“በእርግጠኝነት የብሔራዊ ቡድኑ ቋሚ በረኛ እንደምሆን እተማመናለሁ፤ ምንም ስጋት የለብኝም”ምንተስኖት አሎ /ስሁል ሽረ/ ክፍል 2

ክፍል ሁለት ….

ምንተስኖት፡- በጣም ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ለተገኘው እድል የእኔና የእንዳለየሱስ አባተ ብቻ ስራ አይደለም ብዙ ሰዎች አሉ የእነርሱም ልፋት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል… የግብዣ ወረቀቱ ጥር 4 እና 5/2ዐ2ዐ መጣልኝ ይህን ይዘን ወደ ኤምባሲ ብንሄድም ፕሮሰሱ 2ዐቀን አካባቢ ፈጀና ጥር 25/26 ቪዛውን አገኘሁ ይሄ ማለት ዝውውሩ ሊዘጋ 5 ቀን ብቻ ቀርቶታል….በዚያ አጭር ጊዜ ተመችቻቸዋለው ለ1 ሳምንት የተሰጠኝ ቪዛ ስለፈቀዱልኝ የቪዛውን ቀን አራዝመን 2 ሳምንት ቆይቼ መጣሁ፡፡ በነበረኝ ቆይታ በጣም ደስተኛ ነኝ ጥሩ ነገር ገጥሞኛል፡፡ ከፈጣሪ ጋር የወደዱኝ ይመስለኛል…. ነገር ግን የዝውውር መስኮቱ ስላለቀና ወዲያውኑ ባለመፈረሜ ነገሮች ተንዛዙና ሳልፈርም መጣሁ፡፡ እነርሱ ግን እስከ ቀጣዩ የዝውውር መስኮት ድረስ እነርሱ ጋር ቆይቼ ልምምድ ልሰራ የተወሰነ ክፍያ ሊከፍሉኝ ነበር ሳልስማማ መጥቼ ወደ ስሁል ሽሬ ተመልሻለሁ፡፡ ከክለቤ ጋር ስለምጫወት ከጨዋታ ከጨዋታ አልርቅም በቀጣይ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ መዘጋጀት ስላለብኝ ውላቸውን ሳልቀበል መጥቻለው ሰኔ ላይ ሄጄ እንደምፈርም አረጋግጠዋል፡፡
ሀትሪክ፡- በቆይታህ በጣም የተገረምከው በምናቸው ነው?
ምንተስኖት፡- ለሰው ልጅ ያላቸውን ክብር አይቻለሁ ከሜዳ ውጪ ከሆነ ለሰው ያላቸው ፍቅር ይገርማል፡፡ እዚያ የተባበሩኝ ሰዎች ሙሉ የፕሮሰስ ወጪ ችለው ከሄድኩ በኋላ የሚያስፈልገኝን በሙሉ ሸፍነው ጠብቀውኛል እነዚህን ማመስገን እፈልጋው ምንም ሳይጎድልብኝ ተንከባክበው ሸኝተውኛል፡፡
ሀትሪክ፡-ከቡድኑጋር ልምምድ ሰራህ?
ምንተስኖት፡- አዎ በደንብ ሰርቻለሁ ከኛ ጋር ሲታይ በጣም ይለያያል፡፡ ከልምምዱ አይነት ከፋሲሊቲው ጋር ተያይዞ አንገናኝም በዚያ መሀል መገኘቴ ደስ ብሎኛል፡፡ ራሴ ላይ የተሻለ አቅም ገንብቼ መጥቻለሁ፡፡


ሀትሪክ፡- የክለብህ የስሁል ሽረ ኃላፊዎች እንዴት እንደፈቀዱልህ ግልጽ አድርገው?
ምንተስኖት፡- የስሁል ሽረን የአሰል ጣኞች ቡድንን ከልብ አመሰግናለሁ አመራሮ ቹንም ላመሰግን ይገባኛል፡፡ ከባህርዳር የወጣ ሁት የጀመርኩት የውጪ ጉዞ ፕሮሰስ ስላለኝ ነበር…..ይሄ ከመሆኑ በፊት ሌላ ጓደኛዬ እድል ሲመጣለት ተከለከለ፡፡ ይህን ሰምተን ስለነበር ወደ ሽሬ ስመጣ የውጪ እድል መጀመሬን ከተሳካና ጥሪ ከመጣ አምነው እንደሚለቁኝ ተነጋግረን ስለፈረምኩ እንቢ አላሉም….. ቃላቸውን ጠበቀው ፈቅደውልኛልና ላመሰግናቸው እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ክለቦች ሜዳዎቻ ቸው ለግብ ጠባቂዎች ያመቻል?
ምንተስኖት፡- በጣም ጥሩ የሚባሉ በቁጥር የሚጠሩ ሜዳዎች አሉ፡፡ የባህርዳር፣ የመቐሌና የጎንደር ስታዲየሞች በምሣሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ጥሩ ያልሆኑ ሜዳዎች አሉ፡፡ እንደ የወላይታ ድቻና የወልቂጤ ከተማ ሜዳዎች አይመቹም አብዛኛውን ጊዜ ከኳስ ጋር ተያይዞ መውደቅ መነሳቱ ስላለ ሜዳው ጥሩ አለ መሆኑ ሊያከብድብን ይችላል…. የሜዳውም ችግር ስላለ ፍልሚያው ዘርፈብዙ ነው ማለት ይቻላል / ሣቅ/
ሀትሪክ፡- ስሁል ሽረ 4ኛ ነው በ2ዐ12 ምን ግብ አስቀመጣችሁ?
ምንተስኖት፡- በዚህ አጋጣሚ ለዋንጫ ነው የምናስበው ብዬ መናገር አልችልም…. ከዚያ በዘለለ አሁን በያዝነው ጥሩ የፉክክር መንፈስ ቀጥለን የተሻለ ደረጃ ላይ ለመገኘት እንሞክራለን……ገና ብዙ ጨዋታዎች ስለሚቀሩ በየጨዋታዎቹ እየተፋለምን ቆይተን ያኔ ህልሜን መናገር የምችለው አሁን ላይ ግን ለዋንጫ ነው የምንጫወተው ማለት እቸገራለሁ፡፡ ጥሩ ተፎካካሪ የሆነ የተሻለ ቡድን እንደሚኖረን ግን ርግጠኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- በፕሪሚየርሊጉ 1ኛ እና 2ኛ የወጡ ቡድኖች ናቸው በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያ የሚወክሉት.. ከዚህስ አንፃር ስሁል ሽረ ምን ያስባል?
ምንተስኖት፡- እንዳልኩት ነው ገና ብዙ ጨዋታዎች ስላሉ መናገር አልችልም የሚፈጠረውንም መገመት ይከብዳል ከፊታችን ላለው እያንዳንዱ ግጥሚያ ግን ትኩረት እንሰጣለን፡፡ የወደፊቱን በእንደዚህ መልኩ ነው መናገር የምችለው፡፡ ጥሩና ተፎካካሪ ሆነን መቀጠል የሚያስችለን አቋም ላይ ነው የምንገኘውና ይህን ማስቀጠል ላይ ትኩረት እንሰጣለን፡፡
ሀትሪክ፡- ከሜዳ ውጪ ማሸነፍ ከባድ እየሆነ ነው…. የቅርቡን ፋሲል ከነማ መቐለ 7ዐ እንደርታን ቅ/ጊዮርጊስም ወልዋሎ አዲግራትን ያሸነፉበትን ካልጠቀስን በስተቀር ይህን ያህል ከባድ የሆነው ለምን ይመስልሃል?
ምንተስኖት፡ ሁሉም ክለቦች ጠንክረው ይፋለማሉ የአየሩና የደጋፊው ጫና ታክሎበት በርግጥም ከባድ ሆኗል፡፡
ሀትሪክ፡- በግጥሚያው የደርሶ መልስ ፍልሚያ ይደረጋል በሜዳህ ረተህ ከሜዳህ ውጪ መሸነፍ እግር ኳሳዊ ነው ማለት ይቻላል?
