“በኢትዮጵያ ቡና ቀሪ ውል አለኝ ክለቡን ስለመጥቀም እያሰብኩ ነው”ወንድሜነህ ደረጄ /ኢትዮጵያ ቡና/

“በኢትዮጵያ ቡና ቀሪ ውል አለኝ ክለቡን ስለመጥቀም እያሰብኩ ነው”

“ወደ ባህር ዳር የተጓዝኩት ለሌላ ጉዳይ ሳይሆን የክርስትና አባት ለመሆን ነው”
ወንድሜነህ ደረጄ /ኢትዮጵያ ቡና/


ኢትዮጵያ ቡናን ባሳለፍነው የተ ጨዋቾች ዝውውር መስኮት ከባህር ዳር ከተማ ክለብ በመምጣት አዲሱ ቡድኑን በጥሩ ብቃቱ አገልግሏል፤ በእዚህ ዓመት በነበረው የክለቡ ቆይታውም ሜዳ ላይ ካሳየው እንቅስቃሴ አንፃር ተጨዋቹ በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትንም ሊያገኝ ችሏል፤ በቡና የመጀመሪያ ዓመት የውድድር ተሳትፎው ላይ የተሳካ ጊዜን ያሳለፈው ወንድሜነህ ደረጄ የቀጣዩ ዓመት ላይም ደግሞ በጥሩ ብቃቱ ዳግም በመቅረብ ክለቡን በምን መልክ መጥቀም እንዳለበት በማሰብ ላይ ይገኛል፤ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ጠንካራው የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች የአሁን ሰዓት ላይ በባህር ዳር ከተማ የሚገኝ ሲሆን ተጨዋቹን ወደዛ ስለተጓዘበት ሁኔታ እንደዚሁም ደግሞ ከቡና እና ከራሱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ተጨዋቹን ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አናግሮት ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡


ሀትሪክ፡- ወደ ባህር ዳር መጓዝህን ሰማን፤ /ያናገርነው ሐሙስ ማታ ነው/ እዛ የሄድክበት ዋንኛው ምክንያት ምንድን ነው?

ወንድሜነህ፡- አዎን፤ ወደ እዛ ተጉ ዣለው፤ የሄድኩበት አጋጣሚንም ምንአልባት እዛ ከታየው በአንድአንዶች ዘንድ ለባህር ዳር ከተማ ክለብ ሊፈርም ይችላል በሚል እንዳያስጠረጥረኝም ራሴን የጠየቅኩበት ሁኔታም አለና ግልፅ ለማድረግ ወደ ባህር ዳር ከተማ የመጓዜ ዋንኛው ምክንያት በባህር ዳር ከተማ ክለብ ውስጥ በነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ለክለቡ አብረን እንጫወት የነበረው ጓደኛዬ ስነ-ጊዮርጊስ እሸቱ የልጅ አባት ስለሆነ ለእሱ ልጅ የክርስትና አባት ልሆንለት እንድችል ነው ጥሪው ስለደረሰኝ የተጓዝኩት፡፡

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ የነበረህ የእዚህ ዓመት የተጨዋችነት ቆይታህ ስኬታማ ነበር ማለት ይቻላል?

ወንድሜነህ፡- ለእኔ አዎን የተሳካ ነው፤ ምክንያቱም በመጀመሪያው ዓመት የክለቡ ቆይታዬና ይሄም ክለብ አዲስ የጨዋታ ታክቲክን ለመተግበር ጥረት እያደረገ ባለበት ሰዓት በበርካታ ጨዋታዎች ላይ በቋሚነት ከመሰለፍ በተጨማሪ ታክቲኩንም በጥሩ ሁኔታ የተላመድኩበት ሁኔታንም በራሴ ላይ ስለተመለከትኩኝ በክለቡ ጥሩ ጊዜን ነው ያሳለፍኩት፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና በዘንድሮ የው ድድር ዘመን ተሳትፎው መሻሻልንና ለውጥን እያመጣ በመጣበት ሰዓት በኮቪድ 19 የእግር ኳሱ ሊቋረጥ ችሏል፤ የለውጡ ሚስጥራችሁ ምን ነበር?

ወንድሜነህ፡- የሊጉ ውድድር ሲጀመር ብዙዎቻችን ተጨዋቾች ለክለቡ አዲስ ነበርን፤ የጨዋታው ፍልስፍናውም አዲስ ስለሆነብን ያን ታክቲክ በሜዳ ላይ በመተግበሩ እና መስራት በመቻሉ ላይ የማመን ችግር ስለነበረብን በዛ ደረጃ ላይ መጓዛችን በሲቲ ካፑ ላይ አንድአንድ ችግሮችን ፈጥሮብን በውጤት ደረጃ የጠበቅነውን ሳናገኝ ቀርተን ነበር በኋላ ላይ ግን የሊጉ ውድድር ሲጀመርና ከጨዋታ ወደ ጨዋታም ስንጓዝ በራሳችን ላይና ፍልስፍናውንም በሚገባ ለመተግበር እንደምንችል በመረዳታችንና ውስጣችንንም በጣም ስላሳመንን ያ ለመለወጣችን ዋንኛው ምክንያት ሆኖናል፡፡

ሀትሪክ፡- በኮቪድ 19 የእግር ኳሱ ሊቋረጥ ቢችልም ቡና ያላሳካው ነገር አለ?

