በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ተስተካካይ 1ጨዋታ ዛሬ (ቅዳሜ) ተደርጎ ኢትዮጵያ ቡናን ከሀዋሳ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ይህ ጨዋታ በ12ኛው ሳምንት በዕለተ ቅዳሜ ጥር 5 2010ዓ.ም መደረግ የነበረበት ሲሆን በወቅታዊ ጉዳዮች ምክንያት ሳይደረግ ቀርቶ ወደ ዛሬ ሊተላለፍ ችሏል።
እንደ እስከዛሬው ሁሉ እጅግ ባማረ እና በተዋበ ዝማሬና ድጋፍ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ይሄ ነው የሚባል የጨዋታ ሂደት ሳይስተዋልበት የተካሄደ ነበር። ኢትዮጵያ ቡናም ሆነ ሀዋሳ ከተማ በ4-3-3 የጨዋታ ዘይቤ የገቡ ሲሆን ለደጋፊዎች ይሀረን ያህል ሳቢ የሚባል ጨዋታ ማድረግ አልቻሉም።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና ከሀዋሳ ከተማ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻለ ሲሆን ከተጋጣሚው በተሻለ ወደ ግብ መድረስ ችለዋል። የሀዋሳ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ በጨዋታው ድንቅ ብቃቱን ማሳየት የቻለው ወጣቱ አጥቂ አቡበከር ናስር በግል ጥረቱ ሞክሮት ወደ ውጭ የወጣበት ኳስና ከቅጣት ምት የተሻገረለትን ኳስ አክሊሉ ዋለልኝ በግንባሩ ገጭቶት ወደ ውጭ የወጣበት ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ። በሀዋሳ ከተማ በኩል ለኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ሀሪትሰን ሄሱ ፈተና የሚሆን ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ወደ መልበሻ ክፍል ማምራት ችለዋል።
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው አጋማሽ ተሽለው በመቅረብ ወሳኙን 3ነጥቦች ለመውሰድ ጥረት ያደረጉት ኢት. ቡናዎች በሳሙኤል ሳኑሚ ከሳጥን ውጪ የሞከሩት ኳስ የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ሆሆ ሜንሳህ በቀላሉ ይዞታል። የኢትዮጵያ ቡናው ኤልያስ ማሞ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ማንም ሳይጠቀምበት ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞታል። መስዑድ መሀመድ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ከገባ በኋላ ኢትዮጵያ ቡና የተሻለ መጫን ሲችል ሀዋሳ ከተማ በአንፃሩ ወደኃላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት በመጫወት 3ነጥብ ይዞ ለመውጣት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች 80ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ማሞን ተክቶ የገባው ሚኪያስ መኮንን ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡበት እንዲሁም ከ2 ደቂቃዎች በኋላ 82ኛው ደቂቃ አክሊሉ ዋለልኝ አክርሮ የመታውን ኳስ የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ሆሆ ሜንሳህ በግሩም ሁኔታ አድኖበታል። መደበኛው የጨዋታ ክ/ጊዜ ሊጠናቀቅ 4ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩት 86ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው የኢትዮጵያ ቡናው መስዑድ መሀመድ ከሀዋሳ ከተማ ፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ ያገኘውን ኳስ በተረጋጋ መንገድ ተቆጣጥሮ በድንቅ ሁኔታ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ወደግብነት ቀይሮት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ ነበር። ሆኖም ግን ይህ የኢትዮጵያ ቡና መሪነት መዝለቅ የቻለው ለ2 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። የሀዋሳ ከተማው እስራኤል እሸቱ አክርሮ ወደ ግብ የመታውን ኳስ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ሀሪሰን ሄሱ ሲያወጣው በቅርበት የነበረው ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን አስቆጥሮ ቡድኑ 1ነጥብ ይዞ ወደ ሀዋሳ መመለስ ችሏል። ከዚህ ግብ መቆጠርም በኋላ ኢትዮጵያ ቡና ሶስት ነጥብ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችል ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።