ምንተስኖት፡-አዎ…..የማምነው እንደ ዚያ ነው አብዛኞቹ ጨዋታዎች ላይ በተለይ ከሜዳ ውጪ ባለ ግጥሚያ ዳኛ ይያዝ ብሃል ይባላል የደጋፊ ጫና አይቻልምም ይባላል እኔ ግን አልገጠመኝም የስታዲየም ለውጥ ካልተደረገ በስተቀር ግጥሚያ ነው፡፡ በሜዳህ ያስተናገድከው ክለብን ነው በርሱ ሜዳ የምትፋለመው.. ልዩነቱ ምንድነው ታዲያ…? እኛም ሜዳችን ላይ እንደምናሸንፈው ተጋጣ ሚያችንም ሜዳው ላይ በሞራል ገብቶ ያሸን ፈናል በቃ ይሄ ነው እውነቱ…..ስለዚህ ብዙም የተለየ የምለው ምክንያት የለም በሜዳችን አሸነፍናቸው በሜዳቸው ረቱን በቃ፡፡
ሀትሪክ፡- በእስካሁኑ ከሜዳ ውጪ ጨዋታ አርቢትሮች ለባለሜዳው ሲያደሉ አልታዘብክም?
ምንተስኖት፡- በፍፁም… በእስካሁኑ ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ይሄን ያህል የተጋነነ የዳኛ ተፅዕኖ አላየሁም፡፡ ይሄን ምክን ያት ማድረግ ይከብዳል፡፡
ሀትሪክ፡- ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት መከበር የምትለው ነገር አለ?
ምንተስኖት፡- ደጋፊ እኛን ተጨዋቾች ብሎ ነው የሚመጣው….. እኛም በምናሳየው ድርጊትና ባህሪ ነው የማይገባ ነገር ረብሻ በአጠቃላይ ስፖርታዊ ጨዋነት የሚጓደለውና ተጨዋቾች በሙሉ ሜዳ ላይ የምናሳየውን አላስፈላጊ ባህሪ መተው አለብን፡፡ በዳኛ ውሳኔ ጣልቃ ከመግባት ይልቅ ውሳኔውን በፀጋ ተቀብለን ጨዋታውን ማስቀጠል እሰጥ አገባ ውስጥ መግባት የለብንም…. አለበለዚያ ደጋፊው እኛን ተከትሎ አላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ በመግባት ብዙ ችግር ሊከሰት ይችላልና ከዚህ ድርጊት መታቀብ የግድ ነው…… ለሀገሬ ሠላም እመኛለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ከዋሊያዎቹ ጋር ምን ታስባለህ?
ምንተስኖት፡- ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያደርሰንን ድል ኮትዲቫር ላይ አስመዝግበናል፡፡ ባህርዳር ላይ የተመዘገበው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ድል ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ከፊታችን ጋር ያሉ ግጥሚያዎችን ከፈጣሪ ጋር በድል በመጨረስ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍን እናልማለን፡፡
ሀትሪክ፡- የብሔራዊ ቡድን ቋሚ ግብ ጠባቂነት እነጠቃለው ብለህ አትሰጋም?
ምንተስኖት፡- በርግጠኝነት የብሔራዊ ቡድኑ ቋሚ
በረኛ እንደምሆን እተማመናለሁ ምንም ስጋት የለብኝም፡፡ ከፈጣሪ ጋር ህልሜን አሳክቼ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምችለውን አደርጋለው ብዬ አስባለው፡፡


ሀትሪክ፡- በሁሉም ብሔራዊ ቡድን ስር ስንት ጨዋታ ተሰልፈህ ተጫውትክ?
ምንተስኖት፡- በኢንስትራክተር አብር ሃም መብራቱ ስር መሰልጠን የጀመር ኩት በኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ በመጫወት ነው በኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ ከማሊ ጋር ደርሶ መልስ በቻን ማጣሪያ ከጁቡቲ ጋር ደርሶ መልስ ከሩዋንዳ ጋርም እንዲሁ ተጫውቻለው፡፡ ከዋሊያዎቹ ጋር ኮትዲቯርን ስንገጥም 45 ደቂቃ ተቀይሬ ገብቼ ተጫውቻለው፡፡
ሀትሪክ፡- ለረጅም ጊዜ እጫወታለሁ ብለህ ታምናለህ?