ወንድሜነህ፡- አብዛኛዎቹን ነገሮች አሳክተናቸዋል፤ አላሳካናቸውም ብዬ ልናገር የምችለው ነገር ብዙም የለም፤ ምክንያቱም ቡና አዲስ ቡድን እየገነባ ያለና አዲስ የጨዋታ ታክቲክንም ለመከተል የመጣ ቡድን በመሆኑ በቆይታችን ብዙዎቻችን ተጨዋቾች የሚጠበቅብንን ነገር በተወሰነ መልኩ ስላሳካነው፤ የጨዋታ ፍልስፍናውን እንድንላመድም ጊዜ ተሰጥቶን ስለነበርና ከተሰጠን ጊዜም ፈጥነን በተሻለ መልኩም እንቅስቃሴው ሊገባን ስለቻለም ብዙ ነገሮችን አሳክተናል ብዬ ነው የማስበው፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ ከገነባው ክለቡ ተጨዋቾች እየለቀቁበት ነው፤ ይሄ የመጪው ዘመን ቡድኑ ላይ ስጋትና ችግር አይፈጥርበትም?

ወንድሜነህ፡- ይፈጥራል እንጂ፤ ከክለቡ ጋር የተለያዩት ተጨዋቾች ቡድኑን በደንብ አድርገው የሚጠቀሙ ነበሩ፤ ከዛ ውጪም በቋሚ ተሰላፊነትም ጭምር ቡድኑን የሚያገለግሉም ነበሩ፡፡

ሀትሪክ፡- ስለዚህ ኢትዮጵያ ቡናን ከተጨዋቾቹ መለያየት ጋር ተያይዞ የመጪው ዓመት ላይ በምን መልኩ እንጠብቀው?
ወንድሜነህ፡- አሁን ላይ የተጨዋቾቹ መልቀቅ እውን ሆኗል፤ ባይለቁ ኖሮ ለእኛ በጣም ደስ ይለን ነበር፤ ያ ስለሆነም ከእዚህ በኋላ ማሰብ ያለብን ስለመጪው ጊዜ ቡድናችን ነው፤ ባሉን ቀሪ ተጨዋቾች እና በአሰልጣኛችንም ላይ በግሌ ከፍተኛ እምነቱ ስላለኝ የእነሱን ክፍተት ቦታም የሚተካ እና ለፍልስፍናውም የሚሆኑ ተጨዋቾችንም አሰልጣኙ ስለሚያስመጣ ጠንካራና ጥሩ ቡድን ይኖረናል ብዬም አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት ክለባችሁ በአሁን ሰዓት ምን ማድረግ ይኖርበታል?

ወንድሜነህ፡- የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት መጀመሪያ ምንም ጥያቄ አያስፈልገውም ክለባችንን የለቀቁ ተጨዋቾች አሉና በእነሱ ምትክ ሌሎች ቡድናችንን ሊጠቅሙ የሚችሉ ልጆች ሊመጡ ይገባል፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ለፍልስፍናውም ተገዢ የሆንን ተጨዋቾችም ክለቡ ውስጥ አለንና ከሚመጡት ሌሎች ለፍልስፍናው ምቹ ከሚሆኑ ተጨዋቾች ጋር ቶሎ በአጨዋወቱ ዙሪያ ተግባብተን ቡናን የሊጉን ዋንጫ የሚያገኝበትን ነገር እንፈጥርለታለን፡፡

ሀትሪክ፡- በኮቪድ 19 ለረጅም ወቅት ከእግር ኳስ ሜዳው ለመራቅ ችለሃልና ምንድን ነው የተፈጠረብህ?

ወንድሜነህ፡- በኳስ ጨዋታ ዘመኔ አይደለም ለእዚህን ያህል ጊዜ ክረምት ላይ እንኳን እረፍት ሲሰጠን ከኳሱ ብዙ የምርቅ ተጨዋች አይደለውምና የአሁኑ ከኳሱ መራቃችን እንደ ስፖርተኛ ስታስበው በየጊዜው ልምምድ የምታደርግ ተጨዋች ነበርክና ያ ሲቀርብህ ለሚከፈልህ ነገርም ከአንተ አንድ ነገር ማበርከት እያለብህ ዝም ብለህ ቁጭ ብለህ ሁኔታዎችን ለመመልከት መቻልህ በጣም ነው ተፅህኖ ውስጥ የሚያስገባ እና ያጋጠመን ሁኔታ ከባድ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በኮቪድ ከሜዳ ብትርቁም በተቃራኒው ደግሞ ከቤተሰብም ጋር ለረጅም ጊዜ እንድትገናኙ አድርጎአችዋል?

