መነሻ ገጽ The BiG Interview “በአሰልጣኝ ውበቱ ስር ከዳዊትና መስዑድ ጎን በመጫወቴ ደስተኛ ነኝ”ታደለ መንገሻ /ሰበታ ከተማ/
The BiG Interviewሀትሪክ ስፖርትጋዜጣሰበታ ከተማዜናዎች

“በአሰልጣኝ ውበቱ ስር ከዳዊትና መስዑድ ጎን በመጫወቴ ደስተኛ ነኝ”ታደለ መንገሻ /ሰበታ ከተማ/

አጋራ
አጋራ

THE BIG INTERVIEW WITH TADELE MENGESHA


“ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የምናደርገው ጨዋታ
በዋዛ የምንላቀቅበት አይደለም”
“ቡድናችን የያዛቸው ሲኒየር ተጨዋቾችን ጥቅም የምናየው ክልል
ስንወጣ ነው በነርሱ ደስተኛ ነኝ“


ዮሴፍ ከፈለኝ

ተደጋጋሚ ጉዳቱ የፈለገውን እንዳያደርግ ቢያግደውም ኢትዮጲያ
ከምትጠራቸው ቴክኒካል ተጨዋቾች መሃል ይጠቀሣል….ለቅዱስ
ጊዮርጊስ፣ለደደቢት፣ለአርባምንጭና በውሰት ደግሞ ለኢትዮጲያ መድን
ተጫውቷል.. ቴክኒካል ብቃቱ ተመልካችን ያስደምማል…በርካቶችን
የርሱ ደጋፊ አድርጎ ማርኳል ….በብዙ የሀገራችን ጠጨዋቾች ላይ
የማይታይ ትህትናና መንፈሳዊነት መገለጫዎቹ ናቸው…ጉዳቱ በ2012
የውድድር ዘመን እንዳያገረሽበት በመመኘት ለውበቱ አባተ ሰበታ ከተማ
ፊርማውን ያኖረው እንግዳችን አመለ ሸጋው ታደለ መንገሻ ከዮሴፍ ከፈለኝ
ጋር በነበረው ቆይታ ለበርካታ ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡-በሲቲ ካፑ በቅዱስ ጊዮርጊስ መሸነፋችሁ ተማራችሁበት ወይስ ቅሬታን ፈጠረ?
ታደለ፡- የሲቲ ካፑ ውድድር ይታወቃል፡፡ የቅድመ ውድድር ዝግጅት አካል ነው፡፡ ዝግጅታችን ለዋናው ውድድር
የሚያበቃን ችግራችንን እንድንፈታ የሚያደርገን በመሆኑ መዘጋጃ አድርገን ነው የምናየው፡፡ ራሳችንን ለማየት
ጠቅሞናል፡፡ ከአሰልጣኛችን በተሰጠን መመሪያ መሻሻሎችን እያሳየን የመጣንበት ግጥሚያ ነው ዋንጫውን
ብናጣም ለሊጉ የሚጠቅመንን ትምህርት የወሰድንበት ሆኗል፡፡
ሀትሪክ፡-ከዳዊት እስጢፋኖስና መስኡድ መሀመድ ጋር የፈጠርከውን ጥምረት እንዴት አየኸው?
ታደለ፡-በጣም እድለኛ ነኝ ብዬ የማስበው ከዳዊትና መስኡድ ጋር በመጫወቴ ነው፡፡ ሲኒየር ናቸው
ከችሎታቸው ሌላ ከኳስ እንቅስቃሴ ውጪ የሚሰጡት መመሪያ ምርጥና አስተማሪ ነው ለቡድናችን
ከአሰልጣኙ ቀጥሎ ትልቅ ጥቅም ሰጪ ናቸው፡፡ ከነርሱ ጋር በመጫወቴ ደስ ብሎኛል በአሰልጣኝ ውበቱ ስር
ከዳዊትና መስዑድ ጎን በመጫወቴ ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡-በምትፈልገው ደረጃ ኳስን እየተጫወትኩ ነው ማለት ትችላለህ?
ታደለ፡- በፍፁም እንደዚህ ብዬ አላስብም ገና ኮ ነኝ የተወሰነ ጊዜ ከኳስ ርቄያለው ጉዳት ከ1 አመት በላይ
ከውድድር ውጪ አድርጎኝ ብዙ መሰናክሎችን አልፌ ነው የመጣሁት፡፡ ብዙ ትግል አድርጌያለው ብዬ ባስብም
ገና መሆኔ ይሰማኛል፡፡
ሀትሪክ፡- የታደለ አቅም እየባከነ ነው የምንፈልገውን ከርሱ አላገኘንም የሚሉ አሉና ጊዜ እንዳለፈብህ
ይሰማሃል?

ታደለ፡- ጊዜ አልፎብኛል ብዬ እንኳን አላስብም….. ሁሌ ጠንክሬ ስለምሰራ የምፈልገውንና የሚጠበቅብኝን
እንደማሳካ ውስጤ ያምናል…ዘንድሮም በተሻለ አቅም ያለኝን ለማውጣት እየጣርኩ ነው ለዚህ ደግሞ ጠንክሬ
እየሰራሁ ነው ከእግዚአብሔር ጋር እንደማሳካው ርግጠኛ ነኝ፡፡ ትላንት በጉዳት ያጣሁትን ጊዜ ረስቼ ነገዬን
ለማሳመር እየጣርኩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የማን አድናቂ ነህ? ስታይሉን የኮረጅከው ተጨዋችስ አለ…?
ታደለ፡- ከሀገር ውስጥ የዳዊት መብራቱ አድናቂ ነኝ፡፡ ከውጪ ደግሞ የሮናልዲንሆ ጎቾ አድናቂ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡-የኛ ሀገር ተጨዋቾች ኳስ ይጫወታሉ እንጂ እግር ኳስን አይመለከቱም ማየትም አይወዱም
ይባላሉ…. አንተስ እንዴት ነህ?


ታደለ፡- /ሳቅ በሳቅ/ በእውነት ለመናገር ኳስን ብዙም አላይም ግን እንደውጪ ተጨዋቾች ለመሆንም
አልጥርም ሮናልዲንሆን ብወደውም እንደርሱ ማድረግ አልሻም ባለኝ የራሴ አቅምና ብቃት ከአሰልጣኜ
በሚሰጠኝ ስልጠና ቡድኔን መጥቀም እፈልጋለው ያለኝን በሚገባ ከተጠቀምኩ የተሻለ መሆን እችላለሁ በኛ
ሀገር ደግሞ ችሎታው አለ መጠቀም ነው ያልቻልነው፡፡
ሀትሪክ፡-የተጋጣሚ ቡድንን ደካማና ጠንካራ ጎን የማየት እድሉ አላችሁ?
ታደለ፡- አዎ አለን፡፡ ብሔራዊ ቡድንና በክለብ ደረጃ የተጋጣሚ ቡድንን አጨዋወትና ሁኔታ አይተን… እንዘጋጃለን
ከነርሱ ብዙ መማር ያለብን ነገሮች አሉ የተሻለ ደረጃ የደረሱበትን አካሄድ ማየትና መማር ይኖርብናል አንዳንዴ
ይሄን ነገር አናደርግም ለውጥ ከፈለግን ግን ማየት መማር መጣር አለብን፡፡
ሀትሪክ፡- ያንተ የተጨዋችነት ወርቃማ ጊዜ የትኛው ነው…?
ታደለ፡- ያለ ጥርጥር የደደቢት ቆይትዬ ነዋ! ወደ 5 አመት ሰማያዊውን ማሊያ አድርጌያለው፡፡የፕሪሚየር
ሊጉን ዋንጫ አንስተናል የጥሎ ማለፍ ዋንጫውንም ወስደናል በዚህም በሻምፒዮንስ ሊግና በኮንፌዴሬሽን ካፕ
ኢትዮጵያን ወክለን ተጫውተናል፡፡
ሀትሪክ፡-በ2ዐዐ5 የሊጉን ዋንጫ ያነሣው ደደቢት በ2ዐ12 የሚገኘው በከፍተኛ ሊግ ነው ይሄስ ምን ስሜት
ፈጠረብህ?
ታደለ፡- በጣም ነው የተሰማኝ፡፡ ያሳለፍኩት የውጤት ጊዜን እያሰብኩኝ ሀዘን ይሰማኛል የደደቢት ቦታ እዚጋ
መሆን አልነበረበትም በውጪ ደረጃ ሀገርን የወከለ ክለብ እንዲህ መሆኑ ቅር ያሰኛል ከቡናና ጊዮርጊስ ጋር
ተፎካካሮ የተሻለ ደረጃ ላይ መቀመጥ ነበረበት ያ ባለመሆኑ ግን ቅር አሰኝቶኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ታደለ መንገሻ ለሰበታ ከተማ እንዲፈርም ያስቻለው ዋነኛ ምክንያት ምንድነው?
ታደለ፡- አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እንደሚፈልገኝ ሲነግረኝ ሁለቴ ማሰብ አላስፈለገኝም ከአንድ አንድ ነው እሺ
ያልኩት… ከውበቱ ጋር መስራት እፈልግ ነበርና እድሉን ስላገኘሁ ደስ ብሎኝ ነው የፈረምኩት፡፡ ሌላው ደግሞ