ምንተስኖት፡- እውነት ነው ውስጤ በራስ መተማመን ዳብሯል…. ሀገሬን በምችለው አቅም አገለግላለሁ ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- በቀጣይ መድረስ የምትፈልገው ህልምህ የት ነው?
ምንተስኖት፡- እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ከኢትዮጵያ ውጪ ፕሮፌሽናል ግብ ጠብቂ መሆንን አልማለው በተለይ በአውሮፓ መድረክ መሳተፍ የቅድሚያ ፍላጎቴ ነው….ከፈጣሪ ጋር በተቻለ መጠን አሳካዋለው ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- እድል ብታገኝ የማን ግብ ጠባቂ መሆን ትመኛለህ?
ምንተስኖት፡- /ሳቅ/ የማን.ዩናይትድ ግብ ጠብቂ ብሆን ደስ ይለኛል
ሀትሪክ፡-የማን.ዩናይትድ ደጋፊ ነኝ እያልክ ነው?
ምንተስኖት፡- አዎ የዩናይትድ ነኝ
ሀትሪክ፡- ዴቪድ ደሂያ መተካት አይከብድም?
ምንተስኖት፡- /ሳቅ በሳቅ/ እድሉን ካገኘሁ በርትቼም ከሠራሁ የተሻለ ነገር ማድረግ እችላለሁ ብዬ አምናለሁ
ሀትሪክ፡- ከአሰልጣኞች ለዚህ ደረጃ መብቃትህ ዋነኛ ተመስጋኝ ማነው?
ምንተስኖት፡- መድምም ለገሰ…..ትልቁ ባለውታዬ ነውና በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ከዚህ በፊት የጂንካ ከነማ ግብ ጠባቂ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በአሰልጣኝነት ጂንካ ከነማ ብሔራዊ ሊግና ከፍተኛ ሊግ ያስገባውም እርሱ ነው…. እዚህ እንደምደርስ ታይቶት የተሻለ ድጋፍ ያደረገኝና ሙያዊ ስልጠና ሰጥቶ ያገዘኝ እርሱ በመሆኑ ትልቅ አቅም የገነባሁትም በርሱ ነውና አመሰግናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ፍቅረኛ አለህ.. አገባህ.. ወይስ?
ምንተስኖት፡- /ሣቅ በሳቅ/ አላገባሁም ጓደኝነት ገና እየጀመኩነው /ሳቅ በሳቅ/
ሀትሪክ፡- ከኳስ ውጪ ምንተስኖት በምን ዘና ይላል?
ምንተስኖት፡- ፊልም ማየት ሙዚቃ መስማት ያስደስተኛል…… የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ፊልሞችን አያለው ከሀገር ውስጥ ፊልም “ስስት” የተሰኘውን ፊልም ወድጄዋለው፡፡
ሀትሪክ፡-የመጨረሻ የምታመሰግነው ሰው ካለ እድሉን ልስጥህ?
ምንተስኖት፡- የቅድሚያ ምስጋናዬ ለፈጣሪ ነው የሚሆነው በራሴ እርዳታ ለዚህ ደርሻለሁና አመሰግነዋለው ለዚህ ደረጃዬ መድረስ የብዙ ሰዎች አስተዋፅኦ አለውና እነርሱንም አመሰግናለሁ….. ሙሉ ድጋፋቸው ላልተለየኝ ቤተሰቦቼ፣በቱርክ የሙከራ እድል እንዳገኝ የረዱኝ እንዳለየሱስ አባተ ውበቱ ፣ አቶ ንሴቦ ፍቅሬ፣ ስፔን የሚገኙት አቶ ሰለሞን፣አቶ ኤዶሚያስና አቶ ቢኒያም፣ አቶ አምዴ ቱርክ ተቀብለው የተሻለ ሥራ እንድሰራ ቆይታዬ ጥሩ እንዲሆን ያደረጉልኝ ሚስተር ጂያን፣ ሚስተር ሁሴን፣ ሚስተር አህመድ ኩርት፣ሚስተር አህመድ ኪዮክሳላን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport