መነሻ ገጽ The BiG Interview “በጣም ትንሽ ለሆነችው ሙከራዬ ከደጋፊው የተሰጠኝ ምላሽ መሸከም ከምችለው በላይ በመሆኑ ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ አልቅሻለሁ” ኢንስ. አብርሀም መብራቱ
The BiG Interviewዋልያዎቹዜናዎችየኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን

“በጣም ትንሽ ለሆነችው ሙከራዬ ከደጋፊው የተሰጠኝ ምላሽ መሸከም ከምችለው በላይ በመሆኑ ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ አልቅሻለሁ” ኢንስ. አብርሀም መብራቱ

አጋራ
አጋራ

 

THE BIG INTERVIEW WITH ABRAHAM MEBRAHETU




በይስሐቅ በላይ

ሀትሪክ፡-… ጥያቄዬን የምጀምረው
ሀትሪክ ብ/ቡድኑ ላይ ባቀረበችው ተደጋጋሚ
ትችት ቅሬታ እንዳለህ ገልፀህልኛልና…እስቲ
ከእሱ እንጀምር…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …አሁን ሁሉም
አልፏል…ያን ያህል የከበደ ቅሬታም
የለኝም…፤ …በጣም ቅር ቢለኝ በዚህ መልኩ
የምንገናኝበት እድል አይኖርም ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- የቅሬታህ መነሻ ትችት ነው…
ሀትሪክ የተቸችህ ብ/ቡድኑ ባሳየው ደካማ
እንቅስቃሴ ውጤታማ አለመሆኑን ተከትሎ
ነው…ምነው…አብርሽ…ትችት የሚሸከም
ትከሻ የለህም እንዴ…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …ግለሰብ ላይ
ያላነጣጠረ…ሙያውን መሠረት ያደረገ
ትችት ሲቀርብ በጣም ነው የምቀበለው…
እኔን ተወኝና…በካፍ ኢንስትራክተርነቴ…
አልጣኞችን በማስተምርበት ጊዜ ከየትኛውም
አቅጣጫ የሚመጣውን ትችት ወይም
ተቋውሞ መቀበልና ወደ ፖዘቲቭ ኢነርጂ
(ወደ መልካም ነገር) መቀየር እንዳለባቸው
ነው የማስተምረው…፤…ወደ እኔም
ስትመጣም ለአሰልጣኞች የማስተምረውን
ነው የማደርገው፤ እኔም ከየትኛውም
አቅጣጫ የሚመጡትን ትችቶች ወይም
ተቋውሞዎች ወደ መልካም ነገር ቀይሬ ነው
የምወስዳቸው…ይሄን ስልህ ግን…?

ሀትሪክ፡- …ይሄን ስትለኝ ግን…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …ይሄን ስልህ
ግን…ትችቶች ሙያዊ ከመሆን አልፈው
ግለሰባዊ ይዘት ሲኖራቸው…ሰውን ሆን
ብሎ ለማጥቃት የሚወረወሩ ከሆነ እሱ
ላይ አልስማማም…፤…ትችት ነው ብዬ
ለመቀበልም ይቸግረኛል፡፡…ከዚህ ከፍ ሲልም
እንደ ሰው ቅርም ሊለኝ ይችላል…ምክንያቱም
እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝና፡፡

ሀትሪክ፡- …ከዚህ ቃለ-ምልልስ በፊት
በስልክ ስናወራ በቅሬታ መልክ ካነሳህልኝ
አንዱ ደሞዝህን በተመለከተ ጠቅሰን የፃፍነው
ዘገባ ይጠቀሳል…እሱ ዘገባ አልተዋጠልህም…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …ይሄን ነው
የምልህ…እንደዚህ አይነት ዘገባ ሆን ተብሎ
ግለሰብን ለማጥቃት ካልሆነ በስቀተር ለእግር
ኳሱ ምንም የሚጠቅመው ነገር የለም፤እውነት
ለመናገር የምትዘግቧቸው ዘገባዎች ለእግር
ኳሱ፣ለስፖርት ቤተሰቡ፣ለተጨዋቾች፣
ለአመራሮች፣የሚጠቅሙ የሚያግዙ እኔንም
ራሱ እንደ አንድ ሙያተኛ የሚለውጡ ቢሆኑ
ነው የሚመረጠው፡፡…ደሞዝን በተመለከተ
እናንተ ያቀረባችሁት ዘገባ ከሙያችሁ ውጪ
አካውንታንት የመሆን ባህሪን የያዘ ዘገባ
በመሆኑ…ጥቅሙ ብዙም አልታየኝም…፡፡
…ይሄን ያል መቶ ሺዎች ወይም ሚሊዮን
ብር ተከፈለው ወይም ያገኛል ብሎ መናገሩ
ለማንም አይጠቅምም፤እንደውም ከዚህ ይልቅ
እኔ ከአንተ የምጠብቀው ሌላ ነበር…

ሀትሪክ፡- …ከእኔ የምትጠብቀው ምን
ነበር…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …ከአንተ የምጠብቀው
ስፖርቱንም በቅርበት ስለምታውቀው
በዚህ ደረጃ በተሳሳተ መንገድ ተረድተህ
ትፅፈዋለህ ሣይሆን…የመን ሲያገኝ ከነበረው
ያነሰ ክፍያ ሀገሩን ለመርዳት ካለው ጉጉት
ቀንሶ የመጣ ሰው ነው…የሚል በእውነት
ላይ የተመሠረተ የተቆርቋሪነት ዘገባ ነበር
የጠበኩት፡፡ ምክንያቱም አንተም ረዥም ጊዜ
በግል የማውቅህም በዚህ ደረጃ ነው።እኔ
ወደ ሀገሬ የመጣሁት የመኖች ሲሰጡኝ
ከነበረው ገንዘብ ቀንሼ እንጂ የተሻለ አግኝቼ
አይደለም፤ምክንያቱም ሀገሬ የምትከፍለኝ
ሣይሆን ለሀገሬ የምሰጠውን አገልግሎት
ትልቅ ዋጋ ሰጥቼ ነው የመጣሁት፡፡ ስለዚህ
እንደዚህ አይነት ነገር ላይ መጠመድ ጥቅም
ያለው አይመስለኝም፡፡

ሀትሪክ፡- …ባህር ዳር ላይ ካትዲቯርን
2ለ1 በማሸነፋችሁ ህዝቡ ዳር እስከ ዳር
ተደስቷል፤አንተስ ውጤቱን ያስተናገድከው
እንዴት ነው…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …እኔም እንደማንኛ
ውም የኢትዮጵያ ህዝብ በጣም ተደስቻለሁ፤
ምክንያቱም ያሸነፍነው የአህጉሪቱ ታላቅና
ውጤታማ፣የምድቡም ከባድና ትልቅ ግምት
የተሰጠውን ብ/ቡድን ነው፡፡ ውጤቱ ከደስታም
በላይ ለእኛ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፤
የመጀመሪያው ወደ አፍሪካ ዋንጫው የማለፍ
ፉክክር ውስጥ የመለሰን ነው…ሁለተኛው
በቀጣይ ለሚኖሩን ውድድሮች ትልቅ የሞራል
ስንቅ የሚሆንና መነሳሳትን የሚፈጥርም
ነው፡፡ በራስ የመተማመን መንፈሳኝን ከፍ
በማድረግ የስነ ልበና ጠቀሜታውም ትልቅ
ነው፡፡እንደ ሙያተኛ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ጥሩ
የደስታ ስሜትም አሁንም ድረስ እየተሰማኝ
ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …በእርግጥ ከትዲቯርን
ማሸነፍ ትልቅ ውጤት ነው…፤…ነገር ግን
በብ/ቡድኑ፣በእናንተ በአሰልጣኞች፣በስፖርት
ቤተሰቡና በሚዲያው ላይ ከታየው ከፍተኛ
የደስታ ስሜት አንፃር “አንድ ቡድን ነው
ያሸነፍነው…?…ወይስ ብ/ቡድኑ ለአፍሪካ
ዋንጫ አልፎ ነው…?…የሚል ጥያቄ በውስጤ
እንዲጭር አድርጓል…፤…አብርሽ ደስታውና
ፈንጠዝያው ከልክ አላለፈም…?…ሰው
በተለይ ሚዲያው ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፍን
ያህል በጣም ያራገበው አይመስልህም…?…

ኢንስ.አብርሀም፡- …ግን እኮ ድሉን
ያራገቡት የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ብቻ
አይደሉም…ግርምትም የተፈጠረው እኮ በእኛ
ህዝብ ላይ ብቻ አይደለም…በመላው አለም
የስፖርት ቤተሰብ ጭምር ነው፤ዜናውን የሰሙ
ሁሉ ተገርመዋል፣ደንግጠዋልም። ውጤቱ
ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ በመላው አለም
የሚገኙ ሚዲያዎች እንዴት እንደዘገቡት
ኢንተርኔት ገብተህ ማየት ትችላለህ፤ታላላቅ
የቴሌቪዥን ቻናሎችንም እንደዛው፡
፡ Cafonline “Ethiopia shock cote d’
ivory”፣France 24፣super sport፣Euro
news፣BBC sport ብቻ ሁሉም አስገራሚና
አስደንጋጭ ድል እንደሆነ ዘግበዋል፡፡ ስለዚህ
በሀገር ቤት እንዲህ መሆኑ የሚያስገርም
አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡- …ትክክል ነህ…ትልቅ ሽንፋንም
በውጪ ሚዲያዎች ተሰጥቶታል…የእኔ ጥያቄ
በድሉ ለምን ተደሰትን ሳይሆን…ደስታው
ግድቡን ጥሶ አላለፈም ወይ…? ለአፍሪካ
ዋንጫ ያለፍን ያህል ይሄን ያህል መደሰትና
ማራገብ አያዘናጋንም ወይ…? …የአንተ
ብ/ቡድን የመጨረሻው ግብስ ካትዲቯርን
ማሸነፍ ብቻ ነበር ወይ? ነው ጥያቄዬ?

ኢንስ.አብርሀም፡- …የመጨረሻው
ግባችን በፍፁም ከትዲቯርን በማሸነፍ
የሚጠናቀቅ አይደለም፤ተጫዋቾቼም በደስታ
ባህር ውስጥ ሰጥመው ቀጣዩን እንዳይዘነጉት
የነገርኳቸውም አንተ በጥያቄህ ያነሳኸውን
ነው፡፡ በቀጣይ ለሚጠብቀን ፍልሚያም ሆነ
ማሳካት ለምንፈልገው ነገር ትልቅ የሞራል
ስንቅ ይሆናል እንጂ ይሄ የመጨረሻው
ግባችን አይደለም፤ወደ አፍሪካ ዋንጫ
ለማለፍ የምናደርገውን ጉዘ ያሳምርልናል
እንጂ ገና ጨዋታው ስላላቀ እንዳትዘናጉ
ነው ያልኳቸው፡፡ የደስታው መጠን ከፍ ብሎ
ሁሉም ነገር የተጠናቀቀ ያህል ተደርጎ መታሰብ
የለበትም በሚለው ሃሣብ እስማማለሁ፤ ከዚህ
ውጪ ህዝቡም፣ተጫዋቾቹም፣ ሚዲያውም
ለምን ተደሰተ…?…ለምን ከመጠን ባለፈ
አራገበው…?…ለምትለው…ደስታህ ከውስጥህ
ገንፍሎ ሲወጣ መቆጠብ አትችልም፡
፡ በባህር ዳር በነበረን ጨዋታ ከውጤቱም
በላይ በጨዋታው እንቅስቃሴ፣ እጅግ ተስፋ
ያለው ቡድን በመገንባቱና ያንን በማየታቸው
እንዲሁም በአህጉሪቱ የገዘፈ ስም ያለውን
በውጤትም በጨዋታም በልጠን በማሸነፋችን
የተፈጠረ ስሜት ለመሆኑ በእርግጠኝነት
መናገር እችላለሁ፡፡ ደግVም ይሄ ሁሉ ነገር
የታየው አንድ ሲኒየር ተጨዋች (ሽመልስ
በቀለ) ብቻ ባለበት 99% ወጣቶች ባለበት
ነው፤ከዚህ በመነሣት ተስፋ ያለው ብ/
ቡድን ተገንብቷል፣ተስፋ አለን በሚል ነው
ደስታቸውን የገለፁት እንጂ ለአፍሪካ ዋንጫማ
እንዳላለፍን ሁሉም ያውቃል፡፡ አሁን የታየው
ተስፋ እንዲበለፅግ እንዲያድግ በማድረግ
ላይ መጠመድ እንጂ በደስታ ሰክሮ ለ1
ደቂቃም ቢሆን መዘናጋት አያስፈልገውም፡፡
ከከትዲቯር ጋር የነበረን ጨዋታ ጥሩ የሚባል
ትዝታውንና ድሉን ጥሎልን አልፏል፤9ዐ
ደቂቃውም ተፈፅሟል፣ተጠናቋል።9ዐ
ደቂቃው የሰጠን የደስታ ስሜት ቀጣዩን 9ዐ
ደቂቃ እንዳያስረሳን መጠንቀቅና መሞከሩ
ክፋት የለውም፡፡ ከልክ በላይ መፈንጠዝ
መዘናጋትን ስለሚፈጥር ለተጨዋቾቼ
የነገርኳቸው ለአፍታም እንዳይዘናጉ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ኮትዲቯርን ማሸነፍህ
ለአንተ የተለየ ትርጉም አለው…?…የስልጠና
ህይወትህስ ትልቁ ውጤት ነው…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …በእርግጥ በየመን
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በኤሺያ ሻምፒዮና
ላይ የተሳተፍኩበት ውጤት አለኝ፤
የኮትዲቯሮችን የእግር ኳስ ታሪክና ውጤት
ወደ ኋላ ተመልሰህ ስትፈትሽ በአህጉሪቱ
ትልቁን ቡድን እንዳሸነፍን ትረዳለህ፤ቀደም
ባለው የእግር ኳስ ታሪካችን ከምዕራብ አፍሪካ
ብ/ቡድኖች ጋር ስንገናኝ እዚህም፣በሜዳቸውም
የምንሸነፍበት ሁኔታ ነው የነበረው…
ብዙዎቹ ወደዚህ ሲመጡ ባላቸው ነጥብ
እርግጠኛ ሆነው ሦስት ነጥብ ደምረው ነው
የሚመጡት…አሁን ግን ያንን አሮጌ ታሪክ
የቀየረ ውጤት ነው ያስመዘገብነው…ይሄ
በጣም ያስደስትሃል፤የሥልጠና ህይወትህ
ሌላው አስደሳች ምዕራፍም ያደርገዋል።በተለይ
ከጥሩ ብልጫ፣ከምትፈልገው አጨዋወት ጋር
ማሸነፍ በራሱ የተለየ እርካታ ይሰጥሃል፡
፡ በጨዋታ ሳንበልጣቸው እንዲሁ በተጠለዘ
ወይም በደካማ እንቅስቃሴ ከትዲቯርን አሸንፈን
ቢሆን እርካታ ላይሰጠኝ ይችላል፤ ነገር ግን
በተዘጋጀንበት፣በምናውቀው፣በምንፈልገው
አጨዋወት ትልቅ ቡድኖችን ማሸነፍ
እንደምንችል ማየቴ በራሱ ለእኔ ደስታ ብቻ
ሣይሆን ብዙ ትርጉም ሰጥቶኝ እንዲያልፍም
አድርጓል፡፡

ሀትሪክ፡- …ከትዲቯሮችን ያሸነፍነው
ከእነሱ ተሽለን ነው ብለህ ታምናለህ…?

