“በልቤ ያለው ሲዳማ ቡና ብቻ ነው አሁንም ሲዳማ ቡናዊ ነኝ” አዲስ ግደይ

 

የሲዳማ ቡናው ስኬታማ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች አዲስ ግደይ በየዓመቱ የፕሪምየር ሊጉ ውድድር ላይ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል፤ በግብ አግቢነቱም ጨራሽ ከሚባሉት አጥቂዎች መካከልም ስሙ በተደጋጋሚ ጊዜ ይጠቀሳል፤ ባለፉት ጥቂት የውድድር ዓመታትና ዘንድሮም ለቡድኑ ባደረጋቸው አብዛኛው ጨዋታዎች ለብዙ የተቃራኒ ቡድን የተከላካይ ስፍራ ተጨዋቾችም ፈታኝ ሆኖባቸዋል፤ የሀገሪቱ ስኬታማ አጥቂ ከሚባሉት ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነውን ይህን ግብ አዳኝ የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ በኳስ ህይወቱና ተያያዥ በሆኑ ጥያቄዎች ዙሪያ እንግዳ አድርጎት አቅርቦታልና ተጨዋቹ ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር ያደረገው ቆይታ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፤ ተከታተሉት፡፡

ሀትሪክ፡- በቅድሚያ ለቃለ-ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆንክ በእኛና በሀትሪክ ስፖርት አንባቢዎች ስም ከልብ እናመሰግንሃለን?
አዲስ፡- እኔም እናንተን የጋዜጣችሁ እንግዳ አድርጋችሁኝ ስለጋበዛችሁኝ በጣም አመሰግናችኋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- አዲስ ግደይ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ የት ተወለደ….? የትስ አደገ?
አዲስ፡- ተወልጄ ያደግኩት በጅማ ዞን አጋሮ ከተማ ላይ ነው፤ እዛም በሚገኝ የጨዋታ ሜዳም ላይ የእግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት፡፡
ሀትሪክ፡- የጅማ ዞን አጋሮ ከተማ በምን ትታወቃለች፤ ከተማዋን ማየት ወይንም ደግሞ መጎብኘት ለሚፈልግስ ሰው አሳይ ብትባል ምንን ታሳያለህ?
አዲስ፡- በአጠቃላይ የጅማ ከተማ በቡና ምርቷ ነው ሁሌም የምትታወቀው፤ ሀገሪቷን ለማያውቋት ሰዎች ደግሞ አንድ ነገርን አስጎብኝ ወይንም አሳይ ብባል በቅድሚያ የማሳየው በድሮ ዘመን የነበሩትን የንጉስ አባጅፋር ቤተ-መንግሥትን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ቤተሰቦችህ እንዴት ነው የሚገለፁት? ስንት ወንድም እና እህትስ አለ? እስኪ ጥቂት ስለ እናትህ እና አባትህም አጫውተን?
አዲስ፡- በመጀመሪያ በእኛ ቤተሰብ ውስጥ ስላሉት የእህቶቼና የወንድሞቼ የቁጥር ብዛት ልንገርህ፤ አምስት እህቶች እና ሶስት ወንድሞች አሉኝ፤ ይሄ ማለት በአጠቃላይ አንድ ቋሚ ቡድን ልንሰራ ጥቂት የቀረን እንደማለትም ነው፤ ቤተሰቦቼን በተመለከተ እነሱን የምገልፃቸው ለእኔ በስጋ ብቻ ስለተሳሰርን ሳይሆን ባለን ቀረቤታም ጭምር ነው የምለካቸውና ለእነሱም ከመጨ ረሻዋ የቤታችን ልጅ ቀጥዬ ያለሁትም ወንድ ልጅ እንደመሆኔና ብዙ ነገሮችንም ስላደረጉልኝ እንደዚሁም ደግሞ ለእኔም ከፍተኛ ቦታ ስላላቸው እጅግ አድርጌ ነው በጣም የማመሰግናቸው፤ እወዳቸዋለውም፡፡ ስለ እናቴና አባቴ ለተጠየቅኩት እናቴ አሁንም በህይወት አለች፤ አባቴ ደግሞ በልጅነቴ ነው ያረፈውና የእኛ ቤት ህይወት የሚመስለው ይኸው ነው፡፡


ሀትሪክ፡- ተማሪ ሳለህ በጣም የሚከብድህ እና የሚቀልህ ትምህርት ምን ነበር?
አዲስ፡- በዛን ሰዓት በጣም የሚከብ ደኝ ትምህርት ቋንቋ ነበር፤ ያኔም እኔ ተወልጄ ያደግኩበት ክልል የኦሮሚያ ቢሆንም የኦሮምኛን ቋንቋ ግን ተናጋሪ ስላልነበርኩ እና በክፍል ውስጥም ቋንቋውን ለመናገር በጣም ያስቸግረኝ ነበር፡፡ ያኔ እኔ ኳሱ ላይ ብዙ ትኩረት ስላደረግኩ እንጂ እንደ ጥሩ ተማሪነቴ ቋንቋውን በደንብ የምችልበት መንገድ ይኖረኝ ነበር፤ ሌላው በጣም የሚቀለኝ ትምህርት ደግሞ ማትስ ነበር፤ ቀለል ብሎኝም ነበር ይህን የሂሳብ ትምህርት የምሰራው፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮስ…?
አዲስ፡- ያኔ ልጅ እያለው የደሀ ቤተሰብ ልጅ ነበርኩ፤ የስፖርት ወጪዎቼንም ለመሸፈን ስልና ቤተሰቦቼንም በስራ ለማገዝ ስለፈለግኩ አንዳንድ የንግድ ስራዎችን እሰራ ነበርና ኳስ ተጨዋች ባልሆን ኖሮ ምንአ ልባት ነጋዴ ነበር የምሆነው፡፡
ሀትሪክ፡- ምን አይነት ባህሪ አለህ?
አዲስ፡- እኔንጃ! አንዳንዴ ተናድጅ አይነት ሰው ነኝ መሰለኝ፤ ከሰው ጋር ግን መግባባት ደስ ይለኛል፤ ከምግባባቸው ሰዎች ጋር ደግሞ ቁጥብ ሆኜ መሳቅና መጫወትን እወዳለው፤ እነዚህ የእኔ ባህሪያቶች ናቸው፤ ከዛ በዘለለ ጓደኞቼ ስለ እኔ ብዙ ነገር ሊናገሩ ይችላሉ፡፡
ሀትሪክ፡- የሲዳማ ቡና የተጨዋችነት ቆይታህ አሁን ላይ 5ኛ ዓመቱን ይዟል፤ ወደሌሎች ክለቦች አለማምራትህ የቡድኑ ታማኝ ተጨዋች አድርጎሀል ማለት ይቻላል?
አዲስ፡- እንደመገረም ብሎ እግር ኳስን ስንመለከት በሀገራችንም በውጪም የሚገኙ ተጨዋቾች አንድ ክለብ ውስጥ ብዙ ጊዜ ቆይተው ጫማቸውን እስከመስቀል ደረጃ የሚደርሱ ብዙ ተጨዋቾችን እናያለን፤ በሚዲያ ደረጃም እንሰማለን፤ በእነሱ ደረጃ የእኔ ሲለካ ለክለቤ ታማኝ ተጨዋች ነኝ ለመባል እና ለመናገር ትንሽ ጊዜዎች ይቀሩኛል፡፡ ግን እስከአሁን ባለሁበት ሁኔታ በክለቤ ሲዳማ ቡና እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ አሁንም በልቤ ያለው ሲዳማ ቡናም ብቻ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእዚህ ዓመት ጉዞአችሁ በምን መልኩ ይገለፃል፤ ከዚህ አንፃር ለሻምፒዮናነት የሚኖ ራችሁ ተስፋ የት ድረስ ይሆናል?
አዲስ፡- የፕሪምየር ሊጉን ውድድር ዘንድሮ የጀመርነው ብዙ ነገሩን ከዓምናው መነሻ በማድረግ ነው፤ ውጤታችንንም ማሳመር አለብን በሚልም ጥሩ ስራን ሰርተንና በሚገባ ተነጋግረንበት ነው ለጨዋታዎቹ የቀረብነው፤ ያም ሆኖ ግን የመጀመሪያዎቹ ሰሞን አካባቢ እና አልፎ አልፎ በመሀል ነገሮች እንዳሰብናቸው ስላልሆኑ ትንሽ የውጤት ማጣት ችግሮች ገጠሙን፤ ከዚህ በፊት እንዳልኩትም በሜዳችን ሽንፈትን አናቅም ነበር፤ በዚህ ዓመት ግን ከመቐለ ጋር ያደረግነውን ጨምሮ ሁለት ሽንፈቶች በሜዳችን አጋጠሙን፤ ክፍተቶች ነበሩብንና ለዛም ነው የተሸነፍነው፤ ከእነዛ ሽንፈቶች በኋላም በድክመቶቻችን ዙሪያ በመነጋገርም አሁን ላይ ነገሮችን ለማስተካከል ጥረትን እያደረግን ነው የምንገኘው፤ የሊጉ ውድድር አሁን ላይ በርካታ ግጥሚያዎች ስለሚቀረውም እኛ ዓምና ያጣነውን ዋንጫ ዘንድሮ ለማሳካት ነው እያሰብን የምንገኘውና በዚህ ብዙም የምንሰጋው ነገር የለም፡፡ ለሻምፒዮናነትም ነው የምጫወተው፡፡
ሀትሪክ፡- ሲዳማ ቡና ለአዲስ….?
አዲስ፡- እኔንጃ ቡድኑን የምገልፅበት ቃል የለኝም፤ እንዳልኩ የእግር ኳስን የተጫ ወትኩት ለሁለቱ ቡድኖች ብቻ ነው፤ ለወራቤ ከተማና ለሲዳማ ቡና፤ ወራቤ ከተማም ለእኔ ልዬ ቦታ አለው፤ ሲዳማ ቡና ግን ቅድም ከላይ እንዳልኩት ቤተሰቦቼ ብዬ አስረድቼካለው፤ ቤተሰቦቼ ለእኔ ቅርብ ስለሆኑና የሆኑ ችግሮች ቢመጡ እንኳን ቶሎ ተነጋግረን ችግሮቹን ስለምንፈታውና የዛ አይነት ቤተሰብ ስላለኝ ለእኔ እነሱ እንደ ቤተሰቦቼ ናቸው፤ ከቤተሰቦቼም በላይ ናቸው፤ እጅግ በጣም የምወደውም ክለቤ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የሲዳማ ቡና ክለብ ውስጥ አዝናኙ እና በቀልዱ ጥርሳችሁን የማያስከ ድናችሁ ተጨዋች ማን ነው?
አዲስ፡- የሚገርምህ እኛ ቡድን ውስጥ ሁሉም ተጨዋች ቀልደኛ ነው፤ በተመሳ ሳይ የእድሜ ደረጃ ላይም ስለምንገኝ አንድ ተጨዋችን ነጥለህ መጥራትም አትች ልም፤ ሁሉም እንደባዳ የሚታይ ሳይሆን እንደወ ንድም የሚተያዩም ስለሆኑ ያስቁሃል፤ እከሌ ብዬ ብጠራልህ ኸረ እከሌም አለም ይባላል፤ ግን ለእኔ አንድ ተጨዋችን ነጥለህ ጥራ ብትለኝ ሀብታሙ ገዛኸኝን እጠራልካለው፤ ግን ሁሉም ደስተኛ ስለሆነ አንተን በቀልዳቸው ያዝናኑሃል፡፡

ሀትሪክ፡- አንተ በምትጫወትበት ቦታ ምርጡ እና በጣም የምታደንቀው ተጨዋች ማንን ነው?
አዲስ፡- ጋዲሳ መብራቴን ነዋ! እሱ ብዙ የግል ክህሎቶች ወይንም ደግሞ ታለንቶች አሉት፤ ልዩ ተሰጥኦ ያለውም ተጨዋች ነው፤ ሜዳ ላይ ሲጫወት ሳየው በእሱ ውስጥ ራሴን መመልከትም እፈልጋለው፤ ጋዲሳ ሲጫወት ሁልጊዜ የሚስበኝ እና የሚማርከኝም ተጨዋች ነውና በእዚህ አጋጣሚ በጣም እንደምወደውም መናገር እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከአጠገብህ አብሮ ተጣምሮ ሲጫወትስ ያደነቅከው ተጨዋች?
አዲስ፡- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ሀገሪቷ ውስጥ አሉ ከሚባሉት ተጨዋቾች ጋር ተጣምሬ የተጫወትኩበት አጋጣሚ ቢኖረኝም አሁን ላይ ግን በአንድ ጨዋታ ስለሆነም ይመስለኛል ሲጫወት ተመልክቼው በጣም የወደድኩት እና ያደነቅኩት ተጨዋች ከኢትዮጵያ ቡና የተመረጠውን አቡበከር ናስርን ነው፤ አብሬው ስጫወት የሚያሳየው እንቅስቃሴ በጣም ደስ ይላል፡፡
ሀትሪክ፡- አቡበከር ናስር በችሎታው የተለየ ነገር አለው ማለት ነው?
አዲስ፡- አዎን፤ እሱ እንደምታውቀው ገና ታዳጊ ተጨዋች ነው፤ እኔንጃ ወደፊት አቡኪ ለክለቡም ሆነ ለሀገሩ ብዙ ነገርንም ሊሰራ ይችላል ብዬም አስባለው፤ እሱ ብዙ አቅም አለው፤ ለክለቡም ለሀገሩም ጥሩ ነገርን የሚሰራበት ችሎታ ስላለው ለእኔ ይደንቀኛል፤ በኢትዮጵያ ቡና ውስጥም የአሁን ሰዓት ላይ አንድአንዴ ጉዳት ካላጋጠመው በስተቀር ጥሩ ጊዜንም እያሳለፈ ነው፤ ምናልባት የጉዳት መደራረቦች ቢኖሩበትም ከጉዳቱ ሲያገግም ግን ለክለቡም ለሀገሩም ጥሩ ነገር ይሰራል ብዬም የማስበው ተጨዋች ነው፡፡


ሀትሪክ፡- በሞባይልህ ፌስ ቡክን ጨምሮ ቴሌግራም ኢንስታግራም እና ሌሎች ግልጋሎቶችን ትጠቀማለህ?
አዲስ፡- አላበዛም እንጂ አንድ መረጃዎችን በምፈልግበት ሰዓት እጠቀማለው፤ በተለይ ደግሞ ቴሌግራምን የምጠቀመው ስፖርታዊ ውጤቶችን ለማየት ስል ብቻ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በርካታዎቹ የእግር ኳስ ተጨዋቾቻችን መኪናን እያሽከረከሩ ነው አዲስስ?
አዲስ፡- እሱም እኮ በአቅሙ ያሽከረክራል አላያችሁም እንዴ!
ሀትሪክ፡- አላየንም? የት የት ነው የምትነዳት….የመኪናክ ሞዴልስ ምንድን ነች?
አዲስ፡- የመኪናዬ ሞዴል ኮሎራ 2005 ናት፤ በሐዋሳ ከተማም ላይ ነው መኪናዬን በ አብዛኛው ጊዜ የማሽከረክራት፤ አልፎ አልፎ ግን ወደ አዲስ አበባ ለግል ጉዳዮቼ ስመጣ እ ሷን ነው ይዣት በመምጣት የማሽከረክራት፡፡
ሀትሪክ፡- ፈጣን ምላሽ፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ ታልፋልች….አታልፍም?
አዲስ፡- እኔ እናልፋለን ብዬ አምናለው፤ ለእዚህም እንደመነሻ አድርጌ የምጠቅሰው የኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ቡድን የተጨዋቾች ስብስብ ውስጥ ጥሩ መነሳሳት እና ጥሩ ጅማሬዎች ስላሉ ነው፤ ከብዙ ጥረቶች በኋላም የብሄራዊ ቡድናችን ወደምንፈልግበት ደረጃ እየገባ ያለበት ሁኔታም ስላለ ያንን ነገር ማስቀጠል ነው የእኛ ስራ ሊሆን የሚችለው፤ በቅርቡ በተደረገ ጨዋታ አይቮሪኮስትን አሸንፈናል፤ እነሱን ያሸነፍንበት ጨዋታም ለቀጣይ ግጥሚያ የሚያነሳሳን እንጂ የሚያኩራራን እንዳልሆነ የተረዳንበት ሁኔታ ስላለና ስለተነጋገርንበትም ያንን ጅማሬያችንን በማስቀጠል ሀገራችንን ወደ አፍሪካ ዋንጫው መድረክ እንመልሳታለን የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ብዙ ተጨዋቾች ጎጆ እየመሰረቱ ነው፤ አዲስስ?
አዲስ፡- ይሄ ደስ ይላል፤ ትዳር ጥሩ ነው፤ እኛም በቅርቡ እንቀላቀለዋለን ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- ስለ ልጅቷ ይገለጽ ሃ?
አዲስ፡- እሱን ጥሪው ሲደርሳችሁ ካርዱ ላይ ታይታላችሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ሲዳማ ቡና ሲያሸንፍና ሲሸነፍ ያለህ ስሜት?
አዲስ፡- ሲያሸንፍ ያው ምንም ጥርጥር የለውም በጣም ደስተኛ ነኝ፤ በትክክል ስራዬን እየሰራውም እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፤ ክለቤን በትክክል እያገለገልኩ እንደሆነም ነው የሚሰማኝ፤ ሲሸነፍ ግን ክለቡ እንደ ቤተሰባዊ ስሜት ስለሚሰማኝ ይመስለኛል ቶሎ ሆድ ነው የሚብሰኝ፤ እንደውም የተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ እንባ እስከማቅረር ደረጃም ሁሉ ደርሻለው፤ ያ ለክለቡ ካለኝ ስሜት አንጻር ነው፤ ያንን ነገር የማደርገው ነጥቦችን በምንጥልበት ሰዓት ነው እና ያኔ አዝናለው፡፡
ሀትሪክ፡- የምግብ ምርጫ የተለየ ነው?
አዲስ፡- ብዙ የተለየ ምግብን አልጠቀምም ብዙ ጊዜ ሐዋሳ አካባቢ በምንሆን ሰዓት በብዛት ዓሳ ነክ ነገሮችን እንመገባለን፤ ከዛ ውጪ ብዙ የተለየ የአመጋገብ ሁኔታ የለኝም፤ ግን በይበልጥ ምስር ወጥ እወዳለው፡፡
ሀትሪክ፡- ሎተሪ ወይንም ደግሞ እጣ ቆርጠህ ታውቃለህ?
አዲስ፡- እኔንጃ እንደዚህ ያሉ ነገሮች እድል የለኝም መሰለኝ ቆርጬ አላውቅም፤ ስለመቁረጥ አስታውሼም አስቤም አላውቅም፡፡
ሀትሪክ፡- አሰልጣኛችሁ ዘርዓይ ሙሉ እንዴት ይገለጻል?
አዲስ፡- ምንአልባት አሁን አሰልጣኛችሁ የሚለው ክለቡ እና ከውጪ ያለ ሰው ነው፤ ለእኛ ተጨዋቾች ግን እሱ ጓደኛችን ነው የምንለው፤ ታላቅ ወንድማችንም ነው፤ በቅርቡም ነው ከኳስ ህይወት የወጣው፤ ወደ አሰልጣኝነቱም ለመምጣት ብዙም አልዘገየም፤ ግን ጓደኛችን ነው፤ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም፤ እንደ ካፒቴን የክለቡን ሁኔታዎች ሊያነጋግሩ በሚችሉ ነገሮች ስናወራም እንደ ጓደኛ እንጂ እሱ እንዳለቃ እኔ እንደ ታዛዥ ሆኜም አይደለም፤ እና ችግሮቹን በቀላሉ እንቀርፈዋለን፤ ከዛ ውጪ ደስ የሚል ስብህናም አለው፤ ተጨዋችን የሚረዳበት መንገድ ይገርማል፤ ራሱን ለማሻሻልም የሚተጋም አሰልጣኝ ነውና እኛ በእሱ ስር በመሆናችን በጣም እድለኞች ነን፤ የቡድናችን ተጨዋቾች ታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች ናቸው፤
ለእነሱ እንዲህ ያሉ ኮቾች ናቸው የሚያስፈልጉት፤ የአገራችን እግር ኳስ ነገን አሁን ላይ ያለ ሰው ሳይሆን ታዳጊው ነው የሚረከበውና ለታዳጊው ደግሞ እንደ ዘርዓይ አይነት አመለካከት ያላቸው አሰልጣኞች መብዛት ነው ያለባቸው፤ ለታዳጊዎች የሚሰጠው ነገር ደስ የሚል ስለሆነም በእዚህ አጋጣሚ በጣም ነው የማመሰግነው፡፡
ሀትሪክ፡- ከኳስ ውጪ መዝናኛህክ ምንድን ነው?
አዲስ፡- ከኳስ ውጪ መዝናኛዬ ፑል ነው፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ወደዛ ቦታ ካላመራው ፊልሞችን በማየት እዝናናለው፤ ከክለብ ጓደኞቼም ጋር እጫወጣለው፤ ፑል በጣም ጎበዝ ስለሆንኩም የሚገጥመኝ ሰው ካለ አልፈራም ይፋለመኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የቅርብ ጓደኛህ ማን ነው?
አዲስ፡- ሁሉም ጓደኛዬ ቢሆኑም የቅርቡ ጓደኛዬ ግን ሀብታሙ ገዛኸኝ ነው፤ እሱ እኔ ከምፈልገው አይነት ባህሪ ጋር የሚሄድ ስለሆነም ለዛ ነው ጥብቅ ጓደኛዬ የሆነው፡፡


ሀትሪክ፡- ሙዚቃ ትወዳለህ?
አዲስ፡-በጣም ነው እንጂ፤ በተለይ የድሮ ዘፈኖች ይመቹኛል፤ ለስለስ ያሉት የእነ ጥላሁን ገሰሰ፣ መሐሙድ አህመድ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ እና የመሳሰሉትን ስሰማ የተለየ ደስታም ይሰማኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ለዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስህ እነማንን ታመሰግናለህ?
አዲስ፡- በመጀመሪያ የማመሰግነው የሁሉም ነገር ባለቤት የሆነውን የድንግል ማሪያም ልጅ ስሙ የተመሰገነ ይሁን እሱን ነው፤ ከዛ ውጪ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ምንአልባት ሁሉንም ለመጥራት በተለይ ለኳስ ተጨዋች ገጹ ላይበቃ ይችላል፤ ግን ለእኔ ልዩ ቦታ የምሰጠው የፕሮጀክት አሰልጣኜን ነው፤ ካሳሁን አይሳ ይባላል፤ በቃ እሱ የኳስ አባቴ ብዬ ነው የምገልጸው፤ መሰረቴም ነው፤ እሱ ብዙ ነገሮችን አስጨብጦኛል፤ በመጀመሪያ ላመሰግነው የምፈልገው እሱን ነው፤ ከዛ ጓደኞቼን ለእኔ ቅርበት ያላቸውን እነ ንጋቱን፣ ሀብታሙን፣ እነ ተገኔን መላኩን እና የመሳሰሉትን፤ ምንአልባት በመዘንጋት ስማችሁን ሳልጠራችሁ ላልፍ የምችላችሁ ሰዎች ስላላችሁ እናንተን ጭምር ነው የማመሰግናው፤ ሌሎቹ ቤተሰቦቼ በተለይ ለእኔ በጣም ቅርበት አላቸው፤ እንደ እናት እህት ወንድም ብቻ አይደለም፤ እንደ ጓደኛም ስለሚያየኙ እነሱንም ከዛ ውጪ ደግሞ የክለቤ ደጋፊዎች ለእኔ ልዩ ቦታ አላቸው፤ እኔም ለእነሱ ልዩ ቦታ አለኝና እጅግ በጣም ነው የማከብራችሁ የምወዳችሁ እና የማመሰግናችሁ፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website