሩ፡፡ በኮከብነቴ ዘመን አሰልጣኜ የነበረው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ዛሬ ብሳሳትም በቀጣዩ ጨዋታ ላይ ያስገባኝ ነበር ትልቅ ዋጋ ከፍሎብኛል ከፍተኛ ስራ ሰርቶብኛል በዚህ አጋጣሚ አመሰግነዋለው… ዛሬ ተሳስቼ ነገ ሲያስገባኝ በራስ መተማመኔ እንዲጨምር አድርጎልኛል.. አሁንኮ አንዴ ስትሳሳት ቤትህ ትቀመጣለህ የዛኔ ግን ሁሉም ሰበብ በረኛ ላይ አልዞረም ነበር አሁን ግን ሰበቡ በረኛው ላይ ብቻ ነው የሚሆነው… ድሮም የኢትዮጵያ በረኛ ይባላል ዘንድሮ ለፋሲል ከነማ ነው የምጫወተው እዚያ በምሰራው ስህተት ሁሉም የኢትዮጵያ በረኞች ይጠሩበታል… ይሄ ነው ትልቁ ስህተት፡፡ አንድ የኢትዮጵያ በረኛ ወደ ሜዳ ሲገባ ሁላችንንም ወክሎ ነው እኩል ነው የምንወቀሰው ያኔ ግን እንዲህ አልነበረም ሁላችንም በራስ መተማመን ተሞልተናል ዛሬ ተሳስተን ነገ እንገባና ስህተቱን እናርማለን በረኛ ደግሞ ልምድ የሚያገኘው በመጫወት ነው… ከእንቅልፉ ቀስቅሰህ ግባ ብለኸው ሲሳሳት ነገ ደግሞ ተኛ ማለት ልክ አይደለም… እንደ ድንገትኮ ነው ግባ የምትባለው… ከተኛህበት ቀስቅሰው ያስገቡህና የሆነ ነገር ስተሳሳት ተኛ ይሉሃል ይሄ ለውጥ አያመጣም፡፡ ከእንቅልፍህ ቀስቅሰው ያስገቡሃል ማለት ከብዙ ጨዋታ በኋላ ነው የሚያስገቡህ… ኢትዮጵያዊው በረኛ ሳይገባ ከመቆየቱ የተነሣ የቱ ጋር ነው የምቆመው እዚያ ጋር ነው እዚህ ጋር ነው ሊል ይችላል… ብዙ ጊዜ ስለማይጫወት መስመር ዳኛ ጋር የሚቆም ሊመስለው ሁሉ ይችላል /ሳቅ/ ይሄ መታረም አለበት ባይ ነኝ፡፡


ሀትሪክ፡- ይሄ የበረኛ ችግር ሀገራዊም ሆኗል… ከውጪ ተጨዋቾች መብዛት ወይስ የኛ የአቅም ችግር?

ጀማል፡- አቅም አንሶን ሳይሆን እምነት ነው ያጣነው… ብዙዎቹ ክለቦችና አሰልጣኞች ኢትዮጵያዊ ግብ ጠባቂ ላይ እምነት የላቸውም ይሄ መቀየር አለበት… በአንድ ክለብ ተሰላፊነቴ የገጠመኝን ልንገርህ… የውጪ ዜጋ በረኛ ነበረን ተሳስቶ ጎል ገባበት… አሰልጣኙ ይስተካከላል ሰው ስለሆነ ነው የተሳሳተው አለ …. በቀጣዩ ጨዋታ እኔ ገባሁና ተሳሳትኩ እድለኛ ሆኜ ግቡ ሳይገባ ተከላካያችን አወጣው…. አሰልጣኙ ጨዋታው አልቆ ሲያገኘን ተከላካዩን እያየ ጀማል ተሳስተህ ነበር እሱ ነው ከጉድ ያወጣን አለ… እንዴ ኮች ባለፈውኮ ያኛው በረኛ ተሳስቶ ሰው ስለሆነ ነው የተሳሳተው አልክ እኔስ ሰው አይደለሁም ወይ ብዬ ጠየኩ… ይሄን ስናገር በቀጣዩ ጨዋታ እንማልሰለፍ አውቅ ነበር የሆነውም ያ ነው….
የአሰልጣኞች በረኛ ላይ ያላቸው እምነት መጥፋቱ በረኛው ላይ ያለውን ጫና አክብዶታል ይሄ ሊስተካከል ይገባል…. በርግጥ ያለህን ነገር አምነው ከነስህተትህ የሚያስገቡ ነገ እንደምትለወጥ የሚያምኑ አሰልጣኞች አሉ… እነሱን አመሰግናለሁ በዚያም ላይ የኛም ስህተት አለ እንሳሳታለን ብለን ተቀብለናል ይሄም መስተካከል አለበት በእርግጥ የነበረው ጫና ሲደጋገም ይበላሽብናል የሚለውን እንድንቀበል አድርጎናል…. ይሄ በእኛ በኩል ልናስተካክለው የሚገባ ነው፡፡ ሲጀመር የምንወቀስበትን ነገር መቀነስ አለብን አሰልጣኞቹም ለበረኛ የሚመች አጨዋወት ነው ያላቸው ተብሎም መታየት አለበት… አሰልጣኙም አጨዋወቱን መለስ ብሎ መመልከት አለበት፡፡ እኔ በእግሬ ኳስ መጫወት ብፈልግ አሰልጣኙ ላይመርጥ ይችላል… በዚያ ልዩነት ውስጥ ደግሞ ስህተት ሊፈጠር ይችላልና በአጨዋወት ውስጥ ለኔ የሚመቸኝን አሰልጣኙ መፈለግ አለበት፡፡

ሀትሪክ፡- የውጪ ግብ ጠባቂ መምጣቱ የችግሩ ምክንያት ነው የሚሉ አሉ… በረኛ ከውጪ አይምጣ የሚሉ ወገኖችን ትደግፋለህ…?

ጀማል፡- ይሄኮ ወሬ ሆነ… ሁልጊዜ ነው የሚወራው ተተግብሮ አያቅም… በበረኛ ዙሪያ የውጪ በረኛ ሊመጣ አይገባም ያለንን የራሣችንን አቅም ማሳደግ አለብን.. በተጨዋቾችም ሆነ በግብ ጠባቂ ዙሪያ ያለንን አስተካክለን መገኘት አለብን፡፡ አሰልጣኞችም ይሄን ሊቀበሉ ይገባል ምናልባት የውጪ ሀገር በረኛ የሚመርጡ አሰልጣኞችኮ ብሔራዊ ቡድኑን ሲይዙ በማን ሊጫወቱ ነው? በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ ይሄ ነገር አጋጥሞኛልና ቢስተካከል ደስ ይለኛል.. 3 የውጪ ሀገር በረኛ ይዘህ ነገ ብሔራዊ ቡድኑን አሰለጥናለሁ ማለት ከባድ ነው መጀመሪያ በክለብ ደረጃ በኢትዮጵያዊያን በረኞች ታምንብናለህ ወይ? ካመንክ ለሀገርህ አሰልጣኝ መሆን ትችላለህ… ከውጭ ካመጣህ ደግሞ የምንማርበት ቢሆን ደስ ይላል እንደ ጀማል ግን በረኛም ሆነ ተጨዋች የውጪ ዜጎች ያስፈልጋሉ ብዬ አላምንም ደደቢት እያለሁ ሌላ ችግር ቢኖርበትም በችሎታው አሪፍና ተምሬበት የማውቅ በረኛ ነበር፡፡ ግብ ጠባቂ የነበረ ግብ ጠባቂ ሆኖ እየተጫወተ ያለ ቢመጣ ጥሩ ነው ት/ቤት እያለ ግብ ጠባቂነትን የሞከረ በፎቶ ብቻ እያዩ ይምጡ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ በነርሱ አትማርባቸውም የሀገር ሀብትም ይባክናል ክለቦቻችን በደንብ ሊያስቡበት ይገባል፡፡

ሀትሪክ፡- በጀማል ህይወት ውስጥ ለውጥ ያመጣ ጀማልን የቀረፀ ባለውለታ የሚባል አሰልጣኝ ማነው?

ጀማል፡- መቅረፅ የቻለ ማለት አልችልም መቅረፅኮ በጣም ከባድ ነው ከኤልፓ ሲ ያሳደገኝ ኤሊያስ ጁሃርን ቀርጾኛል ነው የምልህ… ባለኝ ነገር ላይ የጨመረና ጥሩ ጊዜ ያሳለፍኩት ደግሞ ከአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ነው በደደቢት ጥሩ ጊዜ አሳልፊያለሁ…. በእግሬ ስጫወት ተው ግባ የሚለኝ አሰልጣኝ ብዙ ነበር.. ደደቢት ስጫወት በጣም ወጥቼ ነበር አሰልጣኝ ውበቱ የተጣለው ኳስ ወጥቼ እንድጫወት ይፈልግ ነበር ልክ እንደ አሁኑ የአለም እግር ኳስ ማለት ነው ውበቱ ግን ገና በ2002 ይህን እንድጫወት ይፈልግ የነበረ አሰልጣኝ ነው… በኔ ይሁንብህ ውጣና ተጫወት ይለኝ ነበርና በዚህ በኩል ረድቶኛል ብዬ አስባለሁ ያለኝን ነገር በደንብ እንዳወጣ አድርጎኛልና አመሰግነዋለው፡፡


ሀትሪክ፡- በ2005 ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፍን በኋላ 7 አመታት አለፉ… አሁንስ የሚሳካ ይመስልሃል?