ኢንስ.አብርሀም፡- መሻላችንንማ
መጠራጠር የለብህም፤ ምክንያቱም በእለቱ
ተሽለን ማሸነፋችንን ውጤቱም፣ ሚዲያውም፣
ራሣቸው ኮትዲቯሮችም የተናገሩት ነገር
ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ እኔ ከምለው ደግሞ
እናንተ የሚዲያ ሰዎች ብትናገሩ ይመረጣል፡
፡ እንደ እኔ ግን ከእነሱ ተሽለን ጨዋታውን
ተቆጣጥረን የምንፈልገውን አግኝተን
ስለመውጣታችን እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- አንተ ከምትለው በተቃራኒ
ከትዲቯሮች ራሳቸውን በራሣቸው
ነው ያሸነፉት ብለው የሚሞግቱ አሉ…
ትስማማለህ…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …“ራሣቸውን በራሣቸ
ው ነው ያሸነፉት” ማለት ምን ማለት ነው…?
…አልገባኝም?…(እንደመገረም እያለ)…

ሀትሪክ፡- …የመጀመሪያው ብ/
ቡድኑን ንቀው መግባታቸው ሲሆን…
ሌላው ደግሞ አንድ ቀን ሲቀራቸው ወደ
አዲስ አበባ መጥተው ልምምድ ሳይሠሩ
መምጣታቸው…ኤርፖርት ላይ ለረዥም
ሰዓት መጉላላታቸውም ተደምሮ ነው
ለሽንፈት የበቁት ብለው የሚከራከሩ አሉ
ትቀበላለዋለህ…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …እኔ ብዙውን
ጊዜ የሰበብ ሰው ስላልሆንኩ የሜዳ ላይ
እንቅስቃሴውን ብቻ አይቼ ነው የምፈርደው…
ከዚህ በፊት ከሀገር ውጪ ስንሸነፍ ውጪ
የደረሰብንን በደል ለሽንፈታችን ሰበብ አድርጎ
የማስቀመጥ ልምዱ የለኝም፤እንደዚህ
ምክንያት የሚደረደር ከሆነ እኮ እኛም
ርዋንዳም ማዳጋስካርም ስንሄድ በቂ የሆነ ሜዳ
አልተሰጠንም…ልምምድም በተሟላ ሁኔታ
አልሰራንም…መንገላታትም ደርሶብናል…ግን
ደግሞ ተሸንፈን መጥተናል…ግን የሰበብ ሰው
ስላልሆንኩ ለሽንፈታችን የደረደርኩት ነገር
የለም፤የተሸነፍነው ሜዳ ውስጥ በነበረው
እንቅስቃሴ ነው ብዬ ነው ዝም ያልኩት፡፡
ሌላው እነሱ አንድ ቀን ሲቀር የገቡት ለምን
ይመስለሃል…?

ሀትሪክ፡-አንተው መልስልኝ እንጂ…?…
ምናልባት በቀላሉ እናሸንፋለን ከሚል
ንቀት…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …(ሣቅ)…አይደለም
የአየር ንብረት አድቫንቴጃቸውን ለመጠቀም
እንጂ ብ/ቡድናችንን ስለናቁት አይደለም
አንድ ቀን ሲቀረው መጥተው በነጋታው
የተጫወቱት…፤…እንደውም ለውጤት
አልረዳቸውም እንጂ አንድ ሲቀራቸው
ገብተው በነጋታው መጫወታቸው አየር
ንብረትን በተመለከተ ተጠቃሚ ነው
የሚያደርጋቸው። ብዙ የሰሜንና የምዕራብ
አፍሪካ ብ/ቡድኖች ጠዋት ገብተው ከሰዓት
ተጫውተው የሚመለሱት እኮ ከንቀት
ሣይሆን የአዲስ አበባ አየር ንብረት ከባድ
ስለሆነ ያንን አድቫንቴጅ ለመጠቀም ነው፡
፡ ደግሞም እኮ ኮትድቯሮች ከጨዋታው
ሶስት አራት ቀን በፊት ቀድመን እንገባ
ቢሉም አይችሉም …ምክንያቱም እነሱም
እንደ እኛ ውድድር ላይ ነበሩ…ከኒጀር ጋር
ጨዋታ ነበራቸው…እኛም እነሱም ተመሳሳይ
ጨዋታ፣ተመሳሳይ ጉዞ ነው የነበረን…እኛም
ልክ እንደ እነሱ ባህር ዳር የገባነው አንድ
ቀን ሲቀረን ነው… የሪከቨሪ (የማገገም)
ፔሬዳችንም ተመሳሳይ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …የአሁኑ ኮትዲቯር በፕሮፌሽ
ናሎች የተሞላ ቢሆንም የወረደውና
ደካማው ብ/ቡድን ነው…ጠንካራው የኮትዲ
ቯር ብ/ቡድን በእነ ድሮግባ ዘመን ቀረ
ብለው የአሁኑን ኦሪጅናሉ የኮትዲቯር ብ/
ቡድን አይደለም ብለው የሚያሳንሱ አሉ
ትቀበለዋለህ…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …ምናልባት አንተም
ከአንተም ጋር ተመሳሳይ ሃሣብ ያላቸው
ወርቃማውን ድላችንን ለማሳነስ አስባችሁ
ካልሆነ የአሁኑ ለእኔ ጠንካራው የኮትዲቯር
ብ/ቡድን ነው…፤…ደግሞም አንድ ማወቅ
ያለብህ ነገር ሁሉም ጄኔሬሽን (ትውልድ)
የራሱ የሆነ ቡድን አለው፡፡ የእነ ድሮግባን
ዘመን ብ/ቡድን መወዳደር ካለበት አሁን
ካለው የእኛ ብ/ቡድን ጋር ሣይሆን በእነሱ
ዘመን ከነበረው ጋር ነው፤ከዚህ በተረፈ
የኮትዲቯር ብ/ቡድን አርሴናሎች በውድ ዋጋ
የገዙት ፔፔን የመሰሉ ታላላቅ ፕሮፌሽናል
ተጨዋቾችን ያካተተ፣በቅርቡም አለም ዋንጫ
ደርሶ የነበረ፣ብዙ ተተኪዎች ያሉት ትልቅ
ብ/ቡድን እንደሆነ እርግጠኝነት በተሞላበት
ስሜት ነው የምነግርህ፡፡

ሀትሪክ፡- …አይሆንም እንጂ ጨዋታው
የመደገም እድል ቢኖረው ኮትዲቯርን በዚህ
ውጤት ደግመን የማሸነፍ አቅሙ አለን
ብለው የሚጠይቁ ቢኖሩ ምን ትላቸዋለህ…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …አንደኛ ጥያቄህ
ጤነኛ አይደለም…ግን…ያም ቢሆን
ተጨዋቾቼ ላይ ባለው የራስ የመተማመን
መንፈስ ለምን ደግመን አናሸንፋም?…
እናሸንፋለን…! እንደውም ከዚህ የበለጠ
ውጤትም ልናስመዘግብ እንችላለን፡፡

ሀትሪክ፡- …እንደዚህ አይነት ጥያቄ
የማነሳልህ ያለ ምክንያት አይደለም…ከዚህ
በፊት ጅቡቲን በመከራ ከማሸፋችን በዩጋንዳ
በወዳጅነት፣በሩዋንዳ በቻን ከመሸነፋችን
አንፃር ያደረብኝ ስጋት ስላለ ነው…እንደው
አብርሃም አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ ጅቡቲን
ለማሸነፍ ሲቸገር የታየው ብ/ቡደን ላይ
ምን ተአምር ሰርተህ ነው ኮትዲቯርን በዚህ
ውጤት ለማሸነፍ የበቃኸው ብልህ ምን
ትመልስልኛለህ…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …ሌላ ምን
አይደለም…!…ሥራና ሥራ ብቻ ነው…፤…
ከጅቡቲ በኋላ ብ/ቡደኑ ላይ ብዙ ተደክሟል…
ብዙ ተሠርቷል።…በተለይ በድክመቶቻችን
ዙሪያ በአጭሩ የሠራነው ስራ ነው
ኮትዲቯሮችን በልጠን እንድናሸንፍ የረዳን…
ከዚህ በፊት ደጋጋሜ ተናግሬያለሁ…በወቅቱ
ጅቡቲን ብናሸንፍም ቡድኔ ባሳየው እንቅስቃሴ
ደስተኛ እንዳልነበርኩ ተናግሬያለሁ…
ለተጨዋቾቼም የነገርኳቸው ይሄንን ነው፡፡
ያን ጊዜ ተጨዋቾቹ ከእረፍት ነው የመጡት…
በዚያም በጣም ወቅሼያቸዋለሁ…ሊጉ
ቢቆምም እናንተ ለምንድነው የምትቆሙት
ብዬ ወቅሼያቸዋለሁ፡፡ ቆሞ የከረመ ያልሠራ
ተጨዋች ያለበትን ብ/ቡድን ጅቡቲ አይደለም
ማንም ሊያሸንፈው ሊፈታተነው ይችላል፡፡
መስራት ያስፈልግ ነበር…ሠርተናል…፤…
ያነው ወደ ለውጥ ወደ አሸናፊነት ያመጣን፡፡