የቡድኑ ስብስብ ደግሞ ምርጥ በመሆኑ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደርሳለን ብዬ በማሰቤ ፊርማዬን አኑሬያለው፡፡
ከአሰልጣኝ ውበቱ ጋር መስራትን እፈልግ ነበር በአጨዋወት ፍልስፍናው ለተጨዋች በሚሰጠው ድጋፍና
በሚፈጥረው አቅም ልዩ አክብሮት ነበረኝና ከርሱ ጋር በመጫወቴ ደስ ብሎኛል ቡድኑ ውስጥ ገብቼ ደግሞ
ያገኘሁት እውቀት ካሰብኩት በላይ ነው ልምምዱና ምክሩ በጣም የሚገርሙ ናቸው፡
ሀትሪክ፡-ታደለ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የወጣው በሚፈለግበት ደረጃ ሳይጠቅም ነው የሚሉ ወገኖች አሉ…
ትስማማለህ?
ታደለ፡- ብዙ ጊዜ ይህንን አባባል ሰምቻለው…. ታዴ አልጠቀመም ሲሉ መስማቴ ገርሞኛል፡፡ በጊዮርጊስ ቤት
ቆይታዬ በጣም ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ትልቅ ፍቅር አይቻለው ከቡድኑ አመራሮች፣ ተጨዋቾችና ደጋፊዎች ያገኘሁት
ፍቅር የሚገርም ነበር ቆይታዬ ደስ የሚል ነበር የምቆጭበትም አይደለም… ጉዳት የሚፈልገውን በሙሉ
እንዲያወጣ ግን አላደረገውም ከተባለ እስማማለው፡፡ ጉዳት በተጨዋች ህይወት ውስጥ በርግጥ አይጠፋም
የተወሰነ ጉዳት ከጨዋታ አግልሎኛል እንደምጠቅማቸውና ደስ እንደማሰኛቸው አስብ ነበር ያ ባለመሆኑ ግን ቅር
ብሎኛል፡፡
ሀትሪክ፡-ስንብትህን ተቀብለኸዋል?
ታደለ፡- ሳትጫወት ስትቀር ቅሬታ ይፈጥራል ደጋፊው ባለመጫወቴ ቅር ብሎታል አዲስ አሰልጣኝ
እንደመምጣቱና አዲስ ፍልስፍና ስላመጣ ያን ለመልመድ ጊዜ ወስዶ ነበር 2ኛው ዙር ላይ ግን ጉዳት ላይ
አልነበርኩም አሰልጣኙ ብዙ ጨዋታ አስገብቶኛል ስንብቱ ብዙም አልተመቸኝም ተገቢ ነበር ለሚለውም እኔ
እንጃ… አልመሰለኝም፡፡
ሀትሪክ፡-በሲቲ ካፑ ፍፃሜ ላይ አንተና በኃይሉ አሰፋ (ቱሳ) በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የተደረገላችሁን
አቀባበል እንዴት አገኘኸው?
ታደለ፡- አዎ በዚህም ተደስቻለው ከጊዮርጊስ ለወጡ ተጨዋቾች ለነአዳነ ግርማ በኃይሉ አሰፋም ተደርጓል ያ
ነው ትልቁ ፍቅር…… ላሳለፍኩት ጊዜ የተሰጠውን ክብር ያሳያል… በዚህ ደስ ብሎኛል ደጋፊዎቹን ማመስገን
እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡-በወሳኝ የሊግ ጨዋታ ማክሰኞ /ዛሬ/ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ጨዋታ አላችሁ… ጊዮርጊስን
በተቃራኒነት መግጠም ምን አይነት ስሜት ይፈጥራል? የሲቲ ካፑን ውጤት የመመለስ የብቀላ ስሜት
አለባችሁ?
ታደለ፡- ተቃራኒ ሆኜ መጫወቴ የሚፈጥርብኝ ስሜት አለ….ሲቲ ካፑ ላይ ያየናቸውን ደካማ ጎኖች ለይተን
ስንዘጋጅባቸው ቆይተናል በተለይ አሰልጣኝ ውበቱ ጥሩ አድርጎ አዘጋጅቶናል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የምናደርገው

ጨዋታ በዋዛ የምንላቀቅበት አይደለም ይሄ ፕሪሚየር ሊግ ነው ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እንደምንችል
ተስፋ አደርጋለው፡፡


ሀትሪክ፡-ውጤቱን እንገምት.. እንደ ሲቲ ካፑ ድሉ የጊዮርጊስ? ወይስ የሰበታ? ብድሩን ትመልሳላችሁ?
ታደለ፡- /ሳቅ/ እርሱን ማክሰኞ 11 ሰዓት ሜዳው ላይ የምናየው ይሁንና እንደስራው ዝግጅት ጨዋታው ላይ
ከበረታን ውጤቱን ለመቀልበስ ምንም አያቅተንም ደግሞም ውጤቱን እንቀለብሰዋለን፡፡
ሀትሪክ፡-ቡድናችሁ የተዋቀረው በሲኒየሮች ወይም ረጅም ጊዜ በተጫወቱ ተጨዋቾች እንደመሆኑ አመቱን
ሙሉ በብቃት አይወጡትም የሚል ስጋት ያላቸው ወገኖች አሉ ታዴ አንተስ ስጋት የለብህም?
ታደለ፡- ምንም ስጋት የለብኝም ሰበታ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ጥሩ ተፎካካሪ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለው….
ከሚሰጠን ስራ አንፃር ተስፋ ይታየኛል አሰልጣኙ ደግሞ ገና ነን እያለ ነው የሚያሰራን…. ይሄም በርትተን
እንድንሰራ አድርጎናል፡፡ ሲኒየር ተጨዋቾች ደግሞ በደንብ እያገለገሉን ነው በተለይ ክልል ስንወጣ ነው
ጥቅማቸውን የምናየው፡፡
ሀትሪክ፡-እድሜያቸው የገፋ ተጨዋቾች መኖራቸው አመቱን በጥሩ አቋም አይጨርሱም የሚሉ ወገኖችን
አበርክቷል፡፡ ?
ታደለ፡-ቡድናችን ልምድ ባላቸውና በወጣቶቹ የተዋቀረ መሆኑ መካድ የለበትም…. የማንሰጋውም ለዚህ
ነው፡፡ በሲቲ ካፑ የነበረን አቋም እየጠነከረ ይሄዳል ብዬ ተስፋ አደርጋለው፡፡ ከአሰልጣኝ ውበቱ በምናገኘው
ስልጠና ቡድናችን ጥሩ ተፎካካሪ ይሆናል ብዬ አምናለው፡፡
ሀትሪክ፡-በሰበታ ያለህ ቆይታ አጠር ቢልም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸው ልዩነት ምን ይመስላል?
ታደለ፡- ሰበታ ከተማን ከተቀላቀልኩ ገና 2ኛ ወሬ ላይ እገኛለሁ ባየሁት ሁኔታ እንደ ቡድን ጠንካራ ስብስብ
አለው… ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አምና የተጫወትኩት ለ2ኛ ጊዜ ነው፡፡ ቡድኑ ውስጥ ስትመጣ ከድል ውጪ
የሚሰማህ የለም፡፡
ሀትሪክ፡-ጊዮርጊስ ጋር ድል ብቻ የሚጠበቀው 2ኛ መሆን አይፈቀድም… ሰበታ ከተማ ጋርስ ያ ስሜት አለ…?
ታደለ፡- ያ ስሜትማ ሁሉም ክለብ ጋር አለ፡፡ ፉክክር ውስጥ ስትገባ ሁሉም ለዋንጫ ነው የሚፋለመው፡፡
ውድድር ውስጥ ስትገባ የሚፈጠር ክስተት ነው ተፅዕኖ ፈጥሮ ከዋንጫ ውጪ የሚያደርግህ… ሰበታ ከተማ
ራሱን አሻሽሎ መፎካከር የሚፈልግ በመሆኑ የዘንድሮ ውድድር ላይ ጥሩ ውጤት እናመጣለን ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡-ታዴ የ5ዐዐ ብር ጥያቄ ልጠይቅህ ነው…. ?
ታደለ፡- (ሣቅ በሳቅ)
ሀትሪክ፡-16ቱም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች እኩል ለዋንጫ አልመው ይነሳሉ ብለህ ታመናለህ?
ታደለ፡- በፍፁም አላምንም… ላለመውረድ የሚጫወቱና መሀል ላይ ለመቆየት የሚያልሙ ክለቦችም አሉ…
እነዚህ ቡድኖች በርግጥም ዋንጫውን አያስቡትም፡፡ ማን ለዋንጫ እንደሚፎካከር ማን መሃል ሰፋሪ
እንደሚሆን ያውቁታል… በዚህ ደረጃ ያየኋቸው ክለቦች አሉ.. የውድድር አመቱ ሲጀመር ግን ሃሳባቸው ዋንጫ
ላይ ሆኖ ነው፡፡


ሀትሪክ፡-1 ሚሊዮን ብር ይዘህ የ5 ሚሊዮን ብር ማቀድ ትችላለህ…?
ታደለ፡- አይ እንዴት ይቻላል?… አይቻልም እንጂ!
ሀትሪክ፡-ከ16ቱ ክለቦች አመቱን ሲጀምሩ ባላቸው ስብስብ ለዋንጫ
ይፎካከራሉ የምትለው የትኞቹን ክለቦች ነው?
ታደለ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሰበታ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡናና መቐለ 7ዐ እንደርታን ለዋንጫ እጠብቃለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-ዋሊያዎቹን በተገቢው መንገድ ባለማገልገልህ ምን ይሰማሃል?
ታደለ፡- በጣም አዝናለው፡፡ በተወሰኑ የዋሊያዎቹ አሰልጣኞች ጥሪ ደርሶኝ የተሰለፍኩባቸው ጊዜያት አሉ
ሆኖም እንዳሰብኩት ባለመሆኑ ቁጭት ይሰማኛል ሀገሬን ለማገልገል ተግቼ እሰራ ነበር ያ ባለመሳካቱ ሀገሬን
ከጓደኞቼ ጋር ማገልገል ባለመቻሌ ይከፋኛል፡፡ ወደፊት ግን ከእግዚአብሔር ጋር ሀገሬን አገልግላለው ብዬ
አምናለው፡፡
ሀትሪክ፡-ኮትዲቯርን ሲረቱ ምን ተሰማህ?
ታደለ፡- ትልቅ ደስታ ፈጥሮብኛል በጣም ደስተኛ ነበርኩ ያሰብነውን ማድረግ ማሸነፍ እንደምንችል ያሳየንበት
ጨዋታ ነው ተጨዋቾቹና አሰልጣኞቹ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡-ከጉዳት በስተቀር በዋሊያዎቹ ተሰላፊነት የማናይህ የተለየ ምክንያት ይኖር ይሆን?
ታደለ፡- የለም… ምንም የተለየ ምክንያት ይኖራል ብዬ አላስብም… ጉዳት እስኪደርስብኝ ድረስ ከብሔራዊ
ቡድኑ ጋር ነበርኩ ጥሪው ደርሶኝ እሄዳለው…. በርግጥ የመሰለፍ እድል ብዙም አልገጠመኝም በተከታታይ ለ4
አመታት ጥሪ ደርሶኛል የማገኛቸው አሰልጣኞች የየራሣቸው ፍልስፍና ስላላቸው ሳልመረጥ የቀረሁ ይመስለኛል
በቀጣይ ግን ጠንክሬ ሰርቼ ሀገሬን የማገልገል እድል አገኛለው ብዬ አስባለው… ጠንክሬ ከሰራሁ የብሔራዊ
ቡድን ምርጫ መምጣቱ አይቀርም፡፡
ሀትሪክ፡-ዋሊያዎቹን እንዴት አገኘሃቸው?
ታደለ፡- በጣም ደስ የሚል ስብስብ ነው…. አቅማችንን ማወቅ አለብን… ምን አይነት ፍልስፍና ይዘን መግባት
አለብን የሚለውን ያመላከተ ጨዋታ ነበር ከአይቬሪኮስት ጋር ያደረግነው…. እነርሱ ፊዚካሊ ራሱ ትልቅ ናቸው
እኛ ከነርሱ ጋር ስንጫወት ባለን ነገር ላይ ተመስርተን መሆን አለበት፡፡ በአቅም ባንገናኝም በችሎታ በልጠን
ተገኝተናል ባለን ነገር ከሰራን ለውጥ ይመጣል ብዬ አምናለው ለዚህ ደግሞ ትዕግስትና ተስፋ ሊኖረን ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡-ለአንድ ተጨዋች ዘላቂነት ያለው አቅም ምን ይጠበቃል?

ታደለ፡- የመጀመሪያውና ዋናው ዲሲፕሊን ይመስለኛል ከዚያ ስራውን ማክበር ከአሰልጣኞቹ የሚሰጠውን
ምክር መቀበል በቂ እረፍት ማድረግ ለቀጣይነት እድገት ወሳኝ ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ለታዴ ማራኪ ፔዳላዳ 5ዐ ሺህ ብር ደመወዝ አያንስም?
ታደለ፡- /ሳቅ በሳቅ/ 5ዐ ሺህ በዚህ ፔዳላዳማ አያዋጣም /ሳቅ/ የደመወዝ ስኬል ሊወጣ ይችላል ነገር ግን
ሁሉም እኩል ደመወዝ ይከፈለው መባሉ ግን ተገቢ አይደለም ያልተመቸኝ ይሄ ሕግ ነው እኩል ከሆነ ለውጥ
የለም ይሄ መታረም አለበት
ሀትሪክ፡-ፕሪሚየር ሊጉ ተጀምሯል… ከስፖርታዊ ጨዋነት መከበር አንፃር ምን መናገር ትፈልጋለህ?
ታደለ፡- መጀመሪያውኑ ውድድሩ ሰላማዊው እግር ኳስ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ በ2ዐ11 በእግር ኳሱ ጥሩ
ጊዜ አላሳለፍንም በየክልሉ የነበሩ ነገሮች ተገቢ አልነበሩም ብዙ መጥፎ ነገሮችም ገጥመውናል፡፡ ፖለቲካ
የበዛበት ውድድር ነበር ዘንድሮም ይቀጥላል ብዬ ፈርቼ ነበር ነገር ግን የመጀመሪያው ሳምንት ውድድር በሠላም
ማለቁ ደስ ብሎኛል አምና በየሜዳቸው የማይጫወቱ ቡድኖች ዘንድሮ በሜዳቸው ተጫውተው በሠላም
ተጠናቋል ይሄ ደስ ይላል ይሄ መቀጠል አለበት ፌዴሬሽኑም ሆኑ የፍትህ አካላት ይሄን ማሰብ አለባቸው፡፡ ቦታው
ፍቅርና ሠላም የሚሰበክበት መሆን አለበት ተጨዋቹም ብንሆን ደጋፊን የሚያነሳሱ ተግባራትን ማድረግ
ማቆም አለብን ውድድሮቻችን በሠላም አልቀው በሠላም የምንወጣበት እንዲሆን መጣር አለብን፡፡
ሀትሪክ፡-ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ምን ትመኛለህ?
ታደለ፡- ሠላምና ፍቅርን እግዜአብሔር ይስጠን… ለሀገሬ የምመኘው ይህን ነው ሠላምና ፍቅር ካለ ሁሉም
ነገር ይኖራል፡፡
ሀትሪክ፡-የታዴ ህይወት ከመዝናናት ይልቅ ወደ መንፈሳዊነት ያደላ ነው ይባላል… እውነት ነው…?
ታደለ፡- እውነት ነው፤.. ይሄማ ግዴታ ነው መንፈሳዊነት ካልያዘህ ከባድ ነው ጊዜው የከፋ በመሆኑ
ማምለጫው ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት ይመስለኛል መንፈሳዊነት ለብዙ ነገር መልካም መንገድ
ይሆናልና መታሰብ አለበት፡፡ መልካም ነገሮችን ለመፈፀም መንፈሳዊነት ያስፈልጋል ያኔ ነው ፈሪሃ
እግዚአብሔር የሚያድርብህ
ሀትሪክ፡-ታዴ አገባህ? ወለድክ? ወይስ….?
ታደለ፡- /ሳቅ/ ፍቅረኛ አለችኝ በጣም ነው የምወዳት ገና ጋብቻ አልመሰረትንም
ሀትሪክ፡ሽማግሌ ታዲያ መቼ ልትልክ ነው?
ታደለ፡- /ሳቅ በሳቅ/ በቅርቡማ ይላካል /ሳቅ/
ሀትሪክ፡-በህይወትህ በተለይ በኳሱ ተምሳሌት የምትለው ሰው አለ…?
ታደለ፡- አዎ ተምሣሌቴ ወንድሜ አለማየሁ መንገሻ ነው…. ቤት ውስጥ እሱን እያየሁ ነው
ያደኩት….የሙገር፣ የአዳማ ከተማና የጉና ንግድ ተጨዋች ነበር እርሱ ለኔ ተምሣሌት ሆኖኝ ብዙ ነገር
ተምሬያለሁ ብዙ ነገር አድርጎልኛልና በዚሁ አጋጣሚ አመሰግነዋለው፡፡
ሀትሪክ፡- ቤተሰብ በሙሉ ለእግር ኳስ ትልቅ ፍቅር ያላቸው ናቸው ማለት ይቻላል?
ታደለ፡- አዎ ቤተሰቡ ኳስ ወዳድ ነው ሶስት ወንድማማቾች /እሸቱ መንገሻ፣ አለማየሁ መንገሻና እኔ/ ለኳስ
ትልቅ ፍቅር አለን…… እሸቱ ግን በጉዳት የሚፈልገውን ማድረግ አልቻለም ሌላው እኔ እዚህ ደረጃ እንድደርስ
ትልቅ ሥራ የሰራውና የቤታችን የመጀመሪያ ልጅ ግርማ መንገሻ ይባላል እንደ አባትም ሆኖ እዚህ አድርሶናልና
በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው እወዳለው፡፡
ሀትሪክ፡-አቶ መንገሻስ?
ታደለ፡- ፖሊስ ነው… ፖሊስ ሆነብን
ሀትሪክ፡- እርሳቸውምኮ የኦሜድላ ደጋፊ መሆን ይችላሉ!
ታደለ፡- /ሳቅ በሳቅ/
ሀትሪክ፡-ከውጪ የማን ደጋፊ ነህ?
ታደለ፡-የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ነኝ
ሀትሪክ፡- የሰሞኑን የማን ዩናይትድና አርሰናል ደጋፊዎች ሲያምሽ ያመኛል የሚለውን ዜማ እንዴት አገኘኸው?
ታደለ፡- /ሳቅ በሳቅ/ ኧረ ተው!
ሀትሪክ፡-የመቀለው ዳንኤል ደምሴ የማንቸስተር አርሰናል ደጋፊዎች በመዋደዳችን ማማ ወተት ስንጠጣ
እንደሙሽሮች እጃችንን አጠላልፈን ነው አለ… አንተስ…?
ታደለ፡- /ረጅም ሳቅ/ እውነቱን ነው…..አሁንምኮ እንዲህ እየሆነ ነው…/ሳቅ/
ሀትሪክ፡-ስንት አሰልጣኞችስ አሰልጥነውሃል.. በጣም ለውጦኛል የምትለው አሰልጣኝስ ማነው…?
ታደለ፡- ያሰለጠኑኝን በቁጥር ደረጃ መግለፅ ባልችልም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ አሰልጣኞች ሰልጥኛለው
ትልቁን ለውጥ አምጥቶብኛል የምለው ነፍሱን ይማረውና በደደቢት ያሰለጠነኝ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ነው ትልቅ
ውለታ ውሎልኛልና አልረሳውም፡፡ አሰልጣኙ ለብዙ ወጣቶች ትልቅ ድጋፍ የሰጠና አቅም የጨመረ አሰልጣኝ
ነው፡፡
ሀትሪክ፡-የመጨረሻ ቃል….?
ታደለ፡- የቅድሚያ ምስጋና ለዚህ ላበቃኝ ለአምላኬ ይሁንልኝ ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርካት ይጠብቃት
ማለት እፈልጋለው… ለሰበታ ከተማ ደጋፊዎችም ያለኝን ክብር እገልፃለው … ሁሌ ከጎናችን እንደሚሆኑ በሲቲ
ካፑ አሳይተዋልና አመሰግናለው በቀጣይም በፕሪሚየር ሊጉ ድጋፋቸው እንዳይለየን ጥሪ አቀርባለው…የተሻለ