ጀማል፡- 2005 በእግር ኳሱ ምክንያት እንደ ሀገር ለሁላችን አሪፍ ጊዜ ነበር… የህዝቡን አንድነት ሁሉ የፈጠረና ለካ ኳስ እንዲህ ነው ያልንበት ጊዜ ነበር አሁንም ይሄ በሽታ መጣ እንጂ አሰልጣኝ አብርሃም ጥሩ ቡድን ሰርቶ ነበር ተስፋ አድርጌም ነበር፡፡ የኛ 2005 ቡድን አንድ መንፈስ ነበረው ሁሉም የየራሱን አንድ ነገር አዋጥቶ ነው እድሉ የተገኘው…. ማለፍ አለማለፍ የሚለው እንተወውና ሲጫወቱ መሰረት ያለው ነገር አይቼባቸዋለው… ወላሂ ተስፋ አድርጌ ነበር ይህን ያየሁትን ነገር ይዘው ከመጡ ያልፋሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የጀማል ጣሰው ወርቃማ የተጨዋችነት ዘመን መቼ ነበር?

ጀማል፡- ኮሮና የሌለበት ዘመን ሁሉ… /ሳቅ/ ባሳለፍኩት ጊዜ ሁሉ ደስተኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን በ2005 ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፍንበት ልዩ አመቴና የደስታዬ ጊዜ ነበር ከዚያ ውጪ ያዘንኩበት ከጅማ አባቡና ጋር ከፕሪሚየር ሊጉ የወረድንበትና አምና ከፋሲል ከነማ የሊጉን ዋንጫ ያጣንበት ጊዜ ሁለቱንም አልረሳቸውም፡፡

ሀትሪክ፡- መፅናኛ ሆኖ በኮንፌዴሬሽን ካፕ የተሳተፋችሁበት የጥሎ ማለፍን ድልኮ አስመዝግባችኋል?

ጀማል፡- አምና በሊጉ ዋንጫ ያልተቀበልኩበት አመት እንጂ ዋንጫ ያልበላሁበት አይደለም… ዋንጫውን እኛ ምርጥ ስለነበርን በልተናል፡፡ አለመቀበሌ ነው ያሳዘኝ እኔ ዋንጫውን ወስጃለሁ ቅር ያለኝ ስላልተቀበልኩ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ነህ ማለት ይቻላል?

ጀማል፡- የቀድሞ የሚለው ልክ አይደለም ዘንድሮም በጉዳት እንጂ ነበርኩበት…
ጉዳት አጋጥሞኝ ነው የተገለልኩት የቀድሞ የሚለው ላቆመ ግብ ጠባቂ ነው እኔ ግን አሁንም በክለብ ደረጃም ይሁን በሀገር ደረጃ ማገልገል ስለምችል የቀድሞው የሚለው አይመጥነኝም፡፡ በእግር ኳስ ህይወቴ የሊጉን ዋንጫ አልወሰድኩም፡፡ ገዝቼም ቢሆን ቤቴ እወስዳለሁ እንጂ አይቀርም /ሳቅ/ እንደዚህ ተጫውቼ የሊግ ዋንጫ አለመውሰድማ ፍትሃዊ አይደለም ከፋሲል ከነማ ዘንድሮ እወስዳለሁ ብዬ ነበር አላህ አልፈቀደም ተስፋ አለኝ፡፡ ያልተቀበልኩትን ዋንጫ መቀበሌ አይቀርም፡፡

ሀትሪክ፡- የሊጉ መሪ መሆናችሁ ዋንጫ ውን እንደምትወስዱ ማስተማመን ይቻላል?

ጀማል፡- እየመራን ስለሆነ ሳይሆን በቡድናችን ስለምተማመን ነው እየመራ ያለ ቡድን ተደርሶበት አይተናልኮ ብንመራም ጠንካራ ቡድን ይዘን ስለነበር ዋንጫ እንወሰዳለን ብዬ አምን ነበር፡፡ ብትመራ የሚለው ተወው መርቼ እንጂ ተመርቼ አልቆመም /ሳቅ/ እንዳንድ ድክመቶች ነበሩብን እያረምን ስለምንሄድ ድሉ የኛ ይሆን ነበር ከሜዳ ውጪ ጥሩ አልነበረም የሚባለውን ክፍተት በደንብ አስተካክለን ስለመጣን ድሉን ብቻ ነበር የምንጠብቀው፡፡

ሀትሪክ፡- በ2005 የአፍሪካ ዋንጫ እኔ ልቀየርና ሲሳይ ባንጫ ይግባ ያልክበት አጋጣሚ አሁን ድረስ ይወሳል እስቲ ያንን ጊዜ አስታውሰኝ…. ?

ጀማል፡- የእውነት ሰው የሚያደርግህ አጠ ገብህ ያለው ሰው ነው፡፡ አጠገባችን የነበረው ፍቅርና ህብረት ነው ይህን ያመጣው… ከጨዋታው አንድ ቀን በፊት የበረኛ ልምምድ ሪጎሬ እየተመታብን ስንለማመድ ሲሳይ ጥሩ እንደነበር ሪጎሬ ሲያድን አይቼው ውስጤ አስቀምጬዋለው የጨዋታ ቀን ደረሰ እዚህ 1ለ0 ረታን እዚያ 1ለ0 አሸነፍንና ወደ መለያ ፍፁም ቅጣት ምት ልንሄድ ነው እያልኩ ነበር ጨዋታው ሊያልቅ 10 ደቂቃ እንደቀረው ከጀርባዬ የነበረውና ተቀይሮ ሊገባ የተዘጋጀው ብርሃኑ ቦጋለ (ፋዲጋ) ነግሮኝ ነበር፡፡ በዚያ ላይ እርሱ ገብቶ ሳላሀዲን ባርጌቾ ሊወጣ ሲል እኔ ወደቅኩ፡፡ ፊዚዮቴራፒስቱ ይስሀቅ ሽፈራው መጥቶ ምንድነው ምን ሆንክ ሲለኝ ሲሳይ ባንጫ እንዲገባ ብዬ ነው ስለው ደነገጠ.. ምንም አለመሆኔን ነግሬው ባሰብኩት መንገድ ሲሳይ ባንጫ ተቀይሮ ገባ፡፡ ያኔ ከኔነት ስር ወጥተን የህብረት ጉዞ ላይ ስለነበርን ደስ የሚል ጊዜ እንድናሳልፍ አድርጎናል፡፡ ለሀገርህ ስትሰራ ከኔነት ወጥተህ ወደ እኛነት መቀየር የግድ ይላል፡፡ ያኔም ሲሳይ ገብቶ አሸንፈን ወጣን፡፡ እኔ ገብቼ ሪጎሬ ሳላድን ብንሸነፍኮ ማንም አይጠይቀኝም ግን እርሱ ገብቶ ማሸነፋችን ክሬዲቱን ከፍ አድርጎልኛል ሁሌ ይሄ ቢኖር ደስ ይለኛል፡፡ መጀመሪያ ህሊናችን ነው የተደሰተው…. ጥቅሙ በኋላ ይመጣል እኛነት ነግሶ በማሸነፋችን የማልረሳው ገጠመኝ ሆኖልኛል፡፡ እግር ኳስ ላይ ከእኔነት ወደ እኛነት የተለወጠ ቡድን ያሸንፋል፡፡

ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታና ፋሲል ከነማ ከአፍሪካ መድረክ መከልከላቸውን እንዴት አየኸው?

ጀማል፡- እንደ ሀገር ተወካይ ሊኖረን ይገባል፡፡ ክለቡ ማንም ይሁን ሀገሬ መወ ከል አለባት ብዬ አስባለው፡፡ ተሸነፍንም አሸነፍንም ኢትዮጵያ መወከል አለባት፡፡ ከጊዜ በኋላ አገሪቷን ማስጠራታችን የግድ ይሆናል እንደፋሲል ከነማ ተጨዋችነቴ ዋንጫ እንወስዳለን የሚል እምነት ነበረኝ መሳተፍ የሚያስችል አቅም ገንብተን ስለነበር አለመሳተፋችን ቅር ያሰኛል በተለይ የፋሲል ከነማ ደጋፊ ለሚከፍለው ዋጋና ለቡድኑ ከፍታ ከሚሰጠው ድጋፍ አንፃር በአፍሪካ ደረጃ መጓዝ ይገባዋል፡፡ ብዙ የሚደክሙ ምርጥ ደጋፊዎች አሉን፡፡


ሀትሪክ፡- ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ቤት ተቀመጡ ተብሏል… ተቀምጠሃል ወይስ ዟሪ ነህ?