ሀትሪክ፡- …ኮትዲቭዋሮችን 2ለ1
ካሸነፋችሁ በኋላ ከእነሱ ጋር የመገናኘት
እድሉ ነበረህ…?…ከነበረህ ስለሽንፈታቸውና
ስለ ኢትዮጵያ ብ/ቡድን ምን አሉህ…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …ሜዳ ላይ
እንዳያችሁት አሰልጣኙን “Hard Luck”
ለማለት ስሄድ ደስተኛ አልነበሩም…ነገር ግን
የቴክኒክ ዳይሬክተራቸውን አግኝቼው ነበር…
እንደ አጋጣሚ ሆኖ የቴክኒክ ዳይሬክተራቸው
የካፍ ኢንስትራክተር በመሆኑ ከእሱ ጋር
በደንብ እንተዋወቃለን…አንድ ማዕረግ
ውስጥ ስላለን ብዙ ጊዜ በተለያዩ የካፍ
ኮርሶች ላይ የመገናኘቱ እድል ስለነበር
በደንብ ነው የምንተዋወቀው…ከእሱ ጋር
ለተወሰነች ደቂቃም ቢሆን የማውራት
አጋጣሚው ነበረኝ…እሱ በጨዋታው ዙሪያ
ምንድነው ያለኝ በብ/ቡድኖችንም በውጤቱም
ያልጠበቀው ነገር ስለገጠመው እንደተገረመ
ነው ያጫወተኝ፡፡ “በጣም ሰርፕራይዝ
ነው ያደረጋችሁን፤በጣም የተጠና ጨዋታ
የሚጫወት፣ ብልጫ የሚወስድ ብ/ቡድን
ነው የገነባችሁት…በጣም ተገርሜያለሁ…
እንኳን ደስ አለህ…ይሄንን ጠብቀው Keep it
up’’ካለኝ በኋላ ምክሩንም ለግሶኛል “እኛም
በአንድ ወቅት እንደዚህ አይነት በወጣቶች
የተገነባ ብ/ቡድን ነበረን፤ብዙዎቹ ወደ ውጪ
ሲሄዱ ያ ቡድን ጠፋ…ስለዚህ አንተም ይሄ
እንቅስቃሴ እንዳይቀዘቅዝ እና እንዳይጠፋ
ፊፋና ካፍ የሚያዘጋጁትን የወዳጅነት ጨዋታ
ሳትጠብቅ ራስህ እየፈለክ ብ/ቡድኑን አሁን
ባለው ስሜት ይዘህ ለመጓዝ ሞክር…እኔም
በዚህ በኩል በምችለው መንገድ እረዳሃለሁ…”
ብሎኛል፤ከእዚህ ውጪ ያገኘሁትም
ያወራሁትም የለም፡፡

ሀትሪክ፡- …ኮትዲቯርን በማሸነፋችሁ
ህዝቡ ተደስቷል…የሚዲያውም፣የሰውም
ትልቁ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆናችኋል፤ ከዚህ
ጨዋታ በኋላ አብርሃም ራሱን የት ነው
ያስቀመጠው…?

ኢንስ አብርሃም፡- …ማለት…?

ሀትሪክ፡- …አብርሃም ራሱን እንደ ጀግና
መቁጠር ጀምሯል…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …በፍፁም አልጀመ
ረች…! አይጀምርምም…!…በእርግጥ ውጤቱ
ጥሩና ትልቅ ውጤት ነው…በአንድ ጀምበር
ድል ግን ራሴን ታሪክ ሰርተው ካለፉ ጀግኖች
ተርታ የማስቀምጥ ትንሽ አዕምሮ ያለኝ ሰው
አይደለሁም፡፡ እንደውም ከድሉ በ ኋ ላ
ራሴን ወደ ማኮፈስ ወደ ማጀገን ሣይሆን
የሄድኩት ኮትዲቯርን ስናሸንፍ በማሸነፍ
ውስጥ የተፈጠሩ ስህተቶችን እየለቀምኩ
እነሱ በሚታረሙበት ዙሪያ መፍትሔዎችን
እየነደፍኩ ነው ያለሁት…እስከዛሬዋ ቀን
ድረስ፡፡

ሀትሪክ፡- …በኮትዲቯሩ ጨዋታ በተለይ
የእለቱ ምርጥ ወይም ኮኮብ ነበር ብለህ
በተናጠል የምትጠራው ተጨዋች አለ…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …እኔ ሁሌም
ለተጨዋቾቼ የምነግራቸው ነገር አለ…
በተናጠል ስናየው አንደኛው ከአንደኛው
የሚበልጥበት ነገር ይኖራል…በብ/ቡድን
ደረጃ ግን አንዳችሁ ከአንዳችሁ
አ ት በ ል ጡ ም … የ ም ላ ቸ ው
ነገር አለ…ምክንያቱም እግር
ኳስ One man show
(የአንድ ሰው ትርኢት)
ብቻ አይደለም…የቡድን
ሥራ ነው…ከዚህ አንፃር
የማስበልጠው የለም…
ሁሉም ለእኔ የጨዋታው
ኮከቦችና ምርጦች ናቸው…፡፡

