በ2012 ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያለው ሚና

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በክለቦች እንዲመራ ማድረጉ እና ክለቦችም የመሩናል የሚሏቸውን ሰባት አመራሮች በአብይ ኮሚቴነት መምረጣቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ አመራሮችም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወድድር አመራር ዐብይ ኮሚቴ በሚል ተዋቅረው በስራቸው የውድድር እና ስነስርዓት ኮሚቴ በማዋቀር በየሳምንቱ የተደረጉ ውድድሮች ሪፖርቶችን በመመልከት እና የቀጣይ ሳምንት ፕሮግራሞችን በማውጣት ውድድሮችን በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም መሰረት የውድድር እና ስነስራት ኮሚቴው የጨዋታ ታዛቢዎችን ሲመድቡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ድግሞ የጨዋታ አመራሮችን ይመድባል፤ በጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡት የፍትህ አካላት (የዲሲፕሊን እና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች) ከየክለቦች የሚቀርቡ እንዲሁም ከጨዋታ ታዛቢዎች እና ዳኞች የሚቀርቡ ክሶች በሚመለከታቸው አካላት ሲቀርቡላቸው ያጣራሉ ብሎም የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡
የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲጀመር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ውድድር አመራር አብይ ኮሚቴ ውድድሩ የሚካሄድባቸው ሜዳዎች ያሉበት ደረጃን በመመልከት ውድድሩ እንዲካሄድባቸው አወንታዊ ምላሽ የሰጣቸው ብሎም አሉታዊ ምላሽ የሰጣቸው ሜዳዎች እንዳሉ እንዲሁም ሜዳ በመቀየር ውድድር ለማካሄድ የተገደዱ ክለቦች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ይህ አሰራር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተደራጀ የክለብ ላይሰንሲንግ ክፍል እና ባለሙያ ባለመኖሩ የተሰራ ስራ እንጂ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ሳይመለከተው ቀርቶ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአዲስ መለክ ክፍሉን በማደራጀት የክለብ ላይሰንሲንግ ባለሙያ በመቅጠር ካሳለፍነው ሁለት ወራት ወዲህ ወደስራ ገበቷል፤ የክለብ ላይሰንሲንግ ስራ ሜዳን ብቻ በመመልከት ያጫውታል ወይም አያጫውትም ማለት ብቻ ሳይሆን ክለቦች ያላቸውን አደረጃጀት እና የሰው ሀይል በጥልቀት በመመልከት ክለቦች ወደ ተሻለ የክለብ አደረጃጀት እንዲመጡ ማድረግ የክፍሉ ዋንኛ የስራ ድርሻ ነው፡፡
ሰሞኑን ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ክለብ የቀረበውን የሜዳ ምልከታ ጥያቄን የአስተናገደው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥር 22 እና 23/2012ዓ.ም በክለብ ላይሰንሲግ ማኔጀሩ የተመራ ሶስት አባላት ያሉት ቡድን ወደ ስፍራው በመላክ የአዲግራት ስታዲየም ያለበት ደረጃን በመገምገም ተመልሷል፡፡ በመሆኑም ሰኞ ጥር 25/2012ዓ.ም የግምገማውን ሙሉ ሪፖርት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በቀጥታ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አመራር አብይ ኮሚቴ በግልባጭ ገምጋሚ ቡድኑ ያቀረበ ሲሆን፤ ጥር 26/2012ዓ.ም ማክሰኞ በግልባጭ ሳይሆን በቀጥታ ይጻፍልን የሚል ጥያቄ አብይ ኮሚቴው ባቀረበ ጊዜ በዕለቱ ማክሰኞ ጥር 26/2012ዓ.ም ለአብይ ኮሚቴው ሪፖርቱ በድጋሚ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ ሪፖርቱ ለዓብይ ኮሚቴው የተላከበት ዋንኛ ምክንያት ውድድሩን በመምራት ላይ የሚገኙት እነሱ በመሆናቸው ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር የውሳኔ ሃሳብ እንዲያስተላልፉ በሚል ነው፡፡
የካቲት 1/2012ዓ.ም በትግራይ አለማቀፍ ስታዲየም በተካሄደው የ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በስፍራው የታደሙት የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ ያሰሟቸው የነበሩት የተቃውሞ ድምጾች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፕሪሚየር ሊግ ውድድሩ ላይ ያለውን ሚና ካለመረዳት ወይም ካለመገንዘብ የመነጩ መሆናቸውን ተረድተናል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በውድድሩ ላይ ያለውን ድርሻን በተመለከተ ክለቦች ለደጋፊዎቻቸው ግንዛቤ ማሰጨበጥ እንዳለባቸው አጽኖት በመስጠት እና የ2012 የውድድር ዘመን ፍጹም ሰላማዊ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እያሳሰበ ከፕሪሚየር ሊግ አብይ ኮሚቴው በላይ የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት ሁሌም ዝግጁነታችንን እና አጋርነታችንን እንገልጻለን፡፡

Via – EFF

Hatricksport website Editor

Facebook

ሚሊዮን ኃይሌ

Hatricksport website Editor