ስራ ሰርተን ክለባችንን የተሻለ ደረጃ እንደምናደርሰው እምነቴ የጸና ነው የሀትሪክም ዝግጅት ክፍል ጊዜ ሰጥቶ
ቃለ ምልልስ እንዳደርግና እንግዳ እንድንሆን ስላደረኝ በጣም አመሰግናለው፡፡
ሀትሪክ፡-ታዴ አመሰግነናል…. መልካም የውድድር ጊዜ እንመኛለን፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

የሊጉ መሪ ሽንፈት ሲገጥመው በድንጉዛ ደርቢ የጦና ንቦቹ እና ኤሌክትሪክ ድል ቀንቷቸዋል

በሳምንቱ የሁለተኛ ቀን ጨዋታ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ተከታታይ ሽንፈትን በሸገር ሲያስተናግድ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

አዳማ ከአስር ፈረሰኞቹ ከሦስት እና ነብሮቹ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ አሸንፈዋል

በሊጉ የሳምንቱ የመክፈቻ ቀን ጨዋታ አዳማ ከተማ በጎል ደምቆ ሲያሸንፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ...

ዜናዎችየአዲስአበባ እግርኳስ ፌዴሬሽንየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

ውጤት ለውጠዋል የተባሉት ሁለት ዳኞች ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተደረገ

በዮሴፍ ከፈለኝ በወልዋሎ እና ነገሌ አርሲ ጨዋታ ላይ ውጤት ለውጠዋል የተባሉ ሁለት...

ቅዱስ ጊዮርጊስዜናዎችየኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንፊፋ

ፊፋ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ጥሎት የነበረውን የዝውውር ዕገዳ በጊዜያዊነት አነሳ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአራት የቀድሞ ተጫዋቾች ቀርቦበት በነበረው ክስ በፊፋ ጥሎበት የነበረው የተጫዋቾች...