ወንድሜነህ፡- ያ እውነት ነው፤ ምን ከቤተሰቦቻችን ጋር ብቻ በሰፊው ጊዜ ከጓደ ኞቻችንም ጭምር ነው እንድንገናኝና ጠቃሚና ጥሩ የሆነ ሀሳቦችንም እንድንጨዋወት ያደረገን፤ ከእነሱ ውጪም ከራስህ ጋርም አንድ ነገሮችንም እያሰላሰልክ በማውራት ወደፊት ምን ነገሮችን መስራት እንዳለብህም ከውሳኔ ላይ የምትደርስበት ነገር ስላለ ያ መሆን መቻሉ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡

📸 © natanim photo

ሀትሪክ፡- ኮቪድ 19 ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ብዙውን ጊዜህን የት ነው የምታሳልፈው?

ወንድሜነህ፡- አሁን ላይ የራሴን ኑሮ ለመምራት ከቤተሰቦቼ በተለይ ደግሞ በጣም ከምወዳት ወላጅ እናቴ ተለይቼ ነው እየኖርኩ ያለሁት፤ በቦሌ አራፍሳ በተከራየሁት የኮንደሚኒየም መኖሪያ ቤቴም ነው ጊዜዬን በማህበራዊ ኑሮ ከፍተኛ መግባባት ላይ ከደረስን ከጎረቤቶቼ ጋርም እያሳለፍኩ ያለሁት፤ አልፎ አልፎ ደግሞ በአካባቢው ስፖርተኞችም አሉና ስፖርትን ከእነሱ ጋር ለወረርሽኙ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የምሰራበት አጋጣሚውም አለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ምን ናፈቀህ?

ወንድሜነህ፡- ኳሷችን ተጀምሮ በደጋፊ ፊት መጫወት፡፡

ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ጥሩ እንቅስቃሴን ከማሳየትህ አኳያ ለብሔራዊ ቡድን መመረጥ ነበረብኝ ብለህ አላሰብክም?
ወንድሜነህ፡- ሁሉም ተጨዋች ያ የመመረጥ እልሙ ይኖረዋል፤ ከዚህ በፊት በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ለቻንና ለኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን የመመረጥ እድሉን አግኝቼ ነበር፤ እድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ለሆኑት ብሔራዊ ቡድንም ከማሊ ጋር በተደረገው ጨዋታ ለመመረጥ እና ለመጫወትም ችዬ ነበር፤ ወደ ቡና ከገባው በኋላ ደግሞ ካደረግኩት ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ አንፃር እና ህዝቡም ከሚሰጠኝ አድናቆት በመነሳት አንድ ተጨዋች ጥሩ ይሁንም አይሁንም ራሱን ስለሚያስቀድም ከምኞት በመነሳት መመረጡን የእውነት ጠብቄ ነበር፤ ግን የመምረጡ ስራ የአሰልጣኙ ስለሆነ ያን ላሳካው አልቻልኩም፡፡
ሀትሪክ፡- ለብሔራዊ ቡድን ባለመመ ረጥህ ተከፍተሃል?

ወንድሜነህ፡- በፍፁም፤ ነገን ሌላ ቀን ነው ብዬ ስለማስብና ስለማምን ምንም አልከፋኝም፡፡

ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ከባህር ዳር ከተማ በመምጣት ነው የእዚህ ዓመት ላይ ልትጫወት የቻልከው፤ በባህር ዳር በነበረህ የተጨዋችነት ቆይታህ የማትረሳቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

ወንድሜነህ፡- በባህር ዳር በነበረኝ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ሁሌም ቢሆን የማልረሳው በክለቡ መልካም የሚባል የጨዋታ ጊዜን ማሳለፌን እና ለአንድ ወንድ ሜነህ ህይወት መለወጥና ከፍ ማለትም ቡድኑ ያደረገልኝ አስተዋፅኦ ትልቅ መሆን መቻሉ ነው፤ ከዛ ውጪም ጥሩ ወንድሞችንና ጓደኞችንም በክልሉ ቆይታዬ ለማግኘትም ችያለውና እነዛን እንደ ጥሩ አጋጣሚዎች ነው የምገልፃቸው፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ እናጠቃል?

ወንድሜነህ፡- የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች አምስተኛው ዙር የቤተሰብ ቀን ሩጫ የፊታችን ማክሰኞ በተመረጠው 12ኛ ቀን፣ 12ኛው ወር እና 2012 ዓ/ም ላይ በየአካባቢው ታስቦ የሚውል በመሆኑና ይህም የሩጫ ቀን ሊታሰብ የቻለውም የቡና ደጋፊ እንደ 12ኛ ተጨዋች በመሆን ለክለቡ ትልቅ ድጋፍን የሚያደርግ ስለሆነም ቀኑን ክለቡ በጥሩ መልኩ በያለበት እንዲያከብረው ምኞቴን እገልፃለው፤ ለእዚህ የደስታ ቀንም እንኳን አደረሳችሁ እና በቀጣዩ ዓመትም ከክለቡ ጥሩ ነገርን የምትመለከቱበት ጊዜ ይሁንላችሁም ለማለት እፈልጋለው፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website