ጀማል፡- /ሳቅ/ አሁን ቤቴ ጥግ ላይ ነኝ ያለሁት… በደንብ ተቀምጫለሁ… እስካሁን በሽታው እንዳለ ያለማመን ነገር ነበር አሁን እያመንን የመጣን ይመስለኛል በኢትዮጵያ አንድ ሰው በኮሮና ቫይረስ ተያዘ ሲባል ብዙ ይጠነቀቅ ነበር አልኮል የሚቀባ ሰው ብዛቱ… ውሃ የሚያስታጥብም እንደዛው ….አሁን ግን አልኮል ሁሉም ተቀብቶ ጨርሶት ያለ ሁሉ አይመስለኝም…የኮሮና ቫይረስ ሳይኖር ተጠንቅቀን በደንብ ሲሰራጭ ግን እንዲህ ቸልተኛ ያደረገን ምንድነው? እርዳታውን ብታይ እንኳን ብዙ ሰው ነበር የሚረዳው አሁን ግን ቀንሷል.. ሰው ቀዝቀዝ አለ ዋናው ጊዜ አሁን ነው ከዚህም ሊብስ ይችላል፡፡ ጥንቃቄያችንን ጨምረን ከአቅም በላይ የሆነውን ለፈጣሪ መስጠት ይገባል ባይ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የጀማል ጣሰው ምርጡ በረኛ ማነው?

ጀማል፡- ምርጡ በረኛ አስበላህ የማይባል በረኛ ነው /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- አስበላህ የማይባል ግብ ጠባቂ አለ እንዴ?

ጀማል፡- /ሳቅ/ የለም ስለዚህ ምርጥ በረኛ የለም ማለት ነዋ /ሳቅ በሳቅ/ ምርጡ በረኛ ፀጋ ዘአብ አስግዶም ነው ሲጫወት አይቼዋለው አሊ ረዲን ሲጫወት አላየሁትም አላደንቀውም ማለት ግን አይደለም፡፡
ሀትሪክ፡- ጀማል የውጪ ኳስ ያያል….?

ጀማል፡- የውጪ ኳስ ማለት ከአጥር ውጪ… /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ከሀገር ውጪ /ሳቅ/?

ጀማል፡- አያለው.. .በነገራችን ላይ ግጥሚያ ከሌለኝ የሀገር ውስጥ ጨዋታንም ስታዲየም ተገኝቼ አያለሁ፡፡ በረኛነት ላያዝናና ይችላል ነገር ግን እኔ በረኛ ሆኜ ሜዳ ስገባ የምጫወትበት መንገድ ነው ሊያዝናናኝም ላያዝናናኝም የሚችለው ባይ ነኝ፡፡ አንተ የምትጫወትበት መንገድ ቡድኑን ከአደጋ ካተረፈ ደስ ይላል ሜዳ ስገባ እንደተጨዋች ሆኜ ስለሆነ እዝናናበታለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- አንድ በረኛ ጨዋታን ገድሎ ሲወጣ ያየህበት ግጥሚያ አለ….?

ጀማል፡- የአትሌቲኮ ማድሪዱ ኦብላክን አይቻለሁ፡፡ ከዚያ ውጪ አያክስ ከጁቬንቱስ ሲጫወት የአያክሱ በረኛ በርካታ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን አድኗል ያንን አልረሳም፡፡

ሀትሪክ፡- አባይ ይገደባል ወይስ… ግብፅ ታሰጋሃለች…?

ጀማል፡- አባይ የኛ ነው ምንም ጥያቄ የለውም፤የግድ መገደብ አለበት፤የአባይ ግድብ ከአደይ አበባ ስታዲየም ጋር እኩል ቢያልቅ ደስ ይለኛል፤አንድ ላይ እንዳያቸው እመኛለሁ፡፡እናም የግብፅ ዛቻ ውጤት ሳያመጣ አባይ ይገደባል ባይ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ጨረስኩ… የምታመሰግነው አለ…?

ጀማል፡- የቅድሚያ ምስጋናዬ ለአላህ ነው፡፡ ከዚያ በመቀጠል በተጨዋችነቴ ላይ ብዙ ድጋፍ ያደረጉ ሰዎች አሉ የሰፈረ ሠላም ጓደኞቼ ሳይቀር… በኔ ዙሪያ የነበሩትን በሙሉ አመሰግናለሁ፡፡ አላህ ይስጥልኝ…ብድሩን ይከፍላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ሀገሬን በኳሱ አገልግያለሁ በቀጣይም ሀገሬን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡፡ አላምዱሊላሂ ነው የምለው፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport