ቅድመ ጨዋታ ዕይታ| ሀዲያ ሆሳዕና ከ ጅማ አባጅፋር

15ኛው ሳምንት የኢትዮጲያ ፕሪምየር ሊግ በሳምንቱ መጨረሻ አርብ ቅዳሜ እና እሁድ እንዲሁም ሰኞ በሚደረጉ 8 ጨዋታዎች ቀጥሎ ይውላል።

 

እኛም በነገው ዕለት የሚካሄደው ቀጣይ የ15ኛ ሳምንት ብቸኛ መርሐግብር የሆነውና ሜዳው በመቀጣቱ ሳቢያ ከሜዳው ውጭ የሚጫወተው ሀዲያ ሆሳዕና ጅማ አባጅፋርን በሀዋሳ ስታዲየም የሚያስተናግድበትን ጨዋታ በዚህ መልኩ ዳሰነዋል።

 

ጨዋታ:- ሀዲያ ሆሳዕና ከ ጅማ አባጅፋር
የጨዋታ ቀን :-አርብ የካቲት 13/2012
የጨዋታ ቦታ:-ሀዋሳ ስታድየም
የጨዋታ ሰዓት:-9:00
የጨዋታ ኣልቢትር፦  ፌደ. አርቢትር እያሱ ፈንቴ

 

ሀዲያ ሆሳዕናዎች በ11ኛው ሳምንት በሜዳቸው በወልቂጤ ከተማ 2-1 ከተረቱበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ በሜዳቸው በተስተዋለው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ድርጊት በፕሪምየር ሊጉ አወዳዳሪ አካል ሁለት ጨዋታዎች በገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወቱ ባስተላለፈባቸው ብይን መሠረት ሁለተኛ ጨዋታቸውን ከሜዳቸው ውጭ በሀዋሳ ስታዲየም ጅማ አባጅፋርን በማስተናገድ ይጫወታሉ።

 

ባለፈው ሳምንት ወደ መቐለ አቅንተው ስሑል ሽረ ጋር ነጥብ ተጋርተው የተመለሱት ነብሮቹ ይህ ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ወሳኝነት አለው። ሆሳዕናዎች በነገው ጨዋታ አፈግፍጎው ክፍተቶችን በመድፈን እና በአደጋ ክልል የመቀባበያ አማራጮችን በመዝጋት ላይ አተኩሮ እንደሚጫወት ሲጠበቅ በፈጣን መልሶ ማጥቃት አደጋ መፍጠርን ምርጫቸው ያደርጋሉ ተብሎም ይገመታል። እዩኤል ሳሙኤል እና ሁለቱ ቢስማርኮች ከጅማ ተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን በመጠቀም ጎል ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል። ከዚህ ውጪ ይሁን እንደሻው እና አፈወርቅ ኃይሉ የሚልኳቸው ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች ለቡድኑ ወሳኝ ናቸው። እርግጥ ጅማ ካለው የአየር ላይ ጥንካሬ አንፃር ቡድኑ በተሻጋሪ ኳሶች ሊጠቀም እንደማይችል ቢገመትም ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን ተጠቅመው ሆሳዕናዎች ግብ ለማስቆጠር እንደሚጥሩ ይገመታል።

 

በሜዳም ሆነ ከሜዳም ውጪ ባሉ ችግሮቹ ተተብትቦ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው ጅማ አባጅፋር የደሞዝ ጥያቄው አለመፈታቱን ተከትሎም የቡድኑ አባላት ልምምዳቸውን ለሁለት ቀን ያቆሙ ሲሆን አመራሮች የቡድኑን ተጨዋቾች በመሰብሰብ ጥያቄያቸው በአፋጣኝ እንደሚፈቱ ገልፀውላቸው የነገውን ጨዋታ እንዲያደርጉ እንዳስሟሟቸው ተሰምቷል። አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እጅግ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀትን በጅማ የገነቡ ሲሆን በተለይ ከሜዳ ውጪ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ቀይ ለባሾቹ ላይ ጎል ማስቆጠር ፈታኝ እየሆነ መጥቷል። በነገው ጨዋታም ጠጣሩን አቀራረብ ይዘው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ሲጠበቅ ሁለቱ አጥቂዎች ተመስገን እና ብዙዓየሁ ላይ ያተኮረ የመልሶ ማጥቃት በመሰንዘር ጎል ለማስቆጠር ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

 

በጉዳት ደሰታ ጊቻሞ በሀዲያ ሆሳእና በኩል እማይኖር ሲሆን በጅማ አባጅፋር በኩል አምረላ ደልታታን በጉዳት እንዲሁም አሌክስ አሙዙ ፣አብርሃም ታምራት በቅጣት ብሩክ ገብረአብ ከቡዱኑ ጋር በመለያየቱ አባጅፋሮች አገልግሎታቸውን እማያገኙ ይሆናል።

ባሳለፈነው ሳምንት በወላጅ አባታቸው ህልፈት ምክኒያት ቡድናቸውን መምራት ያልቻሉት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ሀይቆቹን ለመግጠም ከቡድናቸው ጋር ወደ ሀዋሳ አምርተዋል።

የእርስ በእርስ ግኑኝነት…..  ሀድያ ሆሳዕና እና ጅማ አባጅፋር በሊጉ ሲገናኙ ይህ ለመጀመሪያ ግዜ ነው

Hatricksport website writer

ዳዊት ታደሰ

Hatricksport website writer