የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ
በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ ተስተካካይ ቀሪ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይቀጥላሉ።
አ/አ ላይ በሚደረገው በዕለተ ዕሁድ ብቸኛ የሊጉ ተስተካካይ ጨዋታ 10፡00 ሲል መከላከያን ከ መቐለ ከተማ የሚያገናኝ ይሆናል።
ሁለት በተለያየ የውጤት መንገድ ላይ በሚገኙ ቡድኖች መካከል የሚካሄደው ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝ ነው። መከላከያ ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው ግቦች 5ብቻ ሲሆኑ ይህም ቡድኑ በአጥቂ ክፍሉ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለበት የሚያሳይ ነው። ካስቆጠራቸው 5 ግቦች 4ቱን ምንይሉ ወንድሙ ማስቆጠሩ ደግሞ ቡድኑ አማራጭ አጥቂዎች እንደሌሉት እና በአንድ ሰው ትከሻ ላይ እንደወደቀ ያሳያል። በተቃራኒው በአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ የሚመራው መቐለ ከተማ ደግሞ እጅግ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው መሆኑ የታየ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ማሳያው ዘንድሮ ቡድኑ ካደረጋቸው 14 ጨዋታዎች 5ግቦች ብቻ ማስተናገዱ ነው። ይህንንም ተከትሎ ዛሬም መከላከያ ተጋጣሚው ላይ ግብ ለማስቆጠር ይቸገራል ተብሎ ይታሰባል።
ወደ ማጥቃቱም ስንሻገር አሁንም እጅግ በተቃራኒ ጎዳና ላይ እንደሚገኙ ያሳያል። መቐለ ከተማ 15 ግቦች ተጋጣሚው መረብ ላይ ሲያሳርፍ የመከላከያ ተከላካይ ክፍል ደግሞ 12ግቦችን አስተናግዶ አስከፊ የውድድር ዘመንን እያሳለፈ ይገኛል።

በ15ኛው ሳምንት እንግዳው መቐለ ከተማ በግዙፉ ትግራይ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ ያለ ግብ አቻ የተለያየ ሲሆን መከላከያ በአንፃሩ አ/አ ስታዲየም ላይ በደደቢት የ4-0 አስከፊ ሽንፈትን ማስተናገዱ የሚታወስ ነው።
በአጠቃላይ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መቐለ ከተማ 14ጨዋታዎችን ማድረግ የቻለ ሲሆን ካደረጋቸው 14ጨዋታዎች 6ቱን አሸንፎ በ7ቱ አቻ የወጣ ሲሆን ሜዳው ላይ በደደቢት የደረሰበት የ2-0 ሽንፈት በሊጉ ብቸኛ ሽንፈቱ ሆኖ ተመዝግቦለታል። ይህንንም ተከትሎ ከመሪው ደደቢት በ3ነጥቦች ብቻ ርቆ በ25 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል 2ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት መከላከያ በአንፃሩ ካደረጋቸው 13ጨዋታዎች 2ቱን ብቻ አሸንፎ በ6ቱ አቻ ተለያይቶ በ5ቱ በመሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው በ1ነጥብ ብቻ ከፍ ብሎ በ12 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ልክ 10:00 ሲል በአሪብትር ሀብታሙ መንግስቴ ዳኝነት አ/አ ስታዲየም ላይ የሚካሄድ ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