በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 5ኛ ሳምንት 8ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ እና በቀጣዩ ሳምንት መጀመሪያ የሚካሄዱ ሲሆን ሁሉም ጨዋታዎች በክልል የሚደረጉ ይሆናል። ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል 6ቱ ጨዋታዎች ቅዳሜ ሲደረጉ እሁድ እና ሰኞ ደግሞ አንድ አንድ ጨዋታ የሚደረጉ ይሆናል። ከነዚህ ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን በዚህ ቅድመ ዳሰሳ ለእናንተ እንዲስማማ አድርገን አቅርበንላችኋል።
ጨዋታ 1
ወላይታ ድቻ ከ ወልቂጤ ከተማ
የጨዋታ ቀን: ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ፌደራል አርቢትር ብርሃኑ መኩሪያ
ቅዳሜ ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ወላይታ ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ከ ወልቂጤ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ 9:00 ላይ የሚጀምር ይሆናል። ሁለቱ ቡድኖች የዘንድሮውን ውድድር በመልካም ሁኔታ መጀመር ተስኗቸው 5ኛ ሳምንት ውድድር ላይ ደርሰዋል። ባለፉት የ4ሳምንት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው 12ነጥቦች ከግማሽ በታች የሆነውን ብቻ ነው ማሳካት የቻሉት። በ4ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻ ወደ አዳማ አቅንቶ በባዬ ገዛኸኝ እና እድሪስ ሰዒድ ግቦች ታግዞ ከአዳማ ከተማ ጋር ሁለት አቻ የተለያየ ሲሆን ወልቂጤ ከተማ በአንፃሩ በአቢዮ አሬርሳሞ ስታዲየም ሌላኛውን አዲስ አዳጊ ሰበታ ከተማን አስተናግዶ በአስቻለው ግርማ ብቸኛ ግብ 1-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል። ሁለቱ ክለቦች በደረጃ ሰንጠረዡ በአንድ ነጥብ ብቻ ተበላልጠው ወላይታ ድቻ በ5 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ወልቂጤ ከተማ ደግሞ በ4ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ጨዋታ 2
ሀዋሳ ከተማ ከሲዳማ ቡና
የጨዋታ ቀን: ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ኢንተርናሽናል አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩ
በሌላ የሊጉ የ9 ሰዓት ጨዋታ በደቡብ ደርቢ ሀዋሳ ከተማ ከሲዳማ ቡና ጋር ሀዋሳ ላይ የሚያገናኘው ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል። ኢንተርናሽናል አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩ የሚመራው ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች በጣም ወሳኝ ነው። ጨዋታውን ወሳኝ የሚያደርገው ነገር በ4ኛው ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ሁለቱም ቡድኖች ሽንፈት በማስተናገዳቸው እና ከሽንፈት መልስ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ መሆኑ ነው። ሀዋሳ ከተማ በ4ኛው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ በኢትዮጵያ ቡና የ4-1 ከባድ ሽንፈት ሲያስተናግድ ሲዳማ ቡናም በሜዳው የአምናውን ሻምፒዮን መቐለ 70 እንደርታን ገጥሞ 2-1 መሸነፉ ይታወሳል። ሁለቱ ቡድኖች ባደረጓቸው 4የሊጉ ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ በ7ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ሲዳማ ቡና ደግሞ በ1ነጥብ ዝቅ ብሎ በ6ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
አስተያየት ይስጡ