ሀትሪክ፡- …ብዙዎች የኮትዲቯሩን ድል
ከስፖርቱ ውጪ ትልቅ ትርፍ አሳይቶናል
በማለት ህዘቡ ስለ አንድነት፣ስለ ሀገር ስምና
ድል በጋራ ቆሞ የታየበት አጋጣሚ ነው
በማለት ጉዳዩን ከወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት
ጋር አያይዘው በመልካም ጎኑ የሚያነሱ አሉ
ይሄንን ታዝበሃል…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …እንደው በጨዋታው
ከነበረው ማሸነፍና መሸነፍ በዘለለ ተገኘ
የምለው ትልቅ ትርፍም ይሄ ነው፤አንድነትን
ሠላምን እየናፈቀ ያለ ህዝብ በሀገሩ ዙሪያ
እንዲህ ሰብሰብ ብሎ ስለድልዋ ሲዘምር ማየት
ለእኔ ከውጤቱም በላይ ነው። ኮትዲቯዋርን
በማሸነፍ አገኘን የምለው ትልቅ ትርፍም
ይሄንን ነው፡፡ በስታዲየም ውስጥ
የነበረው ድባብ…ከስታዲየም
ውጪ ይደርሱኝ የነበሩ
መልዕክቶችም የሚያረጋግጡት
ከእግር ኳስ ባለፈ ሀገራዊዋ
አንድነት ስለመፈጠሩና አጀንዳ
ሁሉ አስቀይሮ እንደነበር
ነው ብዙዎች የአንባ ስሜት
እየተናነቃቸው ሲገልፁልኝ
የነበረው፡፡ በዚህን መሠል ቦታ
ውስጥና ታሪክ ውስጥ መገኘት
ደግሞ እንደ እኔ ትልቅ ደስታ
ይሰጥሃል፡፡ ምክንያቱም ሀገር
ሠላም ስትሆን፣ሀገር አንድ
ስትሆን ነው ብ/
ቡድናችንም ጠንካራ የሚሆነው፡፡ እውነት
ነው የምልህ ለዚህ ተፈጠረ ለተባለው
አንድነት፣ ለሠላሙ ትንሽዬ እርሾ የምትሆን
ነገር በማበርከቴ ደስተኛ ብቻ ሳይሆን
ራሴንም እንደ እድለኛ ነው የምቆጥረው፡፡
እግር ኳስ ለሠላም፣ለአንድነት ትልቅ ኃይል
አለው…በፍቅር ያሰተሳሰራል፣የተራራቁትንም
ያቀራርባል፣ ልዩነትን አስወግዶ በአንድነት
እንዲዘምሩም ያደርጋል። አስታውሳለሁ በእነ
ሰውነት ቢሻው ጊዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫ
ስንመለስ እግር ኳስ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ
አስተሳስሯል፣አፈቃቅሯል፣ ለሀገራቸው
እንዲያነቡ፣ ለሀገራቸው እንዲዘምሩም
አድርጓል፡፡ ከዚህ አንፃር እግር ኳስ ትልቅ
መሳሪያ መሆኑን ነው የሚያሳየን፤ ይሄንን
መሳሪያ መንግስት በአግባቡ ሊይዘው ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡- … ከኮትዲቯር ድል በኋላ ፊትህ
በእንባ የታጠበበት፣ያለቀስክበት ሁኔታም
ነበር…በዚህ ደረጃ ስሜት ውስጥ የከተተህ
ምንድነው…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …(እንደ መተከዝ
ብሎ)…እ…እሱን አጋጣሚ…ዳግም
ባላስታውሰው እመርጣለሁ…ምክንያቱም
አሁንም ስሜቱ ከውስጤ አልወጣም…እ…
(በረዥሙ ከተነፈሰ በኋላ)…የተፈጠረው
ነገር ምን መሰለህ…?…ጨዋታው እንዳለቀ
ወደ መልበሻ ክፍል እየገባሁ ሣለ ተጨዋቾቹ
ወደ እኔ መጥተው “…ተመልካቾቹ
ይፈልጉሃል…”…ብለው መለሱኝ…ወደ
ሜዳው ስመለስ የስታዲየሙ ግለት ይፋጃል…
ህዝቡ በደስታ አሙቆታል…በማየው ነገር
እንደ አዲስ ደነገጥኩ፤የእኛን ህዝብ ያው
ታውቀዋለህ…በጣም ትሁት…በጣም
ጨዋና…የፍቅር ሰው ነው…፤…ለእኔ በጣም
ትንሽ ሰው የተከበረው ደጋፊ ከመቀመጫው
ተነስቶ የሰጠኝ ድጋፍና አቀባበሉ እኔ ለፉትቦሉ
ከሰጠሁት ጋር የሚመጣን አልነበረም…
ኢሚንት ለሆነችው ሙከራዬ የተሰጠኝ
ምላሽ ከምገምተው በላይ በመሆኑ የደጋፊው
ፍቅር አሸንፎኝ ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ
እንዳልከው ሳላስበው እንባዬ ከውስጥ ገንፍሎ
ወጥቶ እንዳለቅስ አድርጎኛል፡፡ ምክንያቱም
ይሄ ሁሉ ፍቅር…ይሄ ሁሉ ድጋፍ ለእኔ
አይገባኝም…(አይኖቹ መሬት መሬት እያዩ
እንደመተከዝ ብሎ)…ብቻ የማይገባኝ ነገር
ነው የሆነው…በስታዲየም የነበረው ደጋፊ
መሸከም ከምችለው በላይ ለእኔ በዚያ መንገድ
ስሜታቸውን ሲገልፁ በእንባ ምላሽ ከመስጠት
በላይ ሌላ ነገር የማድረግ አቅሙ ስላልነበረኝ
በእንባዬ አመሰግናለሁ ብያለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- …የባህር ዳር ስታዲየምና
ደጋፊው እድለኛ ነው…በኢንተርናሽናል
ጨዋታ ሽንፈት እንዳይኖር የሚሰጡት
ድጋፍ አስተዋፆው ከፍተኛ ነውና በእለቱ
የነበረውን የድጋፍ አሰጣጥንስ እንዴት ነው
የምትገልፀው…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …የባህር ዳር
ደጋፊ ለየት የሚለው በምን መሠለህ…?…
ስታዲየም ስትገባ ብቻ ጠብቆ የሚደግፍ
ደጋፊ አይደለም…ደጋፊው በጨዋታ እለት
ብቻ አይደለም የሚደግፍህ…ከገባንበት ቀን
ጀምሮ…ከጨዋታው በፊት በምናደርጋቸው
ትሬይኒንጎች፣ በሆቴል በሚኖሩን ቆይታ
ጭምር ነው የሚያበረታታህ መደገፍ
የሚጀምረው…ስታዲየም በጨዋታው ቀን
ያንን አሣድጎ፣አድምቆ መጥቶ በልዩ ድጋፍ
ነው የሚደግፍህ።ይሄ ለተጨዋቾች ትልቅ
የሞራል ስንቅም ነው…ተጨወቾችም በሙሉ
ስሜት ደም ሰጥተው እንዲጫወቱ ሁሉ
የነዳጅ ያህል የማቀጣጠል ትልቅ አቅም ያለው
ድጋፍ ነው የሚሰጡህ…፤…በአጭሩ ደጋፊው
ከጀርባችን ሆኖ አንደ 12ተኛ ተጨዋች
የደገፈን ህዝብ ነው።ይሄንን ደጋፊ ሁሌም
እንዳመሰገንኩ ነው…አሁንም ይሄንን ምርጥ
ደጋፊ ዝቅ ብዬ እጅ እነሣለሁ፡፡ ሌላ ስለ
ደጋፊው ስናነሳ ይህቺን አጋጣሚ በመጠቀም
ማመሰግን ያለብኝ ሌላ ደጋፊ ደግሞ አለ፡
፡ ጨዋታው መቐለ ላይ ይካሄዳል ተብሎ
ስለነበር ዝግጅታችንን እዛ ነበር ያደረግነው…
የመቐለ ህዝብ ዝግጅታችንን ከጀመርንበት ቀን
ጀምሮ ስታዲየም በመግባት…በየሄድንባቸው
ቦታዎች ሁሉ ኮትዲቯሮችን ታሸንፋላችሁ
በርቱ” ብሎ መርቆ አበርታቶ ነው የሸኘንና
በዚህ አጋጣሚ የመቐለን ህዝብና የትግራይ
ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሸነር ወ/ሮ ገነትን ከልብ
ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- አሁን ኮትዲቯርን በማሸነፍ
ወደ ፍክክር ውስጥ ተመልሰሃል…ጊዜው ገና
ቢሆንም ይሄ ውጤትህ ስለካሜሮኑ የአፍሪካ
ዋንጫ ከወዲሁ ማሰብ እንድትጀምር
አድርጎሃል…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …በቀጥታ ለጥያቄህ
መልስ ከመስጠቴ በፊት ከ3 ወር በፊት የአፍሪካ
ዋንጫ የምድብ ድልድል ሲወጣ የተጠየኩትና
የሰጠሁት መልስ ነበር፤ የእናንተን ሚዲያን
ጨምሮ ሁሉም የውጪውም ሣይቀር ከእኛ
ጋር የተደለደሉትን ብ/ቡድኖች ክብደት
ለማሣየት ምድቡን የሞት ምድብ ነው
ብላችሁ እስከመጥራትና አንደምንቸገር
ገልፃችሁ ነበር…በእርግጥ ከብ/ቡድኖች አንፃር
ስታየው ጠንከር ያለ ይመስላል…ለእኔ ግን
የምድብ ተጋጣሚዎቻችንን የሚመጥንዝግጅት እስካደረግን ድረስ ወደ አፍሪካ ዋንጫ
ለመግባት ምንም የሚያዳግተን ነገር የለም
ብዬ ነበር፤አሁንም ቢሆን ተስፋችን የጨለመ
ጉዳይ አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡- ስለዚህ በ2ዐ21 ብ/ቡድን ይዤ
ካሜሩን ላይ ታዩኛላችሁ እያልክ ነው…?
ኢንስ.አብርሀም፡- …ከሠራን…አሁን
የያዝነውን ካስቀጥልን Why not? (ለምን
አይሆንም?)…ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካ ዋንጫ
መመለስ የማስቻል ሥራ እሰከሰራን ድረስ
ትመለሳለች የሚል ብሩህ ተስፋ ነው በውስጤ
ያለው…፤…እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ ብሩህ
ነው ተስፋዬ…፡፡

ሀትሪክ፡- …አብርሽ ይቅርታ አድርገልኝና
መመኘትህን ባልቃወመውም ቀደም ሲል
ለአፍሪካ ዋንጫ አሳልፍለህ ብለህ ካለመሳካቱ…
ቻን እገባለሁ ብለህ ካለመግባትህና ከኦሎምፒክ
ማጣሪያ ውጪ ከመሆንህ አንፃር አሁን
የምትለውን አምኖ መቀበል አያስቸግርም
ትላለህ…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …(ሣቅ እያለ)
በመጀመሪያ ታረም ከአፍሪካ ዋንጫ ውጪ
አደረክ ላልከው እኔ አልጠየቅም…

ሀትሪክ፡- …ማለት…?…ብ/ቡድኑ በአንተ
የአሰልጣኝነት ዘመን አይደለም እንዴ ከግብፁ
የአፍሪካ ዋንጫ ውጪ የሆነው?…አንተ
ያልተጠየክ ማን ሊጠየቅ ነው…?
ኢንስ.አብርሀም፡- …እኔ በወቅቱ
ከፌዴሬሽኑ ጋር ስዋዋል ለግብፁ የአፍሪካ
ዋንጫ አሳልፋለሁ የሚል ቃል አልገባሁም…
ወደ ብ/ቡድኑ ስመጣ በተጀመረ ውድድር
ስለነበር ልሞክር ነበር ያልኩት፤ብ/ቡድኑን
ልይዝ የቻልኩት በዚህ መልኩ ልሞክር በሚል
እንጂ አሣልፋለሁ የሚል ቃል አልወጣኝም፡፡

ሀትሪክ፡- …የብ/ቡድኑስ ይሁን
አልከራከርህም…ለቻን የአፍሪካ ዋንጫስ ብ/
ቡድኑን አሳልፋለሁ ብዬ ቃል አልገባሁም ብለህ
ልትክድ ነው አብርሽ…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …ተው እንጂ…!…
መካካድ የሚለውን ቃልስ ምን አመጣው…?…
እንዲህ ከማለትህ በፊት እውነታውን ከአንደበቴ
አዳምጥ…

ሀትሪክ፡- … እሺ.. ቀጥል…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …መጀመሪያ የቻን
ውድድር በሀገራችን ይዘጋጃል ተብሎ ስለነበር
በዚህ ውድድር ላይ ጠንካራ ብ/ቡድን ይዤ
እቀርባለሁ ብዬ ነበር የተናገርኩት…፤…እንደ
አጋጣሚ ግን የማዘጋጅት እድሉ ከሀገራችን
ተነጥቆ ለሌላ ተሰጠ…በመሃል ውድድር ውስጥ
እንድንገባ ተደረገ፡፡ ያም ቢሆን በምንችለው
መንገድ ተወዳድሬ ከቻን በክብር ነው
የወጣሁት፡፡

ሀትሪክ፡- …እንዴ አብርሃም ምን እያልከኝ
ነው…ሰውነት ቢሻውና ዮሐንስ ሳህሌ ያሰኩትን
የቻን ተሳትፎ ማሳካት ተስኖህ ከውድድር
ወጥተህ…በክብር ነው ከቻን የወጣሁት ማለት
ምን ማለት ነው…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …ከቻን ውድድር
መውጣት ሳይገባን ነው የወጣነው…ከዚህ
በፊትም ደጋግሜ ተናግሬያለሁ…ውጤቱ
ቡድናችንን የሚገልፅ አልነበረም…የሚገባንንም
አላገኘንም…

ሀትሪክ፡- …አብርሽ እኔ እንድትመልስልኝ
የፈለኩት የቻን ተሳትፎን ማሳካት ተስኖህ
በክብር ነው የወጣሁት ማለትህ ስላልገባኝ…
እሱን ግልፅ እንድታደርግልኝ ነው…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …በውጤት ደረጃ
ስትመዝነው ትክክል ነህ አያስደስትም…
ምከንያቱም ወደ ቻን ሻምፒዮና
አላለፍንም፤እንዳልኩህ ግን ውጤቱ በትክክል
አይገልፁንም… መቐለም ርዋንዳ በነበረን
በሁለቱም የደርሶ መልስ ጨዋታ ብልጫ
ወስደን እንጂ በሚያሳፍር እንቅስቃሴ ተሸንፈን
አይደለም ከቻን ውጪ የሆነው…አለማለፋችን
የሚያስደስት ባይሆንም በሚያሣፋር መልኩ
ሳይሆን በልጠን ተፎካክረን ነው ከውድድር
የወጣነው ለማለት ነው፡፡ መቐለ ላይ
ያስመዘገብነው ውጤት ነው ዋጋ ያስከፈለን
እንጂ ሩዋንዳ ባደረግነው ጨዋታ በልጠን
አስጨንቀን 1ለ1 ሆነን ነው ከውድድር ውጪ
የሆነው ለማለት ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ከኦሉምፒክ ማጣሪያ ውጪ
ለሆንከውስ የምትሰጠኝ ምክንያት ምንድነው?

ኢንስ.አብርሀም፡- …አንተን ጨምሮ
አንዳንድ ሰዎች ከኦሎምፒክ ማጣሪያ ውጪ
እንደሆንኩ አድርጋችሁ ታነሳላችሁ…

ሀትሪክ፡- …ይሄ እኮ በአደባባይ የታየ
እውነት እኮ ነው…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …በመጀመሪያ እንዲህ
ከማለትህ በፊት ወደ ኦሎምፒክ ብ/ቡድን
እንዴትና ለምን እንደመጣሁ ማወቅ ነው
ያለብህ…፤…እኔ ወደ ኦሎምፒክ የመጣሁት
ጃፓን 2ዐ2ዐ ማጣሪያውን አልፈን የመግባት
ግዴታ ተሰጥቶኝ አይደለም፡፡ እኔ ኦሎምፒክን
እንድይዝ የተደረገው ወይም የያዝኩት ኢትዮጵያ
ተተኪ ወይም Shadow team (ሁለተኛ ቡድን)
እንዲኖራት ብቻ ነው…ከዚህ ውጪ የተሰጠኝ
ተልዕኮ የለም፡፡ ደግሞም አንተን አንድ ነገር
ልጠይቅህ…ኦሎምፒክ ዝም ብሎ ይገባል…?…
ምንም ነገር ሳይሠራ ኦሎምፒክ ውስጥ መግባት
ተፈልጎ ነበር እንዴ…?…ኦሎምፒክ ለመግባት
እኮ ለዚያ የሚያበቃ ስራ መስራትን ይጠይቃል፡
፡ እኔ ግን ኦሎምፒክ ለመግባት ብዬ ብ/ቡድኑን
አልያዝኩም፡፡

ሀትሪክ፡-.. ከዚህ ከኦሎምፒክ አሰልጣኝ
ነትህ ጋር በተያያዘ አንድ ሲቀርብብህ የነበረ
ወቀሳ ነበር…አንተ ዋናውንም፣የኦሎምፒክ ብ/
ቡድኑንም ጠቅልለህ በመያዝህ ሀገሪቱ ላይ
ሌላ አሰልጣኝ የለም እንዴ…?…እሱ ሁሉንም
ጠቅልሎ የማይዘው…?…በማለት የሌሎች
አሰልጣኞችን የመስራት ዕድል እንደዘጋህ ተደርጎ
ስትወቅስ ነበር…ወቀሳውን ትቀበለዋለህ…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …እኔ የሙያተኞችን
እድል በመዝጋት አልታወቅም፤እንደውም
ሙያተኞች በብዛት ወደ ስልጠናው እንዲመጡ
በማድረግም በማገዝም ነው የምታወቀው።
ፌዴሬሽኑ የኦሎምፒክ ብ/ቡድንን እንድንይዝ
ሲወሰን አሁን የተባለው ቅሬታ እንዳይፈጠር
ጠይቀናል፤በፌዴሬሽኑ በኩል የተሰጠን ምላሽ
ግን እናንተ ደርባችሁ ብትሠሩ በጣም ጥሩ
ነው፤ ምክንያቱም በማለትም አንደኛ የዋናው ብ/
ቡድን አጨዋዋት ኦሎምፒክ ያሉት ተተኪዎች
እንዲለምዱት እንዲያውቅት ይረዳል…በዚህም
ወደ ላይ ሲወጡ አይቸገሩም የሚል ሲሆን…
ሌላው ደግሞ የአቅም ውስንነት ስላለ እናንተ
ደርባችሁ ብትሠሩት ይመረጣል የሚል
አሳማኝ ነገር ስለቀረበልን እንጂ ሙያተኞችን
ለመጋፋት ያደረግነው ነገር አይደለም።ደግሞም
አሁንም መሰራት ለሚፈልጉ በሩ ክፍት ነው…
ፌዴሬሽኑም የአቅም ውስንነት ካልሆነ በስተቀር
ሙያተኛውን አብዝቶ የመሰራት ፍላጎቱ ጥሩ
እንደሆነ ነው የምረዳው፡፡

ሀትሪክ፡- …በብ/ቡድን አሰልጣኝነት ከ14
ወራት በላይ አስቆጥረሃል…አብርሃም ረዥም
ወራት የዝግጅትና የውድድር ጊዜ እንደማግኘቱ
የቆይታውን ያህል ውጤታማ ጉዞ አላደረገም
ብለው ስምህን ለሚያነሱ ምን ትቀበለዋለህ…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …በከፊል ነው የምቀ
በለው…!…ምናልባት በአሃዝ፣ በቁጥር ደረጃ
ስታያቸው ላያስደስቱ ይችላሉ…ነገር ግን
ቡድኑ እያሳየ በመጣው እድገትና ፐርፎ
ርማንስ (ብቃት) እኔ እደሰትበታለሁ…ግን
ሁላችንም አንድ ነገር ማወቅ አለብን፤ ለእኔ
ተሰጠው ተብሎ የሚቆጠረው ወር ወይም
እኔ የሠራሁበት የ14 ወራት ጊዜ አንድን ብ/
ቡድን ለመገንባት እንደውም በጣም ትንሽ
ጊዜ ነው፤አንድን ጥሩ ብ/ቡድን ለመገንባት
በቂ የሚባል ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ እዚህ
ላይ ጀርመንን በምሳሌ ባነሣልህ ለአባባሌ
ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል…ጀርመኖች ኳስ
የማያባክን ኢኮኖሚካል ፉትቦል የሚጫወት
ብ/ቡድን ለመገንባት በትንሹ 4 አመት ነው
የወሰደባቸው፤የዘሩትን ፍሬ ለመልቀም አራት
አመታትን በትዕግስት መጠበቅ ነበረባቸው…
ጠበቁ ተሳካላቸው፤የአለም እግር ኳስ ላይ
የነገሱበት ዘመንም መጣ፡፡ አሰልጣኝ በማባረርና
በመቅጠር በመጠመድ ተስፋውን ማፍረስንም
አልመረጡም…አሰልጣኝ ዮሐኪም ሎው ከ1ዐ
አመት ላላነሰ ጊዜ የብ/ቡድኑ አሰልጣኝ ሆነው
ቆይተዋል፡፡ ይሄ ነገር የሆነው እኮ እንግዲህ
ሁሉም ነገር በተመቻቸበት ሀገር ነው…ምንም
ነገር ባልተመቻቸበት የተረጋጋ ሊግ (ውድድር)
በሌለበት ሀገር በአንድ አመት ምን አይንት
ተዓምር እንዲፈጠር ነው የተፈለገው? በአንድ
ጀምበር ውጤት ካልተወለደ የምንል ከሆነ
ለእኔ የዋህነት ነው፤የሚሻለን አብርሃም ይሄን
ያህል ወር አስቆጠረ ብሎ ከመቁጠር…ቲሙ
እያሳየ ያለውን እድገትና ለውጥን መቁጠሩ ነው
የሚሻለው…፤…እድገትና ለውጡን እየቆጠርን
ከሄድን ነገ የተሻለ አሸናፊ ብ/ቡድን መፍጠር
እንችላለን። ስለዚህ አሁንም ቢሆን ለእኔ ብቻ
ሣይሆን ለማንኛውም አሰልጣኝ የተሻለ ነገር
እንዲሠራ ጥሩ ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ
በቂ ጊዜ ነው መሰጠት ያለበት፤አሁንም ቡድኑ
ሳይሠራ ውጤት ላይ ብቻ መንጠላጠል፣ ጊዜያዊ
ውጤት የማያጓጓን ከሆነ የትም አንሻገርም፡፡

ሀትሪክ፡-… ብዙ ጊዜ ስትናገር ስሰማ
ኳስ ሳያባክን የሚጫወት ቡድን ስትል
እሰማለሁ፣ይሄ ንግግርህ አብርሃም አዲስ
የጨዋታ ፍልስፍና መከተል ጀምሮ ይሆን?
የሚልጥያቄፈጥሮብኛል፤ለመሆኑ የአንተ
ፍልስፍና ምንድነው?

ኢንስ.አብርሀም፡- …ምንም የተለየና
አዲስ ነገር የለም፤ ኳስን ለረዥም ጊዜ ሳያባክን
መቆየት የሚችል ብ/ቡድን መፍጠር ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ይሄ ማለት…ተጠጋግቶ…
ተረዳድቶ…የሚባለው አይነት የሃሣብ ጨዋታ
ማለት ነው…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …ተጠጋግቶ ምንድነው
… ? …በእርግጥ በእግር ኳስ ተጋጋዘህ
ተረዳድተህ ነው የምትጫወተው፤ ምክንያቱም
የቡድን ጨዋታ ስለሆነ…በነገርህ ላይ ተጋግዞ
የሚለውን እስማማበታለሁ፤ ተጠጋግቶ
የሚለውን ግን በእግር ኳስ የተቀመጠ ዲስታንስ
(ርቀት) ስለሌለ ከዚህ ውጪ ተጋጋዘው መሄድ
እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡ ሁለተኛ ለተጋጣሚ
ቡድን ስፔስ (ቦታ) በሰጠህ ቁጥር አዋጪ
ስላለሆነ ተቀራርበን መጫወታችን አዋጪ
ነው፤አጭርና ፈጣን የሆኑ ኳሶችን ለመቀበል
መቀራረባችን ትክክል ነው።ከዚህ በተረፈ ግን
ቡደኑ ሲጫወት ብልጫ የሚወስድበትን ነገር
መደገፍ ይመረጣል ስያሜው ምንም ይሁን
ምን፡፡ በአብዛኛው የምንጫወተው አጭርና
ፈጣን ኳሶችን ስለሆነ መጠጋጋታችን ወይም
ተጋጋዘን መጫወታችን አዋጪ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን… በደንብ ገብቶኛል…
ሌላው አብርሃም ብ/ቡድኑ ውስጥ አዲስ
አብዮት አምጥተሃል…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …ማለት…?

ሀትሪክ፡- …ይሄ Ice Bath….የFood Nutrition
ባለሙያና ሌሎች አዳዲስ ነገሮች አምጥተሃል ማለቴ
ነው…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …ብዙ ሰዎች ለአንድ
ቡድን ውጤታማነት ስልጠና ብቻውን እንደሆነ
አድርገው ያስባሉ…ግን አይደለም፤ከስልጠናው
በተጨማሪ ለስኬት የሚያበቁ በርካታ
ስራዎችም መሠራት አለባቸው፡፡ ከኮትዲቭዋር
ጋር ከመጫወታችን በፊት ኢትዮጵያዊያን
ተጨዋቾች በሁለት ቀን ልዩነት መጫወት
አይችሉም ይደክማሉ ተብሎ ነበር፡፡ እኛ
ለማዳጋስካር ጨዋታ ስንዘጋጅ ከኮትዲቭዋር
ጋርም ስለነበረብን እያሰብን ነው፡፡ ቅዳሜ
ከማዳጋስካር ጋ ተጨውተን እሁድ ተጉዘን
ሠኞ አዲስ አበባና ባህርዳር ገብተን ማክሰኞ
ኮትዲቫዋርን ስለምንገጥምና ከፍተኛ የጉዞ
መደራረብና ድካም ስለሚኖር ያደረግነው ነገር
ምንድነው በማዳጋስካር ጨዋታ ላይ ያልተሰለፉ
ልጆች ብቻ ልምምድ እንዲሠሩ አድርገን
የተጨወቱት ተጨዋቹ ግን Ice Bath እንዲገቡ
ነው ያደረግነው፡፡ ይሄን ያደረግነው ደግሞ ቶሎ
እንዲያገግሙ (Recovery time) እንዲገኙ
ነው፤ ሌላው የተጫወቱትና ያልተጫወቱት
ተጨዋቾት የሚመገቧቸውና የሚጠጡት ነገርም
የተለያዩ ነበሩ፡፡ ይሄንንም ስናደርግ የነበረው
ቶሎ እንዲያገግሙ(Recovery) እንዲያገኙ
ነው፡፡ ከብ/ቡድኑ ኒውትሪሽኒስት ዶ/ር ተስፋዬ
አማካይነት ለዛ የሚረዱ ስራዎችን ስንሰራ ነበር፡
፡ ሌላው ደግሞ Anti Recovery ቶሎ ማገገም
እንዳይችሉ የሚያደርጉ ነገሮችን ማስቀረት
ነበር፡፡ ለምሣሌ በፊት ሳውና በዛ የመጠቀም
ሁኔታ ነበር፤ ይሄ ሪከቨርን (ቶሎ ማገገምን)
የሚጎዳ በመሆኑ ሳውና ባዝን ከልክለናል፡፡
በሞቀ ውሃ መታጠብንም እንደዛው፤ተጨዋቹ
ቶሎ ለማገገም (Recovery) ለማድረግ
በቀዝቃዛ ውሃ መታጠብ አለባቸው፤በሙቅ ውሃ
የሚታጠብ ተጨዋች ካገኘሁ ልቀጣ እችላለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- …እንደ ማንቸስተር ሲቲው
አሰልጣኝ አንተም የብ/ቡድን ተጨዋቾች
የሞባይል ስልክ እንዳይጠቀሙ ሕግ አውጥተሃል
አሉኝ ትክክል ነኝ…?

ኢንስ.አብርሀም፡-…አዎን ትክክል ነህ…
(ሳቅ)…ብዙ ሰዎች ለምን ይሄን ታደርጋለህ?
ይሉኛል…ግን ይሄን ያመጣሁት እኔ
አይደሁም፤ጊዜው የፈቀደው ነገር ነው፡፡
ሞባይል ስልክ ከልክ በላይ መጠቀም በራሱ
Anti Recovery ነው፡፡ ከዚህ መነሻነት እኔም
ለጨዋታ 72 ሰዓታት ሲቀረን ጀምሮ ማንኛውም
ተጨዋች ከምሽቱ 4፡ዐዐ ሰዓት በኋላ ሞባይል
ስልክ መጠቀም አይችልም፤ከተጠቀሰው ሰዓት
በኋላ ሁሉም ተጨዋቾች ሞባይላቸውን
ሰብስበው ረዳቶቼ ጋር ነው የሚያስቀምጡት።ይሄ
ተገቢ እረፍት ለማድረግ፣ትኩረታቸው
እንዳይሰረቅና በሶሻል ሚዲያው የሚፃፉ ነገሮች
እንዳይረብሻቸው፣በሠላም እንዲተኙ ይሄን ሕግ
በብ/ቡድኑ ውስጥ አውጥቻለሁ፤ መጀመሪያ ላይ
ተጨዋቾቹ አዲስ ስለሆነባቸው አንገራግረው
ነበር፤አሁን ግን እነሱም ስላመኑበት ራሳቸው
ሰጪ ሆኑ፡፡ “ለካ ሞባይል ከእጃችን ሲርቅ ጥሩ
እንቅስቃሴ እንተኛለን” ብለው መመስከርም
ጀምረዋል፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ ከ72 ሰዓታት
በኋላ 9ዐ ደቂቃ ሳይደክማቸው የመጫወታቸው
ምስጢርም ይሄው ነው፡፡ ሌላው ጨዋታ
ከተጠናቀቀ በኋላ እረፍት እንዲያደርጉ በሚል
የተሳሳተ አስተሳሰብ ስንለቃቸው ነው የኖርነው፡
፡ ሣይንሱ ግን ምን እንደሚል ትውቃለህ?
“ጨዋታው እንደተጠናቀቀ እስከ ሚቀጥለው
ትሬይኒንግ ጠብቃቸው ነው” እኛ ግን
በተቃራኒው ልጆቹን ከጨዋታ በኋላ ልቀቃቸው
የሚል ነገር የተማርን ይመስል ስንለቃቸው
ነው የኖርነው፤አንድ በግልፅ መነጋገር ያለብን
ተጨዋቾች ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ወዴት
ነው የሚሄዱት? ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው
የሴት ጓደኛው ጋር፣አንዳንድ ልቅ መዝናኛ
ቦታዎች፣ ከተነፋፈቁት ጓደኞቹ ጋ ለመደሰት
ነው የሚሄደው እንጂ እንደተባለው በአግባቡ
እረፍት አይወስድም። ተጨዋቾች በጨዋታ
ደክመው፣ከፍ ሲልም ጉዳት ደርሶበት
ይሆናል እረፍት ብለህ የምትለቀው…በዚህ
ሁኔታ መልቀቅ ግን ሌላ ተጨማሪ ጉዳት
እንዲያስተናግድ ነው የምትለቀው፤ ስለዚህ ዛሬ
ተጫውቶ በነጋታው እረፍት ብለህ ከምትለቀው
በነጋታው ጠብቀኸው በሚቀጥለው ቀን
በመልቀቅ መጠበቁ ነው የሚመረጠው፤እኔም
ይሄንን ለተጨዋቹ ጥቅም ስል ተግባራዊ
እያደረኩ ነው፡፡ በመጨረሻ በብሔራዊ ቡድኑ
መጣ ብዬ አንድ የማነሣልህ ነገር የስፖርት
ስነ-ልቦና ባለሙያ እያመጣን ትምህርት
እንሰጣለን፤ከዚህ ውጪ አዲሱ ነገር ቪዲዮ
አናሊስት አለን…

ሀትሪክ፡- …ቪዲዮ አናሊስትም አለው ብ/
ቡድኑ…?

ኢንስ.አብርሀም፡- …አዎን አለ…በአለም
ላይ የቪዲዮ አናሊስስ የተጀመረው ከ2ዐ1ዐሩ
የአለም ዋንጫ በኋላ ነው…እኛ ሀገር ግን ዘግይቶ
ነው የገባው፡፡ አሁን አለም ከጌም አናሊስስ ወደ
ትሬይኒንግ አናሊስስ በተጨማሪ እየተሸጋገረ
ነው፤በትሬይኒንግ ሰዓት ተጨዋቾች የሠሩት
ያሳዩት ብቃት (Performance) ይገመገማል…
ከዚያ በኋላ ነው ወደ ጨዋታ የሚገባው፡፡ ማን
ምንድነው…?የሚለውን ትሬይኒንግ ላይ በዚህ
መንገድ ካልገመገምከው ከባድ ነው የሚሆነው፡፡
አሁን ይሄንን ሁሉም የአውሮፓ ሀገሮች ጥቂት
የአፍሪካ ሀገሮች እየሠሩት ነው፤አሁን በእኛ ብ/
ቡድን ውስጥም ከጌም አናሊስስ ወደ ትሬይኒንግ
አናሊስስም አየገባን ነው…ትሬይኒንጎችን ቀርፀን
እየሠራንበት ነው፡፡ ሌላው በፕሪሚየር ሊግ
አሰልጣኞችና በእኛ መካከል ያለውን ግንኙነት
ጤናማ ማድረግ ነው፤ ብ/ቡድኑ ጨዋታ
ጨርሶ ተጨዋቹ ወደ ክለባቸው መመለሳቸውን
ለአሰልጣኞች መንገር ብቻ ሣይሆን ተጨዋቾቹን
ለቀው በትዕግስት ስለጠበቁን አመሰግኛለሁ፡፡
ከዚህ በኋላም ከእነሱ ጋር በመሆን የብ/ቡድን
ተጨዋቾችን እንከታተላለን፤ይሄ መተጋገዝ
ውጤታማ ብ/ቡድንን እንደኖረን ያግዛል፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየዲሲፕሊን ውሳኔዎችዲሲፕሊን ውሳኔ

የዲሲፕሊን ውሳኔዎች

ገዛኸኝ ደሳለኝ (ሸገር ከተማ) : ክለቡ ከ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው የ26ኛ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በዝናባማው ጨዋታ በመቻል ሲረታ የጣናው ሞገድም አሸንፏል

እጅግ በከባድ ዝናብ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ መቻል የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን 3ለ1...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሀድያ ሆሳዕና ፣ ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ ወሳኝ ድል አግኝተዋል

በሊጉ የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን መርሀግብር ሀዋሳ ከተማ ወደ ሊጉ መሪ የሚጠጋበትን ዕድል...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ፈረሰኞቹ በድል ሲቀጥሉ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋም አሸንፈዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድሉን ወደ ቋቱ ሲከት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጨዋታ ብልጫ...