“በእርግጠኝነት የብሔራዊ ቡድኑ ቋሚ በረኛ እንደምሆን እተማመናለሁ፤ ምንም ስጋት የለብኝም”ምንተስኖት አሎ /ስሁል ሽረ/

 

THE BIG INTERVIEW WITH MENTESNOT ALO

“ከሜዳ ውጪ ባለ ግጥሚያ ዳኛ ይያዝብሃል፤ የደጋፊ ጫና አይቻልምም ይባላል እኔ ግን አልገጠመኝም”
“በእግር ኳስ ጨዋታ ወሳኙ ቦታ ግብ ጠባቂነት ነው ክሬዲት የሌለውም ግብ ጠባቂው ነው”

 

ደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ ጂንካ ትሰኛለች ከኢቫንጋዲዋ መንደር ሀመር 14 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኘው ጂንካ የ16 ብሔር ብሔረሰቦች መገኚያ ናት፡፡ ከተማዋ የራሣቸው ባህልና ወግ ተጨምሮበት በኢቫንጋዲ ጭፈራ በሚደምቁበት ቅርብ ርቀት መገኘቷ ለቱሪስት መስህብ አድርጓታል… ሀመር ኢቫንጋዲ ጭፈራ ላይ ሊገኝ ያሰበ ጂንካን መርገጡ የግድ ነው ይላል ከዚህች ከተማ የተገኘው እንግዳችን………በጂንካ የማጎ ፓርክን ጨምሮ በርካታ የሚጎበኙ ፓርኮች መኖራቸው ከተማዋን የጎብኚዎች ልብን እንድትይዝ አድርጓታል፡፡ በርግጠኝነት ይሄ አገላለፅ ከአንድ አስጎብኚ አንደበት የሚደመጥ ቢሆን አይገርመኝም ነበር….. ነገር ግን ከከተማዋ ማህፀን የተገኘው የዛሬው እንግዳችን ቱርክ ተጉዞ በአንታሊያ ስፖር ክለብ የ2 ሳምንት የሙከራ እድል ያገኘው የግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎ መሆኑ ግን እንድገረም አድርጎኛል፡፡ ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ቆይታ ያደረገው ምንተስኖት ከእግር ኳስ ወዳጅ ቤተሰብ የተገኘ ሲሆን በተለይ ግብ ጠባቂ ወንድም እንደነበረው አውግቷል፡፡ ስለ ቱርክ ጉዞው፣ ስለ ዋሊያዎቹ፣ ከስሁል ሽረ ጋር ስላለው ህልም፣ አውሮፓ ውስጥ የማን ዩናይትድ ግብ ጠባቂ ለመሆን ስላለው ህልም፣ ግብ ጠብቂ ለመሆን ለምን እንደፈለገ፣ ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት፣ የውጪ ግብ ጠባቂዎች መብዛት እንደሌለባቸው፣ ስለ ሊጉ ክለቦች የሜዳ አስቸጋሪነት፣ ለዚህ መድረሱ ትልቅ ባለውለታው ስለሆነው አሰልጣኝና ሌሎች ጉዳዮች የሰጠው ምላሽ ይህን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- ቤተሰቡ የስፖርት በተለይ የእግርኳስ ወዳጅ ነው አሉኝ እውነት ነው?
ምንተስኖት፡- አዎ…..በቤተሰባችን ከታላ ላቆቻችን ጀምሮ በስፖርቱ አልፈዋል ግብ ጠባቂም ነበሩ፡፡ ታላቅ ወንድማችን ተመስገን ወንድማገኝ ይባላል/ቅፅል ስሙ የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስና የብሔራዊ ቡድን በረኛ ደያስ ይባል ነበር/ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 4 ኪሎ ካምፓስ ሲማር የዩኒቨርሲቲዎች ውድድር ጎንደር ላይ ተዘጋጅቶ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋንጫ ሲወስድ ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብሎ ተሸልሟል፡፡ በነርሱ ጊዜ ለግብ ጠባቂ ብዙ ትኩረት የለምና ከፍ ባለ ደረጃ እንዳይጫወት አድርጎታል፡፡ እርሱን አይቼ ነው የተሳብኩት… ተከታይ ወንድሞቼም ለኳሱ ፍቅር አላቸው አባቴ እግር ኳስ በጣም ይወዳል… ይህን ይመስላል፡፡
ሀትሪክ፡- ከእግር ኳስ ቤተሰብ አድገህ፣ ግብ ጠባቂ የሆነ ወንድም ኖሮህ ወደ ግብጠባቂነት ባትሳብ ነው የሚገርመው?
ምንተስኖት፡- /ሳቅ በሳቅ/ እውነት ነው ራሱን የቻለ አስተዋፅኦ ነበረው
ሀትሪክ፡- አሁን እዚህ ደርሰህ ሲያይህ ምን ይሰማዋል?
ምንተስኖት፡- /ሳቅ/ በጣም ደስተኛ ነው ሁሌ እየደወለ ያበረታታኛል ይከታተለኛል ትልቅ ድጋፍ አድርጎልኛል በአጠቃላይ ሙሉ ቤተሰቤ ከጎኔ ሆኖ ድጋፍ ማድረጉ ለስኬት አብቆቶኛል መላው ቤተሰቤን ማመስገን እፈልጋው፡፡
ሀትሪክ፡- በተጨዋችነት ዘመንህ የት የት ተጫወትክ?
ምንተስኖት፡- ጂንካ ከተማ መነሻዬ ነው፡፡ ሰበታ ከተማ 1 አመት፣ ፋሲል ከነማ 1 አመት፣ ባህርዳር ከተማ 2 አመት፣ ስሁል ሽረ1 አመት ተጫውቻለው….. በ2ዐ1ዐ ባህርዳር ከተማ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚ የር ሊግ ሲያድግ የቡድኑ በረኛ እኔ ነበርኩ ባለፉት 5 አመታት ጥሩ እድገት እያሳየሁ ነው፡፡


ሀትሪክ፡- ከተወለድክበት ጂንካ ካንተ ውጪ የተገኙ ተጨዋቾች አሉ?
ምንተስኖት፡- አዎ ከቀድሞ ጠንከር አስናቀ፣ የቀድሞ የኢትዮ ኤሌክትሪክ አሰልጣኘ ብርሃኑ ባዩ በጉዳት ቢቸገርም የሲዳማ ቡናው ወንድሜነህ አይናለም ከኛ ከተማ የተገኙ ናቸው….. ከዚያ ውጪ በርካታ ተጨዋቾች ብሔራዊ ሊግና ከፍተኛ ሊግ የሚጫወቱ አሉ፡፡
ሀትሪክ፡- ግብ ጠብቂ ለመሆን ተምሣሌት አለህ? እንዴትስ ቦታውን መረጥከው?
ምንተስኖት፡- ማንም ሰው ግብ ጠባቂ ለመሆን ይፈራል ቦታው በጣም ሪስክ አለው በተቃራኒ ደግሞ ክሬዲት የለውም… በእግር ኳስ ጨዋታ ወሳኙ ቦታ ግብ ጠባቂነት ነው ክሬዲት የሌለውም ግብ ጠባቂ ነው አንድ አጥቂ በ9ዐ ደቂቃ ውስጥ ብዙ ግብ ስቶ በተጨማሪ ሰዓት ቢያስቆጥር የሳታቸው ሳይቆጥሩ ሳይነሱ ቡድኑን ይዞ ወጣ ተብሎ ይሞገሳል…. በተቃራኒው ግብ ጠባቂው 9ዐ ደቂቃ ሙሉ በርካታ ኳስ አምክኖ በተጨማሪ ሰዓት ቀላል የተባለ ስህተት ሰርቶ ቢቆጠርበት ቡድኑን ገደለ ይባላል በኔ በኩል ግብ ጠባቂ ሆኜ ኳስ አልጀመርኩም የክርስቲያኖ ሮናልዶ አድናቂ ነኝ በርሱ ቦታ ስጫወት ደስ ይለኛል፡፡ ሰፈር ውስጥ እርስ በርስ ስንጫወት ተጨዋች ነኝ በሪጎሬ ይለቅ ሲባል በረኛ ያደረጉኝና ኳስ መልሼ አሸንፈን እንወጣለን… በዚህ አጋጣሚ መናገር የምፈልገው መድምም ለገሰ የተባለ ሰው ነው ግብ ጠባቂነት እንደሚመጥነኝ ትልቅ ደረጃ እንደምደርስ እየመከረኝ ለዚህ ደረጃ ያበቃኝ…. አንዴ ጠራኝና ግብ ጠባቂነት ነው ያንተ ችሎታ… ሰውነትህ ቀልጣፋ በዚያ ላይ ገና ልጅ ነህ ብሎ አበረታቶ ለዚህ እንድበቃ አድርጎኛል በዚህ አጋጣሚ አመሰግነዋለው፡፡
ሀትሪክ፡-የመጀመሪያ ክለብን ታውቀዋ ለህ?
ምንተስኖት፡- ጂንካ ከተማ ነው…. በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ላይ መካፈል በ2ዐዐ6 ጀመርኩ.. 2ዐዐ7 ጂንካ ከተማ ጋር በብሔራዊ ሊግ ስካፈል የክለቡ 2ኛ ግብ ጠባቂ ሆኜ ተጫውቻለው፡፡ ወደ ሰበታ ስመጣ ደግሞ ኢዮብ ይልማ የተሰኘ አርቢትር ሁለት ጨዋታ በተከታታይ እኛን የመዳኘት እድል አገኘና መረቡን ሊፈትሽ ሲመጣ ግብ ካልገባብህ ቃል የገባሁት ነገር አለ በርታ የተሻለ ክለብ ትገባለህ አለኝ፡፡ በጨዋታው 1ለዐ ረታን… ሁለተኛው አርባምንጭ ኮንሶ ኒውዮርክ የሚባል ክለብ ጋር ስንጫወት አርቢትሩ ኢዮብ ነበር ዛሬ አለቅህም መረጃ እንለዋወጣለን ብሎ አበረታታኝ…. እንደገና ይህን ጨዋታ ከሜዳ ውጪ አድርገንም ረታን…. ስልኬን ተቀበለኝ ክረምት በመሆኑ በሰበታ ከተማ የተሳካ ሙከራ አድርጌ ክለቡን ተቀላቀልኩ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡
ሀትሪክ፡- የውጪ በረኞች በርከተዋል.. የኛን ልጆች ቦታ የሸፈኑት ስለተበለጥን ወይስ ክለቦች በሀገራችን በረኞች ስላልተማመኑ?
ምንተስኖት፡- ይሄ ጥያቄ የብዙዎቹ ግብ ጠባቂዎች ጥያቄ ነው ከማንም በላይ ኢትዮጵያዊን ሆነው ምርጥ የሚባሉ በረኞች አሉ ከውጮቹ የተሻሉ ምርጥ በረኞች አሉን ግን እድሉን ማግኘት አልተቻለም….. ክለቦችና አሰልጣኞች አምነውብን ከውጪ ማምጣት ካቆሙ ለውጥ ይመጣል….. ከባህርዳር ከተማ የወጣሁትም ለመጫወት ስል ነበር ዋናው በረኛ የውጪ ሀገር ዜጋ በመሆኑ መጫወት አልቻልኩም የውጪ ዜጋ ዋና በረኛ አድርገውም እኔን በጥሩ ገንዘብ በመውሰድ ተጠባባቂ ለማድረግ ጥሩ ክፍያ ያቀረበ ክለብ ነበር ያን ሁሉ እንቢ ብዬ ወደ ስሁል ሽረ መጥቻለው…. በሽረ ቆይታዬ በጣም ደስተኛ ነኝ በአሰልጣኞቹ፣ በአመራሮቹና በደጋፊዎቹ በሙሉ ደስተኛ ነኝ፡፡


ሀትሪክ፡- ከውጪ ዜጎች መሀል የተሻሉ የምትላቸው ግብ ጠባቂዎች አሉ?
ምንተስኖት፡- ጎበዝ ጎበዝ ግብ ጠባቂዎች አሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሚበልጡን በክሮስና በቆሙ ኳሶች ነው እዚያ ላይ ጊዜ አጠባበቃቸው አሪፍ ነው፡፡ በዚህ ላይ ከሰራን ለተሻለ ነገር መብቃት እንችላለን፡፡ እነርሱን የማንበልጥበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ በዚህ ደረጃ የሰበታውን ዳንኤል አጄና የመቐለ 7ዐው………. ጥሩ ግብ ጠባቂ ሆነው አግኝቻቸዋለው ጥሩ ተፎካካሪ በረኛ መሆኔን ሳይረሳ፡፡
ሀትሪክ፡- የግብ ጠባቂን ክፍተት ለመሙላት ፌዴሬሽኑ ምን ማድረግ ይጠበቅ በታል?
ምንተስኖት፡- በነገራችን ላይ የግብ ጠባቂዎች ችግር መፍትሔው ምንድው ነው እየተባለ ይነሣ ነበር፡፡ አንዳንድ የአውሮፓና የአፍሪካ ሀገራት ግብ ጠባቂን ከውጪ አያስፈርሙም ይህ በህግ የተደነገገ ነው፡፡ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ሕጉ ሊወጣ ይገባል ብሔራዊ ቡድንን ለማገልገል በክለብ ቋሚና የማይዋዥቅ አቅም ማሳየት ይጠበቃል፡፡ ይሄን ማድረግ ግን አልቻልንም ፌዴሬሽኑ 2ዐ12 ተግባራዊ ይደረጋል ያለውን ሕግ ሊያወጣ ይገባል ይሄኔ ነው የተሻሉ ግብ ጠባቂዎች የሚገኙት፡፡
ሀትሪክ፡-ምርጥ በረኛ ነኝ ከሌሎቹ የተሻልኩ ነኝ ማለት ትችላለህ?
ምንተስኖት፡- እኔ ብዬ መናገር አልፈልግም፡፡ ሰው ቢናገር ይሻላል፡፡ ከሀገር በህልም አንፃር ሌላ ስም ነው የሚያሰጠው……በጥሩ ደረጃ የመፎካከር አቅም እንዳለብኝ ግን መናገር እችላለው፡፡

ሀትሪክ፡- የቱርክ የሙከራ እድል መነሻ እንዴት ነው?

በክፍል ሁለት ይቀጥላል

